«ኢትዮጵያ ደሃ ናት ሲባል አልወድም»- አምባሳደር በላይነሽ ዘባዲያ በኢትዮጵያ የእሥራኤል አምባሳደር Featured

26 Jul 2017

አምባሳደር በላይነሽ ዘባዲያ ትውልዳቸውና እድገታቸው እዚሁ ኢትዮጵያ ከጎንደር 25  ኪሎ ሜትር ወጣ ብሎ በሚገኘውና አምቦበር በሚባል አካባቢ ነው። የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በትውልድ መንደራቸው በሚገኘው የቤተ እሥራኤላዊያን ትምህር ቤት፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በአዲስ አበባ ኮከበ ጽባህ ትምህርት ቤት  ተከታትለዋል። በትምህርታቸው የቀለም ቀንድ የሚባሉ ነበርና አንደኛ ደረጃን በአንድ ዓመት ሁለት ክፍልን እየተማሩ አጠናቀዋል፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም ጎበዝ ተማሪዎች ብቻ ተመርጠው በሚማሩበት ልዩ ክፍል ውስጥ ነው የተከታተሉት።

የሁለተኛ ደረጃ ማጠናቀቂያ ፈተናን በድል በመቋጨታቸውም በ16 ዓመታቸው አሥመራ ዩኒቨርሲቲ ኢንጅነሪንግ እንዲያጠኑ ተመደቡ። በዚህ ዕድሜያቸው ከቤተሰብ መራቁ እሥራኤል ለሚኖሩት ወንድማቸው አልተዋጠላቸውም። ስለሆነም ወደ እሥራኤል እንዲሄዱ ሁኔታዎችን አመቻችተውላቸው የነፃ ትምህርት ዕድል አግኝተው እአአ በ1984 አገራቸውን ተሰናብተው ወደ እሥራኤል አቀኑ። እዚያም ከወንድምና እህታቸው ጋር ኑሮን የጀመሩት አምባሳደር በላይነሽ በ23  ዓመታቸው ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ይዘው የእሥራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትን እአአ በ1993 ተቀላቀሉ።

ከዚያስ? አዲስ ዘመን ከአምባሳደር በላይነሽ ዘባዲያ ጋር ሰፋ ያለ ቆይታ ነበረው። በቆይታችንም ስለ ኢትዮ-እሥራኤል ግንኙነትና መሰል ተያያዥ ጉዳዮች መረጃዎችን አቀብለውናል። ከአምባሳደሯ ጋር ያደረግነውን ቆይታም እንዲህ አቅርበነዋል። 

አዲስ ዘመን፡- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ከተቀላቀሉ በኋላ የመጀመሪያ ተልዕኮዎ ኢትዮጵያ ሆነች?

አምባሳደር በላይነሽ፡- አይደለም። ብዙ ዓመት የሠራሁት አሜሪካ ነው። ለተወሰኑ ዓመታት በተባበሩት መንግሥታት የእሥራኤል ተልዕኮን ይዤ ሠርቻለሁ። በአሜሪከ ቺካጎ ኮንሱል ነበርኩ፤ ከዚያ በኋላ ሂውስተን ቴክሳስ ነበርኩ። ከአሜሪካን በኋላ ወደ እሥራኤል ተመልሼ ነው እአአ በ2012 ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁት።   

አዲስ ዘመን፡- ወደ ኢትዮጵያ የተመደቡበትን አጋጣሚ ቢነግሩኝ?

አምባሳደር በላይነሽ፡- ዕውነት ለመናገር በመጀመሪያ ወደዚህ ለመምጣት አልፈለኩም ነበር። ምክንያቴም ወደዚህ ከመጣሁ የአምባሳደርነትን ሥራ በሚገባ ጠንቅቄ አውቄ ውጤታማ መሆን እፈልግ ስለነበር ነው። እንዲያውም ቦታው ለውድድር ክፍት ሲሆን አንድ አንድ ሰዎች ለምን አታመለክቺም? አሉኝ። እኔ ግን ባልኩት ምክንያትና ገና አራስም ስለነበርኩ እነሱ ላይ ባተኩር ይሻላል ብዬ እንቢ አልኩ።

በመጨረሻ ግን ሞራሌ ተነሳሳና አመለከትኩ። ከእኔ ጋርም ስድስት ሰዎች ለውድድር ቀረብን። ተወዳዳሪዎቼ ከእኔ በዕድሜም በልምድም የሚበልጡ በጣም ታላላቅ ሰዎች ነበሩ። ከዚህ በፊትም የአምባሳደርነት ልምድ ያላቸው ናቸው። እኔ ደግሞ የአምባሳደርነት ልምዱ የለኝም። ስለሆነም የሚመረጡት እነሱ ናቸው ብዬ ደመደምኩ። ምርጫው የሚካሄደው በኮሚቴ ስለሆነ ኮሚቴው ውድድሩን የሚያካሂደው በደንብ አጣርቶ ጀርባችንን መርምሮ ነው።

የሆነው ሆኖ ድንገት የጠራው የእጄ ስልክ ኢትዮጵያ መመደቤን አበሰረኝ። በጣም ደነገጥኩ። በወቅቱ በድንጋጤ ውስጥ ሆኜ ጓደኞቼ ያነሱኝን ፎቶ በየቦታው በትነውት ነበር። በጣም አስገራሚ ቅፅበት ነበር። እኔ እንዴት እነዚያን ሰዎች ላሸንፍ ቻልኩ፤ በሚል በደስታና በግርምት ውስጥ ሆንኩ። በኋላ ደግሞ የመጣብኝ ሃሳብ ሁለቱም የእኔ አገሮች ናቸው። እዚያ ሄጄ ውጤታማ ባልሆንስ? የሚለው  ደግሞ በጣምም ያስጨንቀኝ ጀመር።

እኔ በዚህ ጭንቀት ውስጥ ሆኜ ቴሌቪዥኑ፣ ጋዜጣው ሁሉ የሚያወራው ስለ እኔ ሆነ። ሰውም ይደውላል። ይሄ ይሄ ሁሉ የባሰ ሃሳብ ውስጥ ጨመረኝ። ቤተሰቦቼ ደግሞ በተቃራኒው በደስታ ሊሞቱ ደረሱ። የእኔ እዚያ መድረስ ልዩ ደስታን ፈጠረላቸው። በመጨረሻ ግን ራሴን ማዘጋጀት ጀመርኩ። ምርጫው የተካሄደው የካቲት ወር ላይ ነበር፤ ወደዚህ እስከ መጣሁበት ነሐሴ ወር ድረስ ሰፊ ዝግጅት አደረኩ። በዚህም ወደ ኢትዮጵያ ኤምባሲ ሄጄ ብዙ ነገሮችን አነበብኩ። ምን ማድረግ አለብኝ በሚለው ዙሪያ ጥሩ ዝግጅት አደረኩ።

ልክ ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣሁ መጀመሪያ ያደረኩት ሴት አምባሳደሮችን እየዞርኩ ማነጋገር ነበር። የጀርመን፣ ብራዚል፣ ኦስትሪያ፣ ኬንያ አምባሳደሮች ሴቶች ነበሩ። ከእነሱ ጋር ጥሩ ውይይት አደረኩ፤ ልምድም ቀሰምኩ። በተጠራሁበት ቦታ ሁሉ እሄድ ነበር፤ ምክንያቴ ደግሞ ሰውን ለመግባባትና የሥራ ሂደቱን ለማወቅ መፈለጌ ነው።

የተረከብኩት ባዶ ቢሮ ነው፤ ሥራውን ያስተላለፈልኝ ሰው አልነበረም። በራሴ ነው የጀመርኩት። እሥራኤል አምባሰደር የነበሩትን አምባሳደር ቆንጅትን አግኝቼ በጣም አማክሬያቸዋለሁ። በአጠቃላይ ሊረዱኝ የሚችሉ ሰዎችን ሁሉ እየደወልኩ አገኘኋቸው። በተጓዳኝም አማርኛዬን ማሻሻል ጀመርኩ። በተለይ ማንበብ ላይ ብዙም አልነበርኩም፤ ስለሆነም የክቡር ዶክተር ከበደ ሚካኤል ግጥሞችን እያነበብኩ ክህሎቴን አሻሻልኩ። በዚህ መልኩ የተጀመረው ሥራ ቀስ እያለ እየተጓዘ ዛሬ እዚህ ላይ ደርሷል።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያን ተሰናብተው ከሄዱ እአአ ከ1984 በኋላ ተመልሰው የመጡት እአአ በ2012 ነው። ድጋሚ ወደ ትውልድ አገርዎ ሲመለሱ ምን ታዘቡ?

አምባሳደር በላይነሽ፡- በጣም ብዙ ለውጦችን ታዝቤያለሁ። በተለይ አዲስ አበባና ባህርዳር ላይ ትልቅ ለውጥ ተመልክቻለሁ። እንደ አገርም ኢትዮጵያ ብዙ ቢቀራትም ብዙ አድጋ ነው ያገኘኋት። ኢትዮጵያ ደሃ ናት ሲባል አልወድም፤ የታደለችና ሀብታም አገር ናት፡፡ ድህነቱ የአስተሳሰብ ነው። እሱም ቢሆን አሁን አሁን ሰው እየገባው ነው።

እሥራኤል ከተመሰረተች 69 ዓመቷ ነው። እኔ ወደ እሥራኤል አገር ስሄድ ዴርሼባ ፍፁም በረሃ ነበር። አሁን ያንን አልምተን፤ ቆፍረን ውሃ አውጥተን የባህር ዳር መዝናኛ ሳይቀር ተሰርቷል። በምንም የማይታሰብና የማይጠረጠር ነው። እሥራኤል በጣም ብዙ ቴክኖሎጂ አላት። የእኔ ምኞትና ፍላጎትም ያንን ቴክኖሎጂ ወደ ኢትዮጵያ ማምጣት ነው። ይህችን የመሰለች አገር፣ ለም መሬት የሞላባት፣ ዝናብ በየአመቱ የማይነጥፍባትን አገር እንዴት ነው መለወጥ የሚቻለው? የሚለውን ነው የማስበው። ኢትዮጵያ ውስጥ በአንድ ዓመት የሚዘንበው ዝናብ እሥራኤል 10 ዓመት የሚዘንበው ነው። እሥራኤል ውሃ የላትም፤ ነገር ግን ለሌሎች አገራት ውሃ እንልካለን። የሜዲትራኒያንን ባህርና ቆሻሻ ውሃን እናጣራለን። እዚህ አገር የጠፋው ቴክኖሎጂ ነው፤ ያንን እናመጣለን።

ኢትዮጵያ ውስጥ ህዝብ እየጨመረ ነው። ለውጡም በዚያው ልክ መጨመር አለበት። ዛሬም ድረስ ዝናብ ተጠብቆ እርሻ የሚያካሂዱ አካባቢዎች አሉ። እንደዚህ መሆን የለበትም። በዓመት ሦስትና አራት ጊዜ ማምረት ያስፈልጋል። በእርግጥ ሦስትና አራት ጊዜ የሚያመርቱ አሉ። ነገር ግን ሁሉም መሆን አለበት። ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉንም አካባቢ ሄጄ ተመልክቻለሁ። ለምሳሌ አፋር ቢለማ አይደለም ኢትዮጵያን አፍሪካን ሊመግብ የሚችል ቦታ ነው። ብዙውን ጊዜ የሚሄደው ከእሥራኤል የግብርና ኤክስፐርቶች ጋር ነው። እናም የሚነግሩኝ ቦታው በጣም ለም እንደሆነ ነው። ይሄን ይሄን ስሰማ በየቀኑ የማስበው እንዴት ነው ኢትዮጵያን ማልማት የሚቻለው እያልኩ ነው። ምክንያቱም በረሃማዋ እሥራኤል ለምታ አይቻለሁና።

አዲስ ዘመን፡- የኢትዮ-እሥራኤል ግንኙነት ዕድሜ ጠገብ የሚባል ነው። መደበኛ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ከተጀመረ ወዲህ ያለውን እንመለከትና፤ እርሰዎ በየዘመኑ የነበረውን ግንኙነት እንዴት ይገልፁታል?

አምባሳደር በላይነሽ፡- በ1960ዎቹ እና 1970ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ያለውን ዕውነታ ብትመለከት የእኛ ትልቁ ኤምባሲ የነበረው አዲስ አበባ ውስጥ ነው። ጥሩ ጥሩ ነገሮች ነበሩ። አሁን ግን በጣም ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሷል። እኔ ከመጣሁ ጀምሮ ያለውን ዕውነታ ብትመለከት ለምሳሌ ብዙ ሚኒስትሮች ወደዚህ መጥተዋል፤ ወደ እሥራኤልም ሄደው ጎብኝተዋል ። ከዚያ በኋዋላ ያለው ትልቁ የዲፕሎማሲ ስኬት የእኛ ጠቅላይ ሚኒስትር ወደዚህ መምጣት ነው፡፡ የእናንተም ወደዚያ ሄደዋል። ከዚህም በላይ በጉብኝቱ ወቅት መሪዎቹ የተነጋገሯቸው ከተተገበሩ ትልቅ ነገር ይደረሳል ብዬ ነው የማስበው።

እሥራኤል የኢትዮጵያን ማደግና መረጋጋት በጣም የምትወድ አገር ናት። ኢትዮጵያም ተመሳሳይ ፍላጎት ነው ያላት። የእኛ ታሪክ የተያያዘ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ሳይቀር ብዙ ጊዜ ስሟ የተጠቀሰው ኢትዮጵያ ናት። ያ ማለት የደም ትስስርም አለን ማለት ነው። ዛሬ እሥራኤል ውስጥ 140 ሺህ የሚደርሱ ኢትዮጵያዊያን ቤተ እሥራኤሎች ይኖራሉ። ይሄ ሁሉ ካለን አብረን ለምን አንሠራም? ብለው ሁለቱ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ተነጋግረዋል። ለምሳሌ በኢትዮጵያ ውስጥ የእርሻ ቦታ ቢሰጠን በጣም ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ሥራ መሥራት እንችላለን፡፡ እኛ ቴክኖሎጂው አለን። እሥራኤልን ችግር ነው ያስተማራት። የምንኖርበት አካባቢ ያልተረጋጋ ሁከት የማያጣው ነው። ውሃ ራሳችን ካልፈጠርን የምንጠጣው ሳይቀር ልናገኝ የምንችልበት ዕድል የለም። ከሌላ አገር አመጣለሁ ማለት የማይቻል ነው፡፡ ምክንያቱም መንገድ ላይ ምን ሊሆን እንደሚችል ስለማይታወቅ የማይሆን አማራጭ ነው። ምክንያቱም ጎረቤቶቻችን ከእኛ ጋር ጥሩ ግንኙነት የላቸውም። በዚህም ምክንያት ከችግሮቻችን ተምረን እዚህ ደርሰናል። 

አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ እያሉኝ ያለው ከነበረው ግንኙነት አሁን ያለ የተሻለ ነው ማለት ነው?

አምባሳደር በላይነሽ፡- አዎን።

አዲስ ዘመን፡- አንድ አንድ ወገኖች ግን በተለይ በንጉሡ ዘመን የነበረው ግንኙነት በጣም ጠንካራ ነበር የሚል መከራከሪያን ያነሳሉ፡፡

አምባሰደር በላይነሽ፡- ዕውነት ነው ነበረ። ነገር ግን በአንድ ቀን የተመሰረተ አይደለም። ንጉሡ እዚያ ኖረዋል። ትልቁ ኤምባሲያችንም የነበረው እዚህ ነው። እዚያ ለመድረስ ብዙ ሂደት አልፏል፡፡ አሁን ያለንበት ዘመንም በጣም ጥሩ ደረጃ ላይ ነው ተብሎ የሚገለጽ ነው። ከዚህም በላይ እንደሚሆን በጣም እርግጠኛ ነኝ። የእሥራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ኢትዮጵያን ሲጎበኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ያ ትልቅ አዎንታዊ ተጽዕኖ አለው። የጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያምም ወደዚያ መሄድ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።

አዲስ ዘመን፡- በደርግ ዘመን ላይ የኢትዮጵያና እሥራኤል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተቋርጦ ነበር። ያንን ዘመን እንዴት ያስታውሱታል፤ እንደ እሥራኤል አምባሳደርስ ያ ግንኙነት ባይቋረጥ ኖሮ እዚህ ደረጃ ላይ እንደርስ ነበር የሚሉት ነገር ይኖር ይሆን?

አምባሳደር በላይነሽ፡- የሁለቱ አገራት ግንኙነት የተቋረጠው እአአ ከ1973 እስከ 1989 ሲሆን፤ ያን ጊዜ ኤምባሲያችን ሥራ አይሠራም ነበር። ቪዛ አገልግሎት ይሰጥ የነበረው በስዊድን ኤምባሲ በኩል ነው። እኔ ራሴ ቪዛ ያገኘሁት እዚያ ነው። እዚህ የነበሩ ቤተ እሥራኤላዊያን ብዙ መከራን አሳልፈዋል። የእኔ ወንድም ለምሳሌ ብነግርህ እስር ቤት ነበር። ተደብድቧል፤ አሁንም ድረስ ጤነኛ አይደለም። ብዙ መከራ ያሳለፍንበት ዘመን ነበር። እኔ የማስታውሰው ያ ዘመን ጥሩ እንዳልነበር ነው። አሁን ግን ያ ተቀይሯል።

አዲስ ዘመን፡- እኔ በግሌ ያለኝ አስተያየት ግን በንጉሡ ዘመን የነበረው አይነት ግንኙነት በደርግ ዘመንም ቢቀጥል ኖሮ ዛሬ ኢትዮጵያና እሥራኤል የሚፈራረሙት አዲስ ነገር ይኖራል ብዬ አላምንም፡፡ የተግባር ዘመን ይሆን ነበርም እላለሁ፡፡ እርስዎስ እንደዚህ አይነት ስሜት የለዎትም?

አምባሳደር በላይነሽ፡- ያንን ዘመን እንተውና አሁን ምን ማድረግ አለብን? ወደፊት ምን ማድረግ እንችላለን? እዚያ አይነት ግንኙነት ላይ ለመድረስ ምን መሥራት እንችላለን? የሚለውን ነው ማየት ያለብን፡፡ ያለፈው አለፈ፡፡ ጠቃሚውም ይሄ ይመስለኛል፡፡

እሥራኤል በእርሻ በጣም ጥሩ ቴክኖሎጂ አላት፤ ያ መምጣት አለበት፡፡ በእርሻ ብቻ አይደለም፤ በመሰረተ ልማት፣ በኢንዱስትሪ ያሉ ቴክኖሎጂዎች መምጣት አለባቸው፡፡ ሰሊጥ ሽጦ ዘይት ከመግዛት ሰሊጡን እዚሁ ዘይት ማድረግ ይቻላል፤ ቲማቲም ሸጦ የቆርቆሮ ቲማቲም ማስገባት መቆም አለበት፡፡ እኔ የማስበው እንደዚህ አይነት ነገሮችን ማምጣት ነው እንጂ የንጉሡ ዘመን ቢመጣ ኖሮ እያልኩ አይደለም፡፡

አዲስ ዘመን፡- ጥሩ፤ የሁለቱ አገራት ግንኙነት አሁን ያለበት ደረጃስ በእርግጥ ሁለቱም አገራት በሚፈልጉት ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት ይቻላል?

አምባሳደር በላይነሽ፡- ገና አልደረሰም፤ መንገድ ላይ ነን፡፡ የእየሩሳሌም ሀውልት በአንድ ቀን አልተሠራም፡፡ መሰረቱ ተጥሏል፡፡ ከዚህ በኋላ መገንባት ነው የሚጠበቅብን፡፡ የሁለቱ መሪዎች መገናኘት ትልቅ  ነገር ነው፡፡ መቶ በመቶ እርግጠኛ ሆኜ የምነግርህ ግንኙነቱ ጽኑ በሆነ መሰረት ላይ መጣሉን ነው፡፡ አሁን የሥራ ጊዜ ነው፡፡ ዋናው ነገር አገራቱ መተማመን መቻላቸው፤ በሁለቱም አገር ዘንድ ፍቅር መኖሩ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ አለ፡፡

አዲስ ዘመን፡- እስኪ የእሥራኤል እጆች የገቡባቸውን ዘርፎች እንመልከት፡፡ ለመሆኑ በአሁኑ ወቅት እሥራኤል በምን በምን ዘርፎች ላይ ወደ ኢትዮጵያ ገብታለች አምባሳደር?

አምባሳደር በላይነሽ፡- ኢንቨስትመንቱን እናስቀድም፡፡ በኢንቨስትመንት መስክ ያለው ትልቁ የጠብታ መስኖ ነው፡፡ ይሄ ኢንቨስትመንት ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያለው ነው፡፡ ከዚህም በላይ ደግሞ ጌጋ ዋት የሚባል የጸሐይ ብርሃን ቴክኖሎጂ ሥራ አለን፡፡ ይሄ ኢንቨስትመንትም ጥሩ እየሄደ ያለ ነው፡፡ ሌሎችም የ30 እና 40 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው ኢንቨስትመንቶች አሉን፡፡ ሌሎች ትልልቅ ኢንቨስትመንቶችንም መጀመር እንፈልጋለን፡፡ ለምሳሌ በቅርቡም ከሆቴል ጋር የተያያዘ ትልቅ የገበያ አዳራሽ መገንባት የሚፈልግ ባለሀብት ይመጣል ብለን ተስፋ አድርገናል፡፡ እንደዚህ አይነት ባለሀብቶች አሉን፡፡ እኛ የምናመጣቸው በእሥራኤል ጥሩ ታሪክ ያላቸውን ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት የሁለቱ አገራት የንግድ ልውውጥ መጠን ምን ያህል ደርሷል?

አምባሳደር በላይነሽ፡- የንግድ ልውውጥ መጠናችን አሁን ከ120 ሚሊዮን ዶላር በላይ ደርሷል፡፡ እኔ ስመጣ 30 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ እያደገ ነው፡፡ ይሄ ጥሩ ጅምር ነው፡፡ በልማቱ መስክ ያየህ እንደሆነ ጥሩ የሚባል ደረጃ ላይ ነው፡፡ በዚህ ወር መጨረሻ በእኛ የልማት ባለሙያ ድጋፍ ከሚደረግላቸው ፕሮጀክቶች ማሳ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ አቦካዶ ለውጭ ገበያ ይላካል፡፡ በዚህ እንኮራለን፡፡

አዲስ ዘመን፡- በግብርናው መስክ እያደረጋችሁት ያለውን ድጋፍ እንዴት ይመለከቱታል፤ በሌሎች መስኮችስ ያለው ድጋፍ ምን ይመስላል?

አምባሳደር በላይነሽ፡- ወደ መስክ ስወጣ የማነጋግራቸው አርሶ አደሮች የሚነግሩኝ በጣም ተጠቃሚ እየሆኑ መሆኑን ነው፡፡ ለምሳሌ ባህርዳር ላይ አንዱ አርሶ አደር 80 ሺህ ብር በዓመት እንደሸጠ ነግሮኛል፡፡ ነቀምቴ ላይም አንድ አርሶ አደር ሁለት ሺህ 400 ችግኝ በየዓመቱ አፈላለሁ፤ አንዱን ችግኝ 40 ብር ሂሳብ እሸጣለሁ ብሎኛል፡፡ እሱን አይተው ጎረቤቶቹም በተመሳሳይ ሥራ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ይሄ የሚያሳየን ለአርሶ አደሩ የዕውቀት ሽግግር እየፈጠርንለት መሆኑን ነው፡፡ እኔን የሚያስደስተኝ ይሄ ነው፡፡ በየዓመቱም 80 ኢትዮጵያዊያንን ለተመሳሳይ ዕውቀት ግብይት ወደ እሥራኤል እንልካለን፡፡ ሌሎች ለአጭር ጊዜ ስልጠናም የምንልካቸው አሉን፡፡    

በጤናው መስክም የእሥራኤል ሐኪሞች ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ ህክምና ይሰጣሉ፡፡ በተለይም የህፃናት ሐኪሞች በተደጋጋሚ ይመጣሉ፡፡ ከጣሊያን የልማት ኮርፖሬሽን ጋር በመሆን ህክምና ይሰጣሉ፡፡ ለምሳሌ በቅርቡም አይተህ ከሆነ የህፃናት የልብ ህክምና ባለሙያዎች መጥተው ህክምና ሰጥተዋል፡፡ የዓይን ህክምና ባለሙያዎችም በተመሳሳይ እየመጡ እስከ 10 ሺህ ለሚደርሱ የዓይን ሞራ ችግር ላለባቸው ሰዎች ህክምና ይሰጣሉ፡፡ እንዲያውም ጂንካ ላይ አንድ የህክምና ክሊኒክ ውስጥ ድጋፍ የሚያደርግ እሥራኤላዊ አለን፡፡

እዚህ ከሚደረገው የህክምና ድጋፍ በተጨማሪ እሥራኤል አገር የሚሰለጥኑ ኢትዮጵያዊያን ዶክተሮችም አሉ፡፡ ለምሳሌ አንድ የልብ ቀዶ ህክምና ባለሙያ በቅርቡ ስልጠናውን ጨርሷል፡፡ ሌሎች ላይም ተመሳሳይ ስልጠናዎችንም እየሰጠን ነው፡፡ በየዓመቱ ከ50 እስከ 60 ህፃናት ወደ እሥራኤል እየሄዱ ህክምና ይወስዳሉ፡፡ ይሄ በቂ ነው ማለት አይደለም፡፡ ግን መጀመሩ ጥሩ ነገር ነው፡፡

አዲሰ ዘመን፡- ምናልባት በእርዳታ በኩል እሥራኤል የምታደርገው ድጋፍ ይኖር ይሆን?

አምባሳደር በላይነሽ፡- አዎን አለ፡፡ ለምሳሌ ባለፈው በተከሰተው ድርቅ ላይ የህፃናት ምግብ ድጋፍ አድርገናል፡፡ ብዙም ባይሆን የቻልነውን ያህል አድርገናል፡፡ አሁን ደግሞ አፋር አካባቢ የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር አለ፡፡ ይሄንን ችግር ለመቅረፍ የአዋሽ ወንዝን አጣርቶ የሚያቀርብ ቴክኖሎጂ ድጋፍ ለማድረግ ከክልሉ ፕሬዚዳንት ጋር እየተነጋገርን ነን፡፡ እሥራኤል በጣም ትንሽ አገር ናት፡፡ ያለን ሀብት የዕውቀት  እንጅ የገንዘብ አይደለም፡፡ ስለዚህ ዕውቀታችንን ማስተላለፍ እንፈልጋለን፡፡ የምንከተለው አሣ መስጠትን ሳይሆን አሣ እንዴት እንደሚጠመድ ማስተማርን ነው፡፡ ለዚያም ነው የእሥራኤል የግብርና ኤክስፐርቶች ሁሌም እዚህ ያሉት፡፡

አዲስ ዘመን፡- ወደ ሌላ ጉዳይ ልውሰድዎ፡፡ የቤተ እሥራኤላዊያን ጉዳይ አንዴ ይነሳል፤ ሌላ ጊዜ ቆመ ይባላል፡፡ እዚህ ያሉ ቤተ እሥራኤላዊያን ጉዳይ መጨረሻቸው ምንድን ነው፤ በትክክልስ ቁጥራቸው ምን ያህል እንደሆነ ይታወቃል?

አምባሳደር በላይነሽ፡- ይሄንን ጥያቄ እኔ በትክክል ልመልስልህ አልችልም፡፡ ምክንያቱም እንደ አምባሳደር ይሄ የእኛ ሥራ አይደለም፡፡ ከአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከአይሁድ ኤጀንሲ የሚመጡ ሰዎች ናቸው ይሄንን ሥራ የሚሠሩት፡፡ እኔ የማወቀው ግማሽ ቤተሰባቸው እዚያ ያሉ ግማሹ ደግሞ እዚህ ያሉ ቤተ እሥራኤላዊያን እንደሚሄዱ ነው፡፡ ቤተሰቦቻቸው እዚያ ያመለክታሉ ሂደቱን ጠብቆ ይሄዳሉ፡፡ ቁጥሩ ግን ይሄን ያህል ነው ልልህ አልችልም፡፡ እንደ ኤምባሲም ይሄንን ሥራ እኛ አንሠራም፡፡

አዲስ ዘመን፡- እርስዎ እንደ አምባሳደር አሳካሁት ወይንም አስመዘገብኩት የሚሏቸው ድሎች ምን ምን ናቸው ቢባሉ ምን ይላሉ አምባሳደር?

አምባሳደር በላይነሽ፡- እኔ በጣም ዕድለኛ ነኝ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ወደ ዚህ በማምጣቴ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምንም ወደ ዚያ መውሰዴ እንዲሁ፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በእሥራኤል የተደረገላቸው አቀባበል ለሌሎች ተደርጎ የማያውቅ ነው፡፡ የእኛ ጠቅላይ ሚኒስትር መኖሪያ ቤታቸው እንግዳ አይጋብዙም፡፡ ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኋላ በጠቅላይ ሚኒስትራችን መኖሪያ ቤት እራት የተጋበዙት ሚኒስትር ኃይለማርያም ብቻ ናቸው፡፡ ይሄ ሁሉ በእኔ ጊዜ መሆኑን ሳስበው ያስደስተኛል፡፡ አንድ ዲፕሎማት በሥራ ዘመኑ ይሄንን አይነት ጉዳይ ነው መመልከት የሚፈልገው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ስለዴር ሡልጣን እንነጋገር፡፡ የዴር ሡልጣን ጉዳይ የሃይማኖት ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ የአገር ጉዳይም ነው የሚሉ አሉ፡፡ የዚያ ገዳምን ጉዳይ በተመለከተ የእሥራኤል መንግሥት አቋም ምንድን ነው?

አምባሳደር በላይነሽ፡- የእሥራኤል መንግሥት ችግሩን ተረድቶታል፡፡ ለምሳሌ መሠራት ያለበት የገዳሙ አካባቢ መሠራት አለበት፡፡ በቅርቡም አካባቢውን ለመመልከት መሀንዲሶች ሄደው ነበር፡፡ ችግር እንዳለ እናውቃለን፡፡ ይሄንን ችግር ለመፍታት እንፈልጋለን፡፡ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሄዱ በኋላ ውይይት ተደርጓል፡፡ የኢትዮጵያ ይዞታ በጣም ጠቃሚ በሚባለው የእየሩሳሌም አካባቢ ላይ ነው ያለው፡፡ የማንም ጥቅም ሳይነካ እንዴት ችግሩ ይፈታል የሚለውን ለማየት እሥራኤል ዝግጁ ናት፡፡ 

አዲስ ዘመን፡- እያሉኝ ያለው ገዳሙን ማደስ በተመለከተ ነው፡፡ የይዞታው የባለቤትነት ጉዳይስ በምንድን ነው የሚዳኘው?

አምባሳደር በላይነሽ፡- ይሄ እሥራኤል የምትፈታው ጉዳይ አይደለም፡፡ በእኔ ዕምነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንና የግብፅ ኮፒቲክ ቤተክርስቲያን መነጋገር አለባቸው፡፡ የተሻለ የሚመስለኝም በግሌ ይሄ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- የእሥራኤል መንግሥት አቋምስ ምንድን ነው?

አምባሳደር በላይነሽ፡- የእሥራኤል መንግሥት የሁሉንም ወገን ችግር መፍታት ይፈልጋል፡፡ ስታትስኮ አለ፡፡ ያችን የምታክል ቦታ ላይ የሁሉም ዓይን አለባት፡፡ ስለዚህ ችግር እንዲፈጠር አንፈልግም፡፡ የእሥራኤል መንግሥት አቋም ይሄ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ይቀረኛል የሚሉት ወይንም የሚቆጭዎት ነገርስ ይኖር ይሆን?

አምባሳደር በላይነሽ፡- ይቆጨኛል የምለው ነገር የለም፡፡ እኔ ማየት የምፈልገው ኢትዮጵያ አድጋ ነው፡፡ የጀመርኳቸው ነገሮች ለውጥ አምጥተው ማየት እፈልጋለሁ፡፡ ከዚህ ውጭ ማድረግ እያለብኝ ያላደረኩት ነገር የለም፡፡ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳልል ማድረግ ያለብኝን ሁሉ አድርጌያለሁ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡኝ ጊዜ በጣም አመሰግናለሁ፡፡

አምባሳደር በላይነሽ፡- እኔም አመሰገናለሁ፡፡

አርአያ ጌታቸው

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።