የፓርቲዎች የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ላይ የተደረገው ድርድር ሲቃኝ

05 Dec 2017

ኢህአዴግ እና 15 አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከዚህ ቀደም በሁለት አጀንዳዎች ላይ ተደራ ድረው ለማሻሻል ከስምምነት ደርሰዋል፡፡ ከእነዚህ ድርድር ከተካሄደባቸው አጀንዳዎች መካከል የምርጫ ሥነ ሥርዓት ላይ የተደረገው ይጠቀሳል፡፡ ፓርቲዎቹ ህዳር 14 ቀን 2010 ደግሞ ሦስተኛ አጀንዳ በሆነው የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ 662/2002 ላይ ተደራ ድረዋል፡፡ በድርድሩም ተቃዋሚዎች መሻሻል፣ መሰረዝ እና መጨመር አለባቸው ያሏቸውን አንቀጾች እና ንዑስ አንጾች አቅርበው ተወያይተዋል፡፡

ለድርድሩ አመቺነት ሲባል አሥራ አንድ ፓርቲዎች የድርድር ሃሳባቸውን በጋራ ያቀረቡ ሲሆን፣ መኦህዴፓ በአዋጁ ላይ የመደራደሪያ ነጥብ የለኝም ቢልም ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሚያቀርቡት የመደራደሪያ ነጥቦች ላይ የድጋፍ እና የተቃውሞ ድምጽ አሰምቷል፡፡ ኢህአዴግ በአዋጁ ላይ የማሻሻያ ሃሳብ ባያቀርብም፣ ተደራዳሪ ፓርቲዎች ባቀረቧቸው የመደራደሪያ ነጥቦች ላይ ተደራድሯል፡፡

የአዋጁ ምንነት እና የድርድሩ አስፈላጊነት

የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ከ2002 ሀገራዊ ምርጫ በፊት አዋጅ 662/2002 በሚል የወጣ መሆኑ ይታወቃል፡፡ አዋጁ የጸደቀው ከሁለት ወራት ድርድር በኋላ ነው፡፡ተደራዳሪዎቹ ኢህአዴግ፣ ቅንጅት፣ ኢዴፓ እና መኢአድ ቢሆኑም በማጽደቅ ላይ ግን በርካታ ፓርቲዎች ተሳትፈዋል፡፡ 39 አንቀጾችን ያቀፈው ይህ አዋጅ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ፓርቲዎች ድርድር የተጀመረበት ነው ሲሉ አንዳንድ ወገኖችም ጉዳዩን ይገልጹታል፡፡

በአዋጁ መግቢያ ላይ እንደተመለከተው፤ ከ2002 በፊት በሀገሪቱ ከተካሄዱ ምርጫዎች ትምህርት በመውሰድ ወደፊት የሚካሄዱ ምርጫዎች በመልካም ሥነምግባር የሚመሩ ግልጽ፣ ነጻ፣ ፍትሐዊ፣ ሰላማዊ፣ ህጋዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እንዲሁም በህዝብ ተቀባይነት ያላቸው እንዲሆኑ ለማስቻል በምርጫ ወቅት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ እጩዎች፣ የፓርቲ አባላት እና ደጋፊዎች የሚመሩበት ዝርዝር የሥነ ምግባር ህግ ማውጣት አስፈላጊነት አዋጁ እንዲወጣ ምክንያት ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡

አዋጁ የጸደቀው ጊዜ ተወስዶ በፓርቲዎች መካከል ብዙ ክርክሮች ከተደረገበት በኋላ ነው፡፡ፖለቲካ በኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ምክንያቶች የሚቀያየር ሲሆን፣ የቴክኖሎጂው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተራቀቀ መሄድም ሌላ ምክንያት ይሆናል፡፡ በመሆኑም ከዓመታት በፊት የወጡ አዋጆችን፣ ደንቦችን እና መመሪያዎችን በአሁኑ ወቅት ለመተግበር አዳጋች ሲሆን ይታያል፡፡

በተለያዩ ሀገራት ከምርጫ ህግ ጎን ለጎን የሚተገበር የፓርቲዎች ሥነ ምግባር ደንብ ያለ በመሆኑ በአዋጁ አስፈላጊነት ላይ አብዛኞቹ ፓርቲዎች እምነቱ አላቸው፡፡ በመሆኑም ይህን አዋጅ ለወቅቱ የሚመጥን ማድረግ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም፡፡የአዋጁን ድክመቶች ነቅሶ በማውጣት አዋጁን ማሻሻልም ያስፈለገው ለዚህ ነው፡፡

በፖለቲካ ፓርቲዎች ለድርድር ከቀረቡ ሃሳቦች በከፊል

መኢአድ፣ ኢዴፓ፣ ቅንጅት፣ መኢዴፓ፣ ኢብአፓ፣ አንድነት፣ ኢዲአን፣ ኢድህ፣ አትፓ፣ ኦህዴፓ እና እሶዴፓ በጋራ የድርድር ሃሳባቸውን አቅርበዋል፡፡ የእነዚህን አሥራ አንድ ፓርቲዎች ሃሳብ ያቀረቡት የአንድነት ፕሬዚዳንት አቶ ትዕግስቱ አወል እንደተናገሩት፤ አዋጁ ከሀገሪቱ አዋጆች ሁሉ ይለያል፡፡ የሌሎች አዋጆች ረቂቅ የሚቀርበው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ሲሆን፣ የዚህ አዋጅ ረቂቅ የቀረበው ግን በፓርቲዎች ስምምነት መሆኑ የተለየ ያደርገዋል፡፡ይህ አዋጅ የተለየ ልምድ የወለደም እና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ልዩ ባህሪ መገለጫ ነው፡፡

በፓርላማ መቀመጫ የሌላቸው ፓርቲዎች ጭምር በጋራ ምክር ቤት አማካይነት በፖሊሲ ላይ ሊወያዩ የሚችልበት ዕድል የፈጠረ አዋጅ መሆኑን በመጥቀስም ፣በሚፈለገው ደረጃ እንዳልተሰራበትም አቶ ትዕግስቱ ይናገራሉ፡፡አዋጁ እንዲሻሻል የአሥራ አንዱም ፓርቲዎች እምነት ነው፡፡

በዚሁ መሰረት አቶ ትዕግስቱ አሥራ አንድ የሚሻሻሉ፣ አራት የሚሰረዙ እና ሁለት የሚጨመሩ፤ በአጠቃላይ አሥራ ስድስት ነጥቦችን አቅርበዋል፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 10 ንዑስ አንቀጽ አንድ ላይ ‹‹ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ በሚመለከተው ህጋዊ አካል የተረጋገጠን የምርጫ ውጤት መቀበል አለበት›› የሚለው መሻሻል ካለባቸው አንቀጾች አንዱ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

የምርጫ ውጤቱ በቦርዱ ከመገለጹ ቀደም ብሎ ታዛቢዎች ስለምርጫው አጠቃላይ ሁኔታ ሃሳባቸውን የሚሰጡበት ዕድል ሊፈጠር ይገባል፡፡ ታዛቢዎቹ ይህን የሚያደርጉ ከሆነ ለቦርዱም እገዛ የሚኖረው ከመሆኑ ባሻገር የምርጫ ውጤት ተዓማኒነት እንደሚጨምር ይናገራሉ፡፡ ‹‹ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ በውጭ እና በሀገር ውስጥ ታዛቢዎች ፍትሃዊ፣ ሰላማዊ፣ ነጻ መሆኑ የተመሰከረለትን የምርጫ ሂደት በምርጫ ቦርድ የተረጋገጠ የምርጫ ውጤት መቀበል፣የምርጫው ውጤት በቦርዱ ይፋ ከሚደረግበት ቀን በፊት የታዛቢዎቹ ሃሳብ መቅረብ አለበት›› በሚል ቢሻሻል የሚል ሃሳብ አቅርበዋል፡፡

በአዋጁ አንቀጽ 16 ንዑስ አንቀጽ 4 የምርጫ አስፈጻሚዎች በጋራ ምክር ቤት ውይይት ላይ እንደማይገኙ ነገር ግን የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በሙሉ ድምጽ ተስማምቶ እንዲገኙ ከወሰነ ያለድምጽ በስብሰባው ላይ መገኘት እንደሚችሉ የተቀመጠውም እንዲሻሻል ጠይቀዋል፡፡

በሙሉ ድምጽ የሚለው ተገቢነት እንደሌለው የገለጹት አቶ ትዕግስቱ፣ ይህ ከሆነ አብዛኞቹ ፓርቲዎች የተስማሙበትን እንኳን አንድ ፓርቲ ብቻውን ሊያፈርስ የሚችልበትን እድል ይፈጥራል፡፡ ይህ አንቀጽ ‹‹በየደረጃው የሚገኙ ምርጫ አስፈጻሚዎች እንደ አስፈላጊነቱ በውይይት ላይ እንዲገኙ በጋራ ምክር ቤቱ አባላት በስምምነት ወይም በ2/3ኛ ድምጽ ሲወሰን ያለ ድምጽ ይሳተፋሉ›› ተብሎ እንዲሻሻል የሚል መከራከሪያ አቅርበዋል፡፡

በተመሳሳይ የጋራ ምክር ቤት ውሳኔ የሚተላለፈው በጋራ መግባባት ወይም በተባበረ ድምጽ እንደሚሆን የሚደነግገው አንቀጽ 26/ 11 ‹‹የጋራ ምክር ቤት ውሳኔ የሚተላለፈው በጋራ መግባባት ወይም በ2/3ኛ ድምጽ ይሆናል›› በሚለው ቢሻሻል የተሻለ እንደሆነ ሃሳብ ቀርቧል፡፡

በምርጫ ህጉ መሰረት በቦርዱ የሚመሰረተው የፓርቲዎች መድረክ እንደተጠበቀ ሆኖ የጋራ ምክር ቤት ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ምርጫ ክልል ድረስ እንዲቋቋም እንደሚደረግ የሚደነግገው አንቀጽ 20 ንዑስ አንቀጽ 2 በደፈናው ይቋቋማል ይላል እንጂ ይህን ተግባር የመፈጸም ኃላፊነት የማን እንደሆነ ግልጽ አላደረገም፡፡ ይህ ተቋም ያቋቁማል የማይል በመሆኑ ለአሻሚ ትርጉም ያጋልጣል፤ በመሆኑም ‹‹የጋራ ምክር ቤቶች ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ምርጫ ዞን ድረስ የማቋቋም ኃላፊነት የምርጫ ቦርድ ይሆናል›› በማለት ኃላፊነቱ የሚመለከተውን አካል መጥቀስ እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል፡፡

አራት አንቀጾች እንዲሰረዙ በአሥራ አንዱ ፓርቲዎች ስብስብ ሃሳብ የቀረበ ሲሆን፣ ለአዋጅ ተገዥ ስለመሆን እና ህግን ስለማክበር የተቀመጡት አንቀጽ 6 እና 7 አላስፈላጊ ናቸው፡፡ ምክንያቱም በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ በፌዴራል የወጡ ህጎች ሁሉ መቀበል ግዴታ መሆኑ ስለተደነገገ እነዚህ አንቀጾች ድግግሞሽ ስለሆኑ መሰረዝ አለባቸው ይላሉ፡፡

አንቀጽ 16/3 የግል እጩዎችን በተመለከተ የጋራ ምክር ቤቱ የሚደራጀው በፓርቲዎች በመሆኑ የግል ዕጩ ተወዳዳሪዎች በታዛቢነት መገኘታቸው ቀጣይነት ስለሌለው እና አዋጁም ስለማይመለከታቸው ቢሰረዝ የሚል ሃሳብም አቅርበዋል፡፡ እንዲሁም በአንቀጽ 21/7 ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሥነ ምግባር አዋጅ ሲቀረጽ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ያልተሳተፉ ሌሎች ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቱ አባል ለመሆን የጋራ ምክር ቤቱ የሚያወጣውን የስምምነት ሰነድ መፈረም እንዳለባቸው የሚደነግገው ‹‹በየደረጃው ለተቋቋሙ የጋራ ምክር ቤቶች አባል ለመሆን የሚጠይቁ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቶቹን መተዳደሪያ ደንብ ተቀብለው የስምምነት ሰነድ መፈረም ይኖርባቸዋል›› በሚል እንዲሻሻል ሃሳብ ቀርቧል ፡፡

የአሥራ አንዱን ፓርቲዎች ሃሳብ ያቀረቡት አቶ ትዕግስቱ መሻሻል እና መሰረዝ አለባቸው ካሏቸው አንቀጾች ባሻገር መጨመር ያለበትንም ሃሳብ ጠቁመዋል፡፡ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ እንዲጎለብት ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገሪቱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ በሚያተኩሩ መድረኮች ላይ ተሳታፊ በመሆን የሚል ሃሳብ በአንቀጽ 22 ስር መካተት አለበት ብለዋል፡፡

የገዳ ስርዓት አራማጅ ፓርቲ በበኩሉ በገዳ ስርዓት መሰረት የሀገሪቱ ምርጫ በየአራት አራት ዓመቱ እንዲሁም የአስፈጻሚ ምርጫ በየአምስት ዓመቱ እንዲሆን በማለት የማሻሻያ ሃሳብ አቅርቧል፡፡አዋጁ በራሱ የፓርቲዎች ሥነ ምግባር አዋጅ በሚል መሻሻል አለበት የሚል ሃሳብም አቅርበዋል፡፡ ምክንያቱም ፓርቲዎች በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ስለሚወያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሥነ ምግባር አዋጅ በሚል ይሻሻል የሚል ሃሳብ ፓርቲው ካቀረባቸው መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

በዚሁ ንዑስ አንቀጽ // ላይ ‹‹የጋራ ምክር ቤቱ አባል የሆኑ ፓርቲዎች እያንዳንዳቸው ለጋራ ምክር ቤት የሚወ ክሏቸው አባላት ቁጥር የጋራ ምክር ቤቱ በሚያወጣው የመተዳደሪያ ደንብ ይወሰናል›› በሚለው ላይ የፓርቲዎቹን መሪዎች ጨምሮ ፓርቲዎቻቸው በሚወክሏቸው ከፍተኛ አመራሮች የሚወሰን ይሆናል›› የሚል እንዲታከልበት ቀርቧል፡፡

በአንቀጽ 21/2/ሀ ምክር ቤቱ በክልል ለምርጫ ውድድር በተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይመሰረታል የሚለው በሀገር አቀፍ፣ በክልል እና በዞን ደረጃ በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ተመዝግበው የምስክር ወረቀት ባላቸው ፓርቲዎች ይመሰረታል በሚል መሻሻል አለበት፤ ምክንያቱም ያኛው ፓርቲዎችን የሚከፋፍል እና የሚነጣጥል በመሆኑ መስተካከል አለበት፡፡

የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ተደራዳሪዎች በበኩላቸው አዋጁ ለሀገሪቱ ፖለቲካ ካስገኘው ጥቅም አንጻር የሚሞካሽ አለመሆኑን በመግለጽ ሃያ አንድ አንቀጾችና ንዑስ አንቀጾች እንዲካተቱ የድርድር ሃሳብ አቅርበዋል፡፡ አዋጁ በርካታ ችግሮች ያሉበት መሆኑንም እንዲሁ አመልክቷል፡፡ ለአብነት ያህል የጋራ ምክር ቤትን በተመለከተ አዋጁ ያስቀመጠው አንቀጽ በራሱ የከፋፋይነት ባህሪ ያለው ነው፡፡ በመሆኑም በምክር ቤቱ የተለያዩ ርዕዮተ ዓለም ያላቸውን ፓርቲዎች በአንድ ጥላ ስር ለመሰብሰብ አዋጁ ምንም የፈየደው የለም፡፡ አዋጁ ፓርቲዎችን አደፋፋሪ ሳይሆን ገፊ ነው፡፡ በመሆኑም የአዋጁ ፋይዳ እምብዛም ነው ብሏል፡፡ በመሆኑም መሻሻል ያለበት ተሻሽሎ፣ መሰረዝ ያለበት ተሰርዞ እና መጨመር ያለባቸው አንቀጾች ተካተው ለወቅቱ በሚመጥን መልኩ ሊስተካከል ይገባል ሲል ሀሳቡን አቅርቧል፡፡

በአዋጁ አንቀጽ 21 ላይ የሰፈሩት ሀሳቦች ፓርቲዎችን የሚከፋፍል እና አብረው እንዳይሰሩ የሚያደርጉ ከመሆናቸውም ባሻገር እርስ በርስ የሚያፋጁ ሃሳቦች ናቸው፡፡ ለአብነት ያህል በዚህ አንቀጽ ስር የጋራ ምክር ቤት በሀገር አቀፍ ለምርጫ ውድድር በተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሚመሰረት የሰፈረው አንቀጽ ተጠቃሽ ነው፡፡ የትኛውም ፓርቲ በፍላጎት እና በነጻነት መርህ ላይ ተመስርቶ ከጋራ ምክር ቤት የመግባትም ሆነ የመውጣት መብትን በሚያስጠብቅ መልኩ ሊደነገግ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

እንደዚህ ዓይነት የሚያራርቁ ሃሳቦች ደግሞ ቢያንስ በህግ ደረጃ ሊኖሩ አይገባም፡፡ በመሆኑም በፖለቲካ ፓርቲዎች የምዝገባ አዋጅ ተመዝግበው የምስክር ወረቀት ባላቸው ፓርቲዎች እንዲመሰረት የሚደነግግ ህግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በመድብለ ፖርቲ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ስለሚመረጥ መንግሥት በአንቀጽ 5 ላይ የሰፈረው ይህ ድንጋጌ በምርጫው ሂደት እና ምንነት፣ ተሳትፎ እና ውጤት ላይ ልዩ ነጥብ ያሳርፋል፡፡ የአንድ ፓርቲ የመንግሥትነት ህጋዊነት የሚረጋገጥበት ተብሎ የተቀመጠው ሃሳብ በጣም ቁንጽል እና ጠባብ ነው፡፡ በምርጫ ወቅት ለ24 ሰዓታት ብቻ ተግባራዊ በሚሆን ጉዳይ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው ያሉት አመራሮቹ፣ መራጮች በምርጫ ዘመቻ አማካይነት ብቻ በሚከናወኑ ነጥቦች ህጋዊ መሆኑ ለአንድ መንግሥት ህጋዊነት በመርህ ደረጃ በቂ ነው ብለን እንድንቀበል ያስገድዳል ሲሉ ጠቁመዋል፡፡

በመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ የሚመረጥ መንግሥት ህጋዊነት የሚረጋገጥበት ሌሎች ነጥቦች ልጨመሩ ይገባል፡፡ የድህረ ምርጫውም ሆነ ቅድመ ምርጫው ሂደት ግልጽ፣ ፍትሃዊ፣ ሰላማዊ፣ ህጋዊ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንከን የለሽ በሆነ ምርጫ ህዝባዊ አመኔታ ባለው መልኩ ህጋዊ ተቀባይነት ያገኘ ብቻ መሆን አለበት፡፡ ህጋዊ ቅቡልነትና ህዝባዊ አመኔታ የሌለው፣ ግልጽ፣ ፍትሃዊ እና ሰላማዊ ያልሆነ፤ በምርጫ ዘመቻና ምርጫ ሂደት ላይ ብቻ በተንጸባረቁ የተወሰኑ አዎንታዊ ጎን በሚመስሉ ጉዳዮች ብቻ ስልጣን ላይ የተቀመጠን ፓርቲ ህጋዊ ነው ብሎ መቀበል ያስቸግራል፡፡

ስለዚህ በመድብለ ፓርቲ የዴሞክራሲ ሥርዓት የሚመረጥ መንግሥት ህጋዊነት የሚመሰረተው በቅድመ ምርጫና ድህረ ምርጫ ያሉ ሂደቶች ነጻ፣ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ህጋዊ በሆነ መንገድ እንከን የለሽ በሆነ ምርጫ የተመረጠ መሆኑን የሚጠቅስ አንቀጽ አዋጁ ላይ ማካተት ያስፈልጋል፡፡ በሚገኘው የምርጫ ውጤት ላይ ሙሉ በሙሉ መተማመኛ ያለው መንግሥት መሆን እንዳለበትም የኢራፓ ተደራዳሪዎች ጠቁመዋል፡፡

አዋጁ የጋራ ምክር ቤት ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ምርጫ ክልል እንደሚቋቋም ይደነግጋል፡፡ ሆኖም የሀገር አቀፍ ፓርቲዎች እና የክልል ፓርቲዎች በምን ደረጃ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚችሉ በግልጽ አልተቀ መጠም፡፡ ስለዚህ የክልል እና የፌዴራል ፓርቲዎች የሀገር አቀፍ ፓርቲዎች በጋራ ምክር ቤት ላይ እንደሚሳተፉ በግልጽ መቀመጥ እንዳለበትም አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

የመላው ኢትዮጵያውያን ብሄራዊ ንቅናቄ (መኢብን) በበኩሉ አሥር አንቀጾች እና ንዑስ አንቀጾች እንዲሻሻሉ ሃሳብ አቅርቧል፡፡ በየሴክተር መስሪያ ቤቱ የልማት ሠራዊት ተብለው የሚቋቋሙ አደረጃጀቶች በምርጫ ላይ በተለያዩ አኳኋኖች ሲሳተፍ ይስተዋላል፡፡ ይህ ደግሞ በምርጫ ላይ ችግር ሲፈጥር ይታያል፡፡ በዚህ አዋጅ ላይ እነዚህ አደረጃጀቶች በምንም መልኩ ምርጫ ላይ ተሳታፊ እንዳይሆኑ የሚደነግጉ አንቀጾች ሊካተቱ ይገባል የሚለው ካቀረባቸው ሃሳቦች መካከል ይጠቀሳል፡፡

ኢህአዴግ ምን አለ

የኢህአዴግ ዋና ተደራዳሪ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ይህ አዋጅ ኢህአዴግ እና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ረጅም ጊዜ ወስደው ከተደራደሩ በኋላ ህግ ሆኖ ወጥቷል፡፡ በአዋጁ ላይ ኢህአዴግ ለድርድር የሚያቀርበው ሃሳብ የለውም፡፡ አቶ ሽፈራው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ካቀረቧቸው ሃሳቦች መካከል የተወሰኑትን ውድቅ አድርገው፣ ሃሳቦቹ ግን ጠቃሚ መሆናቸውን አቶ ሽፈራው ገልጸዋል፡፡ እነዚህ አንቀጾች በሕግ አሠራር ታይተው ሊሻሻሉ እንደሚችሉም ተናግረዋል፡፡

ስለ ምርጫ ውጤት ታዛቢዎች ሊኖራቸው ስለሚገባው ሚና ከፓርቲዎች ለተነሳው የማሻሻያ ሃሳብ በሰጡት አስተያየት ታዛቢዎች ሚናቸው የምርጫ ሂደትን መገምገም ነው፡፡ ታዛቢዎች ሥራቸው የምርጫው ሂደት ፍትሃዊ እና ነጻ ስለመሆኑ መታዘብ ነው፡፡ ውጤት መግለጽ አይደለም፡፡ አንቀጹ ደግሞ የሚያስረዳው ውጤትን ስለመቀበል ነው፡፡ ውጤት የመግለጽ ኃላፊነት ደግሞ ያጫወተው አካል ወይም የዳኛ ነው፡፡ ዳኛው ደግሞ ታዛቢ ሳይሆን የምርጫ ቦርድ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ሃሳብ መነሳት የሌለበት በመሆኑ ሃሳቡን እንዲተውት ጠይቀዋል፡፡ በሌሎች ሀገራትም ቢሆን የምርጫ ውጤትን የሚያሳውቀው የምርጫ ቦርድ ወይም ኮሚሽን መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የታዛቢዎች የምርጫ ውጤት መግለጽ በምርጫ ውጤት ተዓማኒነት ላይ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል አቶ ሽፈራው ይናገራሉ፡፡ታዛቢዎች ለአንድ ወገን ሊያደሉ እንደሚችሉ በመጥቀስም በታዛቢዎች የሚገለጽ ውጤት ተዓማኒ ሊሆን እንደማይችል ያብራራሉ፡፡ ለአብነት ያህል በቅርቡ በኬኒያ በተደረገው ምርጫ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ታዛቢዎች ምርጫው ነጻና ፍትሃዊ እንደነበር ቢገልጹም ምርጫው የተደገመበትን አጋጣሚ ጠቅሰዋል፡፡

የጋራ ምክር ቤት ከፌዴራል እስከ ምርጫ ክልል መኖር አለበት በሚል ከፓርቲዎቹ የተነሳው ጥያቄ ተገቢነት ያለው ነው ያሉት ዋና ተደራዳሪው ፣ በዞንም ሆነ በምርጫ ክልል ምክር ቤቶች መቋቋም ላይ ኢህአዴግ ልዩነት እንደሌለው ያመለክታሉ፡፡

አንዳንድ ለድርድር የቀረቡ ሃሳቦች የአፈጻጸም ችግሮች እንጂ የአንቀጾቹ ችግር አለመሆናቸውንም የጠቀሱት አቶ ሽፈራው፣ በአፈጻጸም ችግሮች ላይ በማውራት ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ ሌሎች መዋቅሮችን ማበጀት ለአላስፈላጊ የገንዘብ ወጪ ይዳርጋል ይላሉ፡፡በአፈጻጸም ችግሮች ላይ በመወያየት ማስተካከል እንደሚቻልም ተናግረዋል፡፡

መኢብን ላቀረበው ሃሳብ በሰጡት አስተያ የትም በተለያዩ የልማት ሠራዊቶች ውስጥ የኢህአዴግ አባላት ካሉ በምርጫ ጊዜ ቅስቀሳ ላይ ይዘምታሉ፡፡ የልማት ሠራዊት የሆነ ሰው ሁሉ ኢህአዴግ ነው ማለት ግን አይደለም፡፡ የተለያዩ ፓርቲዎች አባል ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አባል ለሆኑበት ፓርቲ መቀስቀስ ግን ሊከለከሉ አይገባም ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ምርጫው በየአራት ዓመቱ እና የአስፈጻሚ ምርጫ በየስምንት ዓመቱ እንዲካሄድ በማለት የገዳ ስርዓት አራማጅ ፓርቲ ያቀረበውን ሃሳብም በሁለት ምክንያች ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል፡፡ የገዳ ስርዓትን በሚያራምደው በኦሮሞ ብሄር ዘንድ ምርጫ የሚካሄደው በየስምንት ዓመቱ እንጂ በየአራት ዓመቱ አለመሆኑን በመግለጽ ለፖለቲካ ፍጆታ ተብሎ የህዝብን ባህል ማዛባት ተገቢነት እንደሌለው አቶ ሽፈራው ተናግረዋል፡፡ አዋጁ የኦሮሞ ህዝብ ብቻ ሳይሆን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚተዳደርበት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

 

መላኩ ኤሮሴ

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።