|
|
| Home | About us | Contact us | Forum | Subscribe | |
| Login  | Register  | |
| ዜና |
| አስተያየትና እና አመለካከት |
| ርእሰ አንቀፅ |
| ኢኮኖሚ |
| ፖለቲካ |
| ማህበራዊ |
| መዝናኛ |
| ስፖርት |
| የማስታወቅያ ሚኒስተር መልእክት |
| ፎቶ ጋለሪ |
| Home | About us | Contact us | Forum | Subscribe |
| ከጥያቄው ይ... |
| እንጦጦ የቱ... |
| የፖለቲካ ማ... |
| እኛም የመኖ... |
| የዩኒቨርሲ... |
| እውን የሊዝ ... |
| ሕዝብ ጥቅሙ... |
| መድረክ ወዴ... |
| “የአስመራ... |
| ስለቻይና የ... |
|
ስለቻይና የሚባለውና እውነታው በአስቻለው ታሪኩ የቻይና የለውጥና የተሃድሶ አባት በመባል የሚታወቁትና አገሪቱ የለውጥ ግስጋሴዋን በጀመረችባቸው ዓመታት ታላቋን አገር በፕሬዚዳንትነት የመሯት ዴንግ ሺያዎፒንግ በአባባሎቻቸውና በጥቅሶቻቸው ጥልቅነት እጅጉን ታዋቂ ናቸው፡፡ እኒህ ስመ ጥር መሪ በተለይም የድመቷ ንድፈ ሃሳብ የሚለውና ብዙ የተፃፈለት አባባላቸው ምንጊዜም ይጠቀስላቸዋል፡፡ ዴንግ ቻይናን የመለወጡን ፖሊሲ ወደ ተግባር ባሸጋገሩበት ወቅት የገጠማቸው ቀዳሚው ጥያቄ ምን ዓይነት ሥርዓት ነው የምንከተለው? ወደ የትስ ነው የምናመራው? ዓይነት የአካሄድና የርዕዮተዓለም ጥያቄ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ብልሁ መሪ ታዲያ ለዚህ ወሳኝ ጥያቄ የሰጡት ምላሽ የድመቷን ቀለም መለያ መሠረት ያደረገ ሲሆን ለወቅቱ ወሳኝ ጥያቄ የማያወላዳ ምላሽ ለመስጠት እንደቻሉም ይነገርላቸዋል፡፡ “ድመቷ” አሉ ዴንግ በወቅቱ “ጥቁር ወይም ነጭ ልትሆን ትችላለች፡፡ ነገር ግን አይጥ እስከያዘችልን ጊዜ ድረስ ለእኛ ለውጥ የለውም፡፡” ይህ አባባል ከዛሬ 30 ዓመታት በፊት የተነገረና ዛሬም ድረስ ምሁራንና ፖለቲከኞች ደጋግመው የሚጠቀሱትና የቻይና የለውጥ ግስጋሴ እስከቀጠለ ድረስ የሚዘልቅ፤ ታሪካዊ፣ ህያውና ንድፈ ሃሳባዊ መሠረት ያለው ጥቅስ ተደርጐ የሚወሰድ ነው፡፡ መፃኢው የቻይና የእድገት ግስጋሴም ከዚሁ ንድፈ ሃሳባዊ አባባል ተነስቶ ወደፊት እንደሚራመድ መገመት ይቻላል፡፡ እንደተጠቀሰው የቻይናን ፈጣን እድገት የሚያረጋግጥ እስከሆነ ድረስ የካፒታሊዝምን የእድገት አቅጣጫ ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በሚጣጣም መልኩ ማስኬድና ተመጋጋቢ ማድረግ ለፕራግማቲኮቹ የቻይና መሪዎች ተመራጭና የሚያዋጣ የልማት ስትራቴጂ ነው፡፡ የቻይናን እድገት የማይገታ አማራጭ ሁሉ ከሁኔታዎችና ከፖሊሲዎች ጋር ተጣጥሞ እንዲሄድ ይደረጋል እንጂ፤ የሚጣጣልበት ሁኔታ የሚታሰብ አይደለም፡፡ ለውጭ ባለሀብቶችና ኩባንያዎች በሯን ክፍት በማድረግ ከዛሬ 30 ዓመታት በፊት በአዲስ የለውጥ ርምጃ የማያወላውል አቋም የያዘችው ቻይና እነሆ ዛሬ በተከተለቻቸው ፖሊሲዎች አማካኝነት ከዓለም ሁለተኛውን ግዙፍ ኢኮኖሚ ለመገንባት በቅታለች፡፡ በዚሁ ፈጣን የእድገት ጉዞዋ ከገፋችበት ደግሞ ከአራት ዓመታት በኋላ በዓመታዊ ጠቅላላ ገቢ ስሌት የዩናይትድ ስቴትስን የክብር ሥፍራ እንደምትረከበው ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ጥናት ተቋማት ከወዲሁ ማረጋገጫ በመስጠት ላይ ናቸው፡፡ የቻይና የእድገት አቅጣጫ ትክክለኛና የሚደገፍ ስለመሆኑ ሌሎች ማሳያዎችን በመጥቀስ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ በዓለማችን ለሦስት አሥርት ተከታታይ ዓመታት ፈጣን እድገት እውን ማድረግ የቻለ አገር በዓለማችን ላይ እስከአሁን አለመታየቱ የቻይናን የእድገት ፖሊሲና ስትራቴጂ ትክክለኛነት ያሳያል፡፡ በአሁኑ ወቅት በዓለማችን ካለው የውጭ መጠባበቂያ ገንዘብ ክምችት ውስጥ 40 በመቶው ወይም 3.2 ትሪሊዮን ዶላር ያህሉ የቻይና አንጡራ ሀብት ሆኖ የመገኘቱ እውነታም ሌላው ጉልህ አስረጂ ነው፡፡ በ30 ዓመታት የእድገት ግስጋሴ ውስጥ ወደ 175 ሚሊዮን ያህል ቤተሰቦች ወይም ከ500 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ዓለምን ባስደመመ ሁኔታ ወደ መካከለኛው መደብ መለወጡም የቻይና ልማትና እድገት አብዛኛውን የኅብረተሰብ ክፍል መሠረት ያደረገ ስለመሆኑ ያረጋግጣል፡፡ በዓለማችን ከሚገኙት 500 ምርጥና ዝነኛ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች መካከል 80 በመቶ ያህሉ በቻይና ኢንቨስት ማድረጋቸውና ለትርፋማነታቸው ቻይናን በቀዳሚነት መምረጣቸው ሌላው የውጤታማነት ማስመስከሪያ ነው፡፡ በየዓመቱ በ100 ቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር የንግድ ትርፍ ወይንም ወደቻይና በእጅጉን ያጋደለ የገቢና የወጪ ንግድ ሚዛን ማስመዝገቧ በተለይም አውሮፓና አሜሪካ ለከፍተኛ ቀውስ በተዳረጉበት ዘመን ይህን ዓይነት ግዙፍ ለውጥ ለማሳየት መቻሏም በእርግጥም የስኬትና የትክክለኛ የእድገት ፖሊሲ መገለጫ ተደርጐ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡ ይሁንና ግን የቻይና እድገት ስኬትና ገድል ሲወሳ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ እንደሆነ አድርጐ መውሰድ ስህተት ላይ እንደሚጥል ማመን ተገቢነት ይኖረዋል፡፡ በከተሞችና በገጠር ያለው የቻይና እድገት አሁንም ሰፊ ልዩነት የሚስተዋልበት ነው፡፡ ከወደብ ጋር በተሳሰሩት ከተሞች እና ከወደብ በራቁት ከተሞች መካከል የሚታየው ልዩነትም በጣም እየሰፋ መጥቷል፡፡ የተሻለ ገቢ ባላቸውና በድህነት በሚማቅቁት መካከል የሚስተዋለው ኢፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልም በተግባር ለሚያምኑት የቻይና መሪዎች ታላቅ ፈተና ነው፡፡ ደርሶ የሚመለሰውና እዚያው በዚያው የሚሽከረከረው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት፣ ሙስና፣ የአካባቢ ብክለት፤ የዴሞክራሲ የሰብአዊ መብት መሰል ጉዳዮችም ቻይናን በእጅጉ እንደፈተንዋትና እየፈተኗትም እንደሚገኙ መዘንጋት አይኖርበትም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ቻይና በሰለጠኑት አገሮች ዘንድ የምትታይበት መነፅርና በአንዳንድ መሠረታዊ ጉዳዮች ስሟ የመብጠልጠሉና የመነሳቱ ጉዳይ ከምትከተለው የእድገት አቅጣጫና ፖሊሲ ጋር በተለይም በአፍሪካ አገሮች ከምትጫወተው ሚና አኳያ ተያያዥነት ያለው ስለሚመስል በገደምዳሜም ቢሆን በጥቂቱ ማውሳቱ ተገቢነት ይኖረዋል፡፡ ቻይና ከምትወቅስባቸው ዓለም አቀፍ ጉዳዮች መካከል አንዱ ከአምባገነንና ጨካኝ መሪዎች ጋር አላት የሚባለው ግንኙነት ነው፡፡ ይህንን አስመልክቶ በኢትዮጵያ አዲስ የተሾሙት የቻይና አምባሳደር ሺየ ሺያዎያን ሰሞኑን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አገራቸው የምትከተለውን የማያሻማ ፖሊሲ አጭርና ግልፅ በሆነ አቀራረብ አስቀምጠውታል፡፡ እንደ አምባሳደሩ አባባል ቻይና በማንኛውም አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አትገባም፡፡ አገሮች፣ መንግሥታትና ሕዝቦቻቸው ችግሮቻቸውን በራሳቸው መንገድ እንዲፈቱ ፅኑ ፍላጐት አላት፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት ሽብርተኝነት በሚደግፈው የኤርትራ መንግሥት ላይ የማዕቀብ ውሳኔ ሲያስተላልፍ ቻይና ድምፀ ተአቅቦ ያደረገችበትን ምክንያት በተመለከተም የአምባሳደሩ ምላሽ የቻይና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በአገሮች የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ካለመግባት ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ አስምረውበታል፡፡ ታዳጊ አገሮች በተለይም አፍሪካውያን ችግሮቻቸውን በራሳቸው መንገድ ይፈቱ ዘንድ የቻይና ፅኑ ፍላጐት ነው፡፡ ከቻይና ምርቶችና ሸቀጦች ጋር የተያያዘው ቅሬታና ወቀሳም ለአገሪቱ መብጠልጠልና ውግዘት አንዱ ምክንያት ተደርጐ የሚወሰድ ነው፡፡ እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት ቻይና የዓለማችን ቁጥር አንድ አምራች አገር ናት፡፡ የቻይና እቃዎችና ምርቶች የማይገኙበት የዓለማችን አገርም የለም ለማለትም ይቻላል፡፡ ይሁንና ርካሽና ደረጃቸውን ያልተጠበቁ ሸቀጦችና እቃዎች ከቻይና ወደ አፍሪካና እስያ አገሮች በብዛት ስለምትልክ ታዳጊ አገሮችን ማራገፊያ አድርጋቸዋለች እየተባለች ትወቀሳለች፡፡ በእኛም አገር ለቻይና ምርቶችና እቃዎች ያለው ግምት ዝቅተኛ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በገበያ ላይ የሚታዩት የቻይና ምርቶች ደረጃቸውን ያልተጠበቁና የዋጋቸውን ያህል አገልግሎት እንደማይሰጡም ተደጋግሞ ይነገራል፡፡ ለእንደዚህ ዓይነቱ ወቀሳና ትችት የቻይናው አምባሳደር የሰጡት ምላሽ የጋራ ጥረትና ክትትልን የማጠናከር ተገቢነት ላይ ያነጣጥራል፡፡ እንደ አምባሳደሩ ምላሽ በቻይና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ጥራት ያላቸውና በተሻለ ዋጋ የሚሸጡ ምርቶች ይመረታሉ፡፡ የዚያኑ ያህል ደግሞ ዋጋቸውም ጥራታቸውም ዝቅ ያሉ ምርቶች ለገበያ መቅረባቸው ፀሐይ የሞቀው እውነታ ነው፡፡ ጥራት ያለው እቃ ለመግዛት አቅምና ኪስ ወሳኝነት አላቸው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሙሉ ልብስ ቻይና ውስጥ በ100 ዩዋን፣ (በቻይና የመገበያያ ገንዘብ ሬሚምቢ) ወይንም በኢትዮጵያ በብር 250 መግዛት ይቻላል፡፡ ውዱንና ምርጡን ሙሉ ልብስ ደግሞ በ100 ሺ የቻይና ዩዋን ወይንም በ250 ሺ የኢትዮጵያ ብር መሸመትም ዝግ አይደለም፡፡ ሌላም ምሳሌ እናክል፡፡ ቻይና ውስጥ በአሜሪካኑ ጀኔራል ሞተርስ ሲመረት የነበረውን ሃመር ጨምሮ በርካታ የተሽከርካሪ አምራቾች ቻይና ውስጥ በስፋት ኢንቨስት አድርገዋል፡፡ እናም ያለው በ100 ሺ የተረፈውና የሚቀናጣው ደግሞ በ10 ሚሊዮን ዩዋን ቻይና ውስጥ መኪና መግዛት የሚችሉበት እድል አላቸው፡፡ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ቤጂንግ ውስጥ የእጅ ሰዓት ከአምስት ዩዋን እስከ አንድ ሚሊዮን ማውጣታቸውን ታዝቧል፡፡ እናም ጉዳዩ አንድም ከአቅም ጋር ሲያያዝ በሌላ በኩል ደግሞ ከክትትልና ቁጥጥር መዳከም ጋርም ይያያዛል፡፡ በዚህ ዘመን ለፅድቅና ለቡራኬ ብሎ ንግድና ቢዝነስ ውስጥ የሚገባ የለም፡፡ ሁሉም ትርፍ ማግኘትና መጠቀምን አስቦና አልሞ ነው የሚሰማራው፡፡ ስለሆነም የሁለቱ አገሮች መንግሥታትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አስፈፃሚ መሥሪያ ቤቶች ደረጃቸውን ያልጠበቁ እቃዎች በተለይም ጉዳት የሚያስከትሉ ሸቀጦች እንዳይላኩና አገር ውስጥም እንዳይገቡ መከታተልና መቆጣጠር ይኖርባቸዋል፡፡ የቻይናው አምባሳደር እንዳሉት እንዲህ ዓይነት ችግሮች የሚፈቱት የጋራ ጥረትን በማጠናከርና ኃላፊነትን ለመወጣት የተሻለ ዝግጁነት በማሳየት ነው፡፡ እዚህ ላይ ነጋዴዎቻችንና ጥራት አስጠባቂ ተቋማት፣ ጉምሩክና ንግድ ሚኒስቴርን መሰል መሥሪያ ቤቶች ትልቅ የቤት ሥራ እንዳለባቸው ግልፅ ይመስላል፡፡ “እድሜ ለጉምሩክ” እየተባለ በየአደባባዩ የሚሸጠው እቃና ሸቀጥ ጉዳይም ሊታሰብበት የሚገባ ነው፡፡ አንዳችም ጥቅም የማይሰጡ ወይንም ከወጣባቸው ገንዘብ አንፃር በጥቂቱ እንኳ ለአገልግሎት የማይውሉ ባትሪ ድንጋዮች፣ ቻርጀሮች፣ ሶኬቶች እስከሪብቶዎችና ሌሎችንም ሸቀጦች በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ቻይና “አዲሷ የአፍሪካ ቅኝ ገዥ ሆነች “ ስለሚለው የምዕራቡ ዓለም መገናኛ ብዙኃን ውግዘትና ውንጀላ በተመለከተም የቻይናው አምባሳደር ብዙም ለውጥ የማይታይበትን አገራዊ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መሠረት አድርገው ነው ለማብራራት የሚሞከሩት፡፡ አምባሳደሩ እንዳሉት ቻይና ለታዳጊ አገሮች ልማት መፋጠን ተገቢውን እገዛ ከማድረግ ወደ ኋላ አትልም፡፡ ቅኝ ግዛት የሚገለፀው በባሪያ ንግድ፣ አገሮችን በመውረርና በመበዝበዝ፣ እንዲሁም ነፃነታቸውን በመጋፋት ነው፡፡ ቻይና ደግሞ በጋራ መጠቃቀም መደጋገፍ ላይ የተመሠረተ ፖሊሲ ነው የምትከተለው፡፡ ከታዳጊ አገሮች ለምትገዛው ነዳጅና ማዕድንም የዓለም ገበያን መሠረት ያደረገ ዋጋ ትከፍላለች እንጂ ታዳጊ አገሮችን የሚጐዳ ስውር አሠራር አትከተልም፡፡ በመጨረሻም የ200 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በጠየቀው፣በቻይና መንግሥት ሙሉ ወጪው በተሸፈነው፣ ለአፍሪካ በስጦታ እንደተበረከተ በተገለፀውና ከ40 ዓመታት በፊት ቻይና አፍሪካ ውስጥ ከገነባችው የታንዛራ ፕሮጀክት በኋላ ትልቅ በተባለው ፕሮጀክት ማለትም በአፍሪካ ኅብረት የጉባዔ ማዕከል ምረቃ ሥነሥርዓት ላይ ፕሬዚዳንት ሁጂን ታዎ አለመገኘታቸውን በተመለከተም አምባሳደሩ ጥቂት ብለዋል፡፡ ወቅቱ የቻይና አዲስ ዓመት የሚከበርበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የቻይናው ፕሬዚዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር የላቀ አገራዊ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ እርግጥ ነው የቻይና ከፍተኛ ባለሥልጣኖች ትልቁን የቻይና ክብረ በዓል “ስፕሪንግ ፌስቲቫል” የሚያሳልፉት በኋላቀር አካባቢዎች ከሚኖሩ ምስኪን የአገሪቱ ዜጐች ጋር ስለሆነ ለአፍሪካ ኅብረት የጉባዔ ማዕከል ምረቃ ፕሬዚዳንቱም ሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አለመምጣታቸው ብዙም አነጋጋሪ አይሆንም፡፡ በዚያ ላይ የቻይናው ፕሬዚዳንት በሥልጣን ዘመናቸው በ23 የአፍሪካ አገሮች ኦፊሴላዊ ጉብኝት የማድረጋቸው እውነታ የልማት አጋርነታቸውን የሚያጐላላቸው እንጂ የሚያሳንስባቸው አይሆንም፡፡ ጠቅለል ባለ አገላለፅ በዚህ ወሳኝ ወቅት የቻይና አጋርነት ለአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ወሳኝ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ የምዕራቡ ዓለም ከገባበት ቀውስና አጣብቂኝ ለመውጣት የቻይናን ድጋፍ መጠየቁ አይቀሬ እየሆነ ነው፡፡ በተያያዥነት ባለፉት 30 ዓመታት የታየውና ወደፊትም ለተወሰኑ ዓመታት እንደሚቀጥል ከሚጠበቀው የቻይና ተአምራዊ እድገት ዓለም ብዙ መማር ይችላል፡፡ እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ ካፒታሊዝም ወደ ውድቀት አፋፍ እየተንደረደረ ባለበት ወቅት ቻይና እውነተኛ የልማትና የእድገት ምሳሌ ልትሆን ትችላለች ወይ? የሚለው ነው፡፡ ከዴሞክራሲ ከሰብአዊ መብትና ከመልካም አስተዳደር ጋር በተገናኘ መልኩ አገራትና መንግሥታት የሚከተሏቸው የየራሳቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች አሏቸው፡፡ እርግጥ ነው ከቻይና ፈጣን እድገትና ተአምራዊ ለውጥ ብዙ መማር ይቻላል፡፡ ነገር ግን ቻይናን መሆን ደግሞ የሚቻል ላይሆን ይችላል፡፡ ስለሆነም አገሮች ከራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የተጣጣመ የእድገትና የለውጥ ስትራቴጂ ቢከተሉ ይመረጣል፡፡ በጋራ እድገትና ተጠቃሚነት መርህ ላይ በመመሥረትም ከሌሎች አገሮችና መንግሥታት ጋር ተባብረውና ተደጋግፈው ቢሠሩ ሕዝባቸውን ተጠቃሚ ያደርጋሉ፡፡ አትራፊም መሆን ይቻላቸዋል፡፡
ሪፖርተር
ቀን 2012-01-25 00:00:00 |