ለስፖርቱ ህመም መድኃኒት Featured

12 Jun 2018

 

የመከባበርና ወንድማማችነት ምሳሌ የሆነው እግር ኳስ በአሁኑ ወቅት ይህን መገለጫውን ተነጥቋል። ጨዋነት ተጓድሏል። የሜዳ ውስጥ ሁከትና ብጥብጥ ተለምዷል። በዚህም ምክንያት ደጋፊዎች፣ ተጫዋቾች፣ አሠልጣኞች፣ ዳኞች እንዲሁም ሌሎች ለአካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ተዳርገዋል።
በተለይ በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በርካታ የሁከትና ብጥበጥ ክስተቶች ታይተዋል። ችግሩ እያደር በመጠንም ሆነ በስፋት እየጨመረ መምጣት በርካታ የስፖርቱ አፍቃሪዎች ስጋት እንዲያድርባቸው እያደረገ ይገኛል፡፡ችግሩ የጎላበትን ምክንያትና መከላከያ ዘዴውን አስመልክቶም ምሁራንና ባለድርሻ አካላት ዓለም አቀፍ ተሞክሮን በመቃኘት እና የባለሙያዎችን ሀሳብ በማካተት የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ማቅረብ ጀምረዋል።
የወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ አገር አቀፍ የስፖርት ሳይንስ ጥናትና ምርምር ጉባኤ በቅርቡ ለአምስተኛ ጊዜ በተካሄደበት ወቅትም ለስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል መንስኤው ምን እንደሆነ እንዲሁም መከላከያ ዘዴውስ ምን መሆን ይኖርበታል የሚል ጥናት ቀርቦ ነበር። በመድረኩ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሳይኮሎጂ መምህሩ አቶ ተሾመ አጀበው «በስፖርት ውስጥ የሁከት መንስኤዎችና መከላከያ ዘዴዎች» በሚል ርዕስ ጥናት አቅርበዋል። አዲስ ዘመንም ከጥናቱ አቅራቢ አቶ ተሾመ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ በሚከተለው መልኩ አቅርቦታል።
አዲስ ዘመን፡- በስፖርት ውስጥ የሚፈጠረው ሁከት መንስኤው ምንድን ነው ?
አቶ ተሾመ፡- በስፖርት ውስጥ ሁከት ተፈጠረ የሚባለው ከስፖርት ህግና ደንቦች በተፃረረ መልኩ የፀብ አጫሪነት ባህሪያት ሲታዩና ድርጊቶች ሲፈጸሙ ነው። ሁከቱ ከጨዋታው ደንብና ውድድር ግቦች ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነት የሌለው ጉዳት ወይንም ህመም ለማድረስ ታስቦ የሚፈፀም ሲሆን፣ አብዛኛውን ጊዜም አካላዊ ንክኪ ባላቸው የውድድር ስፖርት አይነቶች በእግር ኳስ በቅርጫት ኳስና በራግቢ ጨዋታዎች ላይ ይከሰታል።
ምንም እንኳን ሁከት ብዙውን ጊዜ ከተጫዋቾች የሚነሳ ቢሆንም፣ ሁከቱን ደጋፊዎች፣ አሠልጣኞች፣ የቡድን መሪዎች፣ መገናኛ ብዙኃንና ሌሎችም ይበልጥ እንዲባባስ የሚያደርጉበት ሁኔታ ይኖራል። ይህም ያልተገቡ ንግግሮች፤ ዜማዎች፤ ዛቻዎች ወይንም አካላዊ ጉዳት የማድረስ መልክ ሊኖረው ይችላል።
አዲስ ዘመን፡- ንድፈ ሃሳቦች ስለ ሁከት መንስኤዎች ምን ይላሉ?
አቶ ተሾመ፡- ይህ ጥያቄ ለእኔ ጥናት መነሻ በሆኑ ሶስት ነድፈ ሃሳቦች ላይ በመመስረት ሊመለስ ይቻላል።ንድፈ ሀሳቦቹ የሥነህይወት፤ የሥነ ልቦናዊና የማህበራዊ ትምህርት ንድፍ ሃሳቦች የሚባሉ ናቸው። እነዚህን ንድፈ ሃሳቦች መሰረት አድርገው ጥናት ያደረጉ የንድፈ ሃሳቦቹ ቀማሪዎች ለእያንዳንዳቸው ምሳሌ ያስቀምጣሉ።
በሥነህይወት ንድፈ ሃሳብ መሰረት የሁከት መንስኤ የፀብ አጫሪነት ተፈጥሮአዊ ባህሪ ሲሆን፣ በሥነልቦናዊ ንድፈ ሃሳብ ደግሞ ግብን ከማሳካት ጋር ተያይዞ የሚነሳ ብስጭት ወይንም ውጥረት ነው። በማህበራዊ ትምህርት ንድፈ ሃሳብ ደግሞ ፀብ አጫሪነት ወይንም ግጭት በማህበራዊ መስተጋብር ውስጥ በልምድና በትምህርት የሚገኝ ባህሪ መሆኑ ይታመናል።
አንድ በአንድ ለመመልከት፤ እንደ ተፈጥሮአዊ የፀብ አጫሪነት እሳቤ የሁከት መንስኤ የሰው ልጅ ተፈጥሮአዊ የፀብ አጫሪነት ባህሪ ነው። በብስጭት ፀብ አጫሪነት እሳቤ መሰረት ደግሞ ሁከት የሚከሰተው በብስጭት እና ጠበኝነት የተነሳ ነው።
የስፖርት ሁከት ክስተት ምንም እንኳን በግልፅ የፀበኝነት ውጤት ባይሆንም ሁልጊዜ ግን ከክስተቱ ጋር የሚያያዝ የተወሰነ የብስጭት ሁኔታ ቀድሞ እንደሚኖር ይገመታል። የብስጭት መኖር የጠብ አጫሪነት ድርጊቶችን ያስከትላል። የብስጭት ምንጮች ደግሞ ከጨዋታ፤ ከብቃት፤ ከአሠልጣኞች፤ ከተቃራኒ ቡድን ደጋፊዎች ጋር የተያያዙ ናቸው።
ከጨዋታ ጋር የተገናኙ የብስጭት ምንጮች በተጫዋቾች እምነት ጨዋታውን የሚመሩ ዳኞች የማይገባ ውሳኔ ሲያሳልፉ የሚከሰቱ ናቸው። ለአብነት አንድ ተጫዋች እያሳየ ያለውን ድርጊት ተከትሎ የማስጠንቀቂያ ካርድ እንዲሁም ለተቃራኒ ቡድኑም የቅጣት ምት ተሰጥቷቸው ግብ ሲቆጠር ተጫዋቾች ራሳቸውን ጥፋተኛ እንዲያደርጉና ጭንቀትና መደናገጥ ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋቸዋል። አሊያም ውሳኔው ያልተገባ ነው ብለው በማመን ሊበሳጩ ይችላሉ። እነዚህ የብስጭት ስሜቶች ተጫዋቾቹን ተረጋግተው እንዳይጫወቱና የጠብ አጫሪነት አሊያም ያልተገባ ድርጊት ውስጥ እንዲገቡ ሊያደርጓቸው ይችላሉ፡፡
ከዚህ በተጓዳኝ በጨዋታ ላይ የሚጠበቅ ብቃትን ማሳየት ካለመቻል ጋር ተያይዞ የጉዳት ጣልቃ ገብነት፤ የአሰልጣኞች አጨዋወት አመዳደብ፤ የደጋፊዎችና አሠልጣኞች የጩኸት ተቃውሞ ለብስጭት ለመደናገጥ፣ ለጭንቅትና ለተስፋ መቁረጥ መንስኤ ይሆናሉ።
በመሆኑም የስፖርት ውስጥ ሁከት ስፖርተኞች በአሠለጣጠን ሂደትና በጠብ አጫሪነት ላይ ባላቸው ግንዛቤ ይወሰናል። ይህ ማለት በስፖርት ውስጥ የሚፈፀም የኃይል ድርጊት በስፖርተኞች አዕምሮ ውስጥ በተፈጠሩ ስሜቶች ላይ የተመሰረተ ነው ማለት ነው። እነዚህ ስሜቶች በተለይ በአሰልጣኞች አማካኝነት የተፈጠሩ ናቸው።
ለምሳሌ አንድ አሠልጣኝ ከአሸናፊነት ውጪ ምንም ነገር ላይ አፅ ንኦኖት የማይሰጥ ከሆነ ተጫዋቾቹ ይህን ዓላማ መፈፀም በማይችሉበት ጊዜ የጭንቀትና የመረበሽ ስሜት ውስጥ ይገባሉ፤ በአግባቡ ችሎታቸውን እንዳይጠቀሙና ለሁከትና ብጥብጥ እንዲነሱ ያደርጋቸዋል። ስለሆነም በተጫዋቾች አዕምሮ ውስጥ የተፈጠረው የሥነ ልቦና ሁኔታ የስፖርቱን ሁከት ለመከላከል ወይንም እንዲከሰት ለማድረግ መስረታዊ ምክንያት ይሆናል።
እንደ ማህበራዊ ትምህርት ንድፈ ሃሳብ እሳቤ የሁከት መነሻ ባህሪያትና ድርጊት ከመማር የመጡ ናቸው። ሌሎች አርአያችን ያሏቸውን ሰዎች ድርጊትና ባህሪ በመመልከትና የሚያስከትለውን ቅጣትና የሚያስገኘውን ሽልማት በመገንዘብ ወደ ራሳቸው በማምጣት አዳዲስ ባህሪያትን ይማራሉ።
በዚህ ንድፈ ሃሳብ መሰረት ልምድ የማግኘት ተግባር ሽልማት ወይንም ማጠናከሪያና ተምሳሌቶ ችን በመኮረጅ ሂደቶች ላይ የተመሰረተ ነው።ሽልማቱም አሉታዊና አዎንታዊ ሊሆን ይችላል።አዎንታዊ ሽልማት ሲሆን ግልፅ ወይንም ግልፅ ያልሆኑ አድናቆት አሊያም ቁሳዊ የሽልማት መድረክ ይኖረዋል። አሉታዊ ሲሆን ደግሞ የተቃውሞ አለመስማማት የትችትና ቅጣት ገጽታ አለው።
በስፖርት ውስጥ ተጫዋቾች የሚያሳዩት ያልተገባ ግጭት ወይንም ሁከት ከተለያዩ የሽልማት ምንጮች ይነሳል። ይህም በሶስት ምድቦች ተከፍሎ ይታያል። አንደኛው ከስፖርተኛው ቀጥተኛ ምንጮች በተለይ አሰልጣኞች፣ የቡድን አጋሮችና ቤተሰብ ሲሆን፤ ሁለተኛው ከስፖርት አስተዳዳሪ አካላትና ከዳኞች የህግ አተገባበር ሶስተኛው ደግሞ ከማህበራዊ ምንጮች ማለትም ደጋፊዎች፤ መገናኛ ብዙኃንና ከአጠቃላይ የማህበረሰቡ አመለካከት ይመነጫል።
ከመጀመሪያው ምድብ የስፖርተኛው ቀጥተኛ ምንጮች በተለይ አሠልጣኞች በልምምድና ውድድር ማህበራዊ ሁኔታ ውስጥ ፀብ አጫሪነትን፤ ብስጭትና ግጭትን የሚያንፀባርቁበት ሁኔታ ያጋጥማል። በዚህም ተጫዋቾች ኃይል የተቀላቀለበት አጨዋወት እንዲከተሉ የሚያደርጉ እንዲሁም ጨዋታቸውን የሚያደንቁ ወይም ለጨዋታቸው የተለየ ዋጋ የሚሰጡ ከሆነ ተጫዋቾች ግጭት፤ ጠብ አጫሪነትና ሁከት ውስጥ ለመሳተፍ ማጠናከሪያ ምንጭ ያገኛሉ።
ሌላኛው ምድብ ለዘብተኛ የስፖርት አስተዳደር ነው። የስፖርተኞች የፀብ አጫሪነት እንዲጠናከር ምንጮች በመሆን የሚታወቁት የስፖርት አስተዳዳሪዎች፣ ዳኞች እና የሥነምግባር ኮሚቴዎች ጥብቅ ያልሆኑ፤ ወጥነት የጎደላቸው ሚዛናዊና ፍትሃዊ ያልሆኑ የቅጣት እርምጃዎች ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት ተጫዋቾች ለሚፈጽሙት ያልተገባ ድርጊት ማጠናክሪያ ይሆናሉ።
ተጫዋቾች በጥፋታቸው ልክ የማይቀጡ ከሆነ ተመሳሳይ ድርጊት እንዲፈፅሙ ምክንያት ይሆናቸዋል። እንደ ማህበራዊ ትምህርት ንድፈ ሃሳብ ደግሞ ጥብቅ ያልሆኑ የቅጣት ውሳኔዎች እና ውጤታማ ያልሆኑ የሥነ ሥርዓት ደንቦችና መመሪያዎች የችግሩ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው።
የማህበረሰብ ምንጭ የመጨረሻውና በሶስተኛ ምድብ የሚቀመጥ ነው። ለስፖርተኞች ያልተገቡ ድርጊቶች ማህበራዊ ማጠናከሪያ ምንጮች በዋናነት ተመልካቾችና መገናኛ ብዙኃን ናቸው። መገናኛ ብዙኃን በተመልካቾች ላይ ያልተገቡ ድርጊቶችን ሲመለከቱ ድርጊቱን ከማውገዝ ይልቅ ችላ ይላሉ፡፡በዚህ የተነሳም ሁከቱ የጨዋታው አካል እንዲሆን በማጠናከሪያነት ያገለግላሉ። መገናኛ ብዙኃን ሁከቶችን ከማውገዝ ይልቅ ድርጊቱን አጉልተው በማሳያነት ያቀርቡታል። አንዳንድ የሁከት ትዕይንቶችን ቀርፀው በተለያዩ ድህረ ገፆች ላይ በመጫን በተመልካች ብዛት ገቢ ለማግኘት ይገለገሉበታል። ይህም የችግሩን ጉዳት ይበልጥ እንዲያይል ያደርጋል።
አዲስ ዘመን፡- የተጫዋቾች የግጭት ፀብ አጫሪነት መንስኤዎች ምንድን ናቸው ?
አቶ ተሾመ፡-ለመጥፎ አገባብ ወይንም ‹‹ታክል›› አፀፋዊ ምላሽ መስጠት፣ በጨዋታ ወቅት ከመጠን በላይ ስሜታዊ መሆን፣ በዳኞች ደካማ ውሳኔ መበሳጨት፣ ብልጫ ለመውስድ ተጋጣሚን የሚጎዳ ችግር መፈጸም፣ የእፆች ተፅዕኖ፣ የመገናኛ ብዙኃን ጫናዎችና በሽንፈት ምክንያት የሚፈጠር ብስጭት ወይንም መደናገጥ፣ የተመልካች ጫና ግፊት፣ የተቃራኒ ቡድን ደጋፊዎች ጩኸትና ዝማሬ፣ የግለሰቦች፣ የቡድኖች እንዲሁም የአገራት የባላንጣነት ስሜት እንዲፈጠር ቀዳሚ ምክንያት ይሆናሉ።
አዲስ ዘመን፡- የተመልካቾች ፀብ አጫሪነት መንስኤዎች ምንድን ናቸው?
አቶ ተሾመ፡- ብዙውን ጊዜ ደጋፊዎች ወደ ሁከትና ብጥብጥ የሚገቡት ንኪኪ በሚበዛባቸው የስፖርት አይነቶች ላይ ነው። ከተመልካች ሁከት ጋር ተያይዞ አጥኚዎች ሶስት አጠቃላይ መንስኤዎችን ለይተዋል። እነርሱም ስፖርታዊ ውድድር ውስጥ የሚከሰቱ ድርጊቶች፤ ተመልካች ውድድሩን የሚመለከትበት ሁኔታና የብዙኃኑ እንቅስቃሴ እንዲሁም ውድድሩን ለማድረግ የታቀደበትና የተካሄደበት ታሪካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች ናቸው።
በስፖርታዊ ውድድር ውስጥ በተጫዋች፣ በአሠልጣኞችና በዳኞች የሚከናወኑ ድርጊቶች በተመልካች ግንዛቤና አመለካከት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ የሚያሳድሩ ከሆነ ተመልካቾች ወደ ሁከትና ግጭት እንዲገቡ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ። ተመልካቾች በውድድሩ ላይ የተጫዋቾችን ድርጊት እንደ ሁከት ከተገነዘቡት በጨዋታው ወቅትና ከጨዋታው በኋላ በሁከት ድርጊት የሚሳተፉበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል።
አንዳንድ ጥናቶች ደግሞ የተመልካቾች ግንዛቤና ድርጊት ከቡድኖችና ስፖርተኞች ጋር ባላቸው ትስስር አሊያም እውቅና መጠን ላይ የተመሰረተ ነው። ከቡድኖች ጋር በጣም የተሳሰሩ ደጋፊዎች የቡድኑን ብቃት ከራሳቸው ስሜትና ማንነት ጋር ያገናኛሉ። ይህ በራሱ ሁከት የማያስከትል ቢሆንም፣ ደጋፊዎች ቡድናቸውን የሚረዳ ከመሰላቸው አጋጣሚውን የሆነ ድርጊት እንዲያከናውኑ ሊጠቀሙበት በማሰብ እርምጃ ለመውሰድ ሊነሳሱ ይችላሉ።
ተመልካቾች ውድድሩን የሚመለከቱበት ሌላው ሁኔታ የብዙኃኑ እንቅስቃሴ ነው። የተመልካቾች መጠን፣ አቋቋምና አቀማመጥ፤ የዕድሜና የፆታ ስብስብ፣ ብሔረሰብ ውድድሩ ለተመልካቹ ያለው አስፈላጊነትና ትርጉም፤ በቡድኖች በደጋፊዎች መካከል ያለው የግንኙነት ታሪክ ለተመልካቾች የብሔራዊ ፣ የክልል የአካባቢና የቡድን ማንነት መገለጫ እስከ መሆን ይደርሳሉ፡፡
ፖሊስና የደህንነት ካሜራዎች እንዲሁም ተመልካቾችን ለመቆጣጣር ጥቅም ላይ የዋሉ የቁጥጥር ስልቶች፤ ተመልካቾች የወሰዱት የአልኮል መጠን፣ የውድድር ቦታ፤ ሌሎች በተመልካቾች ላይ ተጽእኖ የሚያሳድሩ ናቸው ፡፡
ለተመልካቾች ሁከትና ብጥብጥ ሶስተኛው መንስኤ ውድድሩን ለማድረግ የተያዘው እቅድ ፣ውድድሩ የሚካሄድበት ታሪካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጨባጭ ሁኔታ ነው። ማንኛውም የውድድር አይነት ምንም አይነት ማህበራዊ ሁኔታዎች በሌሉበት አይከሰትም። ተመልካቾች ውድድሩን ሲታደሙ የሚኖሩባቸው ማህበረሰቦች ባህሎች፣ ታሪኮች፣ ውዝግቦችና አስተሳሰቦች በስፍራው ይንጸባረቃሉ። በሌላ አባባል በሺዎች የሚቆጠሩ ተመልካቾች በስፖርታዊ ውድድሮች ላይ ሲታደሙ ድርጊታቸው ከስታዲያም ባሻጋር በብዙ ነገሮች ላይ ይመሰረታል ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- መንስኤዎቹን በዚህ መልኩ ከቃኘን መከላከያ ስልቶቹስ ምን ሊሆኑ ይችላሉ?
አቶ ተሾመ፡- በስፖርት ውድድር ወቅት የሚከሰት ሁከትን መከላከልን በተመለከተ የሚካሄዱ በርካታ ጥናቶች የተለያዩ ስልቶችን ይጠቁማሉ። በአብዛኞቹ ዘንድ ተቀባይነት ያገኙት ግን የሚከተሉት ናቸው።
አንደኛው ትምህርትና ሥልጠና ነው። ይህ ማለት የተለያዩ የፀብ አጫሪነት የመቆጣጠሪያ ስልቶችን በመጠቀም ተጫዋቾች ጭንቀትና ስሜትን መቆጣጠር እንዲችሉ ሥልጠና ሊሰጣቸው ይገባል። ተጫዋቾች ባህሪያቸው በሚመለከቷቸው ሰዎች እንደሚቀዳ መገንዘብም አለባቸው።
የግብረ ገብ እድገትን የሚያበረታቱ ስልቶች በስፖርት ላይ የተሻሻሉ ወይም የተስተካከሉ ባህሪያትን ይፈጥራሉ። ተጫዋቾች በሜዳ ላይ ሲሆኑ አዎንታዊ አመለካከቶችን እንዲያሳዩ አሠልጣኞችና አስተማሪዎች ከስፖርቱ ጋር የሚዛመዱ አዎንታዊ እሴቶችን ማስተማር አለባቸው። ይህም ተመልካቹም ተመሳሳይ አመለካ ከት እንዲዳብር ሊያደርግ ይችላል። በመሆኑም በተጫዋቾች መካከል አዎንታዊ እሴቶችን ማስተዋ ወቅ አዎንታዊ አመለካከትን ስለሚያሳድግ በስፖ ርት ውስጥ ሁከትና ግጭትን ማስቀረት ያስችላል።
የስፖርታዊ ጨዋነት ዘመቻ ፕሮግራሞችን ማካሄድም ክስተቱን ለመከላከል ብሎም ለማስቆም የጎላ ፋይዳ አለው። ለአብነት የእንግዳ ቡድን አቀባባል ፕሮግራሞች ወዳጅነት፤ አንድነትና መልካምነትን የሚሰብኩ ማስታወቂያዎች፣ ባነሮችና ቢልቦርዶች መጠቀምን የስፖርታዊ ጨዋነት የዘመቻ አካል ማድረግ ይቻላል። እንዲሁም በየዓመቱ የስፖርታዊ ጨዋነትን ያሳዩ ቡድኖች፣ ተጫዋቾችና ደጋፊዎች አሠልጣኞች እውቅና መስጠት ፋይዳው ግዙፍ ነው።
አንዳንድ አሠልጣኞች ተጫዋች በራሳቸው እንዲደሰቱ የግል ክህሎታቸውን በስፖርቱ ውስጥ እንዲያዳብሩ ከመፈለግ ይልቅ በውድድሮች አሸናፊነት ላይ ብቻ ለማረጋገጥ ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላል። አሠልጣኞች ከዚህ መታቀብ ይኖርባቸዋል፡፡ ስፖርትን ትክክለኛ ገፅታ በተግባር ማስቀመጥና አሠልጣኞችም አሸናፊነትን ለማግኘት ሲባል ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈል በሚል ከሚፈጽሙት ተግባር እንዲቆጠቡ ማድረግ ያስፈልጋል ።
የስፖርቱ አስተዳዳሪ አካላት ሁከት የሚፈጥሩ ተጫዋቾችና ደጋፊዎች ላይ ጥብቅ ቅጣት ማስተላላፍ ይኖርባቸዋል። የሁከት ክስተቶችን ወደኋላ ተመልሰው በመመርመር በአጥፊዎች ላይ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ አለባቸው። ይህን ማድረግ ተመሳሳይ ድርጊት እንዳይከሰት ያስችላል።
ይሁንና ቅጣት ወጥነት ከሌለው ወዲያው የማይተገበርና በይቅርታ የሚነሳ ከሆነ አስተማሪነቱ ይቀርና መጥፎ ድርጊቶች የበለጠ እንዲስፋፉ የማጠናከሪያ ምክንያት /ሽልማት / ሆኖ ሊያገለግል ይችላል። ቅጣት ወጥነት ባለው መልኩ ወዲያው ጥፋቱ እንደተፈፀመ ሲተገበር በስፖርቱ ውስጥ ሁከት በድጋሚ እንዳይፈጠር ማድረግ ያስችላል።
ደጋፊዎች የሚፈጥሩትን ሁከት ለመከላከል በቅድሚያ ማስተማር ያስፈልጋል። የማስተማሩ ተግባርም በቡድንና በደጋፊ ማህበር አመራሮች ሊከወን ይችላል። የመገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም ስለ ደጋፊዎች ሚና እና ኃላፊነት እንዲሁም ስለ ጨዋታ ህግጋት ተመሳሳይ ሥልጠና መስጠት ይቻላል።
አንዳንድ ጊዜ አብዛኞቹ ደጋፊዎች የጨዋታ ህግጋቶችን በደንብ ካለማወቅ የተነሳ ዳኞች የሚያሳልፉትን ውሳኔ ሲቃወሙና ይህንም በጩኸት ሲገልፁ ይስተዋላል። ከዚህ በተጨማሪ የቡድን አመራሮችና የደጋፊ ማህበራት ሁከትና ነውጥ የሚፈጥሩትን በመለየት ቅጣት ማስተላላፍ ቢችሉ ሌሎች ከዚህ ተግባር እንዲቆጠቡ ማድረግ ይቻላል።
የዳኝነት ብቃትን ማሻሻል የግድ ነው። ግጭትና ሁከትን ለማስወገድ ውጤታማ ዳኝነት አንዱ ስልት ነው። በርካታ ጥሩ ዳኞች ግጭት የሚያስከትል ሁኔታ ከመከሰቱ በፊት ቀድመው ስለሚገነዘቡ ሊከተል የሚችል አደጋን መቀነስና ማምከን ይቻላል። ስለሆነም ለዳኞች አጫጭርና የረጅም ጊዜ ሥልጠናዎችን በመስጠት ብቃታቸውን በማጎልበት ከውሳኔ ቅሬታዎች ጋር ተይይዞ ሊፈጠር የሚችል ሁከትን መከላከል ይቻላል።
ህግ ማስክበርና የደህንነት ካሜራዎች በተመልካች ሁከት እንዳይቀሰቀስ እገዛ ሊያደርጉ ይችላሉ። ሁከት ፈጣሪዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው በወንጀል እንዲጠየቁ የሚያደርግ ህግ ማውጣት ያስፈልጋል። ለምሳሌ የእንግሊዝ ፖሊስ ችግር ፈጣሪ ተብለው የተለዩትን በቁጥጥር ስር እንዲውሉ የሚያስችል ደንብ /the football disorder act/ ሥራ አውጥቷል። ይህ ህግ ሁከት ፈጣሪዎችና ነውጠኞች ወደ ውጭ እንዳይጓዙ ጭምር ክልከላ ያደርጋል።
የመገናኛ ብዙኃንም አዎንታዊ እና አሉታዊ የሁከት ድርጊቶችን ተዓማኒና ሚዛናዊ በሆነ መንገድ የመዘገብ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በተለይ በትምህርትና ሥልጠና ስፖርታዊ ጨዋነትን በተግባር ማሳየት፤ መልካም ተምሳሌቶችን ማወደስና እውቅና እንዲያገኙ ማድረግ፣ መልካም ምግባርን የሚያበረታቱ እሴቶችን በስፖርቱ ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ማካተት፤ የወላጆች ተሳትፎንና የደጋፊዎች ቅጣትን ተግባራዊ ማድረግ ጠቀሜታቸው ጉልህ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።
ከሁሉም በላይ የስፖርታዊ ጨዋነት ችግርን ለመፍታት እና ችግሩ በድጋሚ እንዳይከሰት ለማድረግ በስፖርቱ ባለድርሻ አካላት የሁከት መንስኤዎችን ለይቶ ማወቅ እንዲሁም ችግሩን በጥልቀት በመገንዘብ የመከላከያ ዘዴዎችን በመቀየስ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል። በተለይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና ባለድርሻ አካላት ይህን ጥያቄ መሰረት ያደረገ ተግባር ማከወን ይኖርባቸዋል። ምንጩን ለይቶ ማወቅም አስፈላጊውን የቤት ሥራ መውሰድም ለነገ የሚባል የቤት ሥራ መሆን የለበትም።
አዲስ ዘመን፡- ለትብብርዎ ከልብ አመሰግናለሁ
አቶ ተሾመ፡- እኔም ከልብ አመሰግናለሁ

ታምራት ተስፋዬ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።