ለሰላም የሃይማኖት አባቶች ሚና

10 Feb 2018

ኢትዮጵያ በህዝቦች መቻቻልና አብሮነት ከሚጠቀሱ አገራት መካከል ትመደባለች። በተለይም የሃይማኖት መቻቻልና አብሮ መኖር ሲነገር፤ የክርስትና እና የእስልምና ዕምነት ተከታዮች በታሪክ ቀዳሚ ተጠቃሽ ናቸው። ህዝቡ ለሃይማኖቱ ብቻ ሳይሆን ለየሃይማኖቱ መሪዎችም ከፍተኛ ክብር የሚሰጥና ትእዛዛቸውንም የሚያከብር ነው። በዚህም የተነሳ ትልልቅ አገራዊ ጉዳዮችና ችግሮች ሲገጥሙ ህዝቡን በማስተባበሩና በማንቀሳቀሱ ረገድ የሃይማኖት መሪዎች ሲጫወቱት የነበረው ሚና ከፍተኛ ነው። 

ዛሬም አገሪቱ የጀመረችውን ጉዞ ለማፋጠን መሰረታዊ የሆኑት ሰላም፣ መከባበርና ህብረት እንዲሰፍን ከሃይማኖት አባቶች እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ብዙ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ የሰላምና የሃይማኖት መቻቻል ተምሳሌት ሆና ዘመናትን ማስቆጠር የቻለች ሀገር መሆኗን በቅርቡ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ አለም አቀፍ የሃይማኖቶች የመቻቻል ሳምንት በተዘጋጀ ፕሮግራም ላይ ተናግረዋል። ይሄ ከጥንት ጀምሮ የነበረ የመቻቻልና ተከባብሮ የመኖር ባህል ዛሬም ድረስ ያለና በግልፅ የሚታይ ነው። ካለፉት ሁለት አስርት አመታት ወዲህ ደግሞ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ሁሉም ሃይማኖቶች ህገ መንግስታዊ እውቅናና ከለላ አግኝተው መንቀሳቀስ እንዲችሉ ሆነዋል።
ይህ ህገመንግስታዊ እውቅና ለሃይማኖት ተቋማት በየግላቸው ካጎናጸፋቸው መብት ባለፈ በአንድነት በመሆን ለሀገር ሰላም ልማትና ብልፅግና ብሎም ለህዝቦች አንድነት በጋራ እንዲሰሩ ሁኔታዎችንም ያመቻቸ ነው ብለዋል ፕሬዚዳንቱ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ያሉ ሃይማኖቶች በአንድ ጉባኤ ስር ተሰባስበው መንቀሳቀስ መጀመራቸውን በማስታወስ፤ ይህም ሃይማኖቶቹ ያላቸውን የእርስ በእርስ ትስስር እንዲዳብር ከማድረግ ባሻገር፤ በአንዳንድ ቦታዎች የሚታዩ አክራሪነትና ጽንፈኝነትን ለመዋጋትም የሚያስችል ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ጠቅሰዋል።
ሁሉም ሃይማኖቶች ለሰላምና ለአንድነት መስበክ የዘወትር ተግባራቸው ሊሆን ይገባል። በተለይም በሁሉም ሃይማኖቶች አስተምህሮ የሚደገፈውን ወርቃማ ህግ (ባንተ ላይ ሊያደርጉብህ የማትፈልገውን አንተም በሌሎች ላይ አታድርግ) በማጉላትና በተከታዮቻቸው ተቀባይነት እንዲያገኝ ማድረግ፤ እንዲሁም ለሰላም፣ ለመቻቻል፣ ለሰው ልጅ ክብር መስጠት ያለውን ጠቀሜታ በማሳየት ይበልጥ ተቀባይነት እንዲኖር ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሃፊ ፓስተር ዘሪሁን ደጉ በየሃይማኖቱ የተለያዩ አስተምህሮዎች ቢኖሩም ዋናው ተልእኳቸው ለህዝብ ሰላምን መስበክና ማምጣት ነው። በአገሪቱ የሃይማኖት ተቋማትን ተሳትፎ ሲያብራሩም፤ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ላለፉት ሰባት አመታት የሀገር ውስጥ የሃይማኖት ጉባኤን በማቋቋም የሃይማኖት መቻቻልና መተማመን እንዲፈጠር ሲሰራ ቆይቷል። በኢትዮጵያ ታሪክ የነበረው ሁኔታ ሲታይ እስካሁን ችግሮች ሲከሰቱ የእምነት ተቋማትን በመጠቀም ሲፈቱና እንዳይባባሱ ይደረግ እንደነበር መመልከት እንችላለን። ዛሬም ይሄን የቀደመ መልካም ተግባር በመከተል የውስጥ ችግሮች ሲከሰቱ መፈታት ያለባቸው በሃይማኖት አባቶች በእምነት ተቋማት በኩል መሆን ይችላል ይላሉ ።
እንደፓስተር ገለጻ፤ አንድን ሰው ሰላማዊና ለሌሎች የሚያስብና የሚኖር እንዲሆን የሚያደርገው የሃይማኖት እሴት ነው፡፡ በመሆኑም እነዚህን እሴቶች የየእምነቱ ሰባክያን ማስተማርና ማስፋፋት ይጠበቅባቸዋል። ከዚህም በላይ ለሰላም መታጣትና ለግጭት መነሻ የሚሆኑ በርካታ ነገሮች ቢኖሩም በአሁኑ ወቅት እንደ ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ዋነኞቹ ሙስናና የመልካም አስተዳደር መጓደል እንደሆኑ ግልጽ ነው። በመሆኑም እነዚህን ለማስቆም የሃይማኖት አስተምህሮዎች ትልቅ ጠቀሜታ አላቸው።
እነዚህ ሁለት ሀገራዊ ችግሮች በየትኛውም ሃይማኖት የተወገዙና የተነቀፉ ተግባራት ናቸው። ስለዚህም የሃይማኖት አባቶችና ሰባኪያን ሃይማኖታዊ እሴቶችን በአግባቡ ማስተማርና ማስጠበቅ ከቻሉ እነዚህን ነውር የሆኑ ተግባራት መቀነስ ይቻላል። እስከ አሁን በየሃይማኖቶቹ በተሰሩ ስራዎች በርካታ ለውጦች ማምጣት ተችሏል፡፡ በመሆኑም ይሄ እሴት እንዲቀጥል ሰባኪያንና መምህራንም እውነተኛውን መንገድ ማስተማር ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የሃይማኖት አስተምህሮዎች ለተከታዮቻቸው ቅርብና እምነት የሚጣልባቸው በመሆናቸው በጥንቃቄ ካልተመሩ ለሌላ አላማ ሊውሉ የሚችሉበትም አጋጣሚ ሰፊ በመሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ፓስተር ዘሪሁን ይገልፃሉ። ሁሉም ሃይማኖት ሰላምን ፍቅርን ለሰው ማሰብን ይሰብካል ነገር ግን እንደ መሪዎቹና ሰባኪያኖቹ በአንዳንድ አገራት እንደሚታየው በተሳሳተ መንገድ በመተርጎም ለእኩይ ምግባር የሚውሉባቸው ሁኔታዎችም አሉ። በመሆኑም የየሃይማኖቱ መሪዎች፤ ሃይማኖትን ተንተርሶ የተሳሳተ አመለካከት በመንዛት ለሌላ አላማ የሚያውሉ ግለሰቦችን ነቅተው መጠበቅ ይገባቸዋል ሲሉ መክረዋል።
በኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የሰላም ግንባታ መምሪያ ሃላፊ አቶ ማሞ ወጀጋ በበኩላቸው፤ የሰላም ጉዳይ የሃይማኖት ተቋማት ዋናው የቆሙለት አላማ ነው ይላሉ። ሃላፊው እንደሚያብራሩት፤ የሃይማኖት ተቋማት ተጠሪነታቸው ለፈጣሪ እንደመሆኑ ከአምላክ የተሰጣቸው ሃላፊነት በህዝቦች መካከል ሰላምን የማወጅ፣ ሰላምን የመስበክና ሰላምን የማስተማር ሊሆን ይገባል። የሚሰሩትም ስራ በህዝቡ ዘንድ ያላቸውን ተሰሚነት በሚመጥን መልኩ መሆን አለበት። በዚህም ጊዜ ከመስመር የወጣና የህዝብ ሰላም፣ ህብረትን የሚከፋፍል ካለ እንደ መንፈሳዊ አባትነታቸው የማስተማርና የመስበክ ብቻ ሳይሆን ገስጸው የመመለስ መንፈሳዊ ስልጣንም አላቸው።
በተመሳሳይ በመንግስትም በኩል ችግር ሲኖር የሃይማኖት አባቶች እንደ ፖለቲከኞች መንግስት ስልጣን ይልቀቅ ይሄን ያድርግ የማለት ሳይሆን ማስተካከል ያለበትን ጉዳይ ለህዝብ መስራት ያለበትን ስራ እንዲሰራ በፍቅር የማስተማርና የማሳወቅ ሃላፊነት አለባቸው። በተጨማሪም አንዳንድ ጊዜ በሌሎች ሰዎች ዘንድ እንደሚታየው ስሜታዊ በሆነ መንገድ ከሚደረጉ አላስፈላጊ ተግባራትም ወጣቶችን ማስተማርና መስመር እንዲይዙ ለሰላም ቅድሚያ እንዲሰጡ ማስተማር ይጠበቅባቸዋል።
በኢትዮጵያ በአብዛኛው ህዝቡ የሚከተላቸው ሃይማኖቶች ክርስትናና እስልምና መሆናቸውን የጠቆሙት ሃላፊው፤ እነዚህ ሃይማኖቶች ደግሞ ከጥንት ጀምረው አብረው የኖሩ መሆናቸውን በማስታወስ ህዝቡም በሰላምና በፍቅር አብሮ ዘመናትን ማሳለፉን ተናግረዋል። በመሆኑም አሁን ካሉት የሃይማኖት ተቋማትም ሆነ መሪዎችና መምህራን የሚጠበቀው ይህን የቆየ የፍቅር የሰላም ህብረት እንዲቀጥል ማስተማርና የተግባርም አርአያ መሆን ነው ይላሉ።
ሰባኪያንን የሃይማኖት አባቶች በሃይማኖቶቹ መካከል ያለውን የፍቅር የመቻቻል ጉዞ ሲሰብኩ በህብረተሰቡ መካከል ያለውንም የመቻቻልና የአብሮነት ስሜት እያጎለበቱ መሄድ እንደሚችሉም አብራርተዋል።
ሌላው ለሰላምና ለአገር ግንባታ የሃይማኖት አባቶች መስራት ያለባቸው የነገ አገር ተረካቢ በሆነው ወጣቱ ትውልድ ላይ መሆን አለበት የሚሉት ሃላፊው፤ በፊት የነበረውና በዚህ ዘመን ያለው ወጣት እጅግ የተለያየ ሆኗል፡፡ በኢትዮጵያ እስከ 1960ዎቹ መጨረሻ ድረስ የስነምግባር ትምህርት ይሰጥ ነበር። በዛ ዘመን ያለው ወጣትና ዛሬ ያለው ወጣት ስለ ሀገርና ስለ ህዝብ ፍቅር ያለው አመለካከት አንድ አይደለም። በመሆኑም በዚህ ረገድ ከሃይማኖት ስብከት ባሻገር የቀደመው የስነ ምግባር ትምህርት እንደገና መጀመር አለበት ብለዋል።
ሃይማኖትን መስበክ ብቻ ሳይሆን ስነ ምግባርን፣ ኢትዮጵያዊነትንና አንድነትን፣ ፍቅርን በማስተማር ያለውን ሰላምና ፍቅር ማስቀጠል ይቻላል። በዚህ ጉዳይ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከዚህ ቀደም ብዙ ባይሄድበትም በማሳሰብ ደረጃ በጥያቄ መልክ ለፓርላማ አቅርቦ ነበር። አሁንም ቢሆን የሚመለከታቸው አካላት አሁን እንዳለው የስነ ዜጋ ትምህርት ሳይሆን ግብረ ገብነትን በተመለከተ ወጣቶችን ማስተማር ይጠበቃል ይላሉ።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በሁሉም ሃይማኖቶች የተወገዙና የአገርን አንድነትና ሰላም የሚያናጉ በዜጎች መካከል አለመተማመንን የሚፈጥሩና የሀገርን እድገትና ብልፅግና የሚያሰናክሉ ነገሮች አሉ። እነዚህም ሙስናና ወገንተኝነት ናቸው። የሁሉም ሃይማኖቶች አስተምህሮ አትስረቅ፣ አትዋሽ፣ ያንተ ያልሆነውን አትመኝ እንደሚል ይታወቃል። እነዚህን አስተምህሮዎች ክርስቲያኑም ከመጽሀፍ ቅዱስ ሙስሊሙም ከቅዱስ ቁርአን በማውጣት ማስተማርና በተከታዮቻቸው ዘንድ በማስረጽ ሙስናንና ለመቀነስና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ትልቅ ሚና መጫወት ይችላሉ ይላሉ። እነዚህን ተግባራት አለመወጣት ከፈጣሪም ከህዝብም የሚያጋጩ መሆናቸውን መስበክ እንደሚገባም ነው የገለፁት።
ሙስና እና ጎጠኝነት በአገሪቱ ቀስ በቀስ እያደጉና ስር እየሰደዱ የመጡ አገራዊ ችግሮች ናቸው። ቀደም ባሉት ዘመናት ሰው እነዚህን ነገሮች የሚያደርጋቸው ተሸማቆ ነበር፡፡ አሁን ማፈሩ ቀርቶ አደባባይ እየወጣ ነው። ይሄ ግን በአንድ ቀን ጀምበር የተከሰተ ሳይሆን በረጅም ጊዜ ሂደት ቀስ በቀስ የመጣ ነው። ችግሩን ለመቅረፍም እንደዛው ጊዜ መውስዱ አይቀርም፡፡ ዋናው ነገር ግን የሃይማኖት አስተምህሮዎችን በመጠቀም እየሸረሸሩ መቀነስ እንደሚቻል ማመኑና ማስተማሩ ላይ ነው። በተለይም ዛሬ ህጻናት የምንላቸው እና የነገ አገር ተረካቢ ወጣቶች ከዚህ አይነቱ አመለካከት የፀዱ ሆነው እንዲያድጉ ከእያንዳንዱ የሃይማኖት መሪና ሰባኪ ብዙ መስራት ይጠበቃል ይላሉ።
ሃላፊው ጨምረው እንዳብራሩት፤ የሃይማኖት አባቶችና ተቋማት አስተምህሯቸው የሆኑትን ሰላም፣ ፍቅርንና አንድነትን መስበክ ያለባቸው ደግሞ አንድ ችግር ሲከሰት ሳይሆን ዘወትር መሆን አለበት። በየእለቱ ተከታዮቻቸውን አገርን ወደሚጎዳ ህዝብን ወደ ሚያስከፋ ሰላምን ወደ ሚያሳጣ ነገር እንዳይገቡ ማስተማር አለባቸው ሲሉ አሳስበዋል።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።