የከተሞች ፕላንና የመሬት አጠቃቀም እንደ መልካም አስተዳደር ችግር Featured

09 Jul 2018

የሰው ልጅ ኑሮውን እያሻሻለና እየለወጠ በሄደ ቁጥር የተሻለ ኑሮ ወደሚያገኝበት ስፍራ ማቅናቱ አይቀሬ ነው፡፡ ከእነዚህ መዳረሻዎች መካከል ደግሞ ከተሞች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያም ተጨባጭ ሁኔታ ከተሜነት በፍጥነት እያደገ፣ የህዝብ ቁጥሩም እየጨመረ ስለመሆኑ ይነገራል፡፡ ይሁን እንጂ ከተሞች ከመስፋፋት ባለፈ በሚፈለገው መጠን አለማደጋቸው፤ የህዝብ ቁጥራቸው ከመጨመር በዘለለ ለነዋሪዎቻቸው ምቹ ባለመሆናቸው የሚፈልገውን የከተሜነት ኑሮ ለማግኘት አለመቻላቸው በስፋት ሲነገር ይደመጣል፡፡
በዚህ መልኩ ከተሞች ላለማደጋቸውም ሆነ ለነዋሪዎቻቸው ምቹ ላለመሆናቸው ከሚነሱ ምክንያቶች መካከል ደግሞ የከተሞች በፕላን አለመመራት እና የከተሞች የመሬት አጠቃቀም ችግር ስለመሆናቸው የዘርፉ ባለድርሻዎች ይናገራሉ፡፡ የከተሞች ፕላንና የመሬት አጠቃቀምን በተመለከተ ሰሞኑን በጅማ ከተማ በተካሄደው የመጀመሪያው የኦሮሚያ ከተሞች ፎረም ላይ በጥናት የታገዘ ውይይት የተደረገ ሲሆን፤ በወቅቱም ከተሞች ከመስፋትና የነዋሪዎቻቸው ቁጥር ከመጨመሩ ባለፈ በሚፈለገው ልክ ያላደጉና ለነዋሪዎቻቸውም ምቹ ያልሆኑ መሆናቸው ተነስቷል፡፡
በዚህም በተለይ ከተሞች በፕላን አለመመራ ታቸውና ተገቢውን የመሬት አጠቃቀም ሥርዓት ባለመተግበራቸው ለነዋሪዎች ምቹ አለመሆናቸው ብቻ ሳይሆን ለመልካም አስተዳደር ችግር መንስኤ መሆናቸው ተወስቷል፡፡ እኛም በዛሬው እትማችን የከተሞች ፕላንና የመሬት አጠቃቀም በከተሞች ያለውን ገጽታ፣ እያሳደረ ያለውን ተጽዕኖና ቀጣይ አቅጣጫዎችን በተመለከተ በውይይት መድረኩ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡ ሁለት የዘርፉ ባለሙያዎችን ሃሳብ ይዘን ቀርበናል፡፡
የመሬት አጠቃቀምና ፕላን በከተሞች
አቶ ብርሃኑ ታደሰ፣ በኦሮሚያ የከተሞች ፕላን ኢንስቲትዩት የፕላን ባለሙያ ናቸው፡፡ በውይይት መድረኩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞችን መነሻ በማድረግ በከተሞች በሚስተዋለው የፕላን አተገባበር ዙሪያ የውይይት ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፣ ስለከተሞች ፕላን ለማንሳት መጀመሪያ ስለ ከተሜነት ማንሳት ይገባል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ከተሜነት በዓለም ላይ በተለይም ባደጉት አገራት የእድገት ደረጃው ከ77 በመቶ በላይ ሆኗል፡፡ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን ከተማ ውስጥ የሚኖረው ከ20 በመቶ በታች ሲሆን፤ አሁን ባለው እድገትና አገሪቱ በያዘችው ስትራቴጂክ ትራንስፎር ሜሽን መሰረት ደግሞ 5 ነጥብ 4 በመቶ በላይ እያደገ ይገኛል፡፡ ይህን የእድገት ምጣኔና ከተማ ውስጥ ያለውን ህብረተሰብ ደግሞ በከተማ ፕላን ተመርቶ እንዲሰፋ ማድረግ ካልተቻለ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ፕላን የሌለውና በዚሁ ልክ ለትውልድ የሚተላለፍ ከተማ ይፈጠራል፡፡ ይህ ደግሞ የከተማ ፕላን ለከተሞች እድገት ወሳኝ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡
አቶ ቃሲም ፊጤ፣ ላለፉት አስር ዓመታት በከተማ መሬት ላይ በኦሮሚያ ክልል እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የሰሩ ሲሆን፤ በአሁኑ ሰዓት የፌዴራል ቅርስ ጥናትና ጥበቃ በለስልጣን ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ በመድረኩም የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ላይ ትኩረት በማድረግ በከተሞች በሚስተዋል የመሬት አጠቃቀም ችግር ዙሪያ ለውይይት መነሻ የሚሆን ጥናት አቅርበዋል፡፡ አቶ ቃሲም እንደሚናገሩት፤ ኢትዮጵያ በከተሞች ልማት ዘርፍ በከተሞች የሚኖረው የህዝብ ቁጥር በገጠር ከሚኖረው አንጻር ሲታይ ዝቅተኛ ከሚባሉትና ወደመጨረሻ ካሉት አገራት አንዷ ናት፡፡ በዛው ልክ ደግሞ ከተሞች እየሰፉ ያሉበት ፍጥነት ከየትኛውም አገር የበለጠና የፈጠነ ያለ ነው፡፡ ሆኖም ከግሎባላይዜሽን አኳያም እንደ አገርም ሆነ በከተሞች ደረጃ ያሉ የአገልግሎት አሰጣጦች፣ ወደ ኢንዱስትሪ ያላይዜሽን የሚደረጉ ፉክክሮች ኢንቨስትመንትን ለመሳብ መሬት ወሳኝ ነው፡፡ ለልማትም ትልቁ ግብዓት ነው፡፡
በመሆኑም የከተሞች መሬት ከብክነትና ብክለት የነጻ መሆን አለበት፤ በቁጠባ መጠቀምም ይገባል፡፡ ይሄን የመሬት ሀብት በማስተዳደር ሂደትም አሁን ዓለም ከደረሰበት ቴክኖሎጂ መድረስ እንኳን ባይቻል፤ ቶሎ ብሎ አሁን በከተሞች እየታዩ ያሉትን ህገ ወጥ ሰፈራዎችን መግታትና አቅርቦቱን የማሻሻል ስራዎች መሰራት አለባቸው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ከዚህ በፊት የተከማቹ ችግሮች ያሉበትና በዛው ልክ ትኩረትም ስላልተሰጠው የመሬት ዘርፍ ችግሮች ማጽዳትና በዛው ልክ ራስንም ማዘጋጀት ይጠይቃል፡፡
ይሄን ለማድረግ ደግሞ ከተሞች አቅም መፍጠር አለባቸው፡፡ ለዚህም አንደኛ ከአመራር ጀምሮ የሰው ኃይላቸው ስለ ከተማ የተወሰነ እውቀት ሊኖራቸው፤ ከሁኔታዎች ጋር ራስን እያበቁ መሄድንም ይጠይቃል፤ ለዚህ የሚሆን የሰው ኃይልም እያፈሩ መሄድ ይገባል፡፡ ህብረተሰቡንም ሆነ የግል ባለሀብቱን በዘርፉ የሚሳተፉበትን ሁኔታዎች ማመቻቸት አስፈላጊ ነው፡፡ ከላይ ያሉ የፖሊሲ አውጪዎችም ጉዳዩን በተለይ ከፖሊሲ አንጻር ማነቆ የሆኑ ጉዳዮችን ተከታትሎ ከጊዜው ጋር እያጣጣሙ፤ ሕጎችንም እያሻሻሉና ተደማሪ ድጋፍ እያደረጉ መሄድን ይሻል፡፡ በዚህ መልኩ በክልልም ሆነ በፌዴራል ያሉ አካሎች ትኩረት ሊሰጡት ይገባል፡፡
የመሬት አጠቃቀምና ፕላን ወቅታዊ ይዞታ
“እንደ አገርም ሆነ እንደ ኦሮሚያ ክልል ከተሞቻችን መጀመሪያውኑ አፈጣጠራቸው በተለያዩ ምክንያቶች እንደመሆኑ በፕላን ላይ የተመሰረቱ አይደሉም” የሚሉት አቶ ብርሃኑ፤ በዋናነትም የጦር ቀጣና መሆናቸው ወይም ለዚሁ ተግባር ስትራቴጂክ ቦታነታቸው ታይቶ የተፈጠሩ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ይህ ደግሞ የመሬት አቀማመጣቸው ወጣገባ የበዛበት እንዲሆን በማድረጉ አሁን ላይ ለመስፋፋት አስቸጋሪ ሁኔታን መፍጠሩን በመጠቆምም፤ የከተሞች ምስረታ አመጣጥ በፕላን ባለመሆኑ አሁን ባለው ሁኔታ በፕላን ቢሰራ የሚሞቱ ከተሞች መኖራቸውን ይገልጻሉ፡፡ ከዚህ ባለፈም ቀድሞ ገጠር የነበሩ፣ አሁን በተፈጠረው የገበያ ሁኔታ ያረጁ ከተሞችን በልጠው ራሳቸውን ወደከተማነት ያመጡና እያመጡ ያሉም ከተሞች የሚስተዋሉ መሆናቸውን ያብራራሉ፡፡
እንደ አቶ ብርሃኑ ገለጻ፤ ወደ ከተሜነት የሚለወጡትን እነዚህ አዳዲስና ትንንሽ ከተሞች በከተማ ፕላን መያዝ ወሳኝ ነው፡፡ ሆኖም ከተሞች እየተስፋፉ ቢመጡም የከተማ ፕላናቸውን እየተገበሩ አይደለም፡፡ በዚህም የከተማ ፕላን አፈጻጸም ችግር ውስጥ ነው ያለው፡፡ ለዚህ ደግሞ ብዙ ምክንያትና ፈታኝ ሁኔታዎች አሉ፡፡ አንደኛውና ዋነኛው፣ ፕላኑ ራሱ ሲዘጋጅ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ከማድረግ አኳያ ጉድለት መኖሩ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የካርታ ፕላን ስራ በአገሪቱ የቅርብ ጊዜ ስራ የመሆኑ ውጤት ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ፕላን ሲሰራ በአግባቡ ዳታ የመሰብሰብ ችግር አለ፡፡ ምክንያቱም የከተሞች ፕላን ስራ የማዳረስ ወይም የቁጥር ስራ ተደርጎ እንጂ በተገቢው መረጃ ላይ ተመስርቶና ለጥራት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ አይደለም፡፡ ከእነዚህ በላይ አስቸጋሪ የሚያደርገው ደግሞ በተለይ ፕላንን ከማስፈጸም አኳያ ሲሆን፤ ይሄን ከማስፈጸም ጋር በተያያዘ የሚፈጽመው ባለሙያም ሆነ የሚያስፈጽ መው ኃላፊ ሙያው በሚፈቅደው መሰረት ስለማያስ ፈጽሙና ስለማያስተዳድሩ ነው፡፡ በዚህም አሁን ላይ ከተሞች በፕላን ይመራሉ፤ ፕላኖቻቸውም በአግባቡ ይፈጸማሉ ለማለት አይቻልም፡፡
አቶ ቃሲም በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ አሁን ባለው ሁኔታ በከተሞች ያለው የመሬት አጠቃቀም ጤናማ ተብሎ ሊወሰድ አይችልም፡፡ ምክንያቱም አንደኛ፣ በመደበኛነት ይሄንን ፍላጎት ለማሟላት ከተሞች ያላቸው አቅም (የገንዘብም ሆነ የሰው ኃይል) በጣም አነስተኛ ነው፡፡ በአንጻሩ ፍላጎቱ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ሁለተኛም በከተሞች ዙሪያ ያሉ አርሶ አደሮች በመሬታቸው መብት ያላቸው ቢሆንም፤ መሬቱ ለልማት ሲወሰድባቸው የሚያገኙት የካሳ መጠን በጣም አነስተኛ ነው፡፡ እነዚህ አርሶ አደሮች ቀደም ሲል በግብርና ስራ ሲተዳደሩ የኖሩ እንደመሆናቸውም ወደ ከተማነት ሲጠቃለሉም አዲስ ሕይወት ነው የሚጠብቃቸው፡፡ በመሆኑም በህዝቡ በተለይም በአርሶ አደሩ አካባቢ ቀድሞ መፍራት ስላለ የከተሜነት ሽታ በመጣ ጊዜ አርሶ አደሩ ቶሎ ኢመደበኛ በሆነ መልኩ ወይም በህገ ወጥ መንገድ መሬቱን ያስተላልፋል፡፡
በዚህም ከተማው መሬቱጋ ሳይደርስ ጭምር ተወርሮ የሚጠብቅበት ሂደት አለ፡፡ ይህ ደግሞ አንደኛ፣ ቀድሞ የተያዙት ቦታዎች መሰረተ ልማት የተሟላላቸውና በፕላንም የተመሩ አይደሉም፤ ስለዚህ ለከተሜነት ሊውል የማይገባው መሬት ሁሉ ለከተሜነት እየዋለና ለእርሻ ትልቅ አቅም ያላቸው ቦታዎች ጭምር ወደከተማነት እየተቀየሩ ነው፡፡ በመሆኑም ይሄን ሀብት መልሶ ማግኘት በማይቻልበት አግባብ ሁሉ እየታጣ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ ሁለተኛም፣ የከተሞች መስፋፋት ፕላንን ያልተከተለና የጎንዮሽ መስፋፋት እየፈጠረ ስለሆነ ይሄ በቀጣይ በከተሞች ላይ ትልቅ የወጪ ውጤት አለው፡፡ ምክንያቱም አሁን እየተስፋፋ ላለው ከተማ እንደ መንገድ፣ ውሃ፣ መብራትና የመሳሰሉ መሰረተ ልማቶችን ማቅረብ ይጠይቃል፡፡ ይህ ደግሞ ትልቅ ወጪ ነው የሚጠይቀው፡፡ አንድ ከተማ ወደ ጎን በተለጠጠ ቁጥር ለዛ የሚያስፈልገውን መሰረተ ልማት ለማቅረብ የሚፈልገው ወጪ በዛው ልክ ነው የሚጨምረው፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ ከተሞች ከመሬት ማግኘት ያለባቸውን ገንዘብ እያመነጩና እያገኙ አይደለም፡፡
ለከተሞች እድገትና መልካም አስተዳደር መስፈን እንደ ማነቆ
አቶ ብርሃኑ፣ የከተሞች በፕላን አለመመራት ለከተሞች እድገት ትልቅ እንቅፋት ከመሆኑ ባለፈ ለነዋሪዎቻቸው የመልካም አስተዳደር ምንጭ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ አንድ ከተማ ሲመሰረት የራሱ የሆነ ፕሮፋይል ያለው እንደመሆኑ የሚተዳደረውም በዚሁ የከተማው ፕሮፋይል መሰረት ነው፡፡ ከዚህ ፕሮፋይል ደግሞ ፕላን ይሰራል፡፡ ስለዚህ እዛ ላይ የተወከለ ኃላፊ ወይም ባለሙያም ከተማን ሳይሆን ፕላንን ነው የሚያስተዳድረው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ፕላኑን ወደጎን በመተው ከተማውን ለማስተዳደር (ከጸጥታ ስራ ጀምሮ ሌሎች በከተሞች ውስጥ ወደሚከናወኑ ተግባራት) ይኬዳል፡፡
በዚህ መልኩ የፕላን ትግበራን ወደጎን ትቶ ከተማን የማስተዳደር ስራ አሁን ሕገ ወጥ የመሬት ወረራ እንዲስፋፋ፤ ከተሞችም በደላላ እንዲተዳደሩ ያደርጋል፡፡ ለአብነት በኢስቲትዩቱ የተሰራ ፕላን በከተሞች ከንቲባ እጅ አይደም፤ ይሄን ስራ በሚሰሩ በደላሎች እጅ ነው ያለው፡፡ ይህ ደግሞ የከተሞች ፕላን ባለቤት ማጣቱን አመላካች ሲሆን፤ በዚህም በከተማ ደረጃም ባለቤት እንደሌለውና የኦሮሚያ የከተሞች ፕላን ኢንስቲትዩትም የተሰጠው ኃላፊነት በጣም ውስን መሆኑን አመላካች ነው፡፡ ምክንያቱም በክልሉ ከ640 በላይ ከተሞች አሉ፤ በአንጻሩ ኢንስቲትዩቱ አንድ ዋና መስሪያ ቤትና አራት ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶች ነው ያሉት፡፡ ይህ ደግሞ ኢንስቲትዩቱ ፕላኑን ለማዘጋጀት፣ ለማስፈጸምና ለመከታተል በቂ የሰው ኃይል እንዳይኖረው አድርጎታል፡፡ ነገር ግን ሲቋቋም መንግስት ትኩረት ሰጥቶታል፣ ከተሞች ሰዎች የሚኖሩባቸው እንደመሆናቸው፡፡
እንደ አቶ ብርሃኑ ገለጻ፤ ከተማ ሲፈጠር ንጉስ የሚኖርበት፣ ህግ የሚወጣበትና የሚወሰንበት እንደመሆኑ፤ የኢንዱስትሪ ማዕከል እንዲሆንና የአገሪቱንም ኢኮኖሚ እንዲደግፍ ተብሎ ነው ፕላን የሚወጣለት፡፡ ሆኖም ይህ እየተደረገ ባለመሆኑ ከተሞቹ በሚፈለገው ልክ እንዳያድጉ፣ ለነዋሪዎ ቻቸውም ምቹ እንዳይሆኑን የመልካም አስተዳደር ማዕከል እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ከቀጠለም ቀጣዩ ትውልድ ዋጋ የሚከፍልበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን አሁን ላለው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የመልካም አስተዳደር ችግር ምንጭ ሆኖም ይቀጥላል፡፡
አቶ ቃሲም በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ በከተሞች ያለው የመሬት አጠቃቀም ችግር በከተሞች እድገት ላይ ተጽዕኖ ፈጥሯል፤ ለነዋሪዎችም ችግር ሆኗል፡፡ ለአብነት፣ በሕገ ወጥ መንገድ የተያዙ መሬቶች ወደ ህጋዊነት ስላልመጡ ቢያንስ ዓመታዊ ግብር እንኳን እየገበሩ አይደለም፡፡ በመሆኑም ከተሞች በዚህ በኩልም ገቢ እያጡ ነው፡፡ ሁለተኛም፣ ወቅቱን የጠበቀና የጊዜውን ገበያ ያማከለ የዋጋ ክለሳም እየተደረገ አይደለም፡፡ ለምሳሌ በኦሮሚያ ከተሞች ዋጋው ሳይከለስ ለብዙ ጊዜ የቆየና ከወቅቱ የመሬት ገበያ ጋር በጣም የተራራቀ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም ከተሞች በአንድ በኩል አቅማቸው እየተመናመነ፣ በሌላ በኩል በህገ ወጥ መንገድ መስፋፋት እየታየ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከተሞችን አቅማቸውንም ጭምር እየተፈታተነና አሉታዊ ተጽዕኖ እያስከተለ ነው፡፡
ይህ ሂደት ደግሞ በእያንዳንዱ ዜጋ ላይ ተጽዕኖ ያለው ሲሆን፤ አንደኛ በህገ ወጥ መንገድ እየተስፋፉ ያሉ ቦታዎች ለኑሮ ምቹ የማይሆኑ ብቻ ሳይሆን በሌሎች አገራት እንደሚታየውም በቀጣይ ለህገ ወጥነት እየተጋለጡ የሚሄዱበት እድል ሰፊ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም ለአካባቢ ብክለት በመጋለጥ ለዜጎች ጤና ጉዳት የሚፈጥር ይሆናል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎችም የከተማውን ነዋሪ ከከተሜነት ሕይወት ተጠቃሚ ሳይሆን ተጎጂ የሚሆንበትን እድል ያሰፉታል፡፡ በመሆኑም ይሄን ችግር ለመቀልበስ መስራት ያስፈልጋል፡፡
እንደ አቶ ቃሲም ገለጻ፤ ከዚህ ባለፈም የከተሞች የመልካም አስተዳደር ጉዳይ የዓለም አጀንዳ ነው፡፡ ምክንያቱም የመልካም አስተዳደር በየመድረኩ ከሚወራው ያለፈ ነው፡፡ የመልካም አስተዳደር በመታጣቱም ነው ወደ ህገ ወጥነቱ እየተሄደም ያለው፡፡ በህጋዊ መንገድ የመጣውን በማስተናገድ ሂደቱም የሚታዩ እጅጉን የተጓተቱ አሰራሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ፣ ነባር ይዞታዎችን ወደ ህጋዊነት በማምጣትና ካርታ የመስጠት ስራ መንግስት ከወሰነ ቆይቷል፡፡ ሆኖም በአብዛኛው እየተስተናገደ አይደለም፡፡ ለዚህ ደግሞ አንዱ ምክንያት የመልካም አስተዳደር ችግር ሲሆን፤ ሌላኛው የሚሰጠው አገልግሎትም ትልቅ ችግር ውስጥ ያለ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ደግሞ አንድም የኪራይ ሰብሳቢነት (ሌብነት)ና ጥቅም ፈላጊነት ጉዳይ በሴክተሩ ትልቅ ማነቆ የመሆኑ ውጤት ሲሆን፤ በችግር ላይ ችግር እየደረበ ያለበት አግባብ ነው ያለው፡፡
የመፍትሄ አቅጣጫዎች
በከተሞች ውጤታማ ፕላን ኖሮ ከተሞች እንዲያድጉና ለነዋሪዎቻቸውም ምቹ እንዲሆኑ ከማድረግ አኳያ በመጀመሪያ ቅንጅት መኖር እንዳለበት አቶ ብርሃኑ ይናገራሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ በከተማም ሆነ በከተማ ፕላን ላይ የሚሰሩ፣ ፕላኑን የሚያቀርበውም ሆነ የሚያስፈ ጽመው አካል በቅንቅት ስራዎችን ማከናወን ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህ ላይ የተመደቡ የመንግስት አካላትም ሆኑ ሌሎች ባለድርሻዎች የሰው ኃይልን ጨምሮ በተለያየ አቅም ግንባታ፣ በመሳሪያ ድጋፍና ሌሎችም የሀብት ድጋፎች ዙሪያ መቀናጀት ከቻሉ ስራውን ማሳለጥ ይቻላል፡፡ ሁለተኛም ፕላኑ የሚሰራው መሬት ላይ ቢሆንም ለህብረተሰቡ ነው የሚሰራው፡፡ በመሆኑም ለፕላኑ ውጤታማነት ህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲይዝ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ህብረተሰቡ በዚህ መልኩ ተረድቶም ባለቤት ሊሆን ይገባል እንጂ፤ ሦስትና አራት ወይም ሃያ ሰው ሰብስቦ ህብረተሰቡ ተሳትፎ አድርጎበታል በማለት የሚሰራው ስራ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡ በመሆኑም ህብረሰተቡ ግንዛቤ ጨብጦና የባለቤትነት ስሜት ፈጥሮ የፕላኑ አስፈጻሚና ጠባቂ እንዲሆን ማድረግ የግድ ይላል፡፡
አቶ ቃሲም በበኩላቸው እንደሚሉት፤ የከተሞች መሬት አጠቃቀም ችግርን ከማቃለል አኳያ ከሚቀመጡ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ማማከር አንዱና ትልቁ የህብረተሰብ ተሳትፎን ማጠናከር ነው፡፡ ሁለተኛም፣ የሰው ሃይሉን ማብቃት ነው፡፡ የሰው ሃይሉን የማብቃት ሂደቱ ከአመለካከት ጀምሮ መስራትን የሚጠይቅ ሲሆን፤ ችግሩ የአንድና የሁለት ሰው ሳይሆን የዜጎችና የአገርም ችግር እንደመሆኑ በትኩረት ሊሰራበት ይገባል፡፡ ለዚህም ከትምህርት ቤቶች ጀምሮ ሰዉ ያለ አግባብ ከመበልጸግ ይልቅ በላቡ ሰርቶ መበልጸግን አጀንዳ አድርጎ በማሰራት ይሄንን የሚጸየፍ ትውልድ መፍጠር መቻል ያስፈልጋል፡፡ አሁን ያለው ትውልድም የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲያመጣ፣ የተሻለ አመለካከት ያላቸውም ለህብረተሰቡ አገልግሎት የሚሰጡትንም እየለዩና እየሸለሙ በዓርዓያነት ሰው እንዲከተላቸው እያደረጉ መሄድም ተገቢ ነው፡፡ ወደ ህገወጥነት የሚሄደውንና ሰውን የሚያጉላላውን ደግሞ እየለዩ ከምክር እስከ ህጋዊ እርምጃ መውሰድም እጅጉን አስፈላጊ ነው፡፡ አሁን የሚታየው የፍረጃና ሁሉንም ወደዛ የመግፋት አካሄድ መታረም የሚገባው ነው፡፡
ሆኖም ችግሩን ከመቀየር አኳያ ዋናው የመረጃ ጉዳይ ሲሆን፤ አሁንም የመረጃ ችግር ከመሰረቱ እስካልተፈታ ድረስ ዋሻነቱ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ለመልካም አስተዳደሩም ሆነ ለአገልግሎት መጓተቱ መንስኤዎቹ እነርሱ በመሆናቸው እዛጋ ትኩረት መሰጠት አለበት፡፡ እነዚህ መረጃዎች ደግሞ ህብረተሰቡ በቀላሉ እንዲያገኛቸው ሁኔታዎች መመቻቸት አለባቸው፤ ህጎችም ግልጽና ተደራሽ መሆን አለባቸው፡፡ ምክንያቱም አሁን ላይ ብዙዎቹ የመሬት ሕጎች አይታወቁም፡፡ በመሆኑም ህብረተሰቡ መብትና ግዴታውን በአግባቡ የሚረዳበትን መንገድ መፍጠር ይገባል፡፡ የመገናኛ ብዙሃንም በዚህ ዙሪያ ሚናቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡ በዘርፉ የተሰማሩ አካላትም በጥቂት ባለሙያዎችና ደላሎች እጅ ያሉ ህጎችን ለህብረተሰቡ በማድረስ ህብረተሰቡ ላልተገባ ወጪ እንዳደረግ ማድረግ ይገባል፡፡

ወንድወሰን ሽመልስ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።