ለመልካም አስተዳደር መረጋገጥ ቁልፉ ተሳትፎ

12 Feb 2018

ከአገሪቱ ርዕሰ ከተማ አዲስ አበባ በ900 ኪሎሜትሮች እንዲሁም ከትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቐለ በ118 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ የምትገኘው ዓዲግራት ከተማ ከ 120 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን በጉያዋ አቅፋ የያዘችና ወጣ ገባ በሆነው መልከዓ ምድራዊ አቀማመጧ የምትታወቅ ከተማ ናት፡፡ ዙሪያዋን በአይጋ፣ አሲምባ፣ የምጉላት፣ ኣሎቃ፣ ገረኣልታ ሰንሰለታማ ተራሮች እንዲሁም ከአንድ አለት ተፈልፍለው በተሰሩ ገዳማት የተከበበችው ይህች ከተማ በርካታ ጎብኚዎች እንደሚጎርፉባት ይነገራል፡፡ ታዲያ ከአገር ውጪ ጎብኚዎች በተጨማሪ ለልማት በንቃት ተሳትፎ በሚያደርገው ነዋሪዋ ምክንያት ለተሞክሮ ልውውጥ ከዘጠኙም ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የሥራ አመራሮች ከሰሞኑ ከትመውባት ነበር፡፡ እኛም ከዚሁ ጋር በተያያዘ የኅብረተሰብ ተሳትፎው ለመልካም አስተዳደር መስፈን እያበረከተ ያለውን አዎንታዊ አስተዋፅዖ ለመዳሰስ ወደድን፡፡ በዚህም በአሁኑ ወቅት ያለውን ነባራዊ ሁኔታና በቅርብ እየተደረገ ያለውን ጥልቅ ተሃድሶም በማከል ከከተማዋ ነዋሪዎችና ከተለያዩ አካላት ጋር ያደረግነውን ቆይታ ለንባብ እንዲመች አድርገን እንዲህ ይዘንላችሁ ቀረብን፡፡
የከተማዋ ነዋሪዎች
አቶ ኃይለማርያም ዮውሓንስ በአዲግራት ከተማ ቀበሌ አምስት ነዋሪ ናቸው፡፡ በአካባቢያቸው እየተደረገ ባለው የአካባቢ ልማት ሥራ ላይ ተሰማርተው ነው ያገኘናቸው፡፡ ስለአካባቢው የልማት ሥራ ጠይቀናቸው በሰጡን ምላሽም “ሕዝቡ የሥራ ፍላጎት ያለው በመሆኑ በእያንዳንዱ የልማት ሥራዎች ተሳትፎውን ያደርጋል፡፡ ለዚህም በአሁኑ ወቅት ያለው ሰላም አስተዋፅዖ አድርጓል፡፡ ነገር ግን በአገር ላይ በአሁኑ ወቅት ብልጭ ድርግም ሲሉ የሚስተዋሉት የሰላምና መረጋጋት ችግሮች መንግሥት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ምክንያቱም ልማትም ሆነ መልካም አስተዳደር ያለ ሰላም መስፈን አይችሉም”፡፡
በአሁኑ ወቅት ሕዝቡ መንግሥትን ቀድሞት አልፏል የሚሉት ነዋሪው መንግሥት በሚፈጠሩ ችግሮች ላይ አፋጣኝ እርምጃ ያለመውሰድና መለሳለሶችም ይታዩበታል ባይ ናቸው፡፡ በአገሪቱ እየመጡ ያሉ ልማቶችን ብሎም ራሱ የሚጠቀምባቸውንና አገልግሎት የሚያገኝባቸውን መሠረተ ልማቶች እሚያቃጥሉ አጥፊዎች እየተፈጠሩ ነው፡፡ በተግባር የሚሳተፉት ደግሞ ወጣቶች ሲሆኑ ዋነኛው መነሻ አሁን ያለው ትውልድ ስለ ሰላም ያለውን ዋጋ ባለመረዳት በመሆኑ መንግሥት በትምህርት ጭምር እንዲሰጥ ማድረግ እንደሚገባው ይናገራሉ፡፡
በከተማዋ በተለያዩ ተቋማት ያሉ አገልግሎት አሰጣጦችም ላይ የሚታዩ በርካታ ችግሮች እንዳሉ ሳይናገሩ አላለፉም፡፡ በተለይ ከሥራ ዕድል ፈጠራ አንፃር በፍጥነት ውሳኔ አለመሰጠቱና ወደ ሥራ እንዲገቡ አለመደረጉ ማነቆ ሆኗል፡፡ በተያያዘ ሥራ ከመጀመራቸው አስቀድሞ ያለው የብድር አቅርቦት ወደ ሥራ ከገቡ በኋላም የሚታዩ ለሥራቸው ተገቢውን ክፍያ በወቅቱ አለመፈፀም ችግሮች ቅሬታዎችን እያስነሳ ይገኛል፡፡
መንግሥት የሚነሱ ችግሮችን ለማረምም በተለያዩ ጊዜያት ራሱን ፈትሿል፡፡ በቅርቡ ባደረገው ጥልቅ ተሃድሶም ለውጦች እንደሚመጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ዕምነት እንዳላቸው ይገልፃሉ፡፡ ነገር ግን ለማቃለል በተለይ ተጠያቂ ማድረግ ላይ ሊሰራ ይገባል፡፡ እንደከዚህ ቀደሙ ችግር ውስጥ ተዘፍቆ ኅብረተሰቡን ሲበድል የነበረ አመራርን ቦታ መቀየር ሳይሆን በጥፋቱ ልክ ተጠያቂ ማድረግ ላይ በአንክሮ ሊመለከት ይገባል ይላሉ፡፡
በቀበሌ ሦስት ልዩ ስሙ አድሽ ዓዲ ነዋሪ ወጣት መብርሃቱ ገብረመድህን በበኩሉ በከተማዋ የሚገኘው በርካታ ወጣት የሥራ ዕድል እንዲፈጠርለት ከፍተኛ ፍላጎት ያለው ቢሆንም በዚህ ረገድ የሚታዩ ክፍተቶች ግን መኖራቸውን ይናገራል፡፡ መንግሥት የሥራ ዕድል ለመፍጠር ባመቻቸው ጥቃቅንና አነስተኛም ለመደራጀት የሚመረጡት ዘርፎች ውስን መሆን ችግር ሆኖባቸዋል፡፡ በስፋት ያለው ዘርፍም ኮብልስቶን መሆኑ ወጣቱ በሚፈልገው ተደራጅቶ ውጤት እንዳያመጣ ያደርገዋል፡፡ በዚህም ወጣቶች ሥራ ፈላጊ ሆነው ቁጭ ይላሉ በማለት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያለ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ያብራራል፡፡
ሌሎች ስለ ከተማዋ
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የወጣቶች ፌዴሬሽን ረዳት ጸሐፊ ወጣት አብርሃም መሀሪ የዓዲግራት ከተማ በርካታ አስደናቂ ነገሮች እንዳሏት መመልከቱን ያስረዳል፡፡ ከተማዋ ውስጥ ለውስጥ መንገዶቿ በኮብልስቶን ከመነጠፍ በተጨማሪ አንድም ቆሻሻ ተጥሎ አለመታየቱ ግን የበለጠ ውብ እንድትሆን አድርጓታል ይላል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም የመንገድ ሥራዎች ላይ ኅብረተሰቡ የራሱን አስተዋፅዖ ሲያበረክት መመልከቱ ግርምትን ጭሮበታል፡፡ ኅብረተሰቡ የራሱን ድርሻ በአግባቡ መወጣት እንደቻለም ለመገንዘብ ችሏል፡፡
እንደ ወጣት አብርሃም ገለፃ፤ በከተማዋ ያሉት ሥራዎች አስተዳደሩ ከሕዝቡ ጋር ያለው ቅንጅታዊ የሁለትዮሽ ግንኙነትና አንድነት መኖር ምስካሬ ይሰጣሉ፡፡ መንግሥትና ሕዝብ ተናበው እንደሚሰሩም ያሳያል፡፡ የሚታየው ሥራም ለታይታ ሳይሆን ችግር ለመቅረፍ ከውስጥ በዘለቀ አገራዊ ፍቅር የመነጨ በመሆኑ ለሌሎችም ተሞክሮ ይሆናል፡፡ በተለይም አረጋውያን፣ ሲቪል ሰርቫንቱና የሃይማኖት ተቋማት ጨምሮ በነቂስ ወጥቶ በስፋት የሚያደርገው ርብርብ ልምዱ ሊሰፋ ይገባል፡፡ በሌላ በኩል ልማቱ እንዲፋጠን የበኩላቸውን የሚወጡ የሃይማኖት ተቋማትም በጋራ ተሰባስበዋል፡፡ በአገሪቱም ወጥነት ባለው ሁኔታ ኅብረተሰቡን አነቃንቆ ወደ ልማቱ ማስገባት ከተቻለ ለውጡን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማምጣት ይቻላል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ አካባቢዎች የመልካም አስተዳደር ጥያቄ በማንሳት በዚሁ መነሻነት ልማት ሲወድም መመልከት እየተለመደ መምጣቱን እንደታዘበ የሚገልፀው ወጣት አብርሃም አገርን ወደ ኋላ ጎታች ድርጊት የሚፈፅሙ ተግባራትን ለማስቆም የአመራሩ ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው፡፡ በመሆኑም ከከተማዋ ሁለንተናዊ የኅብረተሰብ ተሳትፎ ተሞክሮ ሊወሰድ ይገባል በማለት በክልሉ አንድነት የመፈጠሩ ምክንያት ተቀራርቦ መስራቱ መሆኑን ይጠቁማል፡፡
በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ሙሉጌታ ስመኝ እንደሚናገሩት፤ በዓዲግራት ከተማ ኅብረተሰቡ በተለይ በመሠረተ ልማት በፅዳትና ውበት እንዲሁም አረንጓዴ ሥራዎች የነቃ ተሳትፎ አለው፡፡ በዚህ ውስጥም የባለቤትነት ስሜት ስለሚይዝ ልማቱን ማፍረስ ላይ ሳይሆን ተጨማሪ የመልማት ፍላጎቱን ማሳደግ ላይ ትልቅ አስተዋፅዖ ያደርጋል፡፡
በከተማዋ ውስጥ ለውስጥ ዞረው ቢመለከቱም ምንም ዓይነት ቆሻሻ እንዳልተመለከቱ የሚያስረዱት አቶ ሙሉጌታ ተግባሩ የሥልጡን ሕዝብ መገለጫ ነው ይላሉ፡፡ ይህም በኅብረተሰቡ ንቃተ ህሊና ማደግ ላይ የክልሉ መንግሥት የሰራቸው በርካታ መልካም ተግባራት እንዳሉ ያመላክታል፡፡ የሚሰሩ የልማት ሥራዎችን ኅብረተሰቡ ላይ የባለቤትነት ስሜት መፍጠር ካልተቻ ዞሮ ያፈርሰዋል፡፡ ነገር ግን ግንዛቤ ከማሳደግ ጎን ለጎን ተሳታፊ ከተደረገ እንዲንከባከባቸው ይደረጋል፡፡ በመሆኑም በመላው አገሪቱ ተመሳሳይ ለውጥ ለማምጣት በሁሉም ክልሎች መሰል ተግባራት ሊለመዱ ይገባል፡፡ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በየደረጃው እየፈቱ ለመሄድ በከተማው የታየው ተቀራርቦ መስራት ተሞክሮ ሊሰፋ ይገባል በማለት እርሳቸውም ወደ ክልላቸው ተሞክሮውን ለማስፋት ዝግጁ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡
በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የፊቼ ከተማ የማዘጋጃ ቤት ኃላፊ አቶ ያሬድ የሺጥላ በዓዲግራት ከተማ የተሻለ ተሞክሮ እንደቀሰሙ ይናገራሉ፡፡ ኅብረተሰቡ ከሌሎች አካባቢዎች በተለየ ልማቱን የራሱ ተግባር አድርጎ በባለቤትነት ይሰራል፡፡ ገና ከሌሊቱም ደጃፉን ሲያፀዳና ቆሻሻም ከማጠራቀሚያ ውጪ ተጥሎ ለማየት እንዳልቻሉ ይጠቁማሉ፡፡
የመልካም አስተዳደር አንዱ መርህ የሆነው የሕዝብ ተሳትፎ ላይ ክፍተቶች በመኖራቸውም በአሁኑ ወቅት ለሚታዩት የሰላምና አለመረጋጋት ችግሮች ምቹ መደላደል እየፈጠሩ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ኅብረተሰቡ ይህን መሰል ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ሲችል ማህበረሰቡ ራሱ ለራሱና ለአገሩ የሰላም ዘብ መሆን ይጀምራል፡፡ በመሆኑም በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ለሚሰሩ ተግባራት ኅብረተሰቡን ማሳተፍ ወደ ጎን ሊተው ሳይሆን በልዩ ትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተሞክሮ መውሰዳቸውን ያስረዳሉ፡፡
ከተማዋ በመልካም አስተዳደር
በከተማዋ የሕዝብ ግንኙነት መኮንን አቶ የማነ ተክለማርያም እንደሚያስረዱት፤ በከተማዋ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎችና በክልሉ እንደሚነሳው የመልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ይነሳል፡፡ ኅብረተሰቡ ከሚያነሳው ጥያቄዎችም የተፈቱና በመንገድ ላይ ያሉ እንዲሁም ትልቅ አቅምን የሚጠይቁና ቀጣይ ከኅብረተሰቡ ጋር በመሆን ለመፍታት የዕቅድ አካል ተደርገው የሚሰራባቸው ጥያቄዎች አሉ፡፡
በአገልግሎት አሰጣጥ
ከመልካም አስተዳደር ጥያቄዎቹ መካከል አንዱ በመንግሥትና በግል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ያለ የአገልግሎት አሰጣጥ መሆኑን አቶ የማነ ያስረዳሉ፡፡ ከተሀድሶ አስቀድሞ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት አልፎ አልፎ ኅብረተሰቡ በሰዓቱ ለተገልጋይ ቢሮን ክፍት አድርጎ የተገልጋይን ጥያቄ ለማዳመጥ ዝግጁ መሆን ላይና ውሳኔ የመስጠት ብቃት ላይ ጥያቄ ይነሳል፡፡ ይህም የመነጨው ተገልጋይን በማስተናገድ ምትክ ቢሮዎች ዝግ መሆንና ስብሰባ ላይ ናቸው በሚሉ ምላሾች ተገልጋዩ ለእንግልት በመዳረጉ ነው፡፡
ፈፃሚው አካል የተለያዩ ማህበራዊ ሰበቦችን በማብዛት ቢሮ ዝግ ከማድረግ ባለፈ ራሱንም እንዳገያኝ ዝግ ማድረጉ ተገልጋዩ የሚፈልገውን አገልግሎት በወቅቱ እንዳያገኝ ማነቆ ሆኗል፡፡ በተመሳሳይ አለማዳመጥ ሌላው ችግር መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ የተቀመጠበት ወንበር ለኅብረተሰቡ አገልግሎት የመስጠት ግዴታ እንደሚጥልበት አለመቁጠርና ውሳኔንም በጊዜው አለመስጠት ኅብረተሰቡ ከሚያነሳቸው ችግሮች ዋነኞቹ ናቸው፡፡
እንደ አቶ የማነ ገለፃ፤ በአገልግሎት አሰጣጥ በከተማዋ በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ከሁሉም በባሰ ደረጃ የሚነሳውና እስካሁንም ሙሉ በሙሉ ሊፈታ ያልቻለው የመሬት አጠቃቀም ጥያቄ ነው፡፡ በዋናነት ከዚህ ጋር በተያያዘ ከሲቪል ሰርቪሱና ነዋሪውም የሚያነሳው የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ነው፡፡ በዚህም ሁሉም በሊዝ ተወዳድሮ ማሸነፍ ስለማይችል ተደራሽነቱ ላይ ችግር የሚፈጥር በመሆኑ ተደራጅተው የመኖሪያ ቤት የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲመቻች ይጠይቃሉ፡፡ መንግሥትም ጥያቄው ተገቢነት ያለው ሆኖ በማግኘቱ ከሞላ ጎደል እየመለሰው ሄዷል፡፡ በዚህም በ2009 በጀት ዓመት ብቻ ሲቪል ሰርቫንት፣ ነዋሪ እንዲሁም አካል ጉዳተኞችን ያካተቱ አንዱ ማህበር እስከ 24 ሰዎችን ላቀፉ 60 ማህበራት በየደረጃው በችግራቸው መጠን ተሰጥቷል፡፡ ይህም ይነሳ የነበረውን ችግር ሙሉ በሙሉ ይቀርፋል ማለት ባያስችልም ማቃለል ግን ተችሏል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ከተማው የካሳ መክፈያ ገንዘብ በማነሱ በዚያው ልክ የኅብረተሰቡን ጥያቄ ማስተናገድ አልተቻለም፡፡ ለተደራጁ 1 ሺህ 400 ወጣቶች የመኖሪያ ቦታ ለመስጠት ቢፈለግም የተጠየቀው ካሳ ግን 28 ሚሊዮን ብር በመሆኑና ይህም ከከተማው አቅም በላይ በመሆኑ ድህነቱ ያመጣው ችግር ጥያቄው እንዳይመለስ ጎታች ምክንያት ሆኖ ቆይቷል፡፡
በመሬት አጠቃቀም ላይ ፈጣን አለመሆን እንዲሁም መሐንዲሶች ላይ ኪራይ ሰብሳቢነት እንዳለ ኅብረተሰቡ በግልፅ ያነሳል፡፡ የከተማ አስተዳደሩም ቆራጥ ውሳኔ ወስኗል፡፡ በተሀድሶ መታደስ ያልቻለ ተቋም በማለት ተቋሙን ዳግም ከችግር ለማውጣት ሥራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ በዚህም ስድስት መሐንዲሶች ከነበሩበት እንዲነሱ፣ እንዲባረሩና በሕግ እንዲጠየቁ በተመሳሳይ በኃላፊነት ቦታ ላይ በነበሩ አመራሮች ፖለቲካዊ ውሳኔ አርፎባቸዋል፡፡ በዚህም ከኃላፊነት መነሳትን ጨምሮ ማስጠንቀቂያና ከነበሩበት ተነስተው በሌላ ቦታ ላይ እንዲመደቡም ተደርጓል፡፡ ይህም በቁርጠኝነት ኅብረተሰቡ የሚያነሳው ጥያቄ ትክክለኛነት በማመን በመሰራቱም የለውጥ ብርሃን ፍንጣቂ ማየት መቻሉን ይገልፃሉ፡፡
ከቀበሌና ከቀጣና የሚጀምሩ የአገልግሎት አሰጣጥ ውስንነቶች መኖራቸውን የሚገልፁት የሕዝብ ግንኙነት መኮንኑ ከስኳርና ዘይት ማከፋፈል እንዲሁም መታወቂያ አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ውስንነቶች መኖራቸውን ይገልፃሉ፡፡ ይሁን እንጂ አስተዳደሩ ከነዋሪው ጋር ባለው ጥብቅ ግንኙነት የሚነሱ ችግሮችን ከስር ከስር እንዲፈቱ እየተደረገ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል ውሃና መብራት በሰፊው ችግሮች የሚነሱባቸው ዘርፎች ናቸው፡፡ ተቋማቱ የሚሰጡት አገልግሎት ጥራትና ብቁነት እንደሚጎድላቸው ይነሳል፡፡
በመብራት ዙሪያ በምሬት ኅብረተሰቡ የሚያነሳቸው ችግሮች በመኖራቸው ወደ ኅብረተሰቡ በመውረድና በማነጋገር በሰራው ሥራ ለውጥ መጥቷል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ከአቅም በላይ የሆኑ ችግሮች እንዳሉ ኅብረተሰቡ ተገንዝቧል፡፡ ይህም የትራንስፎርመር ችግር መንግሥት ሊፈታው ያልቻለው መሆኑ ለእርሳቸውም ግራ እንደሚሆንባቸው አቶ የማነ ይናገራሉ፡፡ በአገር ውስጥ ለመብራት የሚሆን በቂ ኃይል አለ ሲባል ቢሰማም ችግሩ ግን ሊፈታ ያልተቻለበት አጥጋቢ ምክንያት ለኅብረተሰቡ መናገር ያልቻለ ተቋምም መብራት ኃይል ነው ይላሉ፡፡ በከተማዋ 25 ሺህ አባወራዎች የመብራትም ሆነ የውሃ ስርጭት የሌላቸው ናቸው፡፡ ይህም በከተማ ነዋሪ የሆነ ዜጋ ማግኘት ያለበት አገልግሎት ቢሆንም ከተማን ከተማ የሚያስመስል አገልግሎት እያገኙ አለመሆናቸውን ይጠቁማሉ፡፡
የጠጠር መንገዶች ዝርጋታ የውሃ ጉድጓዶች ቁፋሮ የመሳሰሉ ከችግር የተነሱ መፍትሄዎችን ኅብረተሰቡ በራሱ ጉልበት እየቆፈረ መንግሥት ቀሪውን ድጋፍ እንዲያደርግ እየሰራ ነው፡፡ ይህን መሰል የነቃ የኅብረተሰብ ተሳትፎ መኖሩም ልማቱን ከማፋጠን ባሻገር የባለቤትነት መንፈስን የሚያዳብር በመሆኑ በቀጣይም እዚህ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል፡፡
እንደ ሕዝብ ግንኙነት መኮንኑ ገለፃ፤ ፍትህ ማስፈንን በተመለከተ በከተማዋ በተለይ ከሴቶች ጥቃት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮች አሉ፡፡ ምንም እንኳን ሴቶች ለዚህ ሰላምና ዴሞክራሲ ከወንዶች እኩል የሕይወትና የአካል መስዋዕትነት ቢከፍሉም አሁንም ግን በማህበራዊ ፆታ የተነሳ እኩል ካለመታየት አልፎ ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃት ሲደርስባቸው ገና በለጋ ዕድሜያቸውም የመደፈር አደጋ ሲደርስባቸው ይታያል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ከ 10 በላይ ሴቶች በሕግ የተያዘ ጉዳይ አላቸው፡፡ ነገር ግን የሕግ ተፈፃሚነት እና ቅጣት አወሳሰን ላይ ተገቢና ፈጣን ብይን አይሰጥም የሚሉ ትችቶች ይሰነዘራሉ፡፡ በጉዳዩ ላይም የፍትህ አካላት ችግሩ ከመከሰቱ አስቀድሞ ግንዛቤ መፍጠር ላይ ችግር ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅትም ይህን ለማቃለል ተቀራርቦ መስራት ላይ እየመጡ ያሉ ለውጦች አሉ፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ኅብረተሰቡ «ሰላሜን እኔ ማስከበር ካልቻልኩ ማን ሊያስከብርልኝ ይችላል» በሚል በራሱ ገንዘብ እያዋጣ ማህበረሰብ አቀፍ ፎረሞችን እየገነባ ይገኛል፡፡
የልማት ሥራዎች
ከተማዋ ያላት መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ በተራራ የተከበበች በመሆኑ ለጎርፍና ተያያዥ ችግሮች ተጋላጭ አድርጓት ቆይቷል፡፡ ምንም እንኳን ለኑሮ ምቹ ብትሆንም በጎርፍ ግን በርካታ ጊዜያትን በጉዳት አሳልፋለች፡፡ የከተማ አስተዳደሩም የጎርፍ መከላከያ ግንባታዎችን ማካሄድ አቅም ያንሰዋል፡፡ ኅብረተሰቡም ከተማዋ ይሄን ያክል በጎርፍ ስትጎዳ የክልሉና የፌዴራል መንግሥት ድጋፍ አለማድረጋቸው ላይ ትችት ያቀርባል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ለዚሁ ችግር ማቃለያ የሚሆን በየዓመቱ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ለጎርፍ ማስወገጃ ቱቦዎች ይመድባል፡፡ ኅብረተሰቡም በዚያው ልክ ከአምስት እስከ ሰባት ሚሊዮን ብር በላይ በገንዘብ፣ በጉልበቱና በእውቀቱ ይደግፋል፡፡ በዚህም በየዓመቱ አንድ ኪሎሜትር ያክል ቁፋሮ ይሰራል፡፡
የከተማው ነዋሪ በሚያነሳው የመልማት ጥያቄዎች ውስጥ ከሚታዩት መልካም አስተዳደር ችግር መካከል የውሃ ጥያቄ ይገኝበታል፡፡ በአሁኑ ወቅት ጊዜያዊ መፍትሄ ያግኝ እንጂ በቅርቡ ከተማዋን የውሃ ችግር ክፉኛ መቷት እንደነበር አቶ የማነ ያስታውሳሉ፡፡ በአንድ ዓመት ውስጥ ባልታሰበ ሁኔታ አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ 11 የውሃ ጥልቅ ጉድጓዶች ደርቀው ሰባት ብቻ ቀሩ፡፡ ባጋጠመው አደጋም ሕዝቡ ተደናግጦ ነበር ይላሉ፡፡ ችግሩም የጉድጓድ ውሃ አስተማማኝ አለመሆኑን አስተምሮ አልፏል፡፡ ለዚህም ግንባታው ቢንጓተትም ጊዜያዊ መፍትሄ ተደርጎ የተወሰደው አውሮፓ ህብረት በመደበው 126 ሚሊዮን 15 ጉድጓዶችን ተቆፍረው ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ በዚህም በአሁኑ ወቅት ከገጠር ወደ ከተማ የገቡት የቧንቧ ዝርጋት ውስንነት ላይ የሚነሳ ችግር ካልሆነ በቀር አቅርቦቱ ላይ ከሞላ ጎደል መሻሻሎች ታይተዋል፡፡ ኅብረተሰቡ የሚጠይቀውን ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣትም በሌሎች አካባቢዎች እንደተሰራው በከተማዋ ትልቅ ግድብ መሰራት ይኖርበታል አልያ ግን ከዚህ ቀደም ተከስቶ የነበረው ዓይነት ችግር ላለመከሰቱ ዋስትና የለም ባይ ናቸው፡፡
ቀድሞ 30 ሺህ ሕዝብ በነበረበት ወቅት አገልግሎት እንዲሰጥ ለምሥራቃዊ ዞንና ለከተማው የተሰራው ሪፈራል ሆስፒታልም ባለበት መቆሙ አሁን እያደገ የመጣውን የከተማዋን ነዋሪ የማይመጥን ነው የሚለው ችግር ሌላው የኅብረተሰብ ጥያቄ ነው፡፡ አገልግሎት አሰጣጡም በዚያው ልክ ችግር እንዳለበት ይነሳል፡፡ በዚህም ኅብረተሰቡ ሌሎች አማራጮችን ፍለጋ በመሄድ ለአላስፈላጊ ወጪ እየተዳረገ ይገኛል፡፡ ዓዲግራት ዪኒቨርሲቲ ለሪፈራል ሆስፒታሉ 30 ሚሊዮን ብር በላይ መድቦ ግንባታ እያካሄደ ቢሆንም ለዘላቂ መፍትሄ ግን መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ለነዋሪው የሚመጥን አገልግሎት እንዲሰጥ መስራት አለበት የሚሉ አስተያየቶች ኅብረተሰቡ ያነሳል፡፡
ሥራ ዕድል ፈጠራ
በከተማዋ በአምስቱ ዕድገት ዘርፎች ለሌሎች ተሞክሮ የሚሆን ሥራ ይሰራ እንደነበር አቶ የማነ ያስታውሳሉ፡፡ ነገር ግን ከዓለም ባንክ ከተማ ልማት ፕሮግራም ለወጣቶች ይቀርብ የነበረው ተዘዋዋሪ ፈንድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መሄዱ አሉታዊ አስተዋፅዖ አበርክቷል፡፡ በዚህም ወጣቱ የሚፈልገውን ያክል ብድር መጠን ማግኘት አለመቻሉ የሥራ ተነሳሽነቱን ቀንሶታል፡፡ ይህም ከሥራ ይልቅ በወጣቱ ላይ ያልተለመዱ ባህርያት በሱስ መጠመዶችን እያመጣ ነው፡፡ ነገር ግን በሌላ በኩል ደግሞ በተፈጠረው የሥራ ዕድል ተሰማርተው ውጤት ማስመዝገብ የቻሉ በርካቶች ናቸው፡፡ በዚህም የራሳቸውን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባሻገር ለሌሎችም የሥራ ዕድል መፍጠር የቻሉና ሀብት ፈጥረው ደረጃቸውን እያሳደጉም መሄድ የቻሉ አርአያ ወጣቶች ይገኛሉ፡፡
መንግሥት ለሚደራጁ ወጣቶች ከሼዶች ጀምሮ አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ ከጥቃቅንና አነስተኛ በመነሳት ወደ ባለሀብትነት እንዲሸጋገሩ ይደግፋል፡፡ ለአብነት ከዚህ ቀደም በከተማዋ ቆሻሻ የነበሩ አካባቢዎችን ወደ አረንጓዴ ልማት ቀይረው መንፈስ ማደሻ ያደረጉ ወጣቶች ይገኛሉ፡፡ በሌላ በኩል በክልሉ አስተዳደርና በወጣቶቹ ከሚፈጠረው የሥራ ዕድል በተጨማሪ ከፌዴራል የተመደበው ተዘዋዋሪ ፈንድ በሳምንት ጊዜ ውስጥ አልቋል፡፡ ይህ የሚያመላክተውም የከተማዋ ወጣቶች መንገድ ከተመቻቸላቸው ያላቸው የሥራ ፍላጎት የናረ መሆኑን ነው ይላሉ፡፡
ወጣቶች ለሚያነሷቸው የብድር አቅርቦት እጥረትና የሥልጠና ዘርፎች ውስንነት ችግር የሕዝብ ግንኙነት መኮንኑ ምላሻቸውን ሲሰጡ በከተማዋ በኮብልስቶን የሚፈጠረው የሥራ ዕድል መሸጋገሪያ ድልድይ እንጂ ዘላቂ እንዲሆን አይጠበቅም፡፡ ነገር ግን ከዚህ ጋር በተያያዘ የግንዛቤ ፈጠራ ላይ የሚታዩ ውስንነቶች አሉ፡፡ በሥራቸው 20 ሺህ መቆጠብ ከቻሉ ያችን ይዘው ከደደቢት ብድርና ቁጠባ ተቋም 100 ሺህ በመበደር ወደ ቋሚ ሌላ ሥራ ሽግግር እንዲያደርጉ ደጋፊ ድልድይ ነው፡፡ ነገር ግን እዚህ ላይ በሚፈለገው ደረጃ በአስተሳሰብ ላይ ባለመሰራቱ የሚጠበቀውን ለውጥ ላይመጣ ችሏል፡፡
ኃላፊነትንና ተጠያቂነት
እንደ አቶ የማነ ገለፃ፤ መንግሥት ባወጣው የተለያዩ ፖሊሲና ስትራጂዎች ላይ ተቃውሞ ሲነሳ ባይሰማም ይህንን መሬት ላይ ወርዶ ተፈፃሚ እንዲሆን ከማድረግ ጋር ተያይዞ ግን ችግሮች ይታያሉ፡፡ በእርግጥ በሥራ ውስጥ ሁሌም ቢሆን የሚታዩ ችግሮች ቢኖሩም በአሁኑ ወቅት ድርጅቱ የተነሳበት ሕዝባዊነት ስሜት እየተሸረሸረና ሕዝበኛነቱ እየነገሰ መጥቷል፡፡ በዚህም የሰላምና ደህንነት እንዲሁም በብዝሃነት ላይ ያንዣበቡ ችግሮችም ይታያሉ፡፡ ለዚህ ችግርም እንደ ዋነኛ መንስኤ የሚሆነው ቀድሞ ለዚህ ሥርዓት መምጣት መሠረት የነበረው ጭቆናዊ አገዛዝ መገርሰስ ቁርሾ ያለባቸው አካላት ዛሬም የአገሪቱን ማደግ ሳይሆን የግል ክብራቸውን ለማስጠበቅ በአገርም በውጪም ሆነው መራወጣቸው መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ ቀድሞ ተሸናፊ የነበረው አካል ዛሬ አገሪቱን አጥፍቶ ሊጠፋ ይፈልጋል፡፡ በዚህም የአገሪቱን መልማት ከማይፈልጉ አካላት ጋር ለጥፋት በመቀናጀት አንበሳ ገዳይነቱን ሊያሳይ የሚፈልግ ኃይል አለ፡፡
ችግሩ የሚፈጠረውም ለሰላምና ለዴሞክራሲ በተከፈለው መስዋዕትነት ምክንያት በወቅቱ ያኮረፉና የግል ጥቅማቸው የቀረባቸው አካላት እያመጡት ያለ ነው፡፡ ቀጣይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለመልካም አስተዳደር በርካታ ትሩፋቶችን ያመጣል ተብሎ የሚጠበቀው የታላቁ ህዳሴ ግድብ እንዳይገነባ ያላቸውን ጥልቅ ፍላጎት በተለያየ መንገድ ሲያንፀባቁም ይስተዋላል፡፡ ይህም ከአገራዊ ስሜት ፍፁም የራቀ እኩይ አመለካከትና ተግባር መሆኑንም መገንዘብ ይገባል፡፡ በውስጡም በአስተሳሰብ ያልበሰሉ ወጣቶች በመያዙ አገሪቱን እያተራመሱ መንግሥት መምራት አትችልም የሚሉ ሀሳቦች ሲነሱ ይሰማል፡፡
እነዚህ ጠላቶች ስር ሰደው ይህንን የሚቋቋምና አስተሳሰቡን የሚሸከም ትውልድ እስኪፈጠር ምን እየሰራ ነበር? የሚል እንዲሁም ይህንን መመከት የሚችል አስተሳሰብ መፍጠር ላይም መንግሥት እንዳልሰራ ታይቷል፡፡ ይህም ለጥፋት ኃይሉ ምቹ ማዳበሪያ የሆነ አመራር እንዳለ አመላክቷል፡፡ ይህንንም መሠረት ተደርጎ በየደረጃው ጥልቅ ተሃድሶ እየተካሄደ ነው፡፡ ይህም ፍፁም የማጥራት ሥራን ማዕከል ያደረገ በመሆኑ ኅብረተሰቡ ገና ከአሁኑ በጎ አስተያየቶችን እየሰጠ ይገኛል በማለት ችግሮቹን ለማቃለል ወደ ውስጡ ማየቱ ለውጥን እንደሚያመጣ ያላቸውን ዕምነት ይናገራሉ፡፡
ቀጣይ
በቀጣይ በአሁኑ ወቅት በየደረጃው እየተካሄደ ባለው ጥልቅ ተሃድሶ መሠረት በተሰጠው አቅጣጫ ሕዝቡን ማዕከል ያደረጉ ሥራዎች መስራት ትኩረት ይሰጠዋል፡፡ ችግሮችንም በምን ዓይነት መልኩ ሊፈቱ እንደሚገባቸው በትኩረትና በጥልቀት ይቀመጣል፡፡ በዚህም የኅብረተሰቡን ተሳትፎ ባማከለ መልኩ የሕዝቡን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ፈጣንና ተከታታይነት ያለው ልማት ለማስመዝገብ እንደሚሰራ አቶ የማነ ይገልፃሉ፡፡
ሚኒስቴሩ
በከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር የኅብረተሰብ ተሳትፎና ያልተማከለ አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ መንግስተኣብ ተክሉ እንደሚናገሩት፤ በከተማዋ የነቃ የኅብረተሰብ ተሳትፎ እንዳለ በሚኒስቴሩ ተለይቷል፡፡ በተጨባጭም ከዘጠኙ ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የመጡ አካላትም ታች ድረስ ወርደው ሥራውን ተመልክተዋል፡፡ ወደየራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ ወስደው ተግባራዊ እንደሚያደርጉ እንደሚያሰፉ ዝግጁ መሆናቸውን መረዳት ተችሏል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ ኅብረተሰቡ በዚህ ደረጃ ተሳትፎ ማድረጉ እጅ ከመጠቆም ባለፈ በሥራው በባለቤትነት እንዲሳተፍ ስለሚያደርገው የመልካም አስተዳደር ችግሮችንም እንዲቃለሉ ያግዛል፡፡ በዚህም አላስፈላጊ ድርጊቶች ተፈፅመው ሲመለከት ራሱ ያጋልጣል ለችግሮችም መፍትሄ ያመጣል፡፡ የሚሰጠው አገልግሎትም በጊዜው በጥራት የተሻለ እንዲሆን በማድረግ የሚነሱ ችግሮችን መጠን በሰፊው ያቃልላል፡፡ የተሰሩ ልማቶችን ከማውደምና ከመከላከል ባሻገር ልማቱ የራሱ በመሆኑ ከሥራው ስር መሠረት ጀምሮ በሚፈለገው ጥራት እንዲሰራ ያደርገዋል፡፡ በመሆኑም ዘላቂ የሆነ ልማት እንዲመጣ የኅብረተሰብ ተሳትፎ ያስፈልጋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ እየወደሙ ያሉት ልማቶች ምንም እንኳን ሌላ ድብቅ አጀንዳ ያላቸው አካላት እጅ ከበስተጀርባ ቢኖርበትም የሚሳተፈው በተለያዩ ችግሮች ብሶት ያለበት ወጣት ነው፡፡ ለዚህም የይስሙላ፣ አስመሳይና ጥገኛ አመራር መሰብሰቡ ተጠቃሽ ምክንያት ይሆናል፡፡ ለሕዝብና መንግሥት መራራቅ አስተዋፅዖ ለማበርከታቸው ተጠያቂ የሚሆነውም መንግሥት ነው፡፡
ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው ወጥተው ሥራ ያላገኙ ወጣቶች ሌሎች ከኋላ ሲገፏቸው ወደ ጥፋት የማይገቡበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ይህንንም መቀልበስ የማይችል አመራር ካለ ችግሮች መስፋታቸው አይቀርም፡፡ «መንግሥት መታገስ እንጂ መልፈስፈስ የለበትም» የሚለውን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ አባባል በማስታወስ አመራሩ የተቀመጠበትን ዓላማ አውቆና ተረድቶ ሕዝቡን ማገልገል እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ ለዚህም መፍትሄ የሚሆነው የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ልማቱን እንዲጠብቅና በአገር ደረጃ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊ ዕድገቶችን ለማስመዝገብ የተያዙ አጀንዳዎችን ለማሳካት ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ዳይሬክተሩ ያመላክታሉ፡፡

ፍዮሪ ተወልደ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።