የፌዴራል ስርዓቱ ጥላ ለኢትዮጵያዊነት ወይስ በኢትዮጵያዊነት ላይ

15 May 2018

ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ የአስተዳደር ስርዓትን ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በላይ ተግብራለች፡፡ በዚህም ስርዓት በርካታ ስኬቶችን ያጣጣመች ሲሆን፣ የአገሪቱ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡ስርዓቱ የብሄር፣ ብሄረሰቦችንና ህዝቦችን የቋንቋ፣ የኃይማኖት፣ የጾታ ብሎም የባህል ብዝሃነት ጥያቄዎችን በብቃት ለማስተናገድ የተቀረጸ እንደመሆኑ ጥያቄዎቹም በልማት፣ በሠላም እና በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታው እውን መሆን ምላሽ እያገኙ መጥተዋል፡፡
ቀደም ባለው አሃዳዊ ስርዓት የህዝቦችን ጥያቄ በአግባቡ መመለስ ባይችልም ዜጎች ለአንድነትና ለኢትዮጵያዊነት ትልቅ ስፍራ እንደነበራቸው በተለያየ ተግባራቸው ሲያንጸባርቁ መቆየታቸው አይካድም፡፡ አገሪቱ አሁን እየተከተለች ባለችው የፌዴራል ስርዓት ሁሉም የኢትዮጵያ ብሄር፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቋንቋቸውን መጠቀም ፣ማሳደግ እንዲሁም ባህላቸውን የማዳበርና የማስፋፋት፣ ታሪካቸውንም የመንከባከብ መብት ያላቸው በመሆኑ ከሌሎች የአገሪቱ ክልሎች ጋር በመሆን ኢትዮጵያዊነትን በመገንባት በኩል እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ ፡፡ በክልልና በፌዴራል አስተዳደሮች ውስጥ ሚዛናዊ ውክልና የማግኘት መብት ስላላቸው ለኢትዮጵያ አንድነት እውን መሆን አያቅማሙም፡፡
ይሁንና ህገ መንግሥቱ በግልጽ በመደንገግ ያጎናጸፋቸው መብት በአንዳንድ ‹‹እኔ ነኝ የማውቅልህ›› ባዮች ሲጣስ ይስተዋላል፡፡ እነዚህ አካላት ብሄሮች ብሄረሰቦቸና ህዝቦች መብታቸው እንዳልተከበረ በማስመሰል በሌላው ብሄር ላይ እንዲነሱ እንዲሁም በኢትዮጵያዊነት ላይ ጥያቄ እንዲፈጠርባቸው ሲያደርጉም ይታያሉ፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ህዝቡ ንቃተ ህሊናው እየጎለበተ በመምጣቱ ስርዓት ምን ያህል እንደጠቀመው እየተረዳ በመሆኑ ኢትዮጵያዊነ ትንና አብሮነትን እያጎለበተ ይገኛል፡፡
የፌዴራል ስርዓቱ ኢትዮጵያዊነትን በመገንባት በኩል ያለውን ሚና አስመልክቶ ካነጋገርናቸው መካከል አንዱ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የህገ መንግሥት ተርጓሚና ….ዳይሬክተር አቶ ሙልዬ ወለላው፣ እንደተናገሩት፤ኢትዮጵያውያን የተለያየ ብሄር፣ ቋንቋ፣ ባህል እምነት እንዲሁም ስነ ልቦና ያላቸው ቢሆኑም፣እነዚህን በመያዝ ለረጅም ዘመናት በአብሮነት የኖሩ ህዝቦች በመሆናቸው ኢትዮጵያዊነታቸውን ሳይዘነጉት እዚህ ደርሰዋል፤ በአሁኑ ወቅትም ይህንኑ ማስቀጠል አስቸጋሪ አይሆንባቸውም፡፡
‹‹ፌዴራሊዝም ለኢትዮጵያ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡ እኛ ብዝሃነት አለን፤ይህን ብዝሃነት ማስተናገድ የምንችለው በፌዴራል ስርዓት ውስጥ ነው፡፡ ትልቁ ነገር ግን እዚህ ላይ የሚነሱ ክርክሮች መኖራቸው ነው፡፡ አሁንም ድረስ ስርዓቱን በተመለከተ በየመድረኩም በተለያዩ ጎራዎች በመከፋፈል የሚከራከሩ እንዳሉ ይታወቃል›› ይላሉ፡፡
‹‹በገዥውም ሆነ በተፎካካሪ ፓርቲዎች ፌዴራሊዝም ለኢትዮጵያ እንደሚያስፈልግ ጥርጥር የለውም››የሚሉት አቶ ሙልዬ፣ ልዩነቱ ያለው ምን አይነት ፌዴራሊዝም የሚለው ላይ ነው ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ አንዳንዶቹ የመልከዓ ምድር አቀማመጥንና ክልልን ለልማትና ለኢኮኖሚ እድገት አመቺ ነውና አካባቢያዊ የሆነ ፌዴራሊዝም ያስፈልጋል እንደሚሉም ይጠቁማሉ፡፡
እንደ አቶ ሙልዬ ማብራሪያ፤ የኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓት አካባቢንና ቋንቋን መሰረት ያደረገ ነው፡፡ ከዚህ በተቃራኒ በኩል የሚቆሙት ደግሞ ስርዓቱ የተመሰረተው በመልከዓምድራዊ አቀማመጥ ሆኖ ቢሆን በብሄር ብሄረሰቦች መካከል መከፋፈል አይኖርም ነበር ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች በዘር፣ በቋንቋ፣ በኃይማኖት ሳይከፋፈሉም በመግባባትና በፍቅር መዝለቅ ይችላል የሚል አስተያየት ያቀርባሉ፡፡
ገዥው ፓርቲ የፌዴራሊዝም ስርዓት እንደየአገሩ ተጨባጭ ሁኔታ ሊመሰረት ይችላል የሚል አመለካከት እንዳለው በመጥቀስም ፣፡ለእኛ አገር ፍትሃዊ የሚሆነው ከነበሩብን ችግሮችና ካሳለፍናቸው ጭቆናዎች የተነሳ በአካባቢና በቋንቋ መደራጀቱ ውጤታማ ያደርገናል እንደሚል ይገልጻሉ፡፡
አቶ ሙልዬ እንደሚሉት፤ ሌሎች ደግሞ ስርዓቱ ዘርን መሰረት ያደረገና በተለይም ደግሞ የአንዱን ጎሳ ከሌላው ጋር የሚያጋጭ ነው ይላሉ፡፡ከዚህም በተጨማሪ ስርዓቱ በተለያዩ ክልሎች ውስጥ ለሚገኙ ብሄር፣ ብሄረሰቦች እውቅና እየሰጠ አይደለም ሲሉ ይከራከራሉ፡፡
እነዚህ ወገኖች ይህን ይበሉ እንጂ ለአገራችን ጠቃሚውና ዘላቂነት የሚኖረው የቱ ነው የሚለው በጥልቀት ተፈትሾ ግንዛቤ መያዝ እንዳለበት አቶ ሙልዬ ያስገነዝባሉ፡፡ ምንም ይሁን ምን ግን ፌዴራሊዝምን በመከተል ኢትዮጵያዊነትን አሳምሮ መገንባት ይቻላል ይላሉ፡፡
ችግሩ ጠባብነት መሆኑንም በመጥቀስ ወደእኔ አካባቢ አትምጣ፣ ከእኔ ክልል ውጣ የሚሉ መኖራቸው በተደጋጋሚ መታየቱን ይናገራሉ፡፡ይህ የመፈናቀል ችግር ከአመራር ችግር የመጣ እንጂ ህገ መንግሥቱ የህዝቦችን ጥያቄ በሚገባ መልሷል የሚሉት አቶ ሙልዬ፣ ይህ ህገ መንግሥቱ ላይ መጻፉ ብቻውን ፋይዳ አለው ማለት አይቻልም ሲሉ ያብራራሉ፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት፤የማይካደው ጉዳይ ስርዓቱ ለውጥንና እድገትን ማምጣቱ ነው፡፡ ለአብነነት ያህል በአገሪቱ ተከታታይ የሆነ ኢኮኖሚያዊ እድገት ተመዝግቧል፣ ዛሬ ያለው መሰረተ ልማት ትናንት እንደነበረው አለመሆኑም እሙን ነው፡፡በተጨማሪም የአገር ገጽታም መለወጡ የማይታበል ሐቅ ነው፡፡
ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፣ የተባሉት ለውጦች ይመዝገቡ እንጂ ስርዓቱ በሚፈለገው ልክ ተግባራዊ አለመሆኑ ግልጽ እንደሆነ ያመለክታሉ፡፡ ለዚህ ምክንያታቸው ደግሞ ስርዓቱን ተግባራዊ የሚያደርጉት የአመራር አባላት የሚፈጽሙት ስህተት ነው፡፡
በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 32 ላይ ሁለት ንዑስ አንቀጾች ያሉ ሲሆን፣ አንደኛው የመዘዋወር ነጻነትን የሚደነግግ ነው፤ በዚህም ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም በህጋዊ መንገድ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኘ የውጭ ዜጋ በመረጠው የአገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመስረት እንዲሁም በፈለገ ጊዜ ከአገር የመውጣት ነጻነት እንዳለው ይደነግጋል፡፡ ንኡስ አንቀጽ ቁጥር ሁለት ደግሞ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወደ አገሩ የመመለስ መብት እንዳለው ያስቀምጣል፡፡ ይህ ግልጽ የሆነ ድንጋጌ እያለ የመተግበርና የማስተግበር ችግር ግን በስፋት የሚታይ መሆኑን ነው የሚያስረዱት፡፡
‹‹ስርዓቱ ምንም ችግር የለበትም፤ ለውጦችንም ማየት አስችሏል፤ ነገር ግን ምንም እንከን የለውም የምንል እና እውነታውን የምንደብቅ ከሆነ መጥፎ ነገሩን እየደመርን ነው የምንጓዘው›› የሚሉት አቶ ሙልዬ፣፡‹‹ለምንድን ነው ሰዎች የሚፈናቀሉት የሚለውን ማየቱ ተገቢ ነው ሲሉ እንደ አብነት ይጠቅሳሉ፡፡
ከደቡብና ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ ወገኖች ፣ ከሱማሌ ክልል የተፈናቀሉ ኦሮሞዎች፣ ከአማራ ክልል የተፈናቀሉ ትግራዮች እንዲሁም ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ ደቡቦች እንደነበሩ በምሳሌነት በመጥቀስም፣ጉዳዩ ጥናት የሚያስፈልገው መሆኑ እንዳለ ሆኖ ምንም ችግር የለም ብለን ማለት ግን አይቻልም›› በማለት ያመለክታሉ፡፡
አቶ ሙልዬ እንደሚሉት፤ ለአንድነት መላላት ምክንያቶች ናቸው ብለው የሚያስቡት ልዩነትን በማስፋት መሰራቱ ነው፡፡አንድነት ላይ የላላ አካሄድ ስለነበረ ሚዛን አልደፋ አለ፡፡ አንድአመራር አሊያም ግለሰብ ሥራ ቦታ እንዲቀጠርለት የሚፈልገው የክልሉ ወይም የአካባቢው ልጅ ነው፡፡ ይህ የፌዴራል ስርዓቱ ችግር ሳይሆን ሰዎች የፈጠሩት ነው፡፡ህገ መንግሥቱ ላይ ግን የትኛውንም ብሄር በእኩል የሚያስተናግድ ድንጋጌ መኖሩ ይታወቃል፡፡
አንድ ብሄር የራሱ ማንነት ሙሉ ለሙሉ እውቅና ባገኘበት በዚህ ወቅት ስለምድን ነው አንድነት ላይ መላላት የሚታየው በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱም የአስተሳሰብ ድክመት ነው ሲሉ ምላሽ ይሰጣሉ፡፡
እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ ጉዳዩ ጥናት ማድረግን ይጠይቃል፡፡ ምክንያቱም ስርዓቱ ችግር አለው ከተባለ ለምድን ነው ይህ ሁሉ ዕድገት የመጣው የሚል ጥያቄም ያስነሳል፤ አይ ችግር የለውም ከተባለ ደግሞ ለምድን ነው ይሄ ሁሉ መፈናቀልና ችግር የመጣው ያሰኛል፡፡ ስለዚህ ይህ ጉዳይ መጠናት ያለበትና ውይይትም የሚያስፈልገው ነው፡፡ በእስካሁንም የተለያዩ መድረኮች ቢኖሩም በአብዛኛው በገዥው ፓርቲና በተፎካካሪዎች በኩል የሚካሄዱና ‹‹እኔ ነኝ ልክ እኔ ነኝ ልክ›› ከመባባል ውጭ ጠንካራ ሥራ የተከናወነባቸው አይደሉም ፡፡አሁን አሁን በተለያዩ መድረኮች የሚነሳው አንድነት ላይ በደንብ አለመሠራቱ ነው፡፡
አቶ ሙልዬ እንደሚሉት፤መፍትሄው ሁሉም ከእኔነት ስሜት በመውጣት ለቀጣይ ልማት አብሮነትን ማጠናከር ነው፡፡ አንድ የኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ማህበረሰብ ለመገንባት መንቀሳቀስ የግድ ነው፡፡ ህገ መንግሥቱ የኢትዮጵያውያን ነው፡፡አንድነቱን ይበልጥ ለማጠናከር አመራሩ በየደረጃው ህዝቡም ጭምር ውይይት ሊያደርግ ይገባል፡፡ አገራዊ መግባባት ማለት አንዱ ይህ ነውና፡፡ ምክንያቱም አገራዊ መግባባት ሲባል በፌዴራል ስርዓቱ ላይ የመግባባት ጉዳይ ነው፡፡
በአርሲ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት አግባብነትና ጥራት ዳይሬከተር ዶክተር እንዳለው ፉፋ እንደሚያብራሩት፤ ብዝሃነት ተስተናገደ ማለት አንዱ ከሌላው ተነጥሎ የሚኖር ሆነ ማለት አይደለም፡፡ ሰው በባህሪው ማህበራዊ ነው፡፡በዚህ ውስጥ ደግሞ አንዱ ከሌላው ጋር የመኖር ስጦታ አለው፡፡ ይሁንና ሰው በባህሪው ደግሞ በሚያደርገው እንቅስቃሴ አንዱ ከሌላው እየበለጠ ሊመጣ የሚችልበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ ዋናው ዓላማ ይህ ነው፡፡ የፌዴራል ስርዓት የወል የሆነውን ጉዳይ መጠቀም የሚያስችልና አንድነት ውስጥ ልዩነት የሚከበርበት ነው፡፡
ማንኛውም በኢትዮጵያዊነት የሚጠራ ዜጋ በህገ መንግሥቱ የተሰጡት መብቶች እንዳሉ ሁሉ ግዳጆችም አሉበት የሚሉት ዶክተር እንዳለው፣ የፌዴራል ስርዓት የሚባለው እነዚህን አውቆና አክብሮ እንዲሁም መብትን አስከብሮ ለአገር ውጤታማ ሥራ የሚከናወንበት ነው ይላሉ፡፡
ዶክተር እንዳለው እንደሚሉት፤ ከዚህ ፌዴራል ስርዓት ላይ ለመድረስ ብዙ ዋጋ ተከፍሏል፡፡ ለዘመናት የቆዩ ግጭቶች እንዲሁም አገር ጥሎ እስከ መኮብለል ያደረሱ አመለካከቶች ቢኖሩም፣ በዚህ መካከል የሚተሳሰር ህዝብ እንዳለ ማስተዋል ግን የግድ ይላል፡፡
‹‹በዚህ በፌዴራል ስርዓት ይሄኛው ያልሰለጠነ ያኛው የሰለጠነ የማይባልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፤ አገር የመገንባት፣ ሰው ራሱ ስለአገሩ ያለውን ግንዛቤ ስናይ፣ መብቱን የመጠየቅ አቅሙ፣ ባህሉን፣ቋንቋውን የማክበር መብቱ እና በርካታ ነገሮች እያስተካከሉ መጥተዋል፡፡››ሲሉ ያብራራሉ፡፡ ‹‹ ስህተት የሚሆነው የተለያዩ ህጎችን ደንቦች መመሪያዎችን በሌላ አካል ይተገበርልናል ብለን ስናስብ ነው፡፡ለምሳሌ መንግሥት ይህንን ለምን አላደረገም እንላለን፡፡ መንግሥት ማለት ግን በዴሞክራሲው ስርዓት ህዝብ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ህዝብ መፍትሄ ነው የሚለውን ተምሮና አውቆ ይተገብራል የሚለው ጉዳይ አጠያያቂ ይሆናል›› በማለት ያብራራሉ፡፡
ዶክተር እንዳለው እንደሚናገሩት፤ አሁን የማመዛዘን ችግር ካልሆነ በስተቀር እንደ ፌዴራል ስርዓትነቱ ሰውን የሚጎዳ፣ ሌላውን ነጥሎ የሚመታ፣ አንዱን አክብሮ ሌላውን የሚያርቅ አካሄድ የለውም፡፡ ምናልባት አንዳንድ ሰዎች ያለፈውን አይነት ቀንበር ሊጭኑ ይፈልጉ ይሆናል ፡፡ እነዚህ ግን ቀስ በቀስ ከጨዋታው ውጪ ይወጣሉ ፡፡ ዴሞክራሲ ዝም ብሎ ተፈብርኮ የሚመጣ ጉዳይ አይደለም፡፡ በመሆኑም ብዝሃነት ለዚህች አገር ትልቅ ጥቅም አለው እንጂ የተለየ ጉዳት የለውም፡፡
የፌዴራል ስርዓቱ ይዘት ለኢትዮጵያዊነት ግንባታ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍ ያለ መሆኑ ታምኖበት መነጣጠልን ሊያመጡ የሚችሉ ክፍተቶችን ግን በመረባረብ መድፈን መቻል ዋናው ጉዳይ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ከክፍተቶቹ አንዱ በብሄር ብሄረሰብ ስም የሚመጡ ጥላቻዎችንና ግጭቶችን ማምከን መቻል ያስፈልጋል፡፡
አንዳንዶች በግለሰብ ደረጃ የተደረገን ጸብ ብሄር ከብሄር ጋር እንደተጣላ አድርገው ሲወስዱ ይስተዋላል፡፡ ይህ መቆም ይኖርበታል፡፡ ይህ አይነቱ ድርጊት ጭርሱኑ ከፌዴራል ስርዓት ጋር ተቃራኒ ነው፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ የህጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ህገ መንግሥት አስታራቂ ዳኛ ሆኖ በመካከል አለና እሱን አውቆ መተግበር ከምንም በላይ ውጤታማ ያደርጋል፡፡
መከባበርና መፈቃቀድ ትልቁን ስፍራ ይይዛል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ከተፋለሱ ዋጋ ያስከፍላል፤ የህይወት መጥፋትም ይከሰታል፡፡ አገርም እንደ አገር እንዳይቀጥል ያደርጋል፡፡ ለእነዚህ እሴቶች ራሳችንን ማስገዛት አለብን፡፡ ስርዓቱን ራሱ ህዝቡ በአግባቡ ይረዳ ዘንድ ሥራዎች መሠራት ይኖርባቸዋል ሲሉ ዶክተር እንዳለው ያብራራሉ፡፡
እንደ ዶክተር እንዳለው አባባል፤ ኢትዮጵያዊነትን ለመገንባት ከሌሎች አገሮች ታሪክ መማርም ይጠቅማል፡፡ ከሌሎች ውድቀት መማርም መልካም ነው፡፡የሶሪያንና ሌሎች አገሮችን ተሞክሮ መውሰድ መልካም ነው፡፡ ዛሬም ድረስ ከትንሽነት አልወጡም፡፡ የአንዳንድ አገራት ጉዳይ ሲታይ ከገቡበት ግጭት ያልወጡበት ምክንያት ምን ይሆን ተብሎ ሲፈተሽ ብዝሃነትን አለማክበራቸው ምክንያት ሆኖ ይወጣል፡፡ ሌላው ደግሞ ትውልዱን መልካም የሆነውን ሁሉ ማስተማር ይጠበቃል፡፡ ስለ ኢትዮጵያ የምንገልጽበት ቃል በራሱ አስተማሪ መሆን አለበት፡፡ ጥሩ የሚባሉ አገሮች እኮ የኢትዮጵያውያን አይደሉም፡፡ ከፋም ለማም ኢትዮጵያ የኢትዮጵያውን አገር መሆኗ መዘንጋት የለበትም፡፡
‹‹ቀደም ሲል በአገራችን እኮ ስም እስከመቀየር የተደረሰበት ወቅት መኖሩ አይካድም ፤ ወደ አሁኑ ሲመጣም ማህበረሰባችን እርስ በእርሱ ምን ያህል ተዋውቋል ብለን መጠየቅ ይኖርብናል›› ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
የፌዴራል ስርዓቱ ፍሬያማ እንዳይሆን እንቅፋት የሆኑ ነገሮችም መዘንጋት እንደሌለባቸውም ዶክተር እንዳለው ጠቅሰው፣፡ አንዳንዶች የፌዴራል ስርዓቱን ወደ ጎን ትተው የራሳቸውን ኳስ ሲጫወቱ ይስተዋላሉ ይላሉ፡፡‹‹ህዝብ ተመለሱ ሲላቸው ‹አንተ አመለካከትህ ችግር አለበት› ብለው ያስሩታል፡፡ ለዚህ ሁሉ ችግሩ ስርዓቱን በአግባቡ ካለመፈጸም የመጣ እንጂ ስርዓቱ በራሱ ችግር ሆኖ እንዳይደለ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ይበልጥ ለመገንባት ስርዓቱን በተሻለ መተግበር አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው››ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር ፐሮፌሰር ተሰማ ታኣ፤ ኢትዮጵያ ስትባል አገር ናት፡፡ ይህች አገር እንዴት እንደተመሰረተችና ሰዎቹ እንዴት እንደተሰባሰቡ ደግሞ ከታሪክ መረዳት ይቻላል፡፡ ልዩ ልዩ ብሄር፣ በሄረሰቦችና ህዝቦች አንድ ላይ የተጠቃለሉበት ጊዜ 19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ መሆኑም ሊዘነጋ አይገባም ይላሉ፡፡
‹‹ይህቺ አገር ስትመሰረት ቆይታ እዚህ የደረሰችው በአንድና በሁለት ሰው ብቻ ሳይሆን በብዙሃኑ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ሁኔታ የመጣው ከላይ ወደታች ነው፡፡ ይህ ማለት በኃይል በጉልበትም የሚከናወን ነው ማለት ይቻላል፡፡ በጥቅሉ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አይደለም›› በማለት ያስረዳሉ፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት፤ ቀደም ባሉት ጊዜያትም የብሄረሰብ ግጭቶች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ የማእከላዊውን መንግሥት ለማዳከም ብዙ ጊዜ ተሞክሯል፡፡ የተለያዩ ብሄረሰቦች ከውጪ ሀይሎች ጋር በማበር ማዕከላዊውን መንግሥት ለማዳከም ጥረት ሲያደርጉ ነበር፡፡ ያንን ያደረጉበት ምክንያት መብታቸው ስለተረገጠ ብቻ ነው፡፡ ሀብታቸውንም በአግባቡ ባለመጠቀማቸውም ነው፡፡ ከእነሱ ግብር ይሰበሰባል እንጂ እነሱን የጠቀመ ነገር ባለመኖሩ ማዕከላዊውን መንግሥት በጣም ይቃረኑ ነበር፡፡
ማዕከላዊው መንግሥት ደግሞ ወታደር አደራጅቶ ሁሉንም ዝም ያሰኛል፡፡ከአንዱ ስፍራ አንስቶ ወደ ሌላ ቦታ ወስዶ ያሰፍራል፡፡ ይህ ሁኔታ በመቀጠሉ ችግሮች በአገርና በህዝብ ላይ ያለ መቋጫ ሲቀጥሉ ነበር፡፡ ደርግም አንዳንድ ችግሮችን ሲፈታ የብሄር ብሄረሰቦችን ጥያቄ አልመለሰም ፡፡ የብሄር ብሄረሰብ ጥናት ክፍል አቋቁሟል ፡፡ የተካሄዱት ጥናቶች ግን የት እንደገቡ አይታወቅም፡፡ግጭትን ለማስቀረትና የአገርን አንድነትና ሉዓላዊነት ለመጠበቅ በሚያስችል መልኩ አደራጃለሁ ብሎ ነበር፤ ግን አልሆነም፡፡
በዚህ ምክንያት ነው የትጥቅ ትግል ውስጥ የተገባውና ኢህአዴግም የተመሰረተው፡፡ የነበረውን ችግር ለማስቀረት የህገ መንግሥቱን መሠረት በፌዴራሊዝም ላይ እንዲሆን አድርጓል፤ ፌዴራሊዝሙ የሁሉንም ጥያቄ የሚያስተናግድ ተብሎም ነው በህገ መንግሥቱ ላይ የተደነገ ገው፡፡
እንደ ፕሮፌሰር ተሰማ ማብራሪያ፤ እያንዳንዱ ክልል ራሱን በራሱ እያስተዳደረ ለራሱ የሚገባውን አድርጎ ለማዕከላዊው መንግሥት የመስጠት ያለበትን ፈሰስ በትክክል ማድረግ ሲችል ነው ፌዴራሊዝም የሚመጣው፡፡ ይህን ሲያደርጉ ግን በየክልሉ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችም አሉና ክልሉን እንደራሳቸው መያዝ ይኖርባቸዋል ፡፡ ይሁንታቸውና ፈቃዳቸው መኖር አለበት፡፡ የውስጣቸውን ጸጥታ መጠበቅ መቻል አለባቸው፡፡ በራሳቸው ውስጥ ያሉትን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በልዩ ልዩ ባህል አደረጃጀት አክብረው ሲገኙ ነው ፌዴራሊዝም ግቡን የሚመታው፡፡ በመሰረቱ የኢትዮጵያን ችግር ይፈታል ተብሎ የታሰበው በትክክል ፌዴራሊዝም በስራ ሲተረጎም ነው፡፡
እንደ ፕሮፌሰር ተሰማ ገለጻ፤ የፌዴራ ሊዝም ስርዓት ለኢትዮጵያ መፍትሄ ነው፡፡ ስርዓቱ የእያንዳንዱን ባህል፣ ቋንቋ ጠብቆ የሚያስኬድ በመሆኑ መልካም ነው፡፡ ሰዎች በባህሪያቸው እውቅና ይፈልጋሉ፡፡ ማንነታቸውም የአገር አንድነትም ሳይነካ እንዲሄድ ይፈልጋሉ፡፡ የትኛውም ህዝብ ደግሞ ማንነቱ ከተጠበቀና እውቅና ከተሰጠው ኢትዮጵያን ከተለያዩ ተጽዕኖዎች ያድናል፡፡ ማንነት ካልታወቀ ኢትዮጵያ ለእኔ ምንድን ናት ወደሚለው ያስኬደዋል፡፡
ኢትዮጵያዊነት የምንገነባው ከስር ወደላይ ነው፡፡ እንዲህ ሲባል ብሄር ብሄረሰብ የራሱ ቋንቋና ባህል ከተጠበቀለት ‹‹አገሬ ኢትዮጵያ ናት›› ማለቱ አይቀሬ ነው፡፡ መብቱ ካልተከበረ ደግሞ ‹‹ትችያት ነው የምወጣው ›› ሊል ይችላል ሲሉ ያብራራሉ ፡፡
እንደ ፕሮፌሰር ተሰማ አገላለጽ ፤ይህ የፌዴራል ስርዓት እንደሚጠበቀው ተግባራዊ ካልተደረገ እንዳለፈው ስርዓት ማንኛውም ትዕዛዝ ከላይ ወደታች ብቻ ይወርዳል፡፡ በዚህ አይነቱ አካሄድ ደግሞ መተማመን አይኖርም፡፡ በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ማንም ማንንም መግዛት አይችልም፡፡ እንደገና ትግል ይከሰታል፡፡ ህግ የሁሉም የበላይ ነው፡፡ ስለዚህም በህግ ነው መንቀሳቀስ የሚጠበቀው፤ የፌዴራል ስርዓቱን በአግባቡ መተግበር ያስፈልጋል ፡፡
በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የአመራርና አስተዳደር ኮሌጅ ዲን ዶክተር አታክልት ሀጎስ እንደሚሉት ፤፤ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ ሰው ለብሄሩ ይበልጥ የመወገን ነገር ይታይበታል፡፡ በራስ ብሄር ላይ ብቻ ትኩረት የማድረጉ ነገር እየጎለበተ በመምጣቱ አገር የተባለው ነገር እየተቀዛቀዘ ነው፡፡
እንደ ዶክተር አታክልት ገለጻ፤የፌዴራል ስርዓቱ ህገ መንግሥቱ ሰው ሰው በመባሉ እንዲኮራ፣ በቋንቋው እንዲማርና መሰል ጉዳዮችን እንዲያደርግ አስችሏል፡፡ አንድ ክልል በራሱ ልጆች መተዳደሩም መልካም ነው፡፡
ይህ ስርዓት ለአንዳንድ ቡድኖች አመቺ ማደናገሪያ እንደፈጠረላቸውም ነው ዶክተር አታክልት የሚናገሩት፡፡ አንዳንዶች ብሄርን ከለላ አድርገው አንዳንድ ጥቃቶችን በዜጎች ላይ ሲሰነዝሩ መታየታቸውን በመጥቀስም ስጋታቸውን ያመለክታሉ፡፡
እንደ ዶክተሩ ገለጻ፤ በተለያዩ ክልሎች ማፈናቀሉ ጎልቶ የታየውም ይህ ክልል የእኔና የእኔ ለሆኑት ብቻ ነው ከሚል አመለካከት የመጣ በመሆኑ ነው፡፡ይህ ደግሞ አግባብ አይደለም፡፡
‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን ከምስራቅ አፍሪካ ጋር አንድ እንሁን እንተሳሰር እያልን ነው›.ሲሉ አብራርተው፣በእርግጥ ሁሉም ስርዓት የራሱ ጥቅምና ጉዳት አለው፡፡ የስርዓቱ ደካማና ጠናካራ ጎን ምንድን ነው በማለት በመለየት ጥንካሬውን መጠቀም ደካማ ጎኑን ደግሞ በሂደት ለማስወገድ መሞከር ግድ ይላል ብለዋል፡፡
‹‹ስርዓቱ ችግር የለበትም፤ የምንጠቀመው ሰዎች ነን እያበላሸን ያለነው፡፡ ቋንቋም ቢሆን የእኔ ብቻ ብለን የምንቀር ከሆነ የአንድ አገር ሰዎች ሆነን ባዕዳን እንዳንሆን እሰጋለሁ፡፡››ያሉት ዶክተር አታክልት፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የትም ሄዶ የመኖር መብቱ መከበር እንዳአለበት፣ ብሄርን ብቻ እንደ ሽፋን እያደረጉ መንቀሳቀስ እምብዛም ሊመከር እንደማይገባ እና ይህ አይነቱ አካሄድ ኢትዮጵያዊነትን በመገንባት ሂደት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳርፍ ያስገነዝባሉ፡፡
እንደ ሙሁራኑ አገላለጽ ፤ ፌዴራሊዝም ለኢትዮጵያ አማራጭ የሌለው ስርዓት ነው፡፡ ስርዓቱ የህዝብን መብት ያረጋገጠ ስለመሆኑም ይታመናል፡፡ ለዘመናት ጥያቄ ሆኖ የቆየውንም ችግር ፈትቷል፤ ነገር ግን በዚህ ስርዓት ሽፋን የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ አካላት ህዝብን ከለላ አድርገው የራሳቸውን ዓላማ ሲፈጽሙ ይስተዋላል፤ በዚህም ስርዓቱ በአግባቡ እንዳይተገበር ሲያደርጉም ይታያሉ፡፡ ይህ ደግሞ ኢትዮጵያዊነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳርፋልና እነዚህ ወገኖች ስርዓቱ ከሚፈቅደው ውጭ ለራሳቸው ጥቅም የሚያደርጉትን ሩጫ መግታት ይኖርባቸዋል፡፡

አስቴር ኤልያስ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።