ለመረጃ ነፃነት ዓዋጁ አለመተግበር እንቅፋቱ ማነው?

05 Jan 2018

ከአንድ ሳምንት በፊት የህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም «በመረጃ ነፃነት አዋጅ 590/2000» ዙሪያ ያካሄደውን የዳሰሳ ጥናቱ በአዋጁ አተገባበር ዙሪያ ያሉ ተግዳሮቶችን ምንነት ላይ በአገር ውስጥ ከሚገኙ የሚዲያ ተቋማት ጋር ለግማሽ ቀን የቆየ ውይይት አድርጎ ነበር። በውይይቱ ላይ ከመንግስት እና ከግል የመገናኛ በዙሀን የተወከሉት ተሳታፊዎች በአዋጁ ተግባራዊነት ላይ እያጋጠማቸው የሚገኘውን ተሞክሮ ለማካፈል ሙከራ  አድርገዋል።

መገናኛ አካባቢ በሚገኘው «ቤልቪው ሆቴል» በተደረገው ውይይት ከተነሱት በርከት ያሉ ጉዳዮች ውስጥ ጎልቶ መውጣት የቻለው የመረጃ ነፃነት አዋጁ አተገባበር ላይ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በዳሰሳ ጥናት አማካኝነት በተገኙ ውጤቶች ለማመላከት የተሞከረበት ሀሳብ ነው። ዳሰሳዊ ጥናቱን ያቀረቡት የተቋሙ ሲኒየር ኤክስፐርት አቶ ታደሰ ገዙ ነበሩ። ከዋና ዋና ነጥቦቹ መካከል የቆየና ስር የሰደደ የሚስጥራዊነት ልማድ፣ የፋይል አያያዝና አደረጃጀት ዘመናዊ አለመሆን ፣ የክህሎት እጥረት፣ የህዝብ ግንኙነት የመዋቅር ችግርና ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶቹ የመረጃ ነፃነት አዋጁ ተግባራዊ እንዳይሆን እንቅፋት ከሆኑት መካከል እንደሚገኙበት በጥናቱ ተመላክተዋል። እነዚህን ሀሳቦች በዝርዝር ምን አይነት ትርጉም እንዳላቸው ባለሙያው  ያቀረቡትን ዳሰሳዊ ጥናት መሰረት አድርገን የምንመለከተው ይሆናል።

በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩት የመገናኛ ብዙሀን ያነሷቸው ነጥቦች ከላይ ከቀረበው ዳሰሳዊ ጥናት ጋር ተመሳሳይነት ያለው ይዘት ቢኖራቸውም በራሳቸው የሚቆሙ እና አዳዲስ ምልከታዎችን እና ተግዳሮቶችን የሚያስቀምጡ ነበሩ። እነዚህ የመገናኛ በዙሀን ባለሙያዎች  በአዋጅ ላይ ከፍተኛ የግንዛቤ እጥረት እንዳለ እና ዋንኛውና የመጀመሪያው ችግር እርሱ መሆኑን ለማስቀመጥ ሞክረዋል። በተለይ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊዎች ከበላይ ማኔጅመንቱ በሚደርስባቸው ጫናም የተጋነኑ እና ትክክል ያልሆኑ መረጃዎችን ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሀን በተለይም ለመንግስት መገናኛ በዙሀን መስጠታቸው ተቀባይነት እና ተአማኒነታቸውን ጥርጣሬ ውስጥ እየከተተባቸው እንደሆነ አበክረው ገልፀዋል። ይህ የመረጃ ነፃነት አዋጁን የሚፃረር መሆኑንም ነው ለመግለፅ ። ከዚህም ሌላ የመገናኛ ብዙሀንን እኩል ያለመመልከት እና ለአንደኛው ወገን አድልቶ መረጃ የመስጠት ሁኔታም በስፋት እንደሚስተዋል አስረድተዋል።

የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በህገ መንግሥታችን አንቀፅ 55(15) መሠረት፣ በአዋጅ ቁጥር 211/1992 የተቋቋመ እና በተጨማሪም የአዋጅ 590/2000 ክፍል ሦስት (የመረጃ ነፃነት ሕግን) የማስተግበር ሥልጣን የተሰጠው ህገ መንግስታዊ ተቋም ነው። ከላይ ያነሳነውን የውይይት አጀንዳም ከመገናኛ ብዙሀን እና ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር የውይይት መድረኮችን በመፍጠር አዋጁ ተግባራዊ እንዲሆን በመስራት ላይ መሆኑንም እየገለፀ ይገኛል። መገናኛ ብዙሀኑ ብሎም ሌሎች በጉዳዩ ላይ በቅርበት የሚመለከታቸው አካላት ተቀራርበው በባለቤትነት መንፈስ መስራት መቻላቸው አዋጁ እየገጠመው ያለውን የተፈፃሚነት ችግር ለማስወገድ እንደሚረዳ ነው ዳሰሳዊ ጥናቱን በባለሙያዎቹ አማካኝነት ያሰራው የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የሚገልፀው። በተለይም መገናኛ በዙሀኑ የመረጃ ነፃነት አዋጁን መርሆች ለህብረተሰቡ ተደራሽ በማድረጉ እና ግንዛቤ በማስጨበጡ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸውም ተገልጿል።

የተቋሙ ሲኒየር ኤክስፐርት አቶ ታደሰ ገዙ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ስልጣን እና ተግባርን አስመልክቶ ሲናገሩ፤ በአዋጅ ቁጥር 211/1992 መሠረት በተለያዩ ጥፋቶች ምክንያት አስተዳደራዊ በደሎች እንዳይፈፀሙ የአስፈፃሚውን አካል የመቆጣጠር እና መልካም የመንግሥት አስተዳደር እንዲሰፍን የመስራት፤ በአዋጅ 590/2000 ክፍል ሦስት መሠረት የመረጃ ነፃነት ሕግን የማስተግበር ሥራ የመስራት ብሎም ሦስቱም የመንግሥት አካላት የመረጃ ነፃነት ሕግን እንዲተገብሩና እንዲያከብሩ ለማድረግ እንደሚሰራ ይገልፃሉ። በዚህም መሰረት የመረጃ ነፃነት መብትን የሚደነግገውን አዋጅ በህብረተሰቡ እና በተለያዩ ተቋማቶች ውስጥ በማስተዋወቅ ክትትል በማድረግ በትክክለኛው መንገድ ተግባራዊ እንዲሆን የተለያዩ ጥረቶች እየተደረገ መሆኑንም ያነሳሉ። ሆኖም ግን በሂደቱ ላይ በርከት ያሉ ፈተናዎች እያጋጠሙ መሆኑን ነው የሚናገሩት።

«አዋጁ የመረጃ ነፃነት ህግን ከተቀበሉ አለም አቀፍ ተቋማትና አገራት ምርጥ ተሞክሮ የወሰደ ነው» በማለት የሚያስረዱት አቶ ታደሰ፤ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአንቀፅ 37 የአዋጁ ማስፈፀሚያ ደንቦችን ማውጣት፣ የአዋጁን ማስፈፀሚያ ደንቦች አፈፃፀም የመከታተልና ተገቢ እገዛዎችን የማድረግ፣ እንደ መንግስት ተቋም አዋጁን ከማስተግበር በተጨማሪ  የመረጃ ነፃነት አዋጅን ተግባራዊነት የሚቆጣጠራቸውን ተቋማት በቅርበት የመከታተል፣ ሌሎች ተቋማት ለምክር ቤቱ ሪፖርት ሲያቀርቡ የመረጃ ነፃነት ሪፖርት ማካተታቸውን መቆጣጠር እንዲችል ስልጣን እና ሀላፊነት ተሰጥቶታል በማለት ይናገራሉ።

በተመሳሳይ ፍርድ ቤቶች እንደ ማንኛውም የመንግስት ተቋም አዋጁን ተግባራዊ ማድረግ፣ ከሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ቀጥሎ በመረጃ ጉዳዮች ላይ የሚቀርቡላቸው አቤቱታዎችን እንዲሁም ይግባኞችን መርምረው ፈጣን ውሳኔ የመስጠት ሀላፊነት አላቸው። እንደ ባለሙያው ገለፃ ይህ ተግባር እና ሀላፊነት  በአዋጁ ላይ በአንቀፅ አንቀፅ 34 ላይ ሰፍሮ ይገኛል። የሚዲያ አካላት ሚና በተመለከተው በዚህ አዋጅ ላይ በዝርዝር የሰፈሩ ድንጋጌዎች አሉ። በዚህም በአብዛኞቹ አገሮች ሚዲያ ሀሳቦችን በማመንጨትም ሆነ በማሰራጨት የጎላ ድርሻ ስላለው ሰብዓዊ መብትን በማሳወቅና በማጎልበት መጠቀም አስፈላጊ ነው። ለዚህም ተቋማት ከሚዲያ ጋር እንዴት እንደሚሰሩ ስትራቴጂዎችን መንደፍና የሚሰሩባቸውን አርዕስተ ጉዳዮች መለየት አስፈላጊ ነው። በመሆኑም በባለድርሻ አካላት መካከል ውይይቶች እንዲካሄዱ ማድረግ፣ የመረጃ ነፃነት ሕጉ ተግባራዊነት ለልማት፣ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መጎልበት፣ ሙስናን ለመከላከል ብሎም ለዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ለማዋል እንዲጠቀሙበት እድሉን የሰጣል። በተለይም አዋጁ ያለውን ጠቀሜታ ግንዛቤ ማስጨበጥ፤ መልካም ተሞክሮዎች እንዲስፋፉ የሌሎች ሀገሮችንም ሆነ በሀገራችን ያሉትን ማበረታታትና ማስፋፋት ላይ ሊሰሩ እንደሚገባ ያመላክታል።

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው አዋጁ ለሁሉም ባለድርሻ አካላት በዝርዝር በመረጃ ነፃነት ዙሪያ ተግባራዊ ስራዎችን እንዲያከናውኑ እድል መክፈት ቢችልም እንደ አቶ ታደሰ ገለፃ፤ ህጉ ወደ መሬት እንዲወርድ ለማድረግ ከፍተኛ የቅንጅት እና ትስስር ጉድለት ይታያል። በዋናነት ይህን ዳሰሳዊ ጥናት ለማድረግ የተፈለገበት ምክንያትም በአዋጁ አተገባበር ላይ ያሉትን ክፍተቶችና ተግዳሮቶች ለይቶ መፍትሄዎቻቸውን  ለማስቀመጥ ነው።

ተግዳሮቶች በርካታ እና የየራሳቸው ባህሪ ያላቸው መሆኑንም የዳሰሳ ጥናቱን ያቀረቡት ባለሙያ ይናገራሉ። ከላይ በመግቢያችን ላይ እንዳስቀመጥነው እነዚህ ማነቆዎቹ በጥንቃቄ ሊታዩ የሚገቡ እንደሆነ የሚያመላክቱ ጉዳዮችን መገንዘብ እንችላለን። አቶ ታደሰ በጥናቱ ላይ በቀዳሚነት የሰፈረው ችግር፤ የመረጃ ነፃነቱ አዋጅ ተግባራዊ እንዳይሆን ምክንያት ከሆኑት ጉዳዮች ተርታ የሚሰለፈው «የቆየና ሥር የሰደደ የምሥጢራዊነት ልማድ» መሆኑን ያነሳሉ። ይህ ማህበረሰባዊ እና ተቋማዊ ልማድ ማንኛውም ሰው መረጃ የማግኘት እና ለፈለገው አላማ ለማዋል የሚያደርገውን ጥረት የሚገድብ ነው። ስለዚህ ይህን ልማድ በቀዳሚነት መቀየርና ሁሉም ሰው ከፈለገው ተቋም እና ህጋዊ አካል ተገቢ የሆነ መረጃን እንዲያገኝ ማመቻቸት አስፈላጊ ይሆናል።

አንድን መረጃ በፍጥነትና በተፈለገው መጠን ለማግኘት እድሉ ሊመቻች እንደሚገባ በአዋጁ ላይ ሰፍሯል። ሆኖም ይህ ህግ ከወጣበት ጊዜ አንስቶ በተቀላጠፈ ሁኔታ ሲተገበር አይስተዋልም። ለዚህ ችግር እንደ ሁለተኛ ተግዳሮት «የፋይል አያያዝና አደረጃጀት ዘመናዊ አለመሆን» ነው በማለት የዳሰሳ ጥናት አቅራቢው ይናገራሉ። ደካማ የመረጃ አያያዝ ስርአቱ መሻሻል ካልቻለ በፍጥነት እና በሚፈለገው መጠን መረጃውን ለጠየቀው ሰው ለመስጠት እንደሚያዳግትም ያስረዳሉ። ይህን ችግር ለማስወገድ ሁሉም ተቋማት በቅንጅት መስራታቸው አስፈላጊ መሆኑንም አበክረው ይገልፃሉ።

የመረጃ ነፃነት አዋጁ «ማንኛውም ሰው» መረጃ ከፈለገበት ተቋም የማግኘት መብቱን ይደነግጋል። ሆኖም ይህ ህግ አንዳንድ ውስን ክልከላዎችን ያስቀምጣል። ማለትም የተፈለገ መረጃ በአገር እና በዜጎች ደህንነት ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ተመዝኖ አሉታዊ ጎኑ ከጎላ ክልከላ እንዲደረግበት ይፈቅዳል። ነገር ግን ይህችን ውስን ድንጋጌ መነሻ በማድረግ ጉዳት የማያስከትሉ መረጃዎችን ጭምር የመከልከል አንድምታ ይታያል። ጥናት አቅራቢው ይህ ጉዳይ በሁለት መልክ ይከሰታል ይላሉ «መረጃ ሰጪውም መረጃ ተቀባዩም  የተሳሳተ ግንዛቤ  በመያዛቸው እና የክህሎት እጥረት በተለይ በመረጃ ሰጪ በኩል» በመኖሩ። ይህም የመረጃ ነፃነቱ ከወጣ ጀምሮ ተግባራዊነቱን ከሚፈታተኑት ተግዳሮቶች ውስጥ እንደሚመደብ መገንዘብ አስፈላጊ ይሆናል።

ከላይ ለማንሳት እንደሞከርነው በውይይቱ ላይ የተነሱ በርካታ ተግዳሮቶች ለመረጃ ነፃነት አዋጁ በተገቢው መንገድ አለመተግበር በወሳኝ ነጥብ የተዘረዘሩ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም  «የሕግ ማዕቀፎች አለመሟላት»    ህጉ አዝጋሚ ለውጥ እንዲኖረው በር መክፈቱን ዳሰሳዊ ጥናቱ ያመለክታል። «በመንግሥት አካላት ዘንድ የቁርጠኝነት ችግር» መኖሩን ጠቁሞም እነዚህ አካላት ህግ ከማውጣት በዘለለ የሚያጋጥሙ ቁልፍ ችግሮችን ለይቶ መፍትሄ በመስጠት ተግባራዊ እንዲሆን አለመስራታቸውን ያሳስባል። የመንግስት ተቋማት በአዋጁ አንቀጽ 36/3 መሠረት ተጠሪ ለሆኑበት ምክር ቤት ሪፖርት አለማቅረባቸው ሌላኛው የችግሩ መንስኤም መሆኑን ለማመላከት ይሞክራል። ምክር ቤቶችም ተገቢውን ክትትል አለማድረጋቸው ፣ በጀትና የሰው ኃይል እጥረት መኖሩ በራሱ ቀላል ግምት ሊሰጠው የማይገባ መሆኑን ያነሳል። የችግሩ መነሻ ለሆኑ ተግዳሮቶች እንደየ ባህሪያቸው መፍትሄ ማፈላለጉና ቅንጅታዊ አሰራር መፍጠሩ እንደመፍትሄ ሊወሰድ የሚገባው ጉዳይ መሆኑን  በማስቀመጥ ያጠቃልላል።

ዳግም ከበደ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።