|
|
| Home | About us | Contact us | Forum | Subscribe | |
| Login  | Register  | |
| ዜና |
| አስተያየትና እና አመለካከት |
| ርእሰ አንቀፅ |
| ኢኮኖሚ |
| ፖለቲካ |
| ማህበራዊ |
| መዝናኛ |
| ስፖርት |
| የማስታወቅያ ሚኒስተር መልእክት |
| ፎቶ ጋለሪ |
| Home | About us | Contact us | Forum | Subscribe |
| ብድር እዳ የ... |
| የሲሚንቶ ኢ... |
| «ከሕንድ ጋ... |
| «የሊዝ አዋ... |
| በጥቃቅንና ... |
| የሳውዲ አረ... |
| የዳያስፖራ... |
| በወንጂ ሸዋ... |
| ባለሀብቶች ... |
| «የሊዝ አዋ... |
|
«የሊዝ አዋጁ መሬትን ሳያለሙ የሚያስተላልፉ ወገኖችን ለመቆጣጠር ፍቱን መድኃኒት ነው» - አቶ ኃይለ ፍስሐ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ሥራ አስኪያጅ ከዚህ ቀደም መሬትን በሊዝ ለመስጠት የሚያስችሉ አዋጆች ወጥተዋል። እነዚህ በ1986ና በ1994 ዓ.ም የወጡት የመሬት ሊዝ አዋጆች የወቅቱን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘቡ ነበር። ሆኖም በተለይ በ1994 ዓ.ም የወጣው የሊዝ አዋጅ አንዳንድ ክፍተቶች ያሉበት በመሆኑና አሁን ካለው ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር መጣጣም ያልቻለ በመሆኑ ተሻሽሎ እንዲወጣ ተደርጓል። ቀደም ሲል የነበረው የሊዝ አዋጅ ኪራይ ሰብሳቢዎችን ተጠቃሚ ያደረገም ነበር። ይህንን ክፍተት ለመዝጋት ሲባልም የወጣው አዲሱ የሊዝ አዋጅ የኪራይ ሰብሳቢዎችን መንገድ የሚዘጋ መሆኑ ያልተዋጠላቸው ወገኖች አሉ። የሕዝብና የመንግሥት ንብረት የሆነው መሬት መሸጥ፣ መለወጥ እንደሌለበት በሕገ መንግሥቱ በግልጽ ተቀምጧል። መሬትን መሸጥ፣ መለወጥ ባይቻልም በመሬት የመጠቀምን መብት አስቀምጧል። በዚህ የሕገ መንግሥት መነሻነትም አዲሱ የሊዝ አዋጅ ወጥቷል። የአዋጁን መውጣት ተከትሎ አንዳንድ ብዥታዎች ተፈጥረዋል። ብዥታዎቹ ሕዝቡን መደናገር ውስጥ የከተቱ በመሆናቸው የሚመለከታቸው አካላት የሊዝ አዋጁን መሠረታዊ ጭብጥ ለማስረዳት የተለያዩ መድረኮችን ፈጥረው እየሠሩ ነው። በተለይም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር እንዲሁም የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤታዊ ተቋማት በጉዳዩ ላይ የጠራ ግንዛቤ እንዲፈጠር እየሠሩ ነው። የመሬት ይዞታን በተመለከተ የጐላ ችግር የሚታይበት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በየወቅቱ ይህንን ችግር ለመፍታት የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል። ችግሮቹን በየጊዜው ለይቶ በማውጣትና ዘላቂ መፍትሔ በመስጠት ረገድ የተሻለ ነገር ቢታይም አሁንም የሚቀሩ የቤት ሥራዎች አሉት። በተለይ መሬትን ለማልማት ወስደው አጥረው የሚያስቀምጡ ባለሀብቶች ላይ የሚወሰደው እርምጃ በቂ አለመሆንና ለልማት ተነሺ የሚሆኑ ባለይዞታዎችን የማስተናገዱ ሥራ ከትችት ያመለጠ አይደለም። እነዚህና ሌሎች ተዛማች ችግሮች የከተማው መሬት አስተዳደር ተግዳሮቶች ናቸው። እነዚህን ክፍተቶች ደግሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍታት ካልተቻለ ለኪራይ ሰብሳቢዎች የሚኖረው ተጋላጭነት የጐላ ነው። የአዲስ አበባ ከተማ መሬት አስተዳደርና ግንባታ ፈቃድ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቃሲም ፊጤ መሬት ትልቁ የልማት መሣሪያ በመሆኑ ለልማት የሚውልበትን አሠራር ለመዘርጋት የሊዝ አዋጅ ቁጥር 721/2004 ወሳኝ መሆኑን ይናገራሉ። ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ድሃ ሀብታም ሳይል ፍትሐዊ በሆነ መልኩ በመሬት የመጠቀም ዕድል እንዲኖረው ለማስቻል ጥረት እንደሚደረግ አቶ ቃሲም ይገልጻሉ። መሬት ላይ ያለውን ሀብት መጠቀም የሚቻልበት ዕድል መኖሩ በግልጽ የተቀመጠ ሲሆን፤ ይህንን በመተላለፍ ሕገወጥ በሆነ መንገድ መሬትን ሳያለሙ እንዳለ መሬቱን በመሸጥ ብቻ የከበሩ እንዳሉ የሚጠቁሙት አቶ ቃሲም ይህንን ለመከላከል ጠንካራ የሆነ የሊዝ አዋጅ ማስፈለጉን ያብራራሉ። በሊዝ አዋጅ ቁጥር 721/2004 መሠረት ባዶ መሬት ማስተላለፍ አይቻልም። ቤት ሠርቶ የማስተላለፍ መብት ቢኖርም ምንም መሬቱ ላይ እሴት ሳይጨመር ባዶ መሬት ማስተላለፍ ሕገ መንግሥቱን እንደመጣስ ይቆጠራል። ይህ ብቻ ሳይሆን ከ50 በመቶ በታች ግንባታ ያከናወነ ከሆነ ሥልጣን ከተሰጠው አካል ቁጥጥር ውጪ የማስተላለፍ መብቱ የተገደበ ነው። 60 እና 70ሺ ብር የማያወጣ ነገር በመሬቱ ላይ ኢንቨስት አድርጐ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር የሚያፈስበት አማራጭ በአዋጁ ዝግ ሊደረግ መቻሉን ያስረዳሉ። ከ50 በመቶ በላይ ግንባታ ተከናውኖ ከሆነ ግን መሬቱን የማያስተላልፍበት ዕድል አለ። ይህ የሚሆነው ግን መሬቱ የኪራይ ሰብሳቢዎችን ኪስ በሚያደልብበት መንገድ ሳይሆን ተገቢውን የሊዝ ክፍያ የሚመለከተው አካል ሲያገኝ ብቻ ነው። አዋጁ በዋነኛነት ኢላማ ያደረገው መሬት ላይ ምንም ዓይነት እሴት ሳይጨምሩ ለመክበር የሚንቀሳቀሱ ቡድኖችን አማራጭ መንገድ ለመዝጋት ነው። ይህ ደግሞ የኅብረተሰቡን ዘላቂ ጥቅም ለማስከበር የሚያስችል ነው። አዋጁ የመሬቱ ተጠቃሚ አካል የሊዝ ዋጋን በወቅቱ ካልከፈለ መንግሥት ምን ማድረግ እንዳለበት አስቀምጧል። በመሬት ላይ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት የሚደረገውን ሩጫ ለመግታት የሚያስችል ከመሆኑም በላይ ልማታዊ የሆነ አስተሳሰብ ያለው የመሬቱ ተጠቃሚ ሁሉ በወቅቱ የሊዝ ዋጋ ክፍያን መፈፀም አለበት። ለኅብረተሰቡ ከፍተኛ ጥቅም ማስገኘት የሚችሉ ፕሮጀክቶች ካሉ ለምሣሌ ትምህርት ከሆነ የውጭ ትምህርት ጉዞን ወይም ሆስፒታል ከሆነ የውጭ አገር ሕክምናን የሚያስቀሩ እንዲሁም የሀገርን ሀብት ለመቆጠብ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች ከሆነ መሬቱን የሚጠይቀው አካል አቅም ያለው መሆኑ ተረጋግጦ መሬት የሚያገኝበት ዕድል ከፍ ያለ ነው። ለእነዚህ ባለሀብቶች ቅድሚያ የሚሰጥበት ምክንያት ፕሮጀክቶቹ የሕዝብንና የሀገርን ጥቅም የሚያረጋግጡ በመሆናቸው ነው። የሊዝ አዋጁ ይህንን ጉዳይ ግልፅ በሆነ መልኩ አስቀምጦታል። ፈጣን ልማት ለማምጣት ሜዳው ሰፊ እንዲሆን የሊዝ አዋጁ የሚጫወተው ሚና የላቀ ነው። እያንዳንዱ የአዋጅ ይዘት ፈጣን ልማት ከማምጣት አንፃር የተቃኘ ነው። በሌላ በኩልም ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመዝጋት የሚያስችል ነው። አዋጁ ፈጣን ልማትን ለማምጣትና ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመዋጋት እንዲያስችል ሆኖ መዘጋጀቱ ያልተዋጠላቸው ወገኖች እንዳሉ አቶ ቃሲም ይገልጻሉ። ይህንን ፀረ -ልማት አስተሳሰብ መዋጋት የሚጠበቅባቸው በዋነኛነት ኅብረተሰቡና በየደረጃው የሚገኙ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት ናቸው። ፈጣን ልማት ሲመጣና ኪራይ ሰብሳቢነት ሲዳከም ልማታዊ አስተሳሰብ ሲጐለብት ሕዝቡ ከልማቱ የሚኖረው ተጠቃሚነት ይጨምራል። የወጣው የሊዝ አዋጅም በዚህ መሠረት መመዘን አለበት። ኪራይ ሰብሳቢነትን ምን ያህል ይዋጋል? ፈጣን ልማትን ምን ያህል ያረጋግጣል? ለሚሉት ጥያቄዎች ከሚሰጠው መልስ አኳያ መመዘን እንዳለበት የሚገልጹት አቶ ቃሲም «እነዚህን ጥያቄዎች በመመለስ ረገድ አዋጁ ጠንካራ ይዘት አለው» ይላሉ። የመንግሥት ሠራተኛውና በአነስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የኅብረተሰብ ክፍል ከአዋጁ ተጠቃሚ የሚሆንበት አማራጭ ተቀምጧል። የውሃ፣ የጤና፣ የትምህርትና የመሳሰሉት መሠረተ ልማቶች የሚከናወኑት የከተማ አስተዳደሩ ከሚሰበስበው ገቢ ነው። ስለሆነም ከሊዝ ከሚገኘው ገቢ ሰፊው ኅብረተሰብ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ዕድል ይፈጥራል። የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማትን እንዲያድጉና እንዲስፋፉ በማድረግ ረገድ የሊዝ አዋጁ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። መሬት ሕገ ወጥ ለሆነ አሠራር ሳይጋለጥ ለተገቢው ጥቅም እንዲውል በማድረግ የሊዝ አዋጁ አስፈላጊነት የላቀ ነው። መሬትን በአግባቡ ለልማት እንዲውል በማድረግና ፈጣን ልማትን በማረጋገጥ በመካከለኛና በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ኅብረተሰብ በስፋት ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችል መሆኑን አቶ ቃሲም ይናገራሉ። መሬትን በሊዝ መግዛት የማይችለው የኅብረተሰብ ክፍል በቁጠባ ማኅበር ተደራጅቶ መሬትን አግኝቶ የሚያለማበት መንገድ በሊዝ አዋጁ በኩል ተከፍቷል። 40 በመቶ በመቆጠብ ቀሪው 60 በመቶ በረጅም ጊዜ ክፍያ በመፈፀም ኅብረተሰቡ የቤት ተጠቃሚ እንዲሆን ዕድል ይሰጠዋል። «የመንግሥት ሠራተኛውን የቤት ባለቤት የመሆን ተስፋውን እውን የሚያደርግ አዋጅ መውጣቱ ኅብረተሰቡን ብዥታ ውስጥ ሊከት አይገባም» ይላሉ አቶ ቃሲም። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኃይለ ፍስሐ በበኩላቸው እንደሚሉት የሊዝ አዋጁ ለፈጣን አገራዊ ልማትና ለኅብረተሰቡ ተጠቃሚነት ሲባል ተገቢው ጥንቃቄ ተደርጐበት የወጣ ነው። ኅብረተሰቡን ብዥታ ውስጥ እየከተቱ የሚገኙት ቀደም ሲል የነበረውን የሊዝ አዋጅ ክፍተት ተጠቅመው ወደ ኪራይ ሰብሳቢነት ገብተው የነበሩ ሕገወጦች እንደሆኑም ይጠቁማሉ። አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል ቤት የመሥራት አቅሙ ዝቅተኛ በመሆኑ የሕዝብና የመንግሥት የሆነውን የመሬት ሀብት መንግሥት ውጤታማ በሆነ መንገድ በማስተዳደር ከመሬት ሊዝ ከሚገኘው ገቢ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በመገንባት የመኖሪያ ቤት እጥረትን ለመቅረፍ እንደሚንቀሳቀስ አቶ ኃይለ ያስረዳሉ። «መሬት በሊዝ ወስደው ለማልማት ከሚፈልጉ ወገኖች በሚገኘው ገቢ የመኖሪያ ቤቶችን በመገንባት ለተጠቃሚዎች የማስተላለፍ ዕቅድ አለ» ይላሉ። አዋጁ መሬትን ሳያለሙ የሚያስተላልፉ ወገኖችን ለመቆጣጠር ፍቱን መድኃኒት ነው የሚሉት አቶ ኃይለ በኅብረተሰቡ ዘንድ ብዥታን እየፈጠሩ ያሉ ሕገወጥ በሆነ መንገድ የከበሩ ኪራይ ሰብሳቢዎች ናቸው ይላሉ። ከነባር ይዞታ ጋር በተያያዘ እየተራገበ ያለው ወሬ ከአዋጁ ተጨባጭነት ጋር ተዛማጅነት የሌለው መሆኑን በመጥቀስ ኅብረተሰቡም ሆነ የማዘጋጃ ቤታዊ ተቋማት ሠራተኞች የጠራ ግንዛቤ እንዲጨብጡ የሚያስችል ተከታታይነት ያለው ሥራ እንደሚሠራ አቶ ኃይለ ይጠቁማሉ።
ሪፖርተር አቢይ ጌታሁን
ቀን 2012-01-25 00:00:00 |