ሥልጠናው የክልሎችን የሙያተኛ እጥረት እንደሚቀንስ ታምኖበታል

15 May 2018

የቼስ ስፖርት የሁለተኛ ደረጃ የዳኝነት ሥልጠና በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ከትናንት በስቲያ መጀመሩን ተከትሎ የኢትዮጵያ ቼስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰይፈ በላይነህ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ በቼዝ ስፖርት የዳኝነት ሥልጠና የተከታተሉ በክልል ያሉ ባለሙያዎች ቁጥር ጥቂት ነው። በመሆኑም ፌዴሬሽኑ ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ለተወጣጡ 15 ዳኞች የቼስ የሁለተኛ ደረጃ የዳኝነት ሥልጠና እየሰጠ ይገኛል።
ዳኞች ከዚህ በፊት የአንደኛ ደረጃ የዳኝነት ሥልጠና ወስደው በሥራ ላይ የሚገኙ መሆናቸውን ኃላፊው ጠቅሰው፤ ክልሎች ውድድር ሲያዘጋጁ የዳኝነት እጥረት እንደሚያጋጥማቸው አመልክተዋል። በመሆኑም የቼዝ ስፖርት የዳኝነት ሥልጠናው የክልሎችን የሙያተኛ እጥረት ችግርን ለመቀነስ ሚናው የላቀ ይሆናል ሲሉ ገልጸዋል።
እንደ አቶ ሰይፈ ማብራሪያ፤ በቼዝ ስፖርት ውድድሮችን በብቃት ለመምራት የሚችል የሠለጠነ ዳኛ የለም። በመሆኑም ክልሎች ውድድር በሚያዘጋጁበት ወቅት ዳኛ ስለሚያንሳቸው ከብሄራዊ ፌዴሬሽን ዳኞችን በመላክ እንዲያከናውኑ ይደረጋል። ሥልጠናው በክልሎች ለሚስተዋለው የዳኞች ችግር በተወሰነ ደረጃ ይፈቱታል ተብሎ ይጠበቃል።
«በቼስ ውድድር ላይ ስላሉ ህጎችና መርሆዎች የንድፈ ሀሳብና የተግባር ሥልጠና ይሰጣቸዋል » ያሉት አቶ ሰይፈ፤ ዳኞቹ አንደኛ ደረጃ የዳኝነት ሥልጠና የወሰዱ እንደመሆናቸው የሁለተኛ ደረጃ ሥልጠናቸውን ሲያጠናቅቁ የአንደኛ ደረጃ የዳኝነት ሥልጠናን መስጠት እንደሚችሉ ገልጸዋል። ይህ ሁኔታ መኖሩ በየክልላቸው መጓዝ ተጨማሪ ዳኞችን ለማፍራት የሚቻልበትን ሥርዓት መዘርጋት የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።
አቶ ሰይፈ አክለው ም፤ የሁለተኛ ደረጃ ሥልጠናውን የሚወስዱት ዳኞች በቀጣይ የዓለም አቀፉ የቼስ ፌዴሬሽንና የአፍሪካ የቼስ ኮንፌዴሬሽን በሚያዘጋጇቸው ሥልጠናዎች ላይ የመሳተፍ እድል የሚያገኙም ይሆናል። ትልቁ የቼስ ዳኝነት ደረጃ በዓለም አቀፉ የቼስ ፌዴሬሽን የሚሰጠው ዓለም አቀፍ አርቢትር ሲሆን፣ ይህን ደረጃ ያገኘ ዳኛ በአህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ውድድሮች የትኛውም አይነት ውድድሮች መምራት ይችላል።
የቼስ ስፖርት የሁለተኛ ደረጃ የዳኝነት ሥልጠናውን ዓለም አቀፍ የቼስ ዳኛ (አርቢትር) በሆነው ደጀኔ ዘላለም አማካኝነት መሰጠቱን ቀጥሏል። በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ እየተሰጠ ያለው ሥልጠናው ከተጀመረበት ባሳለፍነው ቅዳሜ ግንቦት 4 ቀን ሲሆን፣ እስከ ግንቦት 13 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ እንደሚቆይ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።
ቼስ በዓለም ላይ ከሚገኙ የቤት ውስጥ ስፖርቶች አንዱ ሲሆን፣ ከግማሽ ቢሊዮን በላይ ሰዎች ያዘወትሩታል። ከጨዋታነቱ ባሻገርም የሰውን ልጅ አዕምሮ የማስፋት አቅም እንዳለውና በተለይም ሕፃናት ትምህርታቸው ላይ ትኩረት እንዲሰጡ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ይነገራል። በኢትዮጵያ በ16ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ አፄ ልብነ ድንግል፤ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ ደግሞ የሸዋው ንጉሥ ሳህለ ስላሴ ቼስን ይጫወቱ እንደነበር ይነገራል።

ዳንኤል ዘነበ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።