ለስምንት ዓመታት አባሽ ያጣው እንባ

01 Aug 2017

በደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ሀዲያ ዞን በሌሞ ወረዳ ተወልደው ያደጉት አቶ ገዛኸኝ ሳሙኤል ነዋሪነታቸው በሆሳዕና ከተማ ነው፡፡ ግለሰቡ ከ1983 እስከ 1999 ዓ.ም ለአስራ ስድስት ዓመታት በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች በሚገኙ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመምህርነት አገልግለዋል፡፡

በ1999 ዓ.ም ወረዳው ለመምህሩ የትምህርት እድል ይሰጣቸዋል፡፡ የተሰጣቸውን የትምህርት እድል ተጠቅመው የነበራቸውን የትምህርት ደረጃ ከዲፕሎማ ወደ ዲግሪ ለማሻሻል በመደበኛው የትምህርት ፕሮግራም ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያመራሉ፡፡ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ይቆዩና በስነ ትምህርት ኮሌጅ ውስጥ ታሪክ እና ስነ- ዜጋ ትምህርት አጥንተው በ2001 ዓ.ም አጠናቅቀዋል፡፡ ከፍተኛ ውጤት (3 ነጥብ 7) በማስመዝገብም በሀምሌ 17 ቀን 2001 ዓ.ም በማዕረግ ተመርቀዋል፡፡

ቅሬታ ለቀረበበት ምክንያት የሆነው ጉዳይ የተከሰተው በ2001 ዓ.ም ነው። በሐምሌ 24 ቀን 2001 ዓ.ም (በተመረቁ በአንድ ሳምንት) ወደ ወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት ተመልሰዋል፡፡ ለጽህፈት ቤቱ ትምህርታቸውን ስለጨረሱ እና ያስተምሩ የነበሩበት ሌሞ ወረዳ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስለሌለ የዞኑ ትምህርት መምሪያ ተገቢውን ምደባ እንዲሰጣቸው የወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት የድጋፍ ደብዳቤ እንዲጽፍላቸው ያመለክታሉ፡፡

የወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊም ጥያቄያቸው ታይቶ ምላሽ እንዲሰጣቸው መርተዋል፡፡ ሆኖም ጉዳዩን አይቶ ምላሽ እንዲሰጥ የታዘዘው የጽህፈት ቤቱ የቅሬታና ይግባኝ ሰሚ ዋና የስራ ሂደትም ሆነ ወረዳው ለማመልከቻቸው ምላሽ ሳይሰጥ ወራት እንደተቆጠሩ መምህር ገዛኸኝ ያወሳሉ ፡፡

ለጽህፈት ቤቱ ያስገቡት ማመልከቻ የጽሁፍ ምላሽ ሳያገኝ ቀናት እያለፉ ተተኩ፡፡ ወራትም አልፈው ወራት ተተኩ፡፡ ለጽህፈት ቤቱ ያስገቡት ማመልከቻ የውሃ ሽታ ሆኖ ሲቀር ቅሬታቸውን ለዞኑ ትምህርት መምሪያ በአካልና በጽሁፍ ከአንዴም ሶስቴ አቅርበዋል፡፡ ያስተምሩ የነበሩበት ወረዳ ውስጥ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ስለሌሉ የትምህርት ውጤት እና የአገልግሎት ዘመን ከግንዛቤ በማስገባት መምሪያው ምደባ እንዲሰጣቸው አመልክተዋል፡፡ መምሪያው ግን ምንም አይነት ምላሽ በጽሁፍ አለመስጠቱን ተናግረዋል፡፡

ከወረዳው ጽህፈት ቤትም ይሁን ከዞኑ ትምህርት መምሪያ ምንም ምላሽ አለመሰጠቱ ያሳሰባቸው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ክፍት ቦታ እስኪገኝ፤ ወደ ዩኒቨርሲቲ ከመሄዳቸው በፊት ይሰሩ የነበሩበት ማስቢራ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመመለስ ላይ ታች በሚሉበት ወቅት ከወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት የደረሳቸው ደብዳቤ በጣም አስደንጋጭ ነበር፡፡ ደብዳቤውም ዱባንቾ በሚባል የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ተቀጥረው በስራ ገበታ ላይ ስላልተገኙ እና ተደጋጋሚ ማስታወቂያ ወጥቶ ቀርበው ባለማመልከታቸው ከስራ መሰናበታቸውን የሚያስረዳ ነበር፡፡

አቶ ገዛኸኝ እንደሚሉት ምደባ እያላቸው እና ለዘመናት ይሰሩ የነበሩበት የማስቢራ  ትምህርት ቤት በስራ ገበታ ላይ ስላለመገኘታቸው ምንም አይነት ማስታወቂያም አላወጣም፤ ከስራም አላገዳቸውም፡፡ የስራ ስንብት ደብዳቤም ከማስቢራ ትምህርት ቤት አልሰጣቸውም፡፡ ከስራቸው መታገድ ካለባቸውም መታገድ የነበረባቸው ቀድሞ ያስተምሩ በነበሩበት ትምህርት ቤት ነው፡፡ መምህሩ የታገዱት ግን ስለመመደባቸውም እንኳን ከማያውቁበት ከዱባንቾ ትምህርት ቤት ውስጥ መሆኑ ግራ የሚያጋባ መሆኑን ነው የሚያነሱት፡፡

ባለትዳር እና የሁለት ልጆች አባት ለሆኑት እና ብቸኛ መተዳደሪያቸው የመንግስት ደሞዝ ለሆናቸው ለመምህር ገዛኸኝ የስራ መታገድ ደብዳቤ መርዶ የተረዱ ያህል አስደንጋጭ ነበር፡፡ አቶ ገዛኸኝ እንደሚሉት ባጋጠማቸው ውስብስብ ችግር ምክንያት ትዳራቸውም ፈርሷል፡፡ ከእናት አባት ጋር ማደግ የነበረባቸው ልጆችም አባታቸው ከስራ መሰናበታቸውን ተከትሎ በቤተሰብ መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ከእናት አባት ጋር የመኖር መብታቸውን ተነፍገዋል፡፡

መምህሩ ቅሬታቸውን ከማሰማት አልቦዘኑም፤ ጥያቄያቸውን ለሚመለከታቸው ተቋማት ማቅረባቸውን ተያይዘውታል፡፡ ለዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት፣ ለዞን መምህራን ማህበር፣ ለክልል መምህራን ማህበር፣ ለክልሉ ትምህርት ቢሮ፣ ለክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስ እና ሰው ሃብት ልማት ቢሮ እንዲሁም ለርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት አለፍ ሲልም ለፌዴራል እንባ ጠባቂ ተቋም፣ ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እንዲሁም ለትምህርት ሚኒስቴር ያቀረቡበትን ደብዳቤዎች ኮፒ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል አቅርበዋል፡፡

መምህሩ ባቀረቡት አቤቱታ መሰረት አብዛኞቹ ተቋማት ለዞኑ ትምህርት መምሪያ ‹‹ለመምህሩ በዞኑ በሚገኙ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገቢው ምደባ እንዲሰጠው›› በማለት ደብዳቤ ጽፈዋል፡፡ ከእነዚህ ደብዳቤዎች መካከልም ለአብነት ያህል የዞኑ መምህራን ማህበር ጥቅምት 3 ቀን 2002 ዓ.ም  እንዲሁም የክልሉ መምህራን ማህበር ታህሳስ9 ቀን 2002 ዓ.ም ለዞኑ ትምህርት መምሪያ ‹‹መምህራን ደረጃቸውን እንዲያሻሽሉ የሚደረገው የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት በመቅረፍ ለትምህርት ስኬታማነት አስፈላጊውን ሁኔታዎችን በማመቻቸት ተማሪዎች አስፈላጊውን ትምህርት እንዲያገኙ ለማድረግ በመሆኑም መምህሩ ተገቢው ምደባ እንዲሰጠው›› በማለት ደብዳቤ ጽፏል፡፡

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ለዞኑ ትምህርት መምሪያ መስከረም 8 ቀን 2002 ዓ.ም በጻፈው ደብዳቤ ‹‹መምህሩ በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲመደቡ እና ጥቅማ ጥቅማቸው እንዲከበር›› በማለት መመሪያ ሰጥቷል፡፡ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት የአስተዳደራዊ ቅሬታና አቤቱታ ጉዳዮች ውሳኔ አሰጣጥ ዋና የስራ ሂደት በጥቅምት7 ቀን2002 ዓ.ም ለዞኑ ትምህርት መምሪያ በጻፈው ደብዳቤ ‹‹የክልሉ ትምህርት ቢሮ የሰጠው መመሪያ ተግባራዊ እንዲደረግ እንዲሁም ደንብና መመሪያ ተጠብቆ ለአመልካቹ ምላሽ ይሰጥ›› በማለት ጽፏል፡፡ እነዚህን ለአብነት ያህል አቀረብን እንጂ ሌሎች ተቋማትም ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ደብዳቤዎችን ለዞኑ ትምህርት መምሪያ ጽፈዋል፡፡

በአንድ መንግስት የሚመሩ እና ለአንድ አገር የሚሰሩ እነዚህ ተቋማት ግን አንዱ የአንዱን መመሪያ መቀበል ባለመቻላቸው መምህሩ ራሱን እና አገሩን ሳይጠቅም አመታት ተቆጥረዋል፡፡ በወቅቱ ከስራ እንዴት ሊታገዱ እንደቻሉ ዝግጅት ክፍሉ ለማጣራት ተንቀሳቅሷል፡፡

በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ፤ መምህሩ ተቀጥረው ለዓመታት ይሰሩ የነበሩበት ትምህርት ቤት እያለ ያለፈቃዳቸው ለምን ወደ ሌላ ትምህርት ቤት እንደተዘዋወሩ፣ የመልቀቂያ ደብዳቤ ከማስቢራ ትምህርት ቤት መጻፍ እያለበት እንዴት ከዱባንቾ ትምህርት ቤት ሊጻፍ ቻለ ስንል ላቀረብንው ጥያቄ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ጋሼ፤ ችግሩ ከተፈጠረ ከስምንት ዓመት በላይ መሆኑን በማስታወስ፤ በወቅቱ የነበሩ የስራ ኃላፊዎችን ጠይቀው እና ሰነዶችን አገላብጠው ስለተፈጠረው ነገር በሰጡት ምላሽ መምህሩ ከማስቢራ ትምህርት ቤት ለትምህርት ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መሄዳቸውን አረጋግጠውልናል፡፡ 

መምህሩ ትምህርቱን ጨርሶ እስኪመለስ በማስቢራ ትምህርት ቤት የመምህራን እጥረት በማጋጠሙ በመምህሩ ቦታ ሌላ መምህር መቀጠሩን ነው የተናገሩት፡፡ መምህሩ ትምህርቱን ጨርሶ ሲመለስ ዱባንቾ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመድበዋል፡፡  መምህሩ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ሰርተው የመጡ እንደመሆናቸው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መመደብ ነበረባቸው ነው የሚሉት፡፡ ነገር ግን በወረዳው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ስለሌሉ በዱባንቾ እንዲመደቡ መደረጉንም ይገልጻሉ፡፡

መምህሩ ደግሞ ‹‹በሆሳዕና ከተማ ውስጥ በሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መመደብ ካልሆነም ለትምህርት ከመሄዳቸው በፊት በነበሩበት ማስቢራ ትምህርት ቤት ስራዬን መቀጠል አለብኝ›› የሚል አቋም ይዘው እንደነበር ያነሳሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ዱባንቾ ትምህርት ቤት ለማስተማር ፈቃደኛ አልነበሩም ነው የሚሉት፡፡ ዱባንቾ ትምህርት ቤት ተደጋጋሚ ማስታውቂያዎችን አውጥቶ መምህሩ ማመልከት ባለመቻላቸው ከስራ ታግደዋል ብለዋል፡፡

አንድን መምህር ከሚያስተምርበት ትምህርት ቤት ያለፈቃዱ ማስነሳት እና በማይፈልግበት ትምህርት ቤት አስተምር መባሉ ከህግ አንጻር እንዴት ይታያል? ወረዳው የህግ ጥሰት አልፈጸመም ብለው ያስባሉ ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች አቅርበንላቸው ነበር፡፡ ቀደም ሲል ላቀረብንላቸው ጥያቄዎች በጥሩ ስሜት ምላሽ ይሰጡ የነበሩት አቶ ብርሃኑ፤ ‹‹እንዲያውም በዚህ ጉዳይ ላይ ከዚህ በላይ መናገር አልችልም›› በማለት ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

የመጀመሪያ ዲግሪ ሰርተው የተመለሱት መምህር ተደጋጋሚ ማመልከቻዎችን ሲያስገቡ እና ከዞን መምህራን ማህበር፣ ከክልል መምህራን ማህበር፣ ከክልሉ ትምህርት ጽህፈት ቤት፣ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ለተጻፉት ተደጋጋሚ ደብዳቤዎች ለምን ምላሽ መስጠት እንዳልተቻለ የዞኑን ትምህርት መምሪያ ጠይቀናል፡፡

በመምሪያው የመምህራን እና ሰራተኞች አስተዳደር አቶ ግርማ ዮሃንስ መምህር ገዛኸኝ ለዝግጅት ክፍሉ ያቀረቡት ቅሬታ ትክክል መሆኑን ይናገራሉ፡፡ መምህሩ ከዩኒቨርሲቲ ዲግሪያቸውን ይዘው የተመለሱበት ወቅት ዲግሪ ያላቸው መምህራን ዞኑ ይመድብ እንደነበርም ይመሰክራሉ፡፡

መምህራኖቹ ይሰሩበት በነበሩበት ወረዳ ውስጥ በሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ እንዲመደቡ ሲደረግ እንደነበርና መምህራን ይሰሩ በነበሩባቸው ወረዳዎች ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከሌለ ደግሞ በሆሳዕና ከተማ ውስጥ እንዲሰሩ ሲደረግ መቆየቱን ይጠቅሳሉ፡፡ አቶ ገዛኸኝ ሲያስተምሩ የነበሩበት ሌሞ ወረዳ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አልነበረም፡፡ በመሆኑም ሆሳዕና ከተማ መግባት ነበረባቸው ነው የሚሉት፡፡

አቶ ግርማ እንደሚሉት ሆሳዕና ከተማ አቶ ገዛኸኝ በተማሩበት በታሪክ እና ስነዜጋ ክፍት ቦታ ስለሌለው እና ክፍት ቦታ እስኪገኝ የዞኑ ትምህርት መምሪያ አቶ ገዛኸኝን ሊሳና ቁሳ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ እንዲሰሩ መመደቡን እና አቶ ገዛኸኝ ወደተመደቡበት ሄደው ለማስተማር ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የስራ ውላቸው መቋረጡን ያነሳሉ፡፡

ከዚያ በኋላም አቶ ገዛኸኝ ህመም ስላጋጠማቸው ዞን መጥተው ጉዳያቸውን በተከታታይ መጠየቅ አቁመው እንደነበር እና አልፎ አልፎ ግን መጥተው ጠይቀው ይመለሱ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ በሆሳዕና ከተማ ውስጥ በግል ትምህርት ቤቶች ያስተምሩ ስለነበር በመንግስት ትምህርት ቤቶች ለማስተማር እምብዛም ፍላጎት አልነበራቸውም ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥም ከስራቸው ከተነሱ ሁለት ዓመት በላይ ስለሆነ ክፍት ቦታዎች ላይ መመደብ እንዳልተቻለ አንስተዋል፡፡

በዞኑ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እስኪገኙ መምህሩ መጀመሪያ ይሰሩ የነበሩበት ትምህርት ቤት ውስጥ ሆነው እንዲቆዩ ለምን አልተደረገም በሚል ለአቶ ግርማ ላቀረብንላቸው ጥያቄ በወቅቱ በቦታው ስላልነበርኩ አላውቅም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

መምህር ገዛኸኝ ግን በአቶ ግርማ ሀሳብ አይስማሙም በወቅቱ በሆሳዕና ከተማ ውስጥ ክፍት ቦታ አልነበረም የተባለው ሀሰት ነው ይላሉ፡፡ በርካታ ክፍት የስራ ቦታዎች ነበሩ፡፡ እንዲያውም በመደበኛ መርሃ ግብር በሀምሌ 2001 ዓ.ም ተመርቀው የተመለሱት አቶ ገዛኸኝ እያሉ በመስከረም 2002 ዓ.ም በክረምት ትምህርታቸውን ጨርሰው የመጡ በርካታ መምህራኖች በሆሳዕና በሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ መመደባቸውን ይናገራሉ፡፡

‹‹እንዲያውም እኔ  በሰለጠንኩበት የትምህርት ዘርፍ አራት መምህራኖች ስለመመደባቸው መረጃ አለኝ፡፡ ይህንን ነገር የዞኑ መምህራን ማህበርም ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ እኔ እንዳልቀጠር ሆን ተብሎ የተሰራ ስራ ነው›› ብለዋል፡፡

ምንም አይነት የጤና ችግር እንዳላጋ ጠማቸው የሚናገሩት አቶ ገዛኸኝ አቶ ግርማ ምክንያት አድርገው ያነሱት የጤና ችግር ጉዳይ ተገቢነት የሌለው መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ከ2001 ዓ.ም እስከ 2005 ዓ.ም ከወረዳ እስከ ፌዴራል ለተለያዩ አካላት ቅሬታቸውን ሲያቀርቡ እንደነበር የሚያስረዱት መምህር ገዛኸኝ ጉዳዩን በየወቅቱ አይከታተልም የተባለውን እውነታነት የሌለው ነው ይላሉ፡፡ መምሪያው በሊሳና ቁሳ ትምህርት ቤት መድቦ እንደነበርም አላውቅም ያሉት መምህሩ በግል ትምህርት ቤት ማስተማር የጀመሩትም የመንግስት ስራ ለአንድ ዓመት ከግማሽ ጠብቀው ልጆቻቸው በርሃብ እንዳይሞቱ በማሰብ መሆኑን በመጠቆም፤ በመንግስት ትምህርት ቤት ለመስራት ፍላጎት ስለሌለኝ አይደለም፡፡ ‹‹ፍላጎት ባይኖረኝ ለምን ከወረዳ እስከ ፌዴራል አቤቱታ አቀርባለሁ›› ብለዋል፡፡

የወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት መምህሩ ቀድሞ ያስተምሩ የነበሩበት ትምህርት ቤት ክፍት ቦታ ባለመኖሩ ዱባንቾ ትምህርት ቤት ተመድበው በስራ ገበታ ባለመገኘታቸው ከስራ መታገዳቸውን እንደምክንያት ሲያቀርብ የዞኑ ትምህርት መምሪያ ደግሞ በዞኑ በሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ክፍት ቦታ እስኪገኝ ሊሳና ቁሳ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመድበው በተመደቡበት የስራ ገበታ ላይ ባለመገኘታቸው ከስራ መታገዳቸውን በምክንያትነት አቅርቧል፡፡

በአንድ ዞን ውስጥ የሚገኙ ሁለቱም ተቋማት መምህሩን እንዴት አድርገው ሁለት ቦታ እንደመደቡ ለሚሰማው ሰው ግር የሚያሰኝ ነው፡፡ መምህሩ ደግሞ የትም ቦታ መመደባቸውን አላውቅም ማለታቸው ደግሞ ይባስ የሚገርም ነው፡፡ ከዞኑም ይሁን ከወረዳው ስለ መመደባቸው በእጃቸው የደረሰ መረጃም እንደሌላቸው ለዝግጅት ክፍሉ ገልጸዋል፡፡

የወረዳው ትምህርት ቤት በመምህሩ ቅሬታ ዙሪያ በቀጣይ ምን አቅጣጫ እንደያዘ የተጠየቁት አቶ ብርሃኑ ጋሼ ስራ ለቆ ተመልሶ ወደ ስራ መግባት ሂደቱ ከባድ ነው፡፡ ተወዳድሮ እንዲገባ ማድረግ ይቻላል፡፡ ማወዳደር እና ቅጥር መፈጸም ያለበት ዞኑ ሲሆን ዲግሪ የያዙ በመሆናቸው የስራ ልምዳቸውን ታሳቢ አድርጎ ቅጥር መፈጸም ያለበት ዞኑ ነው ብለዋል፡፡

በዞኑ ትምህርት መምሪያ መምህራን እና ሰራተኞች አስተዳደር አቶ ግርማ ዮሃንስ በቀጣይ  ከክልል ትምህርት ቢሮ ጋር በመተባበር የመምህሩ የትምህርት ደረጃ እና የአገልግሎት ዘመን ታይቶ ምደባ ሊሰጣቸው ‹‹እንደሚችል›› ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ከስራቸው ተፈናቅለው የቆዩበትን ጊዜ ደመወዝ እንደማይከፈላቸው አብራርተዋል፡፡

አገሪቱ ካላት ውስን ሃብት በመቁረስ በተለያዩ መርሃ ግብሮች መምህራኖችን የምታሰለጥነው  የመምህራንን አቅም ለማጎልበት ነው፡፡ በትምህርትና ስልጠና ባጎለበቱት አቅማቸው ብቁ ዜጎችን እንዲያፈሩ፣ አገሪቱም የነገ አገር ተረካቢ እንድታገኝ በማሰብም ጭምር መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ መምህር ገዛኸኝ ግን በተለያዩ ውስብስብ ምክንያቶች በሰለጠኑት ሙያ ራሳቸውን እና አገራቸውን እንዳይጠቅሙ ተደርገዋል፡፡ ይህ ደግሞ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ላለባት አገር ትልቅ ኪሳራ ነው፡፡

አሁንም ቢሆን የመምህሩን ቅሬታ መፈታት ይኖርበታል፡፡ መምህሩ ባካበቱት ልምድና ባሻሻሉት አቅም አገራቸውን እና ህዝባቸውን እንዲያገለግሉ መደረግ አለበት፡፡ ዞኑም ይህንኑ ከግንዛቤ በማስገባት የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ አፋጣኝ ውሳኔ ሊወስን ይገባል እንላለን፡፡ 

መላኩ ኤሮሴ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።