«አንድም ቤት እና ሰው ሳይቆጠር መታለፍ የለበትም» - አቶ ሳፊ ገመዲ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር Featured

07 Aug 2017

ኢትዮጵያ 1976 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ባካሄደችው የህዝብና ቤት ቆጠራ 43 ሚሊዮን ዜጎች እንዳሏት አረጋግጣለች። 1987 ዓ.ም ደግሞ የህዝብ ቁጥሯ 53 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን፤ 1999 ዓ.ም ባካሄደችው ሦስተኛው የህዝብና ቤት ቆጠራ 73 ሚሊዮን ህዝብ እንዳላት ታውቋል። የህገመንግሥቱ አንቀፅ 103 ደግሞ በየአሥር ዓመቱ የህዝብና ቤት ቆጠራ እንዲካሄድም ይደነግጋል። ለአራተኛ ጊዜ በ2010 ዓ.ም የመጀመሪያው ሩብ ዓመትም የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ለማድረግ ውጥን አላት። ይህን ዝግጅት አስመልክቶ የዝግጅት ክፍሉ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሳፊ ገመዲ ጋር ያደረገውን ቆይታ እነሆ!

ለአራተኛ ጊዜ የሚካሄደው የህዝብና ቤት ቆጠራ ከቀድሞዎቹ በምን ይለያል?

አቶ ሳፊ፡- በ2010 ለአራተኛ ጊዜ የህዝብና ቤት ቆጠራ ታካሂዳለች፡፡ ሦስቱም ቆጠራዎች ሳይንሳዊ መስፈርት ባሟላ መልኩ  ነው የተከናወኑት፡፡ ሁሉም ከወቅቱ ጋር የተዛመደ ባህሪም ነበራቸው፡፡ ሦስቱም ቆጠራዎች ወረቀት ላይ የተመሰረቱ ቢሆኑም በየጊዜው መሻሻል እያሳዩ ተከናውነዋል፡፡ በ2010 ዓ.ም የሚካሄደው ግን ለየት ያለና ከወረቀት ይልቅ ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረገ ነው፡፡

የቆጠራ ካርታ ዝግጅት የሚባለው ሙሉ ለሙሉ የተዘጋጀው በቴክኖሎጂ የታገዘ ነው፡፡ ቀደም ሲል ካርታ ዝግጅት የሚሰራው ሰዎች በእያንዳንዱ ቦታ ሂደው፤ ካርታውንም በእጅ ነበር የሚሰሩት፡፡ ይሁንና በሚቀጥለው ዓመት ለሚካሄደው ቆጠራ  ግን ጂ.ፒ.ኤስ እና በሌሎች ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ የተሰራ ነው፡፡ 2009 ዓ.ም ዓመቱን ሙሉ ሲሠራበት የቆየ ነው፡፡ የቆጠራ ካርታ ቦታ ዝግጅት በከተማ 200፤  በገጠር ደግሞ 150 አባወራዎችን በቴክኖሎጂ በመታገዝ ማካለል እና ለቆጠራ ዝግጁ ማድረግ ነው፡፡ የዚህ ሥራ 90 ከመቶው ተጠናቋል፡፡ ዋናው ቆጠራውም በቴክኖሎጂ የታገዘ ነው የሚሆነው፡፡

የ2010 ዓ.ም ከሌሎች ቆጠራዎች የሚለየው የቀድሞዎቹ ቆጠራዎች አርብቶአደር አካባቢዎች፤ በቆላ እና ደጋ በተለያየ ጊዜ ይካሄድ ነበር፡፡ በአርብቶአደሩ እና ደጋ አካባቢ ካለው ጋር የተለያየ የኑሮ ዘይቤ ስለሚከተሉ ለቆጠራ በአንድ ወቅት ማካሄድ አስቸጋሪ ነበር፡፡ ለአብነት ኦሮሚያ ክልል ቦረና፤ አፋር ክልል እንዲሁም የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል እና በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች በተመሳሳይ ወቅት ቆጠራ አይካሄድም ነበር፡፡ ለአብነት 1999 ዓ.ም ቆጠራ የተካሄደው የመጀመሪያው ግንቦት ወር ላይ ነው፡፡ ቀሪው ደግሞ 2000 ዓ.ም ነው የተካሄደው፡፡ ይህ ከወጪ አኳያ ከፍተኛ ገንዘብ ያስወጣል፡፡ ይህን ቀደም ሲል የነበረውን ችግር ለማቃለል ሲባል የአካባቢውን ማህበረሰብ እና አርብቶአደሮች መቼ በቀያቸው እንደሚገኙ ተጠንቷል፡፡ ስለዚህ በ2010ዓ.ም የሚካሄደው ቆጠራ በተመሳሳይ ወቅት ይሆናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለቆጠራው የበጀት እና ሎጅስቲክስ አቅርቦት ዝግጅትስ ምን ደረጃ ላይ ነው?

አቶ ሳፊ፡- ለዚህ ቆጠራ ሦስት ቢሊዮን ብር ተመድቧል፡፡ ከዚህም ትልቁን ደርሻ የሚይዘው ለቆጠራው የሚያግዙ 180ሺ ታብሌት ኮምፒዩተሮች ግዥ ወጪ የተደረገው ነው፡፡ ከእነዚህ ኮምፒዩተሮች ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል፡፡ ጨረታውን ያሸነፉት ደግሞ የአሜሪካ እና የቻይና ድርጅቶች ናቸው፡፡ ከዚህ ባሻገር እያንዳንዱ ሥራ በአግባቡ እንዲመራ ኮሚቴዎች ተቋቁመዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- የኮሚቴዎቹ ሥራ ምንድን ነው?

አቶ ሳፊ፡- ኮሚቴዎቹ በርካታ ተግባራትን ያከናውናሉ፡፡ ለአብነት የቴክኖሎጂ ኮሚቴ አለ፡፡ ይህ ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም ማስቻሉን ለማረጋገጥ ታብሌቶችን መፈተሸ ነበረበት፡፡ በዚህም የቴሌኮሙኒኬሽን መሰረተ ልማት ባለበት እንደሚሰራ ኮሚቴው አረጋግጧል፡፡ በጥቂት ቦታዎች የቴሌኮሙኒኬሽን  መሰረተ ልማት ችግር ባለበት እና የመልክዓ ምድሩ አስቸጋሪ በሆነበት አካባቢ ብቻ ነው የማይሰራው፡፡ይሁንና እነዚህን በማይሰሩበት ወቅት በወረቀት ላይ ተሰርቶ ወዲያውኑ የቴሌኮሙኒኬሽን መሰረተ ልማት ባለበት ቦታ ሲደረስ ወደ ኮምፒዩተር ዳታ ይገባሉ፡፡

በሌላው በዓለም ላይ አወዛጋቢ የሆነው ጉዳይ መረጃ የመመንተፍ እና ማጥቃት ስጋት እንዳይኖር  አገር አቀፍ የቴክኖሎጂ ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡ በዚህ ውስጥ የደህንነት እና መረብ ኤጀንሲ፤ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ አትዮ ቴሌኮም እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አባል ናቸው፡፡ ይህ የቴክኖሎጂ ኮሚቴ ታብሌቶቹ ሲገዙም በቴክኒካል ሥራው ላይ ትልቅ ሚና ነበረው፡፡ የመረጃመረብ እና ደህንነት ኤጀንሲ ሥራው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ በተለይም ከመረጃ ደህንነት አኳያ ትልቅ ኃላፊነት ተሸክሟል፡፡

በህዝቡ ዘንድ ግንዛቤ የመፍጠር ለኤሌክትሮኒክስ እና ህትመት ሚዲያ የሚውል መረጃም እየተሰራበት ሲሆን፣  በኮሚቴ እየተመራ ነው፡፡ ሌላው በኮሚቴ የተሰራው ነገር ቢኖር አገሪቱ አሁን ካለችበት የዕድገት ደረጃ እና ከዓለም ነባራዊ ሁኔታ አኳያ የሚመጥኑ መጠይቆችን ተዘጋጅተዋል፡፡ በዚህም ውስጥ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ የኤጀንሲው ከፍተኛ ባለሙያዎች እና የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈውበታል፡፡ ይህ በሥነ ህዝብ ውስጥ አስፈላጊ መረጃዎችን መመለስ በሚችልበት አኳኋን የተዘጋጀ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ቆጠራውን የሚያካሂዱት እነማን ናቸው?

አቶ ሳፊ፡- በቀደሙት ቆጠራዎች በብዛት መምህራን ነበሩ የተሳተፉት፡፡ በአሁኑ ወቅት የቆጠራ ኮሚሽኑ ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት በየቀበሌው በርካታ የጤና፣ የልማት ጣቢያ ሠራተኞች እና መምህራን ይኖራሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ነው የሚመረጡት፡፡ ዋናው መስፈርቱ ግን ቴክኖሎጂ መጠቀም መቻል ነው፡፡ ቆጠራ በሚካሄድባቸው 10 ቀናት ውስጥ ብቁ የአካል ቁመና ያለው እና ፈጣን ሰው ያስፈልጋል፡፡ እነዚህን ብቁ ሰዎች የመምረጥ ጉዳይ ደግሞ የየክልሎቹ ድርሻ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ቆጠራው በ2010 ዓ.ም የመጀመሪያው ሩብ ዓመት አካባቢ እንደሚካሄድ ይጠበቃል፡፡ ስለዚህም ለሥራው ያግዝ ዘንድ ቆጠራው አንድ ወር ሲቀረው ስልጠና ይሰጣል፡፡ በየክልሎቹ ደግሞ የስልጠና ማዕከላት  እየተደራጁ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለቆጠራው   ምን ያህል ሰው ያስፈልጋል?

አቶ ሳፊ፡- የቆጠራ ካርታ ዝግጅት ሲጠናቀቅ ስንት ሰው ለቆጠራ እንደሚያስፈልግ ትክክለኛ አሃዝ እና ፋይናንስ ብሎም ሎጅስቲክስ መመደብ ይቻላል፡፡ በግምት 140ሺህ ቆጠራ ቦታዎች እንደሚኖሩ ይጠበቃል፡፡ ስለዚህ 140ሺ ቆጣሪ ይኖረዋል፡፡ ከ30 እስከ 35ሺ ተቆጣጣሪዎች ይኖራሉ፡፡ በተጨማሪም  ሦስት ሺህ አስተባባሪዎች ይኖራሉ፡፡ በአጠቃላይ 190ሺህ ሰዎች በላይ በቆጠራው እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ቆጠራው በየአስር ዓመቱ የሚካሄድ ከሆነ ታብሌት ኮምፒዩተሮቹ ቆጠራውን ሲያጠናቅቁ በማን እጅ ይቆያሉ?

አቶ ሳፊ፡- አንዱ በጣም አስቸጋሪ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው ይህን ንብረት በአግባቡ ተጠቅሞ  የማስመለስ ጉዳይ  እንዴት ይሁን? የሚለው ጉዳይ  ነው፡፡ እነዚህ ታብሌቶች መገዛታቸው መንግሥት ለመረጃ ጥራት እና ታማኝነት ያለውን ቆራጥነት ያሳያል፡፡ ስለሆነም እነዚህ ታብሌቶች የአገር ሃብት መሆናቸው መታወቅ አለበት፡፡ ታብሌቶቹ ቆጠራው ከተጠናቀቀ በኋላ መረጃውን የያዙ ስለሆኑ ወደ ማዕከሉ ይመለሳሉ፡፡ እንዴት መመለስ እንዳለበት ደግሞ መመሪያ ተዘጋጅቷል፡፡

ታብሌቱ የሚሰጣቸው ደግሞ ቋሚ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ከወንጀል ነጻ የሆኑ፣ ሞዴል ሠራተኞች የሆኑና በአጠቃላይ ኃላፊነት የሚቀበሉ ናቸው፡፡ የ2010 ቆጠራ ሲጠናቀቅ ታብሌቶቹ ከአስር ዓመት በኋላ ቆጠራ እስኪሚካሄድ ድረስ በመጋዘን አይቀመጡም፡፡ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲም ከቆጠራ በኋላ በርካታ ሥራዎችን ስለሚያከናውን ይጠቀምባቸዋል፡፡ ምናልባት ሶፍትዌሮቹን መቀየሩ ያስፈልግ ይሆናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በቆጠራው ምን ምን ይካተታል?

አቶ ሳፊ፡-  ዋናው ትኩረቱ ሰዎችን መቁጠር ነው፡፡ ሴቶች፣ ህጻናት፣ አካል ጉዳተኞች ሁሉም ይቆጠራሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት መንግሥት ትልቁ ዓላማ ለዜጎች ቤት ማቅረብ ነው፡፡ ስለዚህ የአንድ ሰው የቤት ይዞታው መታወቅ አለበት፡፡ ከምን እንደተሰራ፣ መገልገያ ቁሶቹ፣ የሚጠቀማቸው የመረጃ ምንጮች፣ መብራት፣ ውሃ፣ መፀዳጃ ቤት የመሳሰሉት መኖራቸውን ለማረጋገጥ ደግሞ ቤት ቆጠራም ይከናወናል፡፡ ይህ ለመንግሥት በጣም ይጠቅማል፡፡ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ትርጉሙ ከፍተኛ ነው፡፡ መንግሥት ለሚያቅዳቸው ተግባራት ሁሉ የህዝብ ቁጥር ወሳኝ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- የቆጠራውን ትክክለኝነት እንዴት ነው ማረጋገጥ የሚቻለው?

አቶ ሳፊ፡- ለዋና ቆጠራ የተደረገው ዝግጅት ለመስክ ሥራ ላይ መዋሉን ለማረጋገጥ የሙከራ ቆጠራ ተደርጓል፡፡  ይህም ክፍተቶች ካሉ ቀድሞ ለማረም እንዲያግዝ ነው፡፡ በዚህም በገጠር፣ ቆላ ደጋ እና ከተማ ከሁሉም ቦታ ለናሙና ተወስዶ ጥናት ተደርጓል፡፡ በዚህም ናሙና ሥራው ያሰራል ወይስ አያሰራም የሚለው ታይቷል፡፡ እናም በዚህ ሙከራ  በትክክል እንደሚሠራ ተረጋግጧል፡፡

ከቆጠራ በኋላ ድህረ ቆጠራ ይካሄዳል፡፡ ይህ ሳይንሱ የሚያዘው ነው፡፡ ይህ የሚደረገው የመረጃውን ጥራት ለማረጋገጥ ነው፡፡ ይህም ቆጠራ ከተካሄደ በኋላ የተወሰኑ ቦታዎች ለናሙና ተወስደው ቆጠራ ይካሄዳል፡፡ ስለዚህ  አሰራሩ በራሱ ከስህተት የፀዳ ለማድረግም ያግዛል፡፡

አዲስ ዘመን፡- የህዝብና ቤት ቆጠራ አገራዊ፤ አህጉራዊ ብሎም ዓለም አቀፋዊ ትርጉሙ ምንድን ነው?

አቶ ሳፊ፡-  እንደ አገር ለልማት ዘርፍ ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎች ይሰበሰባሉ፡፡ እኒህን በአግባቡ ከተተነተኑ ለአገሪቱ ትልቅ ጥቅም ይሰጣሉ፡፡ በአፍሪካ ደረጃ የአህጉሪቱን የስነ ህዝብ ፖሊሲ ለመቅረጽ ያግዛል፡፡ ይህ በአንድ አገር ያለው ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ምጣኔሃብታዊ ትርጉም በአህጉር ብሎም በዓለም ደረጃም የራሱ የሆነ አንድምታ አለው፡፡ 

አዲስ ዘመን፡- በቆጠራው ምን  ዓይነት ስጋቶች ይኖራሉ ተብሎ ተለይቷል?

አቶ ሳፊ፡- መሰረት ልማቶች ባልተሟላበት አካባቢ ቆጠራ ሥራውን በተሳካ ሁኔታ እና ፍጥነት ለማሳካት እክል ሊፈጥር ይችላል፡፡ በተለይ ከቴሌኮም ጋር በተያያዘ ችግሮች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ ችግሩን ለማቃለልም ቀድሞ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ 

በየአስር ዓመቱ ለሚካሄደው ቆጠራው በባለቤትነት መንግሥት ነው የሚሰራው፡፡ ለዚህም ከላይ እስከታች አደረጃጀት ተፈጥሯል፡፡ አገር አቀፍ የቆጠራ ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ ይህም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ሲሆን፤ ከሦስት ጊዜ በላይ በመገናኘት ጠቃሚ ውሳኔዎችን ወስኗል፡፡ ክልል አካባቢ ያሉ እና በካርታ ላይ እክል ሊፈጥሩ የሚችሉ ችግሮች ቶሎ መፍትሄ እንዲያገኙ የሚያስችል አደረጃጀት ተፈጥሯል፡፡ በዚህም እስከ ቀበሌ ድረስ ጉዳዩን በዋናነት የሚከታተሉ አካላት ተመድበዋል፡፡ እነዚህን በማቋቋም የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ቀዳሚውን ሚና ተወጥቷል፡፡ የቆጠራ ኮሚሽንም ያስተላለፈው ውሳኔ በድንበር አካባቢ ችግሮች በፍጥነት እንዲፈቱ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ችግሮች በሚስተዋሉባቸው አካባቢዎች ‹‹ልዩ ቆጠራ›› ይካሄዳል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን መረጃ አመሰግናለሁ። የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ?

አቶ ሳፊ፡-  ለአራተኛ ጊዜ ለሚካሄደው የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ህዝቡ ተሳትፎ እና ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ በየደረጃው ያለው የመንግሥት ኃላፊዎች  ትልቅ ሚና ይጠበቅባቸዋል፡፡ አንድም ቤት እና ሰው ሳይቆጠር መታለፍ የለበትም፡፡ ለዚህም የሁላችን ትብብር ያስፈልጋል፡፡

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።