የብሔር ብሄረሰቦች የማንነት ጥያቄ መመለሱ አንድነትን አይጎዳም

10 Jan 2018

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለ17 ቀናት ያካሄደው ስብሰባ ማጠቃለያ ላይ በአወጣው መግለጫ ዙርያ፣ በአጠቃላይ የስብሰባው ሂደት፣በተወሰኑ ውሳኔዎች ዙርያ የአራቱ ብሄራዊ ድርጅቶች አመራሮች (የደኢህዴንና ኢህአዴግ ሊቀመንበር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣የብአዴን ሊቀመንበርና የኢህአዴግ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን፣የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል እና የኦህዴድ ሊቀመንበር አቶ ለማ መገርሳ) ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ከዚህ ማብራሪያ ስለወጣቶች፣ስለ መልካም አስተዳደርና ስለ ብሄራዊ ማንነትንና አገራዊነትን በሚመለከት ዙርያ የተሰጡትን ቀጣይ ማብራሪያዎች ይዘን ቀርበናል።
ወጣቶች
አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ስለወጣቶች በሰጡት ማብራሪያ አገራችን የወጣቶች አገር ናት፡፡ ወደድንም ጠላንም አገራችን ሰባ በመቶ የሚሆነው ከሰላሳ ዓመት እድሜ በታች ነው። ከዚህ ውስጥ ህጻናትን እንኳን ብንቀንስ አርባ በመቶ የማይተናነስ ሥራ መስራት የሚችል በስራ ዕድሜ ላይ ያለ ወጣት አለ፡፡ አርባ በመቶ የሆኑ ሴትና ወንድ ወጣቶች በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የበኩላቸውን ድርሻ ካላበረከቱ በስተቀር ይሄ አገር የሚፈለገውን ፈጣን ልማትና ዕድገት ለማስቀጠል አይችልም፡፡ ስለዚህ ለወጣቶቹ ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱ ዕድገትም ሲባል የወጣቶች ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ እንደሆነ በተደጋጋሚ የተወያይንበት ጉዳይ ነው፡፡ አሁን ጉዳዩ ወጣቶችን ራሳቸውን መስማት ፣ ልብ ትርታቸውን ማወቅ ፣ ማዳመጥ ያስፈልጋል፡፡ እነርሱ በጣም ብዙ ነገር በውስጣቸው አለ፡፡ ብዙ ፈጠራ በውስጣቸው አለ፤ ይሄን የፈጠራ ችሎታቸውን ዕውቀታቸውን ትምህርታቸውን ክህሎታቸውን ተጠቅመን ወጣቶች ለአገራችን ዕድገት የሚያበ ረክቱትን ከፍተኛ ሚና የሚመጥን አመራር ልንሰጥ ይገባል፡፡ እዚህ ላይ ያለን የአመራር ጉድለት በጣም ከፍተኛ እንደሆነ አይተናል፡፡ ስለዚህ ከወጣቶቹ ከራሳቸው ጋር ሆነን ልንቀርጽ የሞከርናቸውን ፓኬጆችን ጭምር አሁንም ቢሆን በሚገባ አሳትፈናቸው መስራት የሚገባን ይሆናል፡፡ እንግዲህ ወጣቶች የነገ ተስፋዎች ብቻ አይደሉም። የአሁኑ አገር ገንቢዎችም ናቸው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያችን ወደ ፊት ልትገሰግስ ከሆነ ከወጣቶች ውጭ ሊሆን የሚችል ነገር ይኖራል ተብሎ በጭራሽ ሊታሰብ አይችልም፡፡ እናም መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ አፅንኦት ሰጥቶ ሥራ እንዲሰራ በዚህ ላይ የተደራጁ ግብረ ኃይሎችም ጠንክረው መፈፀም እንደሚገባቸው እስካሁን ድረስ ያለውን ውጣ ውረድ ልናቃልል የምንችልበትን አመራር ልንሰጥ እንደሚገባን መተማመን የተደረሰበት ነው፡፡ ስለዚህ የወጣቶች ጉዳይ አሁንም ለእኛ የሞት የሽረት ጉዳይ ተደርጎ መወሰድ አለበት የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰናል ማለት ነው፡፡
አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው ከወጣት አኳያ ምናልባት አሁንም ቢሆን በግምገማችን በስፋት ታይቷል፡፡ አንዱ በጥንቃቄ መታየት ያለበት እዚያም እዚህም ግጭት ሲነሳ፣ የተለያዩ ጉዳዮች ሲነሱ የእነዚህ ወጣቶች እንደሆኑ አድርጎ የመሳልና የመገንዘብ ሁኔታ ብዙ ቦታ ያጋጥማል፡፡ ግን ወጣቶች የመፍትሄ አካል የሆኑ፣ ለውጡን ወደ ፊት ሊያራምድ የሚችል ትልቅ አቅምና ትልቅ ሀብት ናቸው፡፡ ወጣቶች ዛሬን ለመጠቀም፤ ዛሬ ያልተሟላና የጎደለው ነገር ለነገም ስለሚጎዳቸው በዚህ ደረጃ ለውጥን ከምንም በላይ ይፈልጋሉ፡፡ ተስፋ የሰነቁ ናቸው፡፡ ወጣቶች ፈጣን ምላሽ ይጠይቃሉ፡፡ ዘመኑ በፍጥነት እንድንራመድና እንድንጓዝ ያደርጋል፡፡ በዚህ አይን የወጣቶችን ሁኔታ በዝርዝር ማወቅና ፍላጎታቸውን ማዳመጥ ያስፈልጋል፡፡ ብዙ መፍትሄ ከእነርሱ ይንቆረቆራል፡፡ እንዲሁ ሰብስቦ በርቀት የማየትና የመፈረጅ አይደለም መፍትሄዎች ከእነርሱ አሉ፡፡ መፍትሄውን ራሳቸው በተግባር ሊመሩትና ሊፈጽሙት ይችላሉ፡፡ አቅሙ አለ።ተስፋው አለ። ትጥቁ አለ። ይህንን ሀብት በአግባቡ መጠቀምና በአግባቡ ማራመድ ያስፈልጋል፡፡ ማዳመጥ ይገባናል፤ መገንባት ይገባናል፤
የወጣት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ በኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ውስጥ እንዴት አድርገን ነው ይሄንን ወጣት የምናንቀሳቅሰው? ብሎ መስራት ተገቢ ነው።
ሌላው የወጣቶች ተሳትፎ በልዩ ልዩ መስክ በደንብ መታየት አለበት፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የወጣት ስብእና ግንባታ፣ በምንገነባው ስርአት ውስጥ የኢትዮጵያ ህዝቦችን ታሪክ በተሟላ ሁኔታ የማስገንዘብ፣ ያለፈ ታሪካችን ለአሁኑ እንደ ኩራት ምንጭ አድርገን እንደምንራመድበት፤ ካለፈው ታሪካችን ደግሞ ሊታረሙ የሚገቡ እንዲሁም አሁንም ሊደገሙና ልንሰራቸው የሚገቡ አሉ፡፡ እዚህ አካባቢ የምንሰራውን ስራ ማጠናከር ማስፋትና መማማር ይጠይቃል፡፡ በዚህ ላይ ተመስርተን ዴሞክራሲን ለመገንባት፣ መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና የህዳሴውን ፕሮጀክት ወደ ፊት ለማራመድ ትልቅ ሀብት ወጣት ስለሆነ፤ ይህንን ለማጠናከር ምን እናድርግ ሲባል፤ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ከወሰነው አንዱ ቀደም ሲል በብሄራዊ ደረጃ የወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚያስተ ባብር ብሄራዊ ኮሚቴ ተደራጅቷል፡፡ እስከ አሁን ያለው አካሄድ አዝጋሚ ስለሆነ አሁን ባለው ፍላጎትና አገራዊ ሁኔታ የሚመጥን የብሄራዊ ኮሚቴ እንቅስቃሴ በፌዴራልና በክልል ተደራጅቶ ፖለቲካዊ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲመራና ወጣቶችም ከዚህ አኳያ የሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ የሚሰጠው ቁመና መላበስ አለበት ብለን ነው የያዝነው፡፡ አንድ የትኩረት መስክ ነው ለማለት ነው፡፡
መልካም አስተዳደር
አቶ ኃይለማርያም ደሳላኝ ስለ መልካም አስተዳደር ከመልካም አስተዳደር አኳያ ችግሩ እንዲፈታ ካስፈለገ የፖለቲካ አመራሩ አሁን በስራ አስፈጻሚ ደረጃ እንደታየው ግልጽነት ሁሉ በመላው ካድሬ እና አባሎቻችን እስከታች ድረስ መውረድ አለበት። እስከታች ድረስ በአንድ መንፈስ በአንድ ልብ ሆነን ከታገልን የመልካም አስተዳደር ችግር እየቀረፍን ልንሄድ እንችላለን። ለዚህ ደግሞ ወሳኙ አመራሩ በዚህ ደረጃ ከተስተካከለ ህብረተሰቡ ደግሞ የማይተካ ሚናውን እንዲጫወት ማድረግ የሚቻል ከሆነ ብቻ ነው። አለበለዚያ የመልካም አስተዳደር ችግር የመፈታቱ ጉዳይ ጊዜ መውሰዱ እና ችግሮች እየተባባሱ መሄዳቸው አይቀርም።
አንድ ተገልጋይ አገልግሎት ለመውሰድ በሄደበት ሁኔታ እኛ አገልግሎት ለመስጠት ያስቀመጥናቸው መስፈርቶች (ስታንዳርዶችን) አውቆ በተቀመጠው መሰረት አገልግሎት አልሰጠህም ሲባል በሙሉ ልቡ የማይታገል እና እንግልቱን ተቀብሎ የሚመለስ ከሆነ ችግሩን የማስተካከሉ ሂደት ዘገምተኛ መሆኑ አይቀርም። ስለዚህ በእኔ እምነት መንግስት ወይም ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ እራሱን ለማስተካከል የሚያደርጋቸው ጥረቶች እንዳሉ ከህዝቡ ደግሞ መልካም አስተዳደር እንዲጎለብት ለማድረግ የበኩሉን ሚና የሚጫወ ትበትን ሚና ያስፈልጋል። የሁለቱ ጥረት የመልካም አስተዳደር ስራችን ደረጃ በደረጃ እየተፈታ ይሄዳል የሚል ሙሉ እምነት አለ።
አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው በገጠርም በከተማም የመልካም አስተዳደር ችግሮች ምን ምን ናቸው? አሁንም ቢሆን በተቋም ፣ በስራ ዘርፍና መስክ ደረጃ ምንድናቸው? የሚሉትን የመለየት በእነዚህ ላይ ተመስርቶ ለውጡን ለማምጣት ያስችላሉ የተባሉት ለውጦችን (ሪፎርሞችን) አሟልቶ ተግባራዊ የማድረግ ስራ መስራት አለብን ብለን የመንግስት መዋቅራችን፣ ድርጅታችን ችግሩን በዝርዝር አይቶ በጠንካራ ቁመናው ወደ ንቅናቄው ሲገባ፣አንዱ እርምጃ የመንግስት መዋቅር ምላሽ ሰጭ ማድረግ፣ ተጠያቂ እንዲሆን፣ ለተገልጋዩ ህብረተሰብ በመርህ የተቀመጠውን በተግባር የሚተረጉም እንዲሆን የመንግስት መዋቅርን ማብቃት፣ ተጠያቂ ማድረግ፣ ለምናስበው ለውጥ ቁልፍ መሳሪያ እንዲሆን ማድረግ አለብን፡፡
ሌላው በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያለው የመንግስት ሰራተኛ በዚያ ዙሪያ ያሉበትን ችግሮች የመፍታት የአገልጋይነት ስሜቱን ተላብሶ የሚፈለገውን ተልእኮ እንዲወጣ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የእነዚህ ሁሉ ማጠንጠኛዎች መሪዎች ናቸው፡፡ መንግስት መዋቅርም አብዛኛውን ተቋምንም የሚመራው፣ ክልልም የሚመራው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ነው፡፡ እኔ በአግባቡ ስላልመራሁት በእነዚህ ችግሮች ውስጥ ተነክሬ ስለቆየሁ የመንግስት መዋቅርን ውጤታማ ማድረግ በሁሉም መስክ የሚፈለገውን እርካታ እንዳይረጋገጥ ስላደረግኩ መንግስት መዋቅርን ለዚህ ማዘጋጀት ያስፈልገዋል፡፡ አቅም ግንባታ ፣ የአስተሳሰብ ግልጸነት ፣ የክህሎት ትጥቅ ያስፈልጋል፤ የግንዛቤ እድገት ይጠይቃል፡፡ ይህን መሰረት ያደረገው አንዱ ከተዘረዘሩትና አሁን የስራ ክፍፍል ተደርጎ ስምሪት ከሚደረግባቸው ጉዳዮች አንዱ ይህን ማእከል ያደረገ ስራ መስራትና ውጤታማና ስኬታማ ስራ ማረጋገጥ አለብን ብለን ነው ያስቀመጥነው፡፡ ይህን አጠናክሮ መቀጠል ነው፡፡
ብሄራዊ ማንነትንና አገራዊነት
አቶ ደመቀ መኮንን ብሄራዊ ማንነትንና አገራዊነትን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ ይህንን ከመገንባት አንጻር ክፍተት እንደነበረ ተለይቷል። ከዚህ አንጻር ባለፉት 25 ዓመታት የብሄር ማንነት ምን ያህል ለአገራዊ አንድነት ክፍተት እንዲፈጠር ሆኗል ብለው የሚያነሱ ወገኖች አሉና ይህ እውነት ነው ወደሚል ይወስደናል? ከዚህ ጎን ለጎን ከአሁን በኋላስ ለብሄር መብት ትኩረት አይሰጥም ወደሚል ነው የዚህ አገላለጽ ቅኝት የሚሆነው? ወይስ ምን ማለት ነው? ፡፡ ብሔራዊ ማንነትና አገራዊ ማንነትን አንድም ሁለትም ሆነው ከህገ መንግስታዊና ፌዴራላዊ ስርዓታችን ጋር አስተሳስሮ መመልከት በጣም ተገቢ ነው። በአገራችን ሁኔታ ከዓመታት በፊት የነበረው ሁኔታና ቅራኔ ምን ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበር፣ ከዛ ሁኔታ ለመውጣት የተሠራው ሥራ እና የተገኘው ህገ መንግስታዊ ድል፤ የተረጋገጠው የብሔር እኩልነት እና በዛ ላይ ተመስርተን የገነባነው ብዝሃነት የአንድነት መሰረት እና ትልቅ ውጤት ነው።
ኢትዮጵያዊነት በጣም ጥልቅ ሃሳብ ነው። በእኛ አገር ሁኔታ ኢትዮጵያዊነት ጥልቅ ሃሳብነቱን የበለጠ ለማጠናከር በብዝሃነት ላይ የተመሰረተው አንድነት ለዚህ ጥልቅ ሀሳብ ትልቅ መሰረት ነው። ብዝሃነትን እንደ ጌጥ አድርጎ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች በአካባቢያቸው ጉዳይ በሚመለከታቸው በእኩልነት ላይ ተመስርተው የሚጫወቱት ሚና በአገራዊ ጉዳይ ላይ ደግሞ በፌዴራል ስርዓት የሚጫወቱት ሚና በግልጽ ተቀምጧል።
ብዝሃነት በዚህ አገር ውስጥ ይህን ህገ መንግስታዊ ዋስትና አግኝቶ በተግባር ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በተግባር የተጓዝንበት ጉዞ ነው። የተዘረጋው መሰረት ለአንድነታችን እና ለኢትዮጵያ ዊነት ትልቅ መሰረት ነው ብሎ መነሳት ተገቢ ነው። የበለጠ ጥልቀት ይሰጠዋል። በዚህ ላይ ተመስርተን በብዝሃነት እኩልነት ከተረጋገጠ፤ የብሔር ጥያቄ ህገመንግስታዊ ምላሽ ካገኘ። ሁሉም አካባቢውን የሚመራበት የሚያስተዳድርበት፤ በአገራዊ ጉዳይ ላይ የሚጫወትበት፤ ሊጠቀም፣ በእድገቱ ውስጥ ሊተውን የሚገባውን ሂደት በተመቻቸበት ሁኔታ በዚህ መሰረት ላይ ቆመን ጠንካራ አገራዊነት መሰረቱ ተጥሏል። ይህ የበለጠ መሥራትና ማጠናከር ይኖርብናል።
የብሔር ማንነት ከዚህ አኳያ በመመለሱ ይህኛውን ጎድቷል ብለን ልንወስድ የምንችልበት በምንም መልኩ አይሆንም። በኢትዮጵያ ሁኔታ እንዲያውም ጥልቀት ያስገኘዋል። በዛ ላይ የተመሰረተው የአገራዊ አንድነት ግንባታ ግን ከመጣንበት ጉዞ ከደረስንበት ደረጃ አኳያ የበለጠ ሊጠናከርና ሊፋጠን የሚገባው ነው።
አንደኛ ቀደም ብለን ያልነው ከታሪክና አስተምህሮ አኳያ አንዳንድ ጊዜ በየአካባቢው በተመለሰው ህገመንግስታዊ ስርዓት በአካባቢ ላይ ያለንን እኩልነት መሰረት አድርጎ ወደ አገራዊ አንድነት ሊያራምዱን የሚችሉ እድሎችን ከመጠቀም ይልቅ የተለያዩ መንጠላጠያዎቹን በማንሳት ሁልጊዜ ያንን ታሪክ በመድገምና በመርገም፥ ሁለት አስርት ዓመታትን ከዛ በላይ እየተጓዝን የአዲሱ ፕሮጀክትና የአዲስ ኢትዮጵያን ግንባታ ማፋጠን ማጠናከር እየቻልን፤ እዛ አካባቢ ላይ የተሳሳቱ ዝንባሌዎችና አካሄዶች አሉ።
በሁለተኛ ደረጃ አሁንም በዚሁ ፌዴራል ስርዓታችን እና ህገመንግስቱ ብሔራዊ መግባባት ፋይዳው እና ምን መስራት እንዳለብን በዝርዝር ፖሊሲያችን ላይ ተቀምጧል፤ የብሔራዊ መግባባት ጉዳይ። ብሔራዊ መግባባት ከዳር እስከ ዳር ሁሉም በነቂስ እንኳ ሊላበሰው እና ሊይዘው ባይችል አብዛኛው በአስተሳሰብ ደረጃ ሊይዘው የሚችለው ምንድን ነው የሚለው ነገር ነው። በፌዴራል ስርዓት ውስጥ ከምንገነባው የልማትና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አንድ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ማኅበረሰብ እንዴት እንገንባ ተብሎ የተቀመጠ ጉዳይ አለ።
በዛ ላይ የተዘረጋውን እድል የተነጠፈውን መሰረት ማፋጠንና መገንባት ይጠይቃል። በብሔራዊ መግባባት ዙሪያ ሊጫወቱ የሚገቡ ተቋማትን የበለጠ እያሳተፉና ግንባር ቀደም ሚና እንዲጫወቱ፤ ካለው ታሪካችን አጉልተንና ለአሁኑ ትልቅ እሴት ሆኖ የሚሄደውን ይዘን የምንሄድበት፤ የሚታረሙት እንዳይደገሙ የምናደርግበት፤ የሚያጋምዱንን ገመዶች የበለጠ እያጎለበትን እነዚህን ሰበዞች ትልቅ ቦታ እየያዙ የሚሄድበትን እንቅስቃሴ ማድረግ ያስፈልጋል ማለት ነው።
በዛ ደረጃ የመጣንበት የጣልነው መሰረትና ስኬት አለ። በቂ ስላልሆነ ግን እንዴት አድርገን የበለጠ ትኩረት ሰጥተን እንጓዝበትና ትኩረት እንስጠው የሚለውን ነው እንጂ አንዱን ጥሎ አንዱን ይዞ መሄድ አይቻልም። ሁለቱም ይመጋገባሉ። በጽኑ መሰረት ላይ እየተገነባ፤ ጠንካራ አገራዊ አንድነት የበለጠ ሊጎለብት ይገባዋል። በተለያየ መልክ የሚነሳው ለብሔር ተኮር ሥራ ስለተሠራ ይህኛው ግምት እንዳይሰጠው ሆነ ማለቱ ከመሰረቱ ሊስተካከል የሚገባው ነው።
አቶ ለማ መገርሳ ደግሞ አንድነት እንዴት ይፈጠራል? የሚለውን ማየቱ ነው ጠቃሚ የሚሆነው፡፡ ኢትዮጵያ እንደ አገር ከተመሰረተችበት ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ አብዮቶችና ትግሎች ሲካሄዱ ቆይተዋል፡፡ እነዚህን ትግሎች መለስ ብለን ካየናቸው መሰረታዊ የሆኑ የብሄር ብሄረሰቦች ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ የነበረው አንድነት በውጫዊ ተጽእኖ የተፈጠረ የጭነት አንድነት በመሆኑ በመላው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ዘንድ ተቀባይነትን አላገኘም፡፡ ምክንያቱም የህዝቦችን ውክልና የማያሳይ አንድነት በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ ብሄር ብሄረሰቦች ሲታገሉለት ከነበረው መሰረታዊ ጥያቄ ውስጥ አንዱ የብሄራዊ አንድነት ትልቁ ጉዳይ ነው፡፡ ከመሬት ጥያቄ ቀጥሎ የነበረው የማንነት ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ኢህአዴግ ብቻ ያመጣው ውጤት ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝቦችም ለዘመናት ለዚሁ መብት ሲያደርጉ የነበረው ትግል ውጤት ነውና ብሄራዊ ማንነት እንዲሁ ዝም ብሎ የተፈጠረ ጉዳይ ሳይሆን የህዝቦች ትግል ያመጣውና የፈጠረው ጉዳይ ነው፡፡ ይህም በዚህ ስርዓት እውን ሆኗል፡፡
እስከሚገባኝም ብሄራዊ ማንነታቸው ስለተከበረላቸው ብሄር ብሄረሰቦችም ደስተኞች ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊነቱን የሚያየው መጀመሪያ ከራሱ ነው፡፡ ከራሱ ማለት በኢትዮጵያ ውስጥ የእኔ ድርሻ ምንድነው? ይህች አገር ለእኔ ምንድነች? በዚህች አገር ውስጥ እኔ ማን ነኝ? ምንድነኝ? የሚሉ መሰረታዊ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ይህ ማለት ኢትዮጵያ ማንነት ከግለሰብ ነው የሚጀምረው፡፡ የግለሰብ ማንነቱ፣ የቡድንና የብሄር ማንነቱ ሲከበርለት ነው ኢትዮጵያዊነቱ በዚያ ውስጥ የሚከበርለት፡፡ ይህም በመሆኑ የብሄራዊ ማንነት ጥያቄ መመለሱ የህዝቦችን የዘመናት ጥያቄ የመለሰ የህዝቦች የትግል ውጤት ነው፡፡
ብሄራዊ ማንነት መመለሳቸው አገራዊ ማንነትን አልጎዳም ወይ ተብሎ የሚታየው እንደ ሰው አተያይ የተለያየ ትርጉም ሊሰጠው ይችላል፡፡ ነገር ግን በእኛ ሁኔታ የእያንዳንዱ ብሄረሰቦች የማንነት ጥያቄ መመለሱ ኢትዮጵያዊ አንድነትን የሚጎዳ አይደለም፡፡ እንዲያውም የበለጠ የሚያጠናክር ነው፡፡ ምክንያቱም ለመጀመሪያ ጊዜ ብሄር ብሄረሰቦች በኢትዮጵያ ውስጥ እውቅና ያገኙበት ጊዜ በዚህ ፌዴራላዊ ስርዓት ነው፡፡ እውቅና አገኙ ስንል የብሄራዊ ማንነታቸው መከበሩ ነው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን ደግሞ ብሄራዊ ማንነታችንን ለማጠናከርና ለማጎልበት ስንሰራ አገራዊ አንድነታችንንም በማጠናከሩ ላይ መስራት አለብን የሚለው ግን አስፈላጊ ነጥብ ነው፡፡ አገራዊ አንድነቱ ተጎድቷል ከሚለው በላይ የበለጠ ማጠናከሩ ላይ መስራቱ ይጠቅመናል፡፡
የኢትዮጵያ አንድነት በምንም መልኩ ሊጎዳ አይችልም፡፡ ኢትዮጵያዊነት ማንም ሲፈልግ እንደ ገበያ አንድ ላይ የሚሰበስበው፣ ሲያሻው ደግሞ እንደ ገበያ የሚበትነው ነገር አይደለም፡፡ ብዙ ምስጢርና ታሪክ ያለው በኢትየጵያዊያኖች መካከል ብዙ የታሪክ፣ የማህበራዊ ህይወት ጉድኝትና ትስስር ያለው ማንም በቀላሉ የሚፈታው ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህ ያለ ሀቅ ነው፡፡ ቢታሰብም የሚሆን ጉዳይ አይደለም፡፡ እዚህ ላይ ማንኛውም ሰው ግልጽ መሆን ያለበት ይመስለኛል፡፡
በሆነ አጋጣሚ የኢትዮጵያ አንድነት ሊፈርስ ሊበትን የሚችል የዝምብሎ ስብስብ አይነት አድርጎ የሚያይ አለ፡፡ ነገር ግን በእኔ እይታ በሁላችንም ግምገማ ኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያዊ አንድነት ከምናስበው በላይ በብዙ ህይወት፣ በብዙ ኑሮ፣ ኢኖሚያዊና ማህበራዊ ትስስር የተዋሃደ ህዝብ ነው፡፡ ይህ አንድነት ደግሞ በአንድ ጀምበር የተገነባም አይደለም፡፡ ለዘመናት ሲገነባ የኖረ ነው፡፡ በሆነ አጋጣሚና በሆነ ግርግር ላይ ሊፈርስ የሚችል አይደለም ፡፡
ነገር ግን የኢትዮጵያን አንድነት የሚጎዳው ብሄራዊ አንድነት ነው ወይስ ምንድነው አንድነትን ሊጎዱ የሚችሉት? የሚለውን ነገር ካየን የኢትዮጵያን አንድነት ሊጎዳ የሚችለው ነገር ፍትህ ሲጠፋ ነው፡፡ አንዱ ቤተኛ አንዱ ባይተዋር ተደርጎ የሚሰደድበት ስርዓት እዚች አገር ውስጥ ካለ ኢትዮጵያዊነት በቀላሉ ይፈርሳል ባንልም ግን ሊሸረሸርና ሊጎዳ ይችላል፡፡ በኢትዮጵያዊያኖች መካከል እኩል ተጠቃሚነት ከሌለ ኢትዮጵያዊነት ሊጎዳ ይችላል፡፡ በእኔ ግምገማና በሁላችንም እይታ ኢትዮጵያዊነትን ሊጎዱ የሚችሉ በሽታዎችና ነቀርሳዎች እነዚህ ናቸው ብዬ ነው የማስበው፡፡ ከዚህ በስተቀር የኢትዮጵያን አንድነት ሊጎዳ የሚችል ምንም ነገር የለም፡፡ እንዲያውም የኢትዮጵያን አንድነት ለማጠናከር ብሄር ብሄረሰቦችንም ብሄራዊ ማንነታቸውን እንዲያጠናክሩ ማድረግ አንድ ጉዳይ ሆኖ በዚህ ፌዴራላዊ አወቃቀር ሁሉም ክልል በየብሄራዊ ማንነቱ ለየአካባቢው ሲሰራ፤ ለየአካባቢው፣ ለየክልሉ መስራቱ አንድ ጉዳይ ሆኖ አገራዊ እይታ ሊኖረው ግን ይገባል፡፡ ሁልጊዜ በየቤታችን የራሳችንን ጉዳይ ስንሰራ አገራዊ እይታ ቢኖረን በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ምክንያቱም አንድ ክልል ወይም አንድ ብሄር በራሱ ብቻ በሚሰራው ዘላቂ ጥቅሙ ሊረጋገጥለት አይችልም፤ ዘላቂ ሰላሙ ሊረጋገጥለት አይችልም፤ ዘላቂ እድገት ሊመጣለት አይችልም፡፡ እድገት ሊመጣ የሚችለው በጋራ ስንሆን ነው፡፡
በአገራችን ላይ ዘላቂ ለውጥ በማናችንም ብሄር ብሄረሰቦች ሊመጣ የሚችለው በአንድነታችንና በህብረታችን ውስጥ እስከሆነ ድረስ ሁልጊዜ በየብሄራችን ማንነታችንን ለማጠናከርና ለማጎልበት የምንሰራውን ያህል ሁሉ ለአገራዊ አንድነታችንም ሁልጊዜ እያሰብን እንደ አንድ ትልቅ ስራ ወስደን መስራቱ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ሲሆን ነው የሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ዘላቂ ጥቅማችን ሊከበርና ሊጠበቅ የሚችለው፡፡ ስለዚህ ወደፊትም ከዚህ በበለጠ አሁንም እየተጀመረ ባለው ህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶች በልማቱም በኢኮኖሚውም ለውጥ ማምጣት በዚያ ላይ ተግቶ መስራቱ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱንም ማጠናከር ማጎልበት እጅግ በጣም አስፈላጊ ስለሆነ አሁንም እየተጀመሩ ያሉትን ጉዳዮችና ሌሎች አዳዲስ አንድነታችንን ይበልጥ እያጠናከሩ የሚሄዱ ጉዳዮችን በማጎልበትና በማጠናከር ይገባል፡፡ ይበልጥ እንድነታችንን ለማጠናከር እንደ አንድ ትልቅ ስራ መስራቱ አስፈላጊና ዘላቂ ጥቅማችንን ሊያስጠብቅልን የሚችል ነው፡፡
ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል በበኩላቸው ፌዴራሊዝም ብዝሀነታችንን ለማስተናገድ ተብሎ የተነደፈ ስርአት ነው፡፡ ይህ ህዝብን ለመበተን አይደለም፡፡ እኩልነትን በማረጋገጥ አንድነትን ለማምጣት ነው፡፡ የፌዴራሊዝም ዋና ዓላማው በብዝሀነትና ብሄር ላይ የተመሰረተ አንድነት ማምጣት ነው፡፡ ስለዚህ ብሄራዊ ማንነት ለአንድነት መሰረት ነው፡፡ ተቃርኖ ሊኖረው አይችልም፡፡ መሰረት የሌለው ቤት ቤት ሊሆን አይችልም፡፡ ስለዚህ የእኛ አገር አንድነቱ መሰረቱ ብሄር ነው፡፡ እነዚህ ያሉ እውነታዎች ናቸው፡፡ መሰረቱ ከተዳከመ አንድነት የሚባል ነገር ይፈርሳል፡፡ የእኛ ጠንካራ መሰረት ጠንካራ ብሄራዊ ማንነታችን ማረጋገጥ ነው፡፡ ይህ ሲባል መብቶቹ በትክክል መረጋገጥ አለባቸው፡፡ የተሟሉ መብቶች መኖር አለባቸው፡፡ የዴሞክራሲ መብቶችም ሆኑ የልማት መብቶች፣ በተለያየ መልኩ የሚገለጸው ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ብሄራዊ ማንነታችን ለአንድነት መሰረት ነው፡፡
የአገራዊ ማንነትን ማዳከም የሚባለውን በተጨባጭነት ብናየው፤ በአንድነት በኩል በተጨባጭ አገራችን ተዳክሟል ማለት አንችልም፡፡ የተጠናከረ አንድነት ነው ያለን፡፡ ስርአትን ከስርአት ማነጻጸር አስፈላጊ ባይሆንም ካለፈው ስርአት አነጻጽረን ስናየው ህዝቦች መብታቸው በጣም በተረጋገጠበት፤ የእኩልነት መብቶቻቸው በቋንቋ፣ በባህልና በታሪክም ተከባብረው የማይተዋወቁ ህዝቦች እየተዋወቁ ነው የሄዱት፡፡ ከጫፍ ጫፍ ብዙ ነገር ነው እየተማርን ያለነው፡፡ አገራችንን እያወቅን ነው ያለነው፡፡ በልዩነቱ አንድነቱ ነው እየተገነባ ያለው፡፡ በፊት ልዩነቱም አይታይም፡፡ የተደፈነ፣ የተዘጋ ነበር፡፡ ግን የሚያስተሳስረን ታሪክ ስለነበረን በታሪካችን ነው የቆየነው፡፡ ብዙ ውጣ ውረድ ያለፈ ህዝብ ስለሆነ፡፡ ለሺህ ዘመናት እየተባለ የሚገለጸው ብዙ ታሪክ አለው፡፡ ብዙ መጥፎና በጎ ነገር ያለፈ ስለሆነ አንድነቱን ጠብቋል፡፡ ግን የተሟሉ መብቶች ተረጋግጠዋል ማለት አይቻልም፡፡ ጥቅሞች ተረጋግጠዋል ማለት አይቻልም፡፡ በጭቆናም በችግርም ሆኖ አንድነቱን የጠበቀ ነው፡፡ በዚህ ስርአት ጭቆናውን እየፈታነው የጎደለውን ነገር እየሞላን ነው ያለነው፡፡ የበለጠ አንድነቱን እንዲያጠናክር እንጂ ታሪኩን ለማጥፋት አይደለም፡፡ በታሪክ ላይ ነው ሌላ ታሪክ እየተገነባ ያለው፡፡ ስለዚህ ፌዴራሊዝም የብሄራዊ ማንነት መሰረቱ ስለሆነ አንድነትን የበለጠ ለማጠናከር የሚጠቅም ነው፡፡ አንዳንድ የሚታዩ ችግሮችም ካሉ ምንጫቸው እሱ አይደለም፡፡ ብሄራዊ አንድነት ስለተከበረ አይደለም፡፡ የጋራ የሚያደርጉን እሴቶችን መማር አለብን፡፡
ህዝባችን ብዙ ውጣ ውረድ አልፏል። ነጻነቱን ለምን ጠበቀ? ከስንት ጠላት ተፋልሞ ነው ይህን አገር የጠበቀው። የእገሌ ብሔር የእገሌ ብሔር ተብሎ እየተበታተነ አይደለም። ሲበታተን ቀዳዳ ለጠላት የሰጠ የተጋለጠበት፤ ሲተባበር ደግሞ አገሩን ጠብቆ የሄደበት ብዙ የጋራ የሁላችን ታሪክ አለ። ይህ የጋራ ነው።
ከታሪኮቻችን መማር አለብን። የጎደሉን ነገሮች አሉ፤ አንድነታችንን የበለጠ ማጠናከር እንጂ ብሔራዊ ማንነት አይደለም ችግሩ። እሱ የተለየ አጽንኦት ስለተሰጠው አይደለም። እሱማ መረጋገጥ አለበት ነው ያልነው፤ የጎደለ ነገር ነው የሞላው በዚህ ስርዓት። ይህ የጥንካሬያችን ምንጭ ነው። ተደጋግሞ እንደሚገለጸው በልዩነታችን የመጣ አንድነት ነው ያለው። እንጂ ልዩነት አጥፍተን፤ የብሔር ማንነት አቀዛቅዘን አንድነት የሚባል ነገር ልናመጣ አንችልም። አንድነቱ የሚፈርስ ነው የሚሆነው። ከጋራ እሴቶቻችን ግን ሁላችን መማር አለብን ነው ያልነው። የኢህአዴግ ስብሰባም ሳይቀር ወጣቱ ብቻ ሳይሆን ሁላችን እንማር ነው ያልነው። ያለፉ የሕዝቦች ታሪኮቻችን አሉ። አንድነቱን ለማጠናከር የጎደለ ነገር ግን አለ። ብሔራዊ ማንነቱን የመቀነስ ሳይሆን የጎደለውን መሙላት አለብን። ብዙ የጎደሉ አሉ፥ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት፣ ብዙ ድህነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች አሉ። በጥቅማጥቅም ብዙ ድሆች አሉ። ያልተጠቀመ ከሆነ ችግር ነው ማለት ነው። ለሌላ ግጭት መንስኤ ነው የሚሆነው። ስለዚህ ለግጭት መንስኤ የሆኑትን በሙሉ ለመቀነስ ጥረት ማድረግ አለብን፤ የበለጠ ጠንካራ አንድነት እንዲኖረን።
በሌላ በኩል የጋራ እሴቶችን ሁላችን ማወቅ አለብን። እዚህ ላይ የጎደለ ነገር አለ። ሚዛኑ የተዛባ መስሎ የሚታየውም ለዚህ ነው። ብሔራዊ ማንነቱን አዳክመን እሱ ስለተጠናከረ የመቀነሰ ሳይሆን የጎደለችው በአመለካከትም አንድ ቤት ነው እየሠራን ያለነው። የጋራ ፕሮጀክት ተብሎ በተለያየ መልክ የሚገለጽ ነው። ለዚህም ተመሳሳይ አረዳድ እንዲኖረን ሁሉም ድርሻ ያለው ነው፤ ሁሉም ቤተኛ ነው። ስለዚህ የየራሱን አስተዋጽኦ ማድረግ አለበት። አስተሳሰባችን ራዕያችን፤ አሁን መካከለኛ ገቢ እያልን የምንቀሳቀሰው እንደ አገር ነው። እንደ ህዝብ መለወጥ ነው የምንፈልገው። በዚህ ላይ በየክልሉ ታጥሮ ሳይሆን አገር አቀፍ እይታዎችን የመያዝ፣ ተደጋግፎ የመልማት፤ በመሰረተ ልማት ተሳስረናል፤ በመንገድ፣ በኤሌክትሪክና በመሳሰለው። ይህ መጠናከር አለበት፤ የበለጠ ትስስሮቻችን አንድነታችን በጣም ያጠናከራል። እዚህ የጎደሉትን እንሙላ፤ ያልተጠቀመ ህዝብ እንዲጠቀም ማድረግ አለብን።
ስለዚህ አንድነታችን ለማጠናከር በኢኮኖሚው ዘርፍ የሚሠሩ ብዙ ሥራዎች አሉ ማለት ነው። በገበያ የምናስተሳስረው፤ በየክልል ታጥሮ አይደለም እድገትና ልማት የሚመጣው። በየአካባቢው መልማት የሚችለውን ያህል እናለማለን፤ ይህ ግን እስፔሻላይዜሽን የምንለው ነው። በየአካባቢው የተለያየ ምርት እና የምንተሳሰርበት ገበያ፤ ሁሉም በአንድ አካባቢ እንዲመረት አይደለም። በገበያም ትስስር አንዱ ጋር የጎደለውን አንዱ የሚሞላበት። ተደጋግፈን፤ በገበያም ተሳስረን፥ በኢኮኖሚ ተጠቃሚነታችን ከፍ የምናደርግበት ነው። አንድነታችንን ለማጠናከር መወሰድ ያለባቸው ተጨማሪ እርምጃዎች አሉ ነው እያልን ያለነው። እንጂ ብሔራዊ ማንነት ላይ ያልሆነ ሥራ ተሠርቷልና እንቀንሰው አይደለም። ያቺ የጎደለችዋን አሟልተን የበለጠ አንድነታችንን የሚያጠናክር ሥራ መሥራት ይቻላል። ለአንድነቱ ብሎ ብቻ ሳይሆን ለበለጠ ተጠቃሚነትና የበለጠ ለማድረግ እንድንችል ነው። ጠንካራ ከሆንን በሁሉም ለጠላትም ሳይቀር የሚያስፈራ ነው የምንሆነው። ለምን ትልቅ ጉልበትና አቅም አለን። ማንም የሚደፍረው አገር አይሆንም። ሁለት ሶስቴ አስቦ ነው የሚመጣው። ለውጭ ጠላትም ሳይቀር ነው አንድነታችን የሚያስፈልገው።
ዋናው ግን ለራሳችን ተጠቃሚነት፣ ልማት፣ እድገት፣ የህዳሴ ጉዞ ለማፋጠን የግድ በአንድነት ዙሪያ የጎደሉንን፥ ከአመለካከት ጀምሮ በኢኮኖሚም በመሰረተ ልማትም፥ እና የባህል ልውውጥ፥ ሕዝብ ለህዝብ በሚል የተጀመረውም ተጠናክሮ ነው መሄድ አለበት። በሙዚቃና በዘፈን ብቻ አይደለም የተለያዩ አካባቢዎች መስማት ያለብን። ሕዝብ ለሕዝብ ማገናኘት አለብን። ምሁር ለምሁር መገናኘት አለበት። ወጣት ለወጣት መገናኘት አለበት። የበለጠ መተሳሰር አለብን እንጂ ወደ የክልል አጥር አይደለም መግባት ያለብን፥ ያ መፍረስ ነው ያለበት ። አጥር መኖር የለበትም፥ አስተዳደራዊ ቅርጽ ነው። ዋናው ይዘቱ ግን ትስስሩ ነው።
ያ መልክ ነው። ይዘቱ እንዳልነው ነው፥ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስሩ ሄደን ሄደን አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ እንፍጠር ያልነው ዋናው ጉዳይ። ይህን ለማጠናከር እንሥራ በሚል ነው ውይይት የተካሄደው።

 በጋዜጣው ሪፖርተሮች 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።