በሕዝብ ተሳትፎ የማይፈታ ችግር አይኖርም Featured

14 May 2018
ረዳት ፕሮፌሰር የማነ ዘርዓይ ረዳት ፕሮፌሰር የማነ ዘርዓይ

በየትኛውም አገር  ደረጃቸው ቢለያይም ከማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም ፖለቲካዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ችግሮች ማጋጠማቸው ያለንበት ክፍለዘመን ነባራዊ እውነታ ነው፡፡ በኢትዮጵያም እነዚሁ ችግሮች በየታሪክ ምዕራፉ ሲከሰቱ፤ በሕዝብ ጥረት ሲፈቱና ሲቀለበሱ ታይቷል፡ አሁንም ቢሆን በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ለመሆኑ የሚፈጠሩ ችግሮች መንስኤ ምን ይሆን? በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታስ እንዴት ይገለጻሉ? እነዚህን ችግሮች ከመፍታት አኳያ የሕዝብ ተሳትፎ ምን ይመስላል? በቀጣይስ ለሚፈጠሩ ችግሮች ሕዝቡን እንዴት የመፍትሄ አካል ማድረግ ይገባል? በእነዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የፖለቲካ ዘርፍ ምሑራንን አስተያየት ይዘን ቀርበናል፡፡

የሚፈጠሩ ችግሮችና መንስኤዎቻቸው
በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ረዳት ፕሮፌሰር የማነ ዘርዓይ እንደሚናገሩት፤ አገር የሚባለው መንግሥት፣ ግዛትና ሕዝብን ያካተተ አካል ነው፡፡ እነዚህ ራሳቸውን የቻሉና ሉዓላዊ ናቸው፡፡ የአገር ዋና መገለጫውም የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነቱ ነው፡፡ እነዚህ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነቶች ደግሞ አንደኛ በአገር ውስጥ በሕዝብ ለሕዝብ ወይም ሕዝብ ከመንግሥት ጋር በሚኖራቸው መስተጋብር፤ ሁለተኛ በሁለት ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ አገራት መካከል የሚኖር የመንግሥት ለመንግሥት ወይም በሕዝብ ለሕዝብ ትብብሮች የሚገለጹ ናቸው፡፡
በዚህ መልኩ በውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነቶች ደግሞ አንድም ግንኙነቱን የሚያጠናክር ውጤት የሚገኝባቸው ሲሆን፤ በአገር ውስጥ የሚኖረው የሕዝብ ለሕዝብም ሆነ የመንግሥትና የሕዝብ ግንኙነት በዛች አገር ውስጥ ለሚኖረው ሁለንተናዊ ተግባር ውጤታማነት ያግዛል፡፡ በአገራት መካከል የሚፈጠረው ትብብርም ለዚሁ ተግባር ደጋፊ ይሆናል፡፡ ሁለተኛም በውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖረው ግንኙነት በተለያየ ምክንያት አንዱ በአንዱ ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥርና ጉዳት የሚያመጣ ሆኖ ሊቀርብ ይችላል፡፡ ይህ ሲሆን በውስጥ በሕዝቦች መካከል ያለው ግንኙነት ይሻክራል፤ ሕዝብና መንግሥትንም ወደ አለመተማመን ይወስዳል፤ የውጭው ተጽዕኖም ለውስጡ ችግር መባባስ ድርሻ ይኖረዋል፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር የማነ እንደሚናገሩት፤ በአገር ውስጥም ሆነ በአገራት መካከል የሚኖሩ ግንኙነቶች በአንድ አገር ውስጥ ለሚፈጠር ሰላምና መረጋጋት ብሎም ልማት አጋዥ የመሆናቸውን ያክል፤ የግንኙነቶቹ በተለያየ መልኩ አሉታዊ ሁኔታ ውስጥ መውደቅ በዛች አገር ውስጥ ለሚኖረው የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነቶች ችግር ላይ መውደቅ ምክንያት ይሆናሉ፡፡ ለዚህ ችግር ከሚዳርጉ ጉዳዮች አንዱ በሕዝብና መንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት ሲሆን፤ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያለው አካል ለሕዝቡ መስጠትና ማድረስ የሚገባውን አገልግሎት ሲዘነጋ፣ ለመልካም አስተዳደርና አሠራር ብልሹነት ሲጋለጥ፣ ሥልጣንን አለአግባብ ሲጠቀም ሕዝብ ስለሚበደል በሕዝብና መንግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት ስለሚያሻክረው በአንድ አገር ውስጥ ለሚፈጠረው የማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግር መነሻ ይሆናል፡፡
ሁለተኛም አንድ አገር የተለያዩ ሕዝቦች መገኛ እንደመሆኑ በታሪክም ሆነ ሌሎች የቀደሙና ያሉ ሁነቶች ምክንያት በሕዝቦች መካከል አለመተማመንና መጠራጠር ሊፈጠር፤ ወደ ግጭትም ሊያመራ ይችላል፡፡ ይህም በአንድ አገር ውስጥ ለሚኖር ሰላም መደፍረስና ልማት መደናቀፍ ምክንያት ይሆናል፡፡ ከዚህ ባለፈ አንድ አገር ከዓለም ተነጥላ መኖር አይቻላትም፤ ለዚህም ከተለያዩ አገራት በተለያዩ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ጋር የትብብር ግንኙነት ትፈጥራለች፡፡ ሆኖም በአገራት መካከል የሚኖር ግንኙነት በተለያዩ የጥቅም ምክንያቶች መሻከር በውጫዊ ገጽታው የሚያበቃ ሳይሆን በአገር ውስጥ በሚኖረው የውስጥ ሰላምና ልማት ላይ አሉታዊ ጥላን በማጥላት በአገር ውስጥ ለሚኖረው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች መነሻ ሊሆን ይችላል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ምሑር የሆኑት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ በተለይ በአፍሪካ አገራት ከቅኝ ግዛት ነፃ በሚወጡበት ወቅት ብዙ ተስፋ ያደረጉ ነበሩ፡፡ ሰላምና መረጋጋትን ያመጣሉ፣ ዴሞክራሲን ያሰፍናሉ፣ የሰብዓዊ መብቶችንም ያከብራሉ ተብሎ ተስፋ የተጣለባቸው ነፃ አውጪ ታጋዮችና ፓርቲዎችም የሚፈለገውን ውጤት ሳያመጡ፤ ውጤቱ የተገላቢጦሽ ሆኗል፡፡ ለምሳሌ፣ የዓለም ባንክና የአይ.ኤም.ኤፍ ስትራክቸራል አሰስመንት ፕሮግራም በመጣ ጊዜ የሰውን ኑሮ ቀውስ ውስጥ ስለከተተው ወደ 40 የመንግሥት ግልበጣዎች ነው የተካሄዱት፡፡ በመንግሥት ኃላፊነት ላይ የተቀመጡ ሰዎች አገርን ያለ አግባብ መዝረፍ በመበራከቱ በተፈጠሩ ችግሮችም በአፍሪካ ውስጥ ከ110 በላይ የመፈንቅለ መንግሥት ተካሂዷል፡፡

ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸ


ከዚህ ባሻገር ግን ሰብዓዊ መብቶች መገፈፋቸ ውና የማህበራዊ አገልግሎቶች ከመዳከም አልፈው መሞታቸው ለተከሰቱት 110 የመንግሥት ግልበጣዎች ምክንያቶች ነበሩ፡፡ የመንግሥት ግልበጣን ለማከናወን ደግሞ የወታደሩ ክፍል ሁል ጊዜ ዕድል ያለው ነው፡፡ እንደመሆኑም፤ ምንም እንኳን ኋላ ላይ መልሰው አንድነት ቢፈጥሩም የሕዝብ ቅሬታን ጠብቀው ለግልበጣው ይጠቀሙበታል፡፡ በዚህ መልኩ የሚመጡ ድርጅቶችም ናቸው የሃይማኖት፣ የብሔርና ሌሎች ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጫናዎች በማሳደር ሕዝቡን የሚበድሉት፡፡ ይህ ደግሞ ሕዝቦች ለእርስ በእርስ አለመተማመንና ግጭት እንዲዳረጉ፤ ካልሆነም ለለውጥ እንዲያምጹ ምክንያት ይሆናል፡፡
በተመሳሳይ ጥቂት ሰዎች ሀብታም እየሆኑ ሕዝቡ በሙሉ ሲደኸይ በኢኮኖሚ መስኩ የሚከሰት ችግር ነው፡፡ ከዚህ አኳያ በአፍሪካ አገሮች በኢኮኖሚውም መስክ ሕዝቡ ተሳትፎ ስለሌለው የሚፈለገውን የኢኮኖሚ ማህበረሰብ መፍጠር አልተቻለም፡፡ ለምሳሌ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ 24 ትሪሊዬን የሚገመት ሀብት ቢኖራትም ሕዝቡ ግን በድህነት አረንቋ ነው፡፡ በዚህ መልኩ ሕዝብ ኢኮኖሚያዊ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ሲያጣና ሲነፈግ ለአመጽ ይነሳል፤ ችግሮችም ይፈጠራሉ፡፡
የችግሮቹ ገጽታ - በኢትዮጵያ
ረዳት ፕሮፌሰር የማነ እንደሚሉት፤ እነዚህ አገራዊና ዓለምአቀፋዊ ጉዳዮች አሁን ላይ በኢትዮጵያ ለሚስተዋሉት ብቻ ሳይሆን ቀደም ሲል ለነበሩት የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግር ምክንያት ሲሆኑ ተስተውሏል፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ የፖለቲካ ብቻ ሳይሆን የሥልጣኔ ታሪክ ያላት ሰፊ አገር ናት፡፡ የረዥም ታሪክ ባለቤት ብቻም ሳይሆን ከሦስት ሺህ ዓመት በላይ ዘመናዊ የፖለቲካ አደረጃጀትና በዚህ ሥርዓት የሚመራ ሕዝብ ያላትም ናት፡፡ ዛሬም ሰፊ ቁጥር ያለው ሕዝብ፣ የተፈጥሮ ሀብት ያላት፤ ቅኝ ሳትገዛ የቆየች እና በርካታ ዓለምአቀፍ ጦርነቶችን ያደረገች አገር ናት፡፡ በውስጧም የጭቆና ታሪክ አቅፋ የቆየች ሲሆን፤ ይህ የጭቆና ታሪኳም አሁን ላለው የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግር አሻራውን ጥሏል፡፡
ለአብነት በ1960ዎቹና 70ዎቹ የነበረው ሁኔታ ቀደም ሲል አገሪቱ በነበራት ትልቅ ገጽታ ላይ ጥላ እንዲያጠላ ያደረገ ነበር፡፡ ይሄን ታሪክ ለመቀልበስ ባለፉት አርባ እና ሃምሳ ዓመታት ብዙ ትግል ተደርጓል፡፡ የዚህ ውጤት አዎንታዊ ቢሆንም የትግል ሂደቱ አሉታዊ ጎንም ነበረው፡፡ በመሆኑም እነዚህ ታሪካዊ ዳራዎች አሉታዊ አስተዋጽዖ በማበርከት አሁን ላይ ለተደረሰበት ችግር ድርሻ አላቸው፡፡ አሁን ያለው ትውልድም ከእነዚህ የታሪክ ሁነቶች ሙሉ ለሙሉ ተላቋል ማለትም አይቻልም፡፡ እነዚህን መጥፎ ታሪኮች በአግባቡ መፍታት ካልተቻለ፤ ወይም የአፈታት ሂደቱ ቀርፋፋ ከሆነ ወጣቱ አሁን ላለበት ብቻ ሳይሆን ወደፊት ለሚኖረውም የራሳቸውን መጥፎ አሻራ ያሳርፉበታል፤ የበለጠም የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጽዕኖም ያሳድራሉ፡፡
ከዚህ በተጓዳኝ የአገሪቱ ፖለቲካዊና መልከዓ ምድራዊ ሁኔታ ለውስጣዊ ችግሯ የራሱ አስተዋጽዖ አለው፡፡ ምንም እንኳን አሁን ላይ ኢትዮጵያ ያለችበት ጂኦ-ፖለቲካል ምህዳሯ ጥሩ የሚባል ቢሆንም፤ ይህ ብቻውን የውጫዊ ተጽዕኖውን ይቀንሰዋል ማለት አይቻልም፡፡ በውስጥ ያለውን በአግባቡና በጥንቃቄ ካልተያዘ ከውሃ ሀብቷና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶቿ ጋር በተያያዘም የበርካታ አገራትን ትኩረት የያዘች ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሌሎቹ በአሉታ እንዲመለከቱ ማድረጉ አይቀሬ ነው፡፡ ከዚህ በዘለለም የአክራሪነትና ሽብርተኝነት እንቅስቃሴዎችም ትኩረት የሚሰጣቸው ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በተለይ ባለፉት 26 ዓመታት ያራመደችው የልማታዊ መንግሥት አስተሳሰብ በመጠኑ ውጤት ማሳየት ጀምሯል፡፡ ይህ ደግሞ አዎንታዊ ጎን እንዳለው ሁሉ በተቃራኒውም አገሪቱ በአንዳንድ አገሮች በጥርጣሬ እንድትታይ የሚያደርጋት ነው፡፡
በጥቅሉ ሲታይ ግን የታሪክ ገጽታው ያለፈ ነው፤ ወደኋላ ተሄዶ ሊሰራ አይችልም፡፡ የውጭ ተጽዕኖውም ውጫዊ ምክንያት ነው፡፡ በመሆኑም አሁን ማድረግ የሚቻለው አንድም፣ የታሪኩ አሉታዊ ገጽታ መጥፎ ስዕል እንዳይፈጥር መስራት ሲሆን፤ ሁለተኛም የውጭ ኃይሎች እጃቸውን ለማስገባት ዕድል የሚሰጡ ውስጣዊ ጉዳዮች ላይ በአግባቡ መስራት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ሕዝቡን፣ መንግሥትን፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎችን፣ መገናኛ ብዙኃንንና ሲቪክ ማርበራትን ባጠቃላይ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል የሚመለከት ሥራ እንደመሆኑ፤ ሁሉም የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣትና የድርሻውን ማበርከት ይኖርበታል፡፡
ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ ለየት የሚያደርገው ግዛትን ለማስፋፋት የተደረጉ ጦርነቶች ካልሆኑ በስተቀር አንድ ብሔር የሌላ ብሔር ዘር ለማጥፋት ብሎ የተነሳበትና ጦርነት ያካሄደበት ታሪክ አለመኖሩ ነው፡፡ ከዚህ በዘለለ ግን የኢትዮጵያም ሕዝቦች ከንጉሣውያኑ ጊዜ ጀምሮ ቅሬታቸውን የሚያነሱበት፤ በትግልም ለጥያቄ ዎቻቸው ምላሽ ያገኙበት ተደጋጋሚ የታሪክ ምዕራፎች አሏቸው፡፡ ለምሳሌ በንጉሣውያኑ ዘመንም ጥቂት ሰዎች የአገሪቱን ሀብት ይዘው የሚንቀሳቀ ሱበት፤ ሕዝቡንም እንደ ሁለተኛ ዜጋ የሚመለከ ቱበት ሂደት ነበረ፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳው የቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሲያነሱ የነበረው የብሔር ብሔረሰቦች መብት ጥያቄ በወቅቱ የነበረው የፖለቲካ ተሳትፎ የመብት ጥያቄ አካል ነበር፡፡ የመሬት ላራሹ ጥያቄም የመሬት ሀብቱ በጥቂት ግለሰቦች የተያዘበትን፤ ሰፊው ሕዝብ ግን የምርቱን ሲሶ እየከፈለ የሚኖርበትን የኢኮኖሚ ምዝበራ ለመቀልበስ ነበር፡፡ በ1966 የነበረው አብዮትም በወቅቱ ያልተመለሱ የመሬት፣ የእኩልነትና የማንነት ጥያቄዎችን መሠረት ያደረገ ነበር፡፡
ከዚያም በኋላ የመጣው የማርክሲዝም ሌኒንዝም አስተሳሰብ ግፊትም አገሪቱን ከችግር ያወጣ ሳይሆን ወደችግር ያስገባት፤ ይልቁንም ከቀደመው ተለይቶ የማይታይ ነበር፡፡ በተለይም ከባህል፣ ከቋንቋና ማንነት ጋር የተያያዙ የብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄዎች በሰፊው የሚነሳበትም ነበር፡፡ ይሄም ለተመሳሳይ የሥርዓት ለውጥ ያደረሰ ትግል የተከናወነበት ሲሆን፤ የብሔር ብሔረሰቦች የማንነትና የእኩልነት ጥያቄም በሕገ መንግሥት ጭምር ለመቀረጽ በቅቷል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ የብሔር ብሔረሰቦች መብት የራስን ዕድል በራስ እስከመወሰን የተሰጠው ድንጋጌ የፖለቲካ ፓርቲ ኃላፊዎች ብቻ ተጠቃሚ የሚሆኑበትና አገርን በሙስና ችግር ውስጥ የሚከቱበት እየሆነ መጣ፡፡ አሁን ላይ ያሉ ችግሮችም በዚህ መልክ የሚታዩ ናቸው፡፡
እንደ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ገለጻ፤ አሁን ላይ ኢትዮጵያ በመሠረተ ልማት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሳለች፡፡ ኢኮኖሚዋም እያደገ ነው፡፡ ይህ እንዳለ ቢሆንም የሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ዋና የሕዝቡ በደሎች ናቸው፡፡ በተለይ በወረዳ ደረጃ የሚመደቡ ኃላፊዎች ያለምንም ገደብ ሕዝቡን ሲዘርፉና ሰብዓዊ መብቱን ሲገፉት እንደነበር ነው የሚነሳው፡፡ ከዚህ ባለፈም ከየዩኒቨርሲቲውና ከሙያ ተቋማት የሚመረቁ ወደ 600ሺ ተማሪዎች ሥራ ከማግኘት ጋር በተያያዘ በሚፈጠርባቸው ተስፋ የማጣት ስሜት በቀላሉ ወደ ጽንፈኝነት የመቀየር አዝማሚያ አለ፡፡ በአገሪቱ ሲከሰት ለነበረው ችግርም ከፖለቲካዊ ችግሩ ባለፈ የዚሁ የወጣቶች ሥራ አጥነት ችግር ነበር፡፡
የሕዝብ ተሳትፎና የመፍትሄ አካልነት
ረዳት ፕሮፌሰር የማነ እንደሚሉት? የሕዝብ ተሳትፎ በተመለከተ መንግሥት እንዴት ነው ሕዝቡን እየመራ ያለው? ተቋማዊ ሕጎችስ አሉን? እነዚህ ሕጎችስ ሕዝቡ መክሮባቸውና አውቋቸው ወደሥራ የገቡ ናቸውን? የሚሉት ጉዳዮች መታየት ይኖርባቸዋል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሁነቶች የመንግሥትን ተጠያቂነትም ሆነ የሕዝብን ተሳትፎ ከማረጋገጥ አኳያ የጎላ ሚና አላቸው፡፡ ከዚህ አኳያ ሲታይ ሕዝቡ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮቹ ላይ ከመሳተፍ አኳያ ጅምሮች አሉ፡፡ ሆኖም ተሳትፎውም ሆነ አሳታፊነቱ ዘላቂና ቀጣይነት ባለው መልኩ እየተከናወነ አይደለም፡፡
ምክንያቱም የሕዝቡ ተሳትፎ በሕግ ላይ ሳይሆን በፖለቲካ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ፤ የፖለቲካ ሁኔታውን ተከትሎ ያዝ ለቀቅ፤ ሞቅ ቀዝቀዝ እያለ የሚሄድ ነው፡፡ የሕዝብ ተሳትፎ ደግሞ ሕግ ላይ ካልተመሰረተ በቀር ወጥነት ባለው መልኩ በሁሉም ቦታና በሁሉም ጉዳይ ተሳታፊ ለማድረግ ያስቸግራል፡፡ ይሄም ዜጎች እኩል እንዳይታዩ፣ በሕግ ፊትም እኩል እንዳይዳኙ፣ የፍትሃዊነትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን እንዲያነሱ፣ እንዲሁም የመንግሥት አካል ተጠያቂነት እንዳይኖር ያደርጋል፡፡
እንደ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ገለጻ ደግሞ፤ ችግሮችን ለማቃለል ሕዝብን አሳትፎ መስራት ተገቢ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ሁኔታ ግን በሕገ መንግሥቱ ውይይት ላይ ተሳተፏል ከሚባለው ውጪ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የሕዝብ ተሳትፎ የለም፡፡ ምክንያቱም እስካሁን በነበረው ሁኔታ የሕዝቡን ተሳትፎ ሳይሆን ሲያራምዱ የነበረው ሕዝቡ አዳማጭ ነው የተደረገው፡፡ ሕዝቡም የራሱን ዕድል በራሱ የሚወስንበትን ሕገ መንግሥታዊ መብት ሲተገበር አልታየም፡፡ ይልቁንም የመንግሥት ኃላፊዎች ሕዝቡጋ እየሄዱ ሲያስቸግሩት ከመስተዋል ባለፈ ለተሳትፎውና ተጠቃሚነቱ ከጅምላ ልፈፋ የዘለለ ከልብ አልተሰራም፡፡
የሕዝብ ተሳትፎን ለማረጋገጥ የሚቻለው አንድም ሕዝቡ የሚያምናቸው፣ የሚወዳቸውና ያገለግሉኛል ብሎ የሚያስባቸው ሰዎች መምረጥ ሲችል ነው፡፡ ከዚህ አኳያም የዴሞክራሲ ባህል ባልዳበረበት ሁኔታ ዝም ብሎ ምርጫ ስለተካሄደ ብቻ ሕዝቡ ተቀብሏል ማለቱ በራሱ ችግር ስላለው የዴሞክራሲ ባህሉን ማዳበር ይገባል፡፡ ምክንያቱም ሕዝብ ተሳትፏል ሲባል ሕዝቡ በፖለቲካ ውሳኔ ውስጥ መሳተፍ ይኖርበታል፤ በኢኮኖሚውና በማህበራዊ ልማት ውስጥም መሳተፍ ይገባዋል፡፡ ይህ ደግሞ ዝም ብሎ በጅምላ ተጠርቶ በጅምላ የሚሳተፍበት ሂደት መሆን የለበትም፡፡
ዶክተር ቆስጠንጢኖስ እንደሚናገሩት፤ እነዚህ ሕዝቦች ትምህርት ሳይስፋፋና መንግሥት ሳይቋቋም ጀምሮ ይህችን አገር እንዴት በሰላም ጠብቀው አኖሯት? በዚህ ሂደትስ የሃይማኖት፣ የባህልና ሌሎች ማህበራዊ ተቋማትስ ሚና ምን ነበር? የሚለውን አውቆ ለመጠቀምና የሕዝቡን ተሳትፎ ለማረጋገጥ ሕዝቡ አምኖና አውቆ በህሊናው ተመርቶ እንዲሳተፍ ማድረግ ይገባል፡፡ ምክንያቱም አንድ ቄስ ወይም ኢማም የሚናገረው ቃል፤ ካድሬው ከሚናገረው በላይ በሕዝቡ ዘንድ የመስረጽ፣ ፈቃዳዊ ተቀባይነት የማግኘትም አቅም አለው፡፡
ዛሬ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በየክልሉ እየሄዱ የሕዝቡን ችግር የሚያዳምጡትና እንዴትስ መፈታት አለበት የሚለውን ከሕዝቡ ጋር ለመወያየት ያስገደዳቸው፤ በእስካሁኑ ሂደት ሕዝቡ የመብቱ ተጠቃሚ ሆኖ እንዲሳተፍ ባለመደረጉ ነው፡፡ አሁንም አገሪቱም ሆነች ሕዝቡ መረጋጋት የቻለው በዚሁ በእርሳቸው ንግግር ያውም በመጀመሪያው ቀን ንግግራቸው ባሳደረው ተስፋ ነው፡፡
ቀጣይ ሕዝቡን ለማሳተፍና የመፍትሄ አካል ለማድረግ
ረዳት ፕሮፌሰር የማነ እንደሚሉት፤ በማህ በራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ሕግን መሠረት አድርጎ የሕዝቡ አለመሳተፍ ደግሞ በዋናነት የመልካም አስተዳደር ችግር ሕዝቡ ላይ እንዲጫን ያደርጋል፡፡ ይህ መልካም አስተዳደር ደግሞ ዝም ብሎ የሚመጣ ሳይሆን መሠረቱ ዴሞክራሲ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ያሉ መዋቅሮች በትክክል የሕዝብን ሉዓላዊነት የሚያንጸባርቁ መሆን አለባቸው፡፡ የሕዝብ ሉዓላዊነት የሚረጋገጠው ደግሞ የሕዝብ ተወካይ የሆኑ ምክር ቤቶች በትክክለኛ ምርጫ የመጡ ሲሆኑ እና ሲጠናከሩ ነው፡፡
ከዚህ ባለፈም እነዚህን ተቋማት የሚያግዙ እንደ ምርጫ ቦርድን፣ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና እንባ ጠባቂ፤ የመገናኛ ብዙኃን፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎችና ማህበራዊ ተቋማት መጠናከር የሕዝብን ተሳትፎ ለማረጋገጥ የሚያግዙ ናቸው፡፡ በመሆኑም የሕዝብ ተሳትፎን ማጠናከር የሚቻለው በዚህ መልኩ የተለያዩ አካላትን በማጠናከርና ሕዝቡም በቀጥታም ሆነ በተወካይ እንዲሳተፍ ሲደረግ እንደመሆኑ፤ በተለያዩ ምክንያቶች የሚነሱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን የመፍታቱ ሂደት የሕዝብ ተሳትፎን በእጅጉ የሚፈልግ መሆኑን ተገንዝቦ በዚሁ ልክ ሊሰራ ይገባል፡፡ ይህ ሲሆን የሚፈለገው ውጤት ይገኛል፡፡
ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ አሁን በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ንግግርና ሕዝብን የማነጋገር ሂደት ሕዝቡ ትልቅ ተስፋ አሳድሯል፡፡ ሕዝቡም ብዙ ውጤቶችን ይጠብቃል፡፡ ይህ የሚሳካው ግን በእርሳቸው ብቻ ሳይሆን የሁሉንም አካልና የፓርቲውን ሙሉ ድጋፍ ሲያገኝ ነው፡፡ ሥርዓቱም የሕዝብ መሠረት ሊያዳብር የሚችለው የሕዝቡን ተሳትፎ ማጎልበት ሲችል ነው፡፡ ለምን ቢባል፣ ንጉሡ ሲወርዱ ሕዝብ ለምን አላለም፤ በተመሳሳይ ደርግ ሲወድቅ ማንም ሕዝብ ለምን ወደቀ አላለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ እሰየሁ ነው ያለው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሥርዓቶች የሕዝብ መሠረት አልነበራቸውም፡፡ አሁንም ይሄን ተገንዝቦ መስራት ለችግሮች ሁሉ መፍትሄ የሆነውን ሕዝብ ለማሳተፍና ችግሮችን ለማቃለል ያግዛል፡፡
በዚህ ረገድ የሕዝቡን ተሳትፎ ለማሳደግ የኅብረተሰቡን ባህል፣ እምነት፣ ሥነልቦናና አካባቢያዊ ሁኔታ በጥናት ታግዞ በአግባቡ መለየት ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ሕዝቡን እንደየአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ መድረስና ማሳተፍ ተገቢ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ፣ በአንዳንድ ቦታ ሕብዙ በአባ ገዳ የሚተዳደር ሆኗል፤ በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ የጎሳ ኃላፊዎች ሊያስተዳድሩት ይችላሉ፡፡ በመሆኑም የሕዝብ ተሳትፎ እንደየ ኅብረተሰቡ አካባቢና ቀዬ የሚወሰን እንጂ ለመላው አገሪቱ አንድ ቀመር ወጥቶ እንዲሳተፍ የሚደረግበት አይደለም፡፡
እንደ ዶክተር ቆስጠንጢኒስ አባባል፤ በካድሬዎች የተለመዱ ቃላት “ኪራይ ሰብሳቢ”፣ “አብዮታዊና ልማታዊ መንግሥት”፣ ወዘተ እያሉ ሕዝቡ በማያውቀውና በማይገባው ቋንቋ ከማዳረቅ ይልቅ፣ ለሕዝቡ ቅርብ በሆኑት የሃይማኖት አባቶች፣ የባህል መሪዎችና ሌሎች ማህበራዊ ተቋማት አማካኝነት ሕዝቡ በሚያውቀው ቋንቋ አስረድቶና አሳምኖ ማሳተፍ ይገባል፡፡ የሕዝቡ ሃሳብ የሚንሸራሸርበት ዕድል እንዲኖርም ተፎካካሪ ፓርቲን በማጠናከር ጠንካራ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ መደገፍ፤ ሕዝቡም ለሰላማዊ የፓርቲ የሥልጣን ሽግግር መሳካት ግንዛቤ እንዲይዝ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
የሲቪክ ማህበራትን ሚና ማሳደግ፤ ሚዲያውም በሚዲያው ሕግ እስከሰራ ድረስ በየምክንያቱ ከማስፈራራትና ከማሰር ተቆጥቦ የሕዝቡን ሀሳብ እንዲያራምድ ማገዝ፤ ችግሮችን እያጠኑ መንግሥት ከሕዝብ ጋር ተባብሮና ተደጋግፎ እንዲጓዝ የሚያስችሉ አሠራሮችንም መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ መልኩ የሕዝቡን ፍላጎትና ስሜት ለይቶ ማሳተፍ ከተቻለ ሕዝብን አሳትፎ የማይፈታ ችግር ባለመኖሩ የሚፈጠሩ ችግሮችን ማቃለል፤ የሚፈለገውን አገራዊ ውጤትም ማምጣት ይቻላል፡፡

ወንድወሰን ሽመልስ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።