«የሚሠሩ ሥራዎች ሕግን የተከተሉ መሆናቸው መታወቅ አለበት» - የፖለቲካ ተንታኝ አቶ ሙሼ ሰሙ Featured

09 Jun 2018
«የሚሠሩ ሥራዎች ሕግን የተከተሉ መሆናቸው መታወቅ አለበት» - የፖለቲካ ተንታኝ አቶ ሙሼ ሰሙ ፎቶ ከዶክመንት

የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)ን ከመሰረቱት አንጋፋ ፖለቲከኞች_ አንዱ ናቸው፡፡ ፓርቲውን ከ1992 ዓ.ም ጀምሮ በሕዝብ ግንኙነት ኃላፊነት፣ በዋና ፀሐፊነትና በፕሬዚዳንትነት አገልግለዋል። ከሦስት ዓመት በፊት ከፓርቲው ቢለቁም በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ሃሳባቸውን ከመስጠት፤ አገራዊ በሆኑ የውይይት መድረኮች ላይ ከመሳተፍ አልተቆጠቡም አቶ ሙሼ ሰሙ። አሁን ባለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያም ቃለምልልስ አድርገናል። መልካም ንባብ!
አዲስ ዘመን፡- አሁን ያለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ በእርሶ ዕይታ ምን ይመስላል?
አቶ ሙሼ፡- የፖለቲካ ሁኔታው ሽግግር ላይ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ገና የተጀመረ በመሰራት ላይ ያለ የፖለቲካ ሂደት ነው፡፡ ይህ የፖለቲካ ሂደት የተፈጠረው በሕዝቡ ነው። ሕዝቡ በተለያየ ጊዜ ውስጥ ሲከማቹበት የነበሩ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ቀውሶቹ ከሚሸከመው በላይ ስለሆነበት መንግሥት የአቅጣጫ ለውጥ እንዲያመጣ በአመፅ መልክ ጠይቋል፡፡ መንግሥትም ይህንን በተለመደው መልኩ ሰላማዊ ሰልፎችንና ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎችን በማዳከምና ከጨዋታ ውጪ ማድረግ የማይችልበት ደረጃ ላይ ስለደረሰ በራሱ ለውጥ እንዲኖር አስገድዷል፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ ድርጅታዊ ለውጥ እያካሄደ ነው፡፡ ድርጅታዊ ለውጡ ደግሞ እስከዛሬ ካየነው ለውጥ በይዘቱም ሆነ በባህሪው የተለየ ነው፡፡ ለውጡ ገና ጅምር ነው፡፡ ውጤቱ ደግሞ ወደ ፊት ይታያል፡፡ መዘንጋት የሌለበት ሕዝቡ መንግሥት ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ለውጥ እንዲያመጣ ያስገደደው መሆኑን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እስከ አሁን በጅምር ደረጃ ያሉት ለውጦች እንዴት አዩአቸው?
አቶ ሙሼ፡- እስከ አሁን የሚታየው በጽሑፍ የቀረበ ቃልኪዳን ብቻ ነው፡፡ በተግባር የታየው የእስረኞች መፈታት ነው፡፡ ከኢህአዴግ አስቸጋሪ ባህሪ አኳያ ሲገመገም ቃል መገባቱ ብዙም የሚያስደንቅ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም የኢህአዴግ ታሪክ ወደ ኋላ ሲታይ ቃል የገባውን የማስፈፀም ብቃትም፣ አቅምም ሆነ ተነሳሽነት እንዲሁም ቁርጠኝነት ኖሮት አያውቅም፡፡ አሁን ግን እየተገቡ ያሉ ቃሎች እንዲፈፀሙ ያለው ፍላጎት መልካም ነው፡፡ ሌላው ተወደደም ተጠላ ኢትዮጵያ ላይ አንዣቦ የነበረው አስከፊ አለመረጋጋት፣ የደም መፋሰስና የዕልቂት ስጋት መብረዱ አንድ እርምጃ ወደፊት መባሉን ያሳያል፡፡
በተግባር የታየውም የእስረኞች መፈታት እንደትልቅ ለውጥ መቁጠር ይቻላል፡፡ ምክንያቱም የብዙ ነገሮች መሠረት ሰላምና መረጋጋት ነው፡፡ የሕዝቦችን አንድነት ለማምጣት ቂም፣ በቀልና ቁርሾን መርሳት ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን ሕጋዊ መሠረትን መከተል ደግሞ የግድ ይላል፡፡ እንደየጥፋቱ ደረጃ፣ ሚዛንና ዓይነት ሰዎችን ይቅር ብሎ ማህበረሰቡን እንደገና እንዲያገለግሉ ዕድል መስጠት ትልቅ እርምጃ ነው፡፡ በአጠቃላይ ስንመለከት ጉዳዮችን በቀናነት የማየት መንፈስ አለ፡፡ ነገር ግን ይህ የሁሉ ነገር መጀመሪያና መጨረሻ ነው ማለት አይቻልም፡፡
በኢህአዴግ በኩል ብዙ ለውጦች እንደሚኖሩ በመገለፅ ላይ ይገኛሉ፡፡ ለውጦቹ በንባብ በየስብሰባዎቹ እየተነገሩ ናቸው፤ በፖሊሲ ደረጃ ተካተው በአዋጅ በመመሪያ በደንቡ መሠረት ሲወጡ አልታዩም፡፡ ስለዚህ መተማመን የሚቻለው የተባለውን ለማስፈፀም አዋጅ ሲወጣ፤ ደንብ ሲሆኑና ወደ ተግባር ሲገባ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሕገመንግሥቱ አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብን መገንባት ይገባል ተብሎ ቢቀመጥም፤ በተግባር ልዩነት ሰፊውን ድርሻ ወስዶ ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር አንድነትን መስበክና በቃልም ቢሆን ብዙ ተግባራት እንደሚፈፀሙ መናገር ቀላል ነው?
አቶ ሙሼ፡- ከላይ እንደገለፅኩት ነው፡፡ ኢህአዴግ በተለምዶ የመጣበትን አብዮት ለመቀልበስ ሲፈልግ ቃል መግባት ተፈጥሯዊ መለያው ነው፡፡ ይህንን ላለፉት 27 ዓመታት አብረነው ስንኖር አይተነዋል፡፡ ነገሮች ከተረጋጉና ሁሉም ወደ የሥራውና ወደ ዕለት ተዕለት ሕይወቱ ካመራ በኋላ ወደ ነበረበት ይመለሳል፡፡ ኢህአዴግ የመጣው ይህንን ባህሪውን አድሶና ለለውጥ ተዘጋጅቶ ነው ከተባለ፤ ዕድል መሰጠቱ ትክክል ነው፡፡ በነበረ ታሪክ መውቀስና መክሰስ በቂ አይደለም፡፡ አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ተነስቶ ቃል እየተገቡ ያሉት ነገሮች ሁሉ ወደ ተግባር ይሸጋገራሉ ብሎ ተስፋ ማድረግ ትክክል ነው፡፡ ምክንያቱም ቃል እየተገቡ ያሉት ጉዳዮች በሦስትና በጥቂት ቀናት ውስጥ ዕውን ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ሂደትን ይጠይቃል፡፡ ኢትዮጵያ ካለችበት ውስብስብ ችግር ኢኮኖሚውም ሆነ ፖለቲካዊ እንዲሁም ማህበራዊ ቀውስ ለማውጣት በጣም ብዙ ጉልበት ጊዜና ገንዘብ የሚጠይቅ ነው፡፡ መጀመሪያ ይህንን ለመለወጥ ፍላጎት መኖሩ በራሱ አንድ እርምጃ ወደ ፊት ነው ማለት ይቻላል፡፡
ቃል ብቻ በቂ አይደለም የሚያስብለው አንዳንዴ ቃል የተገቡት ነገሮች ወደ ፖለቲካ ሊመነዘሩ የሚችሉ አይደሉም፡፡ መተባበር፣ መቻቻል፣ ቅድሚያ መስጠት፣ መፋቀር የሚባሉት ነገሮች ወደ መሬት ወርደው ለመተግበርና የሰዎችን ሕይወት ለመለወጥ ጊዜ የሚጠይቁ ናቸው፡፡ የመግባቢያ መነሻ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በሥራ ሊመነዘሩ አይችሉም፡፡ የሰውን ኑሮ ሊያሻሽሉና የመደራጀትና ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ዕውን ሊያደርጉለት አይችሉም፡፡ ዋናው ነገር እነዚህ በሕግ መረጋገጥ አለባቸው፡፡ በቃል የሚነገሩ ነገሮች ሕግ ስለማይሆኑ ዋጋ አይኖራቸውም፡፡ እነዚህ ነገሮች የሌላውንም ፍላጎት ይጠይቃሉ፡፡ ኢህአዴግ ይህን በማለቱ ብቻ ሌላው ሰው ይህን ይፈልጋል ማለት አይደለም፡፡
ሰሞኑን እንደተደረገው ዓይነት የኢኮኖሚ ፖሊሲ አቅጣጫን ማስቀመጥ ግን ተግባራዊ እርምጃ ነው፡፡ የአሁኑ ቃል ይለያል ከተባለ ሕጎች መመሪያዎችና ደንቦች እየፀደቁለት ወደ ተግባር መገባት ሲቻል ነው፡፡
ኢትዮጵያ ምስቅልቅል ውስጥ በገባች ቁጥር ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስብሰባ ይጠራሉ፡፡ ድርድር ይደረጋል፤ ነገር ግን ድርድሮቹ የትም አልደረሱም፡፡ አሁን ለውጥ ካለ ሕጎችንም መለወጥ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ የፀረ ሽብር ሕጉ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ እንቅፋት ነበር፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ማቋቋሚያ አዋጅ፣ የፕሬስ ሕጉም ሌሎችም ችግር የሆኑ ሕጎች በመለወጥ ቁርጠኝት መኖሩን ማሳየት ያስፈልጋል፡፡
አሁን ኢትዮጵያ ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ጊዜው አጭር ነው፡፡ ለልጆቹ ዳቦ ማብላት የማይችል አባወራም ሆነ እማወራ ምን ሊፈጥሩ እንደሚችሉ አይታወቅም፡፡ ሥራ በጉጉት የሚጠብቀው በሚሊዮን የሚቆጠር ወጣት ነገ ከነገወዲያ ዝምብሎ ያያል ብሎ ማመን አይቻልም፡፡ አስቸኳይ መፍትሔ ይፈልጋል፡፡ የተወሰነ ጊዜ ማቆየት ይቻላል፡፡ ነገር ግን በፍጥነት ወደ ተግባር ገብቶ ለውጥ ማምጣት ካልተቻለ ችግሩ የሁሉም ችግር ይሆናል፡፡ ጉዳዩ ከኢህአዴግም አልፎ የመላው ሕዝብ ይሆናል፡፡ የሚፈጠረው ምስቅልቅል ለሁሉም ይተርፋል፡፡ ይህን በመወቃቀስ ብቻ መወጣትም አይቻልም፡፡
ስለዚህ በቀናነት መጀመሩና የሚታየው ተነሳሽነት ጥሩ መሆኑ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ቀናነት፣ በጎነትና መቻቻል ወደ መሬት መውረድ አለባቸው፡፡ ተቋማት ላይ ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ ሕጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች መውጣት አለባቸው፡፡ ምህራኖች በጉዳዮች ላይ እንዲወያዩ በሩን መክፈት፤ መድረኮችም በስፋት መዘጋጀት አለባቸው፡፡ይሄ በጣም ከባድና ትልቅ ሥራ ቢሆንም ምርጫ የለም፡፡ አንዳንዴ ቃል የሚገባው ነገር እውነት የሚቻል ነው ወይ? የሚለውም ያጠያይቃል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ብዙ ጊዜ ተቃዋሚዎች ለድርድር የሚጋበዙት አገር ውስጥ ያሉት ብቻ ነበሩ፡፡ አሁን ግን ውጪ ላሉትም በራችን ክፍት ነው እየተባሉ ነው፡፡ ለምሳሌ በነሌንጮ ለታ የሚመራው ኦዴግ ለድርድር ወደ ኢትዮጵያ ገብቷል፡፡ ይሄ ምን ያሳያል?
አቶ ሙሼ፡-ለሁሉም ፓርቲዎች ጥሪ መቅረቡን አላውቅም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እየታየ ያለውን ለውጥ አገር ውስጥ ገብተን ብንጠቀምበት ያዋጣናል ብሎ በማሰብ ወደ አገር የገቡ አሉ፡፡ ነገር ግን እያንዳንዳቸው ፓርቲዎች የራሳቸው ሚዛን አላቸው፡፡ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ የሚያዩበት ዓይን ይለያያል፡፡ ከፓርቲው አስተሳሰብ፣ ከተፈጥሮ፣ ከተነሳበት ዓላማ ከሚያራምደው ፖለቲካ አሁን የተፈጠረው ሁኔታ ይጠቅመኛል፤ አገር ውስጥ ለመግባትም በር ይከፍትልኛል ብሎ ሊገባ ይችላል፡፡አገር ውስጥ ከገባ በኋላም ፓርቲውን ሕጋዊ አድርጎ ምርጫው ሲቃረብ ይወስናል፡፡
ሌሎችም በዚህ መልኩ ራሳቸውን ገምግመው የሚመጡ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እየተወያዩም ያሉ ይኖራሉ፡፡ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ከነበረበት የትግል ስልት ወጥቶ ወደ ሌላ የትግል ስልት የሚገባው ቁጭ ብሎ በጉዳዩ ላይ ውይይት አካሂዶ ነው፡፡ ስለዚህ ኦዴግም አሁን ያለውን ሁኔታ ገምግሞ በሰላማዊ መንገድ አገር ውስጥ ገብቼ የፖለቲካ ሥራ ብሰራ ውጤታማ እሆናለሁ ብሎ ወይም የዚህ ለውጥ አካል መሆን እንዳለበት ስላመነ ወደ አገሩ መጥቷል፡፡ በዚህም ለውጡ የበለጠ እየጠነከረ እና ሥር እየሰደደ ይሄዳል ብዬ አስባለሁ፡፡ የገቡት ሰዎች መደላድል ከተፈጠረላቸው ሌሎቹም ፓርቲዎች እምነት እያሳደሩ የጀመሩትን መንገድ ትተው የሚመጡበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ ስለዚህ አሁን ሥራ መሰራት አለበት፡፡ ይሄ ጅማሮ ነው፡፡
ደፍረው የመጡ ፓርቲዎች ሕዝባዊ ቅስቀሳ ማድረግ እንዲችሉ መድረኩን ማስፋት፣ ዕድሉን መሥጠት፣ ሰላማዊ ሰልፍ እንዲያደርጉ ሃሳባቸውን እንዲገልፁ ከሕዝቡ ጋር እንዲገናኙ በሩ ከተከፈተ ሌሎቹም ተማምነው ዋስትና አግኝተው ይመጣሉ፡፡ ይህ ደግሞ ለሁሉም በጎ ነው፡፡ ማንም ሆነ ማን በጥይት የሚመጣ ለውጥ ዘለቄታዊ ለውጥ አይደለም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ውጭ ስላሉ ተቃዋሚዎች ሲገልጹ በአሸባሪነት የተፈረጁት የነግንቦት ሰባት ክስ መቋረጥና የሌሎችም እስረኞች በይቅርታ መለቀቅን አስመልክቶ ሃሳብዎ ምንድን ነው?
አቶ ሙሼ፡- ለእኔ መጀመሪያም የፖለቲካ እስረኞች የተያዙበትና የታሰሩበት ሁኔታ ከመርህ አኳያ ትክክል ነው ብዬ ሰለማላምን እርምጃው በጎ ነው፡፡ ነገር ግን ሁሉም ነገር ሕግና ሥርዓት አለው፡፡ የተለቀቁት በሕጉ መሠረት ነው ከተባለ በሕጉ መሠረት ስለመፈታታቸው መታወቅ አለበት፡፡ በሕዝቡ ዘንድ ውዥንብር አለ፡፡
ሰዎቹ የተፈቱት ኢህአዴግ ውስጥ በተፈጠረው መከፋፈል የሁለቱ ኃይሎች ሽኩቻ ውጤት ነው፡፡ አንዱ በአንዱ ላይ ማን አቅም እንዳለው ለማሳየት የሚያደርገው ጥረት ውጤት ነው ብሎ የሚያምን አለ፡፡ እነዚህን ሰዎች በመፍታት በሕዝቡ ዘንድ ይሁንታን ለማግኘት የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው የሚሉም አሉ፡፡ ሕዝቡን ከሌሎች ተቃዋሚዎች ነጥሎ ለመውሰድ የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው የሚሉም መኖራቸው መታወቅ አለበት፡፡ ስለዚህ የዕርቅ የመቻቻል ውጤት ነው ብሎ ለማረጋገጥ የፖለቲካ ሥራ መሰራት አለበት፡፡ በአግባቡ መረጃ ለሕዝቡ ሊደርሰው ይገባል፡፡
ሌላው የቅደም ተከተል ችግሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ክሳቸው የተቋረጡ ሰዎች የተከሰሱት በግለሰብነታቸው አይደለም፡፡ በፓርላማው አሸባሪ የተባለ ድርጅት አባል በመሆናቸው ነው፡፡ ስለዚህ በቅድሚያ ፓርላማው እነዛ ድርጅቶች አሸባሪ አለመሆናቸውን ማፅደቅ ነበረበት፡፡ ሥራ አስፈፃሚው መጀመሪያ ፓርላማው እንዲወስን ሳያደርግ ይህንን ውሳኔ መወሰኑ የሚጣረስ ነው፡፡ አለቃውና አዛዡ መለየት አለበት፡፡ የሥልጣኑ ባለቤት ፓርላማው ነው፡፡ ፓርላማው አሸባሪ ያላቸው ድርጅቶች አሸባሪ አለመሆናቸው መጀመሪያ በፓርላማው ሳይፋቅ በፓርቲው ሲሳተፉ የነበሩ እስረኞች መፈታታቸው ከፓርላማው የሥልጣን ሂደት ጋር የሚጋጭ ነው፡፡ አሸባሪ ተብለው የተፈረጁ ድርጅቶችን የሚመሩት ሰዎች ነፃ ወጥተው ድርጅቱ አሸባሪ ሊሆን አይችልም፡፡ ሥራ አስፈፃሚው ይህን ማድረግ አይችልም፡፡ እንደዚህ ዓይነት ብዙ የአፈፃፀም ችግሮች አሉ፡፡ የይቅርታ ሂደቱ ግን በትክክል ተከናውኖ ሊሆን ይችላል፡፡
ለማንኛውም መንፈሱን በጥሩ መልኩ መውሰድ ይቻላል፡፡ ነገር ግን ሕጋዊ አካሄድን ተከትሎ መፈፀሙ ሰዎች ላይ እምነት ያሳድራል፡፡ ዛሬ ሕጋዊ የሆነውን መንገድ ትቶ የሚፈፀም ተግባር ካለ ሰዎች ሌሎች ሕጎች ስላለመጣሳቸው ዋስትና የላቸውም፡፡ ዛሬ ሕጋዊ የሆነውን መንገድ ለበጎም ቢሆን ሲጣስ ነገ ደግሞ ለክፉ ተብሎም ሕጎች ሊጣሱ ይችላሉ ማለት ነው፡፡ ሁሉንም የሚያስተሳስር ከፍቅርና ከአንድነትም ባሻገር የሕግ የበላይነት ያከባብራል፡፡
ኢህአዴግን ስንታገል የነበረው ሕግ እንዲያከብር ነው፡፡ ሌላው ሁለተኛ ነገር ነው፡፡ ሕግ ማክበር ማለት የሰዎች ሰብአዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሌሎችም መብቶች መከበር ማለት ነው፡፡ ለሕግ የበላይነት ትኩረት መሰጠት አለበት፡፡ የፖለቲካ እስረኞች መፈታታቸው በጎ ነገር ነው፡፡ ሲፈቱ ሕግን ማዕከል አድርጎ መንቀሳቀስ መተማመንን፤ ዕውቅና መስጠትን ያዳብራል፡፡ መንግሥት ሕግን ሲያከብር ሌሎች ሰዎችም ሕግን ለማክበር ድፍረት ይኖራቸዋል፡፡ ሕጋዊ መሠረት ተይዞ ከተለቀቁም ሕዝቡ ይወቅ፡፡ ይህንንም የሰራው አካል አካሄዱን የማሳወቅ ግዴታ አለበት፡፡ በውክልና የተሰጠውን ሥልጣን ሲጠቀም በሕግ መሠረት መሥራቱን ማረጋገጥ አለበት፡፡
በተለይ ከሙስና ጋር ተያይዞ የተፈቱ ሰዎችን ጉዳይ ብዙዎች ማወቅ ይፈልጋሉ፡፡ ከወር እስከ ወር ከማያደርሰው ደመወዙ፣ ከጉሮሮው ላይ ነጥቆ ግብር የከፈለው ኅብረተሰብ የግብሩን ገንዘብ የበሉ ሰዎች ሲለቀቁ አሳማኝ ምክንያት መቅረብ አለበት፡፡ እነዚህ ሰዎች ወደ ኅብረተሰቡ ተመልሰው ኅዝቡን እንዲጠቅሙ ማለት በቂ ምክንያት አይደለም፡፡ ይህ ሌሎችም እንዲዘርፉ የሚያበረታታ ነው፡፡ ሰዎች እንዲህ አድርገው ከተፈቱ እኛም እንፈታለን የሚል ሃሳብን ሊፈጥር ይችላል፡፡
ፖለቲካ የአንድ ድርጅት ጉዳይ ብቻ አይደለም። የአጠቃላይ የ100 ሚሊዮን ሕዝብ ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ ያንን በሚመጥን መልኩ መቅረብ አለበት፡፡ ሥራው ይሰራ ነገር ግን ስለሥራው በቂ ማብራሪያ፣ ትንታኔና ምክንያት ይሰጥ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ማንኛውም ተግባር ሲከናወን ሕግን መሠረት አድርጎ መንገዱንም ለሕዝብ አሳውቆ መሆን አለበት እያሉ ነው?
አቶ ሙሼ፡- አዎ! ሕዝቡን ማሳወቅ ማለት ፓርላማውን ማሳወቅ ማለት ነው፡፡ ፓርላማው የሕዝብን ውክልና የያዘ ነው፡፡ ፓርላማው መሠረታዊ ስትራቴጂካዊ ለውጦች ሲካሄዱ በቂ ግንዛቤ ሊኖረው እና ሕዝቡን እንዲያስተምር ይጠበቃል፡፡ የሁልጊዜ የኢህአዴግ ችግር ይሄ ነው፡፡ ኢህአዴግ ሌሎችን ረስቶ ጋሪና ፈረሱን ይዞ ይገሰግሳል፡፡ አሁንም የራሱን ብቻ ይዞ መንገዱን እየጠራረገ መሄድ ይፈልጋል፡፡ እንደዚያ ሊሆን አይገባም፡፡ በእርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተለያዩ ክልሎች እያነጋገሩ ነው፡፡ ነገር ግን እዚያ ላይ የሚቀርቡት ነገሮች የተጠቃለሉ ናቸው፡፡ ይህችን አገር በአንድነት ስለማቆየት ነው፡፡ በእርግጥ በአጠቃላይ ከሕዝቡ ጋር መወያየት ያስቸግራል፡፡ ነገር ግን ምሁራን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ባለሙያዎችን እንዲወያዩበት ማስቻል ያስፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኤርትራን አስመልክቶ የሰጠውን የውሳኔ ሃሳብ እንዴት ተመለከቱት?
አቶ ሙሼ፡- ኤርትራን በሚመለከት የተወሰደው አቋም ይደገፋል። ዕድሜ ልክ ሰላምም ጦርነትም በሌለበት ሁኔታ መፍትሔ የሌለው ችግር ይዞ ኢኮኖሚውን በሚያላሽቅ መልኩ ተንጠልጥሎ መኖር ተገቢ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ በመረጠው መድረክ በፍርድ ቤት ሂደት ተሸንፏል፡፡ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን የሚያስተናግድበትን መንገድ መፈለጉ ችግር ላይኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን በዚህ ደረጃ መራዘም አልነበረበትም፡፡
ባድመንም ሆነ በአካባቢው ያሉ መሬቶችን አስመልክቶ የተካሄደው ጦርነትና ያስከፈለው መስዋትነት በጣም ያሳዝናል፡፡ ነገር ግን ስህተትን በስህተት መፍታት ተገቢ አይደለም፡፡ ከጦርነቱ በፊት በሕጋዊ መንገድ ሄዶ መፍታቱ ይሻል ነበር፡፡ ያ አለመሆኑ ዋጋ አስከፍሏል፡፡ ነገር ግን ዋጋ አስከፍሏል በሚል ደግሞ ዕድሜ ልክ በጦርነት መኖር አይገባም፡፡ ከዚህ ታሪክ ተላቆ መውጣት ያስፈልጋል፡፡
ሰው አይመስለውም እንጂ በዚያ አካባቢ ያለው የጦርነት መንፈስ ኢኮኖሚውን በብዙ መንገድ ይጎዳል፡፡ የኢንሹራንሱ ዋጋ ይጨምራል፤ ቱሪስቶች ለመምጣት ያላቸው ፍላጎት ይቀንሳል፤ በሚፈለገው መጠን አካባቢው አያድግም፤ ኢትዮጵያ መጠቀም የሚገባትን የባህር በር ማግኘት አልቻለችም፤ በሕዝቦች መካከል ያለው ግንኙነት የለም፤ የንግድ ትስስሩ ተቋርጧል፤ አንዱ አገር ለሌላው አገር ሊያቀርበው የሚችለው ሀብት፣ የሰው ሀይል፣ ገንዘብ፣ ቁሳቁስና የተፈጥሮ ሀብት እንዳይኖር ሆኗል፡፡ ስደተኞችን ማስተናገዱም ቀላል አይደለም፡፡ ስለዚህ መሠረታዊ ምስቅልቅሉ ቀላል አይደለም፡፡ ከዚህ ታሪክ መላቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ኤርትራን አስመልክቶ እንደዚህ ዓይነት ቁርጠኛ አቋም መውሰድ ነበረበት፡፡ ስለዚህ የአሁኑ ውሳኔ ትክክል ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከኤርትራ ጋር የሚኖረው ግንኙነት አሁን በተያዘው አቅጣጫ መሆን አለበት ማለት ነው?
አቶ ሙሼ፡- አዎ! ይህ እኮ የኢህአዴግና የሻዕቢያ ጉዳይ አይደለም፡፡ ሁለቱ ፓርቲዎች ጠባቸውን በፈለጉበት መንገድ ይሞካከሩ፡፡ ነገር ግን ሕዝቦች ዕድሜ ልካቸውን የነርሱ ጥላቻ ምርኮኛ መሆን የለባቸውም፡፡ በእኔ እምነት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ መጠንከር አለበት፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከሌሎች የቅርብ ጎረቤት አገሮች ጋር ያለው ግንኙነትስ?
አቶ ሙሼ፡- ከጎረቤት አገሮች ጋር ያለን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሠረቱና መደላድሉ በተለያየ ምክንያት የተጎዳ ነው፡፡ ከማንም በላይ የሚቀርቡ ጎረቤቶቻችንን ማቅረብ የግድ ነው፡፡ ከአሜሪካና ከቻይና ጋር የሚኖር ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ጠቃሚ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ከጎረቤት አገራት ጋር ያለው ግንኙነት መልካምነት በዜጎች ላይ ያለው በጎ ተፅዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ ስለዚህ እዚህ ላይ መሰራት አለበት፡፡ እነርሱን ተሻግረን ሄደን ከሌሎች አገሮች ጋር የምንፈጥረው ግንኙነት መቼም አመርቂ አይደለም፡፡
የቅርብ ጎረቤቶች ለሰላማችንም ሆነ ለዕድገታችን እንዲሁም ለሕዝብ ግንኙነቱ ለልምድም ሆነ ለባህል ልውውጡ ከፍተኛ ሚና አላቸው፡፡ በጎና ቀና ግንኙነት መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ከአሜሪካና ከሌሎችም አገሮች ጋር ግንኙነት ሳይኖረን ቀድሞ ግንኙነት የነበረን ከእነዚህ ሕዝቦች ጋር ነው፡፡ ብዙ ባህል ተዋርሰናል፤ ብዙ ልምድ ተለዋውጠናል፤ ተዋልደናል፡፡ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያው ያኖችም በእነዚህ የጎረቤት አገሮች ይኖራሉ፡፡ ስለዚህ ግንኙነቱን ለማጠናከር በዚህ መልኩ መሄዱ ጠቃሚ ነው፡፡ ምክንያቱም የአለመረጋጋቱን አጋጣሚ ተጠቅመው ቁርሿቸውን መወጣት የሚፈልጉ አገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ያ መሆን እንደማይገባው ለእነዚህ መንግሥታት በሰላማዊና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መግለፅ ትክክል ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ቀጣዩ የ2012 ዓ.ም አገራዊ ምርጫን አስመልክቶ ምን ይታይዎታል?
አቶ ሙሼ፡- እስከ አሁን የነበረው ውይይት የሚቋጨው በ2012ቱ ምርጫ ነው፡፡ በተግባር የሚተረጎሙት በዚህ ጊዜ ነው፡፡ ተቃዋሚዎችን እንደዕድል ማየት፣ ኢትዮጵያን እንደ አንድ አገር ማየት፣ ለተቃዋሚዎች መድረክ መስጠት የተባሉት ነገሮች በሙሉ የሚተገበሩት በዚያ ወቅት ነው፡፡ አንድ ተማሪ ዓመቱን ሙሉ አጥንቶ የሚፈተነው በዓመቱ መጨረሻ እንደመሆኑ መጠን ኢህአዴግም የሚፈተነው በምርጫው ወቅት ነው፡፡ ይህ ምርጫ ለኢትዮጵያ አንደኛውና ዋነኛው መፍትሄ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
ዜጎችን ለመጠበቅ የተቋቋሙ ነገር ግን አፈና በማካሄድ ላይ ያሉ ተቋማት እጃቸውን ሰብስበው ወደ ትክክለኛ ሥራቸው ይመለሱ፡፡ ፖሊስ ሥራው ወንጀለኛና ሌባን ማደን ነው፡፡ ፖለቲካ ውስጥ እጁን አያስገባ፡፡ መከላከያም ደህንነቱም ከፖለቲካ ጉዳይ ራሳቸውን መነጠል አለባቸው፡፡ ዜጎች የፈለጉትን አማራጭ የመስማት፤ የፈለጉትን ሰምተው የፈለጉትን የመምረጥ መብት አላቸው፡፡ ይህንን በቅድሚያ በእምነት ደረጃ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ለእዚህ እንቅፋት የሆኑ ከፖሊስ፣ ከደህንነትና ከመከላከያም ውጪ የእንባ ጠባቂ፣ የሰብአዊ መብት፣ የወረዳ የቀበሌ መዋቅሮች የምርጫ ሂደቱን የሚያሰናክሉ፣ ምርጫው በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዳይካሄድ በወገንተኝት የሚሰሩ ናቸው፡፡ እነዚህን ጨምሮ መገናኛ ብዙኃን በሙሉ ለውጥ ያስፈልጋቸዋል፡፡
ሁሉንም ፓርቲ እኩል ካስተናገዱ ሕዝቡም ቢሆን ለመምረጥ አይቸገርም፤ ፓርቲዎቹም የሚችሉትን አድርገው ስለተሸነፉ አይከፉም፡፡ ሌላ አገር እንደሚካሄደው ሁሉ ተጨባብጦ መለያየት ይቻላል፡፡ ምርጫው ሲጠናቀቅም ውጤቱን ተቀብለን አገሪቷን በጋራ ለመገንባት የምንነሳበት ሊሆን ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም በጣም አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ሙሼ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

ምህረት ሞገስ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።