ገረመው ደንቦባ - ሮምን በብስክሌት የወረሩ ጀግና Featured

10 Jun 2018
ገረመው ደንቦባ ገረመው ደንቦባ

አንጋፋ ስፖርተኛ ናቸው። ለተሳተፉበት የስፖርት ዘርፍ በኢትዮጵያ እንዲሁም በዓለም ኦሎምፒክ ፈር ቀዳጅ ናቸው። ይሄ ግነት ሳይሆን ታሪክ ቁልጭ አድርጎ በገፆቹ የከተበው እውነት ነው። እኚህ ሰው ለአገር ባለውለታ ናቸው። ስፖርቱ አሁን ካለበት አንፃር ከተመለከትነው የእርሳቸው ሚና የእውነትም ገኖ ሊታየን ይችላል። ለመሆኑ እኚህ ስፖርተኛ ማን ናቸው? በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የሳይክል ተወዳዳሪ፣ የኦሎምፒክ ተሳትፎ ፈር ቀዳጅ፣ አሰልጣኝ እንዲሁም የጠንካራ ስብዕና ባለቤት ጋሽ ገረመው ደንቦባ።

ተነግሮ ከማያልቀው ስፖርቱ ዓለም ትዝታቸው ጥቂት እንዲያወጉን፤ የህይወት ጉዟቸውን እንዴት እንዳሰመሩት እንዲያጫውቱን፤ ለሚወዱት ስፖርት ዕድገት ያላቸውን ልምድ እንዲያጋሩን ከመኖሪያ ቤታቸው ተገኘን። ጋሽ ገረመውን ግን በጥሩ ጤንነት ላይ ሆነው አላገኘናቸውም። ጠንካራው ሰው ህመም አሸንፏቸው ከቤት ውለዋል። በህክምና ላይ እንደነበሩ ለመረዳት አያዳግትም። በአፍንጫቸው ላይ ኦክስጂን ሰክተዋል። እግራቸው ላይ ያጋጠማቸው ጉዳት ብዙም አያራምዳቸውም። እንደዚያም ሆኖ ግን እኛን በእንግድነት መቀበል አላቃታቸውም። እንዳደጉበት ባህል ተቀበሉን። ለጥያቄያችንም ሳይሰስቱ ከታሪክ ባህራቸው እየጨለፉ አጫወቱን። ብዙ የመውጣት እና የመውረድ የህይወት ሂደቶች ላይ አወጋን። ነገር ግን ወደኋላ ተመልሰን የጋሽ ገረመውን የስፖርት ህይወት ከመዳሰሳችን በፊት በቅድሚያ ይህን ማለት ወደድን።
እኚህ ባለታሪክ ከቤት ውለዋል። በእርሳቸው ዘመን ባላቸው ጥንካሬ ለአገር በብስክሌት ስፖርት ፈር ቀዳጅ ውጤቶችን አስመዝግበዋል። እነ አበበ ቢቂላን፣ ማሞ ወልዴ፣ ይድነቃቸው ተሰማ ለዚህች አገር ከሰሩት ውለታ በማይተናነስ በብስክሌት ስፖርት ላይ ተጠቃሽ ሥራ የሠሩ ናቸው። ለዚህ ደግሞ የታሪክ ዶሴዎችን በቀላሉ መግለጥ በቂ ነው። ስለዚህ እኚህን ጀግና ማወደስ፤ ከዚያም ባለፈ በህመማቸው ሰዓት ከጎናቸው መሆን ይኖርብናል። ጀግናን በህይወት እያለ የማወደስ ልምድ ሊኖረን ይገባል። እንደ እድል ሆኖ ብዙ ጀግኖቻችንን ሳናሞግሳቸው ካጠገባችን ተለይተውናል። ይህን ስህተት ሁሌም መድገም ሊበቃን ይገባል። ሁሉም ባለው አቅም ባለውለታ የሆኑ ስፖርተኞችን እውቅና ሊሰጥ ይገባል ።
የጣሊያን ወረራ
የጋሽ ገረመው የትውልድ ከተማ አዲስ አበባ ነው። አንዋር መስጊድ ፊት ለፊት ሀብተ ጊዮርጊስ ድልድይ እየተባለ በሚጠራው ሰፈር ነው ተወልደው ያደጉት። ጣሊያን ዓይኑን በጨው አጥቦ ኢትዮጵያን በድጋሚ ለመውረር ሲገባ የያኔው እምቦቃቅላ የዛሬው አንጋፋ ስፖርተኛ ጋሽ ገረሞ ከተወለዱ የአንድ ዓመት እድሜ አስቆጥረው ነበር። በወቅቱ ለኢትዮጰያውያን መርገምትን ይዞ ከተፍ ያለው ፋሽስት ግን ለርሳቸው የወደፊት ህልም ፈር የቀደደ አጋጣሚን ፈጥሮ ነበር። መቼም ሁሉም ነገር መጥፎ አይሆንም። ወራሪ ወታደሮቹ ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ የጣሊያን ስሪት የሆኑትን እነ ቢያንኪሊ፣ባርታሊ እንዲሁም ቦንሲት የሚል ስያሜ ያላቸው ብስክሌቶችን ይዘው ገብተው ነበር። ታዲያ እነዚህ ብስክሌቶች ፋሽስት በጀግኖች ዓርበኞች ድል ተደርገው ከኢትዮጵያ ሲወጡ በምርኮነት አገር ውስጥ ቀርተው ነበር።
ፋሽስት በአምስት ዓመት የቆይታ ጊዜው ወታደሮቹ በአዲስ አበባ ብስክሌቶችን በጎዳናዎች ላይ በመንዳት፣ ሰዎችን በማለማመድ እና ውድድር በማካሄድ የኢትዮጵያውያንን ልብ ለመማረክ ጥረት ያደርግ ነበር። በወቅቱ በዓለም ላይ በተለይ በፈረንሳይ፣ ቤልጄም እንዲሁም ሆላንድ የመሳሰሉ አገራት ብስክሌት ተወዳጅ እና ቀዳሚው ስፖርት ነበር። ለዚህ ስፖርት ኢትዮጰያውያኑ እንግዳ ቢሆኑም በቀላሉ እውቀቱን በመቅሰም ጥሩ ችሎታን አዳብረው ነበር። በጎዳናዎች ላይ እንደድንገት ከወራሪዎቹ ጣሊያኖች ጋር ሲገናኙ እንኳን በቀላሉ እያለፏቸው ይጓዙ ነበር። በዚህ ሁኔታ ላይ እንዳለ ፋሽስት ከአገሪቷ ሳይወድ በግዱ ተባረረ። የብስክሌት ስፖርት ግን በኢትዮጵያ ተወዳጅነቱ ቀጠለ። ድሮውንም ኢትዮጵያውያን ከፋሽስት እንጂ ከስፖርቱ ቂም አልነበራቸውም። የወደፊቱ ባለታሪክ ጋሽ ገረመውም ጣሊያን ሲወጣ ስድስት ዓመት ሞላቸው። ዕድሜያቸው ለአስኳላ ደርሶ ዘመናዊውን ትምህርት ተያይዘውት ነበር።
ከብስክሌት ጋር ወዳጅነት
የጋሽ ገረመው ብስክሌትን የተዋወቁት ገና በጨቅላ ዕድሜያቸው ውድድሮችን በመመልከት ነው። በአምስት እና ስድስት ዓመታቸው እነ ካሳ ፈዲር፣ ኤርትራዊው ካሳ ርእሶም፣ ሙሉጌታ ካሳ፣ታዬ ክፍሌ የሚባሉ ብስክሌተኞች ከአንዋር መስጊድ ፊት ለፊት እነኡስማን ኪኪያ ሱቆች አካባቢ እነ እራስ ሃይሉን የመሳሰሉ ታላላቅ መሳፍንት እና መኳንንቶች በክብር ቦታቸው ላይ ተቀምጠው ውድድር ሲያደርጉ ሲመለከቱ ጋሽ ገረመውም በራፋቸው ላይ ሆነው በደረታቸው ተኝተው ይከታተሉ ነበር። ከስፖርቱ ጋር ወዳጅነት የጀመሩትም በዚያን ወቅት ነበር።
ጋሽ ገረመው በአንዋር መስጊድ ቢያጆ ተራ ብስክሌት እያከራዩ የሚያለማምዱ ልጆች ጋር በሰባት ዓመታቸው ግንኙነት ጀመሩ። አምስት እና አስር ሳንቲም ከቤተሰቦቻቸው እየወሰዱ በመክፈል ልምምዳቸውን አጧጧፉት። ቁመታቸው ገና ቢሆንም እግራቸውን በፔዳሉ መሀከል እያሾለኩ ቆመው በመጋለብ ተለማመዱ። በዘጠኝ ዓመታቸው የብስክሌቱ ኮርቻ ላይ መቀመጥ ቻሉ። እድሜያቸው እየጨመረ ሲሄድ ግን ከብስክሌቱ ጋር ግንኙነታቸው እየጠነከረ መጣ።
ጋሽ ገረመው ለቤተሰቦቻቸው አስራ አንደኛ ልጅ ናቸው። ሆኖም እናታቸው ወይዘሮ ቶላ ኢጀሬ ለእርሳቸው የተለየ ፍቅር ነበራቸው። በኮኮበ ፅባህ ትምህርት ቤት በእግራቸው እየተመላለሱ ይማሩ ስለነበርም ለልጃቸው ብስክሌት በ30 ብር ገዝተው ለመስጠት አላመነቱም ነበር። የግል ብስክሌት ገና በልጅነታቸው በእጃቸው በማስገባት ከቤት ወደ ትምህርት ቤት፤ ከትምህርት ቤት ወደ ቤት ጓደኞቻቸውን እያፈናጠጡ (ከኋላ እየጫኑ) ይመላለሱ ጀመር። ይሄ ደግሞ የብስከሌት የመንዳት ብቃታቸውን እና ጥንካሬያቸውን እየጨመረው መጣ።
ጊዜው 1943 ዓ.ም ነው። በአካባቢያቸው የታዳጊዎች እና ወጣቶች የብስክሌት ውድድሮች ይካሄዱ ነበር። ታዲያ የያኔው ታዳጊ ጋሽ ገረመው በዚህ ውድድር ላይ በመሳተፍ ድል ማድረግን አሀዱ አሉ። ለተራ የትራንስፖርት አገልግሎት በሚጠቀሙባት ብስክሌት ጓደኞቻቸውን ከኋላ አስከትለው ውድድሩን ሰባተኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቀቁ። 70 የሚደርሱ ተወዳዳሪዎች ተሳታፊ ነበሩ። በጊዜው ለርሳቸው ጥሩ ውጤት ቢሆንም እንዴት አንደኛ መውጣት አልችልም? የሚል ቁጭት ውስጥ ከቷቸው ነበር። ጓደኞቻቸውን እያፈናጠጡ የጀመሩት የሳይክል ስፖርት በውድድሮችም እየተገነባ ከጊዜ ወደ ጊዜ የስፖርት ተክለ ሰውነታቸው እና ጡንቻቸው እየፈረጠመ መጣ። ከተራ ፍቅር ቅልጥ ወዳለው የብስክሌት ሱስ ውስጥ ተንደርድረው ገቡ።
ጊዜው 1945 ዓ.ም። ጋሽ ገረመው እግሮቻቸው ደንበኛ የብስክሌት ሞተር ሆነዋል ድካም የሚባል ነገር አይታይባቸውም። ትምህርታቸውን እየተማሩ አንድ ውድድር ላይ ተካፈሉ። መነሻ እና መድረሻው አሮጌው ፖስታ ቤት የነበረውን አስራ አምስት ዙር ሁሉንም ተወዳዳሪዎች (ሁለተኛ የወጣውንም ጭምር) በመደረብ በድል አጠናቀቁ። አንድ እና ሁለት ተጨማሪ ልጆችን በብስከሌታቸው ላይ በመደረብ ትምህርት ቤት የሚመላለሱት ሰው ብቻቸውን ውድድር ላይ ሲቀርቡ ሁሉም ነገር ቀሏቸው ነበር። ውድድሩን በበላይነት በማጠናቀቃቸው 25 ብር እና እሽግ ብስኩቶችን ተሸለሙ። ሽልማታቸውን ይዘው ወደ ቤታቸው ሲገቡ እናታቸው የማሪያም ፀበል ፀዲቅ ከጎረቤቶቻቸው ጋር እየቀመሱ ነበር። ብስኩቱ ለማህበርተኛው ታደለ። እናታቸው «ልጄ አሸንፎ መጣ እንኳን ደስ አላችሁ» አሉ ማህበርተኞቹም የምርቃት መዓት አዥጎደጎዱ። ሌላ ተጨማሪ ድል።
ውድድሩን ኤርትራ ውስጥ ያደገው የያኔው ሲዳሞ ተወላጅ ፈረደ ካሳ ፣ ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ እንዲሁም አንድ ሌላ ኤርትራዊ በጋራ በመሆን ነበር እንዲጀመር ያደረጉት። ፈረደ በጊዜው የብስክሌት መካኒክ እና እውቅ ባለሙያ ነበር። እያደር ግን ክለቦች መቋቋም እና ብስክሌት ስፖርት ፈር እየያዘ መምጣት ጀምሮ ነበር። ለገሀር ፣መቻል፣ የምድር ጦር እንዲሁም አውራ ጎዳናን የመሳሰሉ ክለቦችም ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል። ጋሽ ገረመው በዚህ አይነት ሁኔታ ለሁለተኛ ጊዜ በተዘጋጀው ውድድር ላይ በድጋሚ ከአስራ አምስት ቀን በኋላ አሸናፊ ሆኑ። የ50 ብር እና የብስክሌት ጎማ እንዲሁም አንድ ቪኖ ተሸለሙ። ድልን ገና በልጅነታቸው የጀመሩት ጋሽ ገረመው በግዜው በነበሩ ክለቦች ዓይን ማረፊያ ሆኑ። በግል ስለሚወዳደሩም አድራሻቸው ጠፍቷቸው ብዙ ባከኑ። አንድ ወቅት ላይ ግን ያልተጠበቀ አጋጣሚ ተፈጠረ።
ያልተጠበቀው ስምምነት
ውድድሮችን በአዲስ አበባ በማዘጋጀት ይታወቃል። የብስክሌት አባት ነው ይሉታል ጋሽ ገረመው። ጊዜው በ1940ዎቹ ነው። የወልዎል ብስክሌት ክለብ የያኔውን ጠንካራ ብስክሌተኛ ለማድረግ አጥብቆ ይፈልጋል። ሁለተኛው ድላቸውን ባጣጣሙ ማግስት ሰኞ ዕለት ትምህርት ቤት አቶ ፈረደ «ቮልሲክ» የምትባል ታዋቂ የመወዳደሪያ ብስክሌት ይዘው በቀበና ትምህርት ቤት ከተፍ አሉ። ጋሽ ገረመው ከጓደኞቻቸው ጋር ነበሩ። «ገ ገረመው ይሄ ብስክሌት ያንተ ነው ያዝ። አሁን ለኛ ክለብ ትወዳደራለህ እናስፈርምሀልን» አሏቸው። ያልተጠበቀ ንግግር ነበር። በዚያ ላይ አዲስ ብስክሌት ሰጧቸው። በውስጣቸው ግርታ ተፈጠረ። እናታቸውን ይወዳሉ። ቃላቸውን ይጠብቃሉ። በዚህ ክለብ ቢሳተፉ ሊቆጧቸው ይችላል። ስለዚህ ችግሩን ለአቶ ፈረደ አጫወቷቸው። እርሳቸው ከእናታቸው ጋር እንደሚነጋገሩ እና እንደሚያስፈቅዱላቸው አሳምነው አዲሱን ብስክሌት ሰጧቸው። እየበረሩ ወደ ቤታቸው ተመለሱ።
አቶ ፈረደ ከእናታቸው ጋር ተነጋግረው አስፈቀዱ። የሚወዷቸው እናታቸው ትምህር ታቸውን ሳይቦዝኑ ከተከታተሉ በብስክሌቱም ቢሳተፉ ቅር እንደማይላቸው ገለፁ። አቶ ፈረደም በዚህ ተስማምተው የመጀመሪያውን ክለባቸውን አስተዋወቋቸው። አዲስ ብስራት፤ ሌላኛው የህይወት መንገድ ነበር። ለጋሽ ገረመው በእርግጥም ከብስክሌት ስፖርት እንደማይለዩ ማረጋገጫ ነበር። እናታቸው የመጀመሪያውን ብስክሌት በመግዛት ፈር የቀደዱ ናቸው። ባለውለታ።
አሁን እድሜያቸው15 ዓመት ሞልቷል። ገና ታዳጊ ናቸው። ወደ ወልወል ክለብ ተቀላቅለዋል። አራት እና አምስት ውድድሮችን አድርገው ጠንካራ በመሆናቸው ከታዳጊዎቹ ተነጥለው ወደ ወጣት ተወዳዳሪዎች ጋር ተቀላቀሉ። በየውድድሩ ላይ ትልቅ ፈተና ይሆኑባቸውም ጀመር። የመጀመሪያው ውድድር ላይ 13ተኛ፤ በሁለተኛው 4ተኛ፤ በሦስተኛው ደግሞ አንደኛ ደረጃን በመያዝ በፍጥነት ከወጣቶቹ ጋር ፉክክር ውስጥ ገብተው ድል ማድረግ ጀመሩ። አሁን እርሳቸውን ማቆም ከባድ ነው። በክለቡ ቴክኒካል እውቀቶችን እና ሳይንሳዊ የብስክሌት ታክቲኮችን ለመዱ። ይህ ደግሞ ተስፈንጣሪ እና ፈጣን ተወዳዳሪነታቸውን አስመሰከረላቸው። ከባድ በሆነው ቁልቁለት ላይ እንኳን ከተፎካካሪዎቻቸው አፈትልከው መውጣት ቻሉ። ዳገትን ደግሞ ንብረታቸው አደረጉት።
ጋሽ ገረመው ከ1945 እስከ 1955ዓ.ም ድረስ በኢትዮጵያ ሻምፒዮና እና በዓለም የኦሎምፒክ ታሪክ ላይ ታሪክ የሰሩበት ዘመን ነው። በ1946 ከጠንካራ ኤርትራዊያን ጋር በኢትዮጵያ ሻምፒዮና ሆለታ ደርሶ መልስ 20 ዙር ውድድር ላይ 11 ዙር ታዋቂና ጠንካራ ተወዳዳሪዎችን በመደረብ ጣፋጭ ድል አስመዘገቡ። ጃንሆይ በተገኙበት በዚህ ውድድር ልዑል ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ ለጋሽ ገረሞ በልዩ ብቃታቸው ተማርከው የወርቅ ሰዓታቸውን ከእጃቸው በማውለቅ ሸልመ ዋቸዋል።
ሜልበርን የመጀመሪያው
የኦሎምፒክ ተሳትፎ
በአገር ውስጥ ጋሽ ገረመውን ማቆም ከባድ ነው። በብስክሌት ስፖርት ታዋቂ የነበሩትን ኤርትራዊያንን ሳይቀር በማንበርከክ በርካታ ድሎችን ተጎናፅፈዋል። አሁን አዲስ ታሪክ የሚያስመ ዘግቡበት ወቅት ነው። ለዚህ ደግሞ አንድ አጋጣሚ ተፈጥሯል። በጊዜው ዓለም ላይ ስፖርቱ ተወዳጅነቱ ከፍተኛ ነበር። የኦሎምፒክ ስፖርት ላይ ደግሞ በቀዳሚነት ተካቶ ጠንካራ ተወዳዳሪዎችን ያፎካክር ነበር። ኢትዮጵያውያን የስፖርቱ ወዳዶች ደግሞ ጋሽ ገረመው በዚህ ውድድር ላይ ቢሳተፉ አሸናፊ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ግምታቸውን ያስቀምጡ ነበር። ለእርሳቸ ውም ተሳታፊ እንዲሆኑ ግፊት ያደርጉላቸው ጀመር። «እንኳን ዘንቦብሽ...» እንደሚባለው የአገሬ ብሂል እርሳቸውም በዚህ መድረክ ላይ ተሳትፈው ፈር ቀዳጅ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ለመሆን ትልቅ ፍላጎት አደረባቸው። ከዚያስ ምን ተፈጥሮ ይሆን?
ጋሽ ገረመው ከንጉስ ከቀዳማዊ ሃይለ ሥላሴ እጅ በስፖርቱ አሸናፊ በመሆናቸው ሁለት ዋንጫዎችን ተሸልመዋል። ይሄ ደግሞ በጃንሆይ እንዲታወቁ ዕድሉን አመቻችቶላቸዋል። በመሆኑም በአውስትራሊያው ሜልቦርን የኦሎምፒክ ውድድር ተሳታፊ ሆነው ታሪክ ለመስራት ለሚያቀርቡት የድጋፍ ጥያቄ ቀና መልስ ሊሰጧቸው እንደሚችሉ አልተጠራጠሩም። ስለዚህ ደብዳቤ ለንጉሱ ለመፃፍ ተነሱ። «በአገሬ ለበርካታ ዓመታት የብስክሌት ሻምፒዮና ሆኛለሁ። በሜልቦርን በሚካሄደው ኦሎምፒክ ላይ በዚሁ ስፖርት ተሳታፊ ብሆን ለአገሬ ጥሩ ስም አስገኛለሁ» በማለት በራሳቸው የእጅ ፅሁፍ ጥያቄያቸውን አቀረቡ።
ጃንሆይ እሁድ እሁድ ወደ ደብረዘይት ያቀናሉ። ጋሽ ገረሞ ደብዳቤውን በአካል ለጃንሆይ ለማቅረብ ፈልገዋል። በአራተኛ ክፍለጦር መሿለኪያ በሚባል አካባቢ ነበር ንጉሱ ወደ ደብረዘይት የሚያልፉት። ሦስት እሁዶችን በዚህ አካባቢ ጥያቄውን ለማቅረብ መጠባበቅ ጀመሩ። በአራተኛው ተሳካላቸው። በብስክሌታቸው ላይ ሙሉ ትጥቃቸውን እንደለበሱ፤ ደብዳቤያቸውን ይዘው ወደ ጃነሆይ መኪና ተጠጉ። በንፋስ ስልክ አድርገው አቃቂ አብረዋቸው በብሰክሌት ተከተሏቸው። ደብዳቤያቸውን ከኪሳቸው በማውጣት ከጃንሆይ መኪና ትይዩ በመሆን ጥያቄያቸውን ሲያቀርቡ ንጉሱ ትእዛዝ በመስጠት አስቆሙ።
ጄኔራል መኮንን ደነቀ የእልፍኝ አስከልካይ ፅህፈት ቤት ሹም ጋሽ ገረመውን ወደ ጃንሆይ ይዘዋቸው ቀረቡ። እርሳቸውም «ከዓለም መወዳደር እፈልጋለሁ» ሲሉ በአውስትራሊያ ሜልቦርን ኢትዮጵያ ተሳትፎ እንዲኖራት ድጋፍ እንዲደረግ ጥያቄ አቀረቡ። ጃንሆይም «ከዓለም መወዳደር እንደምችል በምን አወቅክ» የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡላቸው በሰዓት 42 ኪሎ ሜትር እንደሚፈጥኑ መተማመኛ ሰጧቸው። በጊዜው የዓለም ፈጣን ብስክሌተኞች ሰዓትም ተመሳሳይ ነበር። ጃንሆይ ይህን ሲያውቁ «ማለፊያ» በማለት ለማክሰኞ በቤተ መንግሥት ቀጠሮ ሰጧቸው። ይህ ወቅት ለርሳቸው የፈንጠዝያ እና የደስታ ሲቃ ያስተናገዱበት የማይረሳ ጊዜ ነበር።
በቀጠሮው መሰረት ማክሰኞ በቤተ መንግሥት ተገኙ። ሙሉ ልብሳቸውን ግጥም አድርገዋል። በጊዜው ታዋቂ ስፖርተኛ ስለነበሩ በቤተ መንግሥት ሲገኙ እልፍኝ አስከልካዩ ቅድሚያ እንዲሰጧቸው አደረጉ። ከጃንሆይ ጋር በነበራቸው ቆይታ ወደ ደብረዘይት ሲሄዱ ያደረጉትን ቆይታ በድጋሚ በማንሳት የኦሎምፒክ ተሳትፎው እንዲፈቀድላቸው ጥያቄ አቀረቡ። ጃንሆይ ፍቃዳቸውን ሰጧቸው። በሚያስፈልገው ሁሉ ትብብር እንዲደረግላቸው ትእዛዝ አስተላለፉ። የደስታ ሲቃ። የሀሴት መቅበዝበዝ በጋሽ ገረመው ላይ ይስተዋል ነበር። ጊዜ ማጥፋት አላስፈለጋቸውም ከአጋሮቻቸው ጋር ተሳትፎውን እውን ለማድረግ ሩጫውን ተያያዙት። አዲስ የታሪክ ዶሴ ኢትዮጵያ በሜልቦርን ኦሎምፒክ አንድ ብላ ከፈተች። የፊት አውራሪነቱን ሚና ደግሞ ጋሽ ገረመው ተረከቡ።
በጊዜው ተሳትፎውን ለማድረግ ፈተና የነበረው በአገሪቷ በሁሉም ስፖርቶች ላይ ፌዴሬሽኖች እና የተጠናከሩ ክለቦች አለመኖራቸው ነበር። በኦሎምፒክ ላይ ተሳታፊ ለመሆን የግዴታ አንድ አገር አምስት የተለያዩ የስፖርት ፌዴሬሽኖች ሊኖሯት እና ልታሳትፍ ይገባ ነበር። ነገሮች ትንሽ ቢወሳሰቡም በግሪካዊው ሙሴ ኤድዋርዶ ቢልቢሪስ ዓለም አቀፍ የውድድር ልምድ፤ በንጉሴ ሮባ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፀሃፊ፤ እስጢፋኖስ መንግስቱ የቦክስ ፌዴሬሽን ፀሀፊ እንዲሁም ጋሽ ገረመው ደንቦባ የብስክሌት ፌዴሬሽን ፀሀፊ በማድረግ በፍጥነት አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ አሟልቶ ኢትዮጵያ በኦሎምፒኩ እንድትሳተፍ ተደረገ። ይህ ሁሉ የሆነው ጋሽ ገረመው «በኦሎምፒክ ልሳተፍ» በማለት ባስገቡት ደብዳቤ መሰረት ነበር።
ያልተጠበቀው ክስተት
የብስክሌት፣ የቦክስ እንዲሁም የአትሌቲክስ ስፖርት ቡድን በ1948 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አውስትራሊያ አቀና። ሰባት ቀን ሰባት ሌሊት የፈጀ ከባድ ጉዞ ነበር። ሜልቦርን እንደደረሱም በሆቴል ላይ መጉላላት ደርሶባቸዋል። ማረፊያ ሆቴላቸው ምቹ አልነበረም። በኢትዮጵያ የሰሩት ልምምድ መና ቀርቷል። የአትሌቲክስ ተወዳዳሪዎቹ ባሻዬ ፈለቀ፣ ገብሬ ብርቄ፣ ማሞ ወልዴ ፣መራዊ ገብሩ፣ንጉሴ ሮባ በአስር ሺ፣በመቶ እና በስምንት መቶ እርቀት በኦሎምፒኩ ላይ ተሳታፊ ነበሩ። ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ ስፖርት ለመጀመሪያ ጊዜ እንድትሳተፍ ፈር የቀደደው የጋሽ ገረመው ቡድን ደግሞ መንግስቱ ንጉሴ፣ ፀሀይ ባህታ፣ መስፍን ተስፋዬ የያዘ ነበር። በውድድሩ ወቅት እንደ ቡድን ከዓለም ዘጠነኛ ደረጃን ይዛ እንድታጠናቅቅ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። ጋሽ ገረመውም በግል ከአገራቸው ቀዳሚ በመሆን የ24ተኛ ደረጃን ይዘው ውድድሩን አጠናቀዋል።
በዓለም ታሪክ በኦሎምፒክ ስፖርት ኢትዮጵያ በጋሽ ገረመው ጥረት የመጀመሪያው ጥቁር ተሳታፊ እና አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ቻለች። በታሪክ ዶሴ ላይም ከአፍሪካውያን ቀዳሚ ሆነች። ባለውለታው ጋሽ ገረመው እንዲህ ይላሉ «አፍሪካውያን በሙሉ ጨርሶ ነፃነታቸውን ባልተጎናፀፉበት ወቅት ኢትዮጵያ የዓለም ኦሎምፒክ ተሳታፊ ሆናለች» ከዚህ በላይ ጎልቶ የሚታይ የኮራ ስብእና ከየት ይገኛል። ለዚህ የደመቀ ታሪክ መሰራት ደግሞ ጋሽ ገረመው የፊት መስመሩን ይይዛሉ። እርሳቸውም በኦሎምፒክ ታሪክ በሳይክል ውድድር ላይ የተሳተፈ የመጀመሪያው ጥቁር ተወዳዳሪ በመሆን አኩሪ ገድል ሰሩ
ሮም ኦሎምፒክ አሳዛኙ አጋጣሚ
ጊዜው 1962 ነበር። የሮም ኦሎምፒክ ተሳትፎ። አሁን ፈር ተቀዷል። በድጋሚ ኢትዮጵያን ለመወከል ጋሽ ገረመው፣ አድማሱ መርጊያ፣ አላዛር ክፍሎም እና ጆቫኒ ማሶላ ሮም ላይ ተገኝተዋል። ውድድሩ ተጀምሯል። በመጀመሪያው የኦሎምፒክ ተሳትፎ ጥሩ ብቃት ያሳዩት ጋሽ ገረመው በዚህኛው ውድድር ከፍተኛ የማሸነፍ እድልን ይዘዋል። አጠቃላይ ውድድሩ 11 ዙሮች ነበሩት። ከመጀመሪያው ጀምሮ ተስፈንጣሪው ጋሽ ገረመው መሪ ሆኑ። አንደኛው፣ ሁለተኛው፣ ሶስተኛው ዙር። አሁንም እየመሩ ነው። እንዴት ነው ነገሩ። ሰባተኛው ዙር። አሁንም ጋሽ ገረመው ከፊት ናቸው። ስምንተኛው ዙር ተመሳሳይ ነበር። ዘጠነኛው ዙር ላይ ግን ቀዳሚ የማሸነፍ እድል የተሰጣቸው ኢትዮጵያዊ ያልተጠበቀ አደጋ አጋጠማቸው። ከብስክሌታቸው ላይ ወደቁ። መገፋፋት ነበር። ነገርዬው ሳይሳካ ቀረ። ሆኖም ለ9 ዙር የሮሙን የብስክሌት ውድድር በመምራት ሰፊ ሙገሳ እና ክብርን በማግኘት በድጋሚ ታሪክ ሰሩ። ጋሽ ገረመው በድንገተኛው አጋጣሚ ከውድድሩ በጉዳት ቢወጡም፤ አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ ሮምን ወሮ የጓደኛውን ሀዘን በደስታ አካካሰው። ሌላ ታሪክ በሮም አደባባይ ተሰራ።
ጋሽ ገረመው በብስክሌት ስፖርት የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ። በቶኪዮ ኦሎምፒክ ላይም የብስክሌቱን ልኡካን ቡድን በአሰልጣኝነት በመምራት አገልግለዋል። ከዚያም በኋላ ለረጅም ዓመታት በአሰልጣኝነት ለአገር ውለታ ሰርተዋል። በምላሹ ግን ለአገራቸው ክብር እግራቸው ተሰብሮ ብረት ሲያጠልቁ «አባ ከና» ያላቸው አካል የለም።
በመጨረሻም እንመሰጋገን...እንወቃቀስ
ከግል ጥረቶች በቀር እርሳቸውን ለማክበር እና ለማስታወስ እጃቸውን የያዛቸው አካላት ምን አጋጥሟቸው ይሆን? እርሳቸው ግን «አረ የኔስ ይቅር» ከኔ በተሻለ ለኢትዮጵያ ስፖርት ዕድገት ህይወታቸውን በመክፈል ፈር ለመጣል የታገሉት እነ ክቡር ይድነቃቸው ተሰማስ ቀጨኔ በር ላይ ተጥለው አስታዋሽ አጥተዋል» ይላሉ። አዲስ ዘመን ስፖርትም ይህን ትጠይቃለች «ይህ አይነት ቸልተኝነት እውነት ተገቢ ነው?»
ጋሽ ገረመው አሁንም ለአገሬ ውለታዋን ከፍዬ አልጨረስኩም ይላሉ። ባላቸው አቅም እና ልምድ አሁንም ድረስ የማማከር ሥራ መሥራት እንደሚችሉም ይናገራሉ። በግል ትግል የብስክሌት ስፖርትን ለማሳደግ ጥረት የሚያደርጉትን የብስክሌት የበላይ ጠባቂ አቶ ነብዩ ሳሙኤል ፈረንጅን እና የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንትንም ያመሰግናሉ። የዘኮሊና ኮንስትራክሽን እና የአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን ወደ ከአዲስ አበባ መነሻውን ያደረገ ቱር በማዘጋጀት እኚህን አንጋፋ ሰው ለማስታወስ ጥረት አድርገዋል። የሰሜን አሜሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም እንዲሁ በተመሳሳይ እውቅና ሰጥቷቸዋል። ለእርሳቸው ግን ይሄ ብቻ በቂ አይደለም። ምክንያቱ ጀግና በዚህ ብቻ አይከበርም። የኦሎምፒክ ኮሚቴና የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት የት ነው ያሉት? ነው «በእጅ የያዙት ወርቅ...» ሆኖባቸው ይሆን? ሰላም!

ዳግም ከበደ

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።