‹‹የልማት ጥያቄዎች የሚመለሱት ህዝቡ ግብር ሲከፍል መሆኑን መግባባት ያስፈልጋል››- የአቃቂ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ቦጋለ ጉደታ

26 Jul 2017

የአቃቂ ወረዳ 28 ቀበሌዎች አሉት፡፡ በቅርበት የሚገኙት ዱከምና ገላን እንዲሁም አዲስ አበባ ከተማ አዋሳኞቹ ናቸው፡፡ በወረዳው ከ80ሺ በላይ ነዋሪዎች የሚገኙ ሲሆን፤ ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆነ አካባቢ  ነው፡፡

ወረዳው በመልካም አስተዳደር፣በፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ዙሪያ በተለይም በህገ ወጥ የመሬት ወረራ፣ በልማት ተነሺ የወረዳው አርሶ አደሮች ዙሪያ፣ በቀን ገቢ ግምት አሠራር እንዲሁም በመሳሰሉ ጉዳዮች ዙሪያ ትኩረት በማድረግ ከወረዳ አስተዳዳሪው አቶ ቦጋለ ጉደታ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡

አዲስ ዘመን፦ በአገር አቀፍ ደረጃ  እየተሠራ በሚገኘው የቀን ገቢ ግመታ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ቅሬታ ተሰምቷል። በእናንተ ወረዳስ በዚህ ዙሪያ የሚነሱ ቅሬታዎችን ህጋዊ መንገድን ተከትሎ  የመቀበልና የመፍታት ሁኔታ ምን ይመስላል ?

አቶ ቦጋለ፦ በወረዳችንም አንዳንድ ነጋዴዎች ከግመታው ጋር ተያይዞ ቅሬታቸውን ያቀረቡበት ሁኔታ አለ፡፡ ግመታውን አስመልክቶ ውይይት አድርገን ነበር፡፡ በዚያን ወቅት ስሜታቸው ጥሩ አልነበረም፡፡ ሆኖም  ሦስት ጉዳዮችን ልብ እንዲሉ መክረናቸዋል፡፡ በመጀመሪያ ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ማረጋጋት እንዳለባቸው ፤ ከውጭ ተጽዕኖ ነፃ መሆንና ከጠላት ከሚነዙ አሉባልታዎች መዋጥ እንደሌለባቸው  ነው የነገርናቸው፡፡ 

በሁለተኛ ደረጃ ግብር መክፈል የዜግነት ግዴታ እንደሆነ እንዲገነዘቡት አድርገናል፡፡ በሦስተኛ ደረጃም በልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ለህዝቡ በተፈጠረው የመናገር፣ የመሰብሰብ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ተሰጥቷል፡፡ ይህንን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ቅሬታን ባግባቡ የማቅረብ መብታቸውን እንዲጠቀሙበት አድርገናል፡፡ በውሃ፣ በጤና፣ በትምህርት ዘርፍ ያላቸው ጥያቄ ሊፈታ የሚችለው ህዝቡ ግብር ሲከፍል መሆኑን ባግባቡ በማስረዳት ለማረጋጋት ተችሏል፡፡ እንዲታይላቸው ያቀረቡትን ቅሬታም መንግሥት በሚያስቀምጠው መመሪያና አቅጣጫ መሰረት እንደሚታይ በመነጋገር ነው የተግባባነው፡፡

 ገማቾቹ ሥራ ከመጀመራቸው አስቀድሞ በኦሮሚያ አገር ውስጥ ገቢ ቢሮ በቂ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል፡፡ አሠራሩን በሚገባ የሚያውቁ ናቸው፡፡ እኔ የኮሚቴው ሰብሳቢ ነኝ፡፡ ኮሚቴው ሲዋቀር የነጋዴው ማህበረሰብ ተወካይ እንዲካተት ተደርጓል፡፡ ወደ ሥራ ከመገባቱ አስቀድሞ ሲገመት ተወካዮ፣ ህብረተሰቡና የኮሚቴው አባላት እንዲያውቁ  ነው የተደረገው፡፡

አዲስ ዘመን፦ ከጥልቅ ተሃድሶ በኋላ በወረዳችሁ የለያችኋቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮችና የህዝብ ቅሬታዎች እየፈታችሁ ያለበት ሂደት ምን ይመስላል ?

አቶ ቦጋለ፦ ከጥልቅ ተሃድሶ በኋላ የህዝቡን ቅሬታ በሦስት ደረጃ ለይተናል፡፡ በውሃ ስርጭት፣ በመንገድ ግንባታና በተለያዩ የልማት አውታሮች ላይ የነበሩ ችግሮች ብለን ለይተናል፡፡ በወረዳ ደረጃ ሊፈቱ የሚችሉ ችግሮችን በአንደኛ ደረጃ፣ በዞን ደረጃ የሚፈቱትን ችግሮች በሁለተኛ ደረጃ እንዲሁም በክልል ደረጃ የሚፈቱትን ደግሞ በሦስተኛ ደረጃ ብለን አስቀምጠናል፡፡ እኛ በደረጃችን ልንፈታ የምንችላቸውን ለመፍታትም እየሠራን እንገኛለን፡፡ በበላይ አካላት ሊፈቱ የሚገባቸውንም ለይተን ያደረስን ሲሆን፤ በተያዘው በጀት ዓመት በተሻለ መልኩ ችግሮችን ለመፍታት እየሠራን ነን፡፡

በወረዳ ደረጃ በተለይ ውሃን አስመልክቶ የጥገና ሥራዎችን የምንሠራ ሲሆን፤ ጥገናዎች በጥሩ ደረጃ ተሠርተዋል ማለት ይቻላል፡፡ በመንገድ ግንባታ የተጀመሩ ለበርካታ ዓመታት ሲንከባለሉ የቆዮና ተቋራጮቻቸው የጠፉትን ግንባታዎች በመለየት ውላቸው እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡ በምትኩ በሌሎች ተቋራጮች እንዲገነባ ውል የተሰጠበትና ተገንብቶ አገልግሎት እንዲጀምር የተደረገም አለ፡፡

ለአብነት ከአብኩሴራ - ዶዶታ-ጭሪ አራት ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የመንገድ ግንባታ በቅርብ ጊዜ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡ ሥራው ከ2005 ዓ.ም በፊት የተጀመረ ነው። ሆኖም ሲጓተት ቆይቶ አሁን በመልካም አስተዳደር ችግር ውስጥ ተይዞ እንዲጠናቀቅ ተደርጓል፡፡ ከአቡሎያ- ኦዳናቤይ የሚዘረጋውና ወደ 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው መንገድ የኮንትራት ውል ተገብቶ ግንባታው እየተከናወነ ይገኛል፡፡ የመንገድ ግንባታዎቹ ለብዙ ጊዜ ተቋራጮቻቸው በመጥፋታቸው የተጓተቱ ነበሩ፡፡

በቢሮ ደረጃም የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎትን ለማሻሻል ጥረት በመደረግ ላይ ነው፡፡ ሥራዎችን በአንድ ለአምስት አደረጃጀት መዋቅሩን በማጠናከር በየጊዜው ውይይት በማድረግ ህዝቡ የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኝ እያደረግን እንገኛለን፡፡

አዲስ ዘመን፦ ሠራተኛው የህዝብ አገልጋይነት መንፈሱ ምን ይመስላል ? የለውጥ መሳሪያዎችን የመጠቀም ሁኔታስ እንዴት ነው ?

አቶ ቦጋለ፦ የሥራ ሰዓትን ያለማክበር፣ የአገልጋይነት ስሜት ያለመኖር ወይም የስልጣን አተያይ ክፍተት ነበረበት፡፡ ስልጣንን የመኮፈሻ፣ የግል መገልገያ አድርጎ የማየት ችግር ነበር፡፡ እነዚህና የመሳሰሉ ችግሮች በጥልቅ ተሃድሶው ለይተን ለመቅረፍ ያስቀመጥናቸው ስለነበሩ ትኩረት ሰጥተን ሠርተንበታል፡፡ በተነጻጻሪነትም አሁን የተሻለ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በሲቪል ሰርቫንቱም የመጣ ለውጥ አለ፡፡ የስልጣን ምንጭ ህዝቡ እንደመሆኑ ህዝቡ የሰጠንን ስልጣን በአግባቡ ልናገለግል ይገባል የሚል አስተሳሰብ አሁን በተሻለ መልኩ አለ፡፡ ይህ ጥልቅ ተሃድሶው ያስገኘው ውጤት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ አሁንም የለየናቸው ችግሮች አሉ፡፡ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የጀመርናቸውን ሥራዎች አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡  

አዲስ ዘመን፦ በወረዳችሁ ህዝቡ ቅሬታ የሚያቀርብበትና ቅሬታውን ለመፍታት የሚያስችል ስርዓት አላችሁ ? ካለስ ትግበራው እንዴት እየተከናወነ ይገኛል ?

አቶ ቦጋለ፦ የቅሬታ አቀራረብና አፈታት ስርዓት ቀደም ሲልም በወረዳው ተዘርግቶ ሲሠራበት ነበር፡፡ አሠራሩ የተዘረጋው ከቢ ኤስ ሲ ትግበራ ጋር ተያይዞ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አሠራሩ ደካማ ነበር፡፡ አሁን አሠራሩን በማጠናከር በወረዳችን የተፈቱ ብዙ ቅሬታዎች አሉ፡፡ ለአብነትም በመሬት ዙሪያና በእርሻ ድንበር የነበሩ ቅሬታዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ቅሬታዎቹን በሰከነ መልኩ በመመልከት እንዲፈቱ በማድረግ የተሻለ ሥራ ተሠርቷል፡፡

አዲስ ዘመን፦ ሥራ የሌላቸውን ወጣቶች የማደራጀት፣ የመስሪያ ቦታ የማመቻቸትና ወደ ሥራ የማስገባት ጉዳይ እንዴት እየተከናወነ ይገኛል? የነበሩ ችግሮች ምን ምን እንደነበሩና እንዴት እየተፈታ  እንደሚገኝ ቢገልጹልኝ ?

አቶ ቦጋለ፦ ቀደም ሲል የብድር አሰጣጥ ክፍተት የነበረበት፣አሠራሩም በችግሮች የተተበተበበት ነበር፡፡ በተለይም ከጥልቅ ተሃድሶ በኋላ አሠራሩን በማሻሻል ለውጥ ለማድረግ ተችሏል፡፡ ብዙ ወጣቶች ተደራጅተው ተጠቃሚ እየሆኑ ናቸው፡፡ ወደ 44 የሚጠጉ ማህበራት ሰባት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ብር ብድር ወስደዋል፡፡ ማህበራቶቹ በከብት እርባታና ማደለብ፣ በእርሻ እንዲሁም በመስኖ ሥራ ተደራጅተዋል፡፡ እነዚህን የሥራ መስኮች መሰረት በማድረግ የወረዳችን ወጣቶች ወደ ሥራ ገብተው እየተንቀሳቀሱ ሲሆን፤ ብራቸውን ቆጥበው ለአምና የተያዘው ብድር በማለቁ ዘንድሮ ተጠቃሚ ለመሆን ተደራጅተው ገንዘብ ለማግኘት እየተጠባበቁ የሚገኙ ማህበራት አሉ፡፡

አዲስ ዘመን፦  በልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን በማቋቋም በኩል እየተሠሩ ያሉ ተግባራት አሉ ?

አቶ ቦጋለ፦  ለኢንቨስትመንት ተብሎ የተነሱ ግለሰቦች ወይንም አባ ወራዎች ነበሩ፡፡ እነዚህን ለማቋቋም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት  ባቀረበልን ጥያቄ መሰረት ወደ 280 የሚሆኑ ግለሰቦችን አጣርተንና በወረዳችን ዋና ኮሚቴ ታይቶ ልከናል፡፡ ይህ በቅርብ የተከናወነ ነው፡፡ የክልሉ መንግሥትም ጉዳዩን ተመልክቶ ምላሽ እንደሚሰጥ አምናለሁ፡፡ 

አዲስ ዘመን፦ ወረዳችሁ ለህገ ወጥ የመሬት ወረራ የተጋለጠ ነው፡፡ በዚህ በኩል የሚገጥማችሁ ህገ ወጥ ተግባርና የመልካም አስተዳደር ችግር ካለ ቢነግሩኝ ?

አቶ ቦጋለ፦ በወረዳችን ለህገ ወጥ የመሬት ወረራ የተጋለጡ የተወሰኑ ቀበሌዎች አሉ፡፡ የጁ፣ ግማሼ፣ ገላና አራብሳና ኦዳናቤ ቀበሌዎች ለህገወጥ ተግባሩ ተጋላጭ ናቸው፡፡ በእነዚህ ቀበሌዎች ህገ ወጥ የመሬት ወረራ በማድረግ በሽያጭ መሬት እንዳይተላለፍ የሚመራውን ዘርፍ በማጠናከር አሠራር ዘርግተን እየሠራን ነው፡፡ አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙትን ህገ ወጥ ድርጊቶችም በመከታተል እንዲፈርሱ እያደረግን ነው፡፡ ሆኖም የበጀት እጥረት ስላለብን ሙሉ በሙሉ ሄደንበታል ማለት አይቻልም፡፡ በቀጣይ ግን በከፍተኛ ደረጃ አቅደንበት ከምንተገብራቸው ሥራዎች መካከል አንዱ ይሆናል፡፡

አዲስ ዘመን፦ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለዎት ዕድሉን እንስጦት?

አቶ ቦጋለ፦ የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም የኦሮሚያ ክልል ህዝብ ከውጭ ተጽዕኖ ነፃ መሆን አለበት፡፡ ቅስቀሳ ከሚያደርጉ የጠላት ኃይሎች መጠንቀቅ አለበት፡፡ የሚቃጠለው፤  የሚወድመው ንብረት የራሱ ነው፡፡ የሀገር ነው። ንብረት በማውደም ልማትን ማምጣት አይቻልም፡፡ ስለዚህ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ ይገባል፡፡ ሰላም እንዲሰፍን ደግሞ ህዝቡ ለሰላሙ መጠበቅ አጋር መሆን አለበት፡፡ አገርን ማልማት፣ በሰላም ወጥቶ መግባት የሚቻለው ሰላም ሲኖር በመሆኑ ለሰላም ህዝቡ ዘብ መቆም አለበት፡፡

አዲስ ዘመን፦ ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ እናመሰግናለን።

አቶ ቦጋለ፦ እኔም አመሰግናለሁ

ዘላለም ግዛው

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።