|
|
| Home | About us | Contact us | Forum | Subscribe | |
| Login  | Register  | |
| ዜና |
| አስተያየትና እና አመለካከት |
| ርእሰ አንቀፅ |
| ኢኮኖሚ |
| ፖለቲካ |
| ማህበራዊ |
| መዝናኛ |
| ስፖርት |
| የማስታወቅያ ሚኒስተር መልእክት |
| ፎቶ ጋለሪ |
| Home | About us | Contact us | Forum | Subscribe |
| መድረክ የዋ... |
| «ኤጀንሲው... |
| «ኢህአዴግ ... |
| ውል የሚፈጸ... |
| «የጠቅላይ ... |
| «ቻይና ከአ... |
| «ውጤት እየ... |
| አዲስ አበባ ... |
| የሽብርን መ... |
| «ህገ መንግ... |
|
«ህገ መንግሥታችን የመናናቅና የማንቋሸሽ አመለካከትን የሚፀየፍ ነው» - ዶክተር ፋሲል ናሆም በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ «ሕገ መንግሥቱ ክፍተቶች ስላሉበት ሊሻሻል ይገባል። ሕገ መንግሥቱን የመተርጐም ስልጣንም ለፍርድ ቤቶች መሰጠት ነበረበት። 'ዝርዝሮቹ በሕግ ይወሰናል' እየተባሉ በሕገመንግሥቱ ለተቀመጡ ድንጋጌዎችም ዝርዝር ሕጐች አልወጡላቸውም» በሚል አንዳን ዶች የተለያዩ አስተያየቶችን ሲሰነዝሩ ይሰማሉ። በአንፃሩ ሕገ መንግሥቱ የኢትዮጵያን የዘመናት ችግሮች በአስተማማኝ ሁኔታ በመፍታቱ አሁን የተገኘው ሰላምና ልማት መምጣቱን የሚናገሩም አሉ፤ በዚህ ዙሪያ በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስ ትሩ ልዩ አማካሪ ከሆኑት ዶክተር ፋሲል ናሆም ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል። አዲስ ዘመን፡- «ሕገ መንግሥቱ ክፍተቶች ስላሉበት ሊሻሻል ይገባል» በማለት አንዳንድ ወገኖች በተደጋጋሚ ሲገልጹ ይደመጣል። እርስዎ ደግሞ በቅርቡ በኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ላይ «ሕገ መንግሥቱን ገና በደንብ አጣጥመን አልበላነውም» ሲሉ ተደምጧል። ይህ አባባል ከሚሰነዘረው አስተያየት አንፃር ምን ማለት ነው? ዶክተር ፋሲል፡- ሕገ መንግሥታችን በጣም ዘመናዊ ከሚባሉ ሕግጋተ መንግሥት ተርታ የሚሰለፍ ሕገ መንግሥት ነው። ሰብአዊ መብቶችና ነፃነቶች እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ መብቶችን አስመልክቶ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የደነገጋቸውን መብቶችና ነፃነቶች ሁሉ አሟልቶ ያካተተ ነው። በሌላ በኩል ሕገ መንግሥታችን በሥራ ላይ ከዋለበት ጊዜ አንፃር ሁለት አሥርት ዓመታት ያልሞላው ለጋ ሕገ መንግሥት ነው። ሕገ መንግሥቱ የሚያልመው ራዕይ በጣም ጥልቅና ሰፊ በመሆኑ በእነዚህ ጥቂት ዓመታት ሊገኝ የተቻለው ውጤት አበረታች ቢሆንም አሁንም ገና ነው። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ከብዙዎቹ አገሮች በተሻለ መልኩ የተባበሩት መንግሥታትን የምዕተ ዓመቱን የልማት ግቦች ታሳካለች የሚል ግንዛቤ አለ። የምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች ዓላማ በስምንት ወሳኝ የኑሮ ዘርፎች ድህነትን በግማሽ መቅረፍ ነው። እ.ኤ.አ በ2015 ይህን ውጤት ማምጣት በተለይ የዓለም ሕዝብ እያለፈበት ካለው አስቸጋሪ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የሽብርተኝነትና የኢኮኖሚ ቀውስ አንፃር መልካም ነገር ነው። በ20ና በ30 ዓመታት ጊዜ ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሰለፍ ትልሟን ትቀጥልበታለች። በረጅሙ እቅዷ ደግሞ የብሪክስ አገሮችን (ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቻይናና ደቡብ አፍሪካ) ዘርፍ ይዛ የማትራመድበት ምንም ምክንያት የለም። ከታሪክ አንፃር ኢትዮጵያ ጥቂት ከሆኑ አገሮች ጋር የምትሰለፍ የዓለም ሥልጣኔ ምንጭ ነች። የኢትዮጵያ ሕዝቦች የአስተዳደርና የፈጠራ ችሎታ ኢትዮጵያ ለብዙ ሺ ዓመታት ህልውናዋንና ነፃነቷን አስከብራና ጠብቃ ለዚህ ዘመን እንድትበቃ አድርጓታል። ሕገ መንግሥታችን ያለፈውን የተዛባ የሕዝቦች አመለካከትን በመለወጥ ኢትዮጵያን በሕዝቦች እኩልነት ላይ የተመሠረተች አገር አድርጓታል። የሕዝቦች እኩልነት በውስጡ የዜጎች፣ የፆታ፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋና የባህል እኩልነትን ያካተተ ጥልቅ አስተሳሰብ ነው። ዋና ቀሪ ሥራችን ይህንን ሕገ መንግሥት በቀን ተቀን ኑሮአችን በመተግበር እያንዳንዳችን የተሟላና ሰብእናን የተላበሰ ኑሮ እንድንኖር ማድረግ ነው። ጎዳና ተዳዳሪነትን፣ መሐይምነትን፣ ድንቁርናና ድህነትን እንዲሁም በጾታ፣ በባህል፣ በሃይማኖት የመናናቅና የማንቋሸሽ አመለካከትን የሚጸየፍ ሕገ መንግሥት ነው ያለን። ዋናው ተግባራችን ይህንን ሕገ መንግሥት በሕይወታችን እውን ማድረግ ነው። በመሆኑም ሕገ መንግሥቱን በደንብ አጣጥመን ማወቅና በተግባር መተርጐም አለብን። ለዚህም ተገቢውን ትኩረት መስጠትና መንቀሳቀስ አለብን። አዲስ ዘመን፡- ሕገ መንግሥቱ ሊሻሻል ይገባል በሚል ለሚሰነዘረው አስተያየትስ? ዶክተር ፋሲል፡- ስለ ሕገ መንግሥት መሻሻል ጉዳይ ሲነሳ ጉዳዩን በሁለት ከፍሎ ማየት ያስፈልጋል። በመጀመሪያ ደረጃ ሕገ መንግሥቱ ሊሻሻል ይችላል ወይ? የሚል ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ሕገ መንግሥቱ ዛሬ መሻሻል ይኖርበታል ወይ? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ነው። ሁለቱ የተለያዩ ጥያቄዎች በመሆናቸው ጉዳዩን አድበስብሶ ማለፍ ትክክል አይሆንም። ሕገ መንግሥቱ ሊሻሻል ይችላል ወይ? የሚለው ጥያቄ በማያወላውል መልኩ መልሱ አዎን ሊሻሻል ይችላል ነው። በመሆኑም ሕገ መንግሥቱ በውስጡ የማሻሻያ ሥርዓት ያበጀ ስለሆነ ማሻሻል ሲያስፈልግ ሥርዓቱን ተከትሎ ሊሻሻል ይችላል ማለት ነው። የሕገ መንግሥቱ ባለቤቶች የሆኑት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በሕገ መንግሥቱ ውስጥ በተደነገገው ሥርዓት መሠረት ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል ሲፈልጉ የማሻሻል ሙሉ ሥልጣን አላቸው። ሕገ መንግሥቱ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት አድርጓቸዋል። ይህም በሚያስፈልግበት ጊዜ ሕገ መንግሥቱን የማሻሻል ሥልጣንን የሚያካትት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ሕገ መንግሥቱ ሁለት የማሻሻያ ሥርዓቶችን ዘርግቷል። በሕገ መንግሥቱ የተደነገጉት መብቶችና ነፃነቶችን ከመጠበቅ አንፃር ጠበቅ ያለውን የማሻሻያ ሥርዓት በአንቀጽ 105(1) የተደነገገ ሲሆን፤ ከዚህ ውጪ ላለው ደግሞ በአንቀጽ 105(2) በተደነገገው መሠረት ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል ይቻላል። ሕገ መንግሥቱ ዛሬ መሻሻል ይኖርበታል ወይ የሚለውን ደግሞ እንመልከት። መሻሻል ይኖርበታል ስንል ሕገ መንግሥቱ ሲረቀቅ መታየት የነበረበት ግድፈት ስላለው ወይም ዛሬ ሁኔታዎች ስለተለዋወጡ ከሚል ነው መነሳት የሚቻለው። በየትኛውም አመለካከት የማስረዳትና የማሳመን ግዴታ (burden of proof) የሚኖረው መሻሻል አለበት በሚለው ወገን ነው። ማሳመን ያለበትም ሕገ መንግሥቱን ሊያሻሽሉ ሥልጣን ያላቸውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ነው። ሕገ መንግሥቱ መሻሻል አለበት የሚባለው፣ ሕገ መንግሥቱ ሲረቀቅ በሕዝቦቿ የእኩልነትና የሉዓላዊነት ጉዳይ ሲሰነዘሩ የነበሩትን አንዳንድ ትችቶችን እንደገና ለማንሳት ከሆነ የተጣለውን ጽኑ መሠረት ማነቃነቅ ይሆናል። ይህንን መሞከር የሕዝቦቿን መሠረታዊ የሰላም፣ የዴሞክራሲና የልማት ጥቅም የሚጻረር በመሆኑ ጥያቄው ከመነሻው ውድቅ ተደርጎ መታየት ይኖርበታል። ዛሬ በፈጣን ለውጥ እያለፍን ባለንበት ወቅት ሕገ መንግሥቱ ሊሻሻል ይገባል የሚል አመለካከት ካለም ይህንን ፈጣን ለውጥ ያመጣው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ መሆኑን ማጤን ያስፈልጋል። በመሆኑም ይህንን በጥልቀት ማየት ተገቢ ነው። በኢትዮጵያ ከአምስት ዜጐች አራቱ በገጠር የሚኖሩ፣ በግብርናና በአርብቶ አደርነት የሚተዳደሩ ናቸው። ከሕዝቡም 50 በመቶው ወጣት መሆኑን በመገንዘብ ፈጣን ለውጥ በማኅበራዊ ፍትህ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ማድረግ የሕገ መንግሥቱ ዓላማ መሆኑን አገናዝቦ ማየትን ይጠይቃል። በአገር አቀፍ ምርጫ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስላልቀናቸው ሕገ መንግሥቱ ሊሻሻል ይገባል የሚል አመለካከት ሊኖር ይችላል። ነገር ግን በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ነው ሕዝቡ የሚበጀውን የሚመርጠው። ስለሆነም ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሕዝቡን የልብ ትርታ የማዳመጥ፣ ይህንን ለመፈጸምም በቁርጠኝነትና አቅምን በማዳበር መንቀሳቀስ ይገባቸዋል። በእኔ አመለካከት ዋና ትኩረታችን መሆን የሚገባው በማሻሻል ላይ ሳይሆን ሕገ መንግሥታችንን በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ በየፊናችን መሯሯጡ ላይ ነው። ይቀጥላል
ሪፖርተር ዳንኤል ንጉሤ
ቀን 2012-01-24 00:00:00 |