የአለፈው ዓመት አፈጻጸምና የቀጣዩ አቅጣጫ በፕሬዚዳንቱ ንግግር

12 Oct 2017

 

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ መስከረም 29 ቀን 2010 .ም የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አምስተኛውን ዘመን ሦስተኛ ዓመት የስራ ዘመን በይፋ ከፍተዋል። በአመቱ ትኩረት የሚሰጣቸውን ዋና ዋና ጉዳዮችም በንግግራቸው ዳስሰዋል፤ አዲስ ዘመን ጋዜጣም እንዲህ አቅርቦታል።

2009 አፈጻጸም

የልዑላዊ ስልጣን ባለቤትነትን ከማንኛውም ግለሰብና የፖለቲካ ኃይል አምባገነንነት አውጥቶ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት ባደረገው ህገ-መንግስታችን እንዲሁም እያበበ በመሄድ ላይ በሚገኘው የፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችን ውስጥ ትልቅ ሚና የሚጫወቱት ሁለቱ ምክር ቤቶቻችን፣ የሥራ ዘመኑን መረሃ-ግብር አሀዱ ብለው በሚጀምሩባት በዚህች ቀን፣ አገራችን የተያያዘችውን የህዳሴ ግስጋሴ በተሻለ ፍጥነት በሚያስቀጥሉ ብሎም ወደ ላቀ ከፍታ በሚያሸጋግሯት አበይት ጉዳዮች ላይ ትኩረታችንን አድርገን መወያየት እንዳለብን እሙን ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ባሳለፍነው ዓመት ያገኘናቸውን ጅምር ድሎችና መልካም ተሞክሮዎችን በምናሰፋበት እንዲሁም አጋጥመውን የነበሩትን ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች በሚቀረፉበትና የህዝባችን የላቀ ተጠቃሚነት በሚረጋገጥባቸው ጉዳዮች ላይ ግልጽና ሰፊ ምክክር ማድረግ ይገባል፡፡

2010 .ም የሁለተኛውን ሚሊኒየም አገባደን አዲሱን የኢትዮጵያ ሚሊኒየም ከተቀበልን የመጀመሪያውን አሥር ዓመት በድል ያጠናቀቅንበት ዓመት በመሆኑ ታሪካዊ ተደርጐ የሚወሰድ ነው፡፡

ሀገራችን በሁለተኛው ሚሊኒየም መጀመሪያዎቹ ዘመናት አካባቢ ከነበረችበት ገናና የሥልጣኔ ማማ እየወረደችና እያሽቆለቆለች ቆይታ በሁለተኛው ሚሊኒየም ማገባደጃ አካባቢ በውድ ልጆቿ መራር መስዋዕትነት በተከፈተው አዲስ ምዕራፍ የህዳሴ ጉዞዋን ከጀመረች እነሆ ሩብ ምዕተ-ዓመት አካባቢ ሆኗታል፡፡ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ተሀድሶ ከጀመረችበትና እጅግ ፈጣን፣ ፍትሃዊና ዘላቂነት ያለው ዕድገት ማስመዝገብ ከጀመረችም ወደ አሥራ-አምስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ አዲሱን የኢትዮጵያ ሚሊኒየም ከጀመርንም ጊዜ አንስቶ በነበሩት የመጀመሪያዎቹ አሥር ዓመታት በአማካይ የ10.5 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ በዓለም ፈጣን ዕድገት ካስመዘገቡ ሀገሮች ተርታ በግንባር ቀደም ሥፍራ ላይ እንገኛለን፡፡ የአዲሱን ሚሊኒየም ሁለተኛውን አሥር ዓመት በተመሳሳይ የዕድገት ፍጥነት ከቀጠልንም መካከለኛ ገቢ ያላት ሀገር እንደምትኖረን እርግጠኛ መሆን ይቻላል፡፡

2009 .ም የሥራ አፈፃፀማችን የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ሁለተኛው ዓመት የሥራ አፈፃፀም ይሆናል፡፡ የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን የመጀመሪያ ዓመት ውጤትም የሚታወቀው በ2009 .ም በመሆኑ የዚህኑም ውጤት አብሮ መመልከቱ የሀገራችንን የዕድገት ግስጋሴ ለመረዳት በእጅጉ ይጠቅማል፡፡

2008 .ም በሀገራችን ከፍተኛ ድርቅ ተከስቶ የነበረም ቢሆን ኢኮኖሚያችን በፈጣን ሁኔታ በማደግ የ8.0 በመቶ አማካይ ዓመታዊ ዕድገት ማስመዝገቡ ይታወሳል፡፡ በተለይም በዚሁ ዓመት የተከሰተው ድርቅ ለኢኮኖሚው ወደ 37 በመቶ ድርሻ የሚያበረክተውን የግብርና ዘርፍ ተጨማሪ እሴት በዕቅድ ከተያዘው የ8.2 በመቶ የዕድገት ምጣኔ በማነስ የ2.3 በመቶ ዕድገት እንዲያስመዘግብ ቢያደርግም የሌሎች ዘርፎች ማለትም የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከነባር ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም መሻሻል እንዲሁም ወደ ማምረት የተሸጋገሩ አዳዲስ የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንቶች በመኖራቸው ምክንያት እጅግ ፈጣን ዕድገት ማለትም የ18.4 በመቶ ዕድገት ማስመዝገብ ችሏል፡፡

ለኢንዱስትሪ ዘርፍ የ20.6 በመቶ ፈጣን ዕድገት ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ባሻገር የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍም የ25 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ የአገልግሎት ዘርፉም ፈጣን ዕድገት በመቀጠሉ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የመጀመሪያው ዓመትም ኢኮኖሚያችን የሚያጋጥሙትን የተለያዩ ተግዳሮቶችን የመቋቋም አቅሙ ከፍተኛ እየሆነ መምጣቱን በሚያስመሰክር አኳኋን ፈጣንና ፍትሃዊ ዕድገት ማስመዝገብ መቀጠላችንን አስመስክሮ አልፏል፡፡

2009 .ም የኢኮኖሚ ዕድገት መረጃ በቅርቡ የታወቀ በመሆኑ ኢኮኖሚያችን በዓመቱ በአማካይ የ10.9 በመቶ ማደጉን ያመለክታል፡፡ ይህ ውጤትም ኢኮኖሚያችን በጠንካራ ሁኔታ ማገገሙን የሚያመላክትና በዓመቱ ይገኛል ተብሎ ከተተነበየው የ11.1 በመቶ ጋር እጅግ ተቀራራቢ እንደሆነ ማየት ይቻላል፡፡ ለዚሁ ዕድገት ግብርናችን የ6.7 በመቶ እሴት መጨመሩንና ይህም ከተተነበየው የ8.0 በመቶ ዕድገት በመጠኑ አንሶ የተገኘው የበልግ ግብርናችን በአንዳንድ አካባቢዎች ከድርቅ ክስተት አለመላቀቁና የአሜሪካን መጤ ተምች በአንዳንድ አካባቢዎች የበቆሎ ምርትን በመጠኑ በመጉዳቱ ነው፡፡

ሆኖም ግን የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፎች እጅግ ፈጣን ዕድገት ያስመዘገቡ በመሆኑ የዕድገት ምጣኔውን ከትንበያው ጋር ተቀራራቢ እንዲሆን አድርጐታል፡፡ በዚህም መሠረት የኢንዱስትሪ ዘርፍ ባጠቃላይ የ18.7 በመቶ እጅግ ፈጣን ዕድገት ሲያስመዘግብ የትላልቅና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች የ23.2 በመቶ እና የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የ21 በመቶ ሁለቱም የኢንዱስትሪ ዘርፎች የላቀ ፍጥነት ያለው ዕድገት አስመዝግበዋል፡፡ የአገልግሎቱ ዘርፍም አምና ከነበረው ዕድገት በተሻለ ደረጃ የ10.3 በመቶ ማስመዝገብ ችሏል፡፡

በዚህ ውጤት መሠረትም በ2009 .ም የኢኮኖሚያችንን ጥንቅርና ድርሻ ስንመለከት ግብርና የ36.3 በመቶ፣ ኢንዱስትሪ የ25.6 በመቶ ከዚህም ውስጥ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የ6.4 በመቶ እና የአገልግሎት ዘርፍ የ39.3 በመቶ ድርሻ ነበራቸው፡፡ እነዚህ የድርሻ ሽግሽጐችን በምናይበት ጊዜ ኢኮኖሚያችን ተስፋ በሚሰጥ ደረጃ የመዋቅራዊ ሽግግር ማድረግ መጀመሩን ነው፡፡

ባጠቃላይ በዓመቱ በኢኮኖሚያችን ውስጥ የተካሄደው የኢንቨስትመንት አፈፃፀም ለአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርትና ምርታማነት ዕድገት፣ የሥራ ስምሪትና የድህነት ቅነሳ ጋር ተያይዘው ለተቀመጡት ግቦች መሳካት አዎንታዊ አስተዋፅኦ እንደነበራቸው በውል መመልከት ይቻላል፡፡

ይህም ሆኖ በያዝነው ዓመት በምንሠራው የግብርና ሥራ በተከታታይ የሚከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም የሚያስችል የተፈጥሮ ሃብትና ውሃን ማዕከል ያደረገ የመስኖ ግብርናን ይበልጥ ለማስፋፋት የተሻለ ጥረት ማድረግ ይገባናል፡፡ ከዚሁ በተጓዳኝ በኢንዱስትሪ ዘርፉም ውስጥ እንደ ትላልቅና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች እጅግ በላቀ ፍጥነት ያላደገውን የአነስተኛና ጥቃቅን ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ በፍጥነት እንዲያድግ የላቀ ርብርብ ማድረግም ይገባናል፡፡

2010 የትኩረት አቅጣጫዎች

11 ነጥብ1 በመቶ ዓመታዊ አማካይ ዕድገት

ይህንን በማድረግም በ2010 .ም መጨረሻ ላይ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት (GDP) ያለውን ድርሻ ወደ 7 በመቶ ለማሳደግ መረባረብ ይገባናል፡፡ በአጠቃላይ የአምራች ዘርፎች ወደ ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡ ምርቶች ላይ በማተኮር የእሴት ጭማሪውን ይበልጥ እንዲያጐለብቱ መሥራት የዓመቱ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ይሆናል፡፡ በአነስተኛ ማሳ የቤተሰብ ግብርና ልማትን ማዘመኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የተማሩ ወጣቶችና የግሉ ባለሃብት በግብርና ሥራ ላይ ይበልጥ እንዲሠማሩ የሚሠራ ይሆናል፡፡

በዚህም መሠረት በ2010 .ም ፈጣንና ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲኖረው የ11.1 በመቶ ዓመታዊ አማካይ ዕድገት እንዲሆን ይደረጋል፡፡ የኢኮኖሚው ፍትሃዊነት እንዲረጋገጥም ግብርና አሁንም በርካታ የህብረተሰብ ክፍል የሚሳተፍበትና የዕድገታችን ምንጭ በመሆኑ ቢያንስ የ8.0 በመቶ እንዲያስመዘግብ ይጠበቃል፡፡ ፈጣን ዕድገት ማረጋገጣችን እዚያው ሳለ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ትራንስፎርሜሽን እንዲያቀላጥፍ የኢንዱስትሪ ዘርፍ በተለይም የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ እጅግ ፈጣንና የላቀ ዕድገት ማስመዝገቡን እንዲቀጥል ይደረጋል፡፡ ከጥቃቅን አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች 22.6 በመቶ አካባቢና ከትላልቅ ኢንዱስትሪዎች የ21.8 በመቶ እና ከኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የ23 በመቶ ዕድገት ይጠበቃል፡፡ የአገልግሎት ዘርፉም የ11 በመቶ ዕድገት እንዲያስመዘግብ ይጠበቃል፡፡

2009 .ም የተረጋጋ የማክሮ-ኢኮኖሚን የመፍጠር ጉዳይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ሲተገበር ቆይቷል፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን የዋጋ ንረት በነጠላ አሀዝ እንዲገደብ አቅጣጫ መቀመጡም ይታወቃል፡፡ ይህንኑም ለማሳካት በ2009 .ም የግብርና ምርትና ምርታማነት የማሳደግ፣ የዋጋ ማረጋጊያ የእህል ክምችት መያዝ፣ ከዝቅተኛና የተረጋጋ የዋጋ ምጣኔ ጋር የሚጣጣም የገንዘብ፣ የፊሲካልና የውጭ ምንዛሬ ተመን ፖሊሲዎችን መከተልን እንደ ዋና ዋና የማስፈፀሚያ ስትራቴጂዎች ተወስደው ተሰርቷል፡፡

በዚህም መሠረት የ2009 .ም የአሥራ ሁለት ወራት ተንከባላይ አማካይ የዋጋ ግሽበት በተያዘው ዕቅድ መሠረት በነጠላ አሃዝ መገደብ የተቻለ ሲሆን ይህም አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 7.2 በመቶ ሆና ተመዝግቧል፡፡ በተጨማሪም ጠቅላላ የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ የዋጋ ግሽበት እንደቅደም ተከተላቸው የ7.4 በመቶእና የ7.1 በመቶ ሆኗል፡፡ ይህም በበኩሉ የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ ሆኔታ እንዲኖር ተግባራዊ የተደረጉ የፊሲካልና የገንዘብ ፖሊሲዎች እንዲሁም የተወሰዱ አስተዳደራዊ ርምጃዎች የተፈለገውን ውጤት ያስገኙ መሆናቸውን ያመለክታል፡፡

ታክስና ሌሎች ገቢዎችን ማጠናከር

ከፊሲካል ፖሊሲ አኳያ የአገር ውስጥ የፋይናንስ አቅምን በማጠናከር ከታክስና ሌሎች ምንጮች የሚገኙ ገቢዎችን በአግባቡ መሰብሰብ፣ የመንግሥትን ወጪዎች ፍትሃዊ የሃብት ድልድልንና ፈጣን ዕድገትን በሚያረጋግጥ መልኩ መፈፀም፣ የታክስና የጉምሩክ ፖሊሲዎች ገቢ ከማስገኘት ባለፈ የኢንዱስትሪ ልማትንና የኤክስፖርት ግኝትን በሚያበረታታ መልኩ ለመቃኘት ጥረት ተደርጓል፡፡ ከዚሁ በተጨማሪም መንግሥት የሚወስዳቸውን ብድሮች በአግባቡ ማስተዳደር የሚያስችል የፊሲካል ዲስፒሊን ማስፈንን እንደዋነኛ ስልት በመውሰድም ሲሠራ ነበር፡፡ በተመሳሳይ የመንግሥት የበጀት ጉድለት ከአጠቃላይ አገራዊ ምርት ድርሻ ወደ 3 በመቶ አካባቢ እንዲሆን ታቅዶ የተሻለ አፈፃፀም በመመዝገቡ የ2.5 በመቶ እንዲሆን ከመደረጉም ባሻገር አሸፋፈኑም የሀገር ውስጥ ምንጮችን አሟጦ በመጠቀምና የተሻለ ድርሻ እንዲኖራቸው በማድረግ የተፈፀመ ነበር፡፡

በዚህም መሠረት በ2009 .ም ከታክስና ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች ለመሰብሰብ ከታቀደው የ94.3 በመቶ ለማሳካት ተችሏል፡፡ የታክስ ገቢ ለብቻው በሚታይበት ጊዜ አፈፃፀማችን የ92 በመቶ አካባቢ ሆኗል፡፡ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ17 በመቶ አካባቢ ዕድገት የተመዘገበ ቢሆንም ይህ አፈፃፀም ወትሮ ከተለመደው በትንሹ የ98 በመቶ አፈፃፀም ጋር ሲነፃፀርም ሆነ ኢኮኖሚያችን ከሚያመነጨው ገቢ ሊሰበሰብ ከሚገባው ጋር ሲነፃፀር አንሶ የሚታይ ነው፡፡

በመሆኑም በ2010 .ም ይህንን ሁኔታ ለመቀየር በአዲስ መልክ ተጠናክሮ የተጀመረውን የታክስ ሪፎርም ሥራ በተለይም በትልልቆቹ የታክስ ከፋዮች ላይ በማተኮር መሥራት እንዳለብን የሚያመላክት ነው፡፡ የታክስ ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራሙ የሚያተኩርባቸውን የውዝፍ ዕዳ አሟጦ የመሰብሰብ፣ የታክስ ኦዲት ሥርዓቱን ዓለም አቀፍ ተሞክሮን መሠረት በማድረግ የማዘመንና የስጋት የሥራ አመራርን መሠረት ያደረገ እንዲሆን የማድረግ፣ የታክስ መረጃ ሥርዓት ላይ ያለውን ችግር ለመቅረፍ የመረጃ ቴክኖሎጂን ሥርዓት ባለው መንገድ የመጠቀም፣ እንዲሁም የታክስ አስተዳደር መሥሪያ ቤቱን የውስጥ ድርጅታዊ ጤንነት የመጠበቅና የታክስ ሰብሳቢ ሙያተኞችን በመሥሪያ ቤቱ የማቆየት ሥራ እንዲሁም ውጤት ተኮር የሥራ አመራርን የማጐልበት ሥራ የሚሠራ ይሆናል፡፡

ይህንንም በማድረግ በዘርፉ የሚታየውን ያለአግባብ የመጠቀም ዝንባሌና ተግባር እንዲሁም ሙስና የታክስ ከፋዩን ህብረተሰብ በስፋት በማሳተፍ መታገልና የአስተዳደር ሥርዓቱን ማጐልበት የሚኖርብን ይሆናል፡፡ በትልልቅ ታክስ ከፋዮች ትኩረት ማድረጋችን እንደተጠበቀ ሆኖ በተለይም በኮንስትራክሽን ዘርፉ እንዲሁም በማኑፋክቸሪንግና ሌሎች የታክስ እፎይታ ጊዜ ከተጠቀሙ በኋላ በህጉ መሠረት የማይከፍሉ ታክስ ከፋዮች ላይ ትኩረት ሰጥተን የህግ ማስከበሩን ሥራ አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ በሀገሪቱ ባሉ ዋና ዋና ከተሞች ለንግድና አገልግሎት ተብሎ የተገነቡ ህንፃዎች አካባቢ ከኪራይ ጋር በተያያዘ የሚካሄደውን ማጭበርበርና ታክስ ሥወራም እንደዚሁ ትኩረት ሰጥተን ህጋዊ መስመር ለማስያዝ የምንሠራ ይሆናል፡፡ መንግሥት የተጀመረውን የልማት ሥራ ለማስቀጥልና ብቁ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለው አቅም ከሀገር ውስጥ ሃብት ለማሟላት የተያዘው ውጥን እንዲሳካ የሀገር ውስጥ የታክስ ገቢ መሰብሰብ ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ነው፡፡

በዘንድሮ ዓመት የ"" የግብር ከፋዮች የታክስ ግመታ በተመለከተ የተከሰተው የግምት መዛባትና በአንዳንድ ታክስ ከፋዮች አካባቢ የተከሰተ የዕቃ መሰወር ዓይነት ችግር እንዳይከሰትና የታክስ አከፋፈሉ ተገማች እንዲሆን በጥናት ላይ የተመሠረተና የታክስ ከፋዮች ራሳቸው የተሳተፉበት የመፍትሄ አቅጣጫ ለመቀየስ የሚሠራ ይሆናል፡፡ ይህንን በማድረግም መዝገብ የማይዙ የታክስ ከፋዮች ጋር የሚገጥመውን ውዝግብ ለማስቀረት ጥረት ይደረጋል፡፡

የውጭ ምንዛሬ ተመን ማሻሻያ

2009 .ም የተጠቀምነው የገንዘብ ፖሊሲና የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ልማት ትኩረት ያደረጉት የገንዘብ አቅርቦትና ዝውውር ሚዛናዊ እንዲሆን፣ የተረጋጋና በነጠላ አሃዝ የተገደበ የዋጋ ግሽበት እንዲኖር ማድረግና የተረጋጋና የውጭ ንግድን የሚያበረታታ የውጭ ምንዛሬ ፖሊሲን መከተል እንዲሁም የፋይናንስ ተቋማት የታቀደውን መዋቅራዊ ሽግግር እንዲያግዙ ማስቻል ላይ ነበር፡፡

የተረጋጋ የውጭ ንግድን የሚያበረታታ የውጭ ምንዛሬ ፖሊሲን ከማስፈን አኳያ በ2009 .ም ከሞላ ጐደል የተረጋጋ ተመን የነበረ ቢሆንም ቀጥለን እንደምናየው ለባለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት ኤክስፖርታችን ባለበት በመቆሙ ምክንያት የውጭ ምንዛሪ አቅርቦቱንና ፍላጐትን ለማሟላት ከፍተኛ እጥረት አጋጥሞን ነበር፡፡ ስለሆነም የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ እንዲኖር ከማድረግ አኳያ ሀገራችንን የገጠማት ዋነኛ ፈተና የኤክስፖርት ገቢያችንን በፍጥነት በማሳደግ የሚፈለገውን የውጭ ምንዛሬ በከፊልም ቢሆን በማግኘት እየሰፋ የመጣውን የውጭ ንግድ ሚዛን ማጥበብ ነው፡፡ በመሆኑም የ2010 .ም ዕቅድ ዋነኛ ትኩረትም የኤክስፖርት ምርትና ግብይት ጉዳይ የሞት የሽረት ጉዳይ ተደርጐ መወሰድና ለኤክስፖርት ገቢያችን 80 በመቶ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱትን ቡና፣ ሰሊጥ፣ ጥራጥሬ፣ ቅመማቅመም፣ አበባና የቁም እንስሳት በመጠንና በጥራት በማሳደግ ከፍተኛ ለውጥ በማምጣት ላይ ሊሆን ይገባል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ በማዕድን ዘርፍ ወርቅና ሌሎች ጌጣጌጥ ማዕድናት እንዲሁም እየተስፋፉ የመጡትን ኢንዱስትሪ ፓርኮች ማዕከል በማድረግ የማኑፋክቸሪንግ ምርቶች ኤክስፖርት በፍጥነት እንዲያድግ በማድረግ ላይ ይሆናል፡፡ ይህንንም ለማበረታታት የውጭ ምንዛሬ ተመን ላይ በጥናት ላይ የተመሠረተ ማሻሻያዎች የሚደረጉ ይሆናል፡፡

የሀገራችን የፋይናንስ ኢንዱስትሪ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ትራንስፎርሜሽን የሚያግዝበት አንድና ዋናው መንገድ ቁጠባን በማበረታታትና የፋይናንስ አቅርቦትን በማሳደግ ነው፡፡ ባንኮቻችን ለግሉ ዘርፍም ሆነ ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች የኢንቨስትመንት ፋይናንስና የሥራ ማስኬጃ በማቅረብ ትልቅ ሚና እየተጫወቱ ይገኛል፡፡ የባንኮች ተቀማጭ በዓመቱ ውስጥ በ23 በመቶ ያደገ ሲሆን ለዚህ ውጤት መገኘት ባንኮች በርካታ ቅርንጫፎችን በመክፈት ለህዝቡ ተደራሽ መሆን በመቻላቸው ነው፡፡ የፋይናንስ ተቋማት አትራፊነትም ወትሮ ከሚታወቀው ምጣኔ በላይ መሆኑ የተረጋገጠ በመሆኑ የሀገራችን ባንኮች እጅግ አትራፊ ሆነው ቀጥለዋል፡፡ ይህም ጤናማ የፋይናንስ ተቋማት ሥርዓት እየተዘረጋ መሆኑን ያመለክታል፡፡ በሁለተኛው ዕድገትና ትራንስ ፎርሜሽን ዘመን መጨረሻ ቁጠባ ከሀገር ውስጥ አጠቃላይ ምርት ያለው ድርሻ ወደ 29 በመቶ እንዲያድግ የፋይናንስ ተቋማት የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማድረግ የፖሊሲ ድጋፎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ ይሆናል፡፡

ምርትና ምርታማነት

የሀገራችንን አምራች ዘርፎችን በማጐልበት በጥራት፣ በምርታማነትና በተወዳዳሪነት የላቀ ዕድገት እንዲመጣ በትኩረት ሲሠራ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት የስትራቴጂያዊ የምግብ ሰብሎች ምርትና ምርታማነት በማደጉ ምክንያት ከአምናው ጋር ሲነፃፀር ወደ 9.0 በመቶ የሚጠጋ ዕድገት ለማስመዝገብ ተችሏል፡፡ የምርታማነት ዕድገትን በተመለከተም በአማካይ ወደ 8.4 በመቶ ማሳደግ ተችሏል፡፡ ሆኖም ለምርታማነት ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክተው የምርጥ ዘር አቅርቦት በታሰበው ልክ ባለመሆኑ ምንም እንኳ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ከዕቅዱ ጋር የተመጣጠነም ቢሆን የምርታማነት ዕድገቱ የታሰበውን 12 በመቶ ያህል ዕድገት ሳያስመዘግብ ቀርቷል፡፡ በመሆኑም በ2010 .ም ሥራችን ለአርሶ አደሩና ከፊል አርሶ አደሩ የምንሠጠው የኤክስቴንሽን አገልግሎት ከተሟላ የምርጥ ዘር አቅርቦትና እንደዚሁም የተሟላ የቴክኖሎጂ ምክረ-ሃሣብ መሠረት እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት መደረግ ያለበት ይሆናል፡፡

የዋና ዋና ሰብሎች ምርታማነትና የምርት ዕድገት እንዲጨምር የራሱን የማይተካ ሚና የሚጫወተው የግብርና ሜካናይዜሽን መሆኑ ይታወቃል፡፡ በ2009 .ም ከግብርና ሜካናይዜሽን አኳያ የአነስተኛ እርሻ መሣሪያዎች አቅርቦትና የሰውና የእንስሳት ጉልበትን ምርታማ የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎች አርሶ አደሩ እንዲጠቀም ለማድረግ በተሠራው ሥራ መልካም ውጤቶች መገኘት ጀምረዋል፡፡ ስለሆነም በ2010 .ም የአጨዳና መውቂያ፣ የዘር መዝሪያና ተከላ እንዲሁም የማሳ ማዘጋጃ መሣሪያዎች በነፍስ ወከፍና በቡድን ለማቅረብ የሀገር በቀል ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎችና ከቴክኒክና ሙያ የተመረቁ ወጣቶች ተሳትፎ እንዲጐለብትና መልካም ተሞክሮዎቹ እንዲሠፉ ለማድረግ የሚሠራ ይሆናል፡፡

ግብርናችንን ይበልጥ ለማዘመን ከተያዙ ሥራዎች መካከል አርሶአደሩና አርብቶ አደሩ የላቀ ዋጋ የሚያስገኙ ሰብሎችና የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ላይ እንዲሠማሩ የማድረግ ሥራ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ በዚህም መሠረት በአርሶ አደሩም ሆነ በግል ባለሃብቱ ዓመቱን በሙሉ የመስኖን ውሃ በመጠቀም የሚመረተው የሆርቲካልቸር ምርት በመጠኑ በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል፡፡ የ2009 .ም አፈፃፀም የሚያሳየውም የአትክልት፣ ፍራፍሬና ሥራሥር ሰብሎች የምርት ጭማሪ ወደ 38% መድረሱን ነው፡፡ ይህ መልካም ውጤት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በዚህ ዘርፍ አሁንም እንቅፋት ሆኖ የሚገኘው የጥራት አመራረት ሥርዓት የማስፈንና ከፊሉን ኤክስፖርት ለማድረግ የሚያስችል የሎጅስቲክስ አቅርቦት የማሻሻል እንዲሁም የአርሶ አደሩንና የግል ባለሃብቱን የማምረት ቅንጅት ወይም አውትግሮወር (Outgrower) ሥርዓት ማጐልበት ይሆናል፡፡ በ2010 .ም እነዚህን ማነቆዎች መፍታት መጀመር ያለብን እና ከዘርፉ በ2009 .ም የተገኘውን 220 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ኤክስፖርት ወደ 400 ሚሊዮን ዶላር ለማሳደግ እንሠራለን፡፡

ከሆርቲካልቸር ሰብሎች በተጨማሪ የላቀ ዋጋ የሚያስገኙት ቡናና ሻይ፣ የቅባት እህሎች፣ ጥራጥሬና ቅመማቅመም ሰብሎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰብሎች የላቀ ዋጋ ማስገኘታቸው ብቻ ሳይሆን እዚያ ሳሉ የኤክስፖርት እንዲሁም የኢንዱስትሪ ግብአት ሰብሎችም ጭምር ናቸው፡፡ በሰብሎቹ በአማካይ ከ15% እስከ 20% የሚሆን የምርታማነት ዕድገት እንዲመጣ የሚሠራ ይሆናል፡፡ ይህንን በማድረግም የቁም እንስሳትን ኤከስፖርት ጨምሮ በአጠቃላይ ከግብርና ዘርፍ ወደ 4.0 ቢሊዮን ዶላር ኤክስፖርት ገቢ እንዲኖረን በትጋት የሚሠራ ይሆናል፡፡

የእንስሳትና ዓሣ ሃብት ልማት የላቀ ዋጋ የሚያስገኙ የግብርና ልማት ሥርዓት ውስጥ የሚመደብ ነው፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው ግን የአመራረት ሥርዓቱ ከኋላቀር ባህላዊ የአመራረት ሥርዓት ደረጃ በደረጃ ወደ ዘመናዊ የአረባብና የዝርያ ማሻሻል፣ የእንስሳቱን ጤና መጠበቅና ጥራትና ቁጥጥር ማሳደግ እንዲሁም ዘመናዊ የእንስሳት መኖ አመራረት ሥርዓት ውስጥ ሲገባ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ በአርሶ አደሩም ሆነ በአርብቶ አደሩ አካባቢ ሊሠፉ የሚችሉ ምርጥ ተሞክሮዎች የተገኙ በመሆኑ የ2010 .ም ዕቅድ እነዚህን ምርጥ ውጤቶች በማስፋት ላይ ያተኮረ ይሆናል፡፡

የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ

የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ፈጣንና የላቀ ዕድገት እንዲያረጋግጥ ማድረግ የኢኮኖሚያችንን መዋቅራዊ ትራንስፎርሜሽን ለማረጋገጥ ቀዳሚ ሥራ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ትኩረታችንን የሰው ጉልበትን በስፋት የሚጠቀሙና ኤክስፖርት መር የሆኑ ቀላል የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ላይ በማድረጋችን የሀገር በቀል ኩባንያዎችና የተመረጡ ስመ-ጥር የሆኑ የውጭ ኩባንያዎች በዘርፉ በስፋት መሠማራት ጀምረዋል፡፡ ይህንኑ ጅምር ይበልጥ ለማስፋፋትና ለማጠናከር የሀገር በቀል ኩባንያዎች ከኮንስትራክሽንና ሪልእስቴት፣ ከንግድና አገልግሎት ዘርፎች ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲገቡ አስፈላጊውን ድጋፍ በተከታታይና በጥራት መስጠት የሚገባን ይሆናል፡፡ ከዚሁ በተጨማሪም የክልል መንግሥታት ትኩረት ሰጥተው እየሠሩበት ካለው ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ እንዲሁም ከመካከለኛ ወደ ትላልቅ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ሽግግር እንዲከናወን መትጋት ያለብን ይሆናል፡፡ በዚህም መሠረት ቅድሚያ ትኩረት በተሰጣቸው የጨርቃጨርቅና አልባሳት፣ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ የምግብና መጠጥ እንዲሁም ሌሎች አግሮፕሮ ሰሲንግ ፋብሪካዎች ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋና የነባር ፋበሪካዎች የአቅም አጠቃቀም እንዲሻሻል የሚሠራ ይሆናል፡፡ ሌሎች ማለትም የፋርማ ሲቲካል፣ የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብአቶች ማምረቻ ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ እና የኤሌክትሪካልና ኤሌክትሮኒክስ ኢንዱስትሪዎች በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ የሆነ ምርት ነገር ግን የኢምፖርት ዕቃዎች በመተካት ላይ በማተኮር እንዲሠሩ እየተሠጣቸው ያለ ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

መንግሥት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ልማት እንደ አንድ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ማስፈፀሚያ መሳሪያ አድርጐ እየተጠቀመ ያለ በመሆኑ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎችን የመሬት፣ የመሠረተ ልማት፣ የአንድ መስኮት አገልግሎት አሰጣጥና ለሀገር በቀል ኩባንያዎች ደግሞ የፋይናንስ፣ የክህሎትና የኢንዱስትሪ አመራር ችሎታ እንዲሁም የገበያ ትስስር ችግራቸውን በሚፈታ መንገድ በመቃኘቱ ውጤታማ መሆን ጀምሯል፡፡ ይህንኑ ጅምር ይበልጥ በጥራት የማስፋፋት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

መሰረተ ልማት

የመሠረተ ልማት ክፍተቶችን መሙላትና የአገልግሎት አቅርቦት ጥራትን ማሳደግ የኢኮኖሚያችንን ተወዳዳሪነት ከሚወስኑ ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡ ይህንኑ በመገንዘብ መንግሥት የመሠረተ ልማት ክፍተቶችን ለመሙላት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በ2009 .ም በገጠር ትራንስፎርሜሽን ትልቁን ሚና የሚጫወተውን የገጠር መንገድ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በተሠራው ሥራ ወደ 75 በመቶ የሚሆኑ የገጠር ቀበሌዎች እርስበርስና ከዋና ዋና መንገዶች እንዲገናኙ የሚያደርግ የገጠር መንገድ ተገንብቷል፡፡ የመንገዶቹን እንክብካቤ በቀጣይነት ከሠራን የአርሶአደሩንና አርብቶአደሩን ምርቶች ወደ ገበያ ለማውጣትና ወደ አርሶአደሩና አርብቶ አደሩ የሚቀርቡ ግብአቶችንና አገልግሎቶችን ለማድረስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ በ2010 .ም የተጀመረውን የገጠር ተደራሽነት መንገድ ሥራ ወደ 85 በመቶ ለማድረስና በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ሁሉንም ቀበሌዎች ለማዳረስ የሚሠራ ይሆናል፡፡

2009 .ም ዋና ዋና መንገዶችን ማጠናከርና ደረጃ ማሻሻል፣ አገናኛ መንገዶችን ግንባታና ደረጃ ማሻሻል ሥራ ከዕቅዱ 97 በመቶ ማሳካት ተችሏል፡፡ ወደ 8 በመቶ የሚሆኑ መንገዶች አነስተኛ አፈፃፀም የታየባቸው በመሆኑ ኮንትራቱን አቋርጦ ለሌላ ኮንትራክተር ለመስጠት እየተሠራ ይገኛል፡፡ ባጠቃላይ ግን የመንገዶች ፕሮጀክቶች አፈፃፀም በሚታይበት ጊዜ በአብዛኛው በታቀደው መሠረት የፕሮጀክት አፈፃፀሙ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ የ2010 .ም ትኩረት የሚሆነው የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን የማስጨረስና አዳዲሶቹን የመጀመር ሥራ እንደተጠበቀ ሆኖ የመንገዶች ልማት አካሄዳችንን በህገ-መንግሥቱ በተቀመጠው የፌዴራልና የክልል መንገዶች ክፍፍል መሠረት የፌዴራል ሥርዓት የሚከተሉ ሀገሮች ልምድ በመውሰድ የፌዴራልና የክልል መንገዶች ለመለየት የተጀመረውን ጥናት በማጠናቀቅ ወደ ትግበራ የሚገባ ይሆናል፡፡ በዚህም መሠረት የፌዴራልና የክልል ያልተምታታ የሥራ ድርሻ የሚኖር ይሆናል፡፡

የባቡር መሠረተ-ልማት ግንባታ እጅግ ግዙፍ ፋይናንስ የሚጠይቅ በመሆኑ በቅርቡ የተጠናቀቀውን የአዲስ አበባ ጂቡቲ መሥመር ወደ ተሟላ ሥራ እንዲገባ የማድረግና በግንባታ ሂደት ላይ ያሉትን የማስቀጠል ሥራ የ2010 ዋና ዕቅድ ይሆናል፡፡ አዳዲስ ግንባታዎችን ለማስጀመር የሚያስችል ፋይናንስ ማግኘት ያልተቻለ በመሆኑ ይኽው እስከሚስተካከል ድረስ በዘንድሮ ዓመት አዳዲስ ግንባታዎች የሚጀመሩበት ሁኔታ አይኖርም፡፡

በኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር እጅግ ተፈላጊና ወሳኝ መሠረተ-ልማቶች ውስጥ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ዋናውና ወሳኙ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህም መሠረት በቅርቡ የተጠናቀቀውን የጊቤ-3 ሃይል ማመንጫ በሙሉ አቅሙ እንዲሠራ ማድረግ፣ ስልሳ በመቶ የደረሰውን የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማፋጠን፣ የገናሌ-3ን ግድብ አጠናቅቆ ሃይል ማመንጨት መጀመር እንዲሁም የኮይሻ ግድብ፣ የመልካ ሰዲ ተርማል ማመንጫ፣ የአሉቶ ጂኦተርማል ማመንጫ፣ የረጲ ባዮማስ ማመንጫ፣ የአይሻ የንፋስ ሃይል ማመንጫ ሥራዎች በዕቅዳቸው መሠረት ሥራቸው እንዲፋጠን በዘንድሮ ዓመት ትኩረት የተሰጣቸው ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡

መንግሥት ከሚያከናውነው የሃይል ማመንጫ ሥራ በተጨማሪ በቅርቡ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ያፀድቀዋል ተብሎ በሚጠበቀው የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት Private -Public-Partnership(ppp) ህግ መሠረት ለመጪው ጊዜ ኢኮኖሚያችን የሚፈልገውን ሃይል ከወዲሁ ለማዘጋጀት የግሉ ዘርፍ በሃይል ማመንጨቱ ሥራ እንዲሳተፍ የመጋበዝና የማሳተፍ እንዲሁም በጅምር ላይ ያሉትን ወደ ሥራ እንዲገቡ በትኩረት የሚሠራ ይሆናል፡፡

የሃይል ማስተላለፊያና ሳብስቴሽን ሥራዎች እንዲሁም የሳብስቴሽኖች አቅም የማጐልበት ሥራ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን፣ ክላስተሮችንና ሌሎች የልማት ማዕከላትን መሠረት አድርጐ የሚሠራ ይሆናል፡፡

የኤሌክትሪክ ማከፋፋልና አገልግሎት አቅርቦት ላይ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ እንዲያስችል ያልተማከለ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አቅራቢ ድርጅቶችን ክልሎች እንዲያቋቁሙ በማድረግና አቅማቸውን በማሳደግ ወደ ሥራ እንዲገቡ ይደርጋል፡፡ ይህንንም መሠረት አድርጐ የገጠር ኤሌክትሪክ ተደራሽነት ሥራ ከግሪድ ውጭ ባልተማከለ ሁኔታ ከታዳሽ ሃይሎች የማቅረብ ፕሮጀክቶች በዘንድሮ ዓመት ወደ ሥራ እንዲገቡ ይደረጋል፡፡

የዲጂታል መሠረተ ልማት አቅርቦትን በተመለከተ የማምረቻና የንግድ ሥራዎች፣ የመማር ማስተማር አገልግሎት፣ የመንግሥት የአገልግሎት አሰጣጥ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ የግል ባለሃብቶች በአይ..ቲ ሶፍትዌር ግንባታ እንዲሁም የአይ..ቲ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ እንዲሳተፉ ለማድረግ የተጀመረው ሥራ ፍሬ እያፈራ ያለ በመሆኑ ይህንንም ማጠናከርና ስፋቱም እንዲጨምር ተደርጐ ይሠራል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ በገጠር ማዕከላት የኢንተርኔትና የመረጃ ፍላጐትን ለማርካት በእያንዳንዱ ቀበሌ የህዝብ ኮሙኒኬሽን ማዕከል ለማደራጀት የተጀመረው ሥራ እስካሁን ወደ 12% የሚሆኑ ቀበሌዎችን ያዳረሰ ሲሆን በ2010 .ም ይህንን ሽፋን ወደ 40% ለማድረስ የሚሠራ ይሆናል፡፡

የሰው ሀብት ልማት

የሰው ሃብታችን የተማረ፣ ክህሎት ያለውና ከቴክኖሎጂ ጋር የተዋወቀ እና የሚጠቅም እንዲሆን የትምህርትና ሥልጠና ፕሮግራሞቻችን በሁሉም እርከኖች የትምህርት ተሳትፎ በማሳደግ ረገድ መልካም ውጤቶች ተገኝተዋል፡፡ በዚህ ዙሪያ እንደ እጥረት ወስደን በፍጥነት ማሻሻል የሚገባን የሙአለ-ህፃናት ትምህርትና የገጠሩን ትራንስፎርሜሽን በማቀላጠፍ ዙሪያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክተው የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጐልማሶች ትምህርት አካባቢ ነው፡፡

የአጠቃላይ ትምህርት፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠናም ሆነ የከፍተኛ ትምህርት ላይ ልዩ ትኩረት መስጠት የሚገባን በትምህርት ጥራት ዙሪያ መሆን እንዳለበት ተወስኖ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ ከዘንድሮ ዓመት ጀምሮ ዩኒቨርሲቲዎችን የማስፋፋት እና የህንፃዎችን ግንባታ ሥራ ገታ አድርገን የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና በእያንዳንዱ ወረዳ እንዲስፋፋ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲዎች የላቦራቶሪ፣ የወርክሾፖች፣ የላይብረሪዎችንና ሌሎች ግብአቶች የማሟላት ሥራ ላይ ትኩረት ይሰጣል፡፡ ከሁሉም በላይ ለትምህርት ጥራት ወሳኙን ሚና የሚጫወቱት መምህራን በመሆናቸው በመምህራን የኑሮ ሁኔታ፣ ክህሎትና የሥራ ዲስፕሊን እንዲሁም የሥራ አካባቢ ማሻሻል ላይ ትኩረት ሰጥተን መሥራት የሚገባን ይሆናል፡፡ ከዚሁ ባልተናነሰ ሁኔታ መልካም ዜጋ በማነጽ ትልቁን ድርሻ በሚወስደው የሥነ-ዜጋና የሥነ-ምግባር ትምህርት ዙሪያ በጥናት የተለዩትን ጉድለቶች በማስተካከል ትምህርቱ በጥራት እንዲሠጥ የሚሠራ ይሆናል፡፡ በትምህርት ሴክተሩ ከላይ እስከታች የውጤታማነት ስኬት ወይም ዴሊቨሮሎጂ (Deliverology) ፅንሰ-ሃሳብ ተግባራዊ ለማድረግ የተጀመረውን ሥራ በጥራት እንዲፈፀምም የሚደረግ ይሆናል፡፡

2009 .ም በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም በመታገዝ ፍትሃዊ፣ ተደራሽ፣ እንዲሁም ጥራቱን የጠበቀ መሠረታዊ ጤና አገልግሎት ለመስጠት የሠራነው ሥራ ውጤታማ ነበር፡፡ የእናቶችንና የህፃናትን ጤና አገልግሎት እንዲሁም ተላለፊ በሽታዎችን የመከላከልና ቁጥጥር ሥራ የበለጠ ጥራቱ የተጠበቀ እንዲሆን ከምናደርገው እንቅስቃሴ ባሻገር ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የሚሞተው ሰው ቁጥር እጅግ እየጨመረ የመጣ በመሆኑ በ2010 .ም ተላለፊ ያልሆኑ በሽታዎችን የመከላከል ሥራ ህብረተሰባዊ ንቅናቄ እንዲፈጠር የምንሠራ ይሆናል፡፡ ከዚሁ በተጓዳኝ ደግሞ ጥራቱ የተጠበቀ የሆስፒታል አገልግሎት መሠጠቱን የማረጋገጥ፣ እንዲሁም ከመድሃኒት አቅርቦት ጋር የተያያዘ አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል ትኩረት ይደረጋል፡፡ በተጨማሪም የግሉ ዘርፍ በተለይም በከተሞች አካባቢ በጤና መስክ አገልግሎት በመስጠት የሚኖራቸውን ሚና ይበልጥ ለማጠናከርና ለማስፋት እንዲሁም የሚሠጡት የጤና አገልግሎቶች ጥራታቸውን የጠበቁ እና ሁሉንም ወገኖች የሚያረኩ እንዲሆኑ ተገቢው ድጋፍ፣ የክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት እንዲዘረጋ ይደረጋል፡፡

ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር

2010 .ም የመንግሥት የማስፈፀም አቅም በመገንባትና የህዝቡን ተሳትፎና ባለቤትነት በማጐልበት እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ ልማታዊነትንና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ከፍተኛ ጥረት የሚደረግበት ዓመት ነው፡፡ ይህንን ሁኔታ ለመፍጠር በ2009 .ም የተሀድሶ እንቅስቃሴያችን ይበልጥ ጥልቀት እንዲኖረውና የሥርዓቱ አደጋ የሆነውን ያለውድድርና አለአግባብ የመጠቀም እንዲሁም የሙስና ዝንባሌና ተግባር ለመቆጣጠር በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ ታውጆ መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ የተደረገበት ዓመት ነበር፡፡ ህዝባችን በየህብረተሰብ ክፍሉ በስፋት እንዲወያይና የትግሉ ባለቤት እንዲሆን በተሠራው ሥራ መልካም ውጤቶች ማየት ጀምረናል፡፡ እነዚህ ጅምር ውጤቶች እንዲሠፉና ጥራት ያላቸው እንዲሆኑ ማድረግም የ2010 .ም ዋናው ሥራችን ይሆናል፡፡

መላው የፖለቲካ አመራሮች እና የመንግሥት ሠራተኞች በህዝብ የተሰጣቸውን ኃላፊነት እና በሙያቸው ለማገልገል በተሰለፉበት ሁሉ በቅንነት፣ በትጋትና በታማኝነት እንዲያገለግሉ ለማድረግ፣ ስለሚሠሩበት ሥራ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸውም ለማድረግ ሰፋፊ ሥልጠናዎች ተሰጥተዋል፡፡ ለሥራ መነሻ የሚያገለግል መግባባትም ተፈጥሯል፡፡ ይህንኑ መነሻ ተይዞ በተግባር ሂደት ይበልጥ አቅማቸው እየጐለበተ እንዲሄድ የሚሠራ ይሆናል፡፡

አላግባብ የመጠቀምና ሙስና ጐልቶ በሚታይባቸው የታክስ ሥርዓት፣ የመንግሥት ወጪ አስተዳደር፣ ግዥና የኮንስትራክሽን ኮንትራት አስተዳደር፣ የመሬት ልማትና አቅርቦት እንዲሁም የመሬት አስተዳደርና ግንባታ ፈቃድ አሰጣጥ፣ በውድድር ላይ የተመሠረተ የንግድ ሥርዓትና ፀረ- ኮንትሮባንድ ንግድ እንቅስቃሴ፣ ቀልጣፋና ውጤታማ የፍርድ ሥርዓትና የፖሊስ አገልግሎት እንዲሁም የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች ዙሪያ የተጀመሩት የሪፎርም ሥርዓቶችም በአንዳንድ ቦታዎች ውጤታማ መሆን የጀመሩ ሲሆን ባብዛኛው ቦታዎች ላይ ግን በዝግጅት ላይ ያሉ እና መጓተት የሚታይባቸው በመሆኑ በ2010 .ም ፍጥነታቸውንና ጥራታቸውን በመጨመር የተሟላ ትግበራ ውስጥ የሚገባበት ዓመት ይሆናል፡፡

በእነዚህ ዘርፎች በሙስና ተግባር ላይ የተሠማሩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ተባባሪዎቻቸውን በህግ እንዲጠየቁ ለማድረግ የተጀመረው ሥራም በ2010 .ም በጥናት ላይ ተመሥርቶ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

የሪፎርም ሥራዎቹ ልማታዊነትን ለማጐልበት፣ በአሠራር ሥርዓቶች ውስጥ ግልጽነት እንዲፈጠር፣ ኃላፊዎችም ሆኑ የመንግሥት ሠራተኞች ሥራቸውን በግልጽ አውቀው ባስገኙት ውጤትና ለሕዝቡ በፈጠሩት እርካታ ልክ የሚመዘኑበት ሥርዓት እንዲተገበር የተቀረፁ በመሆናቸውና በሙከራ ደረጃ ውጤታማ መሆናቸው የተረጋገጠ ስለሆነ እነዚህን አጠናክረን ለመተግበር የምንረባረብበት ዓመት ነው፡፡ ውጤታማነትና ስኬት ወይም ዴሊቨሪ ፅንሰ ሃሣብን ተግባራዊ ለማድረግ በተጀመረባቸው ዘርፎች በሙሉ ከወዲሁ መልካም ውጤት ማየት የተጀመረ በመሆኑ አጠናክረንም እቀጥላለን፡፡

ህዝቡ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎውን ለማሳደግ በተደራጀ ሁኔታ በለውጥና በልማት ቡድኖች፣ በፎረሞች፣ በብዙሃን ማህበራትና በሙያ ማህበራት ባጠቃላይ በሲቪል ማህበራት አማካይነት በቀጥታ ከሚያደርገው ተሳትፎ ባሻገር በተወካዮቹ አማካይነት በህዝብ ምክት ቤቶች የሚያደርገውን ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎውም እየጐለበተ መጥቷል፡፡ ይህ ተሳትፎው ወደታችኛው እርከን በሚወርድበት ጊዜ ይበልጥ መጠናከር ሲገባው ላልቶ የሚገኝባቸው ቦታዎች በርካታ በመሆናቸው በ2010 .ም የህዝብ ምክት ቤቶች ህዝቡን ወክለው አስፈፃሚውን አካል የሚቆጣጠሩበት ሁኔታ ተጠናክሮ መሠራት ያለበት ይሆናል፡፡ ከዚሁም ባሻገር የተከበረው ምክር ቤትም ፈጣንና ፍትሃዊ ልማታችንን የሚደግፉ፣ መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲያዊ የህዝብ ተሳትፎ ይበልጥ እንዲጐለብት የሚያደርጉና የፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችን በተጠናከረ መሠረት ላይ እንዲገነባ የሚያስችሉ አዋጆችንና ፖሊሲዎችን ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከነዚህ ውስጥም ባለፈው ዓመት የምርጫ ሥርዓታችንን በተመለከተ ሊደረግ የታሰበው ማሻሻያም ውይይት ሲካሄድበት የቆየ ሲሆን በዘንድሮ ዓመት ለተከበረው ምክር ቤት ቀርቦ በ2012 .ም ለሚደረገው አጠቃላይ ምርጫ እንዲደርስ የሚደረግ ይሆናል፡፡

2010 .ም በመላው ሀገሪቱ የሚካሄደው የአካባቢ እና ማሟያ ምርጫ ዴሞክራሲያዊነቱን ጠብቆ ነፃ፣ ፍትሃዊና በህዝቡ ዘንድ ተአማኒነትን ያተረፈ ሆኖ እንዲጠናቀቅ መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ የሚያደርግ ይሆናል፡፡

ከዴሞክራሲ ተቋማት መካከል በፓርላሜንታዊ ሥርዓት ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱት የፖለቲካ ፖርቲዎች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ በሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ እንዲጐለብት የፖለቲካ ምህዳሩም ይበልጥ እንዲሰፋ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ እና ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጀመሩት ውይይትና ድርድር በተስማሙበት መርህ እና መርሃ ግብር መሠረት እየተጓዘ ይገኛል፡፡ መንግሥት ሁሉም ያገባኛል የሚሉ በህጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሳተፉ ሁሌም በሩን ክፍት አድርጐ ለሂደቱ ስኬታማነት የሚሠራ ይሆናል፡፡

የሚዲያ ተቋማትም በሀገራችን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የበኩላቸውን በጐ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ተከታታይ ውይይቶችና ሴሚናሮች የተካሄዱ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የተጀመረውን የሚዲያ ሪፎርም ሥራ ሁሉም ተሳትፈውበት የተሳካ እንዲሆን በ2010 .ም ተጠናክሮ የሚሰራ ይሆናል፡፡

2009 .ም መጀመሪያ ጀምሮ የተለያዩ ጥገኛ አስተሳሰቦች የወለዷቸው የፀረ-ሰላም ሃይሎችም የተጠቀሙበት አለመረጋጋት በሀገራችን ተፈጥሮ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ይታወሳል፡፡ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት ከህዝባችን ጋር ባደረግናቸው መጠነ ሰፊ ውይይቶችና በተደረሰው መግባባት መሠረት የሀገራችን ሰላምና ፀጥታ ወደ ተረጋጋ ሁኔታ በመመለሱም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ ተደርጓል፡፡ ይህንን ሰላማችንን አሁንም አጠናክረን ማስቀጠል ይገባናል፡፡ ለግጭቶች ምክንያት የሆኑ ያልተፈቱ የድንበር ማካለል ጉዳዮችን ከሞላ ጐደል በሁሉም አካባቢ ለመፍታት የተቻለም ቢሆን አሁንም በኦሮሚያና በኢትዮ-ሱማሌ አካባቢ ቅሪት ያልተስተካከሉ አፍራሽ አመለካከቶች የወለዷቸው ግጭቶች ተከስተው የሰው ህይወት በአሰቃቂ ሁኔታ ያለፈበትና ንብረቶች የወደሙበት ሁኔታ መኖሩ ይታወቃል፡፡ ይህ ሁኔታ በፍፁም መወገዝ ያለበትና መንግሥት ፀጥታውን ከማስከበር ባሻገር አጥፊዎችን ወደ ህግ ለማቅረብ ሳይታክት እየሠራ ይገኛል፡፡ በ2010 .ም እንደዚህ አይነት በህዝቦች መካከል ለዘመናት የቆየውን አንድነት የሚያፈርስ አካሄድ በጭራሽ ሊፈቀድ የማይገባው በመሆኑ የሁለቱም ክልል የሀገር ሽማግሌዎች፣ ባህላዊ መሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶችና ሴቶች እንዲሁም መላው የሁለቱ ክልል ህዝቦች ሁኔታው ወደ ነበረበት እንዲመለስና የተፈናቀሉ ወገኖቻችንም መልሶ እንዲቋቋሙ ለማድረግ ከመንግሥት ጐን እንዲቆሙ በዚህ አጋጣሚ ጥሪዬን ለማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡ በሂደቱ የተጐዱ ዜጐች ቤተሰቦችም መጽናናት እንዲሆንላቸው እመኛለሁ፡፡

ወጣቶችና ሴቶች

በሀገራችን የህዳሴ ጉዞ ውስጥ ልዩ ትኩረት የሚሰጣቸውና የማይተካ ሚና የሚጫወቱ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ወጣቶችና ሴቶች ግንባር ቀደሞች ናቸው፡፡

ባለፈው ዓመት የወጣቶችን እኩል ተሳታፊነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በይበልጥ የማረጋገጥ ጉዳይ ከሥራዎች ሁሉ አውራ ሥራ ተደርጐ እንቅስቃሴ እንዲደረግበት ተወስኖ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት በሀገራችን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ጉዞ የማይተካ ሚናቸውን እንዲጫወቱና በሂደቱም ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል የወጣቶች የዕድገትና የለውጥ ስትራቴጂና ማስፈፀሚያ ፓኬጅ ተከልሶ እንዲዘጋጅ ተደርጓል፡፡ በዝግጅቱ ሂደትም የወጣቶች የነቃ ተሳትፎ እንዲኖር ተደርጓል፡፡ ይህንኑ ፓኬጅ ወደ ሥራ ለማስገባት የሚረዱ የተለያዩ ማኑዋሎችና መመሪያዎች ተዘጋጅተው የሥራ መመሪያ እንዲሆኑም ተደርጓል፡፡ ሥልጠናም ተሰጥቶባቸዋል፡፡

ይህንን የለውጥና ዕድገት ፓኬጅ ወደ ሥራ ለማስገባት የፌዴራል መንግሥት ከመደበው 10 ቢሊዮን ብር የወጣቶች ፈንድ በተጨማሪም ክልሎችም በተመሳሳይ መልኩ በድምሩ ወደ 10 ቢሊዮን ብር መድበዋል፡፡ በድምሩ በፈንዱ ከሚንቀሳቀሰው 20 ቢሊዮን ብር ውስጥ ወደ ሥራ የማስገባቱ ሂደት በዝግጅት ምዕራፍ መጓተት ምክንያት የዘገየ በመሆኑ ወደ ግማሽ ያህሉ በዓመቱ መጨረሻ ወደ ሥራ በመግባቱ ለሁለት ሚሊዮን አካባቢ ወጣቶች ሥራ ለመፍጠር ተችሏል፡፡ ካሉን የወጣት ሥራ-አጦች ቁጥር አኳያ ብዙ መሥራት ያለብን በመሆኑ በ2010 .ም መልካም ውጤቶቹንና በሂደቱ ያጋጠሙንን ተግዳሮቶችና እንቅፋቶች ገምግመን ከምናገኘው ልምድ በመነሳት የተሻለ አፈፃፀም እንዲኖረን የሚጠበቅበት ዓመት ይሆናል፡፡ ከሥራ ዕድል ፈጠራው ባሻገር ከወጣቶች የሰብዕና ግንባታ ጋር የተያያዙ ሥራዎች በራሳቸው በወጣቶቹ ተሳትፎና ባለቤትነት ውጤታማ እንዲሆኑ የምንሠራበትም ዓመት ይሆናል፡፡

ሴቶች በሀገራችን በሚካሄዱ በተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች በባለቤትነት በመሳተፍ በፀረ-ድህነት ትግላችን የማይተካ ሚናቸውን መጫወት ጀምረዋል፡፡ የገጠር ሴቶች ከመሬት ባለቤትነት የጋራ መብት መጐናፀፍ ባሻገር ወደ 2.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ሴቶች በግብርናው ሥራ ውስጥ በጓሮ አትክልት፣ በዶሮ እርባታ፣ በንብ ማነብ፣ በማድለብና በማሞከት እንዲሁም በመስኖ እርሻ በመሳተፍ ተጠቃሚ መሆን ጀምረዋል፡፡ ይህ ጅምር ሥራ ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ባሻገር በቤተሰብ የአመጋገብ ሥርዓት በተለይም በህፃናት የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ላይ ለውጦች እንዲታዩ የራሱን በጐ ሚና ተጫውቷል፡፡

የጤና ኤክስቴንሽን ሥርዓታችን የጀርባ አጥንት የሆኑት ሴቶች በመሆናቸውም ሀገራችን በእናቶችና ህፃናት ሞት መቀነስ በዓለም የተመሠከረለት ውጤት እንድታገኝ አስችሏታል፡፡ በጡትና ማህፀን ካንሠርን ጨምሮ በቤተሰብ ምጣኔ፣ በአመጋገብ ሥርዓትና በተላለፊ በሽታዎች ዙሪያ የተሰጡ ሥልጠናዎችም ውጤታማ መሆን ጀምረዋል፡፡

በሴቶች የትምህርት ተሳትፎ አኳያም በአንደኛ ደረጃ የተመጣጠነ ደረጃ የተደረሰም ቢሆን በ2ኛ ደረጃና ዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ መሻሻሎች ቢኖሩም ወደተፈለገው ደረጃ ለማድረስ በብርቱ መሥራት የሚገባን ይሆናል፡፡ ሴቶች በተግባራዊ የተቀናጀ የጐልማሶች ትምህርት አኳያ ለራሳቸው ካገኙት ዕውቀትና ክህሎት ባሻገር በልጆቻቸው ትምህርት ተሳትፎና ጥራት ላይ የበኩላቸውን ሚና መጫወት ጀምረዋል፡፡ የጐልማሶች ትምህርት ተሳትፎ ገና ከግማሽ ያልዘለለ በመሆኑና የተሟላ ተፅእኖ መፍጠር ባለመቻሉ ይህንን ለማሳደግ መሥራት የሚገባን ይሆናል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ

በመጨረሻም ሀገራችን የመረጠችውና ለዓለም ህብረተሰብም ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ የዓለም ዜግነታችንን የገለፅንበት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂያችንን በየክፍላተ-ኢኮኖሚው ዕቅድ ውስጥ ገብቶ እንዲተገበር እያደረገች ትገኛለች፡፡ በስትራቴጂያችን እንደተቀመጠውም ከቤት እንስሳት፣ ከአፈር መከላትና ከደን መጨፍጨፍ፣ ከሃይል ምንጭ ቴክኖሎጂ፣ ከትራንስፖርት፣ ከኢንዱስትሪና ከከተሞች የሚለቀቀውን የሙቀት አማቂ ጋዝ ለመቀነስ ከፍተኛ ጥረት ስናደርግ ቆይተናል፡፡ ውጤቶችንም አግኝተንባቸዋል፡፡

የአገራችንን ስትራቴጂ ከማንም ቀድመን በይፋ ለዓለም ህብረተሰብ ያስተዋወቅንበትም ዋናው ምክንያት ምንም እንኳን ሀገራችን ለዓለም የአየር ንብረት ለውጥ የምታበረክተው አስተዋጽኦ እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም ተጎጂነታችንን ለመቀነስ ኃላፊነት የሚሠማቸው የበለፀጉና በፍጥነት እያደጉ ያሉ ሀገሮች የስትራቴጂያችንን ማስፈፀሚያ ሃብት እንዲለግሱን ለማድረግ ነበር፡፡ በዚህ መሠረትም በ2009 .ም ወደ 110 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቶ ወደ ሥራ እንዲገባ ተደርጓል፡፡ ይህም ሂደት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ ሥራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ ሀገራችን በዓለም አቀፍ መድረክ ያላት ተሰሚነት ጐልብቶ በመቀጠሉ በአሁኑ ወቅት ሁለት ታላላቅ የአለም አቀፍ የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ መድረኮችን በሊቀመንበርነት እየመራች ትገኛለች፡፡ በ2010 .ም የሀገራችንና የሌሎች ታዳጊ ሀገሮችን መብትና ጥቅም የሚያረጋግጡ ሥራዎችን መተግበርን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡

 

በጋዜጣው ሪፖርተር

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።