የጠቅላይ ሚኒስትሩ የዲፕሎማሲ ዕርምጃዎች

11 May 2018

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ከሆኑበት ጊዜ ጀምሮ በአገሪቱ ልዩ ልዩ ክፍሎች በመዘዋወር ከዜጎች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ አገሪቱ ካጋጠማት ዘርፈ ብዙ ቀውስ ለማገገም የተለያዩ መፍትሄ እርምጃዎችንም በመወሰድ ላይ ናቸው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገር ውስጥ ላደረጉዋቸው ጉዞዎችና ውይይቶች ባሻገር ከምስራቅ አፍሪካ አገራት መሪዎች ጋር እጅ ለእጅ መጨባበጥ ከጀመሩም ሳምንታት ተቆጥረዋል፡፡ የተጨባበጡ እጆችም ጭብጥ ያለው ተግባር እያሳዩ ነው፡፡ የተበተኑ ሃሳቦችንም በማሰባሰብ የአንድነት መንፈስ በምስራቅ አፍሪካ እንዲጎለብት በርካታ አዎንታዊ ትርጉም ያላቸው ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው፡፡ ይህን የጠቅላይ ሚኒስትሩን የአገር ውስጥና የውጭ ጉብኝት ቀጣይ የቤት ሥራዎችን አስመልክቶ ምሁራን ሃሳባቸውን ይሰነዝራሉ፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግና አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ዶክተር ሲሳይ መንግስቴ፤ ከዲፕሎማሲ አኳያ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ተቀባይነት የጎላ እንደሆነ፣ በሳል አተያይና አካሄድ እየተከተሉ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ በአገር ውስጥ እየተከናወነ ያለው ሥራ በውጭው ዓለም የራሱን ነፀብራቅ እየፈጠረ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገር ውስጥ ከህዝቡ ጋር ተቀራርበው ሃሳብ መቀበላቸው ስኬታማ እያደረጋቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከምስራቅ አፍሪካ ካላት ተፅዕኖ ፈጣሪነት አኳያም በርካታ አገራት በትብብር መሥራት ይፈልጋሉ፤ በፍጥነትም ምላሽ በመስጠት ላይ ናቸው ይላሉ፡፡
ወቅታዊ የምስራቅ አፍሪካ ችግሮችን በማለዘብም ሆነ መፍትሄ በመስጠት ኢትዮጵያ ቀዳሚ እና ታላቅ አገር ናት የሚሉት ዶክተር ሲሳይ፤ በማንኛውም መመዘኛ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዞ እና የሥራ ጉብኝት ታላቅ ድጋፍ ያለው ነው የሚል አቋም አላቸው፡፡
ዶክተር ሲሳይ በአሁኑ ወቅት ከጅቡቲ እና ሱዳን ጋር ወደቦችን በጋራ ለማልማት የተፈረሙት ሰነዶች በህግ መነጽር ጥልቅ ትርጉም ያላቸውና የአገራቱን የጋራ ዕጣ ፋንታ በጋራ ለመወሰን የሚያስችል ውሳኔ ነው፡፡ ኢትዮጵያም የብልህ አመራር፤ የጠንካራ ዲፕሎማሲና ምጣኔ ሃብታዊ መሠረቱ የጠነከረ ወዳጅነት እየፈጠረች ስለመሆኑ ማሳያ ናቸው፡፡ ስምምነቶቹ ህጋዊ መሰረት ያላቸውና የጋራ ግንኙነቱን ለማጠናከር ትልቅ ፋይዳ የሚያኖሩ ሲሆኑ፤ በተለይ ደግሞ ከሱዳን እና ኬንያ ጋር የተደረሰው ውሳኔ በእጅጉ የጎላ ፋይዳ እንዳለው ያስረዳሉ፡፡
ኢትዮጵያ በቀጣይም በርካታ የቤት ሥራዎች እንደሚጠብቃት የሚናገሩት ዶክተር ሲሳይ፤ በሱዳን እና በኬንያ በህግ ከለላ ስር የነበሩ ዜጎች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን ያደንቁታል፡፡ የአንድ አገር መሪ ለዜጎቹ ሲል መቆርቆርም ሆነ መደራደር አለበት፡፡ ነገር ግን ይህ እስካሁን አገሪቱን ይመሩ ከነበሩ መሪዎች ያልተሞከረና ለየት ያለ በመሆኑ ትልቅ ጭብጥ ነው ይላሉ፡፡ በሌላውም ዓለም በእስር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከእስር እንዲፈቱ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቱ መጠናከር አለበት፡፡ ከዚህም ባሻገር አገሪቱ ያጋጠማትን ምጣኔ ሃብታዊ ቀውስ ለማስተካከል የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት በሚያስችሉ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲና ኢንቨስትመንት ላይ ሊያተኩሩ ይገባል ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ መካከለኛው ምስራቅ አገራትም ማቅናታቸው እንደማይቀር የሚጠቁሙት ዶክተር ሲሳይ፤ የኢትዮጵያ ዜጎች በሠላማዊ መንገድ ሰርተው ስለሚኖሩበት ሁኔታ ሊመክሩ ይገባል፡፡ ከምንም በላይ ግን በአገሪቱ ውስጥ ላሉ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ እስካሁን ባለው ሁኔታ የጉብኝታቸውም አነሳስና አካሄድም የሚደነቅና ትክክለኛ ውሳኔ ሲሆን፤ በህግ እይታም ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ብሎም በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ትርፋማ የሚያደርግ እንደሆነ ነው የሚያብራሩት፡፡
በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት አቶ ሞላ ዋሴ በበኩላቸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀንድ ላይ ሊኖራት የሚገባትን ሚና ለማሳደግ የጀመሩት ጥረት ‹‹አዎንታዊ ሚና አለው›› ሲሉ የዶክተር ሲሳይን ሃሳብ ይጋራሉ፡፡
እንደ አቶ ሞላ ገለፃ፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአገሪቱ ተከስቶ በነበረው የምጣኔ ሀብት የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ ለማጠናከር የተጀመረው ጥረት በውጪውም ሆነ በአገር ውስጥ የሚሰጠው ትርጉም ከፍያለና ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ላይ የነበራትን ሚና ለማስቀጠል ሰፊ ዕድል የሚሰጣት ነው፡፡ በተለይም ደግሞ ከሱዳን እና ጅቡቲ ጋር ወደቦችን በጋራ በማልማት፤ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተጀመረው ጥረት የሚደገፍ ሃሳብ ነው፡፡ ይህም ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካም ሆነ በሌሎች ዓለማት በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የሚኖራትን ሚና በእጅጉ ያሳድገዋል፡፡ ከዚህም በዘለለ ከተለያዩ አገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ኢንቨስተሮች እና የአገር ውስጥ ባለሃብቶች ምርታቸውን በፈለጉት ጊዜ ወደተፈለገው አቅጣጫ ለማንቀሳቀስ የሚኖረው ፋይዳ ብዙ ነው፡፡
እንደ ምጣኔ ሃብት ባለሙያው ከሆነ፤ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ እየተጫወተች ያለው ሚና ሌሎች አፍሪካ አገራትንም የሚቀሰቅስና አገሪቱን በተሻለ የዕድገት ደረጃ ላይ ሊያስቀምጣት የሚችል እንደሆነ ነው የሚናገሩት፡፡
አገሪቱ በአሁኑ ወቅት በምስራቅ አፍሪካም ሆነ በአገር ውስጥ በሁሉም መስኮች እየተከተለችው ያለው ዘርፈ ብዙ ዲፕሎማሲና አሠራር የሚደነቅ እንደሆነ በመጠቆም፤ በተለይም የአገር ውስጥ ባለሃብቶችን ማበረታታት፣ የውጭ አገር ባለሃብቶችን መሳብና ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገቱን ማስቀጠልና የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ በማጠናከር በምስራቅ አፍሪካ የገበያ መዳረሻዎችን ላይ በሰፊው ማማተር ይገባታል ይላሉ የምጣኔ ሃብት ባለሙያው
የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ አቶ ገዛኸኝ በርሔ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገር ውስጥ እና የምስራቅ አፍሪካ ጉብኝት ብዙ ትርጉም ያለው እንደሆነ በመግለፅ በምሁራኑ ሃሳብ ይስማማሉ፡፡ በተለይም ደግሞ በምስራቅ አፍሪካ ያሉትን አገራት በማግባባትና ተፅዕኖ በመፍጠር ረገድ ኢትዮጵያ የነበራትን ሚና ለማስቀጠል አያሌ ፋይዳዎች አሉት፡፡ ጉብኝቱ በምስራቅ አፍሪካ ያለውን ተግባቦት በሚገባ የሚያጠናክርና በአንዳንድ አጋጣሚዎች ችግሮች እንኳን ቢፈጠሩ ሊጠገን የሚችልበት የስትራቴጂካዊ የተግባቦት አካሄድና ሰፊ ዕድልን የሚፈጥር እንደሆነ ያስገነዝባሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአገር ውስጥ ጀምረው በርካታ የጉብኝት መዳረሻዎቻቸውን በምስራቅ አፍሪካ ማድረጋቸው ተግባራቸው ከንግግር ባለፈ እውነተኛ ወዳጅ ለማፍራት አመቺ መደላድል እንደሚሆን ዳይሬክተሩ ያስረዳሉ፡፡
እንደ አቶ ገዛኸኝ ገለፃ ከሆነ፤ በአሁኑ ወቅት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጀመረው የምስራቅ አፍሪካ ጉበኝት በሌሎች አገራትም እንደሁኔታው መቀጠል ያለበት ጉዳይ ሲሆን በኢትዮጵያ እና በጋራ ጥቅሞች ላይ ጠንካራ የማግባባት ስልትና ዲፕሎማሲ መከተል እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡ መሰል ጉብኝቶችና ግንኙነቶችም ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ ችግሮችን በአፋጣኝ እልባት ለመስጠት ብሎም መፃዒ ዕድል ላይ በሰፊው ለመምከርም ላቅ ያለ መሰረት የሚጥል ነው፡፡
በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑትና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያው አቶ ኀሳቡ ተስፋ በበኩላቸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በምስራቅ አፍሪካ አገራት ያካሄዷቸው ጉብኝቶች በዓለም አቀፍ የግንኙነት ስሌትም ሆነ በውጤታማ ዲፕሎማሲ ቀመር መሰረት ሲመዘን ሚዛን የሚደፋ መሆኑን ያብራራሉ፡፡ በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መሰረት ለጎረቤት አገራት የሚሰጠው ትኩረትም ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚህም አኳያ እየተከናወኑ ያሉት ግንኙነቶች የአገሪቱን ፍላጎት ያስቀደሙና የአገሬውን ህዝብ ጥያቄ ማዕከል ያደረጉ ናቸው ይላሉ፡፡
እንደ አቶ ኀሳቡ ገለፃ፤ ኢትዮጵያ በርካታ የውጭ ምርቶችን ወደ አገር ውስጥ የምታስገባው በጅቡቲ ወደብ ተጠቅማ ሲሆን፤ይህም በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ትልቅ ትኩረት ሊሰጣት የምትገባ አገር በመሆኗ የመጀመሪያው የውጭ አገር ጉብኝቱ በጅቡቲ መሆኑ ተገቢና የሚደነቅ ነው፡፡
በሱዳን የተካሄደው ጉብኘትም በፖለቲካዊ ዳራ ሲታይ እጅጉን ጠቃሚና በቀጣይም ሊጠናከር የሚገባ እንደሆነ ነው የሚጠቁሙት አቶ ኀሳቡ፡፡ በተለይም ደግሞ የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጉዳይ በሁለቱ አገራት የውይይት ወቅት እንደ አጀንዳ ሆኖ መነሳቱ አሁንም ቢሆን ሱዳን ያላትን የማያወላዳ አቋም የሚያሳይ ሲሆን፤ በዓለም አቀፍ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ መርህ የኢትዮጵያ አሸናፊነት እየጎላ ስለመምጣቱ እና ወዳጆችን ለማፍራት የዘረጋችው መረብ የምትፈልገውን ነገር እያጠመደላት ስለመሆኑ ማሳያ ነው ይላሉ፡፡
አቶ ኀሳቡ የሱዳኑ ጉብኝት የሁለቱን አገራት ግንኙኑት እንዲጠናከር ከመምከር በዘለለ ለግብፅም አንዳች መልዕክት እንዳለው ነው የሚያብራሩት፡፡ በተለይም ደግሞ ግብፅ በህዳሴው ግድብ ላይ ለብቻዋ የምታራምደው ግትር ሃሳብ በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ እየተሸነፈ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ያላትን ሃያልነትም እንድትረዳ ትልቅ አጋጣሚ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
እንደ አቶ ሃሳቡ ገለፃ በኬኒያ የተደረገው ጉብኝትም ሁለቱ አገራት የቆየ ወዳጅነታቸውን ለማጠናከርና የላሙ ወደብን በጋራ ለማልማት ከዓመታት በፊት የተፈራረሙትን ስምምነቶች በሰፊው እንዲፈትሹ ዕድል የሚሰጥ ነው፡፡
አቶ ሃሳቡ ቀደም ሲል በነበሩት የአገር መሪዎች ያልተሞከረውና በአሁኑ ወቅት ብቻ እንደ ትልቅ አጀንዳ ተደርጎ የተወሰደው በኬኒያ እና ሱዳን በህግ ጥላ ስር ያሉ የኢትዮጵያ ዜጎች ከእስር እንዲፈቱ ከስምምነት ላይ መደረሱ የጠንካራ ዲፕሎማሲ ማሳያ እንደሆነም ይጠቁማሉ፡፡
ጎረቤት አገራት በስጋትም ሆነ በስኬት የሚገጥማቸው ጉዳይ ሁሉ በኢትዮጵያ ላይ የሚፈጥረው አዎንታዊ ይሁን አሉታዊ ጫና ከፍተኛ በመሆኑ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን መሰረት በማድረግ ጠንካራ ድርድሮችና ግንኙነቶች መደረግ አለባቸው የሚሉት አቶ ሃሳቡ፤ በቀጣይም የአቻ ግንኙነቱን በበለጠ ለማጠናከርና የኢትዮጵያን ጥቅሞች ባስጠበቀ መልኩ ድርድሮችና ውይይቶች መካሄድ እንደሚኖርባቸው ያስገነዝባሉ፡፡

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

 

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።