የተደራጁ ሌቦችን ለመዋጋት

13 Jun 2018

ሰሞኑን በተካሄደው አራተኛው አገር አቀፍ የፀረ-ሙስና ጥምረት ጠቅላላ ጉባኤ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ «የተደራጀ ሌብነትና ዝርፊያ (ሙስና) ሕዝብን ያስመርራል፤ የአገርን ዕድገት ያደቃል፤ ነፃ የገበያ ውድድርን ያከስማል፤ ዴሞክራሲን ያቀጭጫል፤ የሕዝብን የወደፊት ተስፋ ያጨልማል» ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ አያይዘውም መንግሥታዊና ሕዝባዊ ተቋማትን ከተደራጁ ሌቦች ለመከላከል የሚደረገው ትግል በመንግሥት ብቻ ከዳር እንደማይደረስ አስታውቀዋል፡፡ በመሆኑም መገናኛ ብዙኃን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ሲቪል ማኅበራትና የአገር ሽማግሌዎች የተደራጀ ሌብነትን በመዋጋት ለሕዝቡ አርአያ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየታቸውን የሰጡ ምሁራንም፤ የተደራጀ ሌብነትን በዘላቂነት ለመከላከል የቁጥጥር ሥርዓቱን ለማጠናከር ሲቪል ማህበራትና መገናኛ ብዙኃን የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ አስተዳደርና ልማት አመራር ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ፤ በንግድ እና በዝምድና ግንኙነት የሚፈጠሩ ተገቢ ያልሆኑ ጥቅሞች ለሙስና መበራከት ምንጭ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ይህም አገሪቱ ማግኘት የነበረባትን ጥቅም እንዳታገኝ አድርጓል፤ ግለሰቦች መክፈል ያለባቸውን እንዳይከፍሉና አላግባብ እንዲጠቀሙ በር ከፍቷል፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግር ፈጥሯል ይላሉ፡፡
እናም ይላሉ ዶክተር ፈንታ፤ ሙስናን በዘላቂነት ለመፍታት በአጭርና በረጅም ጊዜ የሚወሰዱ መፍትሄዎች አሉ፡፡ በአጭር ጊዜ የፖለቲካ መሪ ቁርጠኛ የሆነ አመራር መስጠት ይኖርበታል፡፡ በተቋም ደረጃ ደግሞ እያንዳንዱ አመራር ከውስጡ ያሉትን የነቀዙ አሠራሮች ለይቶ ማውጣት አለበት፡፡ «ሙስና እንደሚያዋጣ የሚናገሩ ሰዎች ያሉበት አገር ነው ያለነው፡፡ ትሰርቃለህ አራት ዓመት ይፈረድብሀል፤ ካርታህን እየተጫወትክ ቆይተህ ከአራት ዓመት በኋላ ከእስር ትወጣለህ፤ ስትወጣ ዘመናዊ መኪና (ቪ-ኤይት) ትነዳለህ ይሉሃል» የሚሉት ዶክተር ፈንታ፤ ይህ አስተሳሰብ ሊሰበር የሚችለው ያጠፉ ሰዎች በሕግ አግባብ ሲቀጡና የመዘበሩትን የሕዝብ ሀብት ማስመለስ ሲቻል ነው፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ማለት አመራሩ ይህን ኃላፊነት ወስዶ ተቋሙን ንጹህ ማድረግ አለበት፡፡ መንግሥት ኃላፊነትን ቆጥሮ ሰጥቶ፤ ቆጥሮ መረከብ ይገባዋል፡፡ እነዚህን ማስፈጸም ያቃታቸውን አመራሮች ተጠያቂ ማድረግም ይኖርበታል፡፡ በዚህ ጊዜ ነው የፖለቲካ ቁርጠኝነት በግልጽ ታይቷል የሚባለው፡፡ በመሆኑም ተጠያቂነት ለዜጎች በሚገለፅ ደረጃ ሊኖር ይገባል ይላሉ፡፡
ሁለተኛው በሁሉም መንግሥታዊ ተቋማት ግልጽ የሆነ የአሠራር ዘዴ መከተል ሲሆን፤ በሦስተኛ ደረጃ ጠንካራ፣ ነፃ፣ አገር ወዳድና ሙያዊ ሥነ ምግባር ያለው መገናኛ ብዙኃን ያስፈልጋል፡፡ በተለይም የመንግሥትን ተቋማት ጉድለቶች እየፈተሹ በምርምራ ዘገባ የሚያጋልጡ መገናኛ ብዙኃን እንዲበራከቱ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡
«ከዚህ በተጨማሪ የሥነ ምግባር መገንቢያ በሆኑት የሃይማኖት ተቋማት ውስጥ የሚታየው ብልሹ አሠራርና ዝርፊያ ክትትል ሊደረግበት ይገባል፡፡መንግሥት በጸረ ሙስና ትግሉ አይመለከተኝም የሚለው ተቋም ሊኖር አይገባም፡፡ ምክንያቱም የሃይማኖት ተቋማት ጥሩ የሆነ ሥነ ምግባር ያለው ዜጋ መፍጠሪያ በመሆናቸው እነሱ አርአያ ካልሆኑ መልካም ሥነ ምግባር የተላበሰ ዜጋ መፍጠር አይችሉም» ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
ከሙዓለ ሕፃናት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድረስ በሥነ ምግበርና በሥነ ዜጋ የተገነቡ ዜጎችን ማፍራት የግድ ይላል፡፡ ለዚህ ሥራም ከቤተሰብ ጀምሮ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍልና የሚመለከታቸውን አካላት ማሳተፍ እንደሚገባ ዶክተር ፈንታ ይገልፃሉ፡፡
የአፍሪካ ፀረ ሙስና ቦርድ ሊቀመንበር ሆነው ያገለገሉትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሙስና ሁኔታ ብዙ መልክ አለው ይላሉ፡፡አንደኛው መንግሥት ለተቋማት ከሚመድበው በጀት የሚዘረፍ ገንዘብ ነው፡፡ ለዚህም በቅርቡ ዋና ኦዲተር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት መሠረት ወደ 22 ቢሊዮን ብር ምን ላይ እንደዋለ ማረጋገጥ አለመቻሉን ይፋ ማድረጉን ለአብነት ያነሳሉ፡፡ ይህ አሀዝ የመንግሥት በጀት ዝም ብሎ እንደሚዘረፍ በግልፅ ያሳያል፡፡
ሁለተኛው ባለሥልጣናት የተለያዩ ትላልቅ ፕሮጀክቶች በጨረታ ለግል ኩባንያ ዎች በሚሰጡበት ጊዜ በመደራደር የሚዘርፉት ገንዘብ መኖሩ ነው፡፡ ሦስ ተኛ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ሠራ ተኞችም ሆኑ ባለሥልጣናቱ ሕጋዊ የሆነውን አገልግሎት ለደንበኞች ለመስጠት ጉቦ የሚቀበሉበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ ከዚህ አኳያ ከመንግሥት ካዝና ጠፋ የሚባለው ገንዘብ 22 ቢሊዮን ብር መድረሱ ሙስና ወደ ከፋ ደረጃ እየተሸጋገረ መሆኑን ያሳያል ባይ ናቸው፡፡

ጌትነት ምህረቴ
ይህም በሙስና ከሚታ ወቁት እንደ ናይጀሪያ፣ ኬንያ እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ አስፈሪና አስደንጋጭ ደረጃ እየተደረሰ መሆኑን እንደሚያመላክት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ይናገራሉ፡፡ ከዚህ አኳያ ሙስና በአገራችን አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት ይቻላል፡፡ የመንግሥት ፕሮጀክቶችና ኩባንያዎች እየተስፋፉ ሲሄዱ ሙስናው በዚያው ልክ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ለምሳሌ ቻይናና ሕንድ በኢኮኖሚ ዕድገታቸው የሚጠቀሱ አገሮች ቢሆኑም በሙስናም የጦዙ አገሮች ናቸው፡፡ መንግሥት ብቻ ብዙ ነገር ይስራ በሚባልባቸው (ልማታዊ የመንግሥት አቅጣጫ በሚከተሉ) አገሮች ብዙ የሙስና ችግር ይፈጸማል፡፡ ስለዚህ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ማዘዋወሩ ሙስናን ለመከላከል አንዱ ስልት መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
እንደ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ገለጻ፤ ሌላው ችግር የተጠያቂነት ጉዳይ ነው፡፡ የመንግሥት ኃላፊዎች ከፖለቲካ ሥርዓቱ ጋር አብረው ስለተያያዙ አይጠየቁም፡፡ እነሱን ለመክሰስም አስቸጋሪ ነው፡፡ ምክንያቱም የፖለቲካ ጫና ማድረግ ይችላሉና፡፡ ለአብነትም የብረታ ብረትና ኢንጅነሪግ ኮርፖሬሽን ከጦር ኃይሉ ጋር የተያያዘ ስለሆነ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር አባክኗል እየተባለ እሱን ደፍሮ መናገር አልተቻለም፣ ተጠያቂም የሆነ የለም፡፡
እናም መንግሥት ግድቦችን፣ የማዳበሪያና የስኳር ፋብሪካዎችን በአስቸኳይና በተመጣጣኝ ዋጋ ይሰራቸዋል ብለው በቀናነት ያቀዱ ኃላፊዎች ቢኖሩም በተቃራኒው በዚህ አጋጣሚ የሚሰርቁ ሰዎችም ጥቂት አይደሉም፡፡እነዚህን ገንዘብ የሚሰርቁ ሰዎች ትላልቆቹንም ያነካኳቸዋል፡፡ እናም ሌቦቹ የፖለቲካ ከለላ ስላላቸው ተጠያቂነታቸው አነስተኛ ነው ይላሉ፡፡
ፕሮጀክቶችን የሚከታተሉ ኮርፖሬሽኖችና ኤጀንሲዎች በሚቋቋ ሙበት ጊዜ ቢሮ ይከራያሉ፣ ሠራተኛ ይቀጥራሉ፣ መኪናዎች ይገዛሉ፡፡ ይህም ለሙስና በር ይከፍታል፡፡ ስለዚህ መንግሥት እንደ ሰለጠኑ አገራት ትላልቅ መንገዶች፣ ግድቦች፣ ኃይል ማሰራጫዎችን የመሳሰሉ የመሠረተ ልማት ሥራዎች በሚሰሩበት ጊዜ የቁጥጥር ሥርዓቱን ማጠናከር አለበት፡፡ ምክንያቱም ቁጥራቸው በበዛ ቁጥር ዋና ኦዲተርም አሁን እያደረገ ያለውን የናሙና ኦዲት እንኳ ለማድረግ ይቸገራል፡፡
ለምሳሌ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሆነ የፍጥነት መንገዶችን የሚሰሩት የግል ኩባንያዎች ናቸው፡፡ ሆኖም እነዚህን ለማሳለጥ ተብሎ የሚፈጠሩት ኮርፖሬሽኖችና ኤጀንሲዎች ሙስና ውስጥ ይገባሉ፡፡ መንግሥት ይህንን ሊቆጣጠር በሚችልበት ስልት ላይ መሰራት እንዳለበት ምሁሩ አሳስበዋል፡፡
ሙስና በአብዛኛው ከአምባገነናዊ መንግሥቶች ጋር አብሮ የሚሄድ ነው፡፡ በአንጻሩ ዴሞክራሲያዊ በሆኑ አገሮች ላይ ያለው ሙስና በጣም ትንሽ ነው፡፡ ምክንያቱም ሙስናን የሚዋጉ ሁለት ነገሮች አሏቸው፡፡ አንዱ የተደራጀና በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ መሳተፍ የሚችል የሲቪል ማህበራት ሲሆኑ፤ ዕድሮችን፣ ማህበራትና እንደ ገዳ ዓይነት ያሉ ሥርዓቶችን በማጠናከር ሙሰኞችን እንዲያጋልጡ ካልተደረገ በስተቀር መንግሥት ባለው የፖሊስና የምርመራ ኃይል ሊከላከለው አይችልም፡፡ ምክንያቱም ገንዘብ የሚሰርቁት በቀጥታ ሳይሆን ለሥራ ወጪ ሆኗል ብለው የሀሰት ደረሰኝ በማዘጋጀት ነው፡፡
ለምሳሌ በኢትዮጵያ ትራንስፓረንሲ ኢንተር ናሽናል የሲቪል ማህበር ሆኖ ነው የተደራጀው፡፡ የሙስና ችግር ድምጹን ከፍ አድርጎ ማስተጋባት የቻለው እሱ ነው፡፡ እናም እንደ እነዚህ ዓይነት የሲቪል ማህበራት መጠናከር አለባቸው ብለዋል፡፡
አራተኛ ደረጃ የምርመራ ጋዜጠኝነትን ማጠናከር ነው፡፡ መገናኛ ብዙኃን ለአገሪቱ አስተማሪ፣ መረጃ አቅራቢና ጉድለቶችንም አጉልቶ የሚያሳይ ምርመራ መስራት አለባቸው፡፡ እነዚህ ተቋማት የተሻለ በጀት ኖሯቸውና የሕግ ከለላ ተሰጥቷቸው በሚፈጸሙ ሙስናዎች ላይ ምርመራ በማድረግ ማጋለጥ አለባቸው የሚል ሃሳብ አላቸው፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ የጋና እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት ኪዋሲ ናታኪ ገንዘብ ሲቀበሉ የሚያሳይ በድብቅ በተቀረፀ ምስል መረጃ በመውጣቱ ጋና የእግር ኳስ ፌደሬሽኑን በትናለች፡፡ የዚህ ዓይነት የምርመራ ዘገባ በኢትዮጵያም ያስፈልጋል፡፡
ሆኖም ሙስና ችግር በሚታይባት ኢትዮጵያ ያሉ የሕዝብ መገናኛ ብዙኃን አራት ወፍጮ ተተከለ፣ የመስኖ ግድብ ተሰራ ከማለት ውጪ ጠንከር ያለ የምርምራ ዘገባ የሰሩት ነገር የለም ሲሉ መገናኛ ብዙኃኑን ተችተዋል፡፡ በተለይ ሙስናን በማጋለጥ የሕዝብ መገናኛ ብዙኃን ከፍተኛ ሚና ቢኖራቸውም ሥራቸውን እየሰሩ አይደለም፡፡ እነዚህን የሙስና መከላከያ ስልቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ አጠናክሮ መስራት ይገባል፡፡
ሙስናን ከወዲሁ መከላከል ካልተቻለ ለሰላም፣ ለዕድገትና ለንግድ እንቅስቃሴ እንቅፋት መፈጠሩ እንደማይቀር ከሌሎች አገራት ትምህርት መውሰድ ይገባል፡፡ እናም ሙስናን ለመዋጋት የሲቪል ማህበረሰቡ ተሳትፎ ማሳደግ አስፈላጊ ነው፡፡ የምርመራ ጋዜጠኝነትን ማስፋፋትና ከለላ መስጠት ይገባል፡፡ለዚህም የመንግሥትን ቁርጠኝነት ይጠይቃል፡፡

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።