ቀልጣፋ የቪዛ አገልግሎት-ለቱሪዝምና ኢንቨስትመንት እድገት

06 Jul 2018

ኢትዮጵያ በርካታ የቱሪዝም መስህብ ሀብቶች ባለቤትና የበርካታ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫዎች መሆኗ አገሪቱ እያስመዘገበችው ካለው ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ጋር ሲደመር፣ አገሪቱ ለሥራ፣ ለጉብኝትና ለሌሎች ጉዳዮች ወደ ድንበሯ ለሚገቡ የውጭ አገራት ዜጎች ቀልጣፋና አስተማማኝ የቪዛ አገልግሎት መስጠት ከቀዳሚ የትኩረት አቅጣጫዎቿ መካከል አንዱ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡
ታዲያ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግሥትም ለሥራ፣ ለጉብኝትና ለሌሎች ጉዳዮች ወደ አገሪቱ የሚመጡ የውጭ አገራት ዜጎች ቀልጣፋ የቪዛ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችሉ አሠራሮችን ሲተገብር ቆይቷል፡፡ ከነዚህ አሠራሮች መካከል አንዱ የ«ኦንላይን ቪዛ (Online Visa/ኢ-ቪዛ)» ሥርዓት አንዱ ነው፡፡ ይህን አሠራር ተግባራዊ በማድረግም ከባለፈው ግንቦት ወር 2009 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎቱን ለ37 አገራት ዜጎች መስጠት ተጀምሮ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱና ሀገሪቱን ለቱሪስቶችና ባለሀብቶች ክፍት ለማድረግ ከግንቦት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ አገልግሎቱን ለሁሉም የውጭ አገራት ዜጎች መስጠት ተጀምሯል፡፡ ይህ የኢ-ቪዛ አገልግሎት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለሙያዎች የተሠራ የቴክኖሎጂ ውጤት ነው፡፡
በኢትዮጵያ አየር መንገድ ዲጂታል ዳይሬክተር አቶ ምህረተአብ ተክላይ፣ አገልግሎቱ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የሚፈልጉ ሰዎች ባሉበት ቦታ ሆነው በኤሌክትሮኒክ መንገድ ቪዛ ማግኘት የሚችሉበት አሠራር ነው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፣ ይህ አገልግሎት የአገልግሎት ፈላጊውን ግለሰብ ማስረጃዎችን ተመልክቶ፣ አገልግሎት ጠያቂውም ክፍያውን ከፍሎ መረጃው ወደኢሚግሬሽን ተልኮ ቪዛውን ከኢሚግሬሽን መሥሪያ ቤት በኢ-ሜይል አማካኝነት የሚያገኝበት አሠራር ነው፡፡ ይህም የአገልግሎቱ ፈላጊዎች ፈጣን፣ ቀላልና አስተማማኝ የሆነ አገልግሎት እንዲገኙ ያስችላቸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም አገልግሎቱ በኢሚግሬሽን መሥሪያ ቤት የመረጃ ቋት የመረጃ አቅርቦት እንዲሁም የአገልግሎቱ ጠያቂዎች ዝርዝር መረጃዎች ምልከታ ላይ ተመስርቶ ስለሚከናወን ለፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች አስተማማኝ ምላሽ የሚሰጥ አሠራር ነው፡፡
የአገልግሎቱን ፋይዳዎች በተመለከተ ሲገልጹም፣ «አገልግሎቱ ፋይዳው ብዙ ነው፡፡ ለቱሪዝም መጠናከር ትልቅ አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡ ለአብነት ያህል ሩዋንዳ አገልግሎቱን መስጠት እንደጀመረች የቱሪስት ፍሰቷ ከ22 በመቶ በላይ ጨምሯል፡፡ ኢትዮጵያ በርካታ የቱሪስት መስህቦች ቢኖሯትም ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ (ጥቅም) አነስተኛ ነው፡፡ የዚህ አሠራር ሥርዓት መጀመር የቱሪስት ፍሰቱን በመጨመር አገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘው ገቢ እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ የሚሰማሩ ባለሀብቶችንም ቁጥር ይጨምራል» ይላሉ፡፡
አቶ ምህረተአብ እንደሚናገሩት፣ የኢ-ቪዛ አገልግሎት አንድ አገልግሎቱን ጠያቂ ግለሰብ በሦስት ሰዓታት ውስጥ ቪዛ ማግኘት ያስችላል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ቀንና ሌሊት በሦስት ፈረቃዎች አገልግሎቱ እየተሰጠ ነው፡፡
አገልግሎቱ ሰፊ ዝግጅት የተደረገበት ሥራ መሆኑን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፣ በአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱ ላይ ችግሮች ቢፈጠሩ የኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳዮች መምሪያ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመሆን የጋራ ግብረ ኃይል አቋቁመዋል፡፡ ይህም ከቴክኖሎጂ ሽግግርና አገልግሎቱን በራስ አቅም ከመስጠት አንፃር ትልቅ እምርታና ለውጥ ነው፡፡
አሁን እየተሰጠ ያለውን አገልግሎት የበለጠ ተደራሽና ውጤታማ ለማድረግ በቀጣይ የሚሠሩ ሥራዎች እንዳሉ አቶ ምህረተአብ ይገልፃሉ፡፡ ከነዚህ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች መካከልም አገልግሎቱ ዓለም ላይ ብዙ ተናጋሪ ባላቸው በሰባት ቋንቋዎች እንዲሰጥ፣ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች አገልግሎቱን ለማግኘት የሚከፍሉትን ክፍያ በየአገራቸው የክፍያ ሥርዓት መክፈል እንዲችሉና አሁን በኢ-ሜይል ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን እንዲሰጥም የማድረግ ተግባራትም ዋናዎቹ እንደሆኑ ያስረዳሉ፡፡
የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ ዋና መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ገብረዮሐንስ ተክሉ የኢ-ቪዛ አገልግሎት አገሪቱ በዘርፉ ያቀደችውን ለውጥ ለማሳካት ከሚያስችሉ አሠራሮች መካከል አንዱ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፣ ይህ አሠራር ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የውጭ አገራት ዜጎች ቀልጣፋ የቪዛ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ አገሪቱ ከዓለም ጋር የሚኖራትን ትስስር የበለጠ ጠንካራ ያደርገዋል፡፡ ይህም ለጎብኚዎችና ለባለሀብቶችም አገሪቱን ለመጎብኘትና መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ጠንካራ መተማመኛ ይሆንላቸዋል፡፡
አገሪቱ በፍጥነት እያደጉ የመጡትን የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በኢሚግሬሽንና በዜግነት ጉዳዮች ላይም በመጠቀምና ለውጭ አገራት ዜጎች እንቅስቃሴ ምቹ በመሆን ተወዳዳሪ መሆን ስላለባት አገልግሎቱን መስጠት እንደጀመረችም ያስረዳሉ፡፡
ይህን የአሠራር ሥርዓት ከግብ ለማድረስ ባለድርሻ አካላት ብርቱ ጥረት እንዳደረጉ የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፣ «የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ ዋና መምሪያና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች የተጠቃሚዎችን ገንዘብ፣ ጊዜና ጉልበትን የሚቆጥበው ይህ አሠራር እውን እንዲሆን ከ20 ወራት በላይ ደክመውበታል» ይላሉ፡፡ በቀጣይም አገልግሎቱ በየጊዜው በሚደረጉለት ማሻሻያዎች የውጭ አገራት ዜጎች የተሻለና ለወቅቱ የሚመጥን አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ እንደሚሠራም ይጠቁማሉ፡፡
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ፎዚያ አሚን በበኩላቸው፣ የኢ-ቪዛ ሥርዓቱ የቱሪስት ፍሰቱን እንደሚጨምረው ይገልፃሉ፡፡ ሚኒስትሯ እንደሚሉት፣ አገልግሎቱ መንግሥት አገሪቱ ከመላው ዓለም ጋር ያላትን ትስስር ለማጠናከር የወሰዳቸው እርምጃዎች አካል ነው፡፡ የቱሪስት ፍሰቱን እንዲጨምር በማድረግም «ምድረ ቀደምት (Land of Origins)» የሚባለው የአገሪቱ የቱሪዝም መታወቂያም በብዙዎች ዘንድ እውቅና እንዲያገኝ ላቅ ያለ ሚና ይጫወታል፡፡
የምጣኔ ሀብትና ፖለቲካ ጉዳዮች ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ብርሁተስፋ የኢ-ቪዛ አገልግሎት ፋይዳው ብዙ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ እንደርሳቸው ማብራሪያ፣ በቅርቡ ይፋ የሆነውና ለሁሉም አገራት ዜጎች ክፍት የሆነው የኢ-ቪዛ አገልግሎት የ«ቪዛ» አሰጣጥ ሥርዓቱን ቀልጣፋ በማድረግ የጎብኚዎች ቁጥር እንዲጨምርና በርከት ያሉ ባለሀብቶች ወደአገሪቱ መጥተው በኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ እንዲሰማሩ ያደርጋል፡፡
ያደጉት አገራት ብቻ ሳይሆኑ የአፍሪካ አገራትም በዚሁ ሥርዓት መጠቀም ከጀመሩ ብዙ ዓመታት እንደተቆጠሩ የሚያወሱት ባለሙያው፣ እርምጃው ኢትዮጵያ ለውጭ ጎብኚዎችና ባለሀብቶች የበለጠ ክፍት ለመሆን የምታደርገውን ጥረት እንደሚያግዝም ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አገልግሎቱ የቪዛ አሰጣጥ ሥርዓቱን በቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ የኤምባሲዎችን ሥራ እንደሚያቃ ልልም ያብራራሉ፡፡
ከዚህም ባለፈ የኢ-ቪዛ ሥርዓቱ ለቀጣናዊና አህጉራዊ ትስስሮችም ፋይዳ እንዳለው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ይገልፃሉ፡፡ እንደርሳቸው ገለፃ፣ አገልግሎቱ የአፍሪካ ኅብረት የወሰነውን የአፍሪካውያንን ነፃ እንቅስቃሴ ውሳኔ ለማስፈጸም የሚያስችል እርምጃም ነው፡፡ ኅብረቱ አፍሪካውያን በአህጉሪቱ ውስጥ አንድ ወጥ በሆነ ፓስፖርት እንዲዘዋወሩ የሚያስችል መርሃ ግብር ከዚህ ቀደም ይፋ አድርጓል፡፡ ይህ የኢ-ቪዛ ሥርዓት ደግሞ ቪዛ በቀላሉ ለማግኘት ስለሚያስችል ኢትዮጵያ የኅብረቱ ውሳኔ ተፈፃሚ እንዲሆን የራሷን አስተዋፅዖ እንድታበረክት የሚያስችላት አሠራር ነው፡፡
«የውጭ ምንዛሪ እጥረትን የማቃለል ጉዳይም የአገልግሎቱ ሌላኛው ፋይዳ ነው፡፡ የኢ-ቪዛ አገልግሎት የቱሪስቶችን ቁጥር እንዲጨምር በማድረግ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ገቢ እንዲያድግ ያደርጋል፡፡ በዚህም ምንም እንኳ አገሪቱ ለገጠማት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግር ብቻውን መፍትሄ መሆን ባይችልም የበኩሉን አስተዋፅኦ ያደርጋል» ይላሉ፡፡

አንተነህ ቸሬ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።