ከፖለቲካዊ ቁርሾ ይልቅ ማህበራዊ መስተጋብር እንዲጠናከር Featured

11 Jun 2018

የኢትዮጵያዊነትና የአንድነት መገለጫ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ አባይ ነው። ከኢትዮጵያዊያንም አልፎ ለሌሎች ሃገራትም ጭምር አለኝታ የሆነው ይኸው ወንዝ የሚጋሩትን ሁሉ በታሪክና በባህል ያስተሳስራል። በጎጃምና በወለጋ ህዝቦች መካከል የሚፈሰው አባይ የአማራና ኦሮሞ ህዝቦች የአንድነትና የትስስር ማሳያ ሆኖ ኖራል። አባይ እነዚህን ህዝቦች በጋራ ከማጠጣት ባለፈ በጋራ ውለው እንዲያድሩና የጋራ እሴት እንዲገነቡም አድርጓል፡፡ ታሪክ እንደሚያወሳው አባይ ሲሞላ ከንግድ ጋር በተያያዘ ወደ ወለጋ የሄደ የጎጃም ሰው አሊያም ጎጃም የደረሰ የወለጋ ነጋዴ፤ ወንዙ እስኪጎድል በሚኖራቸው ቆይታ ከህብረተሰቡ ጋር ያላቸው መስተጋብር ይበልጥ ሊጠናከር ችሏል።
ከዚህ ባለፈም ሁለቱ ህዝቦች በመልከአ ምድር፣ በታሪክ፣ በአኗኗር ዘይቤና በሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችም የተሳሰሩ ናቸው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይህ የህዝቦች አንድነት በተለያዩ ምክንያቶች ክፍተቶችን እያስተናገደ መምጣቱ ታይቷል። በመሆኑም ሁለቱ ብሄሮች በተነሳሽነት የህዝብ ለህዝብ የግንኙነት መድረኮችን በመፍጠር መስተጋብራቸው እንዲጠናከር አቅደው በመሥራት ላይ ይገኛሉ። በተለይም በህዝቦች መካከል ያለው የጋራ አብሮነት በሳይንሳዊ ጥናቶችና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተደግፎ ከሄደ፤ የህዝቦቹን ግንኙነት በተሻለ መልኩ ለማካሄድ መድረኩ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ታምኖበታል።
በዚህም የመጀመሪያው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መድረክ በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ተካሄዶ ነበር። በመድረኩ ላይም መቀራረብና የህዝቦችን አንድነትና አብሮነት ለማጠናከር አንድ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ተገቢ እንደሆነ ተመልክቷል። ልዩነቶችን በማጥበብ አንድ ሊያደርጉ የሚችሉ ታሪካዊ ዳራዎች ጎልተው እንዲወጡ ማድረግ የግድ የሚል ሲሆን፤ በታሪክ ሂደት የተፈጠሩ ልዩነቶችን በአግባቡ ማስቀመጥም ለታሪክ ባለሙያዎች የሚተው ነው። ከሚያለያዩ ነገሮች ይልቅ አንድ የሚያደርጉት ነገሮች ይበልጣሉና በጋራ ጉዳዮች ላይ በማተኮር መንግሥትም እንደ መንግሥት፣ ምሁሩም እንደ ምሁር የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት የሚገባ መሆኑም ተነስቷል።
ሁለተኛው መድረክ ደግሞ በሁለቱም ክልሎች ያሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮችና ተማሪዎች በተገኙበት ሰሞኑን በጅማ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል። በመድረኩ ላይም ከደብረ ማርቆስና ወለጋ ዩኒቨርሲቲዎች በተወጣጡ ምሁራን የተሠራ «በጎጃምና ወለጋ ህዝቦች መካከል ያለው ታሪካዊና ባህላዊ መስተጋብር» የሚል ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቧል። በጥናቱም ላይ ሁለቱን ህዝቦች የሚያስተሳስሯቸው ጉዳዮች የቀረቡ ሲሆን፤ በጥናቱ መነሻነትም በተሳታፊዎች መካከል ውይይት ተካሂዷል።
ጥናታዊ ጽሑፍ ካቀረቡት ምሁራን መካከል በወለጋ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዕጩ ዶክተር ደሳለኝ ቶሌራ አንዱ ሲሆኑ፤ ጥናቱ የሁለቱን ህዝቦች መስተጋብር በተለይ ከ16ኛው ክፍለዘመን ወዲህ ያለውን ሁኔታ ለመዳሰስ የሞከረ መሆኑን ይገልጻሉ። በዚህም የጎጃምና የወለጋ ህዝቦች የቆየ የቋንቋ፣ የባህልና የሃይማኖት ትስስር እንዳላቸው ጥናቱ ማመላከቱን ይናገራሉ። ከዚህ ቀደም የነበሩ ጥናቶች በጉልህ ሲያሳዩ የነበረው ግን፣ በሁለቱ ህዝቦች መካከል ያለውን ግጭት እንደነበር ያብራራሉ፡፡ በመድረኩ ላይ የቀረበው ጥናት ግን ከዚያ ባሻገር በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ መስተጋብሮችን የሚዳስስ እንደሆነም ያስረዳሉ።
እንደ ጥናት አቅራቢው፤ በተለይ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ኦሮሞዎች አባይን አቋርጠው ከነባህላቸው ከጎጃም ህዝቦች ጋር ሲቀላቀሉ ነበር፡፡ በ17ኛው ክፍለ ዘመን የኦሮሞ ጎሳ በጎጃም በመስፈር በወቅቱ የነበሩትን የአስተዳደር ክፍሎች ከመሰረቱት መካከል አንዱ እንደሆነም በጥናቱ ታይቷል፡፡ በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ደግሞ ንጉሥ ተክለሃይማኖት አባይን አቋርጦ ወለጋ ድረስ በመሄድ የባህል መስፋፋት አካሂዷል። የክርስትና እምነት ወደ ወለጋ ከተስፋፋ በኋላም «በአበልጅ፣ በጉዲፈቻ እና በጡት ማጥባት (ሃርመ ሆዻ)» ስርዓቶች ይበልጥ በመተሳሰር በዘርና በደምም ጭምር የተዋሃዱ መሆኑንም ጥናቱ ያመላክታል።
ጥናት አቅራቢው እንዳስረዱት፤ የኢትዮጵያ ታሪክ ትኩረቱን አድርጎ የቆየው በፖለቲካ ላይ ነው፡፡ በዚህም ማህበረሰባዊው፣ ኢኮኖሚያዊውና ባህላዊው ሁነት በስፋት ሳይጠና ቀርቷል። ህብረተሰቡ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ በተሻለ የተያያዘ በመሆኑም፤ ለወደፊቱም ትኩረት መደረግ ያለበት ህዝቡን ይበልጥ በሚያቀራርብ ነገር ላይ መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም፣ ህዝቦች ከነገሥታቱ ጋር በጦርነቶች ላይ ቢካፈሉም፤ ግጭቱ ነገሥታቱ ግዛታቸውን ለማስፋፋት የሚያደርጉት ሽኩቻ እንጂ በህዝቡ መካከል በተፈጠረ ተቃርኖ እንዳልሆነ ሊታወቅ የሚገባው ሀቅ ነው። የጥናቱም ዓላማ የህዝቡን አንድነትና መስተጋብር የሚያሳዩ ተመሳሳይ ሁነቶችን በማሳወቅ በትውልዱ ዘንድ ይህ አስተሳሰብ እንዲሰርጽ ለማድረግና ይሄን የሚያሳዩ የሰነድ ማስረጃዎችም እንዲዘጋጁ ለማድረግ ነው።  
እንደ ታሪክ ምሁሩ አባባል፣ ሁለቱ ብሄረሰቦች በኢትዮጵያ ውስጥ ግዙፍ የሆኑና የሃገሪቷን ፖለቲካም ሊያራምዱም ሆነ ሊያጠፉ የሚችሉ ናቸው። ነገር ግን ቀደም ሲል ሁለቱ ብሄሮች ጠላት እንደሆኑ ሲነገር እንደነበር በጥናቱ ታይቷል፡፡ ዓለም አንድ በሆነችበት በዚህ ወቅት ደግሞ ይህ አስተሳሰብ የሚያስኬድ አይሆንም፤ ለህዝቡ የሚጠቅመውም መጥፎ ነገሮችን ከማሳየት ይልቅ መልካም መስተጋብራቸውን ማመላከት ነው። ከዚህ ቀደም አንድ የአማራ ምሁር በአንድ ጉዳይ ላይ ከጻፈ የኦሮሞውም ተነስቶ በዚያ ላይ ምላሽ የመስጠት ነገር ይታይ ነበር። ይህ ደግሞ እውነታውን እያፈነ፣ ለህዝቡ መራራቅ ምክንያት ሆኗል። ምክንያቱም ህብረተሰቡ አሁንም በጋራ እየኖረ ቢሆንም በፖለቲካ ላይ ያሉ ሰዎችና የታሪክ ምሁራን እያበላሹ ናቸው። ስለዚህም በጥናቱ ላይ እንደታየው ከሁለቱም ወገኖች የተውጣጡ ምሁራን በጋራ እሴቶች ላይ የተመሰረተና መስተጋብራቸውን የሚያጠናክር የጋራ ታሪካቸውን አጉልቶ በማውጣት ህብረተሰቡን ይበልጥ ማቀራረብ ይጠበቅባቸዋል።
በአማራ ክልል የሚገኙ አስር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ዋና ፀሐፊ ዶክተር ንጉሴ ምትኩ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ የሁለቱ ህዝቦች ግንኙነት የረጅም ጊዜ ታሪክ ያለው መሆኑን ይጠቁማሉ። አጎራባች ከሆኑት ህዝቦች ባሻገር በሩቅ የሚገኙትም ቢሆኑ በንግድ፣ ሃገርን በመጠበቅ፣ በእምነትና በሌሎች ነገሮች ላይም የተጠናከረ ግንኙነት ያላቸው ህዝቦች ናቸው። አሁንም በባህል፣ በታሪክና በቋንቋ የተጠናከረ መስተጋብር አላቸው፡፡ በጎጃም በርካታ ስፍራዎችና ኩነቶች የኦሮምኛ ስያሜ መያዛቸው፤ ህዝቡም በባህልና ቋንቋ ብቻ ሳይሆን በዘርም የተገናኘ ለመሆኑ፤ ስማቸው ወደ ኋላ ሲቆጠር ከሁለቱም ብሄር የተቀላቀለ ሆኖ መገኘት ደግሞ ለዚህ አብይ ማሳያ ነው፡፡
ዶክተር ንጉሴ እንደሚናገሩት፤ ባለፉት ጊዜያት ለተወሰኑ ዓመታት በልዩነት ላይ በመሠራቱ የተዛባ ነገር ቢኖርም ግንኙነቱ ግን አሁንም ጠንካራ ነው፡፡ በምሁራኑ ዘንድ ግን ጥቂት መሻከር ይታያል። በመሆኑም የህዝቦችን ትስስር ለማሳየት እንዲያገለግል በሚመክረው በዚህ ዓይነት መድረግ የህዝቦችን ትስስር የሚያሳዩ እንዲህ ዓይነት ጥናቶች መቅረባቸው ለህዝቡ አንድነት መጠናከር ትልቅ ፋይዳ አለው።
ላለፉት 27 ዓመታት ብዝሃነት የተያዘበት መንገድ መልካም ጎን እንዳለው ሁሉ መልካም ያልሆነ ጎንም ያለው እንደነበር የሚናገሩት ዶክተር ንጉሴ፤ «የሃይማኖት፣ የብሄር፣ የቋንቋ፣ ወዘተ ብዝሃነት በደንብ ከያዝነው ጸጋ ቢሆንም፤ አንድ በሚያደርጉን ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ግን መላላት ነበር፤» ይላሉ፡፡ ከዚህ አኳያም «የአማራና የኦሮሞ ህዝብ ግንኙነት ላለፉት 27 ዓመታት ሲገለጽ የነበረው በዚህ መልክ አልነበረም። ይልቁንም ምንም ግንኙነት እንደሌላቸው ሁለቱ ህዝቦች የተቀራረቡ እንዳልሆኑ፣ ወንድማማች ህዝቦች እንዳልሆኑ ለየብቻ ታሪካቸው ይነገር ነበር። ይህም ሁለቱን ህዝቦች በጠላትነት የመፈራረጅ አዝማሚያ የነበረበት ዓመት ነበር» ይላሉ።
ይህንን ለመቀየርና ሁለቱ ህዝቦች ታሪካዊ ትስስር እንዳላቸው በችግርና በደስታ አብረው የኖሩ እንደሆኑ ማሳየት እንደሚያስፈልግም ያስረዳሉ። ይህንን ለማሳየት ደግሞ ህዝቡን የሚያሳምን ምሁራዊ ጥናቶች እንደሚያስፈልጉ፤ ለህዝቡም በመግለጽ እንዲታወቁ መስረት እንደሚገባ፤ ይህንን ታሪክ ባለማሳየትም ላለፉት ዓመታት እዚህም እዚያም የነበሩ ቁርሾዎች አሁን መጥፋት እንዳለባቸው ያስገነዝባሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት ጥናቶችም ለጋራ አንድነት የሚያግዙ በመሆኑ በስፋት መካሄድ፤ ይህንን ኃላፊነት ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ምሁራን ወስደው ወደኋላ በመመለስ አንድነቱን ማሳየት እንዳለባቸው ይመክራሉ፡፡
 በተቋማቱ የሚማሩ ተማሪዎችም ከተለያየ አካባቢ ብዝሃነትን ይዘው የሚመጡ በመሆናቸው፤ መሰል ጥናቶችን ለማቅረብ ዩኒቨርሲቲዎች ተገቢ ቦታዎች መሆናቸውን ዋና ፀሐፊው ይጠቁማሉ። የጋራ እሴቶችን አውጥተው የሚያሳዩ ጥናቶችን በተማሪዎች ማስረጽም ትልቅ ትርጉም ያለው እንደመሆኑም፤ ይሄን ተገንዝቦ መሥራት ከተቻለ ተማሪዎች ተግባብተውና ተቻችለው የመጡበትን አሳክተው እንዲመለሱ፤ እንዲሁም ወደየመጡበት ሲሄዱም አካባቢያቸውን እንዲያስተምሩ የሚያግዛቸው መሆኑንም አብራርተዋል፡፡ በመሆኑም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ይህንን አጠንክረው መያዝና በመድረኮቹም ላይ በብዛት ተማሪዎች መጋበዝ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ለሜሳ፣ ለመድረኩ መነሻ የሆነው ሁለቱ ክልሎች ባህርዳር ላይ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር በተደረገው ውይይት የታየው መልካም ነገር መሆኑን ያስታውሳሉ። በዚህም በደብረ ብርሃን የተከናወነው የመጀመሪያው ጉባዔም ሆነ በጅማ የተከናወነው ሁለተኛው ጉባኤ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የህዝቡን አንድነት በማጠናከር ታሪካቸው ምን ይመስላል በሚለው ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ በማቅረብ ህዝቡ እንዲነጋገርበት ያስቻለ ነው፡፡ በመድረኮቹ የሚቀርቡት ጥናቶች ይዘትም በምሁራን ተደግፈውና በመረጃዎች ተጠናክረው የተከናወኑ ምርምሮች ስለሆኑ የህዝቦቹ ግንኙነት ምን ይመስላል በሚለውና ወደፊትስ እንዴት ይጠናከር በሚለው ላይ ያተኮረ ነው። የህዝቦች ትስስር ለሃገር ወሳኝ መሆኑን ለማሳየትና ወደፊትም እንዴት መሠራት አለበት የሚለውን ለማስቀመጥ ይረዳል የሚል እሳቤ አላቸው።
«እንደሚታወቀው አሁን በለውጥ ውስጥ ነው ያለነው፤ ለኢትዮጵያ አንድነት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ደግሞ ወሳኝ ነው፤» የሚሉት ፕሮፌሰር ፍቅሬ፤ በተለይ ሁለቱ ህዝቦች በንግድ፣ በፖለቲካና በማህበራዊ ግንኙነት ተቀናጅተውና ተሳስረው የሚኖሩ ህዝቦች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በጥናቶቹ የታየውም ሁለቱ ህዝቦች በከፍተኛ ሁኔታ የተሳሰሩ፣ ተቻችለውም አብረው እየኖሩ መሆናቸውን ማመላከቱን አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን የተለያዩ ጽሑፎች ይህንን አጉልተው እንደማያሳዩና ልዩነቶች ላይ የሚያተኩሩ ስለመሆናቸውም ገልጸዋል።
እንደ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ገለጻ፤ የህዝቦችን አንድነት ዘንግቶ ልዩነትን እያጎሉ መሄድ ራሱን የቻለ ክፍተት ነው፡፡ በመሆኑም ምሁራን የህዝቦችን አንድነትና ትስስር ለህዝቡ በማሳወቅ ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባቸዋል። እስከአሁን ያለው ሂደትም በተቋማት ደረጃም ተቀናጅቶ መሄድ እንደሚያስፈልግ የሚያሳይ ነው። የጋራ ፕሮጀክቶች እንዲኖሩና እርስ በእርስ የመማማር ዕድሎች እንዲፈጠሩ ልዩነቶችን ማቻቻልም ያስፈልጋል። በዚህ መልኩ የሚከናወኑ ጥናቶችንም ወደህዝቡ ማውረድ ይገባል፡፡ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መድረኮችም ምሁራን በጋራ ውይይት የሚያደርጉበትና አቅጣጫም የሚያስቀምጡበት መሆን ይኖርባቸዋል። ከመድረኩ የሚገኙ ውጤቶችም ለፖሊሲ አውጪዎችና ተጠቃሚዎች ደርሰው ህዝባዊና ተደራሽ መሆን አለባቸው።
ከዚህ ባለፈም ህዝብም ተገናኝቶ በሰፊው ውይይት እንዲያደርግ መድረኮች መመቻቸት አለባቸው። በምሁራኑ አማካኝነት ህዝቡ እርስ በእርሱ የሚገናኝበትን መንገድ በማመቻቸትና ግንኙነቱን በማጠናከር እንዲማማሩ ማድረግ ያስፈልጋል። አሁን በተጀመረው መልኩም ተማሪዎች በቋንቋ እንዲግባቡ ለማድረግ በተለያዩ  ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ ቋንቋዎች የሚያስተምሩ የትምህርት ክፍሎችን በመክፈት እንደ ባህርዳርና ወሎ ዩኒቨርሲቲዎች የኦሮምኛ ቋንቋ እንዲሰጡ ማድረጉ ትስስሩን ለማጠናከር የሚያግዝ ዕርምጃ ነው፡፡ ይህን መሰል ዕርምጃም በቋንቋ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን ለመፍታት ያስችላል።
የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ነገሬ ሌንጮ በበኩላቸው፤ ሁለቱ ህዝቦች ድንበር ከመጋራታቸው ባለፈ የማህበራዊና ባህላዊ ቁርኝት እንዳላቸውም ታሪክ እንደሚያስረዳ ይገልጻሉ፡፡ ይህ ደግሞ የሁለት ብሄሮች ብቻም ሳይሆን የአጠቃላይ ህዝቡ መግባባት ውጤት መሆኑን፤ ህዝቡ አንድ ላይ ሲኖር እንደነበርና በሂደት ግን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ከመጠናከር ይልቅ መልኩን የቀየረበትና የተበላሸበትም ሂደት እንደነበር ያስረዳሉ። «ማናችንም በቋንቋ፣ በብሄርና በመሳሰለው ከመለየታችን በፊት ሰው መሆናችን አንድ ያደርገናል፤ በዚህ ደግሞ መከባበርና አብሮነት ተሰጥቶናል፤ ምክንያቱም ሰው ያለ ሰው መኖርም አይችልም፤» ይላሉ።
«የነበረውን ሰላምና መከባበር በማውጣት ጥላቻ የተዘራበት ጊዜም ነበረ፤ ይህ ደግሞ ሁለቱን ህዝቦች ብቻም ሳይሆን ሃገሪቷን ሲጎዳት እንደነበር ይታወቃል። ስለዚህም በዚህ ወቅት ምሁራን ግንኙነቱን ለማጠናከር መሥራታቸው ለሁለቱ ህዝቦች ብቻም ሳይሆን ለሃገር አንድነት የሚጠቅም ነው» ሲሉም ይገልጻሉ። መልካም የሆኑ ነገሮች ጎልተው እንዲወጡ በማድረግ አዲሱ ትውልድ ከዚያ ተምሮ ግንኙነቱን ማጠናከር እንደሚገባ፤ የህዝብ ለህዝብ መልካም ግንኙነት የአንድ ሃገር ጥንካሬ መገለጫ ስለሆነም ግንኙነቱ ጠንካራ ካልሆነ ሰላም ሊኖር ስለማይችል በዚህ መልኩ የሚካሄደው መድረክ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ይገልጻሉ፡፡   
ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ ባሻገር የኦሮሚያ ክልል ከሌሎች ህዝቦች ጋር ያለውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከርና ኢትዮጵያዊነት እንዲያብብ በጋራ እሴቶች ላይ እየሠራ እንደሚገኝ ዶክተር ነገሬ ይገልጻሉ። የነበሩ መልካም ግንኙነቶች በታሪክ ከተፈጠሩ ቁርሾዎች የበለጠ ማደግ ያለባቸው በመሆኑ፤ በዚህ ላይ መሥራት እንደሚገባ በማመን በተነሳሽነት ወደ ባህርዳርና ሌሎች ክልሎች በመሄድ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በማጠናከር ላይም እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በክልሉ መንግሥት የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ምሁራኖች ብቻ ሳይሆን መሪዎችም ይህንን አጠናክሮ የማስቀጠል እቅድ እንዳለና በተግባርም አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል። «ያለ ህዝብ መንግሥት የለም፤ በፊትም መልካም የሆነውን ማህበራዊ መሰረት ቅድሚያ ባለመስጠት ነው አላስፈላጊ ቁርሾዎች የተፈጠሩት። መሠረታችንን ህዝብ ብናደርግ በፊት የነበረውን መልካም ግንኙነት ከላይ ወደታች የሚፈሱ በገዢዎች መካከል ያሉ ጥሩ ያልሆኑ ግንኙነቶች እንዲበረዙ ነው ያደረገው» ሲሉም የነበረውን የተሳሳተ አቅጣጫ ጉዞ አስረድተዋል።
አሁን ግን ሃገሪቷ ተጠናክራ እንድትቀጥል ማህበራዊ መሰረቶች መጠናከር አለባቸው፤ ሁሌም ከላይ ወደታች ብቻ ሳይሆን ከህዝብም ወደ ላይ መምጣት አለበት። በአጭር ጊዜ ውስጥ እየታየ ያለው የፖለቲካ ዲስኩር ብቻ ሳይሆን ህዝብን በማወያየትና በማዳመጥ፤ የተረጋጋ የፖለቲካ አመራር ለማምጣት ተጠናክሮ እየተሠራ ነው። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ብቻም ሳይሆን ከአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ጋር በጋራ እየሠራን እንገኛለንም ብለዋል። ሁለቱ ክልሎች ብቻም ሳይሆን የፌዴራል መንግሥቱ እና ሌሎችም ክልሎች በዚህ ላይ ትኩረት በማድረግ እንዲጠናከር የሚደረግበት ሁኔታ መኖሩንም ጠቁመዋል።     

ብርሃን ፈይሳ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።