ለስኳር ልማት የተከፈለ የሰው ህይወት

12 Feb 2017

በህገመንግስቱ አንቀፅ 44 ንዑስ አንቀፅ 2 ላይ መንግስት በሚያካሂዳቸው ፕግራሞች ምክንያት የተፈናቀሉ ወይም ኑሯቸው የተነካባቸው ሰዎች ሁሉ በመንግስት በቂ ዕርዳታ ወደ ሌላ ቦታ መዘዋወርን ጨምሮ ተመጣጣኝ የገንዘብ ወይም ሌላ አማራጭ ማካካሻ የማግኘት መብት እንዳላቸው በግልፅ ተቀምጧል፡፡ ልማት ህዝብን ያሳተፈ መሆን እንዳለበትም እንዲሁ በህገመንግስቱ ተደንግጓል፡፡ ልማቱ በሚከናወንበት አካባቢ ያለን ህብረተሰብ ማሳመን እና የልማቱ ተጠቃሚ ማድረግም የግድ ነው፡፡

ነገር ግን በኦሮሚያ ክልል የአርጆ ዴዴሳ እና በአማራ ክልል የጣና በለስ የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች የአካባቢውን ህብረተሰብ ከመጥቀም ይልቅ በእጅጉ እየጎዱ መሆናቸውን የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በጥናት ማረጋገጡን ይፋ አድርጓል፡፡ፕሮጀክቶቹ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ እንዳልተደረገላቸው ይነገራል፡፡ፕሮጀክቶቹ በሚገነቡበት አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች ‹‹ልማቱ እኛን ያሳተፈ ሳይሆን ጭራሹኑ ለጉዳት ያጋለጠ ነው›› በማለት፤ በተለያዩ የህዝብ መድረኮች ላይ ድምፃቸውን ከማሰማት አልፈው ለህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አቤቱታ አቅርበዋል፡፡

ተቋሙም የቀረቡ ቅሬታዎችን መሰረት አድርጎ ቡድን በማደራጀት በሁለቱም ክልሎች ምርመራ አካሂዷል፡፡ ምርመራው በቦታው ተገኝቶ በመመልከት፤ ቪዲዮ በመቅረፅ፤ ተጎጂዎቹን ቃለ መጠይቅ በማድረግ፤ የቀበሌ፣ የወረዳ፣ የዞንና የክልል አስተዳደሮችን እንዲሁም የሚመለከታቸው የፌዴራል ተቋማትንም በማነጋገር ተከናውኗል፡፡

የምርምራ ሂደትና ውጤት-በኦሮሚያ

     የምርመራ ሪፖርት እንደሚያመለክተው፤ የአርጆ ዴዴሳ የስኳር ፕሮጀክት እና ለፕሮጀክቱ  የሚያገለግለው የመስኖ ልማት ግድብ የአራት ወረዳ ሰዎችን ለጉዳት አጋልጧል፡፡ በቦርቻ ወረዳ አስተዳደር 373 አርሶ አደሮች ንብረታቸው በትክክል ሳይቆጠር፣ ካሳ ሳይከፈላቸው፣ ምትክ መሬትም ሳይሰጣቸው ከመኖሪያ ቤታቸው እንደዋዛ ተፈናቅለዋል፡፡ ለአንድ አመት ከስምንት ወር በላስቲክ መጠለያ ድንኳን በመኖራቸውና የሚቀርብላቸው እርዳታም በቂ ባለመሆኑ ለተላላፊ በሽታና ለምግብ እጥረት የተጋለጡ ሲሆን፤ በዚህም 33 ህፃናት ሞተዋል፡፡ ስለመስኖ ግድብ ግንባታውና ውሃው አካባቢውን ቢያጥለቀልቅ እንዴት ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ባለመሰራቱ  ለግድብ ተብሎ የተሰራው ውሃ በመሙላቱ 4 ሰዎችና 64 የቤት እንስሳት በአዞ ተበልተዋል፡፡

በተጨማሪም 220 አርሶ አደሮች ካሳና ምትክ መሬት አልተሰጣቸውም፡፡ ለካምፕ መስሪያ በሚል ይዞታቸውን ያጡት 48 አርሶ አደሮችም ካሳ አላገኙም፡፡ ፕሮጀክቱን ለማስተግበር በሚል በደል የደረሰባቸው ሰዎች የጤና እና የትምህርት አገልግሎት እያገኙ አለመሆናቸውን የምርመራ ግኝቱ ያመለክታል፡፡ በቦረቻ ወረዳ ያሉ ነዋሪዎች ላይ የደረሰው ጉዳት ለነገ ህይወታቸውም ትልቅ ጠባሳን ጥሎ የሚያልፍ መሆኑንም ሪፖርቱ ያሳያል፡፡

በሊሙ ሠቃ ወረዳ 289 አርሶ አደሮች በመስኖ ግድቡ ምክንያት ከይዞታቸው ተነስተው ለንብረታቸው ካሳ፣ ለይዞታቸው ምትክ አልተሰጣቸውም፡፡ 47 አርሶ አደሮች ደግሞ ካሳ ቢከፈላቸውም ምትክ መሬት አላገኙም፤ 67 አርሶ አደሮች የተሰጣቸው ምትክ የእርሻ መሬት ውሃ የተኛበት እና ለእርሻ ምቹ አለመሆኑን የእንባ ጠባቂ የምርመራ ቡድን አረጋግጧል፡፡

በበደሌ ወረዳም 358 አርሶ አደሮች የአካባቢው ነዋሪ እና የእርሻ መሬት ያላቸው ቢሆንም ከቦታው ሲነሱ ምትክ መሬት አልተሰጣቸውም፡፡ ሌሎች 170 አርሶ አደሮች ደግሞ በቋንቋ ትርጉም ስህተት ሳቢያ ካሳው ከሚገባው በላይ ዘግይቶባቸዋል፡፡ በጅማ አርጆ ወረዳ አስተዳደርም 45 አርሶ አደሮች ካሳ ያልተከፈላቸው ሲሆን 21 አርሶ አደሮች ደግሞ ምትክ መሬት አልተሰጣቸውም፡፡ በአጠቃላይ በክልሉ በፕሮጀክቱ ሳቢያ አንድ ሺ 638 አርሶ አደሮች የአስተዳደር በደል እንደደረሰባቸው የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋሙ በሪፖርቱ ይፋ አድርጓል፡፡

    የአርሶ አደሮቹ አስተያየት

በኦሮሚያ ክልል ኢሉ አባቦራ ወረዳ የሚኖሩት አቶ አብዲ ከዲር እንደሚናገሩት፤ በፕሮጀክቱ ከመኖሪያቸው ከተፈናቀሉ ሁለት ዓመት ሊሞላ ነው፡፡ በሸራ በተወጠረ መጠለያ ሲኖሩ ትንሽ ብር ቢሰጣቸውም አልቆባቸዋል፡፡ የተወጠረው ሸራም ፀሃይና ዝናብ ሲፈራረቅበት ቆይቶ አሁን መበጣጠስ በመጀመሩ ለሊት በብርድ እየተሰቃዩ ነው፡፡ ልጆቻቸው አይማሩም፡፡ በምግብ እጥረት ሰዎች እየተሰቃዩ እና እየሞቱ ነው፡፡ የእርሳቸውም ስምንት የቅርብ ዘመዶቻቸው ከተፈናቀሉ በኋላ በምግብ እጥረትና በህመም ለሞት በቅተዋል፡፡ የሚመለከተው አካል አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው እየጮሁ ቢሆንም መፍትሄ አላገኙም፡፡

በክልሉ በቦርቻ ወረዳ በኦግዳ አርባ አካባቢ የሚኖሩት አቶ አባ ከድር በበኩላቸው፤ የአርጆ ዴዴሳ ግድብ በመገደቡ ውሃው ወደ ኋላ ሲተኛ ማሳቸው በውሃ መጥለቅለቁን ይናገራሉ፡፡

‹‹ በሁለት ሄክታር ከግማሽ ለም መሬት ላይ ፍራፍሬዎችን ተክዬ ነበር፡፡ በተጨማሪ ማሽላ፣ ሸንኮራ፣ ጫት፣ ማንጎ እና ቡናን የመሳሰሉ ምርቶች ሙሉ ለሙሉ በውሃ ተጥለቅልቀውብኛል፡፡ በዓመት በአጠቃላይ ከ150 ሺ ብር ያላነሰ አገኝ ነበር። አሁን ግን ባዶዬን ቀርቻለሁ›› ብለውናል፡፡

ማሳቸው በውሃ የተጥለቀለቀው በ2007 ዓ.ም መሆኑን በማስታወስ ችግሩ የእርሳቸውን ህይወት ብቻ ሳይሆን የሚያስተዳድሯቸውን 12 የቤተሰቡን አባላት እየጎዳ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ አሁንም አካባቢው በውሃ የተጥለቀለቀ ሲሆን ጥያቄ ደጋግመው ቢያቀርቡም እናዘዋውራችኋለን ከማለት ውጪ፤ በተግባር የታየ ምንም መፍትሄ እየመጣ አለመሆኑን ይገልፃሉ፡፡

   የምርምራ ቡድን መፍትሄ

በህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የኦሮሚያ ቅርንጫፍ የምርመራ ዳይሬክተር እና የምርመራ ቡድኑ መሪ አቶ አድማሱ አበበ፤ ችግሩ አሁንም ያለ መሆኑንና ተጎጂዎቹ በመጠለያ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ ሪፖርቱ የደረሳቸው የፌዴራል ተቋማት የተነጋገሩበት ቢሆንም ተጨባጭ እርምጃ አለመወሰዱን አመልክተው፤ ተጎጂዎቹ አሁንም ለተቋሙ የምርምር አካል እየደወሉ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

መጀመሪያውኑ ህብረተሰቡ የሚሰፍርበትን ሁኔታ ማጥናትና ማስፈር እንዲሁም እስከ ማቋቋም የዘለቀ ስራ መሰራት ነበረበት፡፡ ቀድሞ በጥናት ተመስርቶ አለመሰራቱ ዜጎችን በእጅጉ ጎድቷል፡፡ ከጥናቱም በኋላ ማንም ችግሩን ለመፍታት ቦታው ላይ አልተገኘም፡፡ የክልሉ መንግስት በድንኳን ያለውን ህብረተሰብ ለማንሳት መሬት አዘጋጅቻለሁ እያለ ነው፡፡ በተለይ ቅድሚያ ትኩረት የሚያስፈልጋቸው ህፃናትና አረጋውያን በቀጣይ ክረምት የባሰ ለአደጋ ሊጋለጡ ስለሚችሉ የእነሱን ህይወት ለማዳን ስኳር ኮርፖሬሽንም ሆነ የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሌላውም አካል ተረባርቦ እነዚህን ሰዎች በፍጥነት መጠለያ የሚያገኙበትን ሁኔታ ለማመቻቸት በቅንጅት መስራት ይኖርባቸዋል በማለት መፍትሄ ያሉትን አቶ አድማሱ ተናግረዋል፡፡

በቅንጅት በሃላፊነት ስሜት ካልተሰራ ህብረተሰቡ በቀጣይ ክረምትም በድንኳን ይኖራል :: ህብረተሰቡም የበለጠ ይጎዳል የሚል ስጋት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ በድንኳን ካሉ ተጎጂዎች በተጨማሪ በተበጣጠሰ መልኩ መሰራቱ ካሳ የሚሰጥበትን ሁኔታንም አዘበራርቋል የሚሉት አቶ አድማሱ፤ የጋራ ፅህፈት ቤት ተቋቁሞ፤ ያላቸውን ንብረት መዝግቦና ካሳ የሚከፈላቸውንና የማይከፈላቸ ውን ለይቶ በህግ መሰረት መስጠት ሲገባ ለአርሶ አደሮች በተቆራረጠ መልኩ  እንዲከፈል አስገድዷል፡፡ ይህም ቅሬታ ፈጥሯል፡፡ አንዳንዱ ካሳ የሚገባው ሆኖ ካሳ ያላገኙ አሉ ብለዋል፡፡

አደጋ ሊያጋጥማቸው ይችል ይሆናል ተብለው የሚገመቱ ቦታ የለንም በሚል መነሳት እያለባቸው ያልተነሱ፤ አንድ ሺ 500 ሰዎች መኖራቸውን እና ለእነዚህም ከወዲሁ በቅንጅት ካልተሰራ አደጋው የበለጠ የከፋ እንደሚሆንም ነው የሚናገሩት፡፡ ሃላፊነቱ የኔ አይደለም በማለት ወደ ሌላ ከመግፋት ይልቅ የጋራ ፅህፈት ቤት በማቋቋም መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የምርምራው ሂደትና ውጤት-አማራ ክልል

የአማራን እና የቤንሻንጉል ክልልን አማክሎ 75ሺ ሄክታር ማሳን የሚሸፍነው የጣና በለስ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ላይም 36 የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች ካሳ ያልተከፈላቸው መሆኑን፤ 213 አርሶ አደሮች በህጉ መሰረት ምትክ እርሻ መሬት እንዳልተሰጣቸው፤ 87 አርሶ አደሮች ደግሞ በምትክነት የተሰጣቸው መሬት ምርታማ ያልሆነ፤ ድንጋያማና ተዳፋት የበዛበት እና ለእርሻ የማይውል መሆኑን የዋና እንባ ጠባቂ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ቀንአ ሶና ያመለክታሉ፡፡

ሁለት ሺ 535 አርሶ አደሮች ከነባር ይዞታቸው ጋር ተመጣጣኝ መሬት ያልተሰ ጣቸው መሆኑን፤ 415 አርሶ አደሮች የተሰጣቸው እርሻ መሬት ከመኖሪያ ቤታቸው 60 ኪሎ ሜትር እንደሚርቅ፤ ለ198 ሰዎች የይዞታ ማረጋገጫ አለመሰጠቱን እና 158 ተነሺዎች በደንቡ መሰረት 500 ካሬ ሜትር የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ እንዳልተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

በቂ የንፁህ መጠጥ ውሃ ግንባታ፤ የመብራት አገልግሎት፤ የጤና እና የትምህርት ተቋማት እንዲሁም ለአርሶ አደሮች ተገቢው የኑሮ አማራጭና ድጋፍ አለመኖሩ አርሶ አደሮቹን መልሶ ለማቋቋም የተሰራው ስራ ችግር ያለበት መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ የተቋሙ መርማሪ ቡድንም ይህንን እንዳገኘ አቶ ቀንአ ተናግረዋል፡፡

የልማት ተነሺዎች በተገባላቸው ቃል መሰረት የመስኖ ተጠቃሚ አለመሆናቸው፤ በሚፈለገው ደረጃ ለአካባቢው ህብረተሰብ የስራ ዕድል አለመፈጠሩንም ነው ሃላፊው ያመለከቱት፡፡ በእነዚህ ሰዎች ላይ ለደረሰው በደል፤ የክልል ሃላፊዎች ለስኳር ኮርፖሬሽን እና ለውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ተቋሙ ግኝቱንና የመፍትሄ ሃሳቡን አቅርቧል፡፡

በአማራ ክልል ጃዊ ወረዳ አርጋቦ ቀበሌ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አናጋው ዋሌ እንደተናገሩት፤ በጣና በለስ ምክንያት በ2004 ዓ.ም አርሶ አደሩ ተፈናቅሏል፡፡ እስከ አሁን መሬት ያላገኙ፤ የከብት መዋያ የግጦሽ መሬት ያጡ ብዙ ናቸው፡፡ ምትክ መሬት ቢሰጥም ያለጥናት በዘፈቀደ የተሰጠ ሲሆን፤ መሬቱ የማያበቅል ለእርሻ የማይሆን መሬት በመሆኑ ተነሺዎቹ እየተጎዱ ነው፡፡

ለተነሺዎቹ ምን መደረግ እንዳለበት በወቅቱ መንግስት ማጥናት ነበረበት፡፡ ቦታ ሲሰጥም በረሃ ላይ ለእያዳንዱ አርሶ አደር አንድ ነጥብ አምስት ሄክታር ብቻ ነበር፡፡ ይህ ለበረሃ መሬት በቂ አይደለም፡፡ የካሳ ክፍያውም ለአንዳንዱ ተከፍሎ፤ ሌሎች ካሳ ሳይከፈላቸው ተዳፍኖ የቀረባቸው አሉ፡፡ የመንግስት ልማት ነው በሚል መሬቱ እንዲሁ ተገቢውን ካሳ ሳይከፈል የሚወሰድበት ሁኔታ አለ ብለዋል፡፡ መሬት አሰጣጡም የተዘበራረቀ መሆኑን እና ለክልል ጥያቄ ማቅረባቸውን አመልክተው፤ አዳማጭ አጥተው መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

በአማራ ክልል የባህርዳር ቅርንጫፍ እንባ ጠባቂ ተቋም የምርመራ ዳይሬክተር የሆኑትና ቡድኑን የመሩት አቶ ሃብታሙ ታደሰ እንደሚናገሩት፤ ጣና በለስን አስመልክቶ ምርመራው የተሰራው ጥቅምት ላይ ነበር፡፡ ከዛ ጊዜ ጀምሮ በየደረጃው ለሚመለከተው አካል ሪፖርቱ ቀርቧል፡፡ ልማት መነሻውም ሆነ መድረሻው ህዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ ነው፡፡ ነገር ግን በጣና በለስ ስኳር ፕሮጀክት ላይ በመልሶ ማቋቋምም ሆነ ከልማት ተጠቃሚነት አንፃር ችግር መኖሩን በጥናት ተረጋግጧል፡፡

ምትክ መሬት አሰጣጥ ላይ በዋናነት የሚመለከተው ክልሉን በመሆኑ ለዛው ሪፖርቱ ቀርቧል፡፡ የሚመለከተው የገጠርና መሬት አስተዳደር ቢሮ በየተዋረዱ ያሉ ተቋማት በተለይ የጃዊ ወረዳ ፅህፈት ቤት መሬት የመስጠት ሂደቱ የሚመለከተው እርሱን በመሆኑ የድርጊት መርሃ ግብር በማውጣት በጊዜ ገደብ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ምትክ መሬት ያላገኙት ሰዎች መሬት እንዲያገኙ እንዲሰሩ የተነገራቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የማያበቅል መሬት የተባለው የተረጋገጠው በግብርና ባለሙያዎች ሲሆን፤ ተደፋታማነቱ ከፍተኛ በመሆኑ ተለዋጭ መሬት እንዲሰጣቸው የመፍትሄ ሃሳብ ማስቀመጣቸውንም ተናግረዋል፡፡ የመሬት ችግር ካለም በህጉ መሰረት ዘላቂ መፍትሄ  የሚበጅበት ሁኔታ መኖር አለበት፡፡ ክልሉ በተቀመጠ የጊዜ ገደብ ውስጥ ተገቢውን የማስተካከያ እርምጃ ካልወሰደ በአዋጁ መሰረት የሚመለከታቸውን የስራ ሃላፊዎች ተጠያቂ የማድረግ ሁኔታ ይኖራል ብለዋል፡፡

ነገር ግን ችግሩን ተቀብለው መግባባት ላይ በመደረሱ በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሄ ይገኛል ብለው እንደሚጠብቁም ይናገራሉ፡፡ ልማቱን ለማስጠበቅ ከህብረተሰቡ ጋር ተስማምቶ የባለቤትነት ስሜት እንዲፈጠር ማድረግ ካልተቻለ ዘላቂነት ስለማይኖረው ቢያንስ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ በየደረጃው ከሚመከታቸው አካላት ጋር መነጋገራቸውን ተናግረዋል፡፡

ስኳር ኮርፖሬሽን በተለይ ከመልሶ ማቋቋምና ከስራ ዕድል ፈጠራ ጋር ተያይዞ የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች ልጆች ስራ የሚያገኙበት ሁኔታ በተለይ ፕሮጀክቱ ወደ ምርት ሲገባ ዕድሉ እንደሚፈጠር ተነጋግረናል ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ስራ እስከሚጀምር አርሶ አደሮች የመስኖ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ወይም በመስኖ የለማ መሬት እንዲያቀርብላቸው አልያም በማህበር አደራጅቶ የሸንኮራ አገዳ ለፕሮጀክቱ የሚያቀርቡበትን ሁኔታ መፍጠር እንዳለበት መነጋገራቸውን ተናግረዋል፡፡

የመፍትሄ ሃሳቡ ከቀረበ ሶስት ሳምንት ያለፈው መሆኑን እና ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት ክልሉ ይህን ያህል ችግር መኖሩን እንደማያውቁ፤ ችግሩን ለመፍታት ዝግጁ መሆናቸውን እንደነገሯቸው አመልክተዋል፡፡ ከኮርፖሬሽኑ ጋርም እየተነጋገሩ መሆኑን በማመልከት መፍትሄ ካልተገኘ በአዋጁ መሰረት የሚመለከታቸው አካላት ተጠያቂ እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡

የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር

የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በበኩሉ፤ የአርጆ ዴዴሳ ግድቡ በስኳር ኮርፖሬሽን የተጀመረ መሆኑን በማስታወስ፤ እነርሱ ቢረከቡትም ቀድሞ ካለመሰራቱም ባሻገር በኋላም መልሶ በማቋቋም በኩል ያለውን ክፍተት እንደሚቀበሉት ይናገራሉ፡፡ 373 አርሶ አደሮች ተነሱ በተባለበት አካባቢ 80 ሺ ሄክታር ለማልማት 50ሺ ለስኳር ፕሮጀክቱ ፣30 ሺ ደግሞ ለአካባቢው ህብረተሰብ የመስኖ ልማት የታሰበ ቢሆንም በቅንጅት የመስራት ክፍተት አለ ይላል፡፡

የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ አሸናፊ ካሳ በበኩላቸው፤ አንዳንድ እርምጃዎችን ለመውሰድ ተሞክሯል፡፡የተገባው ትልቅ ግድብ ሳይሆን አነስተኛ ግድብ ነው፡፡የተኛው ውሃ የጎዳቸውን ሰዎች ለመታደግ እና እስከ ክረምት በዛው ቦታ እንዳይቆዩ ይሰራል፡፡ ለተፈናቃዮች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ካሳ ይከፍላል፡፡ ነገር ግን ቀድሞ መሰራት ነበረበት የሚለው እንደሚያስማማ ተናግረዋል፡፡

ይህ ማለት ግን እስከአሁን ምንም አልተሰራም ማለት ሳይሆን፤ የሚቀርቡ የካሳ ጥያቄዎች ምላሽ ሲያገኙ እንደነበር፣ለአብነት በሊሙ ሳቃ ወረዳ ለ698 አርሶ አደሮች የቀረበው የ112 ሚሊዮን ብር የካሳ ጥያቄ ተስተናግዶ ገንዘቡ ለወረዳው ተልኳል፡፡ ወረዳውም 60 ሚሊዮን ብሩን አከፋፍሏል፡፡ የመሰረተ ልማት ስራዎችም ተጀምረዋል፡፡

በቦርቻ ወረዳም ለ634 አርሶ አደሮች 88 ሚሊዮን ብር የካሳ ክፍያ ተጠይቆ 75 ሚሊዮን ብር ተከፍሏል፡፡ ነገር ግን አሁንም ችግር መኖሩ አይካድም፡፡ ከክልልም ሆነ ከዞን እንዲሁም ከወረዳ እና በአጠቃላይ ከሚመለከታቸው የፌዴራል ተቋማት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ አያጠያይቅም፡፡ ያለበለዚያ ትልቁ ግድብ ሲገነባ አደጋው የከፋ ሊሆን እንደሚችልም ነው የሚያመላክቱት፡፡

ስኳር ኮርፖሬሽን

የስኳር ኮርፖሬሽን የካሳ እና የመልሶ ማቋቋም ተወካይ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ደረሰ ለገሰ በበኩላቸው፤ ለማህበረሰቡ ካሳ የመስጠትና የማቋቋም ስራ ከገንዘብ እጥረትም ሆነ ከሌላ ችግር ጋር ተያይዞ ክፍተት ነበር፡፡ ነገር ግን አሁንም እየተሰራ ነው፡፡ በደሌ ወረዳ ላይ 12 ሚሊዮን ብር የካሳ ጥያቄ ቀርቦ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በትርጉም ስህተት ዘግይቷል፡፡ በቀሪው ጊዜ ግን ይለቀቃል፡፡

አርጆ ዴዴሳም ሆነ ጣና በለስ የስኳር ፕሮጀክቶች የአካባቢውን ህዝብ ከመጉዳት ይልቅ ጠቃሚ መሆን አለባቸው የሚለው አስተያየት ትክክል መሆኑን በመግለፅ፤ ምንም እንኳ በቂ ባይሆንም በግንባታ ሂደት ከፍተኛ ሙያ የሚጠይቁትን ካልሆነ በስተቀር ሌላው በአካባቢው ህዝብ እንደሚሰራ እና የስራ ዕድል እየተፈጠረ መሆኑን ፣ልማቱ ሲቀጥልና ወደ ምርት ሲገባ የስራ ዕድሉ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ይገልፃሉ፡፡

     ተጠያቂው ማን ነው?

የኦሮሚያ ክልል የህዝብ እንባ ጠባቂ ቀሲስ በላይ መኮንን በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱ አስፈላጊ እና አገርን የሚጠቅም ቢሆንም በልማቱ በሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ተጎድተዋል፡፡ በግዴለሽነት የሰዎች ህይወት አልፏል፡፡ ብዙዎች በድንኳን እየኖሩ ነው፡፡ የስኳር ኮርፖሬሽኑም ሆነ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፤ ክልሉም ሆነ ወረዳው ባጠፉት ጥፋት ህዝብ ተጎድቷል፡፡ የችግሩን ባለቤት ወደ ሌላ መወርወር አያዋጣም፡፡ በፍጥነት መፈታት ያለበትን ችግር በአስቸኳይ መፍታት ይገባል፡፡ ሁሉም ግዴታውን መወጣት አለበት፡፡ የኦሮሚያ ክልል የደረሰውን ሪፖርት ተከትሎ በማግስቱ ኮሚቴ አቋቁሞ ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑን አሳውቋል፡፡ ልክ እንደዚህ ፈጣን እንቅስቃሴ ማድረግና ችግሩን መፍታት ካልተቻለ ህዝቡም ፕሮጀክቱን ይቀበለዋል ለማለት ያዳግታል፡፡

እንደተባለው የቅንጅትና ያለመናበብ ብቻ ሳይሆን በጥብቅ ሥነሥርዓት ያለመመራት ክፍተት በመኖሩ ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡ ሰዎች ከተፈናቀሉ በኋላ የሚሰጥ ካሳ ለዓመት ከዘገየ የብሩ ዋጋ ምን ያህል እንደሚቀንስ ማሰብ ይገባል፡፡ ጊዜው ተወስኖ ችግሩ የሚፈታበት፤ ምትክ ቦታውም ሆነ ካሳው የሚሰጥበት ሁኔታ በግልፅ መቀመጥ እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡    

 የህዝብ እንባ ጠባቂ ዋና እንባ ጠባቂዋ ወይዘሮ ፎዚያ አሚን እንደተናገሩት፤ ፕሮጀክቶቹ አገርን የሚጠቅሙና የህብረተሰብን የኑሮ ደረጃ የሚያሻሽሉ ቢሆኑም፤ ህዝብን ካፈናቀሉ ልማት ናቸው አይባሉም፡፡ 373 አባወራዎችን ለአንድ ዓመት ከስምንት ወር በመጠለያ ያስቆየ የልማት ስራ የአካባቢውን ህብረተሰብ የሚጠቅም ነው ለማለት ያዳግታል፡፡

የክልልም ሆነ የፌዴራል ተቋማት የምርምር ግኝቱን ያምናሉ፡፡ ችግሩን ይፈታ ሲባል ደግሞ፤ ችግሩን ከማወቅ አልፈው ለመፍታት ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ ተቋማቱ ‹‹ይህ የኔ ሥራ አይደለም›› ካሉ እንደመርህ የሚወሰደው በልማቱ ስራ ህዝብን የማሳተፍ ሂደት ይስተጓጎላል፡፡ ህዝብ ቀድሞ ተወያይቶና ተሳትፎ ቢሆን መዘግየት ቢኖርም ቢያንስ ማፈናቀሉ ይቀር ነበር፡፡ አሁንም ያለምንም ተጨማሪ ጊዜ በድንኳን ያሉና የተፈናቀሉትን አርሶ አደሮች ችግር መፍታት ያስፈልጋል፡፡

ክረምት ሳይመጣ መኖሪያ እናበጅላቸዋለን የሚለው ሃሳብ በደንብ መታየት አለበት፡፡ ከአራት ወር በፊት 33 ህፃናት ህይወታቸው ካለፈ በቀጣይ ካለፉት አራት ወራት ተጨማሪ አራት ወራት እንዲቆዩ ማሰብ ምንም እንኳ የዝግጅት ጊዜ ቢያስፈልግም ከባድ ነው፡፡ ቢያንስ ባሉበት ሁኔታ በደህንነት እንዲኖሩ ተገቢው ድጋፍ ሊሰጣቸው እንደሚገባም ነው ያመለከቱት፡፡ የመፍትሄ ጊዜው ከራቀ ተጎጂዎቹን ጭራሽ ማግኘት እንደማይቻልም ነው የሚያሳስቡት፡፡

የፕሮጀክቶቹ መገንባት ወሳኝነቱ ባይካድም ባለመቀናጀትና በአግባቡ ባለመሰራቱ በሚጎዱ ሰዎች፤ ልማቱ ላይ ዕምነት እንዳይኖራቸውና እንዳይቀበሉት ያደርጋቸዋል፡፡ የወረዳ ሃላፊዎች መቀያየርና ሌሎችም የሚነሱ ምክንያቶች አጥጋቢ አለመሆናቸውን በመጠቆም፤ ሰነድ አዘጋጅቶ ማንም ቢመጣ ሊሰራው በሚችል መልኩ ማስቀመጥና ሃላፊነትን መውሰድ ተገቢ መሆኑንም ነው ዋና እንባ ጠባቂዋ የተናገሩት፡፡ 

ማጠቃለያ

የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ስኳር ኮርፖሬሽን፣የሁለቱም ክልሎች በየደረጃው ያለ የስራ ኃላፊዎች የአርሶ አደሮቹን ችግር በመፍታት ረገድ የእስካሁኑ ጥረታቸው ተገቢ ነበር ማለት አይቻልም።ምክንያቱም የህዝብ እንባ ጠባቂ ምርምራ ሪፖርት ከደረሳቸው በኋላ እንኳን ፈጣን ምላሽ  ሰጥተዋል ማለት አይቻልም። ፋብሪካው የሚሰራው ለሰው ተብሎ ነው።ለሰው ተብሎ ግን የሰውን ውድ ህይወት አደጋ ላይ መጣል የለበትም።ስለዚህ ይህ ለስኳር ተብሎ የተከፈለ ውድ ዋጋ መቆም አለበት።የሰው ህይወት በገንዘብ አይተመንም።ስለዚህ ፈጣን ምላሽ-ውድ የሆነውን የሰው ህይወት ከአደጋ ለመታደግ። 

 

ምህረት ሞገስ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።