በዲላ ዩኒቨርሲቲ በተደጋጋሚ የሚበቅለው የኦዲት አረም Featured

16 May 2018

የፌዴራል ዋና ኦዲተር በ2008 ዓ.ም በሰራው ሂሳብ በዲላ ዩኒቨርሲቲ ጉድለቶች ማግኘቱን አስታውቆ ነበር፡፡ በኦዲት ግኝቱ የሂሳብ አሰራርን የተላለፉ፣ ያልተሰበሰቡ፣ የተጓደሉና ሌሎች ህጸጾችን ዩኒቨርሲቲው እንዲያስተካክል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ ሚያዝያ 15 ቀን 2010 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት እና የዲላ ዩኒቨርሲቲ ኃላፊዎች የተወሰደውን ማስተካከያ ገምግመዋል፡፡
በጥሬ ገንዘብ ቆጠራ ወቅት 37ሺ 900 ብር በመብለጥ የተገኘበት ምክንያት አለመታወቁ፣ ከልዩ ልዩ የገቢ ምንጮች የተሰበሰበ ሁለት ሚሊዮን 833ሺ 280 ብር ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ሪፖርት አለመደረጉ በመደበኛ ሰዓት ሊሰሩ የሚገባቸው ስራዎች በኮንትራት መሰራታቸው፤ የትርፍ ሰዓት፣ የማበረታቻና የአስተባባሪነት በሚል የሚመለከተው አካል ሳይፈቅድ አምስት ሚሊዮን 846ሺ 079 ብር መከፈሉ በኦዲት ግኝት መረጋገጡን ቋሚ ኮሚቴው አንስቷል።
በህጉ መሰረት ትክክለኛ ደረሰኝ መጠቀም እየተገባ ዩኒቨርሲቲው በዱቤ ሽያጭ የአምስት ሚሊዮን 413ሺ 691 ብር ግዥዎችን ፈጽሟል። በዩኒቨር ሲቲው ዋና ግቢ 504ሺ 084 ብር በወጪ ተመዝግቦ ሳለ በድጋሚ ለጤና ሳይንስ ኮሌጅ በዝውውር ተከፍሏል። ለዩኒቨርሲቲው ግንባታ ከሚያከናውኑ ዘጠኝ ሥራ ተቋራጮች እና ውል ገብተው በወቅቱ እቃ ካላቀረቡ ድርጅቶች ዘጠኝ ሚሊዮን 701ሺ 565 ብር አልሰበሰበም፡፡
በጨረታ መገዛት ሲገባው ህግ በመተላለፍ በቀጥታ ግዥ እና ከተቀመጠው የግዥ ጣሪያ በላይ በዋጋ በማወዳደር በድምሩ ሶስት ሚሊዮን 261ሺ 865 ብር ወጪ ተደርጓል። በ2008 በጀት ዓመት ሊሠሩ ከታቀዱ ሥራዎች በጀት ዓመቱን ያልጠበቀ የ30 ሚሊዮን 113ሺ 316 ብር ግዥ ተከናውኗል፡፡ በኦዲት ናሙና ከተመረጡ ሰነዶች ውስጥ ስድስት ሚሊዮን 873ሺ 851 የያዙ የ16 የክፍያ ሰነዶች ለኦዲት አለመቅረ ባቸውንም ቋሚ ኮሚቴው አንስቷል።
በግዥ መመሪያው ለተጨማሪ ግንባታ ቀደም ሲል ከተገባው ውል ከ25 በመቶ መብለጥ እንደሌለበት ቢያስቀምጥም ለዩኒቨርሲቲው ስብሰባ አዳራሽ ተጨማሪ ዕድሳት መከፈል የሚገባው 274ሺ 696 ብር ሆኖ ሳለ አራት ሚሊዮን 720ሺ 701 ብር ተከፍሏል። ለግንባታ የሚፈፀመው ክፍያ በአማካሪ መሀንዲስ በሚሰጥ የስራ አፈጻጸም ምስክርነት መሆን ሲገባው፤ ለ21 የግንባታ የስራ ተቋራጮች እና ጂ አይ ዜድ ለተባለ ድርጅት የምስክር ወረቀት በአማካሪው ሳይረጋገጥ እና ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር የተደረገ የውል ሰነድ ሳይቀርብ 44 ሚሊዮን 36ሺ433 ብር ከመመሪያ ውጪ ክፍያ ተፈጽሟል።
ትምህርት ሚኒስቴር ሲያሰራቸው ከነበሩ ተቋራጮ ወደ ዩኒቨርሲቲው ገቢ የሆነውን 16 ሚሊዮን 501ሺ 754 ብር ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በወቅቱ ፈሰስ አላደረገም። በውጭ አገር አስተምሯቸው በውላቸው መሠረት ካላገለገሉት ግለሰቦች ላይ መሰብሰብ የሚገባውን 142ሺ 740 ብር ገቢ አላደረገም። አንድ መምህር ደግሞ ውል ሳይፈጽም ለትምህርት ወደ ውጭ አገር እንዲሄድ መደረጉም ተመልክቷል፡፡
በተሰብሳቢና ተከፋይ ሂሳብ በኩል ከአንድ እስከ 14 ዓመት የቆዩ ስምንት ሚሊዮን 405ሺ 369 ብር በወቅቱ እንዲወራረድና እንዲሰበሰብ አለመደረጉ፣ በኮንትራት መያዣነት 12 ሚሊዮን 784ሺ 647 ብር የግዴታ ውል ተገብቶባቸው በወቅቱ አለመወራረዳቸው፤ ከውስጥ ገቢ፣ ከካፒታል እና ከመደበኛ በጀት 32 ሚሊዮን 255ሺ 614 በዕቅዱ መሰረት አለመፈጸሙ ተነስቷል፡፡
ከንብረት አስተዳደርና አወጋገድ ጋር በተያያዘ በአንድ ሚሊዮን 720ሺ 500 ብር የተገዙ ዕቃዎች በቴክኒክ ኮሚቴ ሳይረጋገጡ ገቢ ተደርገዋል፡፡ እንዲሁም በሶስት ሚሊዮን 184ሺ ብር የተገዙ ጤፍና ማርማላት ወደ ንብረት ክፍል መግባታቸውን የሚያረጋግጥ የገቢ ደረሰኝ በኦዲት ወቅት አልቀረበም። ከ2006 እስከ 2008 በጀት ዓመት ርክክብ የተፈፀመባቸው ህንፃዎች እና መኖሪያ ቤቶች በቋሚ ንብረት አልተመዘገቡም። የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው የቤተ ሙከራ ኬሚካሎችና መድኃኒቶች አለመወገዳቸው፤ በርካታ ወንበሮችና 25 ተሽከርካሪዎች ተጠግነው አገልግሎት እንዲሰጡ ወይም እንዲወገዱ አለመደረጋቸውም ተጠቅሷል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የሥጋት ተጋላጭነት የዳሰሳ ጥናት አለማድረጉም በኦዲት ግኝቱ ተመላክቷል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው የዩኒቨርሲቲው ስራ አመራር በ2006 እና 2007 በጀት ዓመት የሂሳብ ግኝቶች ላይ የዋና ኦዲተር የማሻሻያ ምክረ ሃሳቦችን ተቀብሎ የዕርምት እርምጃ አለመውሰዱን ጠቁሟል፡፡ ለ2008 በጀት ዓመት የኦዲት ግኝትም በአብዛኛው ምላሽ እንዳልሰጠ ተመልክቷል፡፡ የዩኒቨርሲቲው አመራር በባለቤትነትና በተጠያቂነት ኃላፊነቱን የማይወ ጣበት፤ ለመንግስት ደንብና መመሪያ ተገዥ የማይሆንበትን መሠረታዊ ምክንያት እንዲያብራራ ቋሚ ኮሚቴው ጥያቄ አቅርቧል፡፡ በተነሱት የሂሳብ ግኝቶች ላይ የተወሰደውን የእርምት እርምጃ እንዲያስረዳም ተጠይቋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ቃልኪዳን ነጋሽና ሌሎች የስራ ኃላፊዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በሪፖርቱ በመብለጥ የተገኘው 37ሺ 900 ብር ለሪፈራል ሆስፒታል ሰራተኞች ሊከፈል የተዘጋጀና በእለቱ ለሰራተኞቹ መከፈሉ አስፈላጊ ማስረጃዎችን በማቅረብ ከዩኒቨርሲቲው የውስጥ ኦዲት ጋር መግባባት ላይ መደረሱን ኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡ በማነስ ሪፖርት የተደረገው ገንዘብ ለህክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅና ለሪፈራል ሆስፒታል መድሃኒትና የህክምና መሳሪያዎች ከዕቅድ በላይ በመገዛታቸው ለተፈጠረው የገንዘብ እጥረት የተጠቀሰው ገንዘብ ፈሰስ ሳይደረግ አሰራሩን ጠብቆ ለዩኒቨርሲቲው ወጪ ተደርጓል ብለዋል፡፡
ኃላፊዎቹ እንዳሉት አላግባብ የተከፈሉ ክፍያዎችና ጥቅማ ጥቅሞች በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ተቋርጠዋል። ከሥራ ባህርያቸው አንፃር የትርፍ ሰዓት ክፍያ የሚያስ ፈልጋቸው የሥራ ክፍሎች ተለይተው ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ከፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ሚኒስቴር በተገኘ ፈቃድ መሰረት እየተከፈለ ነው፡፡ ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በመምጣት በማማከርና በማስተባበር የሚሰሩ መምህራንና በድህረ ምረቃ ፕሮግራሞች የሚከፈሉ ክፍያዎችን ማቆም በትምህርት ስራው ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ስላለው በአስተዳደር ካውንስሉ ፀድቀው የነበሩ ክፍያዎች ዝርዝር ጥናት ተደርጎባቸው በቦርድ እንዲፀድቁ ይደረጋል ብለዋል፡፡
በወቅቱ በፋይናንስ የስራ ክፍል የሠነድ አያያዝ ችግር ደጋፊ ማስረጃ ያልቀረበለትና በዱቤ ሽያጭ የተወራረደ ሂሳብ አሁን ደጋፊ ማስረጃዎች መቅረባቸውን ነው ኃላፊዎቹ ያስረዱት፡፡ አላግባብ የተመዘገበው ሂሳብ በሂሳብ ሰነድ ወይም ፋይናንሻል ስቴትመንት ላይ ስለተዘጋ በቀላሉ በዩኒቨርሲቲው የሚፈታ ባለመሆኑ ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ድጋፍ እንዲደረግ ጥያቄ ቀርቦ ባለሙያ እስኪላክ እየተጠበቁ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ኃላፊዎቹ እንዳሉት፤ አብዛኛዎቹ የግንባታ ፕሮጀክቶች ባለመጠናቀቃቸው ወደ ጉዳት ካሳ ጥያቄ ደረጃ አልተደረሰም፡፡ ፕሮጀክቶቹ የሚዘገዩት በዩኒቨርሲቲውና በአማካሪ ድርጅቶች ችግር ጭምር በመሆኑ ሥራ ተቋራጮችን ብቻ ለመጠየቅ አመቺ አልሆነም፡፡ በቀጥታና በዋጋ ማወዳደሪያ የተፈፀመው ግዥ የውሃ መሳቢያን (ፓምፕ) ለመሳሰሉ አጣዳፊ ችግሮች ምላሽ ለመስጠት ነው። የግዥ ችግሮች ከአሰራር ጋር የተያያዘ መሆኑ በግምገማ በመረጋገጡ የግዥ ዳይሬክተሩን በመቀየር ከ2009 ዓ.ም የግዥ ሥርዓቱ የተሻለ ሆኗል፡፡
የተማሪዎች የመፀዳጃና መታጠቢያ ቤቶች እጥረት ስለነበር በወቅቱ አዲሱ የዩኒቨርሲቲው አመራር ችግሩን ለመቅረፍ ከእቅድ ውጪ ግዥ ማከናወኑ ተመልክቷል፡፡ እንደ ጄኔሬተር ያሉ አንገብጋቢ ግዥዎች መፈፀማቸው እና ከበጀት ዓመት የተሻገሩ ክፍያዎች መኖራቸውንም ኃላፊዎቹ ተቀብለዋል፡፡ የተማሪዎች የምግብ አቅርቦት ከጨረታ በኋላ በሚከሰቱ የዋጋ ጭማሪዎች እና ሌሎች ምክንያቶች የተነሳ ክፍያው ለውጥ እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው 29ኛውን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጉባኤ እንዲያስተናግድ በመመረጡ ደረጃውን የጠበቀ አዳራሽ መገንባት በማስፈለጉ ለስብሰባ አዳራሹ ተጨማሪ ክፍያ መፈፀሙ በኃላፊዎቹ ተመልክቷል፡፡ ይህም በመመሪያው ከተፈቀደው ጣሪያ በላይ ክፍያ እንዲወጣ አድርጓል፡፡ የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ለመጀመሪያው የህንፃ እድሳት ግዥ ፈቃድ በመስጠቱ ተጨማሪ ስራውን ሳያስፈቅድ ጥገናው መካሄዱ ስህተት መሆኑን ጠቁመው ጥፋቱን በፈጸመው የቀድሞው አመራር ላይ እርምጃ አለመወሰዱም ተጨማሪ ክፍተት ነው ተብሏል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከአማካሪ ድርጅት ጋር የሁለትዮሽ ውል በመግባት የ21 ግንባታዎችን ክፍያ ፈጽሟል። የዩኒቨርሲቲው ግንባታ ፕሮጀክት አስተዳደር ጽህፈት ቤት ፈጸመ የተባለው ክፍያ ዩኒቨርሲቲዎች በራሳቸው አቅም መስራት ለሚችሉት መለስተኛ ፕሮጀክቶች የግድ አማካሪ መቅጠር እንደማያ ስፈልጋቸው ከትምህርት ሚኒስቴር የወረደውን መመሪያ መሰረት በማድረግ ነው የተከናወነው፡፡ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዩኒቨርሲቲው በመመሪያው መሠረት መፈጸሙን አስታውቋል፡፡ ክፍያውን ለመፈፀም የሚያስችል ዝርዝር መረጃ ስለነበረ ለጂ አይ ዜድ ክፍያው መፈጸሙን ኃላፊዎቹ ገልፀዋል፡፡
ተሰብሳቢ ሂሳብ ለበርካታ ዓመታት የዩኒቨር ሲቲው ችግር ሆኖ መቆየቱን ኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡ የብዙ ዓመታት ተሰብሳቢ ሂሳብ ተንከባሎ መምጣቱን በመጠቆም ይህንንም በየመደቡ ዝርዝር አስረድተዋል፡፡ ከተሰብሳቢ ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆነው ለመምህራን የተሰጠ ብድር ነው። ከ2009 ዓ.ም የመጣው አዲሱ አመራር የሚሰጠው ብድር በመቆሙም ብድሩን እየሰበሰበ ነው። ሌሎች ተሰብሳቢ ሂሳቦችን በተመለከተ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ጋር ውይይት እየተደረገ ሲሆን፤ ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ በተወሰኑት ላይ እርምጃ መወሰድ ይጀመራል፡፡ በኃላፊዎች መቀያየር ምክንያት መፍትሄ ማግኘት ያልቻሉ መኖራቸውን በማንሳት ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ለመስጠት እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡
በየዘርፉ ኮሚቴዎች በአግባቡ ተዋቅረው እቃዎቹ በናሙናው መሠረት መቅረባቸው እየተረጋገጠ ገቢ እየተደረገ ነው። ከህንፃ ምዝገባ ጋር በተያያዘ ችግር መኖሩን ገልጸዋል፡፡ ነባርና አዳዲሶቹ ህንፃዎች አለመመዝገባቸውን ጠቁመው፤ አሁን የመመዝገብ ሥራ ተጀምሯል። ንብረት ሳያስረክቡ የሚሄዱ ሠራተኞች ጉዳይ በውስጥ ድክመት የተፈጠረ ሲሆን፤ የለቀቁትን ተከታትሎ ንብረት የማስመለስ እና በህግ የመጠየቅ ድክመቶች መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡
በሀገር ደረጃ ኬሚካሎችን ማስወገድ ከባድ በመሆኑም ለሚመለከተው አካል በማሳወቅ ችግሩ የሚፈታበት ሁኔታ እየተጠና ነው፡፡ የጤና ጉዳት እንዳይከሰት ሰው ሊደርስበትና ብዙ ንኪኪ ሊኖር በማይችል መጋዘን ውስጥ ኬሚካሎቹ ታሽገው በጥንቃቄ እንዲቀመጡ መደረጉን አመላክተዋል፡፡
ለብልሽት የተጋለጡ በርካታ ወንበሮችን ለማስጠገን ጥረት መደረጉን፤ ሊጠገኑ የማይችሉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ንብረቶችን የማስወገድ ሥራ መከናወኑን፡፡ የተበላሹ ተሽከርካሪዎች ቁጥር መቀነሱንና በጣም ከባድ ችግር ያለባቸውን ለመለየት ጥናት እየተደረገና ለማስወገድ መታቀዱን ኃላፊዎቹ አንስተዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲውን የስራ ኃላፊዎች ምላሽ ተከትሎ የቋሚ ኮሚቴው አባላት ጥያቄዎችንና አስተያየ ቶችን አቅርበዋል፡፡ የተጠያቂነት ስርአት አለማ ስፈን፣ የውስጥ ቁጥጥር ስርአትን አለማ ጠናከር፣ የውስጥ ኦዲት የስራ ክፍልን በመደገፍና የሚያወጣቸውን የኦዲት ሪፖርቶች ተከትሎ እርምጃ አለመውሰድ፣ ለጂአይዜድ ለተፈጸመው ክፍያ መረጃ ካለ አለመቅረቡ፣ ለዩኒቨርሲቲው እድሳት ከመመሪያ ውጪ አላግባብ ለተከፈለው አራት ነጥብ አራት ሚሊዮን ብር እርምጃ አለመወሰዱ፣ ዩኒቨርሲቲውን ከተሰብሳቢ ሂሳብ ነጻ ለማድረግ ቅድሚያ ሰጥቶ አለመሰራቱ፣ የተከማቹና የተበታተኑ ሰነዶችን በቴክኖሎጂ በመታገዝ አደራጅቶ ለመያዝ አለመታቀዱ፤ የዋና ኦዲተር ግኝትን እንደግብአት በመውሰድ ደንብና መመሪያን አክብሮ አለመሰራት ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል ናቸው፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ቃልኪዳን ፤በመርህ ደረጃ የቀጥታ ግዥ መፈፀም ባይገባም፤ በግዥ ህጉ በተቀመጠው መሠረት ግዥው አስፈላጊና አስቸኳይ ከሆነ በማኔጅመንት አስፈቅዶ ቀጥታ ግዥ መፈጸም እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም በተማሪዎች መኝታ ክፍል መቃጠልና በውሃ አቅርቦት ችግር ግዥው መፈፀሙን አስረድተዋል፡፡ ከጉዳዩ አጣዳፊነት አንፃር ለመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ለማሳወቅ ጊዜ ስለሚወስድ ይህን ማድረግ አልተቻለም። ክፍሉን በአዲስ መልክ ለማደራጀት መታቀዱን ገልጸዋል፡፡ ለአዳራሽ ጥገና ከተፈቀደው የክፍያ ጣሪያ በላይ መከፈሉ ጥፋት ቢሆንም ገንዘቡ በአግባቡ የተከፈለ በመሆኑ እንደባከነ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። አዲሱ አመራር የኦዲት ግኝቶችን መሠረት አድርጎ እየሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ፤ ፈስስ የሚደረግን ገንዘብ መደበቅ፣ የትርፍ ሰዓትና የማስተባበሪያ ክፍያን ማቆም ብቻ ሳይሆን አለማስመለስ፣ ዩኒቨርሲቲው ግንባታዎችን ከመጀመሩ በፊት ቅድመ ዝግጅት አለመደረጉ ክፍተት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ክፍያዎችን ከበጀት ዓመቱ ዕቅድ ጋር አጣጥሞ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የገበያ ጥናት ሳይደረግ ለአዳራሽ ጥገና ለወጣው ገንዘብ የሚመለከተው አካል ሊጠየቅ እንደሚገባም አስጠንቅቀዋል። ለትምህርት ወደ ውጪ አገር ለሚሄዱ መምህራን የሚሠጥ ብድር ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ቢቆምም ዩኒቨርሲቲው በ2009 በጀት ዓመት ብድር መስጠቱን አቶ ገመቹ ተናግረዋል፡፡ ይህን ያደረጉና የክፍያ ሠነዶችን ያረጋገጡ ኃላፈዎችን ተጠያቂ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ከጂ አይ ዜድ ጋር ውል የፈጸመው ትምህርት ሚኒስቴር ሆኖ ሳለ ዩኒቨርሲቲው ስራው ስለመከናወኑ የማረጋገጫ ሰነድ ሳይሟላ ክፍያ መፈጸሙ ስህተት በመሆኑም ሊታረም ይገባል ብለዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሪት ወይንሸት ገለሶ፤ የዩኒቨርሲቲው አዲስ አመራር አሰራሮችን ለመዘርጋትና ችግሮችን ለመፍታት እያደረገ ያለውን ሙከራ በማድነቅ፣ የተቀናጀ የሙስና መከላከያ ስትራቴጂ ማዘጋጀቱንም በጥንካሬ አንስተዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የወሰዳቸውን እርምጃዎች ለዋና ኦዲተርና ለሚመለከታቸው አካላት በየጊዜው ማሳወቅ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
የተቀናጀ የሙስና መከላከያ ስትራቴጂውን ተግባራዊ ማድረግ፣ በኦዲት ግኝቶች ላይ እርምጃ መውሰድ፣ ከደንብና መመሪያ ውጪ ክፍያዎች እንዳይፈፀሙ፤ የተከፈሉ እንዲመለሱ ማድረግ ይገባል፡፡ በግንባታ ፕሮጀክቶች አካባቢ ያለውን አሰራር ማጥራትና ለኪራይ ሰብሳቢነት በር የሚከፍቱ ጉዳዮችን ማስተካከል፣ የውስጥ ኦዲትን ማጠናከር፣ የበጀት አጠቃቀምና ግዥን በእቅድ መምራትም አመራሩ ትኩረት ሊሰጥባቸው የሚገቡ ጉዳዮች መሆናቸው ተመልክቷል፡፡ ተሰብሳቢ ሂሳቦችን ለይቶ እንዲመለሱ መስራት፣ ያገለገሉ ንብረቶችን በህጉ መሠረት ማስወገድ የዩኒቨርሲቲው ኃላፊዎች ቀጣይ የቤት ሥራዎች ናቸው፡፡

አጎናፍር ገዛኸኝ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።