ከሕገመንግስቱ አንቀፅ 32 በስተጀርባ

04 Dec 2017

«ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም በህጋዊ መንገድ አገር ውስጥ የሚገኝ የውጪ ዜጋ በመረጠው የአገሪቷ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመስረት እንዲሁም በፈለገው ጊዜ ከአገር የመውጣት ነፃነት አለው» የሚለው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገመንግሥት ነው፡፡ ምንም እንኳ በአንቀፅ 32 ንዑስ አንቀፅ 1 ላይ ይህ ሀሳብ ሰፍሮ ቢገኝም፤ አሁን አሁን በዜናዎቻችን ላይ እንደሚገለፀው፤ በአንድ ክልል ያሉ የሌላ ክልል ተወላጆች ከኑሯቸው የሚፈናቀሉበት ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡

የትኛው ክልል የማን ክልል ሰዎችን አስወጣ? ያስወጣው የክልሉ ህብረተሰብ ነው ወይስ የክልሉ መንግሥት? የክልል ፖሊስ ነው ወይስ የፌዴራል ፖሊስ? የሚለውን ማጣራት ስለሚያስፈልግ ይህን እንተውና በኢትዮጵያ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ መንስኤውና መፍትሄውን አስመልክቶ ምሁራን እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የሰጡንን አስተያየት ይዘን እንነሳ፡፡

ወቅታዊው ሁኔታ

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ ጥላሁን እንዳሻው፤ በእርግጥ ህገመንግስቱ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የአገሪቷ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመስረት መብት እንዳለው አረጋግጦለታል፡፡ ይሁን እንጂ በተግባር ይህ በኢህአዴግ አገዛዝ እየተከበረ አይደለም፡፡ በህገመንግስቱ ብቻ ሳይሆን በአገሪቷ ብሔራዊ መዝሙርም የዜግነት ክብር እየተባለ ሃሳቡ ቢስተጋባም በተግባር ሥራ ላይ እየዋለ አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡

‹‹በህገመንግስቱ አንቀፅ 51 ንዑስ አንቀፅ 1 ላይ ‹የፌዴራል መንግሥት ህገመንግስቱን ይጠብ ቃል፤ ያስከብራል› ይላል፡፡ ነገር ግን መንግሥት ህገመንግስቱን እያስጠበቀ አይደለም፡፡ህገመንግስቱ መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮች ያሉበት መሆኑ ቢታወቅም፤ ከነክፍተቱም ቢሆን የፌዴራል መንግሥት ህገመንግስቱን የማስከበር ግዴታ አለበት፡፡ ዋነኛ ሥራው ፀጥታና ሰላም ማስከበር፤ ማንኛውም ዜጋ በሰላም ሰርቶ እንዲኖር ማስቻል ነው›› የሚሉት አቶ ጥላሁን፤ መንግሥት ህገመንግስቱ ላይ የተረጋገጡ የዜጎች መብቶችን የማስከበር ግዴታ እንዳለበት ሊረሳ አይገባም፡፡ አሁን ግን ዋነኛ ሥራውን ዘንግቶታል፤ ህገመንግስቱን የማስከበርና የማስፈፀም ትልቅ ሃላፊነትን የማይወጣ መንግሥት፤ መንግሥት ነኝ የማለት ብቃት የለውም ይላሉ፡፡ ልማትና እድገት የመንግሥት ተጨማሪ ሥራዎች በመሆናቸው በእነዚህ መስፈርቶች ብቻ መንግስትነቱ የተረጋገጠ ነው ሊባል እንደማይችል አብራርተዋል፡፡

‹‹በግልፅ የሌላ አገር ዜጎች ከሀገር ይውጡ በሚል እንደሚባረሩት ሁሉ፤ የአንዱ ክልል ሰው ሌላ ክልል ሄደው ሲኖሩ ግፍ እየተፈፀመባቸው ነው፡፡ አካላዊና ሞራላዊ ጉዳት የሚደርስባቸው ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ ህገመንግስቱ ደግሞ ማንኛውም ዜጋ በፈለገበት የአገሪቷ አካባቢ መኖር እንደሚችል ቢያስቀምጥም ህገመንግስቱ እየተጣሰ ነው፡፡ ለፌዴራልና ለክልል መንግስታት የተሰጠው ስልጣን ተለያይቷል፡፡ በህገመንግስቱ አንቀፅ 51 እንደተቀመጠው የክልል መንግሥት የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ ፖሊስ ማደራጀት ይችላል፡፡አሁን ግን ክልሎች ልዩ ሃይል ሲያደራጁ የፌዴራል መንግሥት በዝምታ ከማየት አልፎ ድጋፍ እየሰጠ ነው። የትኛውን የህገመንግስት አንቀፅ መሰረት አድርገው ክልሎች ልዩ ሰራዊት እንዲያደራጁ ባይፈቀድም፡፡ ይህ ግን በተግባር እየተፈፀመ ነው» በማለት ይናገራሉ፡፡

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት /መኢአድ/ የቀድሞ ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ አበባየሁ መሃሪ በበኩላቸው፤ በተፈለገው የአገሪቷ አካባቢዎች ተዘዋውሮ የመስራት እና የመኖር መብት እየተጣሰ መሆኑ እሙን ነው ይላሉ፡፡ ከዚህ የመብት ጥሰት በተጨማሪ የተለየ አስተሳሰብ ያለው እና የገዢው ፓርቲ ተቃዋሚ ኢትዮጵያዊ በአገሩ እንዳይኖር እየተደረገ ይገኛል፡፡ ጉልበትና እውቀት ያለው ዜጋ ተወዳድሮ በፈለገበት የአገሪቷ አካባቢ ስርቶ እንዳይበላና ኑሮውን እንዳይመሰርት ያደረጉት የገዢው ፓርቲ የኢህአዴግ ካድሬዎች መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ በክልሎች እንኳን ሰው መኪና ሲያልፍ በታርጋ ቁጥሩ ተለይቶ የሚታይ መሆኑን እና በሌሎች ክልሎች የመኖርም ሆነ የመንቀሳቀስ መብት እየተጣሰ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ ዲን ዶክተር ኪዳነ ግደይ በበኩላቸው፤በጉዳዩ ላይ ትክክለኛ መረጃውን ማግኘት አልተቻለም፡፡ በማህበራዊ ድረገፆችም ሆነ መደበኛ ባልሆነ መልኩ በስሚ ስሚ የሚወሩ ነገሮች እና ካለፉ በኋላ የሚቀርቡ ዜናዎች አሉ፡፡ ማንኛውም ዜጋ በየትኛውም የአገሪቷ አካባቢ ሙያውን ሽጦ ማግኘትና የመስራት መብት አለው፡፡ ይሁን አንጂ የመስራትም ሆነ የመኖር መብት እየተጣሰ መሆኑ ይገለፃል፡፡ ሆኖም የተጣራ መረጃ መስጠት ላይ ክፍተት መኖሩን ይናገራሉ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ኮሌጅ የመንግሥትና የሰብዓዊ መብት መምህሩ ዶክተር ዘመላክ አይተነው፤ «በእርግጥ አሁን ላይ በዚህ ክልል የዚህ አገር ተወላጅ መኖር የለበትም በሚል፤ ይሄ ብሔር በተጨባጭ ተፈናቅሏል ብሎ ማረጋገጥ ቢያስቸግርም ይህንን የሚያመለክቱ ዜናዎች አሉ፡፡ ከቤንሻንጉል አማራ ይውጣ ተባለ፤ ከሶማሌ ኦሮሞ ይውጣ ተባለ፤ ከኦሮሚያም ሶማሌ ይውጣ ተባለ የሚሉ ወሬዎች እየተሰሙ ነው፡፡ ይህ እውነት ከሆነ ግልፅ ህገመንግሥትን የመጣስ ተግባር ነው» ይላሉ፡፡

የቀድሞ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት እና የአሁኑ የእንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ፤ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም ክልል በነፃነት መንቀሳቀስ፤ ሰርቶ የመኖር፤ ንብረት የማፍራት እና ለንብረቱ ዋስትና የማግኘት መብት አለው፡፡ ይህ መብት መከበር እንዳለበት አያጠያይቅም ይላሉ፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ ፅህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት መምሪያ ሃላፊው አቶ ለጥይበሉ ሞቱማ፤ በህገመንግስቱ በአንቀፅ 32 ንዑስ አንቀፅ 1 ላይ እንደተቀመጠው ህገመንግስቱ ለሁሉም ዋስትና ሰጥቷል፡፡ይሁን እንጂ በማንኛውም አካባቢ የመኖር መብት የሚጣስበት ሁኔታ እየተስተዋለ ነው የሚለውን ሃሳብ ይጋራሉ፡፡ ድርጅቱ በተለያዩ ሁኔታዎች እየታየ ያለው የመፈናቀልን ጉዳይ እየለየ እና የችግሩ ፈጣሪ ማን ነው? የሚለውን እያጣራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

የችግሩ ምንጭ

ዶክተር ኪዳነ የችግሩ መነሻ የክልልም ሆነ የፌዴራል መንግስቱ ክፍተት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ የፌዴራል ስርዓቱ ምሰሶ የሆኑትን የብሔር ብሔረሰቦችን መብት መጠበቅ ላይ ትልቅ ክፍተት አለ፡፡ ህዝቡ ችግር የለበትም፡፡ መንግሥት ችግሮችን ተከታትሎ በመለየት መፍታት ቢኖርበትም አሁን ባለው እውነታ ከላይ እስከታች ይህ እየሆነ አይደለም፡፡ ‹‹እታች ያሉ አካላት ግጭት ማስነሳት በሚፈልጉ ቡድኖች የተጠመዱ ይመስለኛል፡፡ እታች ያለው አመራር ላይ ክፍተት በመፈጠሩ ወጣቶችና ተንቀሳቃሽ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመጠቀም ብሔርን ከብሔር በማጋጨት የማቀጣጠል ሥራ እየተሰራ ይገኛል» የሚል ዕምነት አላቸው፡፡

ዶክተር ዘመላክ በበኩላቸው፤ «በኢትዮጵያ የሰዎች መብት ተከበረ፤ ዴሞክራሲ ሰፈነ የሚባለው የብሔር መብት ስለተከበረ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን መብት ይህ ማለት ብቻ አይደለም፡፡ የተለያየ አስተሳሰብና ርዕዮተዓለም ያለው፤ ካለው የፖለቲካ ሥርዓት አስተሳሰብ ውጪ የሚያስበው ሰውም መብቱ ሊከበር ይገባል፡፡ አንድ ርዕዮተዓለምና አንድ አስተሳሰብ ብቻ ከየአቅጣጫው መገፋቱ ጥሩ አይደለም፡፡ትግሬም ሆነ ኦሮሞ እንዲሁም አማራም ሆነ ሌላ የብሔር መብት ተከበረለት ተብሎ አስተሳሰቡ የማይከበርለት ከሆነ እና ህገመንግስቱ ባስቀመጠው መሰረት የሁሉም ሃሳቦች ካልተስተናገዱ ሰዎች ሃሳብን ከመወርወር ይልቅ ወጥተው ድንጋይ መወርወር ይጀምራሉ» በማለት የችግሩን ምንጭ ይናገራሉ፡፡

ሌላው ዶክተር ዘመላክ የገለፁት፤ የብሔር ግጭት የተለመደ መሆኑን ነው፡፡ አንዱ አንዱን አቅፎ እና ደግፎ ይኖራል፡፡ አልፎ አልፎ ደግሞ አንዱ ሌላውን ሲገፋ ማየት ተለምዷል፡፡ ቁምነገሩ አሁን ላይ በጣም ፖለቲካዊ እየሆነ መምጣቱ ነው፡፡ አሁን ህብረተሰቡ ውስጥ ይህ መኖሩ አይካድም፡፡ በኢትዮጵያ የተለያዩ ብሔሮች፣ ሃይማኖቶች እና አስተሳሰቦች አሉ፡፡ አንድ ብሔር፣ ሃይማኖት ወይም አስተሳሰብ ብቻ የበላይ ሆነ የሚል ሃሳብ ሊኖር ይችላል፡፡ ይህ አስተሳሰብ መሰረት የለውም ማለት ባይቻልም፤ ዋናው የተለያየ ብሔር፣ ሃይማኖትና አስተሳሰብ እኩል ማስተናገድ ያስፈልጋል የሚለው ነው ይላሉ፡፡

አቶ ጥላሁን ከላይ በተገለፀው መሰረት ችግሩ ከህዝቡ አስተሳሰብ ጋር የተገናኘ ነው የሚለውን ሃሳብ ይቃወማሉ፡፡ «የኢትዮጵያ ህዝብ የእርስ በእርስ የጥላቻ ስሜት የለውም፡፡ ችግሩ የአገዛዙ ነው፡፡ ከከፍተኛ አመራሮች ጀምሮ እስከታች ድረስ ያለው አገዛዝ ጤነኛ አይደለም፡፡ መንስኤው ይኸው ነው፡፡ ከሶማሌ ክልል ኦሮሞዎችን ያስወጣው የሶማሌ ህዝብ ሳይሆን የተደራጀው አካል ነው፡፡ ስለዚህ ችግሩ ያለው ህዝቡ ውስጥ ሳይሆን አገዛዙ ላይ ነው፡፡ የህገመንግስት ጥሰቱ የሚፈፀመው በፌዴራል መንግሥት ጭምር ነው፡፡ የእዚህ ሁሉ ጉዳይ መንስኤው የትኛውም ብሔር ብሔረሰብና ህዝብ ሳይሆን አሁን ያለው አገዛዝ ነው» በማለት ነው የችግሩን ምንጭ የተናገሩት፡፡

አቶ አበባው ደግሞ፤ ግለሰቦችን የሚጎዱትና ከብሔር ጋር ተያይዞ በደሉን የሚፈፅሙት ካድሬዎች እንጂ የአንዱ ክልል ህዝብ የሌላውን ክልል ህዝብ እየጠላ አለመሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ህዝቡ እርስ በእርሱ ተዋህዶ አንድ ሆኖ መኖር ይፈልጋል፡፡ የማንኛውም ክልል ሰው የሌላውን ክልል ተወላጅ አይጠላም፤ አያባርርም፡፡ ይህን የሚያደርጉት ታች ያሉ የገዢው ፓርቲ አባላት (ካድሬዎች) ናቸው፡፡ ህዝቡ የተጋባ አብሮ የኖረና አብሮ የበላ የተዋለደ ነው፡፡ ተዘዋውሮ የመስራት መብት ጥሰት አሁን እየታየ ያለ ሳይሆን ለ26 ዓመታት የዘለቀ፤ ከሥርዓቱ ጋር የተቆራኘ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

አቶ ለጥይበሉ ሞቱማም በበኩላቸው አሁን ለሚስተዋሉት ችግሮች መንስኤውን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሻቸው ‹‹እየተጣራ ነው፡፡›› የሚል ሲሆን መረጃ ሲገኝ አጥፊዎቹ ለህግ የሚቀርቡ ይሆናል ብለዋል፡፡ ነገር ግን አልፎ አልፎ የሚከሰቱ የአሰራር ችግሮች በዜጎች ላይ ቅሬታ እየፈጠሩ እና እንደዚህ አይነት ጉዳት እያስከተሉ ነው የሚል ግምት እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡ ይህንን መንግሥትም በአንክሮ እየተከታተለ እና እያጣራ ይገኛል፡፡ ህገመንግስቱን ማን ጣሰው የሚለው እየተለየ ነው? በማለት «ክልሎች ከህገመንግስቱ ውጪ ሃይል እንዲያዘጋጁ ተፈቅዷል፡፡ መንግሥት ህገመንግስቱን እየጣሰ ነው» የሚለውን ሃሳብ የሚቃወሙት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ክልሎች ራሳችን መቆጣጠር አልቻልንም ካሉ የፌዴራል መንግሥቱ ህገመንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት ጣልቃ የሚገባበት ሁኔታ መኖሩንም ጠቁመዋል ፡፡

የመፍትሄ ሃሳቦች

ዶክተር ኪዳነ ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ላይ በስፋት መሰራት አለበት፡፡ ወጣቶች መብትና ግዴታቸውን ማወቅና ህገመንግስቱን በጥልቀት መረዳት ይኖርባቸዋል፡፡ በሁሉም ደረጃ ሃላፊነትን መውሰድ መለመድ አለበት፡፡ አጥፍቶ መደበቅ፤ ህዝብን እየጎዳ እና ቁርሾ ውስጥ እየከተተ፤ ይባስ ብሎ የፌዴራል ስርዓቱ ላይ አደጋ እያስከተለ በመሆኑ ጥብቅ ክትትል መደረግ አለበት፡፡ በተለይ የፌዴራል መንግሥቱ ነገሮች ሳይባባሱና ሳይበላሹ ቀድሞ መከታተልና መፍታት እንዲሁም በፍጥነት ምላሽ መስጠት ላይ መዘናጋት የለበትም፡፡

«መንግሥት የእዚህ ሁሉ የበላይ አካል ነው፡፡ ህዝብ ዋስትና ሊሰማው ይገባል፡፡ መንግሥት ይህን ማጠናከርና ጥበቃ ማድረግ አለበት፡፡ በክልልና በፌዴራል መንግሥት መካከል ያለው ልዩነት ግልፅ መሆን አለበት፡፡ የስልጣን ክፍፍሉ ላይ ወጣ ገባነት አለ፡፡ ክልሎች ራሳቸውን ማስተዳደር፤ በጀታቸውን የማስተዳደር ዕድል ሲሰጣቸው፤ በክልላቸው ውስጥ ያሉ ሌሎች ብሔሮችን ማስተዳደር ላይ ክፍተት ሲኖር፤ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ መግባት በሚባል ደረጃ ባይሆንም ክትትል አድርጎ የዕርምት እርምጃ እንዲወሰድ መደረግ ይጠበቅበታል» ይላሉ፡፡

ዶክተር ኪዳነ በበኩላቸው፤የክልል መንግስታትና የፌዴራል መንግሥት ፖሊስም ሆነ ወታደርን ሲያዘጋጅ እንዴት ነው? የክልል መንግስታቱ እስከምን የዘለቀ ስልጣን አላቸው? የሚለው በደንብ ለይቶ ማስቀመጥና ህዝቡና አመራሩ እንዲያውቀው ማድረግ ይገባል፡፡ እንደዚህ አይነት ችግር ሲከሰቱ የክልል መንግስታት ሃይል ሲጠቀሙ የማባባስ ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ በተለይ የክልል ፖሊሶች በየዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ሲገቡ ትንኮሳውና የዘር ጥላቻውን የሚባባስበት ሁኔታ ስለሚፈጠር፤ ሃይል ሲያስፈልግ በትክክል ማየትና የፌዴራል መንግሥት ብቻ ሃይል መጠቀም አለበት፡፡ ከስር ከስር ችግሮችን መፍታት ያስፈልጋል፡፡ የክልል ፖሊሶች የክልል ተቋማት ላይ በማተኮር፤ የፌዴራል ተቋማቱን ደግሞ የፌዴራሉ አካል ጥበቃ ቢያደርግላቸው ይመረጣል ይላሉ፡፡

ሌላው ዋነኛው መፍትሔ ህገመንግስቱን ማስጠበቅና ህብረተሰቡ እኩል ግንዛቤ እንዲኖረው ማስቻል ላይ መሰራት ነው፡፡ አሁን ላይ የሚታየው ምልክት ከባድ ነው፡፡ የኑሮ ውድነት፤ ሥራ አጥነት እና ሌሎችም ይህንን የሚያባብሱ ነገሮች በመኖራቸው ችግሮቹን ከስር መሰረት መንቀል ያስፈልጋል፡፡ የተንቀለቀለውን ዕሳት ማጥፋት ብቻ ሳይሆን፤ ዕሳቱን የሚያስነሱና የሚያቀጣጥሉ ክብሪቶችን ለመቀነስና ከተቻለም ለማጥፋት ቀድሞ መስራት ይገባል ይላሉ፡፡

ዶክተር ዘመላክ መንስኤው የፌዴራል ስርዓቱ ነው ከተባለ መፍትሔው ከባድ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ «የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የአፋር ወይም የሌላ ክልልን እናፍርሰው ቢባል አይቻልም፡፡ ሰው የክልሉን ካርታ፣ ባንዲራውን ያውቃል፡፡ ስለዚህ እሺ አይልም፡፡ በተቃራኒው እነዚህ ሰዎች ሊከፋፍሉንና ሊያዳክሙን ነው የሚል ጥያቄ ይነሳል፡፡ ስለዚህ ወደ ኋላ እንመለስ ማለት ነገሮችን ከማስተካከል ይልቅ ሌላ ችግር ይፈጥራል ብዬ እሰጋለሁ» ከዚህ አንፃር መፍትሔው የአስተሳሰብ ብዝሃነትን ማስተናገድ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡

መፍትሔው የረዥምና የአጭር ጊዜ ዕቅድ በመያዝ ነገሮችን የሚያባብሱ ነገሮችን ማቃለል ነው፡፡ ሰው ስሜታዊ እየሆነ በመምጣቱ እና ትንሿ ጉዳይ እየገነነች የምትመጣ በመሆኑ ችግሩን ለመፍታት የሚወሰዱ መፍትሔዎች በጣም ታስቦባቸውና የሰውን ስሜት በማይነኩና ቅሬታ በማይፈጥሩ መልኩ ቢደረጉ ጥሩ ነው ይላሉ። ህገመንግስቱን እና ህጉን በመጠቀም ችግሩን መፍታት የሁሉም ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡ ከሁሉም በላይ የረዥም ጊዜ መፍትሔ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

በህገመንግስቱ መግቢያ ላይ የተቀመጠው አንድ የኢኮኖሚክ ማህበረሰብ እንገነባለን ብሎ ተስፋ ያደርጋል፡፡ ይህ የሚሆነው ሁሉም በያለበት ሳጥን ታጥሮ ሳይሆን አንዱ ከሌላው ጋር ግንኙነት መፍጠር ሲችል ነው፡፡ ይህ መሆን የሚችለው ደግሞ አንዱ ከራሱ ወደ ሌላው ክልል ተዘዋውሮ በስራም ሆነ በማህበራዊ ግንኙነት መቆራኘት ሲችል መሆኑን ይናገራሉ፡፡

የፌዴራል ስርዓቱ እንዳለ ሆነ በክልሎች ውስጥ ያለ የተለያየ አስተሳሰብ የሚስተናገድበት ሁኔታ መመቻቸት ይኖርበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታዋ ሌላ መሆን ነበረበት ብሎ የሚያምን ግለሰብና ቡድን ይኖራል፡፡ የእነርሱንም መብት ማክበር ያስፈልጋል፡፡ የተነጠሉ ቡድኖችን ለማካተት እና መብታቸው የተጣሱ ሰዎችን መብት ለማስከበር የአሁኑ ህገመንግስት አያንስም፡፡ ስለዚህ ህጎችን በትክክል በሁሉም ሰዎች ላይ መተግበር አለበት፡፡ ለእዚህ ደግሞ ህገመንግስቱ ዝግ አይደለም፡፡ ህገመንግስቱ ላይ ያሉ ከነፃነት፣ ከዴሞክራሲ፣ ከምርጫ፣ ሃሳብን በነፃነት ከመግለፅ፤ ከሰብዓዊ መብት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በትክክል በህገመንግስቱ መሰረት ቢከበሩ ችግሮች እንደማይደራረቡ አስረድተዋል፡፡

ከዚህ አንፃር ዋናው መፍትሔ የተለያዩ ሃሳቦች የሚስተናገዱበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው፡፡ ከምርጫ ጋር የተያያዙ ቅስቀሳዎችም ሆነ ፖለቲካዊ ተሳትፎዎች በነፃነት መካሄድ ካልቻሉ ነገሮቹ ለጊዜው በሚወሰዱ ርምጃዎች ቢበርዱም ቆይተው ተመልሰው መከሰታቸው ስለማይቀር፤አ መጣጡም ከዚህ በከፋ መልኩ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ይገልፃሉ፡፡

ዶክተር ዘመላክ በበኩላቸው፤ ሌላው ቀርቶ የፌዴራል ሥርዓቱ መፍረስ አለበት ሊል የሚችል ይኖራል፡፡ ሥርዓቱ አይደለም አፈፃፀም ላይ ያለ ችግር ነው የሚልም ይኖራል፡፡ በማለት እርሳቸው ግን የፌዴራል ስርዓቱ በዚህ ምክንያት መሻሻል አለበት ማለት ቢያዳግታቸውም ዋናው ቁምነገር ህገመንግስቱ ከተተገበረ ችግሩ ይፈታል ብለው እንደሚያምኑ ይናገራሉ፡፡

ህገመንግስቱ ራሱ ላይ በተቀመጠው የማሻሻያ ህግ መሰረት መሻሻል ይቻላል፡፡ ህገመንግስቱ በትክክል የሚተገበርበት ሁኔታ ቢፈጠር የተሻለ ነገር ይመጣል፡፡ ህገመንግስቱን እየጣሰ ያለው ማን ነው? ከተባለ ሁሉም እየጣሰው ነው፡፡ ችግሩ መንግሥት ህገመንግስቱን ሙሉ ለሙሉ እንዲተገበር የሠራው ሥራ ውስን ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉም መነሻቸውም ሆነ መድረሻቸው ህገመንግስቱ መሆን አለበት ብለው እንደሚያምኑ ይገልፃሉ፡፡

አቶ ጥላሁን ደግሞ መፍትሔው ፓርቲው ራሱን መለወጥ አለበት፡፡ አለበለዚያ ህገመንግስታዊ መብቶችን የማስከበር የመምረጥ የመመረጥ፤ ሃብት የማፍራት፤ ዜጋ እንደዜግነቱ መብቱን ማስከበር አለመቻሉን አምኖ እና ሃላፊነት ወስዶ ኢህአዴግ ከስልጣን መልቀቅ አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ የሁሉንም ህዝብ ተከባብሮ የመኖር ፍላጎትን የሚያራምድ መንግሥት እንዲያቋቁም መፍቀድ ይገባዋል ይላሉ፡፡

ፕሮፌሰር ፍቃዱ ግን እንደአቶ ጥላሁን ፓርቲው ይልቀቅ ከማለት ይልቅ መፍትሔው፤ የሌላውን መብት የጣሰ አካል ተጠያቂ ማድረግ ነው ይላሉ፡፡ በቅድሚያ ማስተማር፤ ችግር የፈጠሩትን መጠየቅ ይገባል፡፡ አገሪቷ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገበች በመሆኑ፤ አልፎ አልፎ በሚከሰቱ ችግሮች ከመደናገጥ ይልቅ ተከታትሎ ችግሩን መፍታት ያስፈልጋል፤ ይህ ከሆነ ችግሩ ቀላል ይሆናል የሚል ዕምነት አላቸው፡፡

አቶ ለጥይበሉ በበኩላቸው፤ የኑሮ ውድነትና ሥራ አጥነት አባባሽ ምክንያቶች ናቸው በሚል የተገለፀውን ሃሳብ ይቃወማሉ፡፡ ኢህአዴግ የሚመራው መንግሥት ምንም እንኳ በሚፈለገው ልክ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል ማለት ባይችልም፤ በዚህ ደረጃ ለሚፈጠሩ ችግሮች ከሚጠቀሱ መንስኤዎች ውስጥ አንደኛው ሥራ አጥነት ነው ብለው እንደማያምኑ ይገልፃሉ፡፡ የኑሮ ውድነቱም ቢሆን አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች የሚፈጥሩት በመሆኑ፤ በሚፈለገው ደረጃ እየተሰራ ባይሆንም ይህኛውም እንደምክንያት የሚጠቀስ አለመሆኑን ያመለክታሉ፡፡ መልካም አስተዳደር ላይም የህዝብ እርካታ ባይረጋገጥም ችግሩን ለማቃለል ሥራ እየተሰራና ለውጦች እየታዩ መሆናቸውን ይጠቁማሉ። እነዚህ ጉዳዮች አባባሾች ናቸው በሚል የተሰጠውን አስተያየት ይቃወማሉ፡፡ እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮች መነሻቸውን በመጣራት ላይ መሆኑን ለአብነት በኢትዮጵያ ሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች የተፈጠሩት ግጭቶች መነሻቸው ለ11 ዓመታት ተንከባለው የመጡና በጊዜ ያልተቋጩ ጉዳዮች መሆናቸውን ይገልፃሉ፡፡

ስጋቶች

ብዙዎቹ አስተያየት ሰጪዎች ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን የተናገሩ ሲሆን፤ ዶክተር ኪዳነ በዚሁ ከቀጠለ ከፍተኛ ስጋት እንዳለባቸው ሲገልፁ፤ ዶክተር ዘመላክ ደግሞ ጉዳዩ ምልክት ነው፡፡ ከፍተኛ ህመምን እንደሚጠቁመው ራስ ምታት መታየት አለበት፡፡ ትልቅ ችግር መኖሩን የሚያሳይ በመሆኑ በህገመንግስቱ መግቢያ የተቀመጠው አንድ ማህበረሰብ የመፍጠሩ ተስፋ ይጨልማል ብለው እንደሚያስቡ ተናግረዋል፡፡

አዝማሚያው አደገኛ በመሆኑ፤ አንዱ ሌላውን ሲያስወጣ በበቀል የሚነሳ አካል ተበራክቶ ወደ ማያቋርጥ ግጭት ውስጥ የሚገባበት ሁኔታ እንዳይፈጠር ከፍተኛ ስጋት እንዳላቸው ያመለክታሉ፡፡ አቶ ጥላሁንም አደጋው የከፋ መሆኑን የተናገሩ ሲሆን አቶ ለጥይበሉ በበኩላቸው፤ መንግሥትም የጉዳዩን ክብደት ተረድቶ በትኩረት እየተከታተለና እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ወደፊት እየተፈጠሩ ያሉት ችግሮች በእርግጥም ቀላል አለመሆናቸውን ፓርቲያቸው የተገነዘበው መሆኑን በማመልከት፤ በእርግጥም ችግሩ እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ አልነበረበትም፡፡ ችግሮች ከስር ከስር መፈታት ነበረባቸው፡፡ አሁንም ግን መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ይናገራሉ። አያይዘውም ሥራዎች እየተሰሩ በመሆናቸው ወደ ፊት ችግሮች ይቃለላሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

 

ምህረት ሞገስ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።