‹‹የተሳሰረ ማንነት ለመፍጠር ኢትዮጵያዊነት ላይ መሥራት ይጠይቃል›› - ዶክተር ሲሳይ መንግሥቴ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰብዓዊ መብትና የፌዴራሊዝም መምህር Featured

12 May 2018
‹‹የተሳሰረ ማንነት ለመፍጠር ኢትዮጵያዊነት ላይ መሥራት ይጠይቃል››    - ዶክተር ሲሳይ መንግሥቴ  በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰብዓዊ መብትና የፌዴራሊዝም መምህር ፎቶ በፀሀይ ንጉሴ

በአንዳንድ የክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ድሮም ጀምሮ በግጦሽ መሬት፣ በውሃ፣ በጎሳ አለመስማማት ላይ የተመሰረቱ ግጭቶች ይከሰታሉ። ይሄ ወደፊትም ሊከሰት ይችላል። ሆኖም ግን ችግሩ ቶሎ መፍትሔ ከተሰጠው አንዳንዴም መልካም ነገር እንዳለው የዛሬው እንግዳችን በአዲስ አበባ ዮኒቨርሲቲ የሰብዓዊ መብትና የፌዴራሊዝም መምህር ዶክተር ሲሳይ መንግሥቴ ይናገራሉ፡፡
የጋራ አገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አለመሰጠቱ፣ ክልሎች ህገ መንግሥቱን አክብረው እንዲሄዱና ሁሉንም ታሳቢ አድርገው እንዲሠሩ አለመደረጉን እንደችግር ይጠቅሳሉ፡፡ በእነዚህና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ቃለመጠይቅ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፦ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞችና ተፎካካሪ ፓርቲዎች «ከቋንቋ ይልቅ በጂኦግ ራፊና የህብረተሰብን አሰፋፈር ያማከለ ፌዴራ ሊዝምን መከተል ይገባል» ሲሉ ይደመጣል። በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?
ዶክተር ሲሳይ፦ የፌዴራሊዝም ስርዓትን በመከተል ላይ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ገዢው ፓርቲ መግባባት ላይ መድረሳቸው አንዱ መልካም ነገር ነው፡፡ አተገባበሩ ላይ ብዙ ነገር ማንሳት ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ የፌዴራል አደረጃጀቱ ሙሉ በሙሉ በቋንቋ ላይ የተመሰረተ ነው ማለት አይቻልም፡፡ በህገ መንግሥቱ በግልጽ እንደሰፈረው በአሰፋፈር፣ በቋንቋ፣ በስነ ልቦና እና የህዝብ ውሳኔ ግምት ውስጥ ያስገባ ነው።
ይህም ሆኖ ባለፉት 27 ዓመታት ለቋንቋ ልዮነት የበለጠ ትኩረት ተሰጥቷል። ያንን ታሳቢ አድርጎ በቋንቋ ላይ መመስረቱ ብቻ ችግር አለበት በሚልም ይገለጻል። ያንን የሚቀይር የመፍትሔ ሃሳብ የማምጣት ጉዳይ ከተፎካካሪ ፓርቲዎችም ሲነሳ ይሰማል፡፡ ይሄ መነሳቱ ጥሩና ጤናማ ነው፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ህዝቦችን፣ ጋምቤላን፣ የደቡብ ብሄሮችና ብሄረሰብ ህዝቦች ክልሎችን ማንሳት ይበቃል። 56 ብሄር ብሄረሰብ ባለበት ደቡብ ክልል ላይ የሥራ ቋንቋቸው አማርኛ ነው፡፡ በቤኒሻንል ጉሙዝ ክልል ነባሮቹን ብንወስድ እንኳን ከአምስት ያላነሱ ብሄር ብሄረሰቦች አሏቸው፡፡ አሁንም የሥራ ቋንቋቸው አማርኛ ነው፡፡ በርታ ወይንም ጉሙዝ ይሁን አላሉም፡፡ ስለዚህ ሊያግባባ የሚችል ነገር ግምት ውስጥ ማስገባት አንዱ ጥሩ ነገር ነው፡፡
ዋናው ነገር ሁለት ጉዳይ በአንድ ጊዜ ወደ ተግባር መጥቷል፡፡ የፌዴራሊዝም ስርዓት ያለዴሞክራሲ ሥራ ላይ አይውልም፡፡ ምክንያቱም የጋራ አመራርና የራስ አስተዳደርን ተግባራዊ ለማድረግ የሚፈቅድ በመሆኑ ነው፡፡ እነዚህን ለመተግበር ምርጫ ያስፈልጋል፡፡ ህዝቦች ራሳቸውን የሚመራቸው አካል መምረጥ አለባቸው፡፡ በጋራ አገሪቱን ለመምራትም መርጠው መወከል አለባቸው፡፡ ምርጫዎች ደግሞ በባህሪያቸው ዴሞክራሲያዊነትን ታሳቢ ያደርጋሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ግምት ውስጥ ገብተው ከታየ የፌዴራል ስርዓቱ ለኢትዮጵያ አስፈላጊነቱ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ነገር ግን አተገባበሩ ላይ አሁንም ችግሮች አሉ፡፡
ከችግሮቹ መካከል አንደኛው አሁንም የማንነት ጥያቄዎች አልተመለሱም፡፡ ሁለተኛ አሁን በታላላቅ ብሄር ብሄረሰቦች ላይ የተመሰረቱ ለክልሎች ባለቤት አድርጎ የመስጠት ነገር አለ፡፡ ለምሳሌ የአማራ ክልል፣ የትግራይ ክልል ወይም የኦሮሚያ ክልል ይባሉና ክልሎቹ የዋና ዋና ብሄር ብሄረሰቦች ብቻ እንደሆኑ አድርጎ የማሰብ ነገር ይታያል፡፡ ለምሳሌ ነባሩ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ ላይ ደግሞ ለተወሰኑ ነባር ብሄረሰቦች ባለቤት አድርጎ በመስጠት ሌላው ህዝብ ባለቤት እንዳልሆነ ወይም እንደ መጤ የመቁጠር፣ እኩል ያለማሳተፍ ችግሮች አሉ፡፡ እነዚህ እንግዲህ በሂደት የሚስተካከሉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
አዲስ ዘመን፦ እኩል ተሳትፎ ሲባል ምን ማለት ነው?
ዶክተር ሲሳይ፦ እኩል ተሳትፎ የሚባለው አንደኛው በአገሪቱ ውስጥ ያለውን ሀብት እኩል የመጠቀም ጉዳይ ግምት ውስጥ መግባት አለበት፡፡ ይህንን በማድረግ ረገድ ለባለቤቶችና ለመጤዎች የመከፋፈል ነገር አለ፡፡ ከመሬት አቅርቦት፣ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣የትምህርት ዕድሎችን በአግባቡ ከመጠቀም ጋር ተያይዞ ዕኩል ተጠቃሚ ያለመሆን እዚህም እዚያም ቦታዎች ላይ ይታያሉ፡፡
ሌላው የሥልጣን ክፍፍል ነው፡፡ የፌዴራል ስርዓት ሲባል በክልል እና በፌዴራል የሥልጣን ክፍፍል ይኖራል። ከዚህም አልፎ በአንድ መዋቅር ላይ የሥልጣን ክፍፍል ይኖራል፡፡ የጎንዮሽና የላይና የበታች ተብሎ የሚወሰደው ማለት ነው፡፡ ክልሎች ላይ በሥልጣን ያለው ሁኔታ ሲታይ የተሟላና ፍትሐዊ የሥልጣን ክፍፍል አይስተዋልም፡፡ ነባር ለተባሉት ሥልጣኑን የማሳለፍ ነገር አለ፡፡ ስለዚህ የሥልጣን ክፍፍሉ ፍትሐዊ መሆን አለበት፡፡ በክልሎች ውስጥ ያሉት ብሄር ብሄረሰቦች ውክልናቸው በትክክል መረጋገጥ አለበት፡፡ ውክልና ሲባል በፌዴራል መንግሥት፣ በክልል፣ በዞን፣ በወረዳ እስከ ቀበሌ ድረስ እኩል መሳተፍ ይኖርባቸዋል፡፡ አሁን ይህንን በሚያረጋግጥ መልኩ ተግባራዊ ባለመደረጉ መስተካከልና መታረም አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፦ የማንነት ጥያቄዎች አሁንም ምላሽ አላገኙም ይባላል። ይሄ ምን ማለት ነው? ዶክተር ሲሳይ፦ ይህ ማለት ህገ መንግሥቱ ግልጽ ነው፡፡ በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 47 ንዑስ ቁጥር ሁለት መሰረት በክልሎች ውስጥ ያሉ ብሄር ብሄረሰቦች በማንኛውም ጊዜ የራሳቸውን ክልል ማቋቋም ይችላሉ፡፡ ይህ አሁን እየተከበረ አይደለም፡፡ ማንነታችን ይሄ ነው እያሉ አይደላችሁም ተብለው የሚከለከሉበት ሁኔታ ትክክል አይደለም፡፡ ይህ ፍትሐዊም፣ ዴሞክራሲያዊም፣ ህገ መንግሥታዊም አይደለም፡፡ ለዚህ በርካታ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል።
የወልቃይት ጥያቄ አንዱ ነው፡፡ የወልቃትን ጥያቄ መነሳቱ ሳይሆን የተስተናገደበት መንገድ ነው ችግር የሆነው፡፡ የተስተናገደበት መንገድ እስከ ግጭት አምርቷል፡፡ የራያ ህዝብ ጥያቄ አለ፡፡ እንደ ወልቃይት ጎልቶ በተደራጀ መልኩ ላይመጣ ይችላል፡፡ ግን በተለያየ መልኩ እየተነሳ ነው፡፡ ስለዚህ ግጭት ሳይፈጠር፣ ወደ እርስ በእርስ አለመግባባት ሳያመራ ህዝብን ማነጋገርና ለመፍትሄ መሥራትን ይጠይቃል፡፡ የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል በተለይ የኮንሶ ህዝቦች ጥያቄ ነበር፡፡ እርሱም ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ግጭት ውስጥ ተገብቷል። የህዝቦች መፈናቀልና የቤት ቃጠሎ ተከስቷል፡፡ ለምን እዚያ ደረጃ ላይ ይደርሳል? ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡
ኦሮሚያ ላይ የዛይ ሕዝቦች ጥያቄ አለ፡፡ ራስን በራስ የማስተዳደርና ማንነትን እንደ አንድ ቡድን፣ እንደ አንድ የህብረተሰብ ክፍል የመቁጠር ሁኔታ ማለት ነው፡፡ እኛ ኦሮሞዎች አይደለንም፤ ዛዮች ነን። የራሳችን ቋንቋ፣ ባህልና ታሪክ አለን ብለው እየጠየቁ ነው፡፡ ግን እስከአሁን መልስ አላገኙም፡፡ ስለዚህ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ቶሎ መልስ መስጠት አለበት፡፡
ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተገቢውን ውክልና እንዲያገኙ መፈቀድ አለበት፡፡ በየክልሉ እንዲህ ዓይነት ጥይቄዎች ስለሚነሱ የፌዴራል መንግሥቱ ይህንን ማበረታታት አለበት፡፡ የአገሪቱ መሪዎች ሳይቀሩ «ይህ የጥቂቶች ጥያቄና ጉዳይ ነው እንጂ የህዝብ አይደለም» ብለው ባገኙት መድረክና አጋጣሚ በድፍረት ይናገራሉ፡፡ ይህንን የሚሉት ግን አስጠንተውና የተሟላ መረጃ ይዘው አይደለም። በመሆኑም ከዚህ መውጣት ይገባል፡፡
ክልሎችም እንደገና መደራጀት አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ በጥናት ላይ ተመስርቶ፣ የህዝቦችን ጥያቄ በሚመልስ መልኩ መሠራት አለበት፡፡ ይሄ ማለት እንደገና ሙሉ ለሙሉ ፈርሰው ይሠሩ ማለት አይደለም፡፡ ትላልቅ ቦታና ብዙ ህዝብ ያለው ክልል አለ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ትንሽ ህዝብና ትንሽ መሬት ያለው ክልል አለ፡፡ ይህንን ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ማጣጣም ይገባል፡፡
የመንግሥትን በጀት ባግባቡ ለመጠቀም፣ የተፋጠነ፣ ቅርበት ያለውና ቀልጣፋ አስተዳደር ለመፍጠርና በልማት ተጠቃሚ ለማድረግ ይጠቅማል፡፡ ለምን ሦስና አራት የኦሮሚያ እና የአማራ ክልሎችን መፍጠር አንችልም? ለምን ሁለት የሶማሌ ክልሎችን መፍጠር አንችልም? በመልክዓምድራዊ የሶማሌ ክልል በጣም ሰፊ ነው፡፡ በህዝብ ቁጥር ብዙ ላይሆን ይችላል፡፡ ግን ከጎዴ እስከ ጅግጅጋ ከተማ ያለውን ስናይ ምናልባትም ከኦሮሚያና ከአማራ በቆዳ ስፋት ሊሰፋ ይችላል፡፡ የደቡብ ክልል አምስት ክልሎች ተጨፍልቀው ነው ወደ አንድ የመጡት፡፡ የፌዴራል ስርዓቱ በደንብ እንዲሠራ ካስፈለገ አምስትና ስድስት የደቡብ ክልሎችን ለምንድን ነው የማንፈጥረው? ምዕራብ ያሉት ሸካና ከፋ አካባቢ ያሉ ዞኖች ወደ ሃዋሳ ለመምጣት ረጅም ኪሎ ሜትሮችን ያቋርጣሉ፡፡ በአዲስ አበባ ዞረው ይሄዳሉ፡፡ መሰረተ ልማታችን የተጠናከረ አይደለም፡፡ ይህ በተሟላ መልኩ ሥራ ላይ እስኪውል ድረስ እንደገና ድንበሮቹን ማስተካከል የሚጠይቅ ይመስለኛል፡፡ ከተስተካከለ የፌዴራል ስርዓት በቋንቋም፣ በመልክዓምድራዊ አቀማመጥም በትክክል ሊያስተናግድ ይችላል ብዬ አስባለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፦ ኢትዮጵያ የተገበረችው ፌዴራሊዝም በራሱ ለግጭቶች መንስኤ እንደሆነ የሚናገሩ አሉ፡፡ ባለፈው በኦሮሚያና ሶማሌ ክልል የተከሰተውን ግጭት ማንሳት ይቻላል እንዲህ ዓይነቱ ነገር የሚመነጨው ከምንድን ነው? መፍትሔውስ ምንድን ነው ይላሉ?
ዶክተር ሲሳይ፦ አሁን በየክልሎቹ እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮች የፌዴራል ስርዓቱ ያመጣቸው ችግሮች ናቸው ብዬ አላምንም፡፡ የፌዴራል ስርዓቱን የተገበርንበት መንገድ ግን የፈጠረው ችግር አለ፡፡ ስለዚህ ችግሩ አተገባበሩ ላይ ነው። በተለይም በብሄር ብሄረሰብ ወይንም በቋንቋ ላይ በተመሠረተ መልኩ የፌዴራል ስርዓት የሚያራምዱ አገሮች አሉ፡፡ ተደጋግሞ በምሳሌ እንደሚነሳውም ስዊዘርላድ ሃይማኖትና በተወሰነ የቋንቋ መልክ አለው፡፡ የህንድ የባህል፣ የቋንቋና የመሳሰሉት ነገሮች ታሳቢ ተደርገዋል፡፡ ስለዚህ በቋንቋ ላይም ይሁን በመልክዓምድራዊ ላይ ተመስርቶ ሥራ ላይ የሚውለው የፌዴራል መንግሥት ለግጭት መንስኤ ሊሆን አይችልም፡፡
በእርግጥ ታፍኖና በተለያየ መልኩ መብቱን አጥቶ የኖረ ህዝብ በአንድ ጊዜ ሁሉም መብቱ ሲሰጠው የሚፈጠር ነገር አለ፡፡ አንድ ቀላል ምሳሌ ላንሳ እምቦሳ እያደገ ሲሄድ ጥጃ ሊባል ይችላል፡፡ መጀመሪያ እምቦሳው እንዳይጠፋ ታስሮ ይቆያል፡፡ በኋላ ላይ ሲለቀቅ በስርዓቱ ካልተያዘ በስተቀር ይፈነጥዛል፣ በጣም ይሮጣል። ስለዚህ አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል፡፡ በመሆኑም ከመለቀቁ በፊት መሄድ መለማመድ አለበት፡፡ በኢትዮጵያም ፌዴራልና ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን በአንድ ጊዜ ተግባራዊ አደረግን፡፡ ዘመናዊ የፌዴራል ስርዓት አዲስ ነው፡፡ አዲስ ነገር ደግሞ ወደ ተግባር ሲመጣ የራሱ ችግሮች አሉት፡፡
ሁለተኛው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለአገሪቱ አዲስ ነው፡፡ ፌዴራሊዝምና ዴሞክራሲ ሁለት ትላልቅ ነገሮች በአንድ ላይ ተግባር ላይ ሲውሉ መደነቃቀፍ ያለ ነው፡፡ ሌላው ትልቁ ችግር ለብሄረሰባዊ፣ ለአካባቢያዊ ማንነት ትልቅ ቦታ ተሰጠ፡፡ ኢትዮጵያዊነትና አካባቢያዊነት ሚዛኑን ጠብቆ እንዲሄድ አልተደረገም፡፡
በተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ወደ ራሳቸው የማድላት አጠቃላይ አገራዊ ማንነትን ያለማየት ችግሮች ነበሩ፡፡ በዚህ ምክንያት በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች ከ700 ሺ በላይ ህዝብ የተፈናቀለበት፤ በትግራይና በአማራም ይነስም ይብዛም ወደ ግጭት ባያመራም ጥያቄዎች ጎልተው ይነሱ የነበሩበት፣ ለረጅም ጊዜም ሳይመለስ የቆየበት ሁኔታ ነበር፡፡ እርሱን ተከትሎ ደግሞ የወልቃይት፣ የቅማንት ጥያቄዎች እንደነበሩ እናስታውሳለን፡፡ የቅማንት ጉዳይ በወቅቱ ምላሽ ባለማግኘቱ ወደ ግጭት አምርቶ ነበር፡፡ በሌሎችም ያሉ ችግሮች እነዚህ ናቸው፡፡
ግጭቶች በፊትም ነበሩ ፤አሁን ጎልቶ የወጣው የማህበራዊ ሚዲያውና የመገናኛ ብዙሃን አጉልተው ስለዘገቡትና ስላራገቡት ነው። ነገር ግን ድሮም ጀምሮ በግጦሽ፣ በውሃ፣ በባህል አለመጣጣም ላይ የተመሰረቱ ግጭቶች ነበሩ፡፡ ጎልተው ግን በብሄር ብሄረሰቦች መካከል ተብሎ ተነስቶ አያውቅም፡፡ ምክንያቱም ማዕከላዊ መንግሥቱ ጠንካራ በመሆኑና በሚዲያ የማይወጣበት ሁኔታም ስለነበረ ብዙ ጎልተው አይነሱም ነበር፡፡ ግጭቶች ወደፊትም ይኖራሉ፡፡ ቶሎ መፍትሔ ከተሰጣቸው አንዳንድ ጊዜ ግጭቶች መልካም ነገር አላቸው፡፡
አዲስ ዘመን፦የተሳሰረ ማንነትን መፍጠር አስፈላጊ መሆኑ በተለያዩ አጋጣሚዎች ይነሳል። ይህንን እንዴት መፍጠር ይቻላል?
ዶክተር ሲሳይ፦ የተሳሰረ ማንነት ለመፍጠር ኢትዮጵያዊነት ላይ መሥራት ይጠይቃል፡፡ ትልቁ ችግር በሚያግባቡ ጉዳዮች ላይ በተለይም በታሪክ ላይ እየተሠራ አለመሆኑ ነው፡፡ የታሪክ ትምህርት አሁን አይሰጥም፡፡ በፊት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ኢኮኖሚና ጂኦግራፊ ትምህርቶች ይሰጡ ነበር፡፡ አሁን የለም፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችም የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ባለመማራቸው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያለው ተማሪ ታሪክን የማያውቅ ነው፡፡
ሁለተኛው የቋንቋ ጉዳይ ነው፡፡ ቋንቋ ለመግባባት በጣም ወሳኝ ቢሆንም የሚያግባባንን እየያዝን አይደለም፡፡ ሊያግባባ የሚችል የጋራ ቋንቋ ሊኖር ሲገባ አሁን የሚያግባባን ቋንቋ አልተያዘም፡፡ አማርኛ ቋንቋ የፌዴራሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ ተብሏል አራት የሚሆኑ ክልሎችም ይጠቀሙበታል፤ ነገር ግን በሚገባው ደረጃ በሚያግባባ መልኩ እየተሠራበት አይደለም፡፡ ከአንዳንድ ክልሎች የሚመጡ ተማሪዎች ከፍተኛ ትምህርት ላይ በጣም ያስቸግራሉ፡፡ ወይ እንግሊዝኛን አልያም አማርኛን ባግባቡ ችለው አይመጡም፡፡ በየትኛው አንግባባ የሚለው አስቸጋሪ ነው፡፡ ይህ ቀላሉ ምሳሌ ነው፡፡ ሁሉም ክልሎች
ፌዴራል ላይ የተሟላ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ካስፈለገ የፌዴራሉን ቋንቋ መቻል አለባቸው፡፡ ተጨማሪ ቋንቋ ቢኖርም ጠቃሚ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ እንደመጫን አድርጎ የማየት ነገር አለ፡፡ ለምሳሌ ካናዳ አንድ ክልል ብቻ ነው የፈረንሳይኛ ተናጋሪ ክልል ያለው ኪዩቤክ ግዛት የሚባለው ነው፡፡ ይሄ የፌዴራሉም የሥራ ቋንቋ ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥም ለምሳሌ ብዙ ህዝብ ያለበትን ብሄረሰብ በቁጥር ወስዶ ተጨማሪ ቋንቋ ቢኖር ምን ችግር አለው? ይህንን ታሳቢ ማድረግ ይቻላል፡፡
ከዚህም በላይ ሌሎች ወደ አንድነት የሚያመጡ፣ የሚያስተሳስሩና የሚያግባቡ ማህበራዊ እሴቶችን ማጠናከር ይገባል፡፡ ከዚህ በፊት ያሉ ሀብቶች፣ ማህበራዊ እሴቶች አሉ። እነዚህን የሚያጠናክሩ ማንነትን ጠብቆ አጣጥሞ መሄድ የሚቻልበት ሁኔታ አለ፡፡ በዚህ ረገድ ባለፉት 26 ዓመታት ጉልህ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡
ኢትዮጵያዊያንን አንድ የሚያደርገን የጋራ ድልና ታሪካችን አንዱ ነው፡፡ ለምሳሌ ዓድዋ በዓልን እናንሳ በትክክል እየተከበረ አይደለም፡፡ የብሄር ብሄረሰብ በዓልን ወይንም የፓርቲ ምስረታ በዓልን የሚያክል የመገናኛ ብዙሃን ሽፋን፣ የገንዘብ በጀት ይሰጠው ነበር ወይ? ብለን ብንመለከት የምንታዘበው ነው፡፡ ስለዚህ የጋራ የሚያደርጉ በዓሎችን ዋጋ በመስጠት በደንብ ማክበር ተገቢ ነው፡፡ ከዚያም የቀዘቀዘውና የደከመውን አንድነት ወደ ትክክለኛው ቦታ ማምጣት ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን፦ ህገ መንግሥቱ ላይ ከአንድ ክልል ወደ ሌሎች ክልሎች በመዘዋወር ማልማት እንደሚቻል ተቀምጧል፡፡ አንዳንድ ክልሎች ይህ መብት እንዳይተገበር ተጽእኖ ሲፈጥሩ ይስተዋላል። እነዚህ ሁለት ሃሳቦች ከህገ መንግሥቱ ጋር አይጣረሱም?
ዶክተር ሲሳይ፦ እውነት ነው፤ በተግባር ያለው ነገር ከህገ መንግሥቱ ጋር ይጣረሳል፡፡ በተግባር ብቻ ሳይሆን አንዳንዴ የክልል መንግሥታትም ከፌዴራል ህገ መንግሥት ጋር ይጣረሳሉ፡፡ ይህንን አይቶ በደንብ ማረም ያለበት የፌዴራል መንግሥት ነው፡፡ ምክንያቱም ህገ መንግሥት የአገሪቱ የበላይ ህግ ነውና፡፡ የክልሎች ህገ መንግሥትም ሆነ ሌሎች ህጎች ትግበራቸው ከዚያ በታች ነው፡፡ ህገ መንግሥቱን የሚጻረሩ ከሆነ ውድቅ መደረግ አለበት፡፡ ይህንን የማስከበር ጉዳይ የፌዴራል መንግሥት ትልቅ ኃላፊነት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ ዜጎች ወደ ፈለጉት አካባቢ ሄደው መሥራትም፣ መኖርም ይችላሉ፡፡ ይህ የእነርሱ ምርጫ እንጂ የመንግሥት ወይንም የክልሎች ኃላፊነት ወይም ስልጣን አይደለም፡፡ ሆኖም ግን አሁን አንድ ሰው ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል ሲሄድ ሃገሩ ላይ የኖረ ሳይሆን ወደ ሌላ አገር የሄደ ያህል የሚቆጥርበት ስሜትና ስጋት ውስጥ የሚወድቅበት ሁኔታ ይታያል፡፡ ይህ ህገ መንግሥታዊም ህጋዊም ባለመሆኑ መታረም አለበት፡፡
ትልቁ ችግር ከአንድ ጽንፍ ወደ ሌላው ጽንፍ የመሄድ ችግር ነው፡፡ ቀደም ሲል ለኢትዮጵያ አንድነት ትልቅ ቦታ ተሰጠና ከጫፍ እስከ ጫፍ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ነው ማውራት ያለብህ የሚል ነበር፡፡ ስለራሱ ማንነት፣ ስለአካባቢያዊ አስተዳደር ብዙ መብት የሚፈቅድ አልነበረም፡፡ አሁን ደግሞ ከኢትዮጵያዊነት የተማከለ አሠራር በጣም የተለጠጠና ያልተማከለ አሠራር ተገለበጠና ክልሎች ራሳችሁን በራሳችሁ ታስተዳድራላችሁ ሲባሉ ያን ክልል ለራስ አድርጎ ብቻ የመውሰድ ነገር ታየ፡፡ ይሄ እንደ ችግር የሆነው አስተምህሮት ላይ በደንብ ባለመሠራቱ ነው፡፡ የጋራ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ አልተተገበረም፡፡ ክልሎችም ህጉን አክብረው እንዲሄዱ፣ ሁሉንም ታሳቢ አድርገው እንዲሠሩ የሚያደርግ ሥራ አልተሠራም፡፡ እነዚህ የፈጠሯቸው እንጂ በህገ መንግሥቱ መሰረት በነፃ የመዘዋወር፣ የመኖር፣ የመሥራት ጉዳይ በዜጎች ምርጫ የሚወሰን እንጂ ክልሎች ወይንም የፌዴራል መንግሥቱ ምርጫ አይደሉም፡፡
አዲስ ዘመን፦ ክልሎች ክልላዊ መንግሥት ተብለው የሚጠሩት የመንግሥት ሥልጣን ስለሚተገብሩ ነው ወይስ ሌላ ምክንያት አለው?
ዶክተር ሲሳይ፦ መንግሥት ሲባል ብዙ ጊዜ ማዕከላዊ መንግሥትን አድርገን ነው የምንረዳው፡፡ ነገርግን ቀበሌም መንግሥት ነው፡፡ የአካባቢ አስተዳደር አለ፡፡ ወደ ፌዴራል ስንመጣ መንግሥት ነው፡፡ ክልሎችም መንግሥት ሊባሉ ይችላሉ ችግር የለውም፡፡ ክልል ላይ መንግሥት አለ፣ ወረዳ ላይ መንግሥት ይኖራል፣ በተመሳሳይ ቀበሌ ውስጥም መንግሥት አለ፡፡ ዞሮ ዞሮ ለእነዚህ ደረጃዎችና እርከኖች በህገ መንግሥቱ መሰረት የተመጠነ ሥልጣን ይሰጣል፡፡
ህገ መንግሥቱ ለፌዴራሉና ለክልል መንግሥታት የሚሰጠው ሥልጣን አለ፣ የክልል ህገ መንግሥታት ደግሞ ለክልሉ፣ ለዞንና ለወረዳ የሚሰጡት ሥልጣንና ተግባር አለ፡፡ ይህ ታሳቢ ተደርጎ ይሠራል። ዋናው ነገር በእነዚህ መንግሥታት መካከል ያለውን ግንኙነት ተቋማዊ የማድረግ ጉዳይ ነው፡፡ ይሄ በስርዓትና በህግ የሚመራ መሆን አለበት፡፡ በአገራችን ያለው አንዱ ችግር በህግና በስርዓት አለመመራት፤ሥራው ብዙ ጊዜ ሲተገበር የሚታየውም በፓርቲ መዋቅር ነው፡፡ በግንባሩ አባላት መካከል ስምምነት ከተደረሰ ወደ ሥራ የሚገባበት ሁኔታ አለ፡፡ ትልቁ ስህተት ይህ ይመስለኛል፡፡
ባለፈው ሰሞን የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ የማዕከላዊ ምርመራ እንዲዘጋ ወስኗል፡፡ ይህንን ዜና የመገናኛ ብዙሃን እንኳን የዘገባችሁት ‹‹የማዕከላዊ ምርመራ እንዲዘጋ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ በወሰነው መሰረት ተዘጋ›› ብላችሁ ነው፡፡ እኔ እንዲህ ዓይነት ስህተት ስመለከት አዝናለሁ፡፡ ይሄ ስህተት በምንም ዓይነት መልኩ ተቀባይነት የለውም፡፡
የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ እንዲህ ዓይነት ውሳኔዎችን እንደ ፓርቲ ሊወስን ይችላል፡፡ ይሄ ውሳኔ ወደ መንግሥት ሄዶ የመንግሥት አካላት ከወሰኑ በኋላ ነው ህጋዊ ሥራዎች የሚፈጸሙት፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ ይወስን አይወስን የመገናኛ ብዙሃን ጉዳዩ መሆን አልነበረበትም፡፡ የፌዴራል መንግሥት በወሰነው መሰረት ተዘጋ፣ የፌዴራል መንግሥት በወሰነው መሰረት እስረኞች ተለቀቁ ሲባል አይሰማም፡፡ በፓርቲ ያሉ ሥራዎች ስለሚጎሉ መደበላለቅ ያለ ይመስለኛል፡፡ ይህ መስተካከልና መታረም አለበት፡፡ መንግሥት የሚለው ስያሜ ችግር የለውም፤ በዚያው ልክ ሥልጣንና ተግባር ስላለው፣ የመንግሥት ኃላፊነትን ስለሚረከብ የክልል መንግሥታት እያልን እንጠራለን፡፡
አዲስ ዘመን፦ ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ዶክተር ሲሳይ፦ እኔም አመሰግናለሁ።

ዘላለም ግዛው

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።