መልዕክት ከኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ማዕከላዊ ኮሚቴ

08 Feb 2018

የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ማዕከላዊ ኮሚቴ የተጀመረው የለውጥ ጉዞና የወደፊት አቅጣጫ ለ10 ቀናት ዝርዝር ግምገማ በማድረግ ትናንት ማምሻውን በስኬት አጠናቋል።
ግንባራችን ኢህአዴግም በጥልቅ ለመታደስ የጀመረውን ንቅናቄ ዳር ለማድረስ በቅርቡ ራሱን ገምግሞ አቅጣጫ ማስቀመጡ የሚታወስ ሲሆን ከግምገማው በመነሳትም ሀገራችን ኢትዮጵያና ክልላችን በፖለቲካዊ፤ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስኮች ያለችበትን ሁኔታ በዝርዝር በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫ አስቀምጧል።
አስር ቀናት በፈጀው የአሁኑ ውይይታችን፣ የሕዝባችን ሰላምና አብሮነት በምንም መልኩ አደጋ ውስጥ እንዳይገባ የክልላችን ሕዝቦች እና መሪ ድርጅቱ ኦህዴድ በቅንጅት በመስራት የሀገራችንን ሕልውና መታደግና የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ በስኬት እንዲጠናቀቅ የተቀናጀ ጥረት ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን አጽንኦት ሰጥቶ ተወያይቷል። ድርጅታችን ከሚታወቅባቸው መለያ ባህሪያቱ እያንዳንዱ ጉድለቶቹን ያለማመንታት መቀበልና ለማረም ጥረት ማድረግ መሆኑ ይታወቃል። ይህ የዴሞክራሲያዊ ድርጅት ባህሪ በመሆኑ ከሕዝብ የሚነሱ ቅሬታዎችን ማድመጥ፣ ሕዝቡን ከልብ ይቅርታ የመጠየቅና የእርምት እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ መሆኑን በዝርዝር በመምከር አቅጣጫ አስቀምጧል።
የፌዴራል ሥርዓቱን አደጋ ውስጥ ሊጥሉ የሚችሉ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶችን ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ለይቶ አፋጣኝ እርምጃዎችን በመውሰድ የሕዝቡን መሻት ማሳካት ለነገ የማይባል ጉዳይ መሆኑን በዝርዝር ተመልክቷል፡፡ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል፣ አሳታፊ የፖለቲካ ስርዓት፣ ሰላምና ፍትህ እንዲሰፍን በጥብቅ ዲስፕሊን በመስራት የሕዝብ እርካታን ማረጋገጥ ጊዜ የማይሰጠው መሰረታዊ አጀንዳ ስለመሆኑ መክሯል፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በመተባበር የሀገራችንን ቀጣይ ጉዞ የማቅናት ሚናውን ዛሬም እንደትናንቱ መጫወት እንደሚገባውም ተወያ ይቷል፡፡
በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል ያለውን ግንኙነት በዴሞክራሲ አግባብ በማጠናከር የጋራ አላማችንን ለማሳካት ርብርብ ማድረግና የሀገሪቱን ሕልውና ከአደጋ መከላከል እንደሚገባ በዝርዝር በመምከር አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
የፌዴራላዊ ሥርዓታችንን አደጋ ላይ የጣሉ ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን፣ ሕዝቡ በመሪ ድርጅቱ ላይ እንዲያምጽ ያስቻሉ የመልካም አስተዳደር እጦቶችን፤ስልጣን ህዝብን ማገልገያ መሳሪያ መሆኑን በመዘንጋት በርስትነት ይዞ ለግል ምቾትና ጥቅም ቅድሚያ መስጠትን፣ በነጻነት ተዘዋውሮ የመስራት መብትን ነፍጎ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሕዝቦችን እስከማፈናቀል የደረሰ ድርጊትን፤ በኢንቨስትመንት ስም የመንግሥትና የህዝብ መሬት መመዝበሩን፤ እንዲሁም የሕዝቦች ሰላምና ፀጥታ መደፍረሱን እና የመሳሰሉትን እየተፈጸሙ ያሉ አደገኛ ድርጊቶችን ሕዝቡን ባሳተፈ መልኩ አምርሮ በመታገል የሀገራችንን ሕልውና መታደግ ልዩ ትኩረት የሚሹ አበይት ጉዳዮች መሆናቸውን በዝርዝር ተመክሮባቸ ዋል፡፡
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተከሰቱ ግጭቶች የበርካታ ዜጎች ሕይወት ጠፍቷል፤ ንብረት ወድሟል፤ የሕዝቦች በሰላም ውሎ ማዳር፣ ወጥቶ መግባት ከፍተኛ ስጋት ላይ ወድቋል፡፡ ለእነዚህ ችግሮች መከሰት ኃላፊነቱን ወስዶ እርማት ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ አጽንኦት ሰጥቶ በመምከር አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
የፌዴራል ሥርዓቱን አደጋ ላይ በመጣል ግላዊና ቡድናዊ ጥቅሞችን ለማስጠበቅ በንጹሃን ዜጎች ሕይወት ላይ አደጋ ያደረሱና በታሪካችን ታይቶ የማይታወቅ ፀያፍ ድርጊቶችን የፈጸሙ ኃይሎች በሕግ እንዲጠየቁ ለማድረግ፣ እንዲሁም መሰል ስህተት እንዳይደገምና የሕግ የበላይነት በመላ ሀገሪቱ እንዲሰፍን ለማስቻል ሕዝቦችን በማሳተፍ ትግሉን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር የግድ መሆኑን ከግንዛቤ አስገብቶ ማዕከላዊ ኮሚቴው አቅጣጫ አስቀምጧል።
ቀንደኛ የሕልውናችን ጠላት ድህነት መሆኑ ቢታወቅም ይህንን ጠላት ለመዋጋት በመንግሥት፣ ድርጅትና ሕዝብ ትስስር ሊሰራ እንደሚገባውና አዳዲስ ሃሳቦችን እያፈለቀ አመራር የመስጠት ጉዳይ ከድርጅታችን እንደሚጠበቅ ከስምምነት ላይ ተደርሷል።
ሀብት ማመንጨት ብቻ ሳይሆን ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ማስቻል፣የሀብት አጠቃቀምንም ከብክነት የጸዳ ማድረግ፣ ግልጸኝነትና ተጠያቂነትን የሚያረጋግጥ አሰራር በማስፈን ሕዝቡ እንዲያለማ ከማስቻል በዘለለ የመቆጣጠር ሚናውንም ከፍ ማድረግ እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
አዳጊ ኢኮኖሚን የሚያንኮታኩቱ መጥፎ ልማዶችን በተለይም ሙስና፣ ኮንትሮባንድ፣ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ፍላጎቱን ማኮላሸት፣ የአቅርቦት ሰንሰለቱን ማስተጓጎል፣ ማንኛውም የገበያ ፍትሃዊነትን የሚያዛቡ አሉታዊ ተግባራትን አጥፍቶ በምትኩ በዘመናዊነት የታገዘ ፍትሃዊ አሰራርን መዘርጋት፣ ያልተገባ የጥቅም ትስስር ያላቸውን ሰንሰለቶች በጥናት ላይ በመመስረት የመበጣጠስ ተግባር በተቀናጀና የሪፎረም ሥራውን በሚያሳልጥ መልኩ እንደሚፈፀም አቅጣጫ ተቀምጠዋል፡፡
ሕገመንግሥታዊ ድንጋጌዎች ሳይሸራረፉ ተግባር ላይ እንዲውሉ፣ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ዜጎች ካለምንም ስጋት ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው እንዲሰሩ በማስቻል በፍትህ ሥርዓቱና በፖሊሲ ሥርዓታችን ላይ ተጨባጭ ለውጥ ሊያስገኙ የሚችሉ ሁለንተናዊ ሪፎርም ማከናወን እንደሚገባ ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
ከክልሎች ጋር የጀመርነውን ህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ህግ መንግሥታዊነቱን ጠብቆ እንዲቀጥልና ፌዴራላዊ ሥርዓታችን ይበልጥ መጠናከር የሚችልበት ሁኔታ አጽንኦት ተሰጥቶት ተመክሮበታል፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ የመቻቻል ፤የመደጋገፍና አብሮ መኖር እሴቶችን ያዳበረ በመሆኑ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በመከባበርና በፍቅር አብሮ በመኖር የሁሉም ዜጎች መብት በእኩል እንዲከበር ከወንድም ሕዝቦች ጋር አብሮ መስራት ይጠበቅበታል፡፡ ጥላቻን በጥላቻ፣ክፉ ተግባርን በሌላ ያልተገባ ድርጊት መመከት ሊቆም ይገባዋል፡፡ በመሆኑም ተከሰቱ ለሚባሉ ችግሮች ሁሉ መፍትሄው ፍትሃዊና ሕጋዊ የትግል ስልትን መከተል መሆኑ ታምኖበት ከጥፋት ተግባራት በመታቀብ ኦሮሙማን በሚያጎላ አቃፊ መሆን እንደሚገባ ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሕዝቦች ጋር የነበረንን መልካም ግንኙነት በመመለስ እንደ ወንድማማች ሕዝቦች የባይተዋርነት ስሜት እንዳይፈጠር በሚያስችል መልኩ በታላቅ የኃላፊነት ስሜት እንዲመራ ጊዜያዊ ችግሮችን ፈተን ለዘላቂ የጋራ ጥቅሞቻችን በወንድማማችነት መንፈስ እንድንረባ ረብ የሶማሌም ይሁን ሌሎች ብህረ ብሄረሰቦች በኦሮሞ ባህልና የገዳ ሥርዓት ባስተማረን መልኩ በፍቅርና በአብሮነት እንዲኖሩ ለማስቻል ሕዝቡ የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ማዕከላዊ ኮሚቴው ጥሪ አቅርቧል፡፡
የሃሳብ ልዩነቶችን ማጥፋት አስቸጋሪ እንደሆነ እሙን ነው፡፡ ስለሆነም ሁል ጊዜ ለውይይትና ለክርክር አውድ ማስፋት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበ ታል፡፡ ፍላጎትን በውይይት እንጂ በኃይል የማስረጽ ዝንባሌ እንዳይታይ በቀጣይነት መስራት እንደሚያስፈልግም መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡
ዛሬ አድገው የሀገራቸውን ህዝብ ኑሮ በከፍተኛ ደረጃ ያሻሻሉ ሀገራት ታሪክ ሲመረመር በአገራዊ ጉዟቸው ውስጥ ሕዝባዊ አመጽን ያስተናገዱ፣ የወጣቶች ቁጣ የደረሰባቸውና መሰል አጋጣሚዎችን በዴሞክራሲያዊ መንገድ መቀልበስ የቻሉት የዘላቂ ልማት ባለቤት እንደሆኑ ታሪካቸው ያሳያል፡፡ በመሆኑም በወጣቶች ላይ የሚታየውን ፍትህ የመሻት ቁጣ ሀገርን በማያፈርስ መልኩ ከኃይል በፀዳ ሁኔታ ሰላማዊ የትግል ስልት እንዲከተሉ በማስተማር የዴሞክራሲ ባህልን ማዳበር አስፈላጊ መሆኑን ኮሚቴው ያምናል፡፡ ዋነኛ ሚናውም የተሻለች ሀገር ለቀጣዩ ትውልድ ማሸጋገር በመሆኑ የተሻለች ሀገር ብቻ ሳይሆን ብቁ ተረካቢ ወጣቶችን ማፍራት እንደሆነም ይገነዘባል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ እየታየ ያለው ድርቅ፣ ግጭት፣ስደት፣ የሕዝብ መብዛትያልተደራጀ ኢኮኖሚና ያልዳበረ የዴሞክራሲ ባህል ባለበት ሀገር ነገሮች እንዲባባሱ ከማድረግ አልፎ የሀገር ህልውናን አደጋ ውስጥ እስከመጣል እንደሚደርስ ታውቆ የተሻለች ሀገር የመፍጠሩና ብዙ ተረካቢ የማፍራቱ ተግባር በጥንቃቄና በኃላፊነት ስሜት እንዲከወን በዝርዝር ተመክሯል፡፡
ይህንንም ከማሳካት አኳያ ቅድሚያ ከተሰጣቸው ተግባራት መካከል ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ ወገኖችን ከጊዜያዊ መጠለያ ወደ ቋሚ ቦታ ማስፈር፤ የወጣቶችን የሥራ አጥነትን በመቀነስ የኑሮ ሁኔታቸውን ማሻሻል፤ የመልካም አስተዳደርና ብልሹ አሰራሮችን ማስተካከል፤ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓትን ማዘመን፤ፍርድ ቤት፣ አቃቤ ህግ፣ ፖሊስ፣ የወረዳና የቀበሌ መዋቅሮችን መልሶ ማደራጀት፤ ሰላምና ፀጥታ በማስከበር የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ይገኙ በታል፡፡
በመላ የሀገራችን ህዝቦች ይሁንታ አፋን ኦሮሞ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ድርጅታችን ይሰራል፡፡ በተጨማሪም በሂደት ላይ ያሉና ያልተጠናቀቁ መሰረታዊ የህዝብ ጥያቄዎች በጥብቅ ዲስፕሊን እንዲፈጸሙ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡
በድርጅቱ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ፤መድረኩ የሚጠይቀውን የትግል ልክ በብቃት ለመፈፀም፣ በቀጣይም ጥንካሬውን አጎልብቶ መጓዝ ይችል ዘንድ 14 የኢህአዴግ ምክር ቤት አባላት እንዲተኩ እና 4 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትም እስከሚ ቀጥለው ጉባዔ እንዲታገዱና አንድ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል በማስጠንቀቂያ እንዲታለፍ የወሰነ ሲሆን፣ የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ የማስፋትና የአመራሩን የሃሳብና የተግባር አንድነት ይበልጥ ማጠናከር በቀጣይነት እንዲሰራበት ተመክሯል፡፡
ለኦሮሞ ሕዝብ
ለዘመናት ትከሻህ ላይ ተጭኖ የነበረውን የጭቆና ቀንበር ለመስበር ሁልጊዜም ታሪክ እየዘከረው የሚኖር አኩሪ መስዋዕትነት ከፍለሃል፡፡ በከፈልከው መስዋዕትነት ከሌሎች ወንድሞችህ ጋር በመሆን አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመፍጠር፤ እኩልነት፣ ፍትህ፣ ዴሞክራሲና ሁሉን አቀፍ መብቶች የተረጋገጡባትን የበለፀገች ሀገር ለመገንባት መሰረት ጥለሃል፡፡ በተጀመረው የግንባታ ሂደት ውስጥ የመጡ ተስፋ ሰጪ ድሎች እንዳሉ ሁሉ የጭቆና መሰረት የሆኑ አስተሳሰቦችና አሰራሮችን የሚፈጥሩ አዝማሚያዎ ችም ይታያሉ፡፡ በእነዚህ አዝማሚያዎች ላይም የጀመርከውን ትግል አጠናክረህ መቀጠል ያንተም ሆነ የወንድም ሕዝቦች የሕልውና ጉዳይ ነው፡፡
የመደብ ጭቆና ምን ያህል አስከፊ እንደሆና አዎንታዊ ለውጥን እንደሚገታ ባለፈው ታሪክህ ካንተ በላይ የሚገነዘብ የለም፡፡ በአሁኑም ሰዓት ተመሳሳይ መደባዊ ጭቆና ዳግም በሀገራችን እንዳያቆጠቁጥ ትግልህን አጠንክረህ መቀጠል ይገባሃል፡፡
በሁሉም የታሪክ ምዕራፎች ኢፍትሃዊነትና ጭቆናን ባለመቀበል ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር በመሆን መስዋዕትነት እየከፈልክ ወደ ድል ስትራመድ እንደነበረው ሁሉ አሁንም ሀገራችንን የገጠሟትን ፈተናዎች በታጠቅከው የገዳ ስርዓት ቱባ ባሕል መሰረት ብሄር፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን በማቀፍና ከጎንህ በማሰለፍ ትግሉን ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር የአዲሲቷን ኢትዮጵያ ህልውና በማስጠበቅ ለውጧን ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ የማስቀጠል ኃላፊነትህን እንድትወጣ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ለኦሮሚያ ክልል ወጣቶች
የክልላችንም ሆነ ሀገራዊ ለውጦች ያለወጣቱ ተሳትፎና መሪነት የሚታሰብ አይደለም፡፡ በዚሁ መሰረት እስካሁን በሀገራችን የመጡ ለውጦች በወጣቱ ተሳትፎና አኩሪ መስዋዕትነት የመጡ መሆናቸውን ኦህዴድ ይገነዘበዋል፡፡ ወጣቶቻችን በሁሉም መስክ የተጀመሩ የለውጥ እንቅስቃሴና መልካም ጅምሮች ወደ ላቀ ድል እንዲሸጋገሩ በባለቤትነት መሳተፍና ኃላፊነትን መወጣት፣ ይህንንም በተደራጀ መልኩ መተግበር ይገባዋል፡፡ ወጣቱ በሁሉም መስክ የሚያደርገውን ትግል ምክንያታዊና ሳይንሳዊ በሆኑ ሃሳቦች እየተመራ፤ ዴሞክራሲያዊነትን በጠበቀና ተደማሪ ለውጦችን በተንከባከበ መልኩ የሁሉም መብት ተከብሮ፣ የሀገራችንም ህልውናና የክልላችን ሰላም እንደተጠበቀ የሚቀጥልበት አካሄድ እንዲረጋገጥ ግንባር ቀደም ኃላፊነቱን እንዲወጣ ድርጅታችን ኦህዴድ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ለኦሮሞ ምሁራን
በሁሉም የታሪክ ምዕራፍ ላይ የኦሮሞ ሕዝብ ባለፈበት የትግል ሂደት ውስጥ እናንተም መስዋዕትነት ከፍላችኋል፡፡ አሁንም በደረስንበት የትግል ምዕራፍ ውስጥ ከሕዝባችሁና ከመሪው ድርጅታችሁ ኦህዴድ ጋር በመሰለፍ ዋንኛው ሥራ የሆነውን ሃሳብን የማፍለቅና የትግሉን አቅጣጫ በጥናትና በምርምር የማሳየት የማይተካ ሚናችሁን እንደሁል ጊዜው መወጣት ይኖርባችኋል፡፡ ድርጅታችን ኦህዴድ፣ ምሁራንን ባላቸው አደረጃጀትም ሆነ በግል ክህሎታቸው፣ እውቀትና የአመራር ብቃትም ጭምር አብሮ ለመስራት የጀመረውን ሥራ በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ አጠናክሮ ለመቀጠል ወስኗል፡፡ በዚሁ መሰረት የተከበራችሁ የኦሮሞ ምሁራን የጀመራችሁትን ጠንካራና ተኪ የሌለው ሚናችሁን በመወጣት አጠናክራችሁ ትግሉን እንድትቀጥሉ፣ ለስኬትም እንድትረባረቡ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ለኦሮሚያ ክልል መንግሥት ሠራተኞች
የኦሮሞ ሕዝብ ባደረገው ትግል የራሱን ክልል መስርቶ ያሉበትን ችግሮች ለመፍታትና ራዕዮቹን ለማሳካት ትልቅ የመንግሥት መዋቅር ዘርግቷል፡፡ በዚህ መዋቅር ውስጥ የሕዝባችንን ችግር መፍታት የሚቻለው ከእውቀትና ክህሎት በተጨማሪ ጠንካራ ዲስፕሊን ባለው የመንግሥት ሠራተኛ ነው፡፡ በመሆኑም፣በመንግሥት መዋቅር ውስጥ እየፈጠረበት ያለውን የመብት ጥሰት፣ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ እየተስፋፋ ያለው ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ኢ-ፍትሃዊነትና የዴሞክራሲ እጦት ችግሮችን ለመፍታት የክልላችን መንግሥት ሠራተኞች ቁልፍ ሚና አላችሁ፡፡ሕዝባችንን አንገት ያስደፋውን ዋነኛ ችግሩን በመቅረፍ ብልጽግናን ለማስፈን፣ የማስፈፀም አቅምን ለማጎልበት፣ቀን ከሌሊት ተግታችሁ የመስራት ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ለኦሮሚያ ክልል የፀጥታ አካላት
በክልላችን ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ ከሕዝባችን ጋር በተለይም ከወጣቶች ጋር በመቀናጀት የሕዝባችንን ጥቅምና ሀብት ሲዘርፉ የነበሩ ኮንትሮባንዲስቶች ላይ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ እንዲሁም በክልላችን የተጀመረውን ሪፎረም ለማደናቀፍ ዝርፊያ ድርጊታቸውን ማስቀጠል የሚፈልጉ የተደራጁ ኪራይ ሰብሳቢዎች የከፈቱትን ጥቃት ለመመከት በግንባር ቀደምነት ተሰልፋችሁ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍላችኋል፡፡ በዚሁም የአዲሲቷን ኢትዮጵያ ሕልውና እንዲቀጥል ድርሻችሁን በመወጣት ከአደጋ እየታደጋችሁ ትገኛላችሁ፡፡
የኪራይ ሰብሳቢዎች ቡድን በመንግሥት ስልጣን የመክበር አባዜ ከስር ተነቅሎ፣ የሕግ የበላይነት ሰፍኖ እስኪሸነፍ ድረስ የጀመራችሁትን ትግል ሕዝብን በማሳተፍ በከፍተኛ ዲስፕሊን ሕዝባዊ ኃላፊነታችሁን መወጣት ይገባችኋል፡፡ በክልላችን አስተማማኝ ሰላምና የሕግ የበላይነት የተረጋገጠበት፣ እንዲሁም ፍትህ የሰፈነበት እንዲሆንና ዜጎቻችን መብታቸው ተከብሮ ሥርዓት አልበኝነት እንዳይኖር የተሰጣችሁን ተቋማዊ ኃላፊነት ከሕዝብ ጋር በመቆም ሕዝባዊ በሆነ መንፈስ እንድትወጡ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ለኦህዴድ አባላት
ተንሰራፍቶ የቆየውን ጭቆና ለማስወገድ ሕዝባችን ሲያካሂድ የነበረውን መራራ ትግል ውስጥ የመርነት ሚናን ተቀብለህ መስዋዕትነት በመክፈል የዛሬው ምዕራፍ ላይ እንዲደርስ የበኩልህን አስተዋፅኦ አበርክተሃል፡፡ ጠንካራ ድርጅት ያለ ጠንካራ አባል ሊታሰብ አይችልም፡፡ ኦህዴድ ያለበትን ታሪካዊ ኃላፊነት እንዲወጣ አሁን በደረሰበት የትግል መድረክ የሚመጥን ቁመና እንዲኖረው ለማስቻልና ለማስቀጠል የድርጅታችን አባላት የድርጅታችሁን አላማ በጥብቅ ዲስፕሊን ለማሳካት ቀን ከሌሊት መታገል ይገባችኋል፡፡ ሕዝባችን በተለያየ ደረጃ እያደረገ ባለው ትግል ውስጥ አባሎቻችን በግንባር ቀደምነት በመሳተፍና በመምራት ችግሮችን በኃላፊነት መፍታት ይገባቸዋል፡፡ አሁን የደረስንበት የትግል ምዕራፍ የሚጠይቀውን መስዋዕትነት በቅድሚያ በመክፈል ለሌሎች ምሳሌ በመሆን የድርጅታችሁን ተልዕኮ በተሰማራችሁበት መስክ ሁሉ በማሳካት የሕዝባችንን ጥያቄ በአፋጣኝ እየመለሰ፣ ትግሉን በግንባር ቀደምነት በመምራት አዲሲቷን ኢትዮጵያ እውን የማድረግ ኃላፊነቱን የሚወጣ፣ ጠንካራና ከለውጥ ጋር ራሱን የሚያሳድግ ድርጅት እውን እያደረጉ መጓዝ ትኩረት የሚሻ በመሆኑ ይህንንም በብቃት መወጣት ይገባችኋል፡፡
በውጭ ሀገራት ለሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች
በኦሮሞ ሕዝብ የለውጥ ጉዞ ውስጥ ባላችሁ እውቀትና ሀብት በተደራጀም ሆነ ባልተደራጀ መልኩ የበኩላችሁን አስተዋጽኦ ለመወጣት ስታደርጉ የነበረውን ርብርብ የሚፈታተኑ ሁኔታዎች እንደነበሩ እና መድረኮችም አስቸጋሪ እንደነበሩ ኦህዴድ ይገነዘባል፡፡ በሕዝባችን አንድነትና ሁለንተናዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ በእውቀት፣ በቴክኖሎጂ፣ባላችሁ ተሞክሮዎችና ትስስር፣ በሀብትና በመሳሰሉት ሁሉ እንድትሳተፉና የሕዝባችንን ችግር በጋራ እንድንፈታ፤ የሚያስፈልጉ ሁኔታዎችም እንዲመቻቹ ኦህዴድ ጠንክሮ እንደሚሰራ ሊያረጋግጥ ይወዳል፡፡ በዚሁ መሰረት በውጭ ሀገር የምትኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች በሕዝባችን ጥቅም ላይ ያለምንም ድንበርና ልዩነት በጋራ እንድንሰራ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ለኢህአዴግ አባል ድርጅቶች
ድርጅታችን ኢህአዴግ፣በሀገራችን ሕዝቦች ላይ የተጫነውን ፀረ-ዴሞክራሲ፣ ድህነት፣ የመልካም አስተዳደር እጦትና ኋላቀርነትን ለመፍታት ባደረገው እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ ድሎችን ማስመዘገብ የጀመረው በውስጡ ያለውን ችግር በተከታታይ በመፈተሽና በመፍታት ላይ ነው፡፡ በቅርቡ በኢህአዴግ ደረጃ በተደረገ ግምገማ በእህት ድርጅቶቹ መካከል የተፈጠረው ያልተገባ ግንኙነት በሂደትም ወደ ጥቅም ቡድንተኝነት እያደገ በመምጣቱ የነበረውን ግንኙነት እያሻከረ እንዲሄድ አድርገዋል፡፡ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴም ጉዳዩን በጥልቀት በመገምገም ማንኛውም ግንኙነቶች መርህና መርህ ላይ ብቻ እንዲመሰረቱና ዴሞክራ ሲያዊ ትግልን ማዕከል ያደረጉ እንዲሆኑ ለማስቻል ትኩረት ሰጥቶ ተወያይቶበት አቅጣጫ አስቀም ጧል፡፡ በዚሁ መሰረት የእህት ድርጅቶች አሁን በደረስንበት የትግል ምዕራፍ በግንባራችን ኢህአዴግ ተገምግመው አቅጣጫ የተቀመጠባቸውን ጉዳዮች ያለምንም መሸራረፍ እንዲፈፀሙና የሕዝባችንን ጥያቄ ለመመለስ ከመቼውም ጊዜ በላይ በአንድነት ርብርብ እንድናደርግ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ለተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች
በብዝሃነት ለተገነባች ሀገራችን ኢትዮጵያ ዴሞክራሲ የህልውና ጉዳይ መሆኑ እሙን ነው፡፡ እንደ ነብር ዥንጉርጉር የሆነው የእርስ በርስ ግንኙነታችን የሃሳብ ልዩነትን ማስተናገድ የሚያስችል አሰራርና ባህል ማዳበር ያስፈልገዋል፡፡ ከኃይል የፀዳ፣ በውይይትና በምክክር የሚያምን፣ ይበልጥ ለሀገር የሚበጅ ሃሳብ የሚፈልቅበት የውይይት ባህል እንዲዳብር የፖለቲካ ድርጅቶች ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ በዚህ ወሳኝ ወቅት የሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች አስተዋይነትና አርቆ አሳብነት የሚፈተ ንበት ጊዜ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ በመቀራ ረብና በመነጋገር የፖለቲካ ባህላችንን እንድናሻሽል ብሎም የሀገራችንን መፃኢ ዕድል በጋራ ማበጀት እንችል ዘንድ ተቀራርበን እንድንሰራ ድርጅታችን ይፈልጋል።
ዴሞክራሲ ለሀገራችን ሕዝቦች የሕልውና ጉዳይ ነው። ዴሞክራሲ ለመገንባት የሃሳብ ልዩነቶች የሚስተናገዱበት ማዕቀፍና አሰራር እንዲሁም ባህልና አስተሳሰብ እንዲዳብር የፖለቲካ ፓርቲዎች ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ኦህዴድ በሚገባ ይገነዘባል፡፡ የሀገራችን ሕዝቦች አማራጭ ሀሳቦች እየቀረቡለት በዴሞክራሲያዊ ሂደት የሚጠቅመውን ሃሳብ እንዲመርጥ፣ለፖለቲካ ፓርቲዎች በሕገመንግሥቱ የተቀመጡ ቃልኪዳኖች ያለመሸራረፍ እንዲተገበሩና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ኦህዴድ ከተቃዋሚ ፖለቲካ ፖርቲዎች ጋር በቅርበት እንደሚሰራ በጥልቅ ተወያይቶበት አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ በዚሁ መሰረት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያላችሁ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩነታችን እንደተጠበቀ ሆኖ በሀገራችንና በሕዝባችን የጋራ ጥቅም ላይ ከድርጅታችን ኦህዴድ ጋር አብራችሁን እንድትሰሩ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ለኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች
የኢትዮጵያ ብሔር፤ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በችግርም ሆነ በመልካም ጊዜ በጋራ ተፈትነው ትናንትን መሻገር ችለዋል። ለገጠማቸው ፈተናዎችም እኩል የታገሉና መስዋትነት የከፈሉ ህዝቦች ናቸው። ሀገራችን ህልው ሆና እንድትቀጥል ከማስቻላቸው ባሻገር በዓለም ታሪክ ውስጥ ጉልህ ቀለም እንዲኖራት አድርገው ለዛሬ ትውልድ አስረክበዋል። በአባቶቻችን ተጋድሎ የተገነባችውን ኢትዮጵያ እኛም አስውበንና አንድነቷን አስጠብቀን ለቀጣይ ትውልድ የማሻገር ታሪካዊ ኃላፊነት አለብን። በአንድ እጅ ማጨብጨብ አይቻልምና ይህን ኃላፊነታችን በብቃት እንድንወጣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከር፣ የጋራ እሴቶቻችንን በማጎልበት፣ የተጀመረው መልካም ጅማሮ ዳር እንዲደርስ እጅ ለእጅ ተያይዘን ለስኬቱ በጋራ እንድንረባረብ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያስተላልፋል።
የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ የ10 ቀናት የለውጥ ግምገማ ቆይታ ድርጅቱ ለአገራችን ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ጉዞ ስኬት እንዲሁም ለህዝቦች እኩል ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ በላይ በላቀ ቁርጠኝነትና ተነሳሽነት ለማከናወን ዝግጁነቱን ያረጋገጠበት መድረክ እንደሆነ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አረጋግጧል።

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።