ፌዴራሊዝም በዓለም አገራት ፌዴራሊዝም በኢትዮጵያ

06 Dec 2017

   

ፌዴራሊዝም የሚለው ቃል ‹‹Foedus›› ከሚለው የላቲን ቃል የተወረሰ መሆኑን መጻህፍት ይነግሩናል፡፡ ትርጉሙም ቃል-ኪዳን፣ ኮንትራት፣ ድርድር ወይም የአብሮነትና በጋራ የመኖር ውልን ይወክላል፡፡

ቃሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ ሲውልም በሰው ልጅና በፈጣሪ መካከል ሊኖር የሚገባውን ግንኙነት ለመግለፅ ነበር፡፡ በጥንታዊ ዘመን በተለያዩ ትናንሽ ግዛቶች የሚኖሩ ማህበረሰቦች ራሳቸውን ከወረራና ከተለያዩ አደጋዎች ለመጠበቅ ሲሉ ውስጣዊ ማንነታቸውንና አከባቢያዊ ግዛቶቻቸውን እንደጠበቁ የጋራ አስተዳደርና ሕብረት ለመፍጠር ይስማሙ ነበር፡፡

ይህንን በፈቃደኝነት የመሰረቱትን ሕብረት የሚገልፅ ቃል በሚፈልጉበት ጊዜም ፌደራል ወይም ፌደራሊዝም የሚል ቃል ተስማሚ ሆኖ አገኙት፡፡ ከዛን ጊዜ ጀምሮ ቃሉ የፖለቲካ ትርጉምና ይዘት እየወረሰ በመምጣት በ1291 የተመሰረተው የስዊስ ኮን-ፌደራላዊ ስርዓትና ከዛ ቀጥሎ የተመሰረቱ ፌደራላዊ ስርዓቶች ሕብረታቸውንና የመንግስታቶቻቸውን ቅርፅ ለመግለፅ ቃሉን እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡

ስለሆነም ፌደራላዊ የመንግስት አወቃቀር ማለት የራስ-አስተዳደርና የጋራ-አስተዳደርን ያጣመረ፣ ሁለት ወይንም ከሁለት በላይ የሆኑ መንግሥታት የሚፈጥሩት በቃል ኪዳን የሚመሰረትና የሚመራ አጋርነት ነው፡፡ አጋርነቱ በመካከላቸው ሊኖር የሚገባውን የሥልጣን ክፍፍልና ዝምድና ይወስናል፤ አንዱ የሌላውን ቅንነትና የአብሮነት መኖር እሳቤ ተቀብሎ በማመን ላይ ይመሰረታል፡፡ እንዲሁም አንዱ የሌላውን ልዩ ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት ወዘተረፈ በማክበርና በእኩልነት ይጠብቃል፡፡

ፌዴሬሽኖች ባለፉት ሁለት ምዕተ ዓመታት በተፈጠሩ የተለያዩ ታሪካዊ ክስተቶች ተፈጥረዋል፡፡ ከዓለም ህዝብ መካከል 40 በመቶ የሚሆነው የሚኖርባቸው 28 የዓለማችን ሀገራት የፌዴራሊዝም ስርዓትን ይከተላሉ፤ወይንም ፌዴራላዊ ተብለው ተፈርጀዋል፡፡ እነዚህ ሀገራት እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ሰፊ ግዛት ያላቸው መሆናቸውና ዴሞከራሲያዊ ስርዓትን መከተላቸው ፌዴራሊዝም ከነጻነትና ከዴሞከራሲያዊ መረጋጋት ጋር ሊጣመር ችሏል፡፡

በተባበሩት መንግስታት ስር ተመዝግበው ካሉ 192 ሀገራት መካከል 28ቱ ፌዴራላዊ ስርዓትን የሚከለተሉ ናቸው፡፡ ብዙዎቸ እንደሚያስቡት ፌዴራሊዝም በኢትዮጵያ ብቻ ያለ አንድነትን ሳይሆን ልዩነትን የሚያሰፋ ስርዓት አይደለም፡፡ ስርዓቱ ይህንን የማድረግ እድሉ እጅግ አናሳ ነው፡፡ ፌዴራሊዝም ሀገርን የሚበታትንና አንድነትን የሚያጠፋ ቢሆን ኖሮ ከኢትዮጵያ በፊት ፌዴራሊዝምን ቀድመው የጀመሩት ሀገራት ህልውና እስከዛሬ አክትሞ በነበር፡፡

እውነታው ግን ለቅል ነው፡፡ ፌዴራሊዝም ብዙነትን በአንድ ላይ አጣምሮ የሚይዝ ስርዓት ነው፡፡ እነ አሜሪካና ስዊዘርላንድ ፌዴራላዊ ሰርዓትን ተቀብለው መተግበር ከጀመሩ ምዕተ አመት አስቆጥረዋል፡፡ እንደ ተባለው ስርዓቱ ሀገርን አደጋ ውስጥ የሚጥልና አንድነትን የሚያጠፋ ቢሆን ኖሮ ዛሬ አሜሪካም ሆነ ስዊዘርላንድ የሚባሉ ሀገራትን ላናይ አንችል ነበር፡፡ ኢትዮጵያም ከዚሁ ተምራ ስርዓቱን አዲዎስ ማለት ትችል ነበር፡፡ እንደተባለው እውነታውና ስጋቱ ውሃና ዘይት ናቸው፡፡

አሜሪካ እአአ በ1789 በህገ መንግስት የተረጋገጠ ፌዴራላዊ ስርዓትን በሀገሯ ላይ እውን አድርጋለች፡፡ ስዊዘርላንድ ደግሞ እአአ በ1848 ስርዓቱን በህገመንግስቷ እውቅና አሰጥታ ዘርግታለች፡፡ ጀርመንም እአአ በ1871 ፌዴራላዊ ህገ መንግስትን ይፋ አድርጋለች፡፡

በመቀጠልም ካናዳ፣ ቤልጂየም፣ ህንድ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያ፣ ሱዳን፣ አርጀንቲና፣ ብራዚል፣ ሜክሲኮ፣ የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ የተለያዩ ግዛቶች፣ ቼኮስሎቫኪያ፣ ከኮሚኒዝም መፈራረስ በኋላ ደግሞ ሶቪየት ህብረት ወደ ፌዴራል ሰርዓት በሂደት ተቀላቅለዋል፡፡

ፌዴራል ስርዓቶች የራሳቸው መሰረታዊ ባህርያት አሏቸው፡፡ እንደ አብነትም ከህዝባቸው ጋር ቀጥታዊ ግንኙነት ያላቸው ሁለት መንግስታት፣ ሕገ-መንግስታዊ ዋስትና ያለው የስልጣን ክፍፍል፣ የተፃፈ ሕገ-መንግስት፣ ክልሎች ወይንም ብሄር ብሄረ-ሰቦች የሚወከሉበት ሁለተኛ ምክር ቤት፣ ገላጋይ ተቋም የሚሉት ባህሪያቸው መሆናቸውን ይጠቅሳሉ፡፡

የፌዴራል አወቃቀር የተጀመረው ከሶስት ሺ 2ዐዐ ዓመታት በፊት በእስራኤሎች እንደሆነ ታሪክ እማኝ ነው፡፡ ፌዴራል ሥርዓት እንደ ጥሩ የመንግሥት አወቃቀር አማራጭ እየታየ በመምጣቱም በርካታ ሀገራት በ19ኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያና ከ2ዐኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ መከተል ጀምረዋል። 21ኛው ክፍለ ዘመን የፌዴራል ሥርዓት ክፍለ ዘመን እንደሚሆን ይታመናል፡፡ የዚህ ምክንያቱ በርካታ ቢሆንም ብዙ ፀሃፊዎች የሚጠቅሱት የሚከተሉትን ነው፡፡

በዓለም ላይ በአሁኑ ወቅት የፀጥታ ችግርና የመስፋፋት አደጋ እየተበራከተ ነው። ይሄንን ለመመከት ጠንካራ የመከላከያ ሐይል ማስፈለጉ የግድ ነው። ለዚህ ደግሞ ፌዴራሊዝም ተመራጭ ስርዓት ነው። በዚህ ምክንያት ፌዴራሊዝምን ከተገበሩ አገራት መካከል ካናዳ፣ ጀርመን፣ ህንድ፣ ማሌዢያ በአብነት ይጠቀሳሉ። ሰፊ የጋራ ገበያና ኢኮኖሚ የመፍጠር ፍላጎትን ለመመለስም ፌዴራሊዝም ተመራጭ ስርዓት ነው። ካናዳ እና የአውሮፓ ህብረት ደግሞ ምሳሌ ሊሆኑ ይችላሉ። አንድነትን ከብዙነት ጋር አጣምሮ ለማስቀጠል፣ ርዕዮተ-ዓለማዊና ለድህረ-ቅኝ ግዛት መፍትሄ መሆኑም ፌዴራሊዝምን የማይተው ያደርገዋል። ኡጋንዳና ናይጀሪያ ጥሩ እማኝ ናቸው። ለድህረ-ግጭት መፍትሄ መሆኑም ሌላው የፌዴራሊዝም ስርዓት ተመራጭ ባህሪው ነው። አሜሪካ፣ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ አፍሪካን በአብነት መጥቀስ ይቻላል። ትልቅ የቆዳ ስፋት ላላቸው አገራትም የሚስማማ አወቃቀር እንደሆነ የዘርፉ አዋቂዎች ከጻፏቸው ሰነዶች መረዳት ይቻላል።

የፌዴራል አወቃቀር በሶስት አይነት መንገድ ሊከሰት ይችላል። በፊት ነጻ የነበሩ መንግስታት በስምምነት አንድ የጋራ መንግስትና አገር ሊመሰርቱ ይችላሉ፡፡ በአንድ ማዕከላዊ መንግስት ይተዳደሩ የነበሩ ሀገራት በሚገጥማቸው ውስጣዊ ችግር ስልጣንን ከፍለው ወደታች በማውረድ ፌዴራል አወቃቀርን ሊከተሉና አንድነትን ሊያስቀጥሉ ይችላሉ፡፡ ሁለቱን በማዳበልም የፌዴራል ስርዓትን መመስረት ይቻላል፡፡

የፌዴራል ስርዓት አወቃቀር ዓይነቶች የሚባሉት ሶሰት ናቸው፡፡ እነዚህም ብሔራዊ /ጂኦግራፊያዊ አወቃቀር/ ሕብረ-ብሔራዊ /ብሔራዊ ማንነት፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ ወዘተን… መሰረት ያደረገ/ እንዲሁም ሁለቱን ያዳበለ አወቃቀር የሚሉት ናቸው፡፡ ከእነዚህ የፌዴራሊዝም አይነቶች ኢትዮጵያ ውስጥ እየተተገበረ ያለው ሕብረ- ብሄራዊ ፌዴራል ስርዓት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይሀ የፌዴራሊዘም አይነት ለቡድን ማንነት እውቅና የሚሰጥ ነው፡፡ የቡድን ማንነት መገለጫዎች የሚባሉት ደግሞ ብሄር፣ ብሄረሰብ፣ ባህል፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ ታሪካዊ አመጣጥ፣ ማህበራዊ መስተጋብር ወዘተ የሚሉት መሆናቸውን ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

የኢትዮጵያ ሕብረ-ብሄራዊ ፌዴራል ስርዓት መነሻዎች የማንነት (የብሄር፣ ብሄረሰብ፣ ሃይማኖት፣ የቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክ … ወዘተ/ ጭቆና፣ የመልማት መብት መነፈግ፣ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ዓፈና፣ የመልካም አስተዳደር እጦት ናቸው፡፡ እነዚህ ጭቆናዎች ለመጣል የኢትዮጵያ ህዝቦች በብሄር ጥያቄ ዙሪያ ተደራጅተው የፊውዳሉን ስርዓትና የደርግ ወታደራዊ አገዛዝን ለመጣል ታግለዋል፡፡ በ1983 .ም የኢትዮጵያ የሽግግር ወቅት ቻርተር ለማፅደቅ የተሰባሰቡ፣ እንዲሁም የሽግግር መንግስትን የመሰረቱ የፖለቲካ ድርጅቶች ከሞላ ጎደል በብሄር ማንነት የተደራጁ ነበሩ፡፡ ትግሉም ከተቋጨ በኋላ እነዚህ ኃይሎች የሽግግር መድረክ በማቋቋም የጋራ ቻርተር አጽድቀዋል፡፡

የሽግግር መድረኩ ተልዕኮውን ካጠናቀቀ በኋላ በ1987 .ም የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሊመሰረት ችሏል፡፡ በመሆኑም የፌዴራል ስርዓቱ የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን ሙሉ በሙሉ በመመለስ አዲስ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ግንኙነቶችን መፍጠር ችሏል፡፡ በኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት ያልተመለሱ ጥያቄዎች የሉም። ህገ መንግስቱ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ጥያቄዎችን መልሷል፡፡ አንድነት ያስቀጠለ ስርዓትን ወልዷል፡፡ መድብለ ፖርቲን ዕውን አድርጓል፤ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትንና የማህበራዊና መሰረተ-ልማት አውታሮች ልማትን ያረጋገጠ ስርዓት ፈጥሯል፡፡

በኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓት ላይ አንዳንድ ጥያቄዎች ወይንም ቅሬታዎች ሲቀርቡበት ይሰማል፡፡ እነዚህ ቅሬታ የሚያቀርቡ አካላት በአንድ በኩል ህብረ-ብሄራዊ ፌዴራል ስርዓቱ አንድነትን አደጋ ላይ ይጥላል ይላሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ህብረ-ብሄራዊ ስርዓቱ የብሄሮችና ብሄረሰቦች መብቶችን አላረጋገጠም ሲሉ ይደመጣሉ፡፡

በስርዓቱ ላይ ከሚቀርቡ ትችቶች መካከልም የተወሰኑትን መጥቀስ ይቻላል። ‹‹ዓንቀጽ 39 ለህብረታችን ተፈላጊ ድንጋጌ አይደለም፣ ፌዴራል ስርዓቱ ውጤታማ የሚሆነው ጂኦግራፊያዊ አወቃቀርን መሰረት ካደረገ ነው፤ ፌደራላዊ አወቃቀር በባህሪው ለአንድነት አደጋ ነው፤ የኢትዮጵያ መንግስት ትኩረት ከአንድነት ይልቅ የቡድን መብትን በመጠበቅ ላይ ያተኮረው፤ ፌዴራል ስርዓቱ አገር አቀፍ የነበረውን ግጭት ወደ ትናንሽ ግጭቶች ቀይሯቸዋል፤ ስርዓቱ የብሄር ብሄረሰቦችን መብት እኩል አላረጋገጠም፤ በየአካባቢው የሚከሰቱ ግጭቶች የዚሁ ውጤቶች ናቸውና” ወዘተ የሚሉ ይገኙባቸዋል፡፡ ነገር ግን የስርዓቱን መሰረታዊ መርሆዎችና ያስገኟቸውን ውጤቶች በመተንተን የተጠቀሱት ጉዳዮች ትክክል እንዳልሆኑ ማየት ይቻላል፡፡

የኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓት ከሌሎች ፌዴሬሽኖች የሚለይባቸው ጉዳዮች አሉት፡፡ ከብዙው በጥቂቱ እነዚህን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል ተረጋግጧል፤ የሉአላዊ ስልጣን ባለቤት ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሆነዋል፤ እነዚህ ህዝቦችም በፌደሬሽን ምክር ቤት እንዲወከሉ እድል ተፈጥሯል፤ ሕገ-መንግስትን የመተርጎም ስልጣንም ለፌደሬሽን ምክር ቤት ተሰጥቷል፡፡ ይህ ባህሪው የኢትዮጵያን የፌዴራል ስርዓት ከሌሎች ለይቶታል አስብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ስርዓት የወደፊት አቅጣጫዎችም አሉት፡፡ እነዚህም የመከባበር፣ የመደማመጥ፣ የመቻቻል፣ የመደጋገፍና የመተባበር ባህልን ማጎልበት፣ ብዙሀነትን ማክበር፣ የጋራ ማንነት መገለጫዎችን ማጎልበት፣ የመንግስታትና የህዝቦች ግንኙነቶችን ማጠናከር፣ ሕገ-መንግስትና ሌሎች የስርዓቱ ሕጎችን ማክበርና መጠበቅ፣ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ መላ ሃብትን ማንቀሳቀስና መረባረብ፣ ጎጂ የውጭ ፖለቲካን (Imported Politics) ማስወገድ፡፡

ወደ መበታተን አደጋ ውስጥ የነበረች አገር በፌዴራላዊ የመንግስት አወቃቀር ምክንያት ለመጀመሪያ ጊዜ በታሪኳ አለምን ያስደመመ የኢኮኖሚ እድገት ልታስመዘግብ ችላለች፡፡ ‹‹…ማደግ እንደምንችል ያረጋገጥነው፤ የማደግ ተስፋችንም በእጃችን እንዳለ ያመንነው በፌዴራል ስርዓታችን ነው›› ሲል መንግስት የሚከራከረውም በአየር ላይ እንዳልሆነ መሬት ላይ ያሉ እወነታዎች ይናገራሉ።

እንደ አጠቃለይ የፌዴራሊዝም ስርዓት በተለያዩ የአለማችን ሀገራት ተመራጭነቱ እየጨመረ ነው፡፡ ለዚህም የራሱ ምክንያቶች አሉት፡፡ በዋናነት ለብዝሃነት ዕውቅና የመስጠት ዝንባሌ እያደገ መምጣቱ፣ህብረ ብሄራዊነትና ህብር ሉአላዊነት መስፋፋቱ፣ ዘረኝነት ኋላ ቀር አስተሳሰብ እየሆነ መምጣቱ፣ የተለያየ ቋንቋ ባህልና እምነት ያላቸው ነገር ግን ተፈቃቅረውና ተከባብረው የሚኖሩባት ሀገር ለመፍጠር እና ራሳቸውን ለማስተዳደር ማስቻሉ እንዲሁም አንድነትን ለመገንባት ጎሳን ማጥፋት የሚለው የአሃዳዊ ስርዓት መክሰሙ የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡

ፌዴራሊዝም ለብዝሃነት እውቅና የሚሰጥና አንድነትን ይበልጥ የሚያጠናክር ሰርዓት ነው፡፡ ከዚሀ ውጪ የሚደመጡት ፌዴራሊዝም ሀገርን ይበታትናል ወይንም አንድነትን ያጠፋል የሚሉት አስተያየቶች ‹‹ያላዋቂ ሳሚ....››ያሰኛሉ፡፡ ምክንያቱም ስርዓቱ በኢትዮጵ የተመረተ ለኢትዮጵያዊያን ብቻ የተተወ አይደለምና ነው፡፡

 

በጋዜጣው ሪፖርተር

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።