«መንግስት ሲያምጽ ህዝቡ በመንግስት ላይ የማመጽ ተፈጥሯዊ መብት አለው» - ሜጄር ጄኔራል አበበ ተክለሃይማኖት የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ Featured

11 Jul 2018
«መንግስት ሲያምጽ ህዝቡ በመንግስት ላይ የማመጽ ተፈጥሯዊ መብት አለው» - ሜጄር ጄኔራል አበበ ተክለሃይማኖት  የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ፎቶ- በፀሐይ ንጉሤ

ሜጄር ጄኔራል አበበ ተክለሃይማኖት በ1967 ዓ.ም በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ተማሪዎች ጋር በመሆን ጭቆናን መቃወም ጀመሩ። ከመቃወም ያለፈ ግን ስለብሄራዊ ጭቆና ብዙም ግንዛቤ አልነበራቸውም። በወለጋ ክፍለ ሀገር ዕድገት በህብረት በዘመቱበት ወቅት ባላባቶች በጭሰኛው ላይ የሚያደርሱት ግፍ ሁኔታውን በደንብ እንዲረዱ አድርጓቸዋል። ያዩት ግፍና ጭቆና ለትግል አነሳሳቸው።
በወቅቱ የኢሀፓ አባል ቢሆኑም አባላቱን በደንብ ከሚያውቋቸው የህወሓት ታጋይ ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን የሁለተኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን አቋርጠው በ1968 ዓ.ም ወደ በረሃ ገቡ። ከትግሉ በኋላም ከ1983 እስከ 1986 ዓ.ም የአዲስ አበባና የሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የጦር አዛዥ፣ ከ1986 እስከ 1993 ዓ.ም የኢትዮጵያ አየር ሀይል ዋና አዛዥ ሆነው አገልግለዋል። በ1993 ዓ.ም ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ጋር በኤርትራ ጉዳይና በህወሓት ውስጥ በተፈጠረው መከፋፈል ከሰራዊቱ ተሰናብተዋል።
ከጦር አዛዥነታቸው ሲሰናበቱም በ48 ዓመታቸው ከመደበኛ ትምህርት ከተለዩ ከ30ዓመት በኋላ ትምህርታቸውን በመከታተል በህግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል፡፡ በመቀጠልም በአሜሪካ በዓለም አቀፍና ህገ መንግስት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ይዘዋል፡፡ ወደ አገራቸው በመመለስም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስተምረዋል። የኢንስቲትዩት ኦፍ ፌዴራሊዝም ዳይሬክተር በመሆንም አገልግለዋል። በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሰላምና ደህንነት ሶስተኛ ዲግሪያቸውን(ፒኤችዲ) እየተማሩ ሲሆን በተለያዩ ወቅታዊና አገራዊ ጉዳዮች በመፃፍም ይታወቃሉ፡፡ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከሜጄር ጄኔራል አበበ ጋር ያረግነውን ቆይታ፤እነሆ!
አዲስ ዘመን፡- አሁን በአገሪቱ ላለው ለውጥ መንስዔው ምንድን ነው ይላሉ?
ሜጄር ጄኔራል አበበ፡- ከኢትዮጵያ አጠቃላይ ሁኔታ እንጀምር። አገሪቱ በዓለም ምርጥ ህገ መንግስት ካላቸው አገራት ተርታ ትመደባለች። ይህን መሰረት አድርጋ ወደ ዴሞክራሲ እየተሻገረች ነው። ሽግግሩ ዴሞክራሲና ካፒታሊዝምን አጣምሮ የያዘ ስለሆነ ፈታኝ ነው። በሌሎች አገራት ሁለቱ በየተራ ነው ተግባራዊ የሆኑት። አገሪቱ ሽግግር እያደረገች ነው ሲባል ጠያቂ ህብረተሰብ እየተፈጠረ ነው።
ህገ መንግስቱ ከጸደቀ በኋላ ለሃያ አምስት ዓመት ሰላም አገኘን። ጥሩ የሚባልም ኢኮኖሚና ማህበራዊ ዕድገት መጥቷል። ፖለቲካው ግን ወደ ኋላ ቀረ። ዴሞክራሲ ጠፋ፤ ፓርቲው የጠቅላይነት አባዜ ተጠናወተው። በፓርቲው ብቻ ሳይሆን ከታች እስከ ላይ ህዝብን ከማገልገል ይልቅ በህዝብ የሚገለገል መንግስት ተፈጠረ። የህዝብን መብት የማያውቅ መዋቅር ተፈጠረ። መንግስት በህዝቡ ላይ አመጸ። መንግስት ሲያምጽ በህገ መንግስት ላይ ያሉትን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ማፈን ጀመረ። ሰላማዊ ሰልፍ ተከለከለ፤ ሚዲያዎች በነጻነት አይዘግቡም፣ ፍትህ ጠፋ፤ በጥቅሉ ህገ መንግስቱን ተጻረሩ። መንግስት ሲያምጽ ህዝቡ በመንግስት ላይ የማመጽ ተፈጥሮአዊ መብት ስላለው ባለፉት ዓመታት ህዝቡ አመጸ። በተለያየ ደረጃ ቢሆንም የህዝቦች ጥያቄ ሆነ። ድንጋይ አልወረወሩም እንጂ፣ መጀመሪያ ይህ ጥያቄ የተነሳው ትግራይ ክልል ነበር። መሬታቸው ሲወሰድ ትክክል አይደለም ሲሉ የነበሩት ታሰሩ፡፡ በትግራይ ክልል ሰልፍ የሚፈቀደው ለኤርትራውያን ብቻ ነበር፤ ሻቢእያን ስለሚቃወሙ። በአጠቃላይ በሁሉም አካባቢ መንግስትና ህዝብ እየተራራቁ፣ አፈናው እየከፋ፣ ህዝብ ወደ አመጽ ገባ።
አዲስ ዘመን፡- በተለያዩ ጊዜያት በአገሪቱ የተፈጠሩ ቀውሶች ምን ያህሉ ወደ መልካም አጋጣሚ ተቀይረዋል?
ሜጄር ጄኔራል አበበ፡- በተለያዩ ጊዜያት ለሚፈጠሩ ችግሮች መፍትሄ የሚሰጥበት መንገድ የተለያየ ነው። በ1993 ዓ.ም በፖለቲካ ልሂቃኑ መካከል ለተፈጠረው ችግር የተፈታበት መንገድ ከአሁኑ ይለያል፡፡ አሁን እንደ አገር አቅም ፈጥረናል። ህዝቡ የመብቱ ጠያቂ ሆኗል። በዚያን ጊዜ ‹‹አንጃ›› በማለት በጠላትነት ነበር የምንፈራረጀው። አሁን ቀውሱ የሚፈታበት መንገድ አግላይነትን በመተው ወደ አካታችነት ተቀይሯል፡፡ ማሰር ሳይሆን መፍታት፣ መገናኛ ብዙሃንን ከማፈን ይልቅ ነፃ ማድረግ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነት እንዲንቀሰቀሱ በሩ እየተከፈተ ነው። ህገ መንግስቱን በመተግበር ረገድ ችግር ነበር። አሁን ህገ መንግስቱን ተግባራዊ ለማድረግ ፍቅርና አንድነት በማምጣት ጥላቻን በማስወገድ ቀውሱን ወደ መልካም አጋጣሚ ለመቀየር እየተሰራ ነው። ከ1997 ዓ.ም በኋላ አፋኝ ህጎች ወጥተዋል። የታራሚዎችም አያያዝ ተገቢነት የሌለው ነበር። ከእነዚህ ችግሮች በመነሳት ችግር ቢኖርም አገሪቱ በለውጥ ውስጥ ናት።
በፌዴራል መንግስት ጅምር ቢሆንም ችግሮች ወደ መልካም አጋጣሚ እየተለወጡ ነው። ለአገሪቱ ችግር የሆነውና ከህገ መንግስቱ ጋር የሚቃረነው አግላይ ፖለቲካ እየተፈታ ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎች በተሟላ ሁኔታ እንዳይሳተፉ ይከለክል የነበረውን የመፍታት ጥሩ ጅምር አለ። ይህን በሁሉም ክልሎችና ቀበሌዎች ተግባራዊ ማድረግ ይገባል። በክልሎች ካሉ ገዥ ፓርቲዎች ውጭ የሚነገሩ ሃ፦ሳቦች እንደ ወንጀል መቆጠራቸው መቅረት አለባቸው።
‹‹ትምክህተኛና ጠባብ›› እያሉ ጠላት ከማድረግ ይልቅ የህብረተሰብ አስተሳሰብ ከሆነ ምክንያታዊ ውይይት በማድረግ መፍታት ይገባል። መከላከያ ሰራዊት የኢህአዴግ የመጨረሻ ምሽግ ነው ይላሉ። ይህ ጸረ ህገ መንግስት ነው። ብዝሃ ፓርቲ ስርዓት በምትከተል አገር መከላከያ ሰራዊት የአንድ ፓርቲ የመጨረሻ ምሽግ አይሆንም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ሰራዊቱን በሰበሰቡበት ወቅት ‹‹የፓርቲ ተቀጥያዎች አይደላችሁም፡፡ ለሚመጣው መንግስት አገልጋይ ናችሁ›› ብለዋል። ይህ በጣም አስፈላጊ አቅጣጫ ነው። በዚህ ይቀጥላል አይቀጥልም የሚለውን በኋላ የምናየው ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተፈጠረውን ቀውስ ወደ መልካም አጋጣሚ እየቀሩት ነው። የተጀመረው ለውጥ በአገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች እስከ ቀበሌ መውረድ አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ነባር ታጋዮችና ባለስልጣናትን ማሰናበታቸውና በአዲስ መተካታቸውን እንዴት አዩት?
ሜጄር ጄኔራል አበበ፡- በእኔ እምነት አንዳንዶቹ ከአስር ዓመት፣ ሌሎቹ ከአምስትና ከሁለት ዓመት በፊት መሰናበት የነበረባቸው ናቸው። የእኛ ትውልድ በዘመኑ ብዙ ሰርቷል፤ አሁን ላለው ሁኔታ በአስተሳሰብ ኋላ ቀር በመሆኑ ከዴሞክራሲ ጋር አይሄድም። በተለይም በትጥቅ ትግል ያለፈ ወታደር ነው። በወታደራዊ ስራ ደግሞ ዴሞክራሲ የሚባል ነገር የለም። በተለይም በብአዴንና በህውሓት ውስጥ ያሉ መሪዎች ይህ አስተሳሰብ የነበራቸው ናቸው። እንደ ትውልድ ይህ ትውልድ ከዴሞክራሲ ጋር የሚሄድ አይደለም። ይህ ትውልድ ደርግን ጥሏል። የተወሰነ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ለውጥ አምጥቷል። የዴሞክራሲ አስተሳሰብ ግን በውስጡ የለም።
በእኛ ትውልድ ዩኒቨርሲቲ ሰላማዊ ሰልፍ እናድርግ ብለን ጓደኞቻችን ካላደረጉ አላደረጋችሁም ብለን እንደበድብ ነበር። ይህን ዓይነት አስተሳሰብ ያለው ሰው ጠብመንጃ ተጨምሮበት ዴሞክራሲ ሊያመጣ አልቻለም። በመሆኑም የህውሓትና የብአዴን ሰዎች ጠብመንጃቸውን ለመከላከያ ቢያስረክቡም አስተሳሰባቸው ግን ወታደራዊ ነው። በመሆኑም አስተዳደራቸው ኢ-ዴሞክራሲያዊ ነው፤ አካታች አይሆኑም። በዚህ ላይ ከጥቂቶቹ በስተቀር አበዛኛዎቹ አልተማሩም። በድሮ አስተሳሰብ ነው ያሉት።
አገሪቱ በለውጥ ውስጥ በመሆንዋ በድሮ አስተሳሰብ ልትመራ አትችልም። ህዝቡ ስለመብቱ የሚሟገት ነው። ይህን የሚመልስ አመራር ያስፈልገዋል። የ‹‹ለማ›› ቡድን በጎልማሳና በተመሳሳይ ዕድሜ ላይ የሚገኙና ለመማር ዝግጁ የሆኑ ናቸው። የድሮው ዘመን ከዚህ ጋር መሄድ አይችልም። የድሮው አመራር መወገድ ነበረበት። ከዛሬ ሶስት ዓመት በፊት ጀምሬም በዚህ ጉዳይ ላይ ስጽፍ ነበር። በክብር ተሸኝቶ ወጣቱ ኃላፊነቱን ይያዝ። ወጣቱ አይሳሳትም እያልኩ አይደለም፡፡ ስለዴሞክራሲ ከድሮው አመራር የተሻለ ትንሽ እውቅት አለው። የተለያዩ ሃሳቦችን ማስተናገድ ይችላል፡፡ የእኛ ትውልድ የትጥቅ ትግል፤ የአሁኑ ደግሞ የዴሞክራሲ ትውልድ ነው። በመሆኑም የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እርምጃ ትክክል ነው።
አዲስ ዘመን፦ በእርስዎ ሃሳብ የማይስማሙና በአዲሱ ትውልድ እምነት የሌላቸው ሰዎች አሉ። እንዲያውም አገርን አደጋ ላይ ይጥላል የሚሉ አሉ። በዚህ ላይ የእርስዎ ሃሳብ ምንድን ነው?
ሜጄር ጄኔራል አበበ፡- ሁልጊዜም አንዱ ትውልድ ሌላውን ይንቃል። ለምሳሌ የእኔ ቤተሰብ የእኔን ትውልድ ይንቅ ነበር። አባቶች ስለድሮው ነው የሚያስቡት። ውጣቱ ደግሞ ስለወደፊቱ ነው የሚያስበው። ድሮ ግለሰባዊ ፍላጎት ብዙም አልነበረም። አሁን ስለሀብታም፣ ስለሰላምና ስለሌሎች ነገሮች ነው የሚታሰበው። የዛሬና የትናንት ኢትዮጵያዊነት መለኪያው እንኳ የተለያየ ነው። ድሮ ኢትዮጵያዊነት ነፃነት ነበር። አሁን መለኪያው እድገት ብልጽግ፣ ሀብታም መሆን፣ የዴሞክራሲ መኖርና ሌሎች መለኪያዎች ናቸው። የአሁኑ ትውልድ ለአሁኑ ኢትዮጵያዊነት ከድሮው በጣም የተሻለ ነው። የአሁኑ ትውልድ ስህተት አይፈጽምም ማለት ግን አይደለም። ከስህተቱ እየተማረ ግን ከድሮው ትውልድ የተሻለ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።
አዲስ ዘመን፡- በዶክተር አብይ የሚደረጉ ውሳኔዎች ከመርህ ውጪነው። በዚህ የተነሳም ኢህአዴግ ውስጥ መከፋፈል እንዳለ የሚያነሱ አሉ። የእርስዎ እይታ ምንድን ነው?
ሜጄር ጄኔራል አበበ፡- ኢህአዴግ ቆሟል ወይም ወደ ኋላ እየሄደ ነው። ኢህአዴግ ህገ መንግስቱን ስፖንሰር አደረገና አወጣው፤ ህገ መንግስቱን ግን ተጻረረ። አሁን ለህልውናው የሚሆን ቦታ የለውም። እራሱን ማደስ ነበረበት። ተሀድሶ፣ ጥልቅ ተሀድሶ አሉ ግን መታደስ አልቻሉም። ነባሮቹ መታደስ ሲያቅታቸው ይህን በማመን ስልጣናቸውን ማስተላለፍ ነበረባቸው። ግን የስልጣን ነገር ሆኖ አልለቀቁም፤ ስለዚህም ወደቁ። ኢህአዴግ የለም። የሌለው ግን እነሱ በመርህ አልባ እንደሚሉት ሳይሆን ህገ መንግስቱን የሚጻረሩ ፓርቲዎች በመሆናቸው ነው።
ኦህዴድ ነባሮቹን አሽቀንጥሮ በመጣል የለማ ቡድን አዲስ አመራር አመጣ። ብአዴንና ህወሓት ባሉበት ይንገዳገዳሉ። ደኢህዴን በመስራት ላይ ያለ ይመስላል። ኢህአዴግ የለም ስንል ጸረ ህገ መንግስት ሆኗል ማለታችን ነው። አራቱም ድርጅቶች ገምግመው ሀጢያት እንዳለባቸው የተናዘዙት ነው። ይህን ሲናዘዙ ግን አልገባቸውም። እንደዚያ ሀጢያተኛ ከሆኑ ሁሉም መቀየር ነበረባቸው። አሁን ህወሓትና ብአዴን ውስጥ በክልሎቻቸው ከእነሱ ሃሳብ ውጪ መናገር አይቻልም። ኦህዴድ ይሻላል፤ ግን ብዙ ይቀራል። ኢህአዴግ እራሱን ያድሳል ወይም ፈርሶ ሌላ ድርጅት ይፈጠራል። ይህ በየትም ዓለም የሚሆን ነው።
ኢህአዴግን አሁን ዶክተር አብይ የያዘው መንገድ ሊለውጠው ይችላል። የሚሆነውም አዲስ ኢህአዴግ ነው። የፓርቲው የምርጫ ስርዓትና ውሳኔ የሚያስተላልፍበት መንገድ የድሮ ነው። ዶክተር አብይ ከበፊቱ በተለየ ወደ ስልጣን ለመምጣት ከምርጫ በፊት ለመመረጥ ሲሰሩ ነበር። ከተመረጡ በኋላም ሰብስበው የሚወስኑት በእሳቸው ስልጣን ስር የሆነውን ስራቸውን መወሰን ጀምረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ መንግስት እንደ መንግስት፣ ፓርቲም እንደ ፓርቲ ሁሉም በተሰጣቸው ኃላፊነት መስራት አለባቸው። ስራ አስፈፃሚዎቹ ስራ ስለሌላቸው እየተሰበሰቡ መወሰን የለባቸውም። የኤርትራ ጉዳይም መወሰን የነበረበት በካቢኔው ነበር። የተወሰነው ግን በስራ አስፈፃሚው ነው። ይህ ጸረ ህገ መንግስት ነው። በህወሓት የሚቀርበው ቅሬታ ብቻቸውን ወሰኑ የሚል ነው። ማን በምን ይወሰናል የሚለው በህገ መንግስቱ የተቀመጠው መታየት አለበት። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተሰጣቸው ስልጠና ላይ መወሰን ያለባቸው እሳቸው ናቸው። የኢትዮጵያ ህዝብም የሚጠይቀው እሳቸውን ስለሆነ። ፓርቲው እንዲወሰንለት የሚፈልገው ነገር ካለ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማሳመን አለበት።
ፓርቲውና መንግስት መለየት አለበት። ፓርቲው የገመገመው መንግስት እንደገመገመው ይቆጠራል። በፓርቲው የሚያደርገውን ግምገማ የሚጠይቅ አካል አልነበረም። መጠየቅ የተጀመረው አሁን ነው። በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ተፈናቅሎ አመራሮች አልተጠየቁም። ከስብሰባ ወደ ስብሰባ ብቻ ነበር የሚሸጋገሩት። አጠቃላይ የፖለቲካ ስርዓቱ የተበላሸ ነበር። አብዛኛዎቹ ኃላፊዎች ህገ መንግስቱን፣ የፌዴራል ስርዓቱንና ሰብዓዊ መብትን አያውቁትም። ህገ መንግስቱን ትተው በእራሳቸው ሲመሩ ነበር። በፓርቲው ውስጥ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ አልነበረም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ማስተካከል ጀምረዋል።
አዲስ ዘመን፡- ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎረቤት አገራት ያደረጉትን ጉብኝትና በኤር ትራ ላይ በተደረሰው ውሳኔ ዙሪያ አስተያየ ትዎን ቢገልፁልን?
ሜጄር ጄኔራል አበበ፡- ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎረቤትና በመካከ ለኛው ምስራቅ ያደረ ጓቸው ጉብኝቶች ከፍተኛ ውጤት የተገኘባቸው ናቸው። በአጭር ጊዜ ውስጥም ለውጥ መጥቷል። የኢትዮጵያና የኤር ትራ ግንኙነት ግን በዚያ መልክ መሄድ አልነበ ረበትም። የተወሰነ ዝግጅትና ከህዝቡ ጋር ውይይት ያስ ፈልግ ነበር። ችግሩ የተፈጠረው የአልጀርስ ስምምነት ሲፈረም ነው። ይህ ስምምነት መፈረም አልነበረበትም። በእኔ እምነት ይህ ስምምነት ተቀዶ አዲስ ስምምነት መደረግ አለበት። የሚደረገው ስምምነትም የኢትዮጵያን የባህር በርና የህዝብ አሰፋፈር በሚያስጠብቅ መልኩ መካሄድ አለበት።
የአልጀርስ ስምምነት ተወረን ከወራሪ ጋር እኩል አድርጎናል። አሸንፈንም እንደተሸናፊ ነው የሆነው። የኢትዮጵያን መብት ያላስጠበቀና በኤርትራ መንግስት የተጣሰ ነው። በፓርላማው የአልጀርስ ስምምነት ይሁንታ አገኘ እንጂ አልጸደቀም። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ለፓርላማው ያቀረቧቸው አምስት ነጥቦች በምክር ቤቱ አልተሰረዘም። ይህ በፓርላማው ሳይነሳ መወሰኑ ትክክል አይደለም። መወሰን ያለበት ምክር ቤቱ ነው። ይህ እንዳለ ሆኖ ግን ሁለቱን አገራት ለማቀራረብ የሚሰራው ስራ በጣም ጥሩ ነው። ኤምባሲ እንዲከፈት፣ የአየር በረራ እንዲጀመር መሰራቱ የሚደገፍ ነው። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኤርትራን ወደ ኢትዮጵያ የቀላቀላት ኢትዮጵያ የባህር በር እንዲኖራት ነው። አንድ መቶ ሚሊዮን ህዝብ ይዘን የባህር በር የማያረጋግጥ ከሆነ ተገቢነት የለውም።
አዲስ ዘመን ፡- በውጭ አገር ያሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የቀረበውን ጥሪ እንዴት ይመለከቱታል?
ሜጄር ጄኔራል አበበ፡- ለቀውስ የዳረገን የፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብ ነው። ጠንካራዎቹ ተቃዋሚዎች በውጭ አገር ነው ያሉት። የፖለቲካ ምህዳሩ ከዚህ በላይ እንዲሰፋ መሰራት አለበት። እስካሁን የተወሰዱት እርምጃ በጣም ጥሩ ናቸው። ጅምሩን አጠናክረው መቀጠል አለባቸው። ነገር ግን የሚወስኑት ውሳኔ ሁሉም ህገ መንግስቱን መሰረት ያደረገ መሆን አለበት። የህዝብ መብት መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ህዝቡን ሲያሰቃዩ የነበሩ ሰዎች መጠየቅ አለባቸው። በጓደኝነት ዝም ተብሎ መኬድ የለበትም። የሚጠየቀው ስላጠፋ ብቻ ሳይሆን ለቀጣዩ ትምህርት መሆን ስላለበት ነው። ተጠያቂነቱም እስከ ወረዳና ቀበሌ መውረድ አለበት። አንዳንዱ ቦታ ላይም ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ መደመር እየተባለ መቀነስን የሚያመላክቱ ጉዳዮች ስላሉ እሳቸውም አቋም መያዝ አለባቸው። አንዳንዶች እንደ ህወሓት ያሉ ለውጥን የሚቃወሙት በግትርነት ነው። እንደ ብአዴን ያሉት ደግሞ ለውጡ ውስጥ ሆነው ጸረ ለውጥ ሁኔታዎችን በማንሳት ነው። ከዚህ መጠንቀቅ ይገባል። ለውጡ ቢፈለግም ባይፈለግም የግድ ነው።
አዲስ ዘመን ፡-ታራሚዎች በተለቀቁበት መንገድ ዙሪያስ ምን ይላሉ?
ሜጄር ጄኔራል አበበ፡- ድርጅቶቹ ባደረጉት ግምገማ ፍትህ አልነበረም ብለዋል። ስለዚህ አብዛኛው ሰው አላግባብ ነው የታሰረው ማለት ነው። ከዚህ አኳያ አብዛኛው ሰው መፈታት ነበረበት። እነዚህ ሰዎች ሲፈቱ የተወሰኑ ወንጀለኞች መውጣታቸው አይቀርም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስር ወንጀለኞችን ከማሰር አንድ መቶ ተጠርጣሪዎችን ለቆ ሲጣራ ወንጀለኞቹን ማሰር ይገባል ያሉት ለዚህ ነው። ከፍትህ አኳያ ሲታይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወሰዱት እርምጃ ትክክል ነው። ታራሚዎቹን በመልቀቅ ሂደት ስህተቶች ሊኖሩ ይችላል። አንዳንድ ሰው ለውጡን ለመቃወም ስህተቱን ያጎላዋል። መሆን ያለበት ግን ስህተት ቢኖርም በሂደት ቀስ ብሎ ማረም ይቻላል። በሙስና ያልሆነ ዶክመንት ተቀላቅሎ የታሰሩ ሰዎች መኖራቸውን እኔ አውቃለሁ። በጥቅሉ በሂደት እየታረሙ መሄድ የሚገባቸው ቢኖርም ውሳኔው ትክክል ነው።
አዲስ ዘመን፡- የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወሰዷቸውን እርምጃ እንዴት አገኙዋቸው?
ሜጄር ጄኔራል አበበ፡- ፍትህ አልነበረም ካልን ሰብዓዊ መብት አልተከበረም ማለታችን ነው። እንዳልነበረም እናውቃለን። ይህ እንዳይቀጥል ያጠፉ ሰዎች መጠየቅ አለባቸው። ህብረተሰቡ ገና መብቱን አላወቀም። በህብረተሰቡ ውስጥ ዴሞክራሲያዊነትና የህግ የበላይነት ገና አልዳበረም። የህብረተሰቡ ግንዛቤ አድጎ መብቱን እስከሚያስከብር ድረስ ይህ ነገር ወደፊትም ይገጥመናል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኃላፊነታቸውን አልተወጡም። ከዚህ በኋላ ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው።
አዲስ ዘመን፡- የምህረት አዋጁን ለማጸደቅ በሂደት ላይ ነው። አሳሪ የተባሉ ህጎችን ለማሻሻልና ወይም ለመሰረዝ የባለሙያዎች ኮሚቴ ተቋቁሟል። በዚህ ዙሪያስ ምን ይላሉ?
ሜጄር ጄኔራል አበበ፡- የምህረት አዋጁ መውጣቱ ዘግይቷል ካልሆነ በቀር ተገቢነት ያለው እርምጃ ነው። ታራሚዎች ከመለቀቃቸው በፊት መውጣት ነበረበት። ሌሎቹ ህጎቹም አንዳንዶቹ ሊሻሩና ሊስተካከሉ የሚገባቸው ናቸው። የተቀሩትንም ከህገ መንግስቱ ጋር በማጣጣም ማስተካከል ይገባል። የፖለቲካ ምህዳሩን የሚያሰፉ ሆነው መስተካከል አለባቸው።
አዲስ ዘመን፡- በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚነሱ ግጭቶች መንስዔው ምንድን ነው? መፍትሄያቸውስ ?
ሜጄር ጄኔራል አበበ፡- አሁን እየተነሱ ያሉ ግጭቶችን ተፈጥሯዊ አድርጌ ነው የማየው። ይህ የማይቀር ነው። ማድረግ የምንችለው መቀነስ ብቻ ነው። የግጭቱ መንስዔ አፈናው ነው። ታፍኖ ሲከፈት እንዲህ አይነት ነገር ይገጥማል። በውይይት እየተፈታ መጥቶ ቢሆን ኖሮ በዚህ ደረጃ አይሆንም ነበር። ለምሳሌ የትግራይ የበላይነት አለ ይባላል። ውይይት አልተደረገም። ውይይት ቢደረግ ችግሩ እንደዚህ አይሆንም ነበር። አሁን ደግሞ ኢትዮጵያዊነት በሚል ብሄር ብሄረሰብ የሚባለው መታፈን እየተጀመረ ነው። ይህ ትክክል አይደለም።
ዴሞክራሲያዊ አካሄድ ሲሰፋ ሁሉም እየቀነሰ ይሄዳል። ይህ ሁኔታ እስኪስተካከል የታፈነው ሲለቀቅ ወደ ግራና ቀኝ ይሄዳል። ማፈን እስካለ ድረስ ይህ ችግር ይቀጥላል፤ ተፈጥሯዊ ነው። ማፈን ሰው እንሰሳ እንዲሆን ማድረግ ማለት ነው። እንስሳ ሲለቀቅ እንደሚናከሰው ሰውም ነፃ ሲሆን እስከሚሰክን እንደዚያ ነው። አሁን የተጀመረው ጥረት ከቀጠለ እየቀዘቀዘ ይሄዳል። የህግ የበላይነት እየተረጋገጠ ከሄደ ችግሩ ይፈታል። በደቡብ ክልል እንደተወሰደው እርምጃው ከቀጠለ ችግሩ ይፈታል። አሁን የተጀመረው ካልቀጠለ ግን እንደሶሪያ ወደ መፍረስ ነው የምንሄደው።
አዲስ ዘመን፡- ሰላማዊ ሰልፎች ሲካሄዱ በተንጸባረቁት አስተሳሰቦችና በተያዙት ሰንደቅ ዓላማዎች ላይ ያለዎትን ሃሳብ ቢገልፁልን?
ሜጄር ጄኔራል አበበ፡- ይህ ባይንጸባረቅ ነበር የሚገርመኝ። በአማራ ክልል ህገ መንግስታዊ ያልሆነ፣ በኦሮሚያ የኦነግን ሰንደቅ ዓላማ ይዘው ወጥተዋል። ይህ ማለትም በአሁኑ ሰንደቅ ዓላማ ተጨቁነናል የሚል ህብረተሰብ ተፈጥሯል ማለት ነው። ስለዚህ ኢህአዴግ ስራውን አልሰራም ማለት ነው።
ጭቆና ካለ ምልክቶቹ ይወጣሉ። በሰላማዊ ሰልፎቹ ሁሉም ቆሻሻ ነገር ወጥቷል። መውጣቱ ጥሩ ነው። የትግራይ ብሄርን መስደብ ይታያል። ይህ እንደመር እየተባለ መቀነስ ነው። ይህም ቢሆን ውይይት ከተካሄደ ችግሩ እየተፈታ ይሄዳል። ጠንካራ የሆነው የአማራና የትግራይ ህዝብ ግንኙነት እየተጠናከረ ይሄዳል። በወሬ እየተጋነነ ችግር እየተፈታ ይሄዳል። ይህ መሆኑ የሚገርም አይደለም። ውይይትና መቀራረብ ሲፈጠር ችግሮቹ እየተፈቱ፤ ትክክል ያልሆኑት እየተስተካከሉ፤ መቻቻል እየተፈጠረ ይሄዳል። ሂደቱ ግን ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሻ ነው።
አዲስ ዘመን፡- አሁን የሚታዩት ለውጦች በተሻለ ሁኔታ እንዲቀጥሉ ከማን ምን ይጠበቃል?
ሜጄር ጄኔራል አበበ፡- ሁልጊዜም ህዝቡ ተመልካች ከሆነ ለውጥ አይመጣም። ከሶስት ዓመት በፊት ጀምሮ ህዝብ እምቢ አለ። ህዝቡ እምቢ ማለቱን መቀጠል አለበት። እምቢ ሲል ግን ድንጋይ በመወርወርና ጥይት በመተኮስ መሆን የለበትም። አሁን ያለው ሁኔታ ከቀጠለ ድንጋይ መወርወር፣ ጥይት መተኮስም አያስፈልግም። የጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር ህገ መንግስቱን በማክበር የህዝቡን ነፃነት ማክበሩን መቀጠለ አለበት።ምሁራን አገሪቱ ወደ ከፍተኛ ደረጃ እስከምትደርስ ዝም ማለታቸው በታሪክ የሚያስወቅሳቸው በመሆኑ የተከፈተውን ቀዳዳ ተከትለው መስራት አለባቸው። የሃይማኖት አባቶች መጀመሪያ እራሳቸው ውስጥ ያለውን ጥላቻ በማስቀረት ፍቅርን መስበክ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የተጀመረው እስከ ቀበሌ መውረድ አለበት። ትክክል ያልሆነ ስራ ሲሰራ ህዝቡ እምቢ በማለት ህገ መንግስታዊ መብቱን ማስከበር አለበት። ተቋማትም ይህን ማክበር አለባቸው።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡኝ ቃለ ምልልስ በጣም አመሰግናለሁ።
ሜጄር ጄኔራል አበበ፡- እኔም አመሰግናለሁ።

አጎናፍር ገዛኸኝ

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።