‹‹ክለቦችን ለማብዛት በሚደረገው ጥረት የብስክሌት መወደድ እንቅፋት ሆኗል›› Featured

16 May 2018

በብስክሌት ስፖርት ኢትዮጵያ በዓለም የውድድር መድረክ ለመጀመሪያ ጊዜ ብቅ ያለችው በአውስትራሊያዋ ሜልቦርን ከተማ እኤአ በ1956 በተካሄደው 17ኛው ኦሎምፒያድ ነው። በወቅቱ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያን በመወከል አስራ ሁለት ብስክሌተኞች (ተወዳዳሪዎች) ተሳታፊ ሆነዋል። ከዚህ የጀመረው የኢትዮጵያና የብስክሌት ስፖርት ዓለም አቀፋዊ ግንኙነት ዓመታትን ተሻግሯል። ስፖርቱ አሁን ካለበት ደረጃ ሲደርስ አንድ ጊዜ ከፍ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ዝቅ በማለት ተጉዟል።
ከውጤት ርቆ ጠፋ ሲባል፤ የታሪክ ክስተት የሚመስሉ ብስክሌተኞች ባልታሰበ አጋጣሚ ብቅ በማለት በዓለም የውድድር መድረክ ውጤት ሲያስመዘግቡ ስፖርቱም መኖሩ ይታወሳል፡፡ እነዚህ ብስክሌተኞች ስፖርቱ እንዳይረሳ በማድረግ ከዛሬ ደጃፍ አድርሰውታል፡፡ በኢትዮጵያ የብስክሌት ስፖርት የተለያዩ ሂደቶችን አልፏል፡፡ የዕድገትና የውድቀት ምዕራፎችን ገልጿል።
በዚህ የታሪክ ሂደት የአዲስ አበባ የብስክሌት ስፖርት ፌዴሬሽን አብሮ ተጉዟል፡፡ ፌዴሬሽኑ በአገሪቱ የብስክሌት ስፖርቱ ዕድገትና ውድቀት ተካፍሏል፡፡ በመዲናይቱ የብስክሌት ስፖርት ከፍታ በሚዘመርበት ወቅት፤ በቁጥር የበረከቱ ክለቦችን በማቀፍ ለስፖርቱ ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽዖ አበርክቷል። እነ ገረመው ደንቦባን የመሳሰሉ ስፖርተኞችን ማፍራት ችሏል፡፡ የብስክሌት ስፖርት ውድቀት በሚባልበት ጊዜ ደግሞ ክለቦችን አፈራርሶ በመቀመጥ ተወቃሽ ሆኗል።
በእነዚህ ሁለት የታሪክ ጽንፎች የሚጠቀሰው የአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን አሁን ላይ ተስፋ ሰጭ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑ ይነገራል፡፡ በተለይም የክለብ ጥንካሬውን መልሶ ለመጨበጥ ጅምር ሥራዎችና ለውጦች ማሳየቱ ነው የሚጠቀሰው፡፡ የፌዴሬሽኑን ወቅታዊ እንቅስቃሴዎች፣ ያለፈውን ስኬት፣ ተግዳሮቶችና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች በተመለከተ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስፖርት ምክር ቤት ሥራ አስፈፃሚ እና የከተማዋ የብስክሌት ስፖርት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ረዘነ በየነ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፦ የአዲስ አበባ የብስክሌት ስፖርት ፌዴሬሽን ከአገር አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሻለ ደረጃ ላይ ለመድረስ ያስቻለ አቅም እንደነበረው ይነገራል፡፡ ይሄን ቢያብራሩልን?
አቶ ረዘነ፦ የብስክሌት ስፖርት በአዲስ አበባ ከተማ ተጽዕኖ እንደነበረው የሚነገረው እውነት ነው። ከዛሬ 30 እና 40 ዓመታት በፊት ከእግር ኳስ እና ሌሎች ስፖርቶች በተለየ መልኩ የብስክሌት ውድድር በህብረተሰቡ ዘንድ ተወዳጅነት ነበረው። የስፖርት ቤተሰቡ በውድድር ቦታዎች ላይ በመገኘት ለዘርፉ የነበረውን ፍቅር ያሳይ ነበር። በተለይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ዙሪያ ልዩ ድምቀት የነበራቸው የብስክሌት ውድድሮች ይካሄዳሉ። በርካታ ክለቦች በእነዚህ ውድድሮች በመሳተፍ ለውድድሮቹ ጥንካሬና ድምቀት በመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርገዋል። ብርሃንና ሰላም፣ መከላከያ፣ ማርፌል የመሳሰሉትን በማሳያነት መጥቀስ ይቻላል።
ስፖርቱ እንደ ዛሬ በየክልሉ በፌዴሬሽን ደረጃ የተከፋፈለ አልነበረም፡፡ አዲስ አበባ፣ ኤርትራ፣ ትግራይ በሚል በአንድ ብሔራዊ ፌዴሬሽን ብቻ ነበር የሚተዳደረው፡፡ በጊዜው ስፖርቱ ከመወደዱም በተጨማሪ ጠንካራና በርካታ ክለቦች ነበሩ፡፡ ያኔ የብስክሌቶች ዋጋ ውድ አለመሆኑ ለክለቦቹ መበራከት የራሱ ሚና ተጫውቷል፡፡ ይህም ስፖርቱ በመዲናይቱ ከፍተኛ እድገት እንዲኖረው አድርጓል። ክለቦቹ ጠንካራ በመሆናቸውም በአገር አቀፍ ውድድሮች ብቻ ሳይሆን በብሄራዊ ቡድን ደረጃ በመመረጥ አገርን የሚወክሉ ስፖርተኞችን ለማፍራት ችለዋል፡፡ በዚህ ደረጃ የነበረው ስፖርት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ መጥቷል።
አዲስ ዘመን፦ ስፖርቱን ከቀደመው ከፍታ አውርዶ ከውጤት በታች ያደረገው ምክንያት ምንድን ነው?
አቶ ረዘነ፦ የስፖርቱ መዳከም በመጀመሪያ ደረጃ ከክለቦች እንቅስቃሴ ጋር የሚያያዝ ነው። እንደጠቀስኩት በወቅቱ በርካታ ክለቦች ቢኖሩም ከእነዚህ ውጭ አዲስ ክለቦች አልተፈጠሩም። ከፍላጎት ማነስም ይሁን በሌላ ምክንያት በአዲስ አበባ አዳዲስ ክለቦች ተቋቁመው የስፖርቱን ድምቀት ሲጨምሩ አልታዩም። እንዲያውም የነበሩት ክለቦች ተዳክመው መፍረስ ጀመሩ። ስለዚህ በአዲስ አበባ የብስክሌት ክለቦች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቶ እስከ መፍረስ ደርሰዋል።
በጊዜው ጠንካራ ከሚባሉት ክለቦች አንዱ የሆነው ብርሃንና ሰላም ለዚህ ትልቁ ማሳያ ነው። ምንም እንኳን ክለቡ ከ13 ዓመታት ቆይታ በኋላ እንደገና የተመለሰ ቢሆንም። በአብዛኛዎቹ ክለቦች በኩል እንደ ችግር የሚነሳው የመወዳደሪያ ብስክሌቶችና ሌሎች የስፖርቱ ግብዓቶች ዋጋ እየናረ መምጣት ነው። የብስክሌት ስፖርት ጠንካራ የፋይናንስ መሰረት ይፈልጋል። ክለቦች የመወዳደሪያ ቁሳቁሶችና ትጥቆችን በማሟላት የስፖርተኞቹን ደመወዝ በመክፈል ካምፕ ማስቀመጥ እየተሳናቸው ለመፍረስ ይገደዳሉ፡፡
ተወዳዳሪዎቹ በበኩላቸው የሚከፈላቸው ደመወዝ አነስተኛ መሆኑን በመግለፅ ራሳቸውን ከስፖርቱ ያርቃሉ፡፡ በስፖርቱ ተወዳዳሪ ሆነው የሚያገኙት ገንዘብ ህይወታቸውን ለመምራት የሚያስችል አልነበረም። አቅም ያላቸው ባለሀብቶች ክለቦችን በመመስረት ስፖርቱን ለመደገፍ ያላቸው ፍላጎት አናሳ ነው፡፡ እነዚህ ተደማምረው የብስክሌት ስፖርት አሁን ደካማ ከሚያስብለው ደረጃ እንዲገኝ አድርገዋል፡፡
አዲስ ዘመን፦ እንደ አዲስ አበባ ከተማ በአሁኑ ወቅት የብስክሌት ስፖርት ያለበት ደረጃ እንዴት ይገለፃል? ወደ ቀድሞው ዝናና ዕድገት መመለስ የሚቻል ይመስልዎታል?
አቶ ረዘነ፦ በእርግጥም እንደተባለው ከተማዋ ከዓመታት በፊት በብስክሌት ስፖርት ከፍተኛ እውቅና ነበራት። ይህ ውጤት ዳግም እንዲመጣ ጥረት ተደርጓል፡፡ የአዲስ አበባ ብስክሌት ዳግም ለማንሰራራት እንደሚችል የሚያሳዩ ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች እየታዩ ነው። ከዓመት በፊት በኢትዮጵያ ሻምፒዮና አዲስ አበባ ከሁሉም ያነሰ ውጤት ይዞ ነበር የሚጨርሰው፡፡
አሁን ግን ወደ ተፎካካሪነት ደረጃ መምጣት ተችሏል፡፡ ከዓመት በፊት ሀዋሳ ላይ በነበረው የኢትዮጵያ ሻምፒዮና የእኛ ልጆች እነ ፅጋቡ ገብረማርያምን ከመሳሰሉ ጠንካራ ተፎካካሪዎች ጋር በመፎካከር ተቀራራቢ ሰዓት ማስመዝገብና የብር ሜዳልያን እስከ ማግኘት ተችሏል፡፡ ይህ ውጤት ለውጦች እየመጡ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው። ስለዚህ ልጆቹ ከተደገፉ በስፖርቱ ከፍተኛ ውጤት ማምጣት ይችላሉ።
አዲስ ዘመን፦ በስፖርቱ ላይ ለታየው ተስፋ ሰጨ ውጤት ምክንያቱ ምንድን ነው?
አቶ ረዘነ፦ ስፖርቱን የሚያውቁና የሚወዱ ግለሰቦች ወደ ፌዴሬሽኑ በማምጣት ቀርበው መሥራት መቻላቸው አንዱ ምክንያት ነው። አንድን ስፖርት ልደግፍ ብለህ ከተነሳህ ስፖርቱን ታሳድገዋለህ፡፡ ስፖርቱ እንዲያድግ ልባዊ መሻት አስፈላጊ ነው። የብስክሌት ስፖርቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ በስፖርቱ ያለፉትን ባለሙያዎቸ በመያዝ መሥራት ችለናል። ስፖርቱን የሚያውቁና የሚወዱን ሰዎች በማሳተፍ ፌዴሬሽኑን በማዋቀር መሥራታችን ተስፋ ሰጪ ውጤት ለመምጣት ረድቷል።
ቀደም ሲል ለስፖርተኞቹ የሚከፈለው ደመወዝ ተወዳዳሪዎቹን የሚያበረታታ አልነበረም። ተወዳዳሪ ዎቹ በየቤታቸው ነበር የሚመገቡትና የሚያድሩት፡፡ አሁን ግን ክለቦች የስፖርተኞች ማደሪያ ካምፕ አዘጋጅተው ነው የሚያሳድሯቸው፡፡ ከስፖርቱ ባህርይ ጋር የሚሄድ የአመጋገብ ሥርዓት ዘርግተዋል፡፡ እነዚህ መልካም ጅማሮዎች በስፖርቱ ቀጣይ ጉዞ ላይ የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያበረክታሉ፡፡
አዲስ ዘመን፦ የታየውን የውጤት ተስፋ አስቀጥሎ ለመጓዝ ምን እየተሠራ ነው?
አቶ ረዘነ፦ በመጀመሪያ ደረጃ ትኩረት ያደረግነው አሁን ያሉት ክለቦች እንዲጠናከሩ የውድድር መድረኮችን ማመቻቸት ላይ ነው። ያሉትን ከማጠናከር በተጨማሪ ሌሎችን በማምጣት ክለቦችን የማስፋትን ሥራ ትኩረት ተሰጥቶታል። ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመምከር ክለብ እንዲያቋቁሙ እያደረግን ነው። የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ከ13 ዓመት በፊት አፈርሶ የነበረውን የብስክሌት ክለብ ዳግም በማቋቋም ጠንካራ ሆኖ መጥቷል።
እንደሚታወቀው ለብስክሌት ስፖርት የሚያስፈል ጉት ግብአቶች በጣም ውድ ናቸው፡፡ ግብዓቶቹን እንደ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ አትሌቲክስ፣ እግር ኳስ ስፖርቶች በቀላል ገንዘብ አሟልተህ ለማቋቋም አስቸጋሪ ነው። ክለቦችን ለማብዛት በሚደረገው ጥረት ላይ የብስክሌት ዋጋ ውድ መሆን እንቅፋት ሆኖብናል። በዚህም የተነሳ ተቋማትን በማሳመን ወደ ስፖርቱ እንዲገቡ ለማድረግ አዳጋች ሆኗል። ህብረተሰቡና አንዳንድ ተቋማት ለስፖርቱ አነስተኛ ግንዛቤ መያዛቸው እርምጃችንን አስቸጋሪ አድርጎብናል። አንዳንድ ድርጀቶችን ስናናግር እንደ እግር ኳስና አትሌቲክስ መልስ አይሰጡንም ።
አዲስ ዘመን፦ እንደ ብርሃንና ሰላም በቅርብ ጊዜ ሊመጣ የሚችል ክለብ ይኖር ይሆን?
አቶ ረዘነ፦ በብስክሌት ስፖርት ዙርያ በህብረተሰቡና በተቋማት ደረጃ ያለው እሳቤ እንደ ሌሎች ስፖርቶች አይደለም። እኛ አገር በአንድ ተቋም ውስጥ በአመራርነት ደረጃ ላይ የሚገኝ ሰው የሚፈልገው (የሚወደው) ስፖርት ብስክሌት ከሆነ ያንን ለማሳደግ ብቻ ነው የሚሮጠው። እሱ ለቆ ሌላው ሲመጣ የቀደመውን አፍርሶ ወደ ራሱ ፍላጎት ይሄዳል፡፡ እኛ አገር ለሙያውና ለስፖርቱ ሳይሆን፤ ለግለሰብ ፍላጎት ነው ጭንቁ፡፡ ወደ ተቋማት በመጓዝ ጥያቄ ስናቀርብ የሚሰጠው ምላሽ ከዚህ አንፃር የተቃኘ ነው። ስፖንሰር እንዲያደርጉና ክለብ እንዲያቋቁሙ ጥያቄ ስናቀርብ የሚሰጠን ምላሽ ይህንኑ ፍላጎት መሰረት ያደረገ ነው።
አንዳንዴ አሳዛኝ ምላሽም እንሰማለን፡፡ ‹‹ ብስክሌት ምንድነው? ምን ዋጋ አለው? የት ደርሳችኋል ?›› የሚሉ ሞራል የሚነኩ አስተያየቶችን አስተናግደናል፡፡ ይህም ሆኖ ግን ፌዴሬሽኑ ያለመታከት ጥረት አድርጓል፤ እያደረገም ይገኛል። ጥረቱ ተስፋ አስቆራጭ ቢሆንም እንደ ቡና፣ ባንክ፣ መከላከያና አየር መንገድን ለመሳሰሉት ተቋማት ፕሮፖዛል አቅርበን መልሳቸውን እየተጠባበቅን ነው። እስካሁን ግን በክለብ ደረጃ ለመምጣት የሚችል የለም።
አዲስ ዘመን፦ ስፖርቱን በሚፈለገው ደረጃ ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ላይ ያሉ መልካም ዕድሎችና ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው?
አቶ ረዘነ፦ ከመደበኛ የውድድር መርሐ ግብሮች ጎን ለጎን በታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክት ላይ በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች እየታዩ ነው፡፡ በከተማ አስተዳደሩ ሥር በመስፋፋት ላይ ከሚገኙ ኩባንያዎችና ድርጅቶች ጋር የጋራ ተጠቃሚነት ላይ ጠንካራ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ እስካሁንም ከኮካ ኮላ ኩባንያ ጋር የተደረገው ስምምነት ተጠቃሽ ነው። እየታዩ ያሉትን ተስፋ ሰጪና ጅምር ተግባራትን በማጠናከር በቀደሙት ኦሎምፒኮች ከአትሌቲክሱ ቀጥሎ አገሪቱ ትወከልበት እንደነበር የሚነገርለትን ብስክሌት ወደ ቀድሞ ስምና ክብሩ ለመመለስ የበኩላችንን ሚና እንወጣለን የሚል እምነት አለኝ።
ስፖርቱ እያሳየ ያለውን ጅምር ውጤት የፋይናንስ እጥረት ትልቁ ፈተና ነው፡፡ ስፖርቱን በከፍተኛ በጀት እያንቀሳቀሱ ከሚገኙት የትግራይና የአማራ ክልሎች ጋር ሲነፃፀር የአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን ይህ ነው የሚባል ጠንካራ የበጀት ድጋፍ የለውም፡፡ የፌዴሬሽኑ ዓመታዊ በጀት 180 ሺ ብር ነው፡፡ በዚህ ደግሞ የአዲስ አበባ የብስክሌት ተፎካካሪነት አቅምን የትም ማድረስ አይቻልም። ይሄንን ባገናዘበ መልኩ ፌዴሬሽኑ ጠንካራ የፋይናንስ አቅም እንዲኖረው ስፖንሰርሽፕ የማፈላለግ ሥራ በትኩረት ይሠራል፡፡
አዲስ ዘመን፦ ክለቦችን ለማጠናከርና ለማስፋፋት ከሚደረገው ጥረት በተጓዳኝ በመዲናዋ ክፍለ ከተሞች ደረጃ ስፖርተኞችን በመመልመል ታዳጊዎችን ለማፍራት የታሰበ ነገር አለ?
አቶ ረዘነ፦ እንደ አዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን ታዳጊዎች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ አቋም ተይዟል። ስለዚህ በከተማዋ ነዋሪ የሆኑ ታዳጊዎችን በፕሮጀክት ደረጃ በማቀፍ ከታች ጀምሮ ይዞ በመምጣት መሰረት ያለው ስፖርተኛ ለማፍራት ታስቧል።
ቀደም ሲል እንደ አዲስ አበባ ትልቅ ችግር የነበረውን ሴት የብስክሌት ተወዳዳሪዎችን ለማፍራት በትኩረት እንሰራለን፡፡ ቀደም ሲል የቤት ኪራይ በመክፈልና በመደጎም ሴት ስፖርተኞችን ለማፍራት ጥረት ቢደረግም የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አልተቻለም። ስለዚህ ታዳጊዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ መሠራቱ ሴት ብስክሌተኞችን ለማፍራት ያግዘናል የሚል ዕምነት አለ።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ እናመሰ ግናለን።
አቶ ረዘነ፦ እኔም አክብራችሁ ስለጋበዛችሁኝ፤ በአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሸን ስም አመሰግናለሁ።

ዳንኤል ዘነበ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።