ሁሉም ያሸነፈበት መድረክ

11 Jan 2018

የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለ17 ቀናት ያካሄደው ስብሰባ ማጠቃለያ ላይ በአወጣው መግለጫ የአራቱ ብሄራዊ ድርጅቶች አመራሮች የሰጡትን ማብራሪያ በተከታታይ ስናቀርብ ቆይተናል። በዛሬው ዕለት የድርጅቶች አመራሮች ለተፈጠሩ ችግሮች የሚወሰደውን ሃላፊነት፣ በመድረኩ ማን አሸነፈ ? ኢህአዴግ ከችግሩ ይወጣል? በሚሉ ጥያቄዎች ዙሪያ የሰጡትን ማብራሪያዎች ይዘን ቀርበናል።
ለተፈጠሩ ችግሮች የሚወሰደውን ሃላፊነት በተመለከተ የደኢህዴንና ኢህአዴግ ሊቀመንበር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዳብራሩት በእርግጥም በእኛ የሥራ አስፈጻሚ ግምገማ ወቅት ከልብም የተመለከትነው ነገር ቢኖር እነዚህ የዘረዘርናቸው ችግሮች በሙሉ እንደ አካል እንደአስፈጻሚ እኛ እየመራን የተፈጸሙ ናቸው። እኚህ ጉዳዮች ከልብ ወደውስጥ ተቀብለን ኃላፊነት መውሰድ አለብን። ማንኛውም ተራማጅ አመራር እንደዚህ ዓይነት ነገሮች በሚፈጠሩበት ጊዜ በማያሻማ በማያወላዳ ሁኔታ የቡድንም የግልም ኃላፊነት መውሰድ የግድ ይላል የሚል ጽኑ እምነት አለን ብለዋል፡፡
የብአዴን ሊቀመንበርና የኢህአዴግ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው እንዳሉት፣እራሱ ስብሰባው ግምገማው ሲጀምር ፣ሀገራችን በምን ሁኔታ ላይ ነው ያለችው? ድርጅታችን በምን ሁኔታ ላይ ነው ያለው? ነባራዊና ህሊናዊ ሁኔታ እና ከዚህ ለመውጣት ምንድነው የሚያስችለው የሚለውን አስቀምጧል። ችግሮችን በዝርዝር ነቅሶ በማውጣት ባለቤት ተቀምጧል። ይህንን እንደ ወሳኝ እርምጃ ወስደን ባለቤቱ ደግሞ ዋናው የላይኛው አመራር ሄድ ኳርተሩ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ራሱ እንደሆነ፣ለሌላው ጣቱን አልቀሰረም፣ለሌላ አላመላከተም።
በስራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ውስጥ እንኳን፣እንደየሀላፊነት ድርሻው በዛ ላይ የነበረው ሚና ሁሉም እዛ ያለ አመራር በግልጽ አስተማሪ በሆነ ሁኔታና በተቆርቋሪነት ይህን በደል፣ይህን አደጋ፣ይህን ችግር ለችግሩ ዕድሜ መግዛት እና ለዚህ ሁኔታ መፈጠር ተጠያቂ ነኝ የሚለውን ነገር አስቀምጧል።ለዚህ ነው ስራ አስፈጻሚው ኮሚቴው ለዚህ ችግር ዋናው ባለቤት እኔነኝ የሚለው።
በዚህ ደረጃ ባለቤትነት ሲወሰድ አሰራርና ስርዓትን ጠብቆ ያኛው ደግሞ ከየብሄራዊ ድርጅቶች ጋር እየተሳሰረ ዝርዝር ግምገማዎች ሲካሄዱ የበለጠ ሁሉም በየድርሻው የሚወስደው ሀላፊነት የሚወስደው ተጠያቂነትና ትምህርት ይኖራል። እዚህ ላይ ትልቁ ቁምነገር ምንድነው? ችግር ሲለይ ሲባል ከግለሰቡ ጋር አጣብቆ አንድን አካል በማውጣት በማውረድ አይደለም።
መጀመሪያ የስርዓት ችግር መለየት ነው። ያ ሰፊ ርብርብ ተደርጎ ተለይቷል። የስርዓት ችግር ሲለይ ለስርዓት ችግር መፈጠር ተዋናዩ የድርሻውን እንዲወስድ ማለት ነው። ሥራ አስፈጻሚው ያንን በግልጽ አስቀምጧል። በዚህ ላይ የተመሰረተ እንደ ቡድን ሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴው ቢወስድም፣ መውሰድም ስላለበት እንዲሁ በአጠቃላይ አነጋገር የሚቀመጥ ብቻ ሳይሆን በዝርዝር ደግሞ ቀደም ባልኩት አሰራሮች ሁሉም ትምህርት የሚወስድበትና ያ ተጠያቂነት የሚቀመጥበት ይሆናል የሚለው ነገር ግልጽ መሆን አለበት። ይሄ ወሳኝ እርምጃ ነው።
የወሳኝ እርምጃው ማሳረጊያ በስርዓት ደረጃ የተለየውን ችግር የችግሩ ባለቤት እኔ ነኝ ብሎ እጅግ አስተማሪ በሆነ ሁኔታ ተቆርቁሮ እንደ ቡድን ችግሩን የተቀበለው አካል የለየውን ችግር ለመፍታት ያስችለኛል ባለው መንገድ ምንም ሳያወላዳ ተጨባጭ መፍትሄና ትግበራ ውስጥ መግባት ነው።የተለያየ ምክንያት በመደርደር አይሆንም። ውሳኔና ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚጠበቀው ጉዳይ ይሄ ነው። በዚህ ማዕቀፍ ከታየ ወሳኝ እርምጃው እስከውጤቱ ድረስ ተያይዞ ፍሰቱ መወሰድ አለበት።የመጀመሪያው ምዕራፍ ግን ለዛ ደረጃ የሚመጥን፣እራሱን ወደውስጡ የተመለከተ እርምጃ ስለሆነ በዛ ደረጃ ቢታይ መልካም ነው።
ማን አሸነፈ? የሚለውን ጉዳይ በተመለከተ አቶ ደመቀ እንዳብራሩት ፤ ተሸናፊ የለም። ሁሉም ችግሮችን ነቅሰው ባወጡበት፣ሚናቸውን በለዩበት፣በዚህ ደረጃ ችግር ሲደርስ የኔ ሚና ምን መሆን ሲገባው፣ምን አምልጦኛል የሚለውን አስተማሪ ነገር በማየት የየብሄራዊ ድርጅቶቹ አመራር የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ እንደ አካል የወሰደው ትምህርትና በችግሮቹ ላይ የፈጠረው ተግባቦትና መፍትሄዎቹን ማስቀመጥ ነው። አንዱ የመጀመሪያው የአሸናፊነት እርምጃ ነው። አሸናፊነት በዚህ አይቆምም።ይህ አሸናፊነት ደግሞ የሚረጋገጠው በዚሁ አግባብ ተጨባጭ የሆኑ ውጤቶች በተፈጠረው የአስተሳሰብ አንድነት ለተግባር አንድነቱ መሰረት ተጥሏል። በዛ መሰረት ላይ ተመስርቶ አፋጣኝ ለውጥና ምላሽ ህብረተሰቡ የሚጠብቀው ንቅናቄ በተግባር በማረጋገጥ ነው።
ይሄ አሸናፊነት በኢህአዴግ ደረጃ እንደ አካል አረጋግጦ ወጥቷል። ይሄ አሸናፊነት ወደ ብሄራዊ ድርጅቶች ዘለግ ብሎ እንዲወርድ ይጠበቃል። ብሄራዊ ድርጅቶቹም በዝርዝር ከዚህ በፊት በጀመሩት ላይ ተመስርቶ አሁን ከቆምንበትና አሁን ከምናስቀምጠው አተያይ ጋር የተያያዘ ብሄራዊ ድርጅቶቹን ሊለውጥና የበለጠ አቅም ሆኖ ሊያስኬድ የሚችል ግምገማዎችን ማየት ይኖርባቸዋል። በዛ ደረጃ አይተው ፣በብሄራዊ ደረጃና እንደ ሀገር በሚያገናኛቸው መስተጋብር ቆጥረው ለይተው የሚያስቀምጡበት መፍትሄና የአስተሳሰብ አንድነት አንድ የአሸናፊነት እርምጃ ይሆናል። ይህ ተያይዞ ከላይ እስከታች እንደ ግንባርም እንደ ብሄራዊ ድርጅቶች የሚደረገው ንቅናቄ የተሟላውን አሸናፊነት ያረጋግጣል። በዚህ አተያይ ነው የሚወሰደው ከዚህ እላፊ የተለያዩ የሚባሉ ነገሮች ቁምነገር አላቸው ተብለው ሊወሰዱ የሚችሉ አይደሉም።
ኢህአዴግ ከችግሩ ሊወጣ ይችላል? በሚለው ጥያቄ ላይም አቶ ደመቀ ማብራሪያ ሰጥተዋል። እውነት ነው ህዝቡ በዚህ ደረጃ ቢሰጋ ፣ቢጠራጠር የሚገርም አይደለም። የተጀመረ የለውጥ ጉዞ አለ።ድህነትንና ኋላ ቀርነትን የመለወጥ፣ጠንካራ ሀገር የመገንባት ፣ብልጽግናን የማረጋገጥ ጅምር አለ፡፡ ይህን የሚፈታተን አካሄድ ሁሉ ዋጋው ከባድ ነው። በስራው ፍጥነት መፍጠን በሚገባን ሁሉ አቀፍ ጉዞ ማረጋገጥ በሚገባን ያለው ጉድለት እንዳለ ሆኖ አሁን አሁን ደግሞ ከግጭት ጋር እየተያያዙ ሰላምና ደህንነቱን የሚያደፈርሱ ፣ስጋት ውስጥ የሚጥሉ፣ጉዳዮች ሲደማመሩበት ሌሎች ሌሎች ችግሮች እዚህ ጋር ሲሆኑ የመልካም አስተዳደር ችግር ዕድሜ እየገዛ በዛ ደረጃ ሲመጣ እና ሌሎች ችግሮች ሲሰፉ ለምን አይጠረጥርም? ኢህአዴግ እንዴት ነው ከዚህ አኳያ የሚታየው? በዘረዘርነው ችግር ልንጠረጠር አይገባም? የሚለውን ነገር ቢጠረጥር አይገርምም።
ኢህአዴግ ሁሌም ለአንድ ጉዳይ መጀመሪያ በውስጡ እራሱን ይፈልጋል። በውስጡ ያለውን ችግር ያንኳኳል።ያንን ደፍሮ ይመለከታል። የእሱን የቤት ሥራ ከሰራ በኋላ ሌሎች ለዚህ መፍትሄ ሆነው እንዲቆሙ ሁኔታዎችን ያመቻቻል። በኢህአዴግ ውስጥ ብቻ የሚሰፈር የሚሰራ ሥራ የትም አያደርስም። መስተጋብሩ ወደ ህዝብና ወደ ለውጥ ይሸጋገራል። ኢህአዴግ ያ ጸጋው ራሱን ዋንኛ ተጠያቂና የችግር ባለቤት አድርጎ ማየቱ ያ ባህርይውና ያ እርሾው ገመዱ እነዛ መርሆዎቹን አለቀቀም ኢህአዴግ። እነዛ በተለያየ ችግር ጫና ደርሶባቸው እየተፋዘዙ ግን ደግሞ ቆም ብሎ ወደዚህ ግምገማና ወደዚህ ሁኔታ በመግባት እነዛ ጸጋዎቹን መሰረት አድርጎ እራሱን ጠይቆ ባለቤት ሆኖ መፍትሄዎቹን ይዞ ለሁሉም ተዘጋጅቷል ማለት ነው።
በዚህ ደረጃ ከተመጣ ይሄንን ይዞ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መግባት ነው፡፡ ብዙ መስቀለኛ መንገዶችን እየፈታ የመጣ ድርጅት የተለያዩ ፈታኝ ሁኔታዎችን እየፈታ የመጣ ድርጅት አሁንም በዚህ ምዕራፍ ላይ ተፈትኗል፡፡ በችግር አፈታት ደረጃ አንዱ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ወደመተማመንና የአስተሳሰብ አንድነት ደርሷል፡፡ በዚህ ደረጃ የመጣው እንደዋዛ አይደለም፡፡ ለሆነ ፍጆቻ አይደለም፤ አገርን አስቀድሞ በማየት፣ ከራሱ በላይ ህዝብንና አገርን በማየት ነው፡፡ ይሄንን ወደ ተግባር መንዝሮ የህዝብ እርካታን ለማረጋገጥ ከዚህ ስጋት ለመውጣት በግምገማ ላይ በዝርዝር በለያቸው ችግሮች፤ በዚያ ላይ ተለይተው በተቀመጡ ችግሮች በፍጥነት ወደ ተግባር መግባትና ምላሽ መስጠትም ይጠይቃል፡፡
ለዚህ ኢህአዴግ ዝግጁ ነው፡፡ እንደ አካልና እንደ ግለሰብ ከፍተኛ መቆርቆር ወስዶ ቀጣይ የሚኖሩ መድረኮችን ተደማሪ አቅም አድርጎ ይሄን ሊለውጥ ይችላል፡፡ ይሄን ለመለወጥ የሁሉም አቅሞች፣ የህብረተሰቡ ተሳትፎ፣ የህብረተሰቡ ጠያቂነት፣ የህብረተሰቡ ባለቤትነት በተለያዩ አደረጃጀቶች፤ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሲቪል ማህበራት፣ የምሁራን፣ ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለመፍትሄው የምንገነባው የጋራ አገራችንን ስለሆነ የራሳቸውን ሚና እንዲወጡ በግልጽ ያስቀመጠው ነገር አለ፤ ያንን ተመስርተን ልንለውጠው እንችላለን፡፡ ትክክለኛ መንገድ ላይ ነው ያለነው፡፡ ለዚያም ኢህአዴግ እሴቶቹንና መርሆዎቹን ጠብቆ እውን ለማድረግ ተዘጋጅቷል፡፡
የሚወሰደውን ሃላፊነት በተመለከተ የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን እንዳሉት ዋናው ነገር አገር ሊበትኑና ህዝብን ወደ ከፍተኛ ትርምስ ሊያስገቡ የሚችሉ ችግሮች መፍትሄ ተቀምጧል፤ በአገራችን እየታየ ያለው ችግር የመጨረሻውን መፍትሄ አግኝቷል የሚለው ነው ? ችግሮቹ በጣም የከፉ ናቸው፡፡ እየተባባሱ የሚሄዱ ናቸው፡፡ ቶሎ ካላስተካከልነው ወደ ትልቅ ጉዳት ያደርሰናል፡፡ ስለዚህ ይሄ መቀየር አለበት በማለት፤ ችግሩ ፖለቲካዊ ስለሆነ መፍትሄውም ፖለቲካዊ መሆኑ ተነስቷል ብለዋል፡፡ ስለሆነም ፖለቲካዊ ግምገማው ቅድሚያ ይሰጠዋል ከሁሉም በላይ፡፡ ፖለቲካዊ መፍትሄ ካልተቀመጠ ሰው ቢቀያየር መፍትሄ አይመጣም፡፡ ስለዚህ ዋናው ችግር መጀመሪያ ተቆጥሮ ተለይቶ መቀመጥ፣ ለዚያ ደግሞ መፍትሄ ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡
መፍትሄ ለማስቀመጥ በችግሮቹ ላይ መተማመን ያስፈልጋል፡፡ ችግሮችን ማስቀመጥ ራሱ ግማሽ መፍትሄ ነው ይባላል፡፡ ሰው ከዚያ በኋላ ነው የሚመጣው፡፡ ይሄ ደግሞ እንዳልነው የአመራር ነው፡፡ እንደ አካል የቡድን የተባለው ትልቅ ውሳኔ ነው፡፡ እንደ አካል ነው ችግር ያለው ተብሏል፡፡
መጨረሻውስ ተግባር ላይ ነው የሚታየው፡፡ ስለዚህ በዚህ በመድረክ ደረጃ በጣም ታሪካዊ ነበር፡፡ እንደተለመደው እንዳይሆን ነበር ያልነው እንደተለመደው አላደረግነውም፡፡ መሰረታዊ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ሥራ ነው የተሰራው፡፡ ውጤት አግኝተንበታል፡፡ በአመራር ላይ የነበሩ ችግሮችን በመሰረቱ ፈትተናል፡፡ አብሮ የመስራት ችግር ነበር፡፡ የላላ ግንኙነት ነበር፡፡ ይሄ ተጠግኗል፡፡ ወደ መስመር ተገብቷል፡፡ ስለዚህ በአመራር ላይ የነበረው ትልቁ ችግር መፍትሄ አግኝቷል፡፡ በቀጣይ ትግል ደግሞ የበለጠ ይጠናከራል፡፡
የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል አሸናፊው ማነው የሚለውን ጥያቄ በተመለከተ እንዳብራሩት በመሰረቱ አሸናፊው አስተሳሰባችን ነው፡፡ የኢህአዴግ ዋናው የአስተሳሰብ መስመር ህዝባዊነት ነው፡፡ መሸራረፍ እና ለግል ጥቅም ማሰብ ነበር፡፡ ቡድንተኝነትና መተሳሰር ነበር፡፡ ይህን ትስስር ለመበጣጠስ ጥረት ተድርጓል፡፡ ስለዚህ ወደ ረድፍ ገብቷል፡፡ አሰላለፉን አስተካክሏል፡፡ ግምገማው በጣም ትልቅ ውጤት ተገኝቶበታል፡፡ ሁሉም አሸናፊ ሆኖ ወጥቷል የተባለው ለዚህም ነው ፡፡ አሸናፊው መስመር ነው፡፡ ተሸራርፈው እና ተዳክመው የነበሩ እሴቶቻችን ተመልሰው መጥተው መድመቅ ጀምረዋል ብለዋል፡፡
የኢህአዴግ ልምድም ይሄው ነው፡፡ ብዙ ችግሮች ሊያጋጥሙት ይችላሉ፡፡ ልምዱ ምንድን መማር ነው፡፡ ራሱን ከፈተሸ ይወጣል፡፡ ስለዚህ አሁን የጀመርነው የዚህ አመላካች ነው ፡፡ ተግባር ይቀጥላል፡፡ እንደተገለጸው በርካታ መድረኮችም አሉ፡፡ የመጀመሪያው ሥራ ሰበብ አስባብ የማምጣት ሳይሆን ራስን መፈተሽ ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ተጠያቂ እኔ ነኝ ብሎ ኃላፊነቱን እወስዳዋለሁ እያለ፡፡
ይህ ማለት ግን ሌሎች እንቅፋት አልተፈጠሩም ማለት አይደለም፡፡ የውጭም እንቅፋቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ችግሩ ግን እነሱ አይደሉም ፣እነሱን ስርዓት ማስያዝ የነበረብኝ እኔ ነኝ፤ ጥፋቱ የኔ ነው፤ያልመለስኩት ብዙ ጥያቄ ስላለ ዋናው ተጠያቂ እኔ ነኝ እያለ ነው፡፡ ስለዚህ የመጀመሪያው ይሄ ነበርና ድርጅቱ ወስኗል፤ ይሄ አመራር አሰላለፉን አስተካክሏል ፡፡ ወደ ቦታው እየገባ ነው፡፡
ኢህአዴግ ህዝብን ነው የማገለግለው ብሏል፡፡ ይህም በጣም ትልቅ ውሳኔ ነው፡፡ ችግሩን አብጠርጥሮ አይቶታል፡፡ይህ ጉዳይ ከፍተኛ አመራሩ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ሊነጋገርበት የሚችል አጀንዳ መሆኑን እናውቀዋለን፡፡
በእኛ አመራር ስንት ሰው እኮ ሞቷል፤ተፈናቅሏል ፡፡ ከዚህ የማይማር ምን ይባላል፡፡ ስለዚህ ችግሩ በጣም ከባድ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ይሄ መታየቱ በራሱ ያሳስባል፡፡ ስለዚህ ሁኔታውን ቀለል አርገን መውሰድ አይኖርብንም፡፡ በጣም ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን መወሰን ያስፈልጋል፡፡ ሀላፊነት መውሰድ የግድ ነው፡፡
ይህን ችግር ለመፍታት ልምዱ ፣መስመሩ እና ህዝባዊነቱ ይጠቅማል፡፡ አሁን እየታደሰ ያለውም ይሄው ነው፡፡ እራሳችን እናድስ ያልነውም ለዚህ ነው፡፡ በጥልቀት መታደስ ማለትም ይሄው ነው፡፡ ተደጋግሞ እንደተገለ ጸው፤ብቻችንን እንሰራዋለን ማለት ግን አይደለም፡፡ በድርጅትም ብዙ ሥራ አለ፡፡ ከህዝብ ጋርም ብዙ ሥራ አለ፡፡ ቀጣይ ስራዎች አሉ፡፡ ግን እየሰራን እንታደሳለን፡፡ እየታደስን እንሰራለን ፡፡
ስለዚህ ይሄ ብዙ መማማል የሚያስፈልገው ነገር አይደለም፡፡ ለውጡ ራሱ መጥቷል፡፡ ይህን አሁን በመድረኩ ኢህአዴግ አሳይቷል፡፡ ይሄን መድረክ ማየት ራሱ በቂ ነው፡፡ ከባለፈው የተሻለ ምን ያህል የራሱን ኃላፊነት ወስዷል፤ ምን ያህል ራሱን ተጠያቂ አድርጓል፤ ይሄኛው የተለየ ነው፡፡ ወደ ኋላ ተመልሰን ማየት እንችላለን፡፡ ይሄ አዲስ ምዕራፍ እና ታሪክ ስለሆነ የተለየ ነው፡፡
እንዳልነው በዚህ መድረክ ብቻ ልንቋጨው አንችልም፡፡ በቀጣይ ይሄ ጅምር በራሳችንም፣ ከህዝቡ ጋርም ሆነን መጠናከር አለበት፡፡ አጀማመሩ የሚባለውን ችግር ለመፍታት ምቹ ሁኔታ፣ ጥሩ መነሳሳት፣ ቁጭትም ያለበት እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
የኦህዴድ ሊቀመንበር አቶ ለማ መገርሳ በበኩላቸው የሚወሰደውን ሃላፊነት በተመለከተ እንዳብራሩት ይህ ሥራ አስፈጸሚ ገዥውን ፓርቲ ፖለቲካውን በመምራቱም፣ የመንግስቱን ሥራ በመምራቱም በኩል ትልቅ ኃላፊነት ያለበት አካል እንደመሆኑ መጠን ለዚህ ሁሉ ችግር ባለቤቱ እኔ ነኝ ሲል እነዚህን ነገሮች ከግምት በማስገባት ነው ብለዋል፡፡ ስለዚህ ተጠያቂ ነው፡፡ ቀጣይ ደግሞ እያንዳንዳችን በግል ኃላፊነቶች አሉብን፡፡ በኃላፊነታችን ልክ እና በጥፋታችን ልክ የምንጠየቅበት አግባብ ይኖራል፡፡
በዚህ ግምገማ ያሸነፈው ፓርቲ ማን ነው የሚለው ቀደም ሲልም ወደዚህ ግምገማ የገባነው ለውድድር አይደለም ብለዋል፡፡ አንዱን ሻምፒዮና ለማድረግ አይደለም፡፡ አንዱ ሻምፒዮና ሆኜ ወጣሁ ቢልም የሚሸለመው ሜዳሊያ አይኖርም፡፡ ነገር ግን በግልጽ መታየት ያለበት፤ ወደዚህ ግምገማ ስንገባ በተለያየ ስሜት ውስጥ ሆነን ነው፡፡
የቆምንለትና የታገልንለት ህዝብ አለ፡፡ እየሰራንም፤ እየወደቅንም እየተነሳንም ብዙ ችግር አጋጥሞናል፡፡ ሀገሪቷ በቀውስ ውስጥ ትገኛለች፡፡ ሀገርን ህዝብን እንደምንመራ ሁሉ ሁላችንም ኃላፊነት እንደሚሰማው አመራር ሆነን ወደዚህ ግምገማ የገባነው ይህን ሁሉ ስሜት ይዘን ነው፡፡
እኔ የግምገማውን ሂደት በሙሉ በቀጥታ ስርጭት ለህዝቡ በለቀቅን ኖሮ እላለሁ፡፡ መቋሰሉ፣ የችግሩ ጥልቀት ምን ያህል እያንዳንዳችንን እንደተሰማን ህዝቡ ቢያይ ኖሮ ፍርዱን መስጠት በቻለ ነበር እላለሁ፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው አንዱን ለማጀገን እና ሌላውን ሎሌ ለማድረግ አይደለም፡፡ በየዕለቱ ህይወት እየጠፋ ነው፤በእጃችን ደም እየፈሰሰ ነው፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከህጻን እስከ አዛውንት ከቀዬያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ሀገሪቷ ቀውስ ውስጥ ወደዚህ ግምገማ የገባነው የግለሰብ ክብር እና ስልጣን ገደል ይግባ፤ ከሀገር አይበልጥም ብለን ነው፡፡ የሁላችንም ስልጣን እና ክብር ከሀገር በታች ነው፡፡ በዚያ ደረጃ እናያለን የሚል ስሜት ይዘን ነው ወደ ግምገማው ገብተን ስናይ የቆየነው፡፡
ሀገራችንን እናድን፡፡ አደገኛ ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ሁለት ምርጫ ነው ያለን፤ የመፍረስ ወይም የመዳን፡፡ በዚህ መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆመን አሸናፊን እና ተሸናፊን የምናማርጥበት ሁኔታ የለም፡፡ ያለውን ሁኔታ በግልጽ ተነጋግረን የምንነቅፈው በግልጽ እንዲነቀፍ፤ የምናስተካክለው በግልጽ እንዲስተካከል ማድረግ ነበረብን፡፡ በዚህ ረገድ የሚገባንን አድርገናል ብለን እናስባለን፡፡
ማናችንም ሳንሸማቀቅ ማድረግ ያለብንን፤ እንደ ኦህዴድ በዚህ ውስጥ ማድረግ የሚገባንን ትግል ሁሉ በቁርጠኝነት አድርገናል ብዬ አስባለሁ፡፡ ደኢህዴን ማድረግ የሚገባውን ትግል አድርጓል ብዬ አምናለሁ፡፤ ብአዴን ማድረግ የሚገባውን ትግል አድርጓል፤ ህወሃትም እንደዚሁ፡፡ ቀጥለን ደግሞ መስራት ይኖርብናል፡ በተግባር ለህዝቡ ማሳየት አለብን፡፡ ይህን ማድረጋችንን ያየነው እኛ ነን እንጂ ህዝቡ አላየም፡፡ ህዝቡ የሚያየው ከተግባራችን ነው፤ በውጤታችን ማሳየት አለብን፡፡ ስለዚህ አንዱን የማንገስ እና አንዱን የመጣል ጉዳይ ውስጥ አልቆየንም፡፡ ይህን የሚፈቅድ ሁኔታ ውስጥ አይደለም፡፡ በእርግጥ የተሸነፉ አካላት ግን አሉ፡፡ መድረካችን ላይ ቢሆንም እውነት አሸንፏል፤ ውሸት ደግሞ ተሸንፏል፡፡ ቡድን እና ኔት ወርክ እያደራጁ ስልጣናቸውን መደላድል አድርገው ለሀገሪቱ ሳይሆን ለራሳቸው ጥቅም የቆሙ ተሸንፈዋል፤ ቡድንን ፈጥረው የሚለፋውን እየገፉ ከዚህ የበለጠ ለመጠንከር የፈለጉ ቡድኖች በግልጽም በዚህ መድረክ ላይ ተሸንፈዋል፡፡
ጉዳቱ የጋራችን ስለሆነ ይህን ማድረግ የሁላችንም ግዴታ ነው፡፡ በስሜት የሚደረጉ ነገሮች ውጤታቸው መልካም አይሆንም፡፡ ሁሉም ነገር በምክክርና በንግግር ሲሆን ውጤቱ ያምራል፡፡
የሃገራችንን የቅርብ ጊዜ ታሪክ መለስ ብለን ማየቱም በጣም ያስፈልጋል፡፡ በኢሃፓ ዘመን በዚህ ሀገር ውስጥ ስንት ጭንቅላት ጠፍቷል፡፡ አንድ ትውልድ ብቻ ሳይሆን የተሻለ ትውልድ በከንቱ ጠፍቷል፡፡ ይህ ጥቁር ጠባሳ በሃገራችን እንዲደገም አንፈልግም፡፡ መግባባትም ሆነ መለያየት በንግግርና በምክክር ብቻ መፈጸም ያለበት፡፡ በጉልበትና በጉልበት የሚሆነን ነገር አያምርም፡፡ ውጤቱንም ኪሳራውንም አይተነዋል፡፡ ያ ታሪክ መደገም የለበትም፡፡ ሁሉንም ነገር ለመቀበልም ለመቃወምም ንግግርና ንግግር መተቻችት መከራከር ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ነው ወደዚያ እንዳንመለስ ዴሞክራሲውን እናስፋ፤ ፣ሰው የሚናገርበትን የሚደመጥበትን ሃሳቡን የሚያንሸራሽርበትን ዕድል እናስፋ የምንለው፡፡ ሃገራችንን ለማዳን ሁላችንም በትእግስትና ሃላፊነት በተሞላበት መንፈስ መስራት ይኖርብናል፤ይህ የሁላችንም ሃላፊነት መሆኑን በዚህ አጋጣሚ እገልጻለሁ፡፡
የአራቱ ብሄራዊ ድርጅቶች አመራሮች በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ የሰጡትን ማብራሪያ በቀጣይ እትማችን ይዘን እንቀርባለን፡፡

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።