‹‹ጣልቃ ገብነት ዳኞችን ዋጋ እያስከፈለ ነው›› -አቶ ሚካኤል አርዓያ ፌዴራል ዳኛ እና የኢትዮጵያ ዳኞች ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት Featured

01 Jun 2018

ኳሷ የምታርፍበትን ትክክለኛውን ነጥብ ለማሳየት የምትለጋዋን የፈጣንዋን ኳስ እንቅሥቃሴ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚቀርጹ በርካታ ካሜራዎች ያግዛሉ፡፡ እናም ዳኛው ኳሷ ከመሥመር ውጭ መሆን አለመሆኗን በተረጋገጠ ሁኔታ መወሰን ይችላል ማለት ነው፡፡ ይህም ይግባኝ የማይልበት የመጨረሻ ውሳኔ ነው የሚሆነው፡፡ በዚህ ሂደት በዘመናዊ ቴክኒክ በመታገዝ፣ ለአካራካሪ የስፖርት ውድድር ውጤት፣ ፍጹም ትክክለኛ የሆነውን ብይን መስጠትም ይቻላል፡፡
የተጫዋቾችንና የኳስን ፍጥነት፣ በአጠቃላይ የውድድር እንቅስቃሴን ምንጊዜም በዓይን ብሌን ብቻ ተመልክቶ ትክክለኛ ብይን መስጠት ያዳግታል፡፡ ውድድሮች በሚካሄዱባቸው ጊዜያት አልፎ አልፎ አከራካሪ ውጤትን ለማስተካከልም ሆነ ለማጽናት፣ በቪዲዮ የተቀረፀውን መልሶ መመልከት የሚቻልበት ሁኔታ በዓለም ላይ ቢፈጠርም፤ ኢትዮጵያውያን ዳኞች የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ ስላልሆኑና ቅጽበታዊ ውሳኔን ስለሚሰጡ በእርጋታ እንዲያመዛዝኑና ውሳኔያቸውን እንዲከልሱ ዕድል ሳያገኙ ለበርካታ ዓመታት ሰርተዋል፡፡
በስህተትም ሆነ በሌላ ምክንያት የተላለፈ ውሳኔን ባለመቀበል ከተለያዩ አካላት ጥቃት ሲሰነዘርባቸውም ተስተውሏል፡፡ ለመሆኑ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የዳኝነት ሥርዓት ምን ይመስላል? ዳኞች ላይ የሚደርሰው ጥቃት መነሻው ምንድነው? ችግሩን ለመፍታት እየተደረገ ያለው ጥረስት? እነዚህንና ሌሎች ከእግር ኳስ የዳኝነት ሥርዓት ጋር የሚነሱ ጉዳዮችን ለመዳሰስ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ፌዴራል ዳኛና የኢትዮጵያ ዳኞች ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሚካኤል አርዓያ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
አዲስ ዘመን፦ የእግር ኳስ ዳኝነት ሙያን እንዴት ያዩታል?
አቶ ሚካኤል፦ ዳኝነትን በአጭሩ ለመግለጽ ያህል በተሰጠው ህግ መነሻነት ሜዳ ላይ ተጋጣሚ የሆኑ ሁለቱንም ተፎካካሪ አካላት በእኩል ማየትና ያልተዛባ ፍትህ መስጠት ነው፡፡ በእግር ኳሱ ለዳኝነት የተቀመጡ ወደ 17 ህጎች አሉ፡፡ እነዚህን ህጎች በሚታወቀውና ግልጽ በሆነው መንገድ ልክ እንደ ፍርድ ቤት አሰራር በጥንቃቄ ብይን መስጠት ነው፡፡ ህጎችንም በትክክል እፈፅማለሁ ተብሎ ነው ቃለ መሃላ የሚፈጸመው፡፡
አዲስ ዘመን፦ የእግር ኳስ ዳኝነትን ከሌሎች የስፖርት ዓይነቶች ዳኝነት ምን ልዩ ያደርገዋል?
አቶ ሚካኤል፦ በእርግጥ በእግር ኳሱ ዳኝነት የሚሰጡት አካላት ከሌሎች የስፖርት አይነቶች ዳኞች የጎላ ልዩነት የላቸውም፡፡ ምክንያቱም በየትኛውም የስፖርት አይነት ውስጥ ዳኝነት ፍርድ መስጠት ነው፡፡ ስፖርቶች የየራሳቸው የውድድር ህግ ቢኖራቸውም፤ ፍትህ በመስጠት በኩል ያለው አሰራር ግን ተመሳሳይነት አለው፡፡ ነገር ግን በተወሰነ ደረጃ የእግር ኳስ ስፖርት ደጋፊው ብዙ በመሆኑ ልዩ ኩረት እንዲሰጠው ሆኗል፡፡
አዲስ ዘመን፦ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የዳኝነት ብቃት እንዴት ያዩታል?
አቶ ሚካኤል፦ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ዳኞች በብቃት አይታሙም፡፡ ይህ ደግሞ ዛሬ ብቻ ሳይሆን ቀደም ብለው የነበሩ ኢንተርናሽናል ዳኞቻችን ይህንን አስመስክረዋል፡፡ በብቃት ማነስም ሆነ ጉቦ ከመቀበል አኳያ ስማቸው አይነሳም፡፡ ብቃት ባይኖራቸው ኖሮ እነ ባምላክ ተሰማ እና ሊዲያ ታፈሰ የመሳሰሉት ዳኞች በትልልቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ሲዳኙ ማየት ባልተቻለ ነበር፡፡ በእርግጥ ሁሉም ተመሳሳይ የሆነ ብቃት ላይ ናቸው ማለት አይቻልም፡፡ ነገር ግን እንደየ ባህሪያቸው የአቅም ውስንነት ሊኖርባቸው ይችላል፡፡ በዚህም አንዱ ከአንዱ የሚበልጥበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ ለዚህም ክህሎትን በየጊዜው ሊያዳብር የሚችል ትምህርት ያስፈልጋል፡፡ ከብዙ ውድድሮች ጥቂት ስህተት ሲፈፀም ጠቅላላ ዳኛ ተሳሳተ ተብሎም መፈረጅ የለበትም፡፡ እንደውም ብዙ እገዛ ሳይኖራቸው ይህን ያህል መሥራታቸው ሊያስመሰግናቸው ይገባል፡፡ በሌላው አገር ዳኞች ልምምድ የሚያደርጉበት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ እንኳ ሳይቀር ይፈቀድላቸዋል፤ እዚህ አገር ያለው ግን ከዚህ በተቃራኒው ነው፡፡
አዲስ ዘመን፦ ዳኞች በሜዳ ላይም ሆነ ከሜዳ ውጭ ምን አይነት ተጽዕኖዎች ይደርስባቸዋል?
አቶ ሚካኤል፦ አብዛኛውን ጊዜ ህግን በመተርጎም ሂደት ሜዳ ላይ ችግሮች ይደርሳሉ፡፡ ከሥነ ምግባር ውጭ የሚሆኑ ስፖርተኞች በዳኞች ላይ ከድብደባ ጀምሮ ሥነ ልቦናን እስከ መጉዳት የሚያደርስ ጸያፍ ተግባራትን ሲከውኑ ይስተዋላል፡፡ ከዚህ ውጭ አገሪቷ በእግር ኳስ ዳኝነቱ የምትመራበት ህግ እያላት ህጉ በአግባቡ ሳይተረጎም ሲቀርም ተጎጂው ዳኛ ነው፡፡ ችግሩ በዋናው ፕሪሚየር ሊግ ለሚዲያ ተጋላጭ በመሆኑና ብዙ ሰው የማየት እድሉን ስላገኘ እንጂ፤ ስፖርታዊ ጨዋነት መጓደሉ ከስር ባሉ ሊጎች ላይ ነው ጎልቶ የሚታየው፡፡
ከፍተኛ ሊግ ላይ የሚያጫውቱ ዳኞች ተደብድበው ለኩላሊት ህመም እስከመዳረግ የደረሱ አሉ፡፡ ብሄራዊ ሊግ ላይ የሚያጫውቱ ዳኞች የተለያዩ ማስፈራሪያና ዛቻ የደረሰባቸውም አሉ፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ግን መመልከት የተቻለው ሁሉም ተጫዋች ሥርዓት አልባ እንዳልሆኑ፣ ከደጋፊዎችም ጥቂቶች እንጂ አብዛኞቹ ስፖርቱን በጨዋነት የሚደግፉ እንዳሉና እንደ ማሳያም ሊሆን የሚችለው አልፎ አልፎ ከሥርዓት ውጭ የሆኑ ተጫዋቾች ዳኛው ላይ ጥቃት ለመፈጸም ሲቃጡ ሜዳ ድረስ በመዝለቅ የሚከላከሉና ምሳሌ የሚሆኑ ደጋፊዎችም አሉ፡፡
አዲስ ዘመን፦ የእግር ኳስን ህግ ከመተርጎም አንፃር ምን ክፍተት ይታያል?
አቶ ሚካኤል፦ ቅጣት ሲቀመጥ የፍትህ አካላት አብረው ነው መስራት ያለባቸው፡፡ ዳኞች ተጽዕኖ እየደረሰባቸው ያሉት በፍትህ አሰጣጥ ጉድለት ነው፡፡ ከተቀመጠው ደንብ ውጭ ሌላ ህግ በመጣስ ኮሚቴ ሲዋቀርና ከዳኞች ውሳኔ ውጭ የሆኑትን ውሳኔዎች ሲያስተላልፍም በብዙ መልኩ ዳኞችን ዋጋ ያስከፈለ ጉዳይ ነው፡፡ ህጉ በአግባቡ ቢተረጎም ኖሮ ግን ሜዳ ላይ ተጫዋቾችም ሆኑ አሰልጣኞች ስፖርቱን ሊያደፈርሱ ከሚችሉ ፀብ አጫሪ ክስተቶች ራሳቸውን ይቆጥቡ ነበር፡፡
የአውሮፓ አገራትን ተሞክሮ መመልከት እንደሚቻለው ህጋቸው ጠንካራ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በአግባብ መተርጎም መቻሉ ስፖርታዊ ጨዋነት እንዲጠበቅ አድርጓል፡፡ ህጋቸው ጥብቅ ስለሆነ ዳኛ ውሳኔ በሚሰጥበት ጊዜ አሰልጣኝ፣ ደጋፊው፣ ጋዜጠኞችና ሌሎች ባለሙያዎች የመተቸት መብት አላቸው፡፡ ትችቱም ሲቀርብ የተቀመጠ ህግ በመኖሩና ህግን ጥሶ የተገኘ አካል በህግ ይቀጣል የሚል ደንብ አለ፡፡ ነገር ግን ይህ ሲተረጎምና ሥራ ላይ ሲውል አይታይም፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ በተቀመጠው ህግ አንድ አጥፊ አካል መጀመሪያ የሚቀጣው በዲሲፕሊን ነው፡፡ አንድ የሚቀጣ አካል ከስድስት ጨዋታ እስከ እድሜ ልክ ምንም አይነት ጨዋታ እንዳያደርግ ሲቀጣና የተቀጣበትን ግማሽ ያህል ጊዜ ሲያደርስ ይቅርታ መጠየቅ እንደሚችልና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴውም ይቅርታ ሊያደርግለት እንደሚችል ተቀምጧል፡፡ ከዚያ በታች ባለው ገደብ በቁጥርም ሆነ በገንዘብ የተቀጣ ግን ምህረት የለውም ነው የሚለው፡፡ ይህ ህግ ግን በኢትዮጵያ ውስጥ ሲጣስ ነው የሚታየው፡፡ ለምሳሌ ጥፋት ያጠፋን ተጫዋች ዳኞች በቀይ ሲያስወጡ ተጫዋቹ አምስት ሺህ ብር ወይም አራት ጨዋታ ሊሆን ይችላል የሚቀጣው፡፡ እንደ ፊፋ ህግ ተጫዋቹ የተጣለበትን ቅጣት ግዴታ መቀበል አለበት፡፡ ይሁንና ይህ ተጫዋች ቅጣቱን ሳይጨርስ በሁለተኛው ጨዋታ ሜዳ ገብቶ ሲጫወት ይታያል፡፡ ምህረት አድራጊው አካልም አይታወቅም፡፡ ይህ ልምድ እያደገ በመምጣቱም ነው ህጎች ተጥሰው ውጥረት ውስጥ ስንገባ የሚታየው፡፡
ክለቦችም ነጥባቸው እስከመቀነስ የሚደያርስና በዝግ ስታዲየም እንዲጫወቱ የሚያደርግ ቅጣት የተላለፈባቸው ጊዜ ነበር፡፡ ነገር ግን ውሳኔዎች ተሽረው ይታያሉ፡፡ እግር ኳሱን የሚያስተዳድረው አካል በፈጠረው ክፍተት ችግሮች እየሰፉ በዳኞች ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ይፈጠራል፡፡ ሜዳ ላይ ቅጣት ሲሰጡ ‹‹ዛሬ ብትቀጣኝ ነገ እገባለሁ›› የሚል ስፖርተኛ ተፈጥሯል፡፡ ይህም ሜዳ ላይም ሆነ ከሜዳ ዳኞችን ጫና ላይ የጣለ ችግር ነው፡፡
አዲስ ዘመን፦ ለሚከሰተው ችግር ኃላፊነቱን ማነው የሚወስደው?
አቶ ሚካኤል፦ ሁሉም የየድርሻውን መውሰድ ይኖርበታል፡፡ ቁጥሩ ይነስ እንጂ ዳኞችም ጥፋቱ ላይ ይኖራሉ፤ አሰልጣኞች፣ ክለቦች፣ የፌዴሬሽን አመራሩ፣ ኃላፊነትን መውሰድ አለበት፡፡ ብዙ ጊዜ ግን ችግሩ በዳኞች ላይ ጎልቶ ይታያል፡፡ አንዳንድ ክለቦች የአቅማቸውን ማነስ ወደ ዳኛ ጥፋት ያመጡታል፡፡ ይህ ጥፋተኝነትን ወደ አንድ አካል ያመዘነ ድምዳሜ ስፖርቱን ያዳክመዋል፡፡
ብዙ ጊዜ የሚታዩ የጣልቃ ገብነቶች አሉ፡፡ ክለቦች ይህ ዳኛ አይመደብብኝ ይላሉ፤ የውድድር አመራርም እከሌ የሚባል ዳኛ አትመድብ በማለት አስተያየት የሚሰጥበት አጋጣሚ አለ፡፡ ዳኞችን ለመገምገም የተቀመጠው አካል እስካለ ድረስ በአሰራሮች ላይ ጣልቃ ገብነት ፈጽሞ መታየት የለበትም፡፡ በተለይ የምርጫ ሰሞን ተወዳጅነትን ለማትረፍ በማይመለ ከታቸው ነገር ጣልቃ የሚገቡ አሉ፡፡ ጨዋታዎች በሚካሄዱበት ወቅት ለተፈጠሩት ክስተቶች ጨዋታ ማቋረጥ ወይም አለማቋረጥ የዳኛ ስልጣን ነው፡፡ በዚህ ሂደትም እጃቸውን ለማስገባት የሚጥሩ አሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ኮሚሽነሮች በሚመድቧቸው አካላት ተጽዕኖ ስለሚፈጠርባቸው ዳኛ ተደበደብኩኝ አላጫውትም ሲል በግድ አጫውት በማለት ያስገድዳሉ፡፡ ውሳኔ በሚሰጠው አካል አሰራር ውስጥ ገብቶ ውሳኔ መስጠት ወዳልተገባ አቅጣጫ ይወስዳል፡፡ የግለሰቦች ጣልቃ ገብነት ስፖርቱን እንዲዳከም ካደረጉት ምክንያች ውስጥ አንዱ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፦ የዳኞች ውሳኔ ፍፁም ትክክል ነው ማለት ይቻላል?
አቶ ሚካኤል፦ በእርግጥ ዳኞች የሰው ልጆች በመሆናቸው ስህተቶች የሉም ማለት አይቻልም፡፡ እግር ኳስን ያለ ስህተት መዳኘትም አይቻልም፡፡ ለምሳሌ በአንድ ወቅት አዳማ ከነማና ቅዱስ ጊዮርጊስ በሚጫወቱበት ወቅት ቢጫውንና ቀዩን ካርድ በደረት ኪሶቼ ላይ አቀያይሬ በማስቀመጤ ቢጫ ለሚገባው ተጫዋች በስህተት ቀይ አውጥቼ ሰጠሁት፡፡ በኋላም ተጫዋቹ ሜዳውን ጥሎ ሊወጣ ሲል ግባ አልኩት፡፡ ቀይ ካርድ እንደሰጠሁት ነገረኝ፤ በስህተት ያደረግኩት መሆኔን ነግሬው እንዲጫወት አደረግኩት፣ በወቅቱ ስታዲየሙ ውስጥ የነበረው ደጋፊ በሙሉ ለተወሱ ደቂቃዎች መነጋጋሪያ አድርገውኝ ነበር፡፡ አንዳንድ ስህተቶች አዝናኝም ሆነው ያልፋሉ፡፡ ነገር ግን የገባው ጎል ትክክል ሆኖ መሻር አሊያም አግባብ ያልሆነ ጎል ማጽደቅ ዋጋ የሚያስከፍል ስህተት ነው፡፡ ስህተቶችን ላለመስራት ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚወሰድ ግን መታወቅ አለበት፡፡
ዳኞችን በእኩል ደረጃ የሚያስኬድ የስልጠና አሰጣጥ ሥርዓቱ ክፍተት ስላለበት የዳኞች አቅም ላይ የሚያሳርፈው አንዳች ተጽዕኖ አለው፡፡ የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ማህበር ለሁሉም የሚሰጠው የኢንስትራክተሮች ስልጠና አንድ አይነት ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ግን ስልጠናዎች የተለያዩ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በጨዋታ ወቅት አንዳንድ ረዳት ዳኞች ባንዲራ ዘርግተው ይገባሉ፤ ሌሎች ደግሞ ይህን አይቀበሉም፡፡ ይህንን ያመጣው በዚህ ዘርፍ የሚሰጠው ትምህርት ቋሚና ሁሉን አንድ ያደረገ ባለመሆኑ ነው፡፡ ይህ በሜዳ ላይም ሲተገበር ይታያል፡፡ ስለዚህ የሚሰጡ ትምህርቶች ወደ አንድ መምጣት ይኖርባቸዋል ማለት ነው፡፡ ህግ ተርጓሚው አካል ሲያስተምር የዓለም አቀፉን ልምድ ወስዶ ነው ግንዛቤ መስጠት ያለበት፡፡
በዳኝነት የመለኪያ መስፈርት ዳኞች የሚጠበቅባቸውን ያህል ካልሰሩና ካጠፉ ቅጣት ይጣልባቸዋል፡፡ ምንም እንኳን በዚህ ሂደት የኢትዮጵያውያን ዳኞች የጎላ ችግር ባኖርም ጥፋተኞች ካስባለንም በዳኞች የሚፈጸም አንዱ ትልቅ ስህተት ግን ተጫዋቾች ላይ የበዛ እርምጃ አለመውሰዳችን ነው፡፡ ይህ በብሄራዊ ቡድናችንም ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ፈጥሯል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚያደርጉት ውድድሮች ላይ ንትርክ ውስጥ በመግባት ቅጣት ሲተላለፍባቸው ይስተዋላል፡፡ ይህም የሆነው እዚህ የሚወሰደው ውሳኔ አናሳ በመሆኑና ብዙ ጊዜ በልምምጥ ስለሚታለፉ ነው፡፡ ይህንንም ማስተካከል ከዳኞች የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡
አዲስ ዘመን፦ የዳኞች ማህበር ዳኞች ላይ ችግሮች እንዳይከሰቱ ምን ምን ጉዳዮችን አከናውኗል? ከፌዴሬሽን የተገኘው ግብረ መልስ ምን ይመስላል
አቶ ሚካኤል፦ ይህ ማህበር ከተመሰረተ ሰባት ዓመት ሆኖታል፡፡ በጉዞውም በሚከሰቱት ችግሮች ዙሪያ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር የደብዳቤ ምልልሶችን ጨምሮ ብዙ ጊዜ ውይይቶች ተደርገዋል፡፡ በተለይ ህጎች አይፍረሱ፤ በትክክል ይተርጎሙ፣ ዳኞ በሚወስኑት ውሳኔ ላይ ጣልቃ ገብነት አይኑር በሚሉ ጉዳዮች መፍትሄ እስከሚገኝ ድረስ ብዙ ርቀቶችን ሄደንበታል፡፡ ሆኖም ግን ይህ ሳይስተካከል እንዲሁ በመጓተት ሂደት ውስጥ ሆነ፡፡ ችግሩ ስር እየሰደደ በመምጣት በቅርብ ጊዜ የምናስታውሰውን ፍጹም ከስፖርታዊ ጨዋነት ያፈነገጠና ዳኞችን ለድብደባ የጋበዘ ክስተት እንዲፈጠር አደረገ፡፡ የአገሪቱም የእግር ኳስ ስፖርት በመልካም ስም እንዳይነሳ ምክንያት እየሆነ መጥቷል፡፡
የሜዳ ላይ ችግሮች መፍትሄ እስከሚያገኙ ውድድር እንዲቋረጥ በጠቅላላ ጉባኤው ተነጋግር ወስኖ ነበር፡፡ ይህም አድማ ሳይሆን ቆም ብሎ በማሰብና ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት ነበር፡፡ ከዚህ ውጭ ችግሮች እንዲቃለሉ በዳኞች ማህበር በኩል ቅድመ ሁኔታዎችም ተቀምጠዋል፡፡ ከኢንሹራንስ፣ ከለላ ከመስጠት፣ ከአውሮፕላን ቲኬት፣ ወንጀለኞችን ለህግ ከማቅረብ፣ ትምህርትና ስልጠና ከማግኘት አንጻር ጥያቄዎችን በማቅረብ ለጊዜው መፍትሄ ሊሆኑ የሚችሉ ምላሾች ተሰጥተዋል፡፡
በተለይ የኢንሹራንስ ጉዳይ ከምንም በላይ አስቸኳይ እንዲሆን ስለታሰበ የመፍትሄ ምላሽ ተሠጥቶበታል፡፡ በዚህም መሰረት በዚህኛው አመት 30 ሰዎች ኢንሹራንስ እንዲያገኙ፣ ለሚቀጥለው ዓመት ደግሞ 461 ዳኞችና 160 ኮሚሽነሮች ኢንሹራንስ እንዲገቡና ይህ ካልሆነ ግን ውድድሩ እንደማይጀመር በደብዳቤ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ በትምህርትና ስልጠናው ላይም በጋራ ለመስራት ስምምነት ተፈጽሟል፡፡ ከለላ በማግኘት በኩል ያለው ሂደትም በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡ ይህንን ማስከበር ደግሞ ጥቅሙ የዳኞች ብቻ ሳይሆን የጋራ ነው፡፡ የዳኞች ማህበር እንዲወሰንና ስምምነት ላይ እንዲደረሱ የሚሻቸው ጉዳዮች እነዚህ ብቻ አይደሉም፡፡ በቀጣይ ፌዴሬሽኑ ከሚመሩ አካላት ጋር እየተነጋገርን ጥያቄዎችም እያቀረብን መልስ እንዲያገኙ እናደርጋለን፡፡
አዲስ ዘመን፦ ችግሮችን በማረም ረገድ በቀጣይ ምን መደረግ አለበት?
አቶ ሚካኤል፦ ሜዳ ውስጥ የሚከሰቱ ችግሮች እየተባባሱ ከሄዱ የሰው ህይወትም ሊጠፋ ይችላል፡፡ ስሜታዊ በመሆኑ የሚወሰዱ እርምጃዎች ከባድ ጉዳት ያስከትላሉ፡፡ አሁን ላይ አገሪቷ በተረጋጋ ችበት ሰአት የእግር ኳስ ስፖርቱም ተረጋግቶ መከናወን አለበት፡፡ ስፖርትን ከፖለቲካዊ አስተሳሰብ ነጻ ማድረግ አለብን፡፡ ብሄር ተኮር አመለካከቶችም መጽዳት አለባቸው፡፡ በውሳኔዎች ላይ ጣልቃ የሚገቡ አካላት ከተግባራቸው ሊቆጠቡ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ዳኞችን በስፋት ዋጋ እያስከፈለ ያለው ይህ በመሆኑ፡፡ ፌዴሬሽኑ ጾታዊ ስብጥርን መሰረት ያደረገ የአመራር ሥርዓትም ሊኖረው ይገባል፡፡ ዳኝነት ፍጹማዊነት እንዳልሆነ በመገንዘብ ዳኞች ጥፋት ሲያጠፉ ስለሚጠየቁ ይህንን አምኖ መቀበል ያስፈልጋል፡፡ በጥቃቅን ስህተት ችግሩን አጉልቶ በማሳየት ባላደገው ስፖርት ላይ መርዝ የመጨመር አባዜ እንዲቀረፍ ፌዴሬሽኑና በስሩ ያሉት አካላት ዘወትራዊ ምክክር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን፦ ለሰጡኝ ማብራሪያ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ሚካኤል፦ እኔም ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

አዲሱ ገረመው

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።