በተቃርኖ የታጀበው የምህረት አሰጣጥ Featured

12 Jun 2018

በቅርቡ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል አንድ ጥናት ይፋ አድርጓል፡፡ ጥናቱ የኢትዮጵያን የሙስና ደረጃ የሚያሳይ ሲሆን፤ በደረጃው መሰረትም ኢትዮጵያ ከ188 የዓለም አገራት መካከል 107ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ አመላክቷል፡፡ ይህም አገሪቱ ምን ያህል በሙስና ወንጀል ውስጥ እንደተዘፈቀች ይጠቁማል፡፡
ሙስና በሀገሪቱ በዚህ ደረጃ ላይ ከተቀመጠ በኢኮኖሚው ላይ ሊያሳርፍ የሚችለው ጉዳትም የዚያኑ ያህል ከፍተኛ ስለመሆኑ መገመት አይከብድም፡፡ ችግሩ እንዲህ ከፍ ብሎ ለመገኘቱ ዋነኛ ምክንያትም በሀገሪቱ ሙስናን የማይሸከም ትውልድ ካለመፈጠሩ ጋር የሚያያዙ አካላት ይስተዋላሉ፡፡
ሰሞኑንም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ በ4ኛው የአገር አቀፍ የፀረ ሙስና ጥምረት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር የተደራጀ ዘረፋና ሌብነት ሀገሪቱን እንደሚያሳስባት አስገንዝበዋል፡፡
‹‹አምስተኛው መንግሥት እንዲያቆጠ ቁጥና እንዲስፋፋ የሚያግዘው ሌላኛው ኃይል አስተሳሰባችንና ባህላችን ነው›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሰርቆ ማደግንና ዘርፎ መክበርን በማይጠየፍ ባህል ወስጥ ሌብነትና ዘረፋን መዋጋት ከባድ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በአገራችን ከዓመታት በፊት አንስቶ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የንግዱ ማህበረ ሰብ አባላት በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉና የተፈረደባቸው፣ ከፊሎቹም ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ሲታይ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች መካከልም አንዳንዶቹ እጅ ከፍንጅ በሚያስብል ሁኔታ ጭምር በቁጥጥር ስር የዋሉ ናቸው፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ለዓመታት ከታሰሩ በኋላ በቅርቡ ከእስር መለቀቃቸውም ይታወሳል፡፡
በትራንስፓረንሲ ኢንሼቲቭ መረጃ መሰረት ሀገሪቱ ያለችበት የሙስና ደረጃ አሳሳቢ መሆኑ እና በሀገሪቱ የተደራጀ ሌብነትና ዘረፋ እየተንሰራፋ ያለበት ሁኔታ እንዲሁም በቅርቡ ባለፉት ዓመታት በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የቆዩ የመንግሥት ባለሥልጣ ናትና ባለሀብቶች ከእስር እንዲለቀቁ መደረጉ የፀረ ሙስና ትግሉን ይፈትኑታል ሲሉ ተንታኞች ያስገነዝባሉ፡፡
የፖለቲካ ተንታኙ ዶከተር ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ እንደሚሉት፤ በፖለቲካ ምክንያት የታሰሩ አካላት አቃቤ ህግ ማስረጃ ማቅረብ እንዲሁም ዳኞች መፍረድ ካልቻሉ ቢለቀቁ ምንም አይደለም፡፡ አምስት ዓመት ሙሉ ያለፍርድ መቀመጥ ችግር ነው፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ፍርድን አካልቦ መስጠት ‹‹ሞተ›› የተባለ ሰውም በህይወት የመገኘት ጉዳይ ሊከሰት ይችላልና ዳኞች ጉዳዮችን የማጣራት ኃላፊነትም ስላለባቸው አይቸኩሉም፡፡
‹‹እኔ የአፍሪካ ህብረት የፀረ ሙስና ቦርድ ሊቀመንበር ሆኜ ሁለት ጊዜ አገልግያለሁ፡፡ የቦርዱ ዋና ዓላማም በአጠቃላይ በአፍሪካ ላይ ያለውን ሙስና እንዴት አድርገን እንዋጋ የሚል ነው፡፡ በአራት ዓመት ቆይታዬም የተማርኩት ሙስና የሚበዛው ሥርዓት ሲበላሽ መሆኑን ነው፡፡ በማናለብኝነት ዝም ብለው የሚዘርፉ ሰዎችም አሉ፡፡ እነዚህ ደግሞ በፓርቲ የተሾሙና የፓርቲ ከለላ ያላቸው ለፓርቲ የተባለ ገንዘብ የሚቀበሉ እንደሆነ በአህጉር ደረጃ ይታያል›› ሲሉ ያብራራሉ፡፡
‹‹ብዙ ጊዜ ለዚህ አይነት አካሄድ ማስረጃ ያለው ነገር አይገኝም፡፡ ለምሳሌ ቤት ውስጥ ገንዘብ ተገኘ ይባላል፡፡ ነገር ግን ያንን ገንዘብ ከየት እንዳመጣው የመጠየቁ ጉዳይ ያን ያህል ነው፡፡ ለፍርድም ለማቅረብ ያስቸግራል፡፡ ምክንያቱ ሰው ገንዘብ የሚቀበለው በቼክ ወይም ደረሰኝ እየቆረጠ ባለመሆኑ ነውና በማለት ያስረዳሉ፡፡
ሙስና የአመለካከት ጉዳይ ነው፡፡ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል በሙስና ላይ የሕዝቡ አመለካከት አለ የለም የሚለውን ጉዳይ ነው ያየው ማለት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ አንድ አገልግሎት ፈላጊ አካል አንድ የጥበቃ ሠራተኛ ቶሎ እንዲያስገባው አሰር ብር የከፈለም አሊያም ካርድ ለማውጣት የሻይ መጠጫም የሰጠ ሁሉ ሙስና አለ ብሎ ነው የሚናገረው፡፡
‹‹ድርጅቱ (ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል) ራሱ ግልጽ አይደለም›› የሚሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፣ የሙስናው መጠን ምንድን ነው? ምን ያህል ድግግሞሽ አለው? ብሎ ጥናት ቢሠራ ለምሳሌ አዲስ አበባ ውስጥ ያለው የህዝብ ብዛት ወደ አራት ሚሊዮን ቢሆን ከዛ ትክክለኛ የሆነ ማሳያ ወስዶ ቢሠራ እውነት ሊሆን ይችላል በማለት ያብራራሉ፡፡ አንድ ግለሰብ ወይም ደግሞ አኔን ወይም ሁለት ሶስት ግለሰብ በመጠየቅ መረጃ ማስቀመጡ እምብዛም ተዓማኒነት አይኖረውም ነው የሚሉት፡፡
‹‹በአንድ በኩል ይህን መንግሥት የማይወዱና የማይቀበሉ አካላት መጥፎ ገጽታውን ማሳየት ነው የሚፈልጉትና በዛም በኩል የተፋለሰ ነገር ሊኖር ይችላል፡፡ በስሌቱም ሆነ በሳይንሱ ሲታይ ጠቃሚ አይደለም፡፡ እነሱ የሚሠሩት የህዝቡ አመለካከት ምን ይመስላል የሚለውን ነው በማለት ያብራራሉ፡፡
የፖለቲካ ተንታኝ አቶ ካህሳይ ገብረእየሱስ «ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ሙስናን መዋጋት ብርሌን እንደ መስበር ይቆጠራል፡፡›› ይላሉ፡፡ ምክንያቱም ሙስና በዚህች ህገር ውስጥ ሥርዓት ሆኗል፤ በአጋጣሚ አይፈጸምም፡፡ ‹‹ብርሌ አንገቱ በጣም ቀጭን ሲሆን፣ ሆዱ ደግሞ በጣም ሰፊ ነው፡፡››ያሉት አቶ ካህሳይ፣ «አንዴ ብርሌ ውስጥ የገባን ነገር ማስወጣት ይከብዳል» በማለት የሙስናን አሳሳቢ ደረጃ መድረስ ያብራራሉ፡፡
ሙስና እንዲህ በሆነበት ጊዜ ዘገየ እየተባለ የተወሰደ እርምጃ አለ፡፡ በጣም ከተበላሸ በኋላ የተወሰዱ እርምጃዎች አሉ፡፡ እነዚህ እንግዲህ ማስረጃ ተሰባስቦባቸው ለፍርድ ውሳኔ ቀጠሮ የተሰጣቸውም ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ‹አጥፍተናልና፤ ምህረት ይሰጠን› አላሉም፡፡
የፍትህ ሥርዓቱ ደግሞ ፍትህን ማረጋገጥ እንዲሁም ሙስናን መከላከልና ማጥፋት አለበት፡፡ ያ ሁሉ ተደክሞበት የመንግሥት መዋቅሮች በሙሉ ከፓርላማ ጀምሮ እስከ ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ድረስ እንዲሁም ፖሊስን ጨምሮ ማስረጃ ያቀረቡበት ሁኔታ በሙሉ ተጥሶ ምንም አይነት እርምት ሳይደረግበት በኢህአዴግ ፍላጎት ብቻ ኢህአዴግ በሠራው ሥራ የህዝብ ጥያቄ ስላለ እንዲፈቱ አዘዘ›› በማለት አቶ ካህሳይ ያስገነዝባሉ፡፡
መንግሥታት በተለያየ ጊዜ ምህረት ይሰጣሉ፡፡ የሚሰጡት ግን ህጎችን መሰረት አድርገው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ምህረት መስጠት የቆየ ታሪክ አለው፡፡ ነገር ግን ምህረት የሚሰጠው ለማነው? የሚለው መታየት አለበት፡፡ ምክንያቱም ምህረት የሚመለከታ ቸውና የማይመለከታቸው አሉ፡፡ አሰራሩ በራሱ ግልጽ ሊሆን ይገባል፡፡ ምክንያቱም ደንቦችና መመሪያዎች አሉትና፡፡ ነገር ግን እስረኛ በዝቷልና መቀነስ አለበት አንድ ጉዳይ ነው፡፡ የለም በማይገባ መንገድ ነው የታሰሩት እና ያሰርንበት መንገድ ስህተት ስለነበረ ቶሎ ይፈቱ ካሉ እንግዲህ ይሁን፤ ይህም ቢሆን ግን አፈጻጸም አለው፡፡
‹‹ማስረጃ ካልተገኘ ነጻ ማውጣት ነው እንጂ ምህረት ብሎ ነገር የለም፡፡ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከተፈቱ ምህረት አይሆንም፡፡ ነገር ግን አሁን እየተደረገ ያለውን ሳስተውል ለእኔ የሚሰማኝ ምህረት በገፍ ነው የተሰጠው፡፡ ማን ነው ምህረቱ የሚመለከተው የሚል አንድም ዝርዝር ሳይወጣለት የህግ አስፈጻሚው አካልም ሳይወያይበት ነው የተከናወነው፡፡ የወሰነው መንግሥት ሳይሆን ኢህአዴግ ነው፡፡ ኢህአዴግ ገዥ ፓርቲ ቢሆንም በፓርቲ የሚተላለፉ ውሳኔዎች የውስጥ ውሳኔዎች ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ ቀና ስሜት ወይም ፍላጎት ሊሆን ይችላል›› ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
እንደ እርሳቸው አገላለጽ፤ በህገ መንግሥት የተቋቋመ መንግሥት አለ፡፡ ይህ መንግሥት ደግሞ በእዚህ ላይ መወሰን ነበረበት፡፡ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ተጠሪነቱ ለፓርቲው ሳይሆን ለመንግሥት ነው፡፡ በፓርቲው ውሳኔ እንዲህ አይነቱን ድርጊት መፈጸም የህግ ሥርዓት ማፍረስ ወይም መጣስ ነው፡፡ አንዱ መነሻ ነጥብ ይህ ነው፡፡ በፓርቲና በመንግሥት በኩል ያለው ግንኙነትና የሥልጣን ድንበሩ አልተለየም፡፡ በአሰራር መደበላለቅ ይታያል፡፡
‹‹መንግሥት የሚታወቀው በመዋቅሮቹ ነው፡፡ ህግ አውጪም አስፈጻሚም ተርጓሚም አለው፡፡ በኢህአዴግ ውሳኔ ለምን ሲባል ነው የመንግሥት መዋቅሮች የሚታዘዙት›› ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ ‹‹ይህ የሕግ አፈጻጸም ክፍተት የታየበት ነው፡፡ ስለዚህ የህግ የበላይነት የሚያረጋግጥ አሰራር እየተሠራ አይደለም›› ብለው እንደሚያስቡ አቶ ካህሳይ ያብራራሉ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ማን ነው መፈታት ያለበት፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በሚመሩበት ወቅት ደረቅ ወንጀል ፈጽመው የታሰሩ ሰዎች ለየትኛው የህዝብ ጥቅም ነው የተፈቱት፡፡ ምክንያቱም ምህረቱ የሚፈቅድላቸውና የማይፈቅድላቸው እስረኞች አሉ፡፡ ለምሳሌ የማይፈቀድቸው የሚባሉት ደረቅ ወንጀል የፈጸሙ፣ ህዝብን የጨፈጨፉና ንብረት ያቃጠሉ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ፖቲካዊ እንቅስቃሴያቸው አይደለም ያሳሰራቸው፡፡ እነዚህ ህገ መንግሥቱንና ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማፍረስና ለመጫን በመሞከራቸው ነው፡፡ የሰዎችን የመንቀሳቀስና ሠርቶ የመኖር መብት የተጋፉ ናቸው ተብለው ነበር የታሰሩት፡፡
ስለዚህ ይላሉ አቶ ካህሳይ እነዚህ ሰዎች በየትኛው አንቀጽ ነው ምህረቱ የሚገባቸው ሲሉ ጠይቀው፣ ፍርድ ሳያገኙ እንዲለቀቁ ማድረግ ወይ መጀመሪያውኑ የማይታሰሩ ሰዎችን ነው ያሰርነው፤ አሊያም ደግሞ የፍትህ ሥርዓታችን ትክክል አይደለም ማለት ነው ሲሉ ይስረዳሉ፡፡
እንደ እርሳቸው አባባል፤ ይቅርታ የሚያሰጡ ፖለቲካዊ ጉዳይ ያላቸው፣ የእነርሱ መለቀቅ ለህብረተሰቡ ጠቀሜታ ወይም ደግሞ ለፖለቲካ ሥርዓቱ ጠቀሜታ ያለው ከሆነ ወይም ቢቀጡም ባይቀጡም ለህዝቡ ፋይዳ ከሌለው እንደዛም ቢሆንም ግልጽ በሆነ መንገድ እነርሱም ይቅርታ ጠይቀው ፍርዳቸው ሊቀልላቸው ይችላል፡፡
‹‹ የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት አንቀጽ ዘጠኝ ንዑስ አንቀጽ አንድ ላይ ሁሉም ዜጋ የተፎካካሪ ፓርቲዎችንም ጨምሮ ህገ መንግሥቱን የማከበርና የማስከበር ግዴታ እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡›› የሚሉት አቶ ካህሳይ፣ አሁን ህገ መንግሥቱን ማክበር ነው የተያያዝነው ወይስ መሻር፤ የህግ የበላይነት እየተከበረ ወይስ እየተጣሰ ›› ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡
‹‹ይህ ጉዳይ ለእኔ አገሪቱን ወደኋላ የሚመለስ ሆኖ አግኝቼዋለሁ›› ሲሉም ያስገነዝባሉ፡፡ ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አሁን የፀረ ሙስና ሥራ ለመሥራት ምን አይነት ተልዕኮ ተሰጥቶኛል ሊል ይችላል? ተልእኮዬ የሚለውን ለመፈጸምስ ምንስ አይነት ሞራል ይኖረዋል ? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡
‹‹ሰሞኑንም የህግ አውጪው ፓርላማ ፊት ተሰብስቦ የምህረት አሰጣጥ አዋጅ ሲያወጣ ነበር፡፡ ይህ ማለት የምህረት አሰጣጥ አዋጅ አልነበረንም፡፡›› የሚሉት አቶ ካህሳይ፣ አዋጁ በሌለበት ነው ይህ ሁሉ እየተሠራ ያለው ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
የኦሮሞ ራስ መረዳጃ ድርጅት ሥራ አስኪያጅና የፖለቲካ ምሁር ዶክተር ሙሉጌታ ደበበ በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለው ነገር አያዎ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹በአንድ በኩል ለግለሰቦች መብት ከምንም በላይ ነው ብለን እየታገልን ነው የሚሉት ዶክተር ሙሉጌታ፣‹‹እነዚህ ሰዎች ታሰሩ፤ ማስረጃ ከሌለ ውሳኔ የማግኘት መብት አላቸው፡፡ ምክንያቱም ዜጎች ናቸው፡፡ የመንግሥት ድክመት እንዳለ ሆኖ ቶሎ አጣርቶ ውሳኔ የመስጠቱ ጉዳይ ተገቢ ሆኖ ሳለ ለዓመታት ታስረዋል›› ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት፤ ዋናው የእስራት ትርጉሙ ማረም ነው፡፡ ማንም ሰው ማስረጃ ከተገኘበት መታሰር አለበት፡፡ እነዚህ ሰዎች ወንጀል ሠርተዋል፤ ማስረጃ ተይዞባቸዋል ከተባለ ክትትሉን በማጠናከር ውሳኔ መሰጠት ነበረበት፡፡
‹‹መንግሥት ይህን አለማድረጉ የሰብዓዊ መብትን እንደ መጫን ነውና የምቆጥረው ድክመቱ አለ›› ይላሉ፡፡ ‹‹ተጣርቶ ወንጀል የለባቸውም ተብለው ቢወጡም በጣም ለረጅም ጊዜ ታስረዋልና ይህም የሚያሳየው የፍትህ ሥርዓቱን ድክመት ነው›› ሲሉ ያብራራሉ፡፡ ምክንያቱም ለግለሰብ መብት፣ ለቡድን መብት እየታገልን ነው በሚባልበት ወቅት የፍትህ ሥርዓቱ ያሳየው ድክመት ተለቀቁ የተባሉትን እና ቤተሰባቸውን ጨምሮ ችግር ላይ እንዲወድቁ አድርጓቸዋል ይላሉ፡፡
ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በመፍትሄነት የሚያስቀምጡት ሙስናን ለመዋጋት በጣም የዳበረ የሲቪል ማህበረሰብ ማስፈለጉን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ለምሳሌ እድሮች፣ የገዳ ሥርዓትና የመሳሰሉት ወደ 199 ሺ እንደሚሆኑ ይጠቅሳሉ፡፡ እነዚህ እኤአ በ2005 ‹የኢትዮጵያ ሲቪል ሶሳይቲው ምን ይመስላል› በሚል ጽንሰ ሐሳብ ለአውሮፓ ህብረት ጥናት ስንሠራ የመዘገብናቸው ናቸው ይላሉ፡፡
ኢትዮጵያ የዳበረ ሲቪል ማህበረሰብ ያላት እንደመሆኗ ይህን ማህበረሰብ ሙስና ለመቆጣጠር ተግባር አጋር ሁኑ ቢባሉ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ይጠቁማሉ፡፡
ዶክተር ቆስጠንጢኖስ እንዳብራሩት፤ መንግሥት እንደዚህ አይነቶችን ማህበራት የሚያቀርብ ከሆነ፣ ሲቪል ማህበረሰቡ ወደ ዴሞክራሲ ጥያቄ መሄዱ አይቀርም፡፡ በዚህ ምክንያት መንግሥት ይህንን አልፈለገም፡፡ ምክንያቱም ሁልጊዜ ተቃዋሚዎች የሚወጡት ከሲቪል ማህበረሰብ ነውና፡፡ አጀንዳ ይዘው ነው የሚወጡት፤ ለምሳሌ ሙስና አጠፋለሁ ብለው ሊነሱ ይችላሉ፡፡ ወይም ደግሞ እድገት አመጣለሁ ብለው ሊሆን ይችላል፡፡
እንደ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ገለጻ፤ የመገናኛ ብዙኃን በራሳቸው ትልቅ ድርሻ ያለባቸው ቢሆንም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ስለሙስና እንኳ በወጉ አይዘግቡም ነበር፡፡ ለምሳሌ የምርመራ ጋዜጠኝነትን ለአብነት ብንወስድ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት እንዲመረጡ ያደረገችው ሩሲያ ናት የሚለውን እነዋሽንግተን ፖስት፣ እነኒውዮርክ ታይምስ ናቸው መጀመሪያ ያወጡት፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ልዩ ዓቃቤ ህግ ተመድቦ ዓቃቤ ህጉ ምርመራ የጀመረው፡፡ የመገናኛ ብዙኃኑ የምርመራ ዘገባ ሲሠራ ደግሞ ብዙ ነገር መውጣት ይጀምራል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ግን የመንግሥት ሚዲያው ራሱ እንደዚህ አይነት ሥራ ሊሠራ የሚችልበት ሀብትም የለውም፡፡ በመሰረቱ የተሻለ ደመወዝ ተከፍሏቸው የምርመራ ዘገባ ሊሠሩ የሚችሉ ሊኖሩ ይገባል፡፡ ዋናው ነገር የምርመራ ጋዜጠኝነት ነው አስፈላጊው፡፡
‹‹ዋናው ጉዳይ ህዝቡን ማስተማር ማስፈለጉ ነው›› የሚሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፣ አንድ ኢትዮጵያዊ አገልግሎት ፍለጋ ቀበሌ ሄዶ አገልግሎት ለማግኘት እምቢ ከተባለ የት ነው መሄድ ያለበት፤ ማንስ ዘንድ ነው አቤት ማለት የሚጠበቅበት›› ሲሉ ይጠይቃሉ።፡
የፍትህ ሥርዓቱን የማጠናከር አስፈላጊ ነትንም ያመለክታሉ፡፡ ምክንያቱም ገንዘብ ያላቸው ሰዎች ዳኛ ፊት ቀርበው ይታሰራሉ ማለት ዘበት ነው፡፡ ብዙዎች ‹‹የታሰራችሁት በቂ ነው›› ተብለው ተለቀዋል፡፡ ሲሉ ያብራራሉ፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ማሰር ከደርግ ጀምሮ ባህል ሆኗል፡፡ ፍርድ ቤት ቀጠሮ በማራዘምም ማመላለስ ተለምዷል፡፡ ይህ ደግሞ መንግሥት ራሱ ያደረጀላቸው የሌብነት መስመር ነው፡፡ በቢሊዮን የሚቆጠር ብር ጠፋ ሲባል ‹እንዴ መንግሥት አለ ወይ?› ያሰኛል፡፡ በመሆኑም ዝርፊያው የተደራጀ ይመስላል፡፡ የውስጥ ኦዲተሩም ከእነሱ ጋር ይስማማል፤ ይካፈላልም» ሲሉ ያብራራሉ፡፡
እንደ እርሳቸው አነጋገር፤ይህን መጥፎ ልምድ መግታት ያስፈልጋል፡፡ በመንግሥት በኩል በየቀኑ ኤጀንሲ፣ ኮርፖሬሽን ተቋቋመ፤ የሚል አዋጅ ይሰማል፡፡ የግሉ ዘርፍ መሥራት የሚችለውን ነው መንግሥት ገብቶ እየሠራ የሚገኘው ፡፡ ይህ መሆን የለበትም፤ በራሱ ዝርፊያ ነው፡፡ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች መቀነስ አለባቸው በሚባልበት በዚህ ጊዜ በመንግሥት አካላት መሠራቱ አስፈላጊ አይደለም፡፡
ዶክተር ሙሉጌታ በበኩላቸው በኢኮኖሚ ማደግ ሙስና እንዳይከሰት ዋስትና አይሆንም ይላሉ፡፡ ዛሬ በሙስናው ወንጀል ከፍተኛ ደረጃ ላይ ያሉት እነ ናይጄሪያ እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ በኢኮኖሚያቸው የላቁ መሆናቸውን በመጥቀስ በኢኮኖሚ ማደግ ሙስናን እንደማያስቀረው ያስገነዝባሉ፡፡ ‹‹በኢኮኖሚ ማደግ ብቻውን መፍትሄ ሊሆን አይችልም፤ በራሱ የተስተካከለ ሥነ ምግባር ይፈጥራል ማለትም አይደለም ሲሉ ያብራራሉ፡፡
‹‹አድገዋል የሚባሉ የእስያ አገራት መልካም ሥነ ምግባር ያላቸው ህዝቦች መሆናቸውን በብዙ አጋጣሚዎች ማስተዋል ችያለሁ፡፡ ሲንጋፖርን፣ ታይላንድን፣ ኮሪያን፣ ህንድን፣ ባንኮክን እንዲሁም ቻይናን ጎብኝቻለሁ›› የሚሉት ዶክተር ሙሉጌታ፣ ህዝቡ ከምንም በላይ ሥራውን አክባሪ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡
እኛ ከዚህ አኳያ ራሳችንን ስንፈትሽ ገና ብዙ መጣል ያለብን አላስፈላጊ ግታንግት አለ ሲሉም ይገልጻሉ፡፡ መገንባት ያለብን በርካታ ጉዳዮችም አሉ፤ በዚህም ሁሉንም አካላት ማሳተፍ እንደሚገባም ይጠቁማሉ፡፡ ሁሉም ህብረተሰብ መብቱንና ግዴታውን ሊያውቅ፣ አገሪቱ የእኔ ናት የሚል ስሜት ሊያዳብር እንደሚገባም ያስገነዝባሉ፡፡
ተንታኞቹ በቅርቡ ክሳቸው እየተቋረጠ ከእስር በተፈቱት የሙስና ወንጀል ተጠርጣሪዎች ላይ የተለያየ አተያይ ቢኖራቸውም፤ ሙስናን በማስወገድ አስፈላጊነት ላይ ግን ተመሳሳይ አቋም አላቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እንዳሉትም ሙስና በመንግሥት አቅም ብቻ የሚወገድ ባለመሆኑ ሁሉም የየራሱን ድርሻ መወጣት ይኖርበታል፡፡

አስቴር ኤልያስ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።