ውስንነቶቹን በመፍታት ወደ ከፍታው መምዘግዘግ

13 Feb 2018

ኢትዮጵያ ላለፉት አስራ አራት ዓመታት ገደማ በተከታታይ ባለሁለት አኃዝ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት አስመዝግባለች፡፡ በዚያው ልክ የዜጎች ተጠቃሚነት በመሰረተ ልማት ፣በትምህርት፣ በጤና እና በመሳሰሉት በኩል እየተረጋጋጠ ይገኛል፡፡ አንድ ሀገር የምግብ ዋስትናዋን ማረጋገጥ ችላለች፡፡ ሀገሪቱ ይህን እድገት ለማምጣት ባደረገችው ርብርብ በተመዘገቡ ስኬቶች የድህነትን ተራራ መናድ ጀምሯል፡፡
በግብርናው በኩል እየተካሄደ ያለው እንቅስቃሴ አገሪቱ እያስመዘገበች ለምትገኘው ለውጥ ከፍተኛውን ሚና እየተጫወተ ነው። የዘርፉ ምርትና ምርታማነት እያደገ መጥቶ የአርሶ አደሩም ተጠቀሚነት በዚያው ልክ እየጨመረ ነው፡፡
ኢኮኖሚውን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር እየተደረገ ባለው ርብርብ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢንዱስትሪ ዘርፉ የሚከናወኑ ተግባሮች ተበራክተዋል። በሀዋሳ ፣ ኮሞቦልቻ እና መቀሌ የተገነቡ ግዙፍ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለዚህ በማሳያነት ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡
ለሁሉም እንቅስቃሴ ወሳኝ እየሆነ ለመጣው የኤሌክትሪክ ልማትም ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው፡፡ ባለፉት 26 አመታት የተከዜ የጊቤ አንድ ፣ሁለት እና ሴ ሦስት ግደቦች ተገንብተዋል፤ የጣና በለስ እና በተለያዩ አካባቢዎች የንፋስ ሀይል ማመንጫዎች ተገንብተው ወደ ስራ ገብተዋል፡፡ በዚህም ሀይል የማመንጨት አቅም በ1984 አ.ም 379 ሜጋ ዋት ከነበረበት ወደ 4ሺ 200 ሜጋ ዋት ማድረስ ተችሏል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እና ሌሎች ግድቦች እንዲሁም የንፋስ የእንፋሎት ፣እና የፀሐይ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ ይገኛሉ፡፡ የኤሌክትሪክ ሀይል ልማቱ ሀገሪቱ ኢኮኖሚዋን ከግብርና ወደ ኦንዱስትሪ ለማሸጋገር ለምታደርገው ጥረት ሚናው ከፍተኛ ይሆናል፡፡
ኢህአዴግ አስረኛውን ድርጅታዊ ጉባኤ በመቀሌ ከተማ ባካሄደበት ወቅት የኢንዱስትሪ ፓርኮችና ክላስተሮችን በስፋት በማልማትና ሌሎች ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ኢንቨስተሮችን ለመሳብ የሚያስችል ውሳኔ ማሳለፉ ይታወቃል፡፡ ይህ ውጥኑ በእነዚህና በሌሎች የኢንዱስት
ሪ ፓርኮች እውን እየሆነ መጥቷል፡፡ ይህም ከቦታ ከመሰረተ ልማት እና ከተቀናጀ አሰራር ጋር በተያያዘ ዘርፉን ያጋጥሙት የነበሩ ችግሮችን መፍታት በማስቻሉ በተለይ የውጭ ባለሀብቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያለምንም ውጣ ውረድ ወደ ዘርፉ እንዲገባ አስችሏል፡፡
እነዚህ በመሰረተ ልማት፣ በግብርና በኢንዱስ ትሪ መስክ የተከናወኑ ተግባሮች ለአብነት ተጠቀሱ እንጂ ልማቱ በተለያዩ ዘርፎችም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ አገሪቱ እያከናወነቻቸው በምትገኘው እንደ ታላቁ የህዳሴ ግድበ ያሉ ዘርፈ ብዙ ተግባሮች በርካታ የሚያስጎመጁ የልማት ተስፋዎች ባለቤት ሆናለች፡፡ ይሁንና በተከናወኑት ተግባሮች የኢትዮጵያውያን የዘመናት ባላጋራ ድህነት ቀነሰ እንጂ አልተወገደም፤ እንደ ሀገር የምግብ ዋስትና ተረጋገጠ እንጂ በቤተሰብ ደረጃ ገና ያልተሰሩ ስራዎች አሉ፡፡
እነዚህ ችግሮች ሳይፈቱ ሀገሪቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ሌሎች ችግሮች ፈተና ሆነውባታል፡፡ እያደገ የመጣው ኢኮኖሚዋ ያስከተለው ፍላጎት አለ፤ ህዝቡ ከመልካም አስተዳደር እጦት፣ ከሙስና ከኪራይ ሰብሳቢነት ጋር አያይዞ የሚያነሳቸው ቅሬታዎች በአናት በአናቱ እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ በየጊዜው የሚቀሰቀሱ ግጭቶች፣አለመግባባቶች የእነዚህ ችግሮች መገለጫዎች ናቸው፡፡ ግጭቶቹንና አለመግባባቶቹን በማራገብ የውጭ ሀይሎች እና የሀገሪቱ ጠላቶች ለከንቱ አላማቸው ሊጠቀሙባቸው እየቋመጡ ናቸው፡፡
የስራ አጡም ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መጥቶ ወጣቶች የስራ ያለህ የሚሉባት ሀገር ሆናለች፡፡ ወጣቶችን ከስራ አጥነት ለመታደግም መንግስት 10 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ብድር ፈቅዶ የስራ እድል ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ ያለውም ለዚሁ ነው። የፓለቲካ ምህዳሩ መጥበብም ሌላኛው ችግር ሆኖ ቆይቷል፡፡
በሀገሪቱ በተለያዩ መስኮች ስኬቶች የተመዘገቡት ፈተናዎችን በማለፍ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሀገሪቱ በጸጥታና በደህንነት በኩል ፈተና አጋጥሟታል፡፡ በሀገሪቱ እየተመዘገበ ስላለው ለውጥና ስላጋጠው ስጋት እና መፍትሄ የተለያዩ የህብረተሰቦች ክፍሎች ምን ይላሉ፡፡
ኢትዮጵያ የድሮ ኢትዮጵያ አይደለችም›› የሚሉት የፌዴራል ጠቅላይ ሸሪዓ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ መሀመድ አልሙባረክ ሼህ መሀመድ አወል፣ ሀገሪቱ አሁን ወሳኝ ሀገር መሆኗን ይገልጻሉ፡፡ በአፍሪካ ግንባር ቀደምና የአህጉሪቱ ቃል አቀባይ ናት፤ በልማትም ከመሪዎቹ ተርታ ተሰልፋለች ሲሉ ያብራራሉ፡፡
አጓጓጊ የልማት አጀንዳ ይዛ እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች የሚሉት ሼህ መሀመድ፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ለዚህ በአብነት ይጠቅሳሉ፡፡ ግድቡ መሰራት የለበትም፤ እንዴት ሲባል ነው በአባይ ወንዝ ላይ ኢትዮጵያ ግድብ የምትገነባው›› ከሚለው የማጣጣል ንግግር ተወጥቶ የግድቡ ግንባታ አሁን እዚህ ላይ መድረሱ በአድናቆት ሊታይ የሚገባው ነው ይላሉ፡፡
ኢትዮጵያም በአባይ ወንዝ ይደርስባት ከነበረው ጫና ወጥታ የተፋሰሱን ጉዳይ በሶስትዮሽ ግንኙነት መመልከት የሚያስችል ሁኔታ ውስጥ እንደምትገኝ ጠቅሰው፣ ጉዳዩን በሰከነ መንገድ ማስኬድ መቻሏንም እንደ ታላቅ ስኬት ይመለከቱታል፡፡ ይህም በርካታ ውዝግብ ታልፎ የተደረሰበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ለአገሪቱ ስኬታማነት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ያስረዳሉ፡፡ እዚህ ስኬት ላይ ለመድረስ ያስቻላት በፖለቲካውም ሆነ በዲፕሎማሲው መስክ የተጫወ ተችው ሚናና ያላት ተደማጭነት መሆኑንም ያብራራሉ፡፡
መንግስት በርካታ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን እያካሄደ መሆኑን በመጥቀስም፣ በሌሎች አገልግሎት፣ በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖር ቱንና እንዲሁም በኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር አገልግሎትም የተከናወን ተግባር ይጠቅሳሉ፡፡ ልማቱ ከራሷ አልፎ ለጎረቤት አገራትም መነቃቃት እየፈጠረ ይገኛል ይላሉ፡፡
የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ናስር ካንሶ አገሪቱ በእስካሁኑ ሂደት በኢኮኖሚው በፖለቲካውና በማህበራዊው መስክ የተቀዳጀቻቸው በርካታ የሚያስጎመጁ ስኬቶች እንዳሉ ይጠቅሳሉ፡፡ እሳቸውም የመሰረተ ልማት ዝርጋታውን በመጥቀስ በመንገድ ልማት የተከናወኑ ተግባሮችን ያብራራሉ፡፡ ቀበሌዎችና የገጠር ወረዳዎች በመንገድ በኩል ከፍተኛ ችግር ያጋጥማቸው እንደነበር አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት ችግሩ እየተቃለለ እንደሚገኝ ይገልጻሉ።
አቶ ናስር እንደሚሉት፤በግብርናው ዘርፍ ስኬታማ ተግባር ተከናውኗል፤ ይህም የአርሶ አደሩን ሕይወት መቀየር ያስቻለ ከመሆኑ በተጨማሪ ላለፉት 14 ዓመታት የኢኮኖሚ እድገቱ ባለሁለት አኃዝ እንዲሆን ካስቻሉት መካከል ግምባር ቀደሙ ነው።
አገሪቱ በርካታ ግንባታዎችን እያካሄደች ትገኛለች። ልማቷ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር ሲነጻጸር እየጨመረ መጥቷል። ለዚህ አንዱ ማሳያ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ነው፡፡ አገሪቱ ለዘመናት በቁጭት ስትንገበገብለት የኖረችው የአባይ ጉዳይ በህዳሴ ግድብ ግንባታ ወደ ወሳኝ ምዕራፍ እያሸጋገረ ነው ።
በማህበራዊ ተቋማት በተለይም በትምህርት ተደራሽነት ላይ አመርቂ ተግባር ተከናውኗል፡፡ የትምህርት ጥራት ጉዳይ ትኩረት ሊደረግበት የሚገባ ጉዳይ ቢሆንም ተደራሽነት ላይ ግን ብዙ ርቀት ተሄዷል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአንድ የገጠር ቀበሌ ውስጥ እስከ ሁለት ትምህርት ቤቶችን መክፈት፣ በዚህም ማንኛውም እድሜው ለትምህርት የደረሰ ታዳጊ በትምህርት ገበታ ላይ እንዲገኝ ማድረግ ተችሏል ።
በጤናው ዘርፍም ውጤታማ መሆን በመቻሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭምር እውቅና ማግኘት መቻሉን ይጠቅሳሉ። በዘርፉ የሚጠቀሱ ክፍተቶች እንዳሉም ይጠቁማሉ፡፡ በልብ፣ ኩላሊትና በመሳሰ ሉት ህክምናዎች ላይ የሚጠበቀውን ያህል አገልግ ሎት መሰጠት አለመቻሉን ጠቅሰው፣ በዘርፉ አሁንም ይበልጥ መስራት እንደሚያስፈልግ ይጠቁማሉ።
አቶ ናስር ሌሎች የሚያስጎመጁ ድሎች ብለው ካነሷቸው መካከልም የአየር ትራንስፖርቱ እድገት ይገኝበታል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ውጤታማ ስለመሆኑ ለቀባሪው እንደማርዳት ይሆናል ያሉት አቶ ናስር፣ ተቋሙ ከስኬታማነቱ የተነሳ የሌሎች የአፍሪካ አገሮችን የአየር ትራንስፖርት ለማዘመንም እምነት የተጣለበት ለመሆን መብቃቱን ይጠቅሳሉ፡፡
የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር በአጭር ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ ለትራንስፖርት አገልግሎት መብቃቱ፣ በምድር ባቡር በኩል የአገሪቱን የተለያዩ ክፍሎችንም ሆነ አገሪቱ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር ለማስተሳሰር እየተካሄደ ያለው እንቅስቃሴ እንደሚያስጎመጁ ያብራራሉ።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽኑ አቶ ነጋ አደሬ በሀገሪቱ በልማት ደረጃ በርካታ ስኬቶች መመዝገ ባቸውን መጥቀስ እንደሚቻል ይናገራሉ፡፡ ለማሳያነትም አገሪቱ እያስመገበች ያለችውን ባለ ሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት ያመለክታሉ፡፡
እርሳቸው እንደገለጹት፤ አገሪቱ እያስመዘ ገበች ያለችው የኢኮኖሚ እድገት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያስጎመጀ መጥቷል፡፡ በኢንዱስትሪው መስክ ተገንብተው ባለሀብቶች እየገቡባቸው የሚገኙትን አሁንም እየተገነቡ ያሉት ፓርኮች አገሪቱ በኢንዱስትሪው ዘርፍ በትክክለኛው መስመር ላይ መሆኗን ያመለክታሉ፡፡ ኢንዱስትሪው ግብርናውን እንዲረከብ ሁኔታዎች እየተመቻቹ ናቸው፡፡ ይህ ሁሉ ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካም ሆነ በዓለም ላይ ከፍተኛ እድገት በማስመዝገብ ላይ ካሉ አገራት ተርታ መሰለፏን ይጠቁማል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ ለአገሪቱ ምን ሊያመጣ ይችላል የሚለውን ከወዲሁ ማየት በራሱ አንዱ የሚያስጎመጅ ተግባር ነው የሚሉት አቶ ነጋ፣ ይህ ጥረት የመጣው በአንድ ጀምበር እንዳልሆነም ይናገራሉ፡፡ ሕዝቡ ለግንባታው ገንዘቡን፣ እውቀቱን ፣ጉልበቱን በአጠቃላይ ማንነቱን እንደሰጠም ጠቅሰው፣ ይህ በኢኮኖሚው ላይ የሚያመጣው ለውጥ በጣም ትልቅ እንደሆነም ያብራራሉ፡፡
ከዚህ ታላቅ ግድብ ግንባታ ጋር ተያይዞ የተከናወነውን የዲፕሎማሲ ስራም ለግባታው ትልቅ አቅም መሆኑን በመጠቆም የሼህ መሀመድ አልሙባረክ ሼህ መሀመድ አወል እና የአቶ ናስርን ሀሳብ ያጠናክራሉ፡፡
የአቶ ናስርን ሃሳብ በማጠናከርም የአገሪቱ አየር ትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሽ ተግባር እያበረከተ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ እንደ አቶ ነጋ ማብራሪያ፤ ይህ በአህጉር አቀፍ ደረጃ ግንባር ቀደሙን ስፍራ የያዘ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት በአገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ላይ የራሱን አሻራ እያሳረፈም ነው፡፡ ለአገሪቱ ገጽታ ግንባታ የበኩሉን እየተወጣ ሲሆን፣ ኢንቨስትመንትን የመሳብ አቅሟ እያደገ እንዲመጣ እያደረገም ነው፡፡
አቶ ናስር አገሪቱ በቀረጸቻቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በመመራት ላለፉት ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ጊዜያት በርካታ ድሎችን ያስመዘገበች የመሆኗን ያህል ልታሳካቸው ያልቻለቻቸው ጉዳዮች እንዳሉም ይጠቁማሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ብሄራዊ መግባባትን ከመፍጠር አኳያ ውስንነቶችን መታየታቸውን፣ የፌዴራል ስርዓቱ መሰረቱ ህብረ ብሄራዊነት እንጂ ጎሰኝነት አለመሆኑ በሚገባ ግንዛቤ ያልተጨበጠበት መሆኑን በማመልከት ከዚህም አኳያ የሚታዩ የተዛቡ አመለካከቶች መኖራቸውን ያመለክታሉ፡፡
እንደ አቶ ናስር ማብራሪያ፤ ህገ መንግስቱን በተመለከተ ዜጎች ግንዛቤ እንዲጨብጡ ማደረግ ላይ እንዲሁም ህዝቡ ህገ መንግስቱን መረዳት ብቻ ሳይሆን መተግበርም እንዲችል በማድረጉ በኩል ውስንነቶች ይስተዋላሉ። ወጣቶችም፣ ሴቶችም ሆኑ ቀሪው የህብረተሰብ ክፍል መብቱንም ሆነ ግዴታውን ማጣጣም እንዲችል ሁኔታዎች በሚገባ አልተመቻቹም፡፡ ከዚህም የተነሳ ከፍተኛ ችግር እያጋጠመ ነው።
የዴሞክራሲ ስርዓት ከመገንባት አኳያ በተለይ የመድብለ ፓርቲን በማጠናከሩ በኩል ክፍተት ይታያል። ክፍተቱ ጥቂት ለማይባሉ ዜጎች የቅሬታ ምንጭ እየሆነ መጥቷል፡፡ ሌላው በዋናነት የሚጠቀሰው የመልካም አስተዳደር ችግር ነው። የመንግስት ተሿሚዎችና አመራሮች ድምጹን የሰጣቸውን ህዝብ በአግባቡ ማገልገል ሲገባቸው ራሳቸው ተገልጋይ ሆነዋል፡፡ ይህ ጉዳይ ህዝብን በከፍተኛ ደረጃ እያስቆጣ ነው፡፡
አቶ ናስር በፌዴራል ስርዓቱ ላይ ያለውን የግንዛቤ እጥረት የአገሪቱ ዋና ችግር በማለት ያብራራሉ፡፡ በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ውስጥ የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱን ከማሳደግ አኳያ የተሰጡ መብቶችን በትክክል እንዲጠቀሙ አለማድረግ፣ ህዝቡ የስልጣን ባለቤት ሆኖ እያለ የመልካም አስተዳደር ችግር በመፍጠር ህዝብን መበደል፣ ስልጣንን የህዝብ ማገልገያ ማድረግ ሲገባ የሀብትና ንብረት ማካበቻ አድርጎ የማየት ጉዳይን ዋና ዋና ችግሮች ብለው ያብራራሉ፡፡ ሙስና እና ኪራይ ሰብሳቢነት የሀገሪቱ ችግር ስለመሆኑ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባልም ይላሉ።
በሀገሪቱ የተመዘገቡ ስኬቶችን አይቶ እንዳላየ ማለፍ ካልተፈለገ በስተቀር አገሪቱ የሚያስጎመጅ እድገት እያስመዘገበች እንደምትገኝ መረዳት አያስቸግርም የሚሉት አቶ ነጋ፣ ጎልተው የሚታዩ ውስንነቶች እንዳሉም በመጠቆም የአቶ ናስርን ሀሳብ ያጠናክራሉ፡፡ ‹‹ችግሮቹም በዋናነት የመልካም አስተዳደር ችግሮች ናቸው›› የሚሉት አቶ ነጋ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮቹ በአብዛኛው መፈታት ሲችሉ ያልተፈቱ መሆናቸውን ያብራራሉ፡፡ ከሙስና ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮች፣ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ድርጊት በስፋት መታየቱ እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግር መባባሱ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት የሚያስገነዝቡ መሆናቸውን ይጠቁማሉ፡፡ እነዚህ ችግሮች ከተወገዱ አገሪቱ ወዳቀደችው ከፍታ የማትምዘገዘግበት ምንም ምክንያት እንደሌለም ይጠቁማሉ፡፡
አቶ ነጋ አገሪቱ ከጎረቤት አገራት ጋር የተሻለ ግንኙነት እንዳላት ገልጸው፣ ኤርትራ አሁንም ችግር እንዳለበት ይናገራሉ፡፡ ኢትዮጵያ በአሸባሪ ድርጅት የፈረጀቻቸውን አካላት በማስጠጋት በኢትዮጵያ ሰላም እንዳይኖር የማትፈነቅለው ድንጋይ እንደማይኖርም ይጠቁማሉ፡፡ የኤርትራ መንግስት በውስጡ የሚፈለፍላቸው ተቃዋሚ ሃይሎች የሽብር አጀንዳ ይዞ ይንቀሳቀሳል፡፡ በዚህም በርካታ ችግሮች ተፈጥረው አስተውለናል፡፡ ይህ ችግር ኢትዮጵያ ከህዝቧ ጋር ተቀራርባ በመስራት ትፈታዋለች የሚል እምነት እንዳላቸውና በዚህ አቅጣጫ መንግስትም ትልቅ ትኩረት መስጠቱን ያብራራሉ፡፡
እንደሚታወቀው መንግስት የፓለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እንደሚሰራ ካለፈው አመት አንስቶ እየሰራ ነው፡፡ በቅርቡም ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ እነዚህን ችግሮች ተረድቶ የልማቱም የዚህ ችግርም ባለቤት እኔ ነኝ በማለት ለመፍታት ከህዝቡ ጋር እንደሚንቀሳቀስ አረጋግጧል ፡፡
ገዥው ፓርቲ የፓለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የተያያዘውን ጥረት በተጨባጭ ለማረጋገጥ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ እየተደራደረ መሆኑ እንዳለ ሆኖ በቅርቡ የኢህአዴግ ማእከላዊ ኮሚቴ የፓለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በሚል ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ያሉ እንዲሁም ተፈርዶባቸው በእስር ላይ የሚገኙ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችንና ሌሎችን በምህረትና በይቅርታ ለመፍታት በገባው ቃልና ህጉ በሚፈቅ ደው መሰረት በሺዎች የሚቆጠሩ ክሳቸው ተቋርጦ እየተፈቱ ናቸው፤ በይቅርታ እየተ ለቀቁ ይገኛሉ፡፡

አስቴር ኤልያስ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።