«በክልሉ በፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነት ረገድ ችግር እንደነበር ተገምግሟል» - አቶ ይርሳው ታምሬ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ Featured

16 Feb 2017

ምክር ቤቶች  በህዝብ ውክልና የሚቋቋሙ የመንግሥት ከፍተኛው አካል ናቸው። በዚህ ረገድ ፌዴራላዊ ሥርዓት በምትከተለው ኢትዮጵያም የክልል መንግሥታት የራሳቸውን ምክር ቤት በማቋቋም የተሰጣቸውን ተልዕኮ እየተወጡ ይገኛሉ። ለዛሬ ከአማራ ክልል ምክር ቤት  አፈ ጉባዔ አቶ ይርሳው ታምሬ ጋር  በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ያደረግነውን ቃለ መጠይቅ ይዘን ቀርበናል።

አዲስ ዘመን ፦  የአማራ ክልል ምክር ቤት የክልሉን ህዝቦች በመወከል ረገድ በአካባቢ፣ በፆታ፣ በዕድሜና በማህበረሰብ ክፍል ስብጥሩ ምን ይመስላል?

አቶ ይርሳው ፦ ምክር ቤቱ የሕዝብን ቀጥተኛ ውክልና ለማረጋገጥ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ይዟል፡፡ የአርሶ አደሩ ውክልና ሰፋ ያለ ነው፡፡ የሴቶች ውክልና ከጠቅላላው የምክር ቤቱ አባላት 47 በመቶ ነው፡፡ የንግዱን ማህበረሰብ፣ምሁራንና ወጣቶችንም ታሳቢ አድርጓል፡፡ ስለዚህ ከሞላ ጎደል ከሁሉም የኀብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጣ ነው፡፡ በተዋረድም የሚገኙት ምክር ቤቶች በተመሳሳይ ሁኔታ የተለያየ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚወክሉ ናቸው።

አዲስ ዘመን ፦ የኀብረተሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መነሻ በማድረግ ለተፈፃሚነታቸው የምታደርጉት ክትትል ምን ይመስላል?

አቶ ይርሳው ፦  ምክር ቤቱ ሦስት ተልዕኮዎች አሉት፡፡ የመጀመሪያው የአካባቢን ልማት፣ ዴሞክራሲ፣  ሰላምና ማህበራዊ ፍትህ ለማምጣት የሚያስችል ሕግ ማውጣት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የክትትልና ቁጥጥር ሥራ ነው፡፡ ይሄም የአስፈጻሚና የዳኝነት አካሉን ዕቅድ እንዲሁም አፈጻጸም ይመረምራል፡፡ ከዚያ በመነሳት ውሳኔዎችን ያስተላልፋል፡፡ ሦስተኛ ውክልናን መወጣት ነው፡፡ አባላቱ የሕዝቡ ቀጥተኛ ወኪል ስለሆኑ የሕዝቡን ችግርና ፍላጎት በሚገባ ተረድተው እንዲፈታ የሚያደርጉበት መስተጋብር አለ፡፡

ምክር ቤቱ ስድስት የቋሚ ኮሚቴ አደረጃጀቶች አሉት፡፡ በእርግጥ የክልል ምክር ቤት እንደ ፌዴራሉ ምክር ቤት አባላቱ በቋሚነት አይቀመጡም፡፡ ነገር ግን የቋሚ ኮሚቴ ስብሳቢዎች በቋሚነት ቢሮዎችን ይከታተላሉ፤ የሕዝብ ቅሬታዎችን ያዳምጣሉ፡፡ ከዚህ ውጪ ጉባዔ ለማካሄድ በሚቃረቡበት ወቅት ሁሉም የቋሚ ኮሚቴ አባላት የመስክ ቅኝት ያደርጋሉ፡፡ ሪፖርት ይመረምራሉ፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ ጉባዔ እናካሂዳለን፡፡ ለዚህ ጉባዔ የክልሉ መንግሥት የስድስት ወር አፈፃፀም ምን ይመስል ነበር? የሚለውን ወረዳና ቀበሌ ድረስ ወርደው አይተው ለመመለስ ስምሪት ላይ ናቸው፡፡ እንደተመለሱ የእያንዳንዱን ተቋም ሪፖርት ይገመግማሉ፤ ሪፖርቱንና መስክ ላይ ያዩትን ወስደው የውሳኔ ሃሳብ ለምክር ቤቱ ያቀርባሉ፡፡ ምክር ቤቱ ያን ይዞ ይወያያል፤ ይወስናል፡፡

አዲስ ዘመን ፦  አባላቱ በመስክ ቅኝት የሚመለከቷቸው የአፈጻጸም ክፍተቶችን ተከታትሎ ውሳኔዎች እንዲወሰኑ ግፊት ይደረጋል?

አቶ ይርሳው፦  አዎ! ይሄን ሁሉም የአገሪቱ ዜጋ መታዘብ ይችላል፡፡ ምክንያቱም ውይይቱ የሚደረገው በክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀጥታ ስርጭት ነው፡፡ ምክር ቤታችን የአንድ ፓርቲ አባላት ያሉበት ምክር ቤት አይመስልም፡፡ በማንኛቸውም ጉዳዮች ላይ በግልጽ ይወያያል፤ ይከራከራል፤ ከዚያም ባለፈ በልዩነት ጭምር ይወስናል፡፡ በጣም በርካታ ውሳኔዎችን በድምፅ ብልጫ ወስኗል፡፡

አዲስ ዘመን ፦  በማሳያነት ማንሳት የሚቻሉ የልዩነት ውሳኔዎች አሉ?

አቶ ይርሳው ፦ ሹመት ላይ በልዩነት ይወስናል፡፡ በሚቀርቡ ሪፖርቶች ዙሪያ በማፅደቅና ባለማፅደቅ ዙሪያ፤ በአዋጅ እንዲሁም ብዙ ውሳኔዎች በልዩነት ተወስነው ያውቃሉ፡፡ ኀብረተሰቡ ውስጥ በአብዛኛው በአንድ ፓርቲ ምክር ቤት ውስጥ በልዩነት ይወስናል የሚል ግምት የለም፤ በእኛ ምክር ቤትም ይህ አመለካከት እንዳይኖር እየተሰራ ነው፡፡ ምክንያቱም የሕዝብ ጥቅም የምናስከብረው በዚህ መንገድ ስንሰራ ብቻ ነው በሚል እንወያያለን፡፡

በተጨማሪም አባላቱ ከተለያየ የኀብረተሰብ ክፍል የተውጣጣ መሆኑም ምክር ቤቱን ጠንካራ አድርጎታል፡፡ ለምሳሌ አርሶ አደሮችና ሴቶች የጎላ ድርሻ አላቸው፤ ያዩትን ነገር በቀጥታ ትክክለኛውን ችግር በማቅረብ ይጋፈጡታል፡፡ ውይይቶቹ ችግሮችን ያሳያሉ፤ ምክር ቤቱም እንዲታረሙ ውሳኔ ያሳልፋል፡፡ ምክር ቤቱ ‹‹ችግር አለ›› ብሎ ከወሰነ በኋላ ችግሩ ሳይፈታ ሲቀር፤ ውሳኔ ከማሳለፍና ከመከራከር ባለፈ እርምጃ መውሰድ አለበት፡፡ ከዚህ አንጻር የሚቃረን ነገር አለ ብለን ገምግመናል፡፡ 

አዲስ ዘመን ፦  ምክር ቤቱ በክትትል ደረጃ በበቂ ሁኔታ እንዳልሄደ የገመገማቸው ጉዳዮች የሉም?

አቶ ይርሳው፡- በርካታ የሕዝብ ጥያቄዎች አሉ፡፡ እነኛ ሁሉ ተፈተዋል ማለት አይቻልም፡፡ በግምገማ ውጤት መሰረት ጥያቄዎችን ባነሳነው ልክ ተፈፃሚ ሳይሆን ሲቀር ያልፈጸመውን አካል እርምጃ መውሰድ አለመቻል ነው፡፡ አሁን ያልተፈጸሙ ጉዳዮችን እየለቀሙ የቋሚ ኮሚቴ አባላት ማቅረብ ጀምረዋል፡፡ ነግር ግን እርምጃ ማስውሰድ ላይ የሚቀረን ሥራ አለ፡፡ ለዚህ አንዱ ምክንያት የአስፈጻሚው አካል የብቃት ችግር ነው፡፡ ሕዝቡ የሚያነሳው ጥያቄ በጣም ብዙ ነው፡፡ በምትሄድበት መንደር በሙሉ የአስፋልት ጥያቄ ያነሳል፡፡ ነገር ግን እንደ መንግሥት የተነሱትን ጥቄዎች በሙሉ መመለስ አይቻልም፡፡ ስለዚህ የሚፈቱት ላይ አተኩሮ መነጋገር ይገባል፡፡

አዲስ ዘመን ፦  ከሌሎች ክልሎች ምክር ቤቶች ጋር ሲነጻጸር በጥንካሬ የሚጠቀሱ ጉዳዮች ምንድን ናቸው?

አቶ ይርሳው ፦  በየስድስት ወሩ ተገናኝተን ሥራ የምንገመግምበትና ልምድ የምንለዋወጥበት የሁሉም ምክር ቤቶች መድረክ አለን፡፡ በዚህ ረገድ ከሌሎች ክልሎች የምናገኛቸው ልምዶች አሉ፡፡ ከእኛ ክልልም የሚወሰድ ልምድ በሚል በጋራ እውቅና ከተሰጣቸው አንዱ ምክር ቤቱ የግልፅነትና ተጠያቂነት ሥርዓት ሊያሰፍን የሚችል የቀጥታ ስርጭት ውይይት ማካሄዱ ይጠቀሳል፡፡ ምክር ቤቱ የሚያደርገው ትግል በሌሎች ክልሎች በጥንካሬው ይበረታታል፡፡ ለምሳሌ ባለፈው ዓመት አዲስ መንግሥት ሲቋቋም ከፍተኛ የሆነ ውይይት ነበር፡፡

አዲስ ዘመን ፦  በኀብረተሰቡ በኩል የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በግልጽ ለይቶ መፍትሄ ከመጠቆም አንጻር ክፍተት የለም ?

አቶ ይርሳው ፦  ምክር ቤቶች የሚነጋገሩት የሕዝቡን ጥያቄ ይዘው ነው፡፡ ጥያቄውንም በተለያዩ መንገዶች ያገኙታል፡፡ አባላቱ የሚኖሩት ከሕዝቡ ጋር ነው፡፡ ስለዚህ ኀብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ችግር ይዘው ይመጣሉ፡፡ በሌላ በኩል በዋናው ምክር ቤት የሚገኙ የክልሉ ወኪሎችና የአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት በዓመት አንድ ጊዜ በተደራጀ ሁኔታ ወደ መራጩ ሕዝብ ሄደው ያወያያሉ፡፡ በውይይት የሚነሱት ችግሮች በወረዳ፣ በዞን፣ በክልልና በፌዴራል ደረጃ የሚፈቱ ይሆናሉ።

አባላቱ መፍትሄዎቹን በተመለከተ ለወረዳና ለዞን የቤት ሥራ ሰጥተው ይመጣሉ፡፡ ወደ ክልል የሚመጣው ደግሞ በሪፖርት ተደራጅተው ርዕሰ መስተዳድሩና የካቢኒ አባላት ባሉበት ችግሮችን ይለያሉ፡፡ ወደ ፌዴራል የሚመጣውንም የፌዴራል ፓርላማ አባላት ይዘው ይመጣሉ፡፡ ሦስተኛው በቋሚ ኮሚቴ በኩል ሲወርዱ የተሰራውን ሥራና ሕዝቡን በአካል አግኝተው ያነጋግራሉ፡፡ በእነዚህ መንገዶች የተገኙትን ችግሮች ነው አባላቱ ጉባዔ ላይ የሚነጋገሩት፡፡ ማጠንጠኛቸውም የሕዝቡ ትክክለኛ ጥያቄ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፦  በአምስተኛው ዙር የክልሉ ምክር ቤት ምን ውሳኔዎችን አሳልፏል?

አቶ ይርሳው፦   ጎላ ብሎ የሚነሳው ከማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ የቅማንት የማንነት ጥያቄ ዙሪያ ምክር ቤቱ ሁለት ጊዜ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ አንደኛው ውሳኔ የቅማንት ብሔረሰብ የራሱ ማንነት ያለው ብሔረሰብ ነው የሚል ውሳኔ ወስኗል፡፡ በተጨባጭ በጥናትም 42 ቀበሌዎች ላይ የሚኖር የቅማንት ሕዝብ አለ፡፡ ይሄን ይዘን ተግባራዊ መደረግ አለበት በሚል ወስኗል፡፡ ይሄ ውሳኔ የምክር ቤቱ ውሳኔ በመሆኑ አስፈፃሚው ሊመልሰው የማይችል ውሳኔ ነው፡፡

ባለፈው ዓመት ሌላ ክርክር ተነስቶ ስለነበር እርሱን መሰረት ተደርጎ ከ42ቱ ቀበሌዎች ውጪ ሌሎች ‹‹ቅማንት ነን›› የሚሉ የኀብረተሰብ ክፍሎች ጥያቄ አላቸው፡፡ ነገር ግን የሚኖሩት ተቀላቅለው ነው፡፡ ይሄን በተመለከተ ምክር ቤቱ በስፋት ተወያይቶ አማራና ቅማንት ተቀላቅለው የሚኖሩባቸውና ከ42ቱ ቀበሌዎች ጋር ኩታ ገጠም የሆኑ ቀበሌዎች በሕዝበ ውሳኔ እንዲለይ የሚለውን አስፈጻሚው እንዲወስን ምክር ቤቱ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ አሁን ይሄ እየተሰራ ነው ያለው፡፡ ሕዝብ እየተወያየ ነው፤ አሁን በሕዝበ ውሳኔ እንጨርሰው ወደሚል ስምምነት እየተደረሰ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፦  ባለፈው ዓመት በክልሉ ተከስቶ የነበረውን የወልቃይት የማንነት ጥያቄ ለመፍታት የምክር ቤቱ ሚና ምን ነበር?

አቶ ይርሳው፦  ባለፈው ዓመት በክልላችን የተፈጠረው ችግር በጠቅላላ ምን ይመስላል? የሚል ራሱን የቻለ ሪፖርት ባለፈው የምክር ቤታችን ጉባዔ  እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡ ችግሩ እንዴት ተፈጠረ? ለምን ተፈጠረ? እንዴት ተፈታ? ወደፊት እንዳይደገም ምን መደረግ አለበት? በሚል ርዕሰ መስተዳድሩ ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ ሰፊ ውይይት ተደርጎ ምክር ቤቱ በሦስት ጉዳዮች ውሳኔ አሳልፏል፡፡

አንዱ ውሳኔ ምክር ቤቱ ከቅማንት ጋር የተያያዘውን ጉዳይ በፈታበት መልኩ ውሳኔ ባሳለፈበት መንገድ ይፈጸም የሚል ነው፡፡ ሁለተኛ ከትግራይ ክልል ጋር ያለው የድንበር ጥያቄ ሁለቱ ክልሎች በጋራ ተቀምጠው ይፍቱ፡፡ ይህ ካልሆነ ጥያቄው ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን ተከትሎ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ይሄዳል የሚል ውሳኔ ወስኗል፡፡

ሦስተኛው የወልቃይት ጉዳይ ነው፡፡ የወልቃይት ጉዳይ ትግራይ ውስጥ የሚገኙ አማራ ነን የሚሉ ሕዝቦች ጥያቄ ነው፡፡ በሕገመንግሥታችን ደግሞ አንድ ክልል ውስጥ እየኖረ የማንነት ጥያቄ አለኝ የሚል የኀብረተሰብ ክፍል ጥያቄውን እንዲያቀርብ የሚፈቀደው ለሚኖርበት ክልል ነው፡፡ ስለዚህ የወልቃይት ጥያቄ ለአማራ ክልል ምክር ቤት ሊቀርብ የሚገባው ጥያቄ አይደለም፡፡ ጥያቄ አለን የሚሉ አካላት ጥያቄያቸውን በሚኖሩበት ክልል ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን ተከትለው ሊያቀርቡ ይገባል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የእኛ ምክር ቤት አጀንዳ አድርጎ ውሳኔ ሊያሳልፍ የሚችልበት ነገር ሊኖር አይገባም በሚል ወስኗል፡፡

አዲስ ዘመን፦ ጉዳዩ ሁለቱን ክልሎች የሚመለከት እንደመሆኑ በጋራ እያከናወናችሁ ያላችሁት ነገር አለ?

አቶ ይርሳው፦  በምክር ቤት ደረጃ ሁለቱ ክልሎች የተለየ እንቅስቃሴ አላደረጉም፡፡ ነገር ግን የሁሉም ክልሎች የጋራ ፎረም አለን፡፡ በዚያ መንገድ እንነጋገራለን፡፡ የተለየ ነገር ግን የለም፡፡

አዲስ ዘመን፦  በሰሜን ጎንደርና በምዕራብ ትግራይ መካከል በወሰን ጉዳይ የተነሳ የሚታየውን አለመግባባት ለመፍታት የተጀመረው ሥራ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል?

አቶ ይርሳው፡- ይሄ የምክር ቤቱም ጥያቄ ነው፡፡ ምክር ቤቱ በዚህ ጉዳይ ላይ ተወያይቶ ይሄ ጥያቄ በሁለቱ አስፈጻሚ አካላት እልባት ማግኘት አለበት በሚል ወስኗል፡፡ እስካሁን ባለን መረጃ መጀመሪያ የመንግሥት መዋቅር በሚገባ መጠናከር አለበት፤ ጥያቄውን በአግባቡ ለመፍታት የመንግሥት አካላት በራሳቸው ችግር ውስጥ ነበሩ፡፡ ስለዚህ በሁለቱም አካላት በኩል መንግሥት በተሃድሶ አስተሳሰባቸውን በማነፅና መልሶ በማደራጀት መጀመሪያ መዋቅሩን እናጠናክር፡፡ ከዚያም እርሱን ይዘን እንሰራለን የሚል  ነበር፡፡ ምክር ቤቱ በቀጣይ ጉባዔ ሲያካሂድ ይሄን ጉዳይ መልሶ ‹‹ወስነን ነበር፤ የት ደረሰ?›› ብሎ ይጠይቃል፡፡ እንደ አንድ አመራር ያለውን ሁኔታ የማውቀው በዚህ ደረጃ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፦  ጥያቄው ወዳልተፈለገ አጀንዳ እንዳይቀየር ከማድረግ አንጻር የተከናወኑ የግንዛቤ ሥራዎች አሉ?

አቶ ይርሳው፦  በእኛ በኩል ምን መስራት አለብን? የሚለውን ተመልክተናል፡፡ ‹‹ጥያቄ አለን›› የሚሉ የኀብረተሰብ ክፍሎች አሉ፡፡ የማንነት ጥያቄም ይሁን ከዚያ የዘለለ ሊሆን ይችላል የሚነሱ የኀብረተሰብ ክፍሎች አሉ፡፡ ይሄን ማንሳት ሕገመንግሥታዊ መብት ነው፡፡ በየትኛውም ክልል ተመሳሳይ ነገር ይነሳል፡፡ ጥያቄውን ማንሳት የሚችሉት ግን ሕጉ በሚፈቅደው መልኩ መሆን አለበት፡፡ በክልሉ ምክር ቤት የሚያረካ ውሳኔ ካልተሰጠ አቤቱታውን ይዘው ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት መምጣት ይችላሉ፡፡

እንደ ክልላችን መሰራት ያለባቸው ነገሮች ግን አሉ፡፡ በአንድ በኩል የኀብረተሰብ ክፍሎቹን ጥያቄ ምክንያት በማድረግ የብጥብጥ ማዕከል የሆነው እኛ ነን፡፡ እየተጎዳን ያለነው እኛ ነን፡፡ እየሞቱ ያሉት የእኛ ዜጎች  ናቸው፡፡ ስለዚህ ትክክለኛውን ጥያቄ ትክክለኛ ካልሆነው ጋር መለየት እንዲችል ኀብረተሰቡ ላይ ሰፊ ሥራ ማከናወን አለብን፡፡ ምክንያቱም ጎንደር አካባቢ አማራ ተበደለ እያሉ ጉዳዩን ከፍ አድርጎ የማስጮህ ነገር አለ፡፡ ይሄን በአስተሳሰብ ግልፅ ማድረግ ያስፈልጋል ተብሎ በተለይ በሰሜን ጎንደር አካባቢ የአመራር መልሶ ማደራጀቱ ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡ የክልል አመራር ድጋፉም ከሌሎች ዞኖች በተለየ እንዲደረግ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ ኀብረተሰቡ ጉዳዩን በትክክለኛው ሚዛን እንዲያየው ያስፈልጋል፡፡ ይሄን ግልፅ ማድረግ ይገባል በሚል የጋራ ስምምነት እየተሰራ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፦  የተጠቀሰውን የግንዛቤ ችግር ለመፍታት የተሄደው ርቀት በቂ ነው?

አቶ ይርሳው፦  በቂ ነው ብለን አናምንም፡፡ ምክር ቤቱ ያስቀመጠውም የበለጠ መስራት አለብን በሚል ነው፡፡ እንዲያውም በዚህ ጉዳይ ላይ ግልፅ ውይይት ሲደረግ ጎልቶ የታየው የግንዛቤ ችግሩ ነው፡፡ አንደኛ አንዳንዶች ትግራይ ውስጥ ያለው የወልቃይት አማራን ጥያቄ የአማራ ክልል መንግሥት እንደሚፈታው ያስባሉ፡፡ ‹‹ለምን አትፈቱም?›› ብሎ ይጠይቃል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ‹‹አማራ ተበደለ፤ ጥያቄ ያነሳ ሰው ታሰረ›› የሚለው ኀብረተሰብ ውስጥ በሰፊው ሰርጿል፡፡ ሦስተኛ አብረው የሚኖሩ ምናልባትም የተለየ ጥብቅ ትስስር ባላቸው ሕዝቦች መካከል ተገቢ ያልሆነ ቁርሾ ተፈጥሯል፡፡ ይሄን ቁርሾ መፍታት አለብን፡፡ ይሄን ለመፍታት ምክር ቤቱ ባስቀመጠው አቅጣጫ እየተሰራ ነው፤ ነገር ግን ከዚህ በላይ መስራት ይቀረናል፡፡

አዲስ ዘመን፦  ለጉዳዩ ከሚሰጥ አተረጓጎም ጋር በተያያዘ በምክር ቤቱ አባላት በኩልስ የሚታይ ክፍተት አልነበረም?

አቶ ይርሳው፦  አባላቱ የኀብረተሰቡ ወኪሎች በመሆናቸው ይሄ ችግር በምክር ቤቱ ሊጠፋ አይችልም፡፡ ከሕዝቡ ውስጥ ነው የወጡት፡፡ ሕዝቡ ውስጥ የአመለካከት ልዩነት አለ፡፡ ይሄ ልዩነት ከሕዝቡ በተቀዳ ምክር ቤትም ይኖራል፡፡ በውይይት ጊዜ በግልፅ የተለያዩ አቋሞች ይሰማሉ፡፡ እንደ ምክር ቤት ግን መናገር ያለብን ምን ሃሳብ ተነሳ? ሳይሆን የተነሱት ሃሳቦች በምን ተጠቃለሉ? በምን ተደመደሙ? የሚለው ነው፡፡

አዲስ ዘመን፦  በክልሉ አንዳንድ ዞኖች ፍትሃዊ የልማት ስርጭት አለመኖሩ ይነሳል፤ ይሄን ምክር ቤቱ እንዴት ያየዋል?

አቶ ይርሳው፦  ትክክል ነው፡፡ በተለይ ባለፉት 15 ዓመታት የመንግሥት አፈጻጸም ላይ ውይይት ሲደረግ የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ችግር በተለያየ ቦታ መኖሩን መገንዘብ ተችሏል፡፡ ምከር ቤቱ የደመደመው ነገር በተለይ የክልሉ ከፍተኛ ቆላማ እና ከፍተኛ ደጋማ አካባቢዎችን የልማት ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ መሰረታዊ ችግር እንዳለ ነው፡፡ የኑሮ ደረጃውም በዚህ መልኩ የሚገለጽ ነው፡፡ የሰሜን ጎንደር ቆላማ አካባቢዎች፣ የዋግህምራ ቆላማ አካባቢዎችና ሌሎችም ተመሳሳይ አየር ንብረት ያለባቸው አካባቢዎች ላይ የኀብረተሰቡ ተጠቃሚነት በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ በከፍተኛ ደጋማ አካባቢዎች የሚገኘው የኀብረተሰብ ክፍልም አሁንም በከፋ ድህነት ውስጥ ይገኛል፡፡ ስለዚህ በክልሉ ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነት ላይ  ችግር  ነበር  የሚል ግምገማ   ተደርጓል ፡፡

ምክር ቤቱ መሰረተ ልማት በተለይም መንገድን በተመለከተ በዚህ ዓመት አይደለም የገመገመው፡፡ በ2008 ዓ.ም በግልፅ ተወያይቶ ሰሜን ጎንደር አካባቢ የሚገኝ የመንገድ ትስስር መሰረታዊ ችግር አለበት ብሎ ለይቷል፡፡ ስለዚህ መንግሥት ይሄን ችግር መፍታት አለበት የሚል አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ አስፈጻሚውም ይሄን ይዞ ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመነጋገር በዚህ ዕቅድ ዘመን አብዛኛው የአስፋልት ሽፋናችን ሰሜን ሸዋና ሰሜን ጎንደር ላይ ነው፡፡ የገጠር መንገድም አብዛኛው ሰሜን ጎንደር እንዲሸፍኑ ተደርጎ እየተሰራ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በክልሉ ስድስት የልማት ኮሪደሮች በተፋሰስ ተለይተው ቢቀመጡም ያለውን አቅም ያህል እያለማን አይደለም በሚል ተገምግሟል፡፡ በመሆኑም ውጤታማ ማድረግ ቀጣዩ ሥራ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፦  ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ አለመጠናቀቅ ኀብረተሰቡን ከሚያማርሩ ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳል፤ በፕሮጀክቶች ቁጥጥር ላይ ያላችሁ ቁርጠኝነት ምን ያህል ነው?

አቶ ይርሳው ፦  በክልሉ የፕሮጀክት አፈጻጸም ላይ በጣም መሰረታዊ ችግር አለ፡፡ በ2007 ዓ.ም አንድ ጥናት ተደርጎ ፕሮጀክቶች ከተያዘላቸው የኮንትራት ጊዜ በላይ መውሰዳቸው አንድ ችግር ሆኖ ተለይቷል፡፡ ሁለተኛው ችግር በተቀመጠው የጥራት ደረጃ አለመሰራት ነው፡፡ ሦስተኛው ከአቅም በላይ የፕሮጀክቶች መለዋወጥ ነው፡፡ በዚህ ላይ ብቻ ሳይሆን የንብረትና ግዢ አስተዳደራችንም ችግር እንዳለበት ታይቷል፡፡ ስለዚህ በምክር ቤቱ በኩልም ዋና የትኩረት ነጥብ ሆኗል፡፡ በዚህ መልኩ እንሄዳለን አንሄድም የሚለውን አብረን የምናየው ይሆናል፡፡

አዲስ ዘመን ፦  ከክልሉ ውጪ የሚኖሩ የአማራ ክልል ተወላጆች ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥያቄዎችን ምክር ቤቱ እንዴት ይገመግመዋል ?

አቶ ይርሳው ፦ ምክር ቤቱ ይሄን ጉዳይ የዕለት ከዕለት አጀንዳው አድርጎ አያነሳም፡፡ ነገር ግን በተለያዩ አጋጣሚዎች ጉዳዮች ጥያቄዎች ተነስተው ውይይት ይደረጋል፡፡ ለምሳሌ የተለያዩ አካባቢዎች የክልሉን ተወላጆች ቅር የሚያሰኙ ድርጊቶች ተፈፅመውባቸው ነበር፡፡ ይሄን መነሻ አድርጎ ምክር ቤቱ ተመካክሯል፡፡ በሌሎች ክልሎች የሚኖሩ የክልሉን ተወላጆች መንግሥት መጠበቅ አለበት በሚል ውይይት ተደርጓል፡፡ መጨረሻ ላይ የተደረሰው ስምምነት እንደ መንግሥት ከሌሎች አካባቢ ከሚኖሩ አማራዎች ጋር ግንኙነት መፍጠር ያስፈልጋል የሚል ነው፡፡

ነገር ግን በመሰረታዊነት ሌላ ክልል ላይ የሚኖር አማራ መብት የሚከበረው በአማራ ክልል አይደለም፡፡ በመሰረታዊነት መብታቸው የሚከበረው በሚኖሩበት አካባቢ በሚኖር ሚዛናዊ አስተዳደር ነው፡፡ ስለዚህ እንደ አገር ሚዛናዊ አስተዳደር እንዲኖር ትግል ማድረግ አለብን፡፡ በታሪክ አጋጣሚ የአማራ ክልል ተወላጅ የሌለበት ክልል የለም፡፡ ስለዚህ በዚህ ሁሉ ክልል ተወካይ ልኮ ማስተዳደር አይቻልም፡፡ በመሆኑም የተጠቀሰው አስተሳሰብ እንዲኖር የራሳችንን ሚና መወጣት አለብን የሚል ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

አዲስ ዘመን፦  ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ይኖራል?

አቶ ይርሳው፦  እንደ አገርም እንደ ክልልም የተነሱ ችግሮች ነበሩ፡፡ አሁንም ሕዝባችን የሚፈልገው የተቆጠረ ሥራ ነው፡፡ የተነሳው ችግር ተፈትቶ ማየት ይፈልጋል፡፡ ለዚህም ማረጋገጫ የሚሆን ሪፖርት መስማት ይፈልጋል፡፡ ሌላው መስራት የማንችል ከሆነ መስራት ለምን እንደማንችል በግልፅ ማሳየት አለብን፡፡ ከዚህ ውጪ የሆነውን ነገር ሕዝቡ አይቀበልም፡፡ በተደጋጋሚ ሕዝቡ የሚለን ‹‹ችግር ታዳምጣላችሁ ግን አትፈቱም›› ነው የሚለን፡፡

ሁሉም የመንግሥት አካላት ችግሮችን ፈትተው ለሕዝቡ ማሳያት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተለያየ ምክንያት መፍታት የማይቻል ከሆነ ደግሞ በአሳማኝ ምክንያት ማስረዳት ይጠይቃል፡፡ ሕዝባችን ችግርን የመግለፅ ክፍተት የለበትም፡፡ ስለዚህ መፍትሄ የሚሰጥና የሚያገለግል መንግሥት መፈጠር አለበት፡፡ እኛም መስራት ያለብን የመንግሥት አካላት እውነትም ለሕዝቡ አገልጋይ እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡ ሕዝቡም የልማት ጥያቄ ሲያቀርብ አቅምን ባገናዘበ መልኩ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡      

አዲስ ዘመን ፦ ለትብብርዎ  በጣም እናመሰግናለን !

አቶ ይርሳው፦  እኔም አመሰግናለሁ !

ብሩክ በርሄ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።