በመገናኘት መተዋወቅ፤ በመተዋወቅ መተሳሰብ

07 Dec 2017

ነጻነቷን ሳታስደፍር ጠብቃ ለመኖር የቻለችና የሰው ዘር መገኛም የሆነች ታላቅ አገር ኢትዮጵያ በአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት በሰመራ ከተማ የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓልን ልታከብር ዝግጅቷን አጠናቃ የነገውን እለት በጉጉት በመጠባበቅ ላይ ትገኛለች። የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) 1983 .ም መንበሩን ከተረከበ በኋላ አገሪቱ ከ1999 .ም ጀምሮ ለተከታታይ 11 ዓመታት ይህን በዓል ስታከብር መቆየቷ ይታወሳል። ዘጠኙ ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮችም በዓሉን በየተራ በማስተናገድ ወደ እነርሱ የሚመጣውን ህዝብ በአክብሮት በመቀበል መሸኘታቸውም አይዘነጋም።

የበዓሉ ባለቤት የሆነው ህዝብ፣ በዓሉ ወደሚከ በርበት ክልል አሊያም ከተማ አስተዳደር ጉዞውን ሲያደርግ እግረ መንገድ የሚገኙ ከተሞችም ሆኑ የገጠር ቀበሌዎች እንግዶቹን ጎራ እንዲሉ በመጋበዝ ቤት ያፈራውን በማቅረብ እንዲሁም ባህሉንም በማሳየት ደማቅ አቀባበል እያደረገ ሲሸኛቸው ላለፉት ዓመታት ተስተውሏል። በነገው እለትም ይህንኑ አይነት መስተንግዶ በማለፍ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በአንድ ላይ ታድመው ቀናቸውን ለማክበር የሰው ዘር መገኛ ወደሆነችው አፋር ክልል በማቅናት ላይ ሲሆኑ፣ ቀደም ብለው የገቡም አይታጡም።

በዓሉ በየዓመቱ በድምቀት የመከበሩ ምስጢር የብሄር ብሄረሰብ መብትን ያስከበረ፣ ለህዝቦች አንድነትና ተቻችሎ መኖር ዋስትና የሰጠ ህገ መንግሥት የጸደቀበት ቀን በመሆኑ ነው። በዚህ ህገ መንግሥት መሰረት ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ማንነታቸው ታውቋል። ቋንቋቸውንና ባህላቸውንም ያለምንም ገደብ የማሳደግ መብት ተጎናጽፈዋል። እንዲሁም የኃይማኖት እኩልነትም ተጠብቆላቸዋል። ይህን መብት ያጎናጸፈው የህጎች ሁሉ የበላይ ህግ በሆነው ህገ መንግሥት ሲሆን፣ በአንጻሩ ደግሞ ይህን ህገ መንግሥት ወደጎን በመግፋትና እውቅና ካለመስጠት እየታየ ያለ ግጭትም በአገሪቱ አንዳንድ ቦታ ሲስተዋል ቆይቷልና ለሰላም መስፈን የበዓሉ መከበር ምን ፋይዳ አለው? በሚለው ሐሳብ ላይ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንዲሁም የበዓሉ አስተባባሪ የሆነውን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አነጋግረናል።

የመላው ኢትዮጵያውያን ብሄራዊ ንቅናቄ ፕሬዚዳንት ልጅ መስፍን ሽፈራሁ እንደሚሉት፤ በመጀመሪያ ደረጃ አብሮነት የሚጀመረው ከቤተሰብ ነው። የቤተሰቡ በአንድ ጣራ ስር መሆንና በተለያዩ የቤተሰብ ጉዳዮች ላይ መወያየት መቻል በርካታ ችግርን መፍታት ያስችላል፤ እርስ በእርስም የመተጋገዝ እሴትን ያዳብራል። ይህን ሰፋ አድርገን ስንወስድ እንደ አገር የተለያየ ባህል፣ ኃይማኖትና ቋንቋ ያለው ሰው በአንድ ስፍራ ሲሰባሰብ ድምቀቱ ሳቢ ከመሆኑም ባሻገር ተሞክሮውን የመለዋወጡ ጉዳይ ጠቃሚ ነው የሚሆነው።

ይህ በአንድ ላይ ተሰባስቦ ባህልን፣ እሴትንና ተሞክሮውን የመለዋወጡ ጉዳይ ኢትዮጵያ ለምትገነባው አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ አለው። ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በአንድ መድረክ መገናኘታቸው ችግር እንኳ ቢኖር ለመነጋገርና አብሮነትን ለማጠናከር ትልቅ ፋይዳ አለው። አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመፍጠር በሚደረገው ትግል ውስጥ የበዓሉ መከበር በጣም ወሳኝና አስፈላጊ ነው። «የኢኮኖሚ ችግራችን ዋነኛ ማነቆ ሆኖብን እንጂ ግንኙነቱን የሚያጠናክሩ መድረኮች በየጊዜው ቢካሄዱ መልካምነቱ ነው ጎልቶ የሚታየው» ይላሉ።

እስካሁን በተደረገው የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በየተራ የማስተናገድ እድል አግኝተዋል የሚሉት ልጅ መስፍን፣ በዚህም የአገሪቱ ህዝብ እርስ በእርስ በመተዋወቅ ላይ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት። ይህ መሰባሰብ ህዝቡ በአገሪቱ ላይ የእኔነት ስሜት እንዲሰማውም በማድረጉ በኩል ትልቅ ፋይዳ አለው። ቀደም ሲል የነበረው መገለል ጠፍቶ አብሮነት እያበበ ይገኛል። ይህ ደግሞ በዓመት ለመገናኘት እንኳ ናፍቀው እንዲመጡ ሁሉ እያደረጋቸው ነው። «እኔም አንዱ የበዓሉ ታዳሚ ነኝና እጅግ በርካታ ብሄር ብሄረሰብ በአንድ ቦታ ተገኝተን እርስ በእርስ እንድንተዋወቅ መደረግ መቻሉ መንግሥትን በራሴና በፓርቲዬ ስም ላመሰግን እወዳለሁ» ሲሉም ይገልጻሉ።

«የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግም ሆነ ለሰላሟ መከበር የብሄር ብሄረሰቦች መቀራረብ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። ባለመተዋወቅ ውስጥ መጠላላት ሊፈጠር ይችላል። ምክንያቱም አንዱ የሌላውን ሐሳብ እና አመለካከት በአግባቡ ካልተረዳ መተሳሰቡና አብሮነቱ ሊፈጠር አይችልም። ቀደም ሲልም እንቅፋት ሲፈጥር የነበረው አለመግባባቱ ነው። ባለፉት ጊዜያት በጠላትነት እንድንፈራረጅ ያደረገን የእርስ በእርስ ግንኙነት ባለመኖሩ ነው። ሰላም ላለመፍጠር አንዱ ምክንያት አለመገናኘቱ ነው» የሚል አመለካከት እንዳላቸው ልጅ መስፍን ይናገራሉ።

«ያለን አንድ አገር ነው፤ በውስጥ ያለው የአስተዳደር መዋሰን ሊለያየን አይገባም» ሲሉም ያክላሉ። በአገሪቱ ከርሰ ምድርም ሆነ ገጸ ምድር ገና ያልተነካ ሀብት አለ። ይህ ደግሞ በውስጧ ያሉትን ብሄር ብሄረሰብ ሁሉ ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል ነው። ከህዝቡ የሚጠበቀው ዋናው ጉዳይ እርስ በእርስ በመግባባት ሰላምን ማስጠበቅ እንደሆነ ያመለክታሉ። በበርካታ መመዘኛ ኢትዮጵያ ታላቅ ስለመሆኗ ብዙ ማሳያዎችን ማንሳት እንደሚቻል የጠቀሱት ልጅ መስፍን፣ ለአብነት ያህል የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ፣ የሰው ዘር መገኛ፣ እንዲሁም የታላላቅ ቅርሶች ባለቤት መሆኗን ነው የገለጹት። ይህን እሴት ጠብቆ ለመዝለቅም የህዝቧ አብሮነት የግድ እንደሚል ጠቅሰዋል።

«በዚህ በዓል ላይ የእርስ በእርስ ግንኙነት ላይ በደንብ ተጠናክሮ ቢሰራበት ኖሮ የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር የሚሮጡ ግለሰቦች የሚፈጥሩት ችግር እምብዛም አይፈጠርም ብዬ አስባለሁ። ህዝቡንም መሳሪያ ማድረግ አይችሉም ነበር። ህዝብን ከህዝብ ጋር በማጋጨት የራስን ፍላጎት ማግኘት የሚቻለው የህዝብ አብሮነት ሳይኖር ሲቀር ነው» በማለት ይናገራሉ።

እንደ እርሳቸው አባባል፤ የህዝቡን ጥያቄ አቅጣጫ ለማስቀየርና ህዝብን በህዝብ ላይ ለማነሳሳት የሚፈልጉ አካላት እንዳሉ ይታወቃል። ይህ ግን የሚሆነው ህዝብ እርስ በእርሱ መግባባትና አብሮነትን መፍጠር ሳይችል ሲቀር ነው። ይህ በዓል ደግሞ አብሮነትን የሚያጎለብት፣ አንዱ ሌላውን የሚያውቅበት እንደመሆኑ መተሳሰቡም የሚከተል ነውና እጅግ ጠቃሚ ነው።

እነዚህ ጸረ ሰላም ኃይሎች አሁን ላይ እንኳ ሲተኙ አይስተዋሉም። ህዝብ በተፈጠረለት መልካም ሁኔታ ህይወቱን በመምራት ላይ እንኳ እያለ «ቀደም ሲል ስትጨቆን ብትቆይም አሁን ባገኘኸው መብት መሰረት ጊዜው የአንተ ነውና ያንን እንዲህ በለው ያኛውን ደግሞ አጥፋው» በማለት እርስ በእርስ ህዝብ እንዲባላ ሰላምን በማወክ ላይ ይገኛሉ። ይሁንና እንዲህ አይነቱ ገንጣይ አመለካከት የህዝብ አብሮነት እየተጠናከረ ሲመጣ ሊጠፋ ይችላል። ስለዚህ ለሰላሙም ሆነ ለመልካም አስተዳደሩ የህዝቦች አብሮነትና አንድነት ትልቅ ስፍራ ያለው ጉዳይ በመሆኑ ለዚህ አብሮነትና አንድነት ደግሞ የበዓሉ መከበር ቸል ሊባል እንደማይገባው ያስረዳሉ።

«ስለዚህ እሴቶቻችንን ጠብቀን የብሄር ብሄረሰቦች አንድነት የበለጠ የሚጠናከርበትን መንገድ መፈለጉ ለአገራዊ አንድነት ለልማት እና ለሰላም ትልቅ ፋይዳ ያለው በመሆኑ የነበረንን ታላቅነትም የምናሳይበት መድረክ ሊሆን ይችላል። በታሪክ ታላቅ ነበርን ተብሎ ሲነገር የነበረውን ተረት እውን ማድረግ ይቻላል። በዓሉ ህዝብ ከህዝብ ጋር እንዳይጋጭ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረክታል። የመገናኛ ድልድይም ነውና ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብዬ አስባለሁ» በማለት አስተያ የታቸውን አጋርተዋል።

የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ በዓሉ የተነሳበትን ዓላማ አሳክቷል ማለት ይከብዳል። በእርግጥ ሰላም ለአካባቢ፣ ለዜጎች፣ ለአገር፣ ለአህጉር ብሎም ለዓለም ሁሉ መሰረት ነው። ነገር ግን ዋናው መሰረታዊ ችግር ሳይመረመርና ሰንኮፉ ሙሉ ለሙሉ ሳይወጣ ሰላም ሊመጣ አይችልም። አምና እና ካቻምና የተከበረው ከዛ በፊትም የነበረው በዓል ለሰላም መኖር ምን ፋይዳ አመጣ የሚለው ሲፈተሽ እንደ እርሳቸው አመለካከት ችግሩ በዛ እንጂ ምንም የተቀየረ ነገር የለም።

«በተለይ አምና በዓሉ ከተከበረ በኋላ እንዲያውም የብሄር ብሄረሰቦች ግጭት ባሰ እንጂ ለውጥ አላመጣም። የኦሮሞና የሱማሌን ግጭት ብንወስድ አስደንጋጭ ነበር። ሁለተኛው ደግሞ በአማራ እና በትግራይ መካከል ያለው ችግር ሌላው ተጠቃሽ ጉዳይ ነው። በደቡብም ቢሆን እንዲሁ ችግር ተከስቷል። ለምሳሌ አማራን ውጣ በማለት የተፈጠረ ችግር መኖሩ ይታወሳል። ስለሆነም በፖለቲካው ዙሪያ ሰላምና መረጋጋት አይታይም። የበዓሉ መከበር እለቱን ከማድመቅ ባሻገር መሰረታዊ ችግር ፈቷል ወይ ቢባል ገና ውሃው እንኳ አልሞቀም የሚል ምላሽ ነው ያለኝ» ሲሉ ይናገራሉ ።

በዓሉ ብሄር ብሄረሰቦችን የሚያቀራርብ ነው ተብሎ ከታመነ ውጤቱን ይዞ መገኘት ነው የሚያስፈልገው። ግን ፋይዳው ምንድን ነው ሲባል ምንም የሚል ነገር ነው መልስ ሊሆን የሚችለው። ብሄር ብሄረሰቦች በድንበር እንዳይጋጩ፣ ሰው እንዳይሞት፣ የአካል ጉዳት እንዳይከሰት፣ ንብረት እንዳይጠፋ እንዲሁም ልማት እንዳይስተጓጎል አጥጋቢ ሥራ አልተሰራበትም ይላሉ።

ግጭት የተፈጠረው በህዝብና በህዝብ መካከል ሳይሆን አንዳንድ ጸረ ሰላም ኃይሎችና አመራርም በፈጠሩት ራስ ወዳድነት እንደሆነ መንግሥት ሲናገር ነበርና እርስዎ ህዝብና ህዝብ ተጋጭቷል ብለው ይደመድማሉ? ተብሎ ለተነሳላቸው ጥያቄ የሰጡት ምላሽ፤ አመራር ማለት ያው ህዝብ ነው፤ ስለዚህም የክልል አመራርንና ህዝብን ለይቶ ማየት የዋህነት እንደሆነ ነው የተናገሩት።

እንደ አቶ ተሻለ አገላለጽ፤ ችግር ለመፈጠሩ ዋናው ምክንያት የፌዴራሊዝም ስርዓቱ ነው። በቋንቋና በጎሳ የተመሰረተ ፌዴራሊዝም ለኢትዮጵያ አይጠቅምም። ምክንያቱም ስርዓቱ ከዓመት ወደ ዓመት ይሂድ እንጂ ችግር ሲፈታ አይስተዋልም። ግጭት ከተከሰተ በኋላ የሚሰጡ ምክንያቶች ፋይዳ የሌላቸው ናቸው።

«አንድ ነገር ግን አምናለሁ፤ በዓሉ የተወሰኑ ቀናትን ሊያደምቅ ይችላል። ግን ደግሞ ወዲያው ወደ ግጭት ሲገባ ይስተዋላል። ስለዚህ ወደ መፍትሄ ሲመጣ አንደኛ ነገር ግጭቱ ለምን ይፈጠራል በማለት ምክንያቱን ማወቅ ይገባናል። ከዛም ዘላቂና ዴሞክራሲያዊ የሆነ መፍትሄ ያስፈልጋል» ይላሉ።

«አመራር የህዝብ አይደለም ከተባለ በበኩሌ ስርዓቱ ፈርሷል ወደሚለው ይወስደኛል። አመራሩ ለህገ መንግሥቱ የማይገዛና የማይሰራ ነውም ለማለት ያስደፍራል። ምክንያቱም አመራሩ ራሱ ህዝብን ማገልገል ይጠበቅበታል እንጂ ለህዝብ ጠንቅ መሆን የለበትም። ስለዚህ ችግር ሲመጣ አመራሩን ከህዝብ ለይቶ እነሱ ናቸው ችግር የፈጠሩት ማለት እምብዛም የሚያስኬድ ጉዳይ አይደለም። ችግሩ ዞሮ ዞሮ የፌዴራሊዝም ስርዓቱ ቋንቋ ላይ መንጠልጠሉ ያመጣው ነው። ሁሉም በራሱ ክልል አበጅቷል። ጠለቅ ብለን ጉዳዩን ስንመለከተው ህገ መንግሥቱ በራሱ መሻሻል አለበት ወደሚለውም ይወስደናል» በማለት ይናገራሉ። ይሁንና የበዓሉ መከበር በብዙ መልኩ ፋይዳ አለው የሚለውን ይስማማሉ።

አቶ ተሻለ በሌላ በኩል ደግሞ «ብሄር ብሄረሰቦች በመጀመሪያ ደረጃ የሚሰበሰቡት ለምንድን ነውሲሉ ይጠይቃሉ። በሚሰበሰቡበትም ወቅት ገንዘብ ያለአግባብ እንደሚባክን ነው የሚያስረዱት። መቼም ይህ በዓል ሲዘጋጅ የራሱ የሆነ ዓላማ ይዞ ነው የሚሉት አቶ ተሻለ፣ አንዱና ዋናው ህዝቡን ለማቀራረብ እንደሆነ ይናገራሉ። ይህም መቀራረብ ግን ጸንቶ መቆየት ሲገባው ወደየመጡበት በተመለሱበት ቅጽበት ግጭት መከሰቱ አጠያያቂ ነው በማለት ይጠቅሳሉ።

«በየዓመቱ ወጪ ወጥቶ በዙር እየተከበረ ያለው በዓል ግቡና ዓላማው እስከሚገባኝ ድረስ ለብሄር ብሄረሰቦች አንድነትና መቀራረብ እንዲሁም እሴት ለመለዋወጥ እንደሆነ ነው የምረዳው። ይሁንና እየታየ ያለው ነገር በበዓሉ ማግስት ችግር እየተፈጠረ መሆኑን ነው» በማለት ይገልጻሉ። መፍትሄ መሆን የሚችለው ህገ መንግሥትን ማክበርና ማስከበር እንደሆነም ይጠቁማሉ። የህዝብም ጥያቄ በአግባቡ ምላሽ ማግኘት ይኖርበታል ሲሉም ይናገራሉ። በልዩነት አንድነትን እንደ አገር ማስቀጠል ዓላማ ከሆነ የብሄር ብሄረሰቦችን ጥቅም ማስከበር ይበጃል። ለዚህ ደግሞ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ሊሰሩ ይገባል የሚል እምነት አላቸው።

በዓሉን እርሳቸውም እንደሚካፈሉት የሚናገሩት ደግሞ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ትዕግስቱ አወሉ በበኩላቸው፤ በዓሉን በየዓመቱ እንደሚመጣ ፌስቲቫል አድርገው ከመውሰዳቸውም በተጨማሪ የአንዱ ብሄር ባህል ከሌላው ብሄር ባህል ጋር ያለውን ልዩነትና አንድነት ማወቅ የሚቻልበት መድረክ እንደሆነ አድርገውም ይቆጥሩታል። ሌላው ቀርቶ ወደ በዓሉ ቦታ ለመድረስ በሚደረገው ጉዞም የተለያዩ ክልሎችንና ከተሞችንም በማወቅ ደረጃ አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል። ህዝብም ከህዝብ ጋር እንዲተዋወቁ ይረዳል ይላሉ።

ይሁንና ይላሉ አቶ ትዕግስቱ፣ ለሰላም ያለው ፋይዳ የተባለው ሲስተዋል ሱማሌና ኦሮሞ የተጋጩት 11 ጊዜ የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል ተከብሮ ባለበት ጊዜ በመሆኑ ለውጡ እምብዛም ነው ያስኛል። እንዲያው11ኛው በዓል ሐረሪ ክልል በሐረር ከተማ ሲከበር ከቦታው ቅርበት አኳያ በዋናነት በብዛት በበዓሉ ታድመዋል ተብለው የሚታወቁት ሁለቱ ብሄረሰቦች ሆነው ሳለ ነው ግጭቱ የተፈጠረው። ችግሩ ሊመጣ የቻለውም ስርዓቱ ልዩነትን ሲሰብክ የቆየ በመሆኑ ነው። ሲሰበክ የነበረው ስርዓት አንድነት እንዲጠናከር የሚያደርገው እድል አልነበረም በማለት ከአቶ ተሻለ ጋር የሚያስማማቸውን ሐሳብ ያጋራሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት፤ ፌስቲቫሉ በራሱ ብቻ የሚያመጣው ነገር የለም። ነገር ግን መደረግ ያለበት ዓመት ተጠብቆ ፌስቲቫል ማከናወን ብቻ ሳይሆን በመጀመሪያ ደረጃ፣ በሁለተኛ ደረጃና በመሰናዶ እና በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ ሥራዎች መሰራት አለባቸው። ለምሳሌ የተማሪዎች የእርስ በእርስ ግንኙነትን ማጠናከር አንዱ የሌላውን ባህል ለማወቅና ለማክበርም የራሱ ድርሻ ይኖረዋል። ከዚህ ሌላ ደግሞ በስፖርቱ በኩል አገር አቀፍ ውድድር ሲኖር በዓመት አንዴ የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል ላይ ብቻ የሚዘጋጀውን ሲምፖዚየም በዚህ በስፖርቱም ማድረግ ተገቢ ነው።

በተለይ ትንሿ ኢትዮጵያ ተብሎ በቅጽል ስም እስከ መጠራት በደረሰው በእያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲ ላይ ጠንካራ ሥራ መስራት ግድ ይላል። በዚህ ጊዜ አብሮነት ይጠናከራል። ስለዚህ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ መደረግ የለበትም። በየጊዜው ግንዛቤ ማስጨበጥ ይቻላል። በሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ ህገ መንግሥቱን የማስረጽ ሥራ መስራት ውጤቱን ያማረ ያደርገዋል በማለት ይናገራሉ።

ሁሉም የተለያየ ብሄር፣ ኃይማኖትና ማንነት ሊኖረው ይችላል የሚሉት አቶ ትዕግስቱ፣ አንዱ የሌላውን ማደግ እንደ ራሱ አድርጎ መቀበል ይኖርበታል ሲሉ ያመለክታሉ። ለዚህ ደግሞ አብሮነትን ማጠናከር ትልቅ ሚናን እንደሚጫወት ነው የሚገልጹት። የጋራ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር ይህ ደግሞ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ይሆናል ሲሉም ተናግረዋል።

በዓሉ የሚከበረው በዙር እንደመሆኑ በሚከበርበት ከተማ የሚፈጠረው የኢኮኖሚ መነቃቃት ይበል የሚያሰኝ ነው። አዳዲስ መንደር ከመሰራት እስከ አዲስ ስታዲየም መገንባት ድረስ ከመዝለቁም በተጨማሪ መንገዶች ይሰራሉ፤ ሌሎች ልማቶችም ሲከናወኑ ይታያሉና መልካም ነው። እንዲሁም በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ የቱሪዝም መስህቦችም ለተመልካች እይታ ስለሚበቁ የተሻለ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል። ከዚህም በተጨማሪ ክልሎቹ ከፌዴራል መንግሥት ጋር ተባብረው የመስራት ባህልን ያዳብራል። ምክንያቱም የፌዴራል መንግሥቱም በጀት አለ። በመሆኑም ልማቱን በአግባቡ ያንቀሳቅሳል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

አበው «ዝናብ ከሌለ ሁሉ ቤት እንግዳ ከሌለ ሁሉ ሴት» እንደሚሉት እንግዳ ይመጣል ስለሚባል ብቻ መስራት አይሁን እንጂ የበዓሉ መከበር ለአስተናጋጁ ክልል እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ቀላል የሚባል እንዳልሆነ አቶ ትዕግስቱ ይገልፃሉ። ልማቱ በአዘቦቱም ጊዜ በደንብ ሊሰራ ይገባል ይላሉ። በእርግጥ ይላሉ በልማቱ ላይ ያለው ተነሳሽነት ምንም አይወጣለትም። ለእርሳቸው ግን ትልቁ ልማት ብለው የሚያስቡት በአመለካከት ላይ የሚሰራውን እንደሆነም ያስረዳሉ።

በኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የህገ መንግሥት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ዳይሬክተር ሙልዬ ወለላው በበኩላቸው፤ በአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት በሰመራ ከተማ የሚከበረው በዓል ለኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ከፍተኛ የሆነ ድልና ታላቅ በዓላቸው መሆኑን ይናገራሉ። በዓሉ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነትና በአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት አስተናጋጅነት የሚከበር መሆኑንም ይገልጻሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት፤ ይህን በዓል ልዩ የሚያደርገው የአፋር ክልላዊ መንግሥት ሰመራ ከተማ የመጀመሪያውን ዙር የመጨረሻውን በዓል የምታስተናግድ በመሆኗ ነው። ስምንቱ ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች በየተራ ማስተናገዳቸው ይታወሳል። በየዓመቱ በመከበር ላይ ያለው በዓል የእርስ በእርስ ግንኙነትን፣ የባህል ልውውጥን እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ አብሮነትን ከፍታ ላይ እያወጣ ነው።

የኢትዮጵያ ህዝብ ለዘመናት ተገልሎና ተገፍቶ በማንነቱ እንዳይኮራ ሲደረግ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ግን ይህ ጭቆና ቀርቶ ሁሉም በራሱ ቋንቋና ማንነት እንዲጠቀም ህገ መንግሥቱ ደንግጓል። ከዚህም በተጨማሪ በነጻነትም ከአንዱ ስፍራ ወደ ሌላው መዘዋወር እንዲቻል ምቹ ሁኔታ በመፈጠሩ የበዓሉ ዋና ባለቤት የሆነው ህዝብ ደጋግሞ እየገለጸ መሆኑ ታውቃል።

አቶ ሙልዬ እንደሚሉት፤ ቀደም ሲል ፊውዳሎች ይፈጥሩት የነበረው የእርስ በእርስ ትርምስ ኢትዮጵያን ሰላም ያሳጣ ነበር። ወታደራዊ መንግሥት በመባል የሚታወቀውም ደርግ በብልጠት የህዝቡን ድል በመንጠቁ ሰላም በአገሪቱ ሳይሰፍን ቆይቷል። በ1983 .ም ኢህአዴግ አገሪቱን ሲቆጣጠር በመጀመሪያ ያደረገው ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር ነው። ህገ መንግሥቱ እንዲረቀቅና ሁሉም ህዝብ ተወያይቶበት የራሱ እንዲያደርግም ሥራዎች መሰራታቸው እውን ነው። በዚህም ሁሉም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በክልልም ሆነ በፌዴራል መንግሥት እውቅና ያገኙበትና በአንጻራዊ ሰላማቸው ተጠብቆ አገሪቱ ከማሽቆልቆል ወደ ከፍታ መውጣት መጀመሯም በዚህ ጊዜ እውን ሆኗል። በዓለም አቀፍ ደረጃም ቢሆን የነበራትንም ገጽታ እያሻሻለች መምጣቷ ከማንም የተሰወረ አለመሆኑ ይታወቃል። ነገር ግን አልፎ አልፎ የሚነሱ ጥያቄዎችና የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች የሚታዩት ከአፈጻጸም ጉድለት እንደሆነ ደግሞ የሚሸሸግ ጉዳይ አይደለም። ይሁን እንጂ በጥቅሉ ሲታይ ዛሬ አገሪቱ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በማህበራዊ ጉዳዮች ከፍተኛ የሆነ እድገት እያሳየች ያለች ስለመሆኗም አይካድም።

ለዚህ እድገቷ ደግሞ በዋናነት ተጠቃሽ የሚሆነው አገሪቱ እየተከተለች ያለው የፌዴራል ስርዓት መሆኑ ሊዘነጋ የተገባው ጉዳይ አይደለም። ሌላው ቀርቶ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች «ይህ ልክ አይደለም፤ ያኛው ደግሞ ልክ ነው» ብለው መቃወም የቻሉትም ይኸው ስርዓት ባመጣው፣ ህገ መንግሥቱ በሰጣቸው መብት ተጠቅመው ነው። እንዲያም ሆኖ ግን መሰረታዊ የሆነን እውነት መቃወም ተገቢ እንደማይመስላቸው ነው አቶ ሙልዬ የሚናገሩት።

እውነታ ነው ብለው የጠቀሷቸው ጉዳዮችም ለአብነት ያህል ሲዘረዝሯቸው እንዳመለከቱት፤ አስተናጋጅ ክልሎች በልማቱ ተሻሽለዋል። በተለይ በመሰረተ ልማቱ እንደ መብራት፣ ውሃ ሆነ ሌላው መሰረተ ልማት በመዘርጋት ላይ ይገኛል። እውነታውን ለማመን በየአዘጋጁ ክልል የተካሄደውን ልማት ማየት በቂ ነው። ይህ ሁሉ ልማት ሲሰራ ደግሞ መቶ በመቶ ችግር የለም ማለት አያስደፍርም። መንግሥትም ቢሆን ይህን አልካደም። በአገሪቱ አንዳንድ ቦታዎች ሰላም መታጣት የሚስተዋል ሲሆን፣ ግጭት ደግሞ ተፈጥሯዊ ስለመሆኑ መዘንጋት የለበትም። ነገር ግን ግጭቱን ያመጣው የፌዴራሊዝም ስርዓት ነው ብሎ መደምደም አይቻልም። የፌዴራሊዝም ስርዓት ለኢትዮጵያ ማስፈለጉ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው። በስርዓቱ አስፈላጊነት ላይ ስምምነት አለ።

በሱማሌም ሆነ በኦሮሚያ ክልል መካከል የተነሳው ጉዳይ ይታወቃል። ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ሆኑ ሌሎች እንደሚሉት ግን ኢትዮጵያ የምትከተለው ስርዓት ፌዴራሊዝም በመሆኑ የተፈጠረ ችግር አይደለም። የአፈጻጸምና የአመራር ችግር ሊኖር ይችላል። በእርግጥ ለችግሩ መቀሰቅስ የመልካም አስተዳደር ችግር ጥያቄዎች ያለመመለሳቸው ምክንያት ወይም ሌላም ሊሆን ይችላል እንጂ ስርዓቱ በራሱ ችግር የሚፈጥር እንዳልሆነ የሚታወቅ ጉዳይ ነው ይላሉ።

ኢትዮጵያ ኃይል የሚኖራት ተከብራና ሳትደፈር እስከመጨረሻ ታላቅ አገር ሆና እንድትቀጥል ሲደረግና ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በማንነታቸቸው ኮርተው አገራዊ ግንባታቸውን አጠናክረው መቀጠል ሲችሉ ነው የሚሉት አቶ ሙልዬ ይህ ደግሞ ለአገሪቱ ሰላም፣ መግባባት፣ አብሮ መቀጠልን ማምጣት እንደሚችል ነው የሚያስረዱት።

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ አቶ ለጥይበሉ ሞቱማ እንደሚናገሩት፤ ኅዳር 29 ቀን በየዓመቱ የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ሆኖ እንደሚከበር ይታወቃል። በዓሉ የሚከበርበት ዋናው ምክንያት የብሄር ብሄረሰብ መብትን ያስከበረ በመሆኑ፣ ለህዝቦች አንድነትና እኩልነት እንዲሁም ዋስትና የሰጠ ህገ መንግሥት የጸደቀበት ቀን በመሆኑ ነው። ስለዚህ በዚህ ህገ መንግሥት መሰረት ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ማንነታቸው ታውቆ፣ ቋንቋቸውና ባህላቸውን ያለምንም ገደብ የሚያሳድጉበት መብት የተጎናጸፉ በመሆኑ ነው የሚከበረው።

ስርዓቱ ለአገሪቱ ምሰሶ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል። ለዚህም ምክንያቱ ደግሞ ፌዴራሊዝም ለሰላም፣ ለዴሞክራሲና ለልማት አመቺ ሁኔታን የፈጠረ ከመሆኑም ባሻገር ለህዝቦች አንድነት፣ ለማንነታቸው መከበር እና ተቻችለው ለመኖር ወሳኙን ድርሻ የሚወስድ መሆኑ ነው። ይህ ስርዓት ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር በመሆኑ ደግሞ ህዝቦች በጋራ ሆነው አገሪቱ የተያያዘችውን የህዳሴ ጉዞ ለማሳካት እድል ይፈጥርላቸዋል። የዴራሊዝም ስርዓቱ በዚህ አይነት ኢትዮጵያ ወደ በለጸጉ አገራት የምታደርገውን የልማት ጉዞ ለማፋጠን ሚናው ከፍተኛ ነው በማለት አቶ ለጥይበሉ ይናገራሉ።

እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ አንዳንዶች የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ከድግስ ያለፈ ፋይዳ የለውም እንደሚሉት ሳይሆን፣ በየዓመቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ አብሮነቱም ሆነ መተሳሰቡ እየጎለበተ መምጣቱን ነው የሚያሳየው። ከዚህ ቀደም የማይተዋወቁ ብሄር ብሄረሰቦች እርስ በእርስ እንዲተዋወቁ፣ ባህላቸውና ማንነታቸውም እንዲታወቅ ያደረገ ነው። ለሰላማቸውም ሆነ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታው አመቺ ሁኔታ እየፈጠረ ነው የሄደው።

«ስለዚህ እንደ ዋና ቁልፍ ነገር የሚታየው ሶስት ነገር ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት እንዲመጣ አመቺ ሁኔታ ፈጥሯል ማለት ይቻላል። ስለዚህ የፌዴራል ስርዓቱ አሁን ለታየው ችግር ነው ተብሎ መፈረጅ የለበትም። ዋናው ነገር የአፈጻጸም ችግር ነው። ችግሩ ከስርዓቱ ሳይሆን አንዳንድ አመራር ከሚፈጽሙት የአሰራር እክል መሆኑና የህዝብን ጥያቄ ደግሞ ለራሳቸው ርካሽ የፖለቲካ ፍጆታ በሚጠቀሙ አካላት ምክንያት መሆኑ ከዚህ በፊት በጥልቅ ተሃድሶ ተፈትሿል። በዚህ ውስጥ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ በሚፈለገው ደረጃ የሥራ አጥነት ሁኔታን መቀነስ አለመቻልና የተለያዩ ውስጣዊ ችግሮች እዚህም እዚያም የሚታዩት ችግሮች እንዲከሰቱ ካደረጋቸው ውጪ የፌዴራል ስርዓቱ ለዚህ ለሰላም መደፍረስ አስተዋጽኦ አበርክቷል ተብሎ የሚነዛው ነገር ከእውነት የራቀ ነው» ሲሉ ተናግረዋል።

እርሳቸው እንደሚሉት፤ ዋናው ነገር ህገ መንግሥታዊ ስርዓቱን በትክክል መተግበር ላይ የሚታይን ጉድለት ማስተካከል ነው እንጂ ዋናው ምሰሶ ለዚህ አገርና ለህዝቡ አብሮ መኖር ዋስትና የሰጠውን ስርዓት ማውገዙ እምብዛም ተቀባይነት የሚኖረው አይሆንም። ዴሞክራሲ በአንድ ጀምበር ተገንብቶ የሚያበቃ ጉዳይ አለመሆኑም ልብ ሊባል ይገባል። ግጭቶች ደግሞ በየትኛውም ስርዓት ሊፈጠሩ ይችላሉ። መነሻቸው ምንድን ብሎ ማሰብ ግን ወደ መፍትሄ ያደርሳል እንጂ ምኞትን ብቻ መናገሩ ከእውነታ የራቀ በመሆኑ ብዙ የሚያስኬድ አለመሆኑ መታወቅ ይኖርበታል። ስለዚህ ሌላ የተሻለ አማራጭ ያለ ይመስል በእጅ ላይ ያለውን ማጣጣል ተገቢ አይሆንም።

 

አስቴር ኤልያስ

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።