አርብቶና ከፊል አርብቶ አደሩን በመንደር የማሰባሰቡ ትሩፋት

10 Oct 2017

የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ትኩረት አድርጎ ከሚሰራባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ልዩ ድጋፍ በሚሹ ክልሎች የሚገኙ አርብቶና ከፊል አርብቶ አደሮችን በመንደር በማሰባሰብ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል ነው፡፡ እነዚህ ልዩ ድጋፍ የሚሹ ክልሎች የሚባሉት አፋር፣ ቤኒሻንጉል-ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ሶማሌ ሲሆኑ፣ እንዲሁም በኦሮሚያና በደቡብ ክልል የሚገኙ አርብቶ አደሮችም ይካተታሉ፡፡

እነዚህ ልዩ ድጋፍ በሚሹ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ አርብቶና ከፊል አርብቶ አደሮች አኗኗራቸውና አሰፋፈራቸው በተበታተነ ሁኔታ ስለሆነ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት ተጠቃሚ አልነበሩም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በሀገሪቱ በተለያየ ጊዜ የሚከሰተው የሰው ሰራሽም ሆነ በተፈጥሮ አደጋ በቀላሉ የሚጎዱ ሲሆን፣ ድህነትም በከፋ ደረጃ የሚያጠቃቸው አካባቢዎች ናቸው፡፡

እነዚህን በተበታተነ መልኩ ሰፍረው የሚገኙ ህዝቦችን ለማሰባሰብ መንግሥት የትኩረት አቅጣጫ አድርጎ የተንቀሳቀሰው ውሃን ማዕከል ያደረገ የመንደር ማሰባሰብ መርሐ ግብር መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለአርብቶ አደሩም ሆነ ለከፊል አርብቶ አደሩ ህልውና ዋናው ውሃ ነው። ውሃ ለእነርሱም ሆነ ለሚያረባቸው እንስሳት መሰረታዊ ጉዳይ በመሆኑ እሱን ፍለጋ ከቦታ ቦታ መንከራተ ታቸው እሙን ነው። ይሁንና ይህን ድካማቸውን ሊያስቀር የሚችል በጥናት ላይ የተመሰረተ የመንደር ማሰባሰብ መርሐ ግብር በህዝቡ መልካም ፈቃድ በእነዚህ ክልሎች ላይ ይከናወናል፡፡

የመንደር ማሰባሰቡ መርሐ ግብር በጥናት ላይ የመመስረቱ ምስጢር ሰዎች ያለበቂ ምክንያት ከቦታ ቦታ መዘዋወር ስለሌለባቸው ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ያሉበት አካባቢ ላይ ቢቆዩ ምን ያገኛሉ ምንስ ያጣሉ እንዲሁም ወደ ሌላ ቦታ ሄደው መስፈራቸውስ በአገርም አሊያም በክልል በዋናነት ደግሞ በራሳቸው ላይ ምን ለውጥን ያመጣል የሚለው ለይቶ ለማከናወን ስለሚያስችል ነው። ይህ ከሆነ በኋላም በአካባቢው ያስፈልጋሉ የሚባሉ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አገልግሎቶች እንዲሟሉ ተቋማትም እንዲፈጠሩ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ይሆናል፡፡

ከምንም በላይ ደግሞ በአካባቢው ላይ አስፈላጊ የሆኑ መሰረተ ልማቶች በሙሉ በአፋጣኝ እንዲሟሉ ያስችላል፡፡ በእነዚህ ሥራዎች አማካይነትም የዜጎቹ የምግብ ዋስትና የሚረጋገጥበት ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል፤ በተጨማሪም በገበያ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶችንም በማምረት ከራሳቸው አልፈው የሀገርን ኢኮኖሚ ሊገነባ ወደሚችል እንቅስቃሴም ሊያስገባ ይችላል።

በሌላ በኩልም በመንደር የተሰባሰቡ ሰዎች ሰላማቸው ይጠበቃል፡፡ በተበታተኑ ጊዜ ፀረ-ሰላም ኃይሎች በቀላሉ ሊያጠቋቸው የሚችሉ ሲሆን፣ በአንድ ላይ መሰባሰባቸው ግን በመልካም አስተዳደሩም ሆነ በፀጥታው በኩል የተሻለ ህይወት እንዲመሩ ያስችላቸዋል።

መሰባሰብ ኃይል እንደመሆኑ መጠን በአንድ አካባቢ መገኘታቸውም መብታቸውን ከሌላው በተሻለ ሁኔታ እንዲጠቀሙ ያስችላቸዋል። በተጨማሪም የትምህርት፣ የጤና የኤክስቴንሽን አገልግሎት፣ የመብ ራት፣ የውሃ፣ የእህል ወፍጮና ሌሎች አስፈ ላጊ ማህበራዊ ተጠሜታዎች እንዲያገኙ ያግዛ ቸዋል፡፡ይህም ጤናማ እና የተረጋጋ ህይወት እንዲመሩ ያስችላቸዋል።

ምርታቸውንም በቀላሉ ለገበያ የሚያቀርቡ በት ዕድል ስለሚያገኙ የተሻለ ኑሮን ለመኖር ይችላሉ፡፡ እንዲሁም ለጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት መስፋፋት ምቹ ሁኔታ ስለሚፈጥር በአንድ አካባቢ መሰባሰባቸው ከግብርና ውጪ ባሉ የሥራ ዘርፎችም ላይ ተሰማርተው ሀብት እንዲያፈሩ መንገድ ይከፍታል፡፡

በፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር የከፊል አርሶ አደር ተመጣጣኝ ልማት ማረጋገጥ ዳይሬክተር ጀኔራል አቶ ወንድማገኝ ኃይሉ እንደሚሉትም፤ በየዓመቱ በተለይም ልዩ ድጋፍ የሚሹ ክልሎች ላይ መሰራት ያለባቸውን ተግባራት ከክልሎቹ ጋር በመሆን ያቅዳሉ። ከዚህ መካከል አንዱ የመንደር ማሰባሰብ መርሐ ግብር ነው። ይህ ሥራም ከድጋፍ ቦርዱ ጋር በቅንጅት የሚሰራ ሲሆን፣ ክልሎቹ ካሉባቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንዲላቀቁ በማድረግ በኩል ሰፊ ሚና ተጫውቷል።

ከዚህ አኳያ ከ2003 በጀት ዓመት ጀምሮ የመንደር ማሰባሰብ ሥራው በተቀናጀ መልኩ በመከናወን ላይ ይገኛል፤ በዚህም ከ2003 እስከ 2008 በጀት ዓመት የተከናወኑት ነባር የመንደር ማሰባሰብ ሥራ የሚባሉ ሲሆን፣ በ2009 በጀት ዓመት የተከናወነው ግን አዲስ የመንደር ማሰባሰብ ሥራ በመባል እየተከናወነ እንዳለም ይናገራሉ።

በአዲሱ የመንደር ማሰባሰብ መርሐ ግብር ከአመራር ጀምሮ እስከ ታችኛው ፈጻሚ ድረስ እቅዱን የጋራ የማድረግ፣ ህብረተሰቡን የማሳመንና ፈቃደኛ መሆናቸውን የማረጋገጥ ሥራዎች ይከናወናሉ፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ይህንን የማስተባበር ኃላፊነት አለበት። ከዚህ አኳያ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በህዳሴው ግድብ ግንባታ ምክንያት የሚነሱ 2880 አባወራ እማወራዎች እንዲሁም በጋምቤላ ክልል በአኮቦ ወረዳ 2ሺ እማወራ አባወራዎች ፤ እነዚህን 4880 አባወራ እማወራዎች ወደ ሌላ አካባቢ የማሰባሰብ እቅድ በመያዝ በተጠኑና በተመረጡ የመንደር ማሰባሰብ ማዕከላት ላይ እንዲያርፉ ሆኗል ።

በቤኒሻንጉል ክልል 2488 እንዲሁም በጋምቤላ ክልል 539 እማወራ አባወራዎችን በፍቃደኝነት በመንደር ማሰባሰብ በመቻሉ ሰዎቹ በአንድ አካባቢ ላይ ተረጋግተው በመኖር ላይ መሆናቸውን ዳይሬክተር ጀኔራል አቶ ወንድማገኝ አስረድተዋል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ በነባር የመንደር ማሰባሰብ ማዕከላት ላይም ቢሆን በተለይም ከ2003 እስከ 2008 .ም በተከናወኑ ተግባራት በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሥራዎች ተከናውነዋል። በዚህም በሁለቱም ክልሎች ባሉ 338 ማዕከላት 127542 እማወራና አባወራዎች ተሰባስበው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነታቸው መረጋገጡን አመልክተዋል።

እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ለማድረግም በተለይም የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ የመደገፍና የማሳደግ ሥራ እንደሚከናወን የሚናገሩት አቶ ወንድማገኝ፤ ከዚህ አኳያ በ2008 /2009 የምርት ዘመን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብቻ 458405 ሄክታር መሬት በሰብል ለመሸፈን ታቅዶ በተደረገው ድጋፍና ክትትል 419126 ሄክታር መሬት በሰብል በመሸፈን 9ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰበ ታቅዶ 8 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ማግኘት ተችሏል። በተመሳሳይ በጋምቤላ ክልልም 106497 ሄክታር መሬት በሰብል ለመሸፈን ታቅዶ 72765 ሄክታር መሬት በሰብል ለመሸፈን ከመቻሉም በላይ ከ1ነጥብ2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርትም ለመሰብሰብ መቻሉን ነው ዳይሬክተር ጀኔራሉ የሚናገሩት ።

የመንደር ማሰባሰብ ሥራው የሚከናወነው ውሃን ማዕከል በማድረግ ነው የሚሉት አቶ ወንድማገኝ፤ ከዚህም ባሻገር እንደ ትምህርት ቤት፣ የህክምና ተቋም፣ ወፍጮ ቤትና መንገድን የመሳሰሉ መሰረተ ልማቶች እንደሚሟሉም አብራርተዋል።

በተለይም የነባሩን መንደር ማሰባሰብ መርሐ ግብር በዋቢነት አንስተው እንደጠቀ ሱት፤ ከ2003 እስከ 2008 በጀት ዓመት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የተደረገው የመንደር ማሰባሰብ ሥራ ምን ያህል ህብረተሰቡን ተጠቃሚ አድርጓል የሚለው የዳሰሳ ጥናት ተደርጓል። በውጤቱም በመጠጥ ውሃ፣ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ፣ በሰውና በእንስሳት ጤና ኬላ ግንባታ፣ በአርሶ አደር ማሰልጠኛ፣ በእህል ወፍጮ እንዲሁም ማዕከላቱን የሚያገናኙ የገጠር መንገዶች ዝርጋታ ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡ ተረጋግጧል።

በዚህም በአማካይ 76218 የህብረተ ሰብ ክፍሎች በአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ከመቻሉም በላይ 89 120 እማወራና አባወራዎች በማዕከላቱ ተረጋግ ተው መኖር መጀመራቸውንም ለመረዳት እንደሚቻልም ገልጸዋል።

ይህ ሁኔታ ደግሞ የልማት ጣቢያ ሠራተኞች ተረጋግተው ሙያዊ ድጋፍን እንዲያደርጉ ህብረተሰቡም በተገነቡለት ተቋማት የመጠቀም ልምዱ እንዲጨምር ከማድረጉም በላይ የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርትም ምንም ካልነበረበት አሁን እጅግ ወደ ተሻሻለ ሁኔታ ለመድረስ መቻሉን ነው የሚያመለክቱት።

ሥራው እነዚህንና መሰል ውጤቶችን ያስገኘ ቢሆንም ህብረተሰቡን የማሳመን፣ የማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ተቋማት ግንባታ የመጓተት ችግሮች እንደነበሩ የሚናገሩት አቶ ወንድማገኝ ችግሮቹን ለማለፍም ተከታታይ የህዝብ ግንኙነት ሥራዎችን በመስራት ህብረተሰቡን የማሳመን እንዲሁም የተጓተቱትን ፕሮጀክቶች በጥናት የመለየትና የመፍትሔ ርምጃ የመውሰድ ተግባር መከናወኑንም ገልጸዋል።

«ህብረተሰቡን የማሳመን ሥራ በሰፊው ተሰርታል፤ ሆኖም ህብረተሰቡ አልፈልግም ካለ በምንም መልኩ የማይገደድበትን ሁኔታ ለመፍጠር ተችሏል፤ ይህ ቢሆንም ተጠቃሚነቱ ሲረጋገጥ አንፈልግም ያሉትም አካላት ሃሳባቸውን የመቀየር ሁኔታ ስላሳዩ ተከታታይነት ያለው የንቅናቄ ሥራ በመስራት ችግሮቹን ለማለፍ ችለናል» ይላሉ።

ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚሰጡ ተቋማትን ገንብቶ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረጉ በኩልም ከአቅም ውስንነት ጋር በተያያዘ ሁሉም ጋር ማዳረስ አልተቻለም፤ ሆኖም ተከታታይ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ እንዲሁም የክልሎቹንም አቅም በመገንባት ችግሮቹን መፍታት መቻሉን ነው የሚያብ ራሩት።

ያልተጣራ ውሃን ይጠጡ የነበሩ የህብረተ ሰብ ክፍሎች ንጹህ የመጠጥ ውሃን እንዲያገኙ ማስቻል፣ የትምህርት ቤት ደጃፍ ረግጠው የማያውቁ ህጻናትና ወጣቶች ዕድሉን እንዲያ ገኙ ማድረግ ብሎም ጤናቸው ሲጓደል የሚታ ከሙበት የጤና ኬላ ማግኘት መቻሉ ይበል የሚያሰኝ ነው። በመሆኑም በሌሎች አካባቢ ዎችም የተበታተኑ ካሉ በመንደር ተሰባስበው ተጠቃሚ መሆን ቢችሉ የተሻለ ማህበረሰብን መፍጠር እንደሚያስችል ተናግረዋል።

በጋምቤላ ክልል ባለፉት ዓመታት ህዝቡን በመንደር በማሰባሰብ በተሻለ መልኩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ደግሞ የተናገሩት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጋትሉዋክ ቱት ነሐሴ 30 ቀን 2009.ም ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሰጡት መረጃ ነው።

በክልሉ ቀደም ሲል ተበታትኖ ይኖር የነበረውን ህዝብ በመንደር በማሰባሰብ በዘላቂነት የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግ ሎቶች ተጠቃሚ በማድረግ በኩል ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን የሚናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የመንደር ማሰባሰብ መርሐ ግብሩ የፈጠራቸውን ምቹ ሁኔታዎች በመጠቀም በተለይም በግብርና፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ በመንገድና በሌሎችም መሰረተ ልማት ዘርፎች ስኬታማ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን አብራርተዋል።

በመንደር ማዕከላቱ አርሶና ከፊል አርብቶ አደሩ የተሻለ የግብርና ኤክስቴንሽንና የግብዓት አቅርቦት እንዲያገኝ በመደረጉ በአሁኑ ወቅት የምግብ ዋስትናቸውን ማረጋገጥ ተችሏል። ለዚህም በተጠናቀቀው የምርት ዘመን በመኸርና በአነስተኛ መስኖ ከለማው 105ሺ ሄክታር መሬት ከ1ነጥብ7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ርዕሰ መስተዳድሩ በማሳያነት ያነሳሉ።

እንደ አቶ ጋትሉዋክ ገለጻ፤ በክልሉ ባለፉት አሥር ዓመታት 98 የመንደር ማዕከላትን ጨምሮ በሁሉም አካባቢዎች 180 የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመገንባታ ቸው በክልሉ ያለውን አጠቃላይ የትምህርት ቤቶች ቁጥር ወደ 346 ከፍ አድርጓል። የተማሪዎች ተሳትፎም ከ148 ሺ በላይ ደርሷል።

በሌላ በኩልም በሁሉም የመንደር ማሰባሰብ ማዕከላት የንጹህ መጠጥ ውሃና የጤና ተቋማትን በማስፋፋት ጤናማና አምራች ዜጋ እንዲፈጠር የማድረግ ሥራዎች ተከናውነዋል። በክልሉ ከአሥር ዓመት በፊት 250 ኪሎ ሜትር ብቻ የነበረው አገናኝ የጠጠር መንገድ በአሁኑ ወቅት ክልሉን ከዞን፣ ከወረዳና ከቀበሌ የሚያገናኝ 1520 ኪሎ ሜትር የአስፓልትና የጠጠር መንገድ መዘርጋቱን ርዕሰ መስተዳድሩ አመልክተዋል።

በጋምቤላ ከተማ ብቻ ተወስኖ የነበረው የቴሌኮምና የኤሌክትሪክ አገልግሎትም ከተወሰኑ ጠረፋማ ወረዳዎች በስተቀር በሁሉም አካባቢዎች ተዳርሶ ህዝቡ የአገልግሎቱን እያገኘ መሆኑን ገልጸዋል። በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ መስኮች የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል የህዝቡን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ነው ያመለከቱት።

በአሁኑ ወቅት በተለይ በግብርና ልማት፣ በወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በመልካም አስተዳደር፣ በትምህርት ጥራት እንዲሁም ድንበር ዘለል የፀጥታ ችግሮችን በመከላከል በኩል በአትኩሮት እየተሰራ ነው የሚሉት አቶ ጋትሉዋክ፤ በክልሉ ከ2000 .ም ጀምሮ ሕዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ተጠቃሚ በማድረግ በኩል የታዩትን መልካም ጅምሮች በአዲሱ በጀት ዓመትም ይበልጥ አጠናክሮ በማስቀጠል የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራና እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

 

እፀገነት አክሊሉ

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።