«ተፈናቃዮችን በዘላቂነት የማስፈሩ ሂደት የእነሱን ፍላጎትና ጥቅም ያስጠበቀ ነው» አቶ ምትኩ ካሳ - የብሄራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር Featured

04 Jan 2018

በቅርቡ በኦሮሚያና በሱማሌ ክልሎች አዋሣኝ አካባቢ በተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ጥቂት የማይባሉ ዜጎች ለሞትና ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩትም ግጭቱን ሽሽት ሀብት ንብረት ያፈሩበትን ቀዬ ለቀው ለመሰደድ ተገደዋል፡፡ እነዚህ ዜጎች ታዲያ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የአገሪቱ  አካባቢዎች ባሉ መጠለያዎች ተጠልለው በመንግሥት እንዲሁም በበጎ አድራጊ ድርጅቶችና ግለሰቦችም ጭምር ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛሉ፡፡ በእነዚሁ ተፈናቃዮች አያያዝ፥ ቀጣይ ዕጣ ፈንታቸው፥ በድርቅና  በሌሎች አገራዊ አጀንዳዎች  ዙሪያ ከብሄራዊ አደጋ   ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር ከአቶ ምትኩ ካሳ ጋር ቆይታ አድርገናል፤ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

       አዲስ ዘመን፡- ኮሚሽኑ በበጀት ዓመቱ ከያዘው ዕቅድ አኳያ አሁን ያለበት አፈፃፀም ምን ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት ይቻላል?

      አቶ ምትኩ፡- ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ዓላማ አኳያ ከአደጋ በፊት የመከላከል፥ በአደጋ ወቅትና ከአደጋ በኋላ መልሶ የማገገም ድጋፍ ነው ለዜጎች የሚያደርገው፡፡ በዚህ አግባብ በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ሦስት የሥራ ግንባሮች ትኩረት ሰጥቶ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በዋናነትም በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎች መልሰው የሚያገግሙበት ሁኔታ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ሰፊ ሥራ አከናውኗል፡፡ ባለፈው በልግ አብቃይና አርብቶ አደር አካባቢዎች በተደረገው ግምገማ መሰረት ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ስምንት ነጥብ አምስት ሚሊዮን  ዜጎቻችን  ዕርዳታ መስጠት ተችሏል፡፡

       ሁለተኛው ደግሞ  ባለፈው ክረምት ወቅት በነበረው ከባድ ዝናብ ምክንያት በደረሰው ደራሽ ጎርፍና የወንዞች ሙላት ከቀያቸው ለተፈናቀሉ 100 ሺ ዜጎች ምግብና የምግብ ነክ ያልሆኑ አቅርቦቶችን የማሟላት ሥራም ተከናውኗል፡፡ እነዚህን ዜጎች መልሰው እንዲያገግሙም ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ተደርጎላቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ካለፈው ነሐሴ ወር ጀምሮ በአገሪቱ የኦሮሚያና ሱማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት ከሁለቱም ክልሎች የተፈናቀሉ ወደ 856 ሺ ዜጎች ድጋፍ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የምግብና ምግብ ነክ ያልሆነ አቅርቦት እያደረግን ነው የምንገኘው፡፡ ስለዚህ በጥቅሉ የኮሚሽኑን አፈፃፀም ስናይ በድርቅ፣ በጎርፍና በግጭት ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ለዕለት ፍጆታ የሚሆናቸውን አቅርቦት የማቅረብ ሥራ በስፋት በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ለመረዳት እንችላለን፡፡

       አዲስ ዘመን፡- የኮሚሽኑ አቅም አደጋን አስቀድሞ ከመከላከል አኳያ ምን ደረጃ ደርሷል?

    አቶ ምትኩ፡- ብሄራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ስትራቴጂ ላይ በተቀመጠው መሰረት  በመከላከልና አደጋውን በማቅለል ረገድ ዋና ተዋናይ አስፈፃሚ መስሪያ ቤቶች ናቸው፡፡ ኮሚሽኑ የማስተባበር እና ሀብት  የማፈላለግ ሚና ነው ያለው፡፡ በዚሁ አግባብ መሰረት የሚመለከታቸው ተቋማት ዜጎች በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሠራሽ አደጋዎች እንዳይጎዱ የሚያደርጉ ሥራዎችን በቅንጅትና ተናበው እንዲያከናውኑ የማስተባበር ሥራ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ከዚህ አኳያ ባጋጠሙ አደጋዎች የተገኘውን ተሞክሮ በመቀመርና የሚሰጠውን ድጋፍ  ተደራሽነት በማጎልበት ረገድ አቅሙን እያጎለበተ ነው የሚገኘው፡፡

     ከዚህ አኳያ ዋናው ሥራ የአስፈፃሚ ተቋማት ቢሆንም፤ በተለይም የሚሠሩ የልማት ሥራዎች በዋናነትም ድርቅን ከመከላከል አኳያ ዜጎችን ማዕከል ያደረጉ እንዲሆኑ ኮሚሽኑ የበኩሉን ሚና ይወጣል፡፡ ለአብነት ያህል እንኳ ብንጠቅስ ድርቅ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች የውሃ እቀባ ሥራ አስቀድመው እንዲያከናወኑ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ይመክራል፤ ይሠራል፤ ያስተባብራልም፡፡ በአርብቶ አደር አካባቢዎችም የመኖ ማምረቻዎች በርከት ብለው እንዲገነቡ  የበኩሉን ጥረት ያደርጋል፡፡

      አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት የድርቅ ተጎጂዎች ቁጥር ምን ያህል ደርሷል? ካለፈው አንፃርስ ሲተያይ እንዴት ይገለጻል?

      አቶ ምትኩ፡- በመላው አገሪቱ በተደረገው የዳሰሳ ጥናት ካለፉት ጊዜያት አንፃር ዘንድሮ  የድርቅ ተረጂዎች ቁጥር ይቀንሳል የሚል ትንበያ አለ፡፡ በተለይም ባለው ክረምት ወቅት ከፍተኛውን የህዝብ ቁጥር የሚይዙት የደጋና ወይና ደጋ አካባቢዎች በቂ ዝናብ በመዝነቡና  ምርቱም በስፋት በመመረቱ የዕርዳታን እጅ የሚጠብቁ ሰዎች መጠን ያንሳል የሚል እምነት አለን፡፡ ስለዚህ  የተረጂዎቹ ቁጥር  ከአምስት እስከ ሰባት ሚሊዮን ብቻ ይሆናል ብለን እንጠብቃለን፡፡ ይሁንና በአሁኑ ወቅት ትክክለኛውን ቁጥር በአግባቡ ተደራጅቶ ክልሎችና የፌዴራል መንግሥት ተማምነው ሲያፀድቁት ይፋ የምናደርገው ይሆናል፡፡

       አዲስ ዘመን፡- እነዚህን ተረጂዎች በአገር ውስጥ አቅም ለመደገፍ የሚደረገው ጥረት ምን ይመስላል?

     አቶ ምትኩ፡- እንደሚታወቀው አገራችን ሦስት ተዋናዮች ነው ያሏት፡፡ አንድ መንግሥት ራሱ ሲሆን፣ የዓለም የምግብ ፕሮግራምና ከዚያ ባሻገር ደግሞ ሌሎች የልማት ድርጅቶች በዕርዳታ አቅርቦቱ ተዋናይ ይሆናሉ፡፡ እነዚህ አጋር ድርጅቶች ከዚህ ቀደም ከመንግሥት ጋር የገቡት ስምምነት የሚጠበቅ ነው የሚሆነው፡፡ መንግሥት ሲባል የክልል መንግሥታትና የአገር ውስጥ ባለሀብቱንም ጭምር ሲሆን፣ በአገር ውስጥ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ሀብት መጠቀምም የግድ ይላል፡፡

       አዲስ ዘመን፡-  ከዚህ ቀደም በተለይም በደቡብ ክልል አንዳንድ ቦታዎች በተነሱ ግጭቶች የተፈናቀሉ ዜጎች በምን ሁኔታ ላይ ነው የሚገኙት? 

     አቶ ምትኩ፡- በግጭቱ ወቅት አስቸኳይ ዕርዳታ ከተሰጣቸው በኋላ ግጭት በተነሳባቸው አካባቢዎች የሰላምና ልማት ኮንፍራንስ ተደርጎ ከህዝቡ ጋር መተማመን ላይ በመደረሱ ወደቀያቸው እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡ ወደቀድሞው ሰላምም በመመለሳቸው ነዋሪዎቹ መደበኛ ኑሯቸውን እየኖሩ ነው የሚገኙት፡፡

       አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ በኦሮሚያና ሱማሌ ክልሎች መካከል በተነሳው ግጭት ምክንያት ከመኖሪያ አካባቢያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች እየተደረገ ያለው ድጋፍ ምን ያህል ተደራሽ ነው ተብሎ ይታመናል?

     አቶ ምትኩ፡-  አስቀድሜ ለመግለጽ እንደሞከርኩት በአሁኑ ወቅት እንደ ትልቅ ሥራ ትኩረት ተወስዶ እየተሠራ ያለው ሥራ በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልልና በኦሮሚያ ክልል መካከል አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎችን መደገፍ ላይ ነው፡፡ በዚህ ግጭት ሳቢያ በኦሮሚያ ክልል  615 ሺ እንዲሁም በሱማሌ ክልል 241 ሺ  በድምሩ 856 ሺ ለሚሆኑ ዜጎች የምግብና ምግብ ነክ ያሉ ግብዓቶችን እንዲያገኙ በማድረግ ላይ ነን፡፡

       በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ እነዚህን ተፈናቃዮች መልሶ የማቋቋም ሥራ ከድጋፉ ጎን ለጎን እየተካሄደ ነው የሚገኘው፡፡ በእቅዱ መሰረት በአሁኑ ወቅት የኦሮሚያ ክልል ተወላጆችን  በክልሉ በሚገኙ 12 ከተሞች የማስፈር ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ በዋናነትም በፊንፊኔ ዙሪያ ባሉ ከተሞች እንዲሁም በሃዋሳና ሻሸመኔ መካከል በሚገኘው ቢሻን ጉራቻ በሚባለው አካባቢ መልሶ የማቋቋሙ ሥራ በስፋት እየተከናወነ ነው፡፡ ይህ ሥራ እንግዲህ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሰሞኑን በሰጠው አቅጣጫ መሰረት በሱማሌ ክልልም ተጠናክሮ የሚቀጥል ነው የሚሆነው፡፡

      አዲስ ዘመን፡- ተፈናቃዮቹን በዘላቂነት ወደቀያቸው ለመመለስ እየተደረገ ስላለው ጥረት ቢያብራሩልን?

     አቶ ምትኩ፡-  ከዚህ አኳያም በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው የሚገኙት፡፡ በዋናነትም በዘላቂነት ከማስፈር ባለፈ ለሥራ ፈጠራ ምቹ የሆነ እቅድ በብሄራዊ አደጋ መከላከልና ዘግጁነት ቴክኒክ ኮሚቴ ተዘጋጅቷል፡፡ እቅዱ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊትም የተፈናቃዮቹን በጎ ፈቃድ የሚያሻ በመሆኑ የሥነ ልቦና የማማከር ሥራ በባለሙያዎች እየተሰጠ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም የሰላምና የልማት ኮንፈረንስ የሚካሄድ ሲሆን፣ በዚህም በሚገኘው ግብዓት በተፈናቃዮቹ ፍላጎት  መሰረት በዘላቂነት የማስፈሩ ሥራ የሚሠራ ይሆናል፡፡ 

      አዲስ ዘመን፡- በዚህ ሥራ ላይ የክልሎችን ድጋፍ እንዴት ይገልጹታል? ተናቦና ተቀናጅቶ  ከመሥራት አኳያ ያጋጠመ ችግር የለም?

      አቶ ምትኩ፡-  ይህ ሥራ እንግዲህ የሚሠራው በኮሚሽኑ ብቻ እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡  ጉዳዩ አገራዊ እንደመሆኑ ግጭቶችን አስቀድሞ ለመከላከልና ከተከሰቱም በኋላ ጉዳታቸው አነስተኛ ይሆን ዘንድ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው ብሄራዊ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ቴክኒክ ኮሚቴ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው፡፡ በዚህ ኮሚቴ ውስጥ የተለያዩ ባለድርሻ ተቋማትና ክልሎች የሚሳተፉ በመሆናቸው በእቅዱ አፈፃፀም ላይ የበኩላቸውን ሚና እየተጫወቱ ነው፡፡ በተለይም ግጭቱን በአፋጣኝ ከማስቆም አኳያ መከላከያ እንዲሁም የፌዴራልና የክልል የፀጥታ ኃይሎች ጉልህ አስተዋፅኦ ነበራቸው፡፡ ምላሽ የመሰጠቱና መልሶ የማቋቋሙም ሥራ በክልሎች የነቃ ተሳትፎ ነው እየተከናወነ ያለው፡፡

       በሌላ በኩል ደግሞ የአደጋ ዝግጁነት ቢሮ በሁሉም ክልሎች እስከ ቀበሌ ድረስ በተዋረድ የተቋቋመ በመሆኑ እቅዱም ሆነ የሚሰጡት አቅጣጫዎች በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እንዲከናወኑ ነው የሚደረገው፡፡ በዚህ ረገድ የታየ ክፍተት የለም፡፡ በተለይም የዕርዳታ አቅርቦቱና ስርጭቱ በክልል መስተዳድሮቹ የሚመራ በመሆኑ ተጎጂዎችን በሚገባ ተደራሽ ማድረግ ተችሏል፡፡

      አዲስ ዘመን፡- እስካሁን ባለው ሂደት በወረርሽኝ መልክ በሽታ እንዳይስፋፋ በእናንተ በኩል እየተደረገ ያለው ጥረት ምን ይመስላል?

      አቶ ምትኩ፡- እንደተባለው በሽታዎች ሊከሰቱ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ ስለመሆኑ ከዚህ ቀደምም በድርቅ የተገኘ ተሞክሮ አለ፡፡ በርከት ያሉ ሰዎች በአንድ ካምፕ ሲሰባሰቡ ከአቅርቦትና ከተለያዩ አገልግሎቶች አለመሟላት ጋር ተያይዞ ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና ችግሮች አሉ፡፡ ይህንን ታሳቢ በማድረግ  የብሄራዊ ኮሚቴው አባል  የሆነው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር  ከክልል ጤና ቢሮዎች ጋር በመቀናጀት በመደባቸው የጤና ባለሙያዎች አማካኝነት የክሊኒክ አገልግሎት በየጣቢያዎቹ ለሚገኙ ተረጂዎች እየሰጠ ነው፡፡ ስለዚህ እስከአሁን ድረስ  በወረርሽኝ መልክ የተከሰተ ምንም ዓይነት በሽታ የለም፡፡  ከዚህ በተጨማሪ የስነ ልቦና የማማከር ሥራውም በባለሙያዎች ነው እየተሠራ ያለው፡፡

አዲስ ዘመን፡-  ተፈናቃዮቹን ወደሚፈልጉበት አካባቢ የማስፈሩ ሂደትና በሚሰፍሩበት አካባቢ ደግሞ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር እንዳይከሰት የሚደረገው ጥንቃቄ ምን ያህል ነው?

      አቶ ምትኩ፡- አሁን የተፈለገው አዲስ አበባ ዙሪያ መሆኑ ሳይሆን፤ ለማስፈር ምቹ መሆኑ ላይ ነው፡፡ ከአዲስ አባባ በተጨማሪ ባቱ፣ ሻሸመኔና በሌሎችም ከተሞች ላይ የሚሰፍሩ ነው የሚሆኑት፡፡ በቀጣይ ደግሞ ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመሆን ሥራው በምክክር የሚሠራ ይሆናል፡፡ ዋናው ግን ሥራ ለመፍጠር ምቹነቱን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ የሰዎችን ዝንባሌ መሰረት አድርገን ነው ሥራ የምንፈጥረው፡፡ በተጨማሪም የመሰረተ ልማት ሥራዎች አብረው የሚሟሉ ይሆናሉ፡፡ በዚሁ አግባብ በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ ክልል ወደ ስድስት ኮሚቴዎችን አቋቁመዋል፡፡ መሰረተ ልማት ብቻ ሳይሆን የምግብ አቅርቦት፥ ገቢ አሰባሰብና የመሳሰሉትን ሥራዎች የሚሠሩ ይሆናል፡፡

      አዲስ ዘመን፡-  በቀጣይ ሰላምን አረጋግጦ ተፈናቃዮች ሰላማዊ ህይወታቸውን እንዲቀጥሉ ከማድረግ አኳያ ከማን ምን ይጠበቃል?

      አቶ ምትኩ፡- በዚህ ጉዳይ ዋናው ተዋናይ ህዝብ ነው፡፡ ህብረተሰቡ ደግሞ በተለያዩ አጋጣሚዎች እንደምንረዳው ሰላም ፈላጊ ህዝብ ነው፡፡ በመቻቻል የሚያምን፣ ተቻችሎ የኖረ አሁንም እየኖረ ያለ ህዝብ ነው፡፡ ትልቁ እሴታችን ይሄ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ከህዝብ ጋር ማሳካት እንደሚቻል ሙሉ እምነት ተይዟል፡፡

       በሌላ በኩል ከህዝብ የተደበቀ ምንም ነገር የለም፡፡ ስለዚህ ሰላም የሚያውኩ አካላትን ህዝቡ ጠንቅቆ ያውቃቸዋል፡፡ በተጨማሪም በዚህ መንግሥት በኩል ደግሞ ቁርጠኝነቱ አለ፡፡ ስለዚህ ህዝብና መንግሥት በጋራ በመሆን ተግባራዊ የሚያደርጉት ይሆናል፡፡ እዚህ ላይ ሊታሰብ የሚገባው ጉዳይ ከአገራችን ብዝሃነት አኳያ የአገራችንን ህልውና ለማስቀጠል ለሰላምም፣ ልማትም ለዴሞክራሲም ግዴታ አስፈላጊ ናቸው፡፡ ስለዚህ ለልማትና ዴሞክራሲ መኖር ደግሞ የሰላም መሰረት ነው፡፡ የአገራችንን ልማት ቀጣይነት ለማረጋገጥም ህብረተሰቡ ተረጋግቶ እንዲኖርም ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን የሚሠራ ነው የሚሆነው፡፡

        አዲስ ዘመን፡- እንደስጋት የሚያነሱት በተለይ ተቋሙ ተልዕኮውን ከማስፈፀም አኳያ ተግዳሮት የሆኑበት ጉዳዮች ይኖሩ ይሆን?

      አቶ ምትኩ፡- ከዚህ አንፃር ዋና ተግዳሮት ብለን ያስቀመጥነው የግጭቱ ስፋት ነው፡፡  ከመኢሶ ይነሳና እስከ ሞያሌ ነው የሚደርሰው፡፡ ይህ ማለት ወደባሌ ሲኬድ መዳወላቦ አለ፤ ምሥራቅ ጉጂ አካባቢ እስከ ሞያሌ ይመጣል፡፡ ስለዚህ የቆዳ ስፋቱና ርቀቱ በጣም ፈታኝ ነው የሚሆነው፡፡ ዕርዳታ ሲኬድ በፀጥታ ኃይሉ መጠበቅ ስላለበት መከላከያ እንዲሁም የፌዴራል ፖሊስን ተይዞ ነው የሚኬደው፤ ይህም በራሱ ሥራውን ከባድ ያደርገዋል፡፡

     አዲስ ዘመን፡- በፀጥታ ችግር ምክንያት ዕርዳታውን በማጓጓዝ ሂደት የተስተጓጎለበት አጋጣሚ አለ?

     አቶ ምትኩ፡- አዎ፤ አንዳንድ ቦታዎች ላይ በአንዳንድ ፀረ ሰላም ኃይሎች  መንገድ በመዘጋቱ ምክንያት ዕርዳታው ለተፈናቃዮች በታሰበው ጊዜ እንዳናደርስ እንቅፋት ሆኖብን ነበር፡፡ ይሁንና ከክልሎች ጋር በመነጋገር በሦስትና በአራት ቀናት ውስጥ ችግሩ የሚፈታበት አግባብ ነበር፡፡

      አዲስ ዘመን፡-  ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ !     አቶ ምትኩ፡- እኔም አመሰግናለሁ !

ማህሌት አብዱል

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።