‹‹ፋግ›› የባህል ጨዋታ - በሰሜን ጎንደር እና አጎራባች አካባቢዎች Featured

08 Jun 2018
አቶ አማረ ጥጋቡ፤ አቶ አማረ ጥጋቡ፤

የእነ እገሌ ቡድን ዓይኑ የታወረው፣
አርባ ኳስ ሰጥተነው አርባውንም ሳተው፡፡
እንዲህ ላትችሉን አትላወሱ፣
ዓይንን እንደ ንስር፤ እጅ እንዳንበሳ ከኛ ተዋሱ፡፡
እየተባለ ተሸናፊው ቡድን በሥነ ቃል ሲሸነቆጥ፤ በሌላ ጎራ ደግሞ ለጀብደኛውና አሸናፊው ቡድን ተከታዩ የሙገሳ ቃል ግጥም ይደረደርለታል፤ ይሽጎደጎድለታል በ‹‹ፋግ›› ጨዋታ፡፡
ጆሮው እንደቆቅ ዓይኑ እንደ ንስር፣
በአንዴ መትቶ ወንዝ የሚያሻግር፡፡
በረጅም ዱላ ቢቀረድዳት፣
ኳሲቱ ጠፋች የሄደችበት፡፡
በማለት አሸናፊው ቡድን ይወደሳል፡፡ ጨዋታው ደግሞ ሸካ፣ ፋግ ወይንም ሹካ ተብሎ ይጠራል፡፡
ሹካ በአብዛኛው በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር፣ የትግራይ ክልል አክሱም አካባቢ እና በአጎራባች ቦታዎች ከሚዘወተሩ ባህላዊ የስፖርት ጨዋታዎች አንዱ ነው፡፡ ጨዋታው በተለምዶ ስሙ ከቦታ ቦታ ቢለያይም በጎንደርና አካባቢው ‹‹ፋግ›› ወይንም ‹‹ሹካ›› በመባል የሚታወቅ ሲሆን፤ በትግራይ አክሱምና አካባቢው ‹‹ሸካ›› በመባል ይታወቃል፡፡
አቶ አማረ ጥጋቡ ይባላሉ፡፡ የሰሜን ጎንደር ተወላጅና በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህር ናቸው፡፡ ይህንን ስፖርት ከልጅነታቸው ጀምሮ ሲያዘወትሩት እንደነበር አጫውተውናል፡፡ ይህ የባህል ስፖርት በብዙዎች ዘንድ ይታወቅና ስፖርታዊ ፋይዳውም ጎልቶ ይታይ ዘንድ የማስተዋወቅ ሥራውን እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ይህ ስፖርት እንደ አብዛኞቹ የባህል ስፖርት መቼና የት እንደተጀመረ ባይታወቅም፤ ሲወርድ ሲወራረድ የመጣና አሁንም በተጠቀሱት አካባቢዎች እየተዘወተረ ያለ ነው የሚሉት አቶ አማረ፤ የሹካ ጨዋታ ከፍተኛ አካላዊ ጥንካሬንና ቅልጥፍናን የሚጠይቅ፣ በተፈጥሮው ጉልበትንና አቅምን ከሚፈትሹ ጨዋታዎች ውስጥ እንደሚመደብና ጨዋታው ያልተገደበ ክፍት የመጫወቻ ሜዳ እንደሚያስፈልገው ነው የሚናገሩት፡፡
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ ይህ ጨዋታ በሁለት ቡድኖች መካከል የሚደረግ ፍልሚያ ሲሆን፤ ኳስን በዱላ በመምታትና በተቃራኒ ቡድን በኳስ ላለመመታት የሚደረግ ፉክክር ነው፡፡ ተከላካይ ቡድን ኳስን የሚቀልብና በቀለበው ኳስ ተቃራኒ ቡድን ለመምታት ሲሞክር አጥቂ ወይንም ኳስ የሚመታው ቡድን ደግሞ ኳስን በዱላ ላለመሳትና በቀላቢ ቡድን ላለመመታት ይጫወታል፡፡ በዚህ ጊዜ ኳስ ለውጥ የሚደረገው አጥቂ ቡድን ኳስ የመምታት እድሉን ሙሉ በሙሉ ከሳተ ወይንም ከመዝመቻና ከመነሻ ምልክቶች መካከል ባለው የሜዳ ክፍል በተቃራኒ ተጫዋች በኳስ ከተመታ ነው፡፡
የተጫዋቾች ቁጥር በእያንዳንዱ ቡድን ውስጥ ከ 3 እስከ 7 ተጫዋቾች እንዲሆኑ የሚመረጥ ቢሆንም፤ ይህ ነው የተባለ ውስን ቁጥር ግን የለውም፡፡ በሹካ ጨዋታ ውስጥ ማሸነፍ ማለት ለረጅም ሰዓት ወይንም ለተደጋጋሚ ጊዜ ኳስ የመቅለብ ብልሐትና ብቃት ያለው ቡድን መሆን አለበት፡፡
አጨዋወት
አቶ አማረ የአጨዋወት ስልቱንም ሲገልፁ፤ በመጀመሪያ ከሁሉም ተጫዋቾች ውስጥ ሁለት የቡድኑ መሪ ወይንም የቡድን አባት በመምረጥ ሁለት ቡድኖችን ይመሰረታሉ፡፡ ጨዋታውን ሁለቱ የቡድን አባቶች እጣ አውጥተው በሥራቸው ልጆቹን አቧድነው የቡድን አጋሮቻቸውን ያውቃሉ፡፡ ቡድን ከመሰረቱ በኋላ የመዝመቻ ቦታውን ተስማምተው በምልክት ይወስናሉ፡፡ ከዛ እጣ የደረሰው ቡድን አባት ኳስ በመምታት የቡድን አባላቱ ዘምተው እንዲመጡ ያደርጋል፡፡ ለእርሱ በተሰጠው አራት እድል ከቡድን አጋሮቹ አንድና ከዚያ በላይ ዘምተው ከመጡ ጨዋታው በነሱ በኩል ይቀጥላል፡፡ ካልሆነ ግን ለሌላኛው ቡድን ኳስ ተቀይሮ በዚህ መልኩ ጨዋታው ይካሄዳል፡፡
የጨዋታው ዋና ዋና ህጎች
አቶ አማረ፤ ‹‹ይህ የባህል ጨዋታ እንደሌሎች የስፖርት ዓይነት ጨዋታዎች ሁሉ የራሱ የሆኑ ህጎች አሉት፡፡›› ይላሉ፡፡ ጨዋታው የሚጀመረው በእጣ ሲሆን፤ እጣ የደረሰው ቡድን ኳስ በይ ወይንም አጥቂ ሲባል፤ ሌሎቹ ደግሞ ኳስ አብይ ወይንም ቀላቢ ይሆናሉ፡፡ ጨዋታው ሁለት የቡድን አባቶች ሲኖሩት ሌሎች የቡድን አባላትን በማቧደን ይመለምላሉ፡፡ ኳስ በዕጣ የደረሰው ቡድን ከተቃራኒ ቡድን የሚሰጠውን ኳስ በመምታት የሚጀምር ሲሆን፤ ቀሪ ባልደረቦቹ ግን ኳስ መምታት የሚችሉት ለቡድን አባቱ በተሰጠው አራት ኳስ የመምታት ዕድል በተቃራኒ ቡድን በኳስ ሳይመቱ ዘምተው ከመጡ ብቻ ነው፡፡ ኳስ የሚመታው የቡድን አባት በሁሉም ሙከራ አንድ ሰው ዘምቶ ሳይመጣ ከጨረሰ ኳስ ተቀይራ ለተቃራኒ ቡድን ይሰጣል፡፡ አንድ ተጫዋች ኳስ የመምታት የሙከራ ዕድሉ አራት ጊዜ ብቻ ሲሆን፤ ኳስ የሚመቱ አባላት ቡድን ከመዝመቻውና ከመነሻው መካከል ባለው ሜዳ መቆም አይፈቀድላቸውም፡፡
እስከ አንድ ሜትር ርዝመት ሊደርስ የሚችልና ውፍረቱ ከሁለት እስከ ሦስት ሳንቲ ሜትር የሚሆን ድቡልቡል በትር ወይንም ዱላ ያስፈልጋል፡፡ እንዲሁም በግምት የሜዳ ቴኒስ ያክል መጠን ያላት ከጨርቅ፣ ከፀጉር፣ ከፕላስቲክ ወዘተ ሊሰራ የሚችል ለስላሳ፣ ለመወርወር ቀላልና በአንድ እጅ በቀላሉ ሊያዝ የሚችል ኳስ ያስፈልጋል፡፡ ኳሷ ስትመታ ጉዳት ልታደርስ የማትችል መሆን እንዳለባትም ነው አቶ አማረ የሚያብራሩት፡፡
በጨዋታው ወቅት ደልዳላና ክፍት ሰፊ የመጫወቻ ቦታ ይመረጣል፡፡ የመጫወቻ ቦታውም ኳስ መምቻው አካባቢ በግምት 10 ሜትር ስፋት ያለው ሆኖ ኳስ ወደሚመታበት አቅጣጫ እንደ ጎን ሶስት ወይም እንደ ውርወራ ስፖርት ሜዳዎች ቅርጽ ያለው ሲሆን ርዝመቱ ኳሷ እስከሄደችበት ድረስ ሲሆን፤ በሜትር አይወሰንም፡፡ በመነሻው በኳስ መቅለቢያው መስመር እና በመድረሻው ምልክት መካከል ያለው ርቀት በሁለት ቡድኖች ስምምነት የሚወሰን ሲሆን፤ በግምት ከ50 እስከ 60 ሜትር ሊረዝም ይችላል ይላሉ፡፡
ከአጥቂ ቡድን አንድ ተጫዋች የቡድን አጋራቸው ኳስ ሲመታ አንድ ወይም ከዚያ በላይ አባል በአንድ ጊዜ ዘምቶ መምጣት ይችላል፡፡ ብዙ ዘምተው የመጡ አባላት ካሉ የማጥቃት እድላቸው እየሰፋ ይሄዳል፡፡ አንድ ዘማች ፈጣን እና ቀልጣፋ ከሆነ በአንድ ኳስ ምት ከመዝመቻው ደርሶ መመለስ ይችላል፡፡
ማንኛውም የአጥቂ ቡድን አባላት በመዝመቻውና በመብያው ክልል መካከል በተቃራኒ ቡድን በኳስ ከተመታ የኳስ ለውጥ ይደረጋል፡፡ ኳስ የሚያበላ ቡድን ተጫዋች የተቃራኒን ቡድን አባል በመዝመቻ እና በመነሻ ነጥብ መካከል ያገኘውን ማንኛውንም ተጫዋች በኳስ የመምታት መብት አለው፡፡ ጨዋታውን ለመጫወት የሚያስፈልጉ የቡድን አባላት ብዛት ከሦስት እስከ ሰባት ቢሆን ይመረጣል፡፡
አቶ አማረ እንዳሉት፤ በዚህ ጨዋታ ላይ ይህ ነው የሚባል ነጥብ አያያዝ ባይኖርም ለተደጋጋሚ ሰዓት ኳስ ሲበላ የቆየ ቡድን እንደአሸናፊ ይቆጠራል፡፡ የኳስ ለውጥ የሚካሄደው አንደኛ የአጥቂ ቡድን የተሰጠውን ሙከራ ሁሉ ተጠቅሞ ኳስን ከሳተ ወይንም ሙከራውን እስኪጨርስ ከቡድን አባላት ዘምቶ የመጣ ሰው ከሌለ ይሆናል፡፡ ሌላው ደግሞ ተቃራኒ ቡድን አባላት አልቻልናችሁም እድል ስጡን ብሎ ከጠየቀ ነው፡፡
የጨዋታው ጠቀሜታ
ስፖርት ለሰው ልጅ የሚሰጠውን በርካታ ጠቀሜታዎች በዚህ የባህል ስፖርት አማካኝነት ማግኘት እንደሚቻል የሚናገሩት አቶ አማረ፤ ይህ ጨዋታ ቀልጣፋና ፈጣን ሩጫን ስለሚጠይቅ ለተጫዋቾች የአካል ብቃታቸውን እንደሚያ ዳብርና ይህ ደግሞ እግረ መንገዱን የአተነፋፈስና የደም ዝውውር ስርዓትን ጤና ለማሻሻል ይረዳል፡፡ ከዚህ ባሻገር ጨዋታው ትኩረትን ስለሚጠይቅ የአዕምሮ ንቃትን ያዳብራል፡፡ ኳስ በሚመታ ሰዓት የግብረ መልስ ችሎታን ስለሚጠይቅ የእይታና የድርጊት ቅንጅታዊ አሰራርን ያዳብራል፡፡ በአጠቃላይ እንደማ ንኛውም ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የአካልና የአእምሮ ጤንነትን በመጠበቅና በማሻሻል ጤናማ እንድንሆን ያደርጋል፡፡
የተጫዋቾች ማህበራዊ መስተጋብር ምን ይመስላል
አቶ አማረ እንደገለጹት፤ ይህ ጨዋታ እንደማንኛውም የቡድን ጨዋታና ስፖርት ተሳታፊ ለሆኑ ስፖርተኞች ከጓደኞቻቸውና አብሮ አደጎቻቸው ጋር ማህበራዊ ግንኙነታ ቸውን ያዳብራል፡፡ በተጨማሪም የማሸነፍና መሸነፍ ባህሪን ተላብሰው በማደግ በሥነ ምግባራቸው ጥሩ እንዲሆኑ ከማድ ረጉም በላይ በራስ የመተማመን ክህሎታ ቸውን ያዳብሩ በታል፡፡ በአጠቃላይ የተስተካከለ ሁለንተናዊ እድገት እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡
የጨዋታው አሁናዊ ገፅታ
‹‹ቆየት ባሉት አመታት ልጆች እያለን ሰብል ተሰብስቦ በሚያበቃበትና በዓላትን ተንተርሰው በሚኖሩን ትርፍ ጊዜያቶች፣ ከብቶችን በምናግድበት ወቅት ፣ ጨዋታ ውን በብዛት እናዝወትር ነበር፡፡ ነገር ግን ከጊዜ ሂደት በኋላ ጨዋታው እየተቀዛቀዘ መጥቷል፡፡ ትኩረቱ ወደ ዘመናዊ ስፖርት ስላደላና የባህል ጨዋታ እንደ ኋላ ቀር ተደርጎ ስለሚታሰብ የዚህ ስፖርት አዝወታሪዎች ፊታቸውን ወደ እግር ኳሱ አዙረውታል፡፡›› በማለት አቶ አማረ ጨዋታው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደበዘዘ መምጣቱን ይናገራሉ፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት፤ ስፖርቱ ዘመናዊ ከሚባሉ የስፖርት ዓይነቶች ባልተናነሰ ሁኔታ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን ስለሚሰጥ መዘንጋት የለበትም፡፡ ጨዋታውን ሽልማት ለማግኘት ሳይሆን ጎበዝና ሰነፍን በመለየት የአቋም መለኪያ ማድረግ እንዲሁም ተዝናኖትን ለመፍጠር ነው፡፡ ከፍተኛ ፍጥነትንና አነጣጥሮ ኳስ መምታትን ይጠይቃል፡፡ ሆኖም ግን ሰው ስለ ስፖርቱ ያለው ግንዛቤ አናሳ በመሆኑ ከነበረበት የተሻለ ተዘውታሪነት ቁልቁል እየተጓዘ ነው፡፡
ምክር
እንደ አቶ አማረ ገለጻ፤ የ‹‹ሹካ›› ባህላዊ ጨዋታ ሰርቶ መብላትን በምሳሌነት በውስጡ የያዘና በአስተማሪነቱ ትልቅ ድርሻ ያለው ነው፡፡ ባህልን ከመጠበቅ አንፃር ስፖርቱ ትኩረት ይሻል፡፡ ማህበረሰቡን በአስተሳሰብ ከመለወጥ ጀምሮ ተግባራዊ ሊደረጉ የሚገቡ መፍትሄዎች በባህል ስፖርት ፌዴሬሽን በኩል መፈጸም አለባቸው፡፡ ከፍተኛ ንቅናቄ ተፈጥሮ እንዲህ አይነት ለመጥፋት የደረሱ የባህል ስፖርቶችን ግንዛቤ በመፍጠር መጠበቅ ይገባል፡፡
ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ ከ290 በላይ የሚሆኑ የባህል ስፖርቶች አገሪቷ ውስጥ አሉ፡፡ ነገር ግን ተመዝግበው እውቅናን ያገኙና አገር አቀፍ የባህል ፌስቲቫል ላይ ለተሳትፎ የሚቀርቡት 11 ብቻ ናቸው፡፡ የባህል ስፖርት ፌዴሬሽን በየዓመቱ ሁለት የባህል ስፖርቶችን ለመመዝገብ እቅድ እንደያዘ ቢናገርም እነዚህን ሁሉ መዝግቦ ለመጨረስ ብዙ አመታን ስለሚፈጅ አሰራሩን መለወጥ ይኖርበታል፡፡ በተለይ አሁን ላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በየአካባቢው ተስፋፍተው ስላሉ በትብብር ቢሰራ ባህላዊ ጨዋታዎችን ከመጥፋት መታደግ ይቻላል፡፡ በዚህ ረገድ ለአብነትም የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ በሰሜን ሸዋ ውስጥ ያሉ የባህል ስፖርቶችን በመመዝገብ ላይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
‹‹ሹካ›› ባህላዊ ጨዋታን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች እየተረሱ የሚመጡ የባህል ስፖርቶችን ሰብስቦ መሰነድ ብቻ ሳይሆን እየተተገበሩ እንዲቆዩ በማድረግና የተሳታፊን ቁጥር መጨመር ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ተግባር ነባር የዚህ የባህል ስፖርት ከዋንኞችንም መጠቀም የግድ ይላል፡፡ የተሳታፊ ቁጥር መጨመሩ ጨዋታዎቹ አካላዊ እንቅስቃሴን ስለሚከተሉ ጤንነታቸውን የሚጠብቁ ዜጎች ቁጥርም እንዲበዛ ይሆናል፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት፤ ብዙዎች ስፖርትን ከኢኮኖሚ ችግር ማምለጫነት ለመጠቀም ያስባሉ፡፡ በዚህ ዘመን በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው ግንዛቤ ስፖርት የሚጠቅመው ገንዘብ ለማግኘት ነው የሚል ሲሆን፤ ይህ ደግሞ ለጥቂት ስፖርተኞች ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ ሽልማትን አስቦ የሚደረግ ስፖርታዊ ጉዞ አድካሚ ነው፡፡ ነገር ግን በለስ ከቀናው በዘርፉ ኢኮኖሚያዊ ጥቅምን ማግኘትም ይቻላል፡፡ ፍላጎቱ የጤና ጥቅም ማስቀደም ላይ ማተኮር መሆን አለበት፡፡ ስለሆነም ስፖርት የሚሰራ ሰው መጀመሪያ ጤናውን እየጠበቀ ነው ተብሎ ስለሚታሰብ ኪሳራ እንደሌለበት ማስገንዘብ ይገባል፡፡ በተለይ መገናኛ ብዙኃን እከሌ እከሌን አሸነፈ ብቻ ሳይሆን፤ የስፖርት መሰረታዊ ጥቅሞችንም በመዘገብ ረገድ ከፍተኛውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል፡፡ የባህል ስፖርት ዝንባሌውም የጠፋው ከስፖርቱ የሚገኘውን የጤና ጥቅም ካለመረዳት ነው፡፡ ከምንም በላይ የማንነት መገለጫና የአገር ክብር የሆኑ የራስን ባህላዊ ስፖርት መጠበቅ ታሪክ እንደመስራት ስለሚቆጠር በዚህ ልክ መረዳት ከሁሉም ባለ ድርሻ የሚጠበቅ ነው፡፡
ለባህል ውድድር ከቀረቡት ጥቂት ጨዋታዎች በተጨማሪ ሌሎችም ተካተው በውድድር ፌስቲቫሎች ውስጥ ሊካተቱ ይገባል፡፡ የባህል ስፖርቶች የሚካሄድ ባቸው የመወዳደሪያ ስፍራዎች ለዘመናዊ ስፖርት መወዳደሪያ የተዘጋጁ እንጂ ራሳቸውን ችለው ለባህል ስፖርት መወዳደሪያ የተሰሩ አይደሉም፡፡ በመሆኑም ከመወዳደሪያ ስፍራ ጀምሮ የተለያዩ ግብዓቶችን ከማግኘት አንጻር ውስንነት ስላለ ስፖርቶቹ እየተዳከሙ ይሄዳሉ፡፡ ስለዚህም ክዋኔዎች ላይም ከፍተኛ ትኩረት ማድረግ ይገባል፡፡ ስፖርቶቹ ከጠፉ በኋላ ከመፈለግ በቁመናቸው እያሉ መንከባከብ አቻ የሌለው አማራጭ ነው፡፡
ባህል ሲባል፤ ሙያዊ ጥበብ፣ ሙዚቃ ወይንም ማህበራዊ ልማዶች ብቻ አይደለም፡፡ በትርጉሙ ሠፊና ጥልቅ የሆነው የባህል እሳቤ በውስጡ አካቶ ከያዛቸው ጉዳዮች አንዱ የባህል ስፖርት ነው፡፡ በአገራችን ያሉት የባህል ስፖርቶች በተለያዩ ማህበራዊ ቡድኖች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች የሚማማሩበት፣ የሚፈጥሩትና የሚለዋ ወጡት የባህሪና የእሣቤ መወራረስ የሚፈጥሩበት፣ የሚዝናኑበት አንዱን ከአንዱ በጉብዝና የሚለዩበት አይነተኛ ሚና አለው፡፡ ከዚህም ባሻገር ማህበረሰቦች በሚያከና ውኗቸው የባህል ስፖርት ጨዋታዎች የሥነምግባር መመሪያቸውን፣ ቋንቋቸውን፣ የአምልኮ ሥርዓታቸውን፣ ሙያቸውን፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራቸውን፣ የአለባበሣቸውን ሁኔታ፣ የምግብ አመራረታ ቸውንና አዘገጃጀታቸውን፣ የፖለቲካና የምጣኔ ሀብት ሥርዓታቸውን ሁሉ ሊያንጸባርቁበት ይችላሉ፡፡ በመሆኑም ‹‹የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ›› እንዲሉ ሳንቀደም የኛ የሆኑትን በመጠበቅም ሆነ ተንከባክቦ ለትውልድ በማስተላለፍ አሻራችን ማሳረፍ አለብን፡፡ የባህል ስፖርቶች ለዘመናዊ ስፖርት መሰረት ናቸውና ትኩረት ሊሰጣቸ ውም ይገባል፡፡ እነዚህ ባህላዊ ስፖርቶች የእርስ በእርስ ግንኙነትን ከማጠናከርም በላይ ለባህል እድገት እና መስፋፋት ከፍተኛ ትርጉም አላቸው፡፡
የባህል ስፖርቶችን ከጤና ለውጥና ሌሎች ፋይዳዎች ጋር በማስተሳሰር የተለያዩ የመስህብ ሀብት የሆኑና አደባባይ ያልወጡ ስፖርቶችን የማሳወቅ ተግባራት ሊከናወኑ ይገባል፡፡ የአገሪቷ ስፖርት ፖሊሲ ዋና የትኩረት አቅጣጫ ህዝባዊ መሰረት ያለው ስፖርት በሁሉም ማህበረሰብ ዘንድ በማስፋፋት እንደ ዘመናዊ የስፖርት ዓይነቶች ሁሉ ህብረተሰቡን በባህል ስፖርት ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል የሚለው የዝግጅ ክፍላችን መልዕክት ነው፡፡

አዲሱ ገረመው

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።