‹‹የሚወጡ ህጎች ጥራታቸውን የጠበቁ፣ ግልጽና ዝርዝር ለማድረግ ይሰራል›› -ዶክተር ሙሉጌታ መንግስት የህግና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባኤ አስተባባሪ Featured

07 Jul 2018

በአገራችን በተግባር ላይ ከዋሉ ህጎች መካከል በተለይ የፀረ ሽብር፣ የመገናኛ ብዙሃን እና የመረጃ ነፃነት እንዲሁም የበጎ አድራጎት ማህበራት አዋጅ በተደጋጋሚ ጊዜ በአገር ውስጥ እና በውጪውም ጭምር ቅሬታ እና ትችት ይሰነዘርባቸዋል። በመሆኑም በህጎቹ ዙሪያ ያሉ ችግሮች ምንድን ናቸው? የሚለውን ጥናት የሚያጠና የህግና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባኤ በቅርቡ ተቋቁሟል። አማካሪ ጉባኤው 13 አባላት ያሉት ሲሆን ይህን የአማካሪ ጉባኤ በማቋቋም ስራ ላይ ከሚሳተፉት መካከል ዶክተር ሙሉጌታ መንግስት አንዱ ናቸው።
ዶክተር ሙሉጌታ ቀደም ሲልም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮች ዙሪያ የፍትህ እና የህግ ዘርፉ ላይ ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ ከእርሳቸው ጋር በነበረን ቆይታ የአማካሪ ጉባኤው መቋቋም አስፈላጊነት እና ከዚህ ጋር ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ቃለመጠይቅ አድርገናል፡፡
አዲስ ዘመን፦ እንደ ችግር ለሚነሱ ህጎች የማሻሻያ ሃሳብ የሚያቀርብ የህግና ፍትህ አማካሪ ጉባኤ ተቋቁሟል፡፡ የህግና ፍትህ አማካሪ ጉባኤ ሲባል ምን ማለት ነው? ለምንስ አስፈለገ?
ዶክተር ሙሉጌታ፦ የህግና ፍትህ አማካሪ ጉባዔ መንግስትን የማማከር ስራ የሚሰራ ነው፡፡13 አባላት ያሉት ሲሆን፤ የተመረጡትም በጉዳዩ ዙሪያ ባላቸው የትምህርት ዝግጅት፣ የስራ ልምድ፣ የተለያዩ ትውልዶችንና የስራ መስኮችን ይወክላሉ ተብለው የሚታሰቡ ሰዎች ናቸው፡፡ በርካታ ባለሙያዎች ተመርጠው በመመዘኛዎች መሰረት ተለይተዋል፡፡ የተመረጡት ባለሙያዎች በዘርፉ የምርምር ስራ የሚሰሩ፣ የጥብቅና ሙያ ላይ የተሰማሩ፣ በዳኝነትና በዐቃቤ ህግነት ስራ ያገለገሉ ናቸው፡፡ ወጣቶች፣ በመካከለኛ ዕድሜ ላይ የሚገኙና ረጅም እድሜ ያላቸው እንዲሁም ህግና ፍትህን ከስነ ጾታ አኳይ በመመልከት ሲሰሩ የነበሩ ሰዎች ተካትተውበታል፡፡ በተቻለ መጠንም ለማመጣጠን ተሞክሯል፡፡
የጉባኤው ዋና ተልእኮ የአገሪቱን የህግና ፍትህ ስርዓትን ማሻሻል ነው፡፡ እንዲሁም ሲተገበሩ ከነበሩ የለውጥ ስራዎች በመማር የህግና የፍትህ ስርዓቱ ወደማያቋርጥ የለውጥ አዙሪት ውስጥ እንዲገባ ለማድረግ የሚያስችሉ ምክረ ሃሳቦችን ለመንግስት ማቅረብ ነው፡፡ ጉባኤው ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ እንደመሆኑ ባለሙያዎቹ ጥናታቸውን መሰረት አድርገው ምክራቸውን ለእርሳቸው ያቀርባሉ፡፡
ምክር ከመስጠት ባሻገር መንግስት ምክሩን ተቀብሎ ሲተገብር አተገባበሩን በመገምገም ተከታትለው የማስተካከያ ሃሳቦችና ሙያዊ ድጋፎችን ይሰጣሉ፡፡ የጉባኤ አባላቱ የሚሰሩት ተከፍሏቸው አይደለም፡፡ ‹‹ለአገራችን አስተዋጽኦ እናደርጋለን›› ብለው ፍቃደኝነታቸውን የገለጹ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ሙሉ ጊዜውን መስዋዕት አድርጎ ጉባኤውን የሚያግዝ ጽህፈት ቤት አለ፡፡ ጽህፈት ቤቱ እየተደራጀ ይገኛል፡፡ በጉዳዩ ላይ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ይካተቱበትና ጉባኤው በሚሰጠው ሥራ መሰረት ጥናት ይከናወናል፡፡
አዲስ ዘመን፦ ጉባኤው ለቀጣይ ሊሰራቸው ያቀዳቸው የስራ መርሃ ግብሮች ምን ምን ናቸው?
ዶክተር ሙሉጌታ ፦ የሶስት ዓመታት የስራ መርሃ ግብር አለው፡፡ ጉባኤው ለቀጣይ ሊሰራቸው ያቀዳቸው የስራ መርሃ ግብሮች ስምንት ንኡሶችን ይዟል፡፡ በቀዳሚነት ያስቀመጠው የስራ ዕቅድ ህግ የማመንጨትና የማውጣት ስርዓቱን ማሻሻል ነው፡፡ ወይም የህግ ማመንጨትና ማውጣት ስርዓቱን ለማዘመን የሚያስችሉ የለውጥ ሃሳቦችን ለመንግስት ማቅረብ ነው፡፡_ይህ ስራ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወጣ አዋጅ፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚወጣ ደንብ፣ በተለያዩ የአስተዳደር ተቋማት ባልተማከለ ሁኔታ የሚወጡ መመሪያዎች አሉ፡፡ ህግ፣ አዋጅ ፣ደንብና መመሪያዎች የሚወጡበትን ስርዓት በማጥናት ያለባቸው ችግሮች፣ ህጎቹ ጥራታቸውን ያልጠበቁ የሆኑት ለምንድን ነው? የሚለውን ጥያቄ መርምሮ የማስተካከያ ሃሳብ ያቀርባል፡፡
በሁለተኛነት የተቀመጠው የህግ ማሻሻያ ንዑስ ፕሮግራም ከመጀመሪያው ንዑስ መርሃ ግብር ጋር የሚቀራረብ ነው፡፡ የሚለየው የመጀመሪያው ንዑስ መርሃ ግብር ስርዓቱን የሚያሻሽል ሲሆን፤ ይህ ደግሞ የተመረጡ ህጎችን ወስዶ ያሻሽላል፡፡ በእርግጥ ስርዓቱ ሲሻሻል የህጎቹም ጥራት አብሮ ይሻሻላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ግን ያ ረጅም ጊዜ ይወስዳል ፡፡ እስከዛው ጊዜ የማይሰጣቸው ተብለው የተለዩ ህጎች አሉ፡፡ እነዚህን ህጎች የማሻሻል ሃሳብ ያቀርባል፡፡
ሶስተኛው ንዑስ መርሃ ግብር የዳኝነት ስርዓቱ ማሻሻያ ነው፡፡ በአገራችን የዳኝነት ስርዓት ሲባል ሁለት ተቋማትን ይመለከታል፡፡ በአንድ በኩል ፍርድ ቤቶች ሲሆኑ ሌላው በከፊል የዳኝነት ስልጣን የተሰጣቸው አስተዳደራዊ ተቋማት ናቸው፡፡ እነዚህ ሁለቱ ያሉበትን ሁኔታ አጥንቶ የበለጠ ህዝብን አገልጋይ፣ ውጤታማና ፍትሃዊ ሊሆኑ የሚችሉበትን ሁኔታ መርምሮ ሃሳብ ያቀርባል፡፡
አራተኛው ንዑስ መርሃ ግብር የወንጀል ፍትህ ስርዓቱን የሚመለከተው ነው፡፡ በወንጀል ፍትህ ስርዓት ውስጥ ሶስት ዋና ተቋማት አሉ፡፡ ፖሊስ ኮሚሽኖች፣ ዐቃቤ ህግና ማረሚያ ቤቶች፤ በእነዚህ ተቋማት ጥናት በማካሄድ ያሉባቸውን ችግሮች ለይቶ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችላቸውን የመፍትሄ ሃሳብ ያቀርባል፡፡
የፍትሃብሄር ህግና በአስተዳደር ተቋማት የህግ ማስከበር ስርዓቱን ማስተካከል ሌላው ተግባር ነው፡፡ ለምሳሌ ፍትሃብሄር የሚባለው የግለሰቦች ሙግት፣ ውል፣ ንብረት ሊሆን ይችላል። የሚሟገቱት ግለሰቦች ናቸው፡፡ የሚሟገቱትም ፍርድ ቤት ሄደው ነው፡፡ እዚህ ላይ የመንግስት ሚና ውስን ነው፡፡ የመንግስት ሚና በዋናነት የመረጃ እና የመዝገብ ስርዓትን ማደራጀት ነው፡፡ ለምሳሌ የንብረት፣ የተሽከርካሪ ባለቤትነት፣ የመሬት ባለይዞታ ፣ የውልና ሰነዶች ምዝገባ ስርዓቶች ማጠናከር ነው፡፡ ስርአቶቹ ትስስራቸው የጠበቀ፣ ዋስትናቸው የተረጋገጠ እና ተደራሽ መሆን ይገባቸዋል፡፡ ንብረት መመዝገቡ ብቻ ሳይሆን አንድ ዜጋ ውል መፈጸም ቢፈልግ እና መረጃ ቢያስፈልገው የመረጃ ስርዓቱ ተደራሽ መሆን ይኖርበታል፡፡ በዚህ ዙሪያ ችግሮችን የማስተካከል ስራ ነው የሚሰራው፡፡
ህጎች የሚከበሩት በአብዛኛው በፖሊስ ሳይሆን በአስተዳደር ተቋማት ነው፡፡ ለምሳሌ የአካባቢ ጥበቃ ህጎች የሚጠበቁት በአስተዳደር ተቋማት ሲሆን፤ የአካባቢ፣ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር በየአካባቢዎቹ እየሄደ የሚያደርገው የቁጥጥር ስራ አለ፡፡ የኢትዮጵያ የምግብ የመድኃኒትና የጤና አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን የሚያደርገው የቁጥጥር ስርዓትም አለ፡፡ ብዙ የአስተዳደር ተቋማት በሚያደርጉት የቁጥጥርና የክትትል ስርአት ነው ህጎቹ የሚከበሩት፡፡ ነገር ግን ይህ የክትትል ስርዓት እየተከናወነ ያለው ባልተማከለ መንገድ ነው፡፡ ይህንን ሁኔታ አጥንቶ የመፍትሄ ሃሳብ ማቅረብ _አምስተኛው ንዑስ መርሃ ግብር ሆኖ ተቀምጧል፡፡
ስድስተኛው የዴሞክራሲ ተቋማትን ይመለከታል፡፡ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንን ማለት ነው፡፡ በሰባተኛነት የተቀመጠው ንዑስ መርሃ ግብር ደግሞ የህግና ተያያዥ አገልግሎቶች የሚባሉት ናቸው፡፡ አቅም ለሌላቸው ሰዎች የሚሰጥ ነጻ የህግ አገልግሎት ሲሆን፤ በእነዚህ ውስጥ ነጻ ምክር፣ ነጻ ጥብቅና እና የመሳሰሉትን ይመለከታል፡፡ ጠበቆች የፍትህ ስርዓቱ አንድ አካል በመሆናቸው የፍትህ ስርዓቱን ማሻሻል የሚቻለው የእነርሱን ሁኔታ በማሻሻል እንደመሆኑ ጠበቆችንም ይመለከታል፡፡ በመጨረሻም የህግና ስልጠና ተያያዥ ትምህርት ይታያል፡፡ ፖሊሶችና የማረሚያ ቤት ባለሙያዎች እንዴት እንደሚሰለጥኑ ይመረምራል፡፡ በጥቅሉ ሁሉን አቀፍ መርሃ ግብር አቅፏል፡፡
እንዲህ ሆኖ የተቀረጸው ከዚህ በፊት ከነበሩ የለውጥ ስራዎች ትምህርት በመውሰድ ነው፡፡ የፍትህና የህግ ስርዓቱ እርስ በእርሱ የተቆራኘ፣ በብዙ ተዋንያን እና በብዙ ግንኙነቶች የተዋቀረ ነው፡፡ ፍርድ ቤቶች፣ ማረሚያ ቤት፣ ፖሊስ፣ ዐቃቤ ህግ፣ጠበቆች፣ ህግ አውጪው፣ ህግ አስፈጻሚው አካል አለ፡፡ እነዚህ ሁሉ የፍትህና የህግ ስርዓቱ አካል ናቸው፡፡ በመሆኑም አንዱን ነጥሎ በመሄድ ችግሩን መፍታት አይቻልም፡፡ እርስ በእርሱ ተመጋጋቢ በመሆኑ ሁሉን አቀፍ እይታና ምልከታ ሊኖር ይገባል፡፡ በመቀጠል በቅደም ተከተል ስርዓት በማስያዝ መፍትሄ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም አማካሪ ጉባኤው ከላይ የተዘረዘሩትን ስምንት ንዑስ ፕሮግራሞች በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት ውስጥ ተግባራዊ ያደርጋል፡፡
አዲስ ዘመን፤ የሚሻሻሉት የትኞቹ ህጎች ናቸው? እንዴትስ ተመረጡ ? ስራዎቹን ለማጠናቀቅ ሶስት ዓመት አልበዛም ?
ዶክተር ሙሉጌታ፤ እስካሁን አራት የሚደርሱ ህጎች ተለይተዋል፡፡እነዚህም የፀረ ሽብር ፣ የመገናኛ ብዙሃን እና የመረጃ ነፃነት እንዲሁም የበጎ አድራጎት ማህበራት አዋጆችና ጠበቆችን የሚመለከተው የህግ ማእቀፍ ናቸው፡፡ እነዚህን በአጭር ጊዜ ለማሻሻል እቅድ አለ፡፡ ወደፊትም በምክክር መድረኮች፣ በጥናቶች የሚለዩ ጊዜ የማይሰጣቸው ተብለው የተለዮ ህጎች አሉ፡፡ እነርሱንም ወደ ማሻሻሻል ሊገባ ይችላል፡፡ ይህ ማለት ሁሉም ስራዎች ለማለቅ ሶስት ዓመታት ይፈጅባቸዋል ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ በሁለተኛነት የተጠቀሰው የህግ ማሻሻያ ንዑስ መርሃ ግብር የተመረጡ ጊዜ የማይሰጣቸው የህግ ማሻሻል ስራዎች ከሶስት እስከ ስድስት ወራት ማጠናቀቅ አለብን፡፡
አዲስ ዘመን ፦ የሰንደቅ ዓላማ ጥያቄና የጠቅላይ ሚኒስትር የስልጣን ጊዜ ገደብን በሚመለከት የህገ መንግስት ማሻሻልን አይጠይቅም? የህገ መንግስት ማሻሻያ በሌለበት አንዳንድ አከራካሪ ህጎችን ለመለወጥ የሚደረገው ጥረትስ ምን ያህል ለውጥ ያመጣል?
ዶክተር ሙሉጌታ፦ በስምንቱ ንዑስ መርሃ ግብሮች ውስጥ ህገ መንግስት ማሻሻል የሚል የለም፡፡ ዋናው ስራው የህግና ፍትህ ስርዓት አቤቱታ የሚነሳባቸውን ህጎችና የህግ አወጣጥ ስርዓቱን ማሻሻል ነው፡፡ ከህገ መንግስቱ ወረድ ያሉ ህጎችና ተቋማትን ማሻሻልና የማጠናከር ስራ ይሆናል፡፡ ጉባኤው በቀጥታ ህገ መንግስትን የማሻሻል ስልጣን አልተሰጠውም፡፡ ግን ህገ መንግስቱም የኢትዮጵያ የፍትህ ስርዓት አንድ አካል በመሆኑ ጉባኤው ስራውን በደንብ ሲጀምር፣ ከህዝብ ጋር እየተወያየ፣ ጥናቶችን እየሰበሰበ የሚያየው ነው የሚሆነው፡፡ እስካሁን በተለያዩ ሁኔታዎች በተደረጉ ጥናቶች በዋና ችግርነት ህገ መንግስቱ አልተነሳም፡፡ በዋናነት የተነሱ ጥናቶች ህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጡ መብቶችን ለመተግበር የሚያስችል ተቋማዊ አሰራር አለመኖር ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ስራ ለመስራት ህገ መንግስቱን ማሻሻል አያስፈልግም፡፡
በእርግጥ ህጎቹ የሚወጡት ህገ መንግስቱን መሰረት አድርገው ነው፡፡ ህግ የሚወጣው ህገ መንግስቱ ውስጥ የተቀመጡ መርሆዎች፣ መብቶችንና ድንጋጌዎችን የበለጠ ለመዘርዘር ተብሎ ነው፡፡ ህግ ማውጣት የሰው ስራ ስለሆነ ስህተቶች ሊፈጸሙ ይችላሉ፡፡ በአፈጻጸምም ችግሮች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም ህጉ ሲቀረጽ ስህተት ተሰርቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ህጉ ሲተገበር በአፈጻጸም ሂደት ችግሮች ታይተው ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ህጎቹ የሚሻሻሉት ከልምድ በመነሳት ነው፡፡
የተመረጡት ህጎች ለምሳሌ የጸረ ሽብር ህጉ ዓላማ፣ ይዘቱ፣ በአፈጻጸም ያጋጠሙ ችግሮች ይታይሉ፡፡ መሻሻል አለበት ወይ? ይህን ጥያቄ ጉባኤው በመጀመሪያ መመለስ አለበት፡፡ በአፈጻጸም ሂደት የተገኙ መረጃዎችን፣ ልምዶችንና ህገ መንግስቱን መሰረት አድርጎ ይህ አዋጅ ሊሻሻል የሚገባው ከሆነ እንዴት መሻሻል እንዳለበት ጥናት አድርጎ ምላሽ ይሰጣል፡፡ የአማካሪ ጉባኤው አባላት ገለልተኛ ሆነው እንዲሰሩ ነው የሚፈለገው፡፡ ሙያቸውንና ህገ መንግስቱን መሰረት አድርገው እንዲተገብሩ ይጠበቃል፡፡ ስለዚህ ህገ መንግስቱ መመሪያቸው ነው የሚሆነው፡፡ ህገ መንግስቱ ውስጥ የህግ የበላይነት የሚል መርህ አለ፡፡ የህግ የበላይነት መርህ የዚህ ስራ መመሪያ ነው፡፡ ስለዴሞክራሲ ስርዓት፣ ስለህዝብ ተሳትፎ፣ ስለሰብአዊ መብት፣ ፍትህ ስለማግኘት፣ ስለእኩልነት መብት ያወራል፤ እነዚህ ነገሮች ለዚህ ስራ መሰረት ናቸው እንጂ እነርሱን ለማሻሻል አልታሰበም፡፡
አዲስ ዘመን፦ አሁን እንደሚሉኝ ከሆነ እንዲሻሻሉ የተለዩ ህጎችን ለመቀየር ይጠናል እንጂ ውሳኔ ላይ አልተደረሰም፡፡ ታዲያ ይሻሻላሉ የተባሉት እንዴት ተመረጡ?
ዶክተር ሙሉጌታ፦ ጥሩ ጥያቄ ነው። ውሳኔ የሚወሰነው ጥናትን መሰረት አድርገው ነው፡፡ ህጎቹ የተመረጡበት ምክንያት በተደጋጋሚ በተለያዩ የውይይት መድረኮች እና በተሰሩ ጥናቶች ችግር እንዳለባቸውና መቀየር እንደሚገባቸው ስለሚነሳ ነው፡፡ አንዳንዴ ከአፈጻጸም ጋር ተያይዞ፣ አንዳንዴ ህጎቹ ለአስፈጻሚው አካል ሰፊ ወይም ያልተገደበ ስልጣን የሚሰጡ መሆናቸው ይጠቀሳል፡፡ ይህ ሁኔታ ‹‹ለብልሹ አሰራር ያጋልጣቸዋል›› የሚል አቤቱታም ይቀርባል፡፡
በሌላ መልኩ ደግሞ ከአላማውና ከይዘቱ ጋር ተያይዞ አቤቱታ ይቀርባል፡፡ አቤቱታ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ አካላት የተሰሩ የተለያዩ ጥናቶችም አሉ፡፡ ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ መድረኮች በእነዚህ ህጎች በተለይም የፀረ ሽብር አዋጅ፣ የመገናኛ ብዙሃን እና የመረጃ ነፃነት አዋጅ እንዲሁም የበጎ አድራጎት ማህበራት አዋጆች በተደጋጋሚ ትወቀስበታለች፡፡ ህጎቹ ከወጡ የተወሰኑ ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ በመሆኑም መሻሻል አለባቸው ወይ? መሻሻል ካለባቸው እንዴት ይሻሻሉ? የሚለው ባለሙያዎችንና ህዝብን በማሳተፍ ጥናት በማካሄድ ይወሰናል፡፡
እዚህ ላይ ሶስት የአሳታፊ ስርዓቶችን እንከተላለን፡፡ ለምሳሌ የመገናኛ ብዙሃን እና የመረጃ ነፃነት አዋጅን አስመልክቶ ጥናት ይካሄዳል፡፡ ለጥናቱ ግብዓት የሚሆኑ መረጃዎች የሚሰበሰቡት ከባለድርሻ አካላት ነው፡፡ ህጉን ከሚያስፈጽሙ፣ በህጉ ከሚገዙ ከሚዲያና ከአስፈጻሚ አካላት መረጃ ይሰበሰባል፡፡ በቃለ መጠይቅ፣ እስካሁን ባለድርሻዎቹ የሰሯቸውን ጥናቶች በግብአትነት በመጠቀምና የተለያዩ የምክክር መድረኮችን በማካሄድ ሊሆን ይችላል፡፡
ሁለተኛው የተሳትፎ መንገድ ባለሙያዎቹ ረቂቁን ሲያዘጋጁ በጉባኤው ድረ ገጽ ላይ የሚለቀቅ በመሆኑ ማንኛውም ዜጋ አስተያየት እንዲሰጥበት ይደረጋል፡፡ ከባለድርሻዎች ጋር የሚዘጋጀው የምክክር መድረኮች ሶስተኛው የአሳታፊነት መንገዱ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ፦ በፍትህ ማሻሻያ መርሃ ግብር ትግበራ ብዙ ስራዎች እንደተሰሩ ይታወቃል፡፡ በትግበራው ምን ውጤት ተገኝቶ ነው አሁን ወደ ሌላ አሰራር እንዲገባ ያስገደደው?
ዶክተር ሙሉጌታ፦ ህገ መንግስቱ ከወጣ ጀምሮ በፍትህ ስርዓቱ ህጎችን ከማጣጣም ጀምሮ ብዙ የማሻሻያ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ ህገ መንግስቱ አንድም የፌዴራል የአገር አወቃቀርን አምጥቷል፡፡ ከዚህ በፊት የነበረውን አሀዳዊ የአገር አወቃቀር ጋር ማጣጣም ይገባል፡፡ ፍርድ ቤቶችንም በዚህ መንገድ ማደራጀት፣ ህጎችን ማሻሻል ለምሳሌ የወንጀለኛ መቅጫ ህጉን፣ የቤተሰብ አዋጅ፣ የፍርድ ቤት አዋጅን የማሻሻል ስራዎች ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው አንድ የህግ ትምህርት ቤት ብቻ ነበር፡፡ የህግ ትምህርት ቤቶች መስፋፋትም አንዱ የለውጥ አካል ነው፡፡ ይህ የህግ ማሻሻያ አካል ነው፡፡
በአንድ ወቅት የአቅም ግንባታ ሚኒስቴር በነበረበት ጊዜ ሁሉን አቀፍ የፍትህ ስርዓት ማሻሻያ መርሃ ግብር ተነድፎ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ የአቅም ግንባታ ሚኒስቴር ሲፈርስ ወደሚመለከታቸው አካላት ተዘዋውሯል፡፡ ወደ ፍርድ ቤት፣ ፐብሊክ ሰርቪስ ሚኒስቴር፣ በቀድሞው አጠራር ፍትህ ሚኒስቴር ተዘዋውረው ሲሰሩ የነበሩ ናቸው፡፡ በፍርድ ቤቶች ቢ ፒ አር፣ ቢ ኤስ ሲ የለውጥ ስራዎች ሲተገበሩ ነበር፡፡ የዳኞችና የችሎቶች ቁጥር መብዛት፣ የዳኞችና የዐቃቤ ህግ ስልጠና ማዕከል መቋቋም ሌላው የተሰሩ የለውጥ ስራዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ ለውጦች ተደርገውም አሁንም ህዝቡ በተለያዩ መድረኮች ስለ ፍትህ ስርዓቱ ያማርራል፡፡ ስለአገልግሎት ጥራቱ መጓደልና ስለብልሹ አሰራሩ ይነሳል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሁሉ የለውጥ ስራዎች እየተሰሩ ችግሩ ያልተቀረፈበት ሁኔታ ጥያቄ ይነሳል፡፡
በአንድ በኩል የለውጥ ስራዎቹ ሲቀረጹ በአቀራረጽ የዲዛይን ወይም የንድፍ ችግር ነበረባቸው፡፡ የፍትህ ስርዓቱን ጸባይ ግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም፡፡ የመንግስት የህዝብ አስተዳደር ስራ በሙሉ የህግ አስተዳደር ስራ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ፍርድ ቤቶች፣ ዐቃቤ ህግ፣ ማረሚያ ቤት፣ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ጠበቆች፣ የህግ ትምህርት ቤቶችና የህግ ምርምር የሚሰሩ፣ ህግ አውጪ ከአዋጅ እስከ መመሪያ ብዙ አካላቶች አሉበት፡፡ እነዚህ ተነጣጥለው የሚሰሩ አይደሉም፡፡ በመሆኑም የለውጥ ስራ ሲታቀድ ይህንን ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ ባተገባበርም ሰፊ ችግር አለ፡፡ ያዝ ለቀቅ አሊያም የዘመቻ አይነት ስራ ይታያል፡፡
ዘመቻ ህዝብን ማነቃነቁ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ችግር ሰፊ ነው፡፡ ግን በተወሰነ ጊዜ ተተግብሮ የሚፈጸም አሰራር አለ፡፡ እንደ ቋሚ የመንግስት ስራ አይታይም፡፡ የዘመቻ ስራ በመከተል ለምሳሌ ቢ ፒ አር ተተግብሮ እሱ ተቋማዊ ቅርጽ ሳይይዝ ሌላ አዲስ ነገር ይተገበራል፡፡ ይህንን ትተን አዲሱን አንጠልጥለን የመሮጥ ስራ ሲሰራ ነው የቆየው፡፡ ቢ ፒ አር በአንዳንድ መስሪያ ቤቶች ለውጥ ማምጣቱ በግምገማ ተረጋግጧል፡፡ ይህ የለውጥ ስራ በአንድ ተቋም ለውጥ ስላመጣ ፍርድ ቤት አይተገበርም፡፡ ከየተቋማት ባህሪ ጋር መታየት አለበት፡፡ ፍርድ ቤት ያለው ችግር አንዱ ይህ ነው፡፡ ባለሙያዎቹ ሳያምኑበት ነው ይተገብሩት የነበረው፡፡
አዲስ ዘመን ፦ በፍትህ ስርዓቱ ውስጥ ያለው አመራር ባልተለወጠበት፣ በቀድሞ ቅኝት ውስጥ ያለውን አመራር ይዞ በዘርፉ እንዴት ለውጥ ማምጣት ይቻላል?
ዶክተር ሙሉጌታ ፦ይህ በተለያዩ ንዑስ ዘርፎች ውስጥ የሚዳሰስ ነው የሚሆነው፡፡ ዞሮ ዞሮ አማካሪ ጉባኤው በሚያደርገው ጥናትና ግምገማ ላይ ተመስርቶ በሚያቀርበው ውሳኔ ላይ የሚመሰረት ይሆናል፡፡ ይህንን አስቀድሞ መተንበይ አይቻልም፡፡ የሚያቀርባቸው ምክረ ሃሳቦች ተቋማዊ መሆን አለባቸው፡፡ ጉባኤው የሚያመነጫቸው የለውጥ ሃሳቦች ተቋማዊ፣ ስር የሰደደና የማይቀለበስ መሆን ይኖርበታል፡፡ ያዝ ለቀቅ አሰራር መቀየር አለባቸው፡፡ ግለሰብ ወይም አንድ አመራር ወሳኝ ነው፡፡ ግን አንድ አመራር ብቻውን አይወስንም፡፡ ተቋማዊ አሰራሩ ነው የሚወስነው፡፡ ስራው በአንድ ሰው ላይ የሚንጠለጠል መሆን የለበትም፡፡ ተቋማዊ አሰራሩ የሚገለጸው በህግ በመሆኑ ዝርዝር ሆኖ አመራሩንም ሰራተኛውንም የሚመራ የህግ ማዕቀፍ ሊኖር ይገባል፡፡ በእኔ እምነት አመራር ስለተለወጠ ሳይሆን ዋናው ነገር ተቋማዊ አሰራሩን ማጠናከር ላይ ማተኮር ነው የሚገባው፡፡
አዲስ ዘመን ፦ከህግና ፍትህ አማካሪ ጉባኤው ምን ውጤት ይጠበቃል ?
ዶክተር ሙሉጌታ ፦ በአጠቃላይ በህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጡ መርሆዎች መሰረት ያደረገ የህግና የፍትህ ስርዓት እየገነባን እንድንሄድ የሚያደርግ ስራ መስራት ይጠበቃል፡፡ የተጠናከረ የህግ የበላይነት፣ የዜጎች ፍትህ የማግኘት መብት በተግባር መዋል አለበት፡፡ ህገ መንግስቱን ያከበረ፣ የሕዝብ አገልጋይ፣ ሰብአዊ መብትን ያከበረ፣ ፈጣን፣ ውጤታማ፣ ፍትሃዊና አዋጭ የፍትህና የህግ ስርዓት ማውጣት አስፈላጊ ነው፡፡
የሚወጡ ህጎች ጥራታቸውን የጠበቁ፣ግልጽና ዝርዝር እንዲሆኑ ለማስቻል ይሰራል፡፡ ለአስፈጻሚው አካል የሚሰጡት ፈቃደ ስልጣን ምክንያታዊ የሆነ፤ ለፈቃደ ስልጣን የቁጥጥር ስርዓት የተዘረጋለት፤ ውጤታቸው በየወቅቱ እየተገመገመ የሚፈተሽበት ስርዓት የተዘረጋበት መሆን አለበት፡፡ ስርዓቱ ራሱን እያሻሻለ የህጎች ጥራት የሚሄድበት ስርዓት መፍጠር ይጠበቃል፡፡ ዜጎች በፍርድ ቤቶች በአጭር ጊዜ ጉዳያቸውን የሚጨርሱበት፣ ዳኝነት የሚጠናከርበት ስርዓት፣ ተጠያቂነት፣ ተደራሽነት፣ ግልጽነት የሚባሉት የህገ መንግስት መርሆዎች የሚከበሩበት እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ጠቅለል ባለ መልኩ የሚፈለገው ለማስቀመጥ የህግና ፍትህ ስርዓቱ የህዝብ አገልጋይ፣ በህዝብ የታመነ፣ ውጤታማና እየተጠናከረ የሚሄድ የህግና ፍትህ ስርዓት መዘርጋት ነው፡፡
አዲስ ዘመን ፦ ስለነበረን ቆይታ ከልብ አመሰግናለሁ!
ዶክተር ሙሉጌታ ፦ እኔም አመሰግናለሁ!

ዘላለም ግዛው

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።