«ለዘላቂ ልማት ግቦች ስኬት የተሻለ ጥረት ያስፈልጋል» - ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ Featured

29 Sep 2015

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ የዘላቂ ልማት ግቦችን አጽድቋል፤

 

ኒውዮርክ (ኢዜአ)፦ የምዕተ- ዓመቱን የልማት ግቦች አፈጻጸም መነሻ በማድረግ ለዘላቂ ልማት ግቦች ስኬት የተሻለ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለፁ። ላለፉት አስራ አምስት ዓመታት ሲያገለግሉ የነበሩትን የሚሌኒየሙን የልማት ግቦች የሚተኩ 17 ዓቢይና 169 ንዑሳን ግቦችን ያካተቱት የዘላቂ ልማት ግቦች ፀደቁ።

በኒውዮርክ 70ኛ ዓመት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ በመሳተፍ ላይ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ባደረጉት ንግግር፤ የድህረ 2015 የዘላቂ ልማት ግቦች ለዓለም፤ በተለይም ለአፍሪካ የተለየ ትርጉም እንዳላቸው አመልክተዋል።

«መጪው ጊዜ ከድህነት ጋር ለመሰነባበት የምንሰራበት፣ የዜጎች ፍላጎት የሚሟላበትና የዓለም ኢኮኖሚያዊና፣ ፖለቲካዊ ማዕቀፍ የሚቀየርበት ይሆናል» ብለዋል። ከዚህም ቀድሞ ሲተገበሩ የነበሩትን የምዕተ ዓመቱን የልማት ግቦች ስኬትና ችግሮች መነሻ በማድረግ ለአዳዲሶቹ ግቦች የተሻለ ትግበራና ውጤት ሊኖረን እንደሚገባም ተናግረዋል።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ገለፃ፤ በአሁኑ ወቅት በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ በድህነት ላይ ይገኛል፤ ከ800 ሚሊዮን በላይ የዓለማችን ነዋሪም በቂና ተመጣጣኝ ምግብ አያገኝም። እነዚህና ሌሎችም የዓለም አቀፍ ማነቆዎችን በማስወገድና የተሻሉ ስራዎች በመተግበር የሚሊዮኖችን ህይወት ማትረፍ ይገባል። ኢትዮጵያ ድህነትን ለመቀነስ እየሄደችበት ያለውን መንገድም አሳይተዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ ባን ኪ ሙን፤ «ግቦቹን በአጥጋቢ ሁኔታ በመፈጸም የታሰበው እንዲሳካ ዓለም ሊረባረብ ይገባል ሲሉ» ጥሪ አቅርበዋል። «ፍላጎታችን በሁሉም የዓለም ክፍል የሚገኝ ዜጋ ጤንነቱና ደህንነቱ ተጠብቆ በሠላም ሲኖር ማየት ነው» ብለዋል።

የሮማው ሊቀጳጳስ ፖፕ ፍራንሲስም፤ የዓለም ሰቆቃ እንዲያበቃ፣ እኩልነት እንዲሰፍን፣ የአካካቢ ጥበቃ እንዲጠናከርና መንግሥታት ለማኅበራዊ ፍትህና ሠላም እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ባለፉት 15 ዓመታት በማደግ ላይ ባሉ አገራት ሲተገበር የቆየው የምዕተ ዓመቱ የልማት ግብ በመጪው ታህሳስ ሲጠናቀቅ አዲሱ የድህረ 2015 የዘላቂ ልማት ግቦች አጀንዳ ጥር ላይ ወደ ስራ ይገባል። ግቡን ለማሳካት 38 ትሪሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ሲያስፈልግ ይህን ለማገዝም የተለያዩ አገራትና ተቋማት በአዲስ አበባ በተካሄደው ሦስተኛው የፋይናንስ ለልማት ጉባኤ ላይ ቃል መግባታቸው ይታወሳል።

አገራቱ በመጪው ህዳር በፈረንሣይ መዲና ፓሪስ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ተገናኝተው መፍትሔ ባሏቸው ጉዳዮች ላይ ከመግባባት ይደርሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም በጉባኤው ተገልጿል።

በዘላቂ የልማት ግቦች ውስጥ ከተካተቱ 17 ዓቢይ ግቦች መካከል ድህነትንና ረሃብን ማጥፋት፣ የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ፣ መልካም ጤንነት፣ የጾታ እኩልነትን ማስፈን፣ ለዜጎች ንጹህ ውሃን ማቅረብ፣ ሠላምና ፍትህን ማምጣት፣ ጠንካራ ኢንዱስትሪዎችን መገንባት እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት ከሰባት ቢሊዮን በላይ የደረሰው የዓለም ህዝብ ቁጥር ከ35 ዓመታት በኋላ በሁለት ቢሊዮን ዕድገት እንደሚኖረው ይገመታል። ይህም አሁን በዓለም ላይ በሰፊው የሚታየውን ፍትሀዊ ያልሆነ የሀብት ክፍፍልና የኑሮ ውድነት ይበልጥ ያባብሰዋል የሚል ስጋት አስከትሏል። ችግሩ በተለይም በማደግ ላይ ባሉ አገራት ተባብሶ ይታያል። ስጋቱን ለመቅረፍና ሁሉም በፍትሃዊነት የሚኖርባትን ዓለም ለመፍጠር 17 ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና አካባቢያዊ ጉዳዮችን የያዘ የዘላቂ ልማት አጀንዳ በቀጣዮቹ 15 ዓመታት ሊተገበር ዝግጁ ሆኗል።

ላለፉት አስራ አምስት ዓመታት ሲያገለግሉ የነበሩትን የሚሌኒየሙን የልማት ግቦች የሚተኩ 17 ዓቢይና 169 ንዑሳን ግቦችን ያካተቱት የዘላቂ ልማት ግቦች (አጅንዳ) ፀድቀዋል።

የተባበሩት መንግሥታት 193 አባል አገራት በኒውዮርክ ያጸደቁትን የልማት ማዕቀፍ የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ ባን ኪሙን «ዓለም አቀፍ፣ ሁሉን አቀፍና ሽግግራዊ ርዕይ» ብለውታል።

«አዲሱ አጀንዳ መሪዎች በየትኛውም ክፍለ ዓለም ላሉ ሕዝቦች የገቡት ቃል ነው፤ ለሕዝብ፣ ድህነትን ጨርሶ ለማስወገድና ለጋራ መኖሪያችን መሬት የተገባ ቃል ነውሲሉም አክለው ገልፀዋል።

«ዓለማችንን መቀየር፣ የ2030 የዘላቂ ልማት አጀንዳ» የጸደቀው የልማት ማዕቀፍ ይፋዊ መጠሪያ ሲሆን፤ ግቦቹን ከማጽደቅ ባለፈ ሁሉም የዓለም ሀገራት ለተግባራዊነቱ ጠንክረው መሥራት እንዳለባቸውም ባን ኪሙን አስረድተዋል።

ባለፈው ሐምሌ የዓለም መሪዎች አዲስ አበባ ላይ ተሰባስበው የዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት የሚያስፈልገውን የገንዘብ መጠን ማሰባሰብ በሚቻልበት መንገድ ላይ ከስምምነት ደርሰው እንደነበር ይታወሳል።

የወቅቱ የዓለም አሳሳቢ ስጋት በሆነው የአየር ንብረት ለውጥ ላይም በህዳር መጨረሻ በፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ ተገናኝተው የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ ከመግባባት ላይ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0002770766
TodayToday790
YesterdayYesterday2274
This_WeekThis_Week10297
This_MonthThis_Month100001
All_DaysAll_Days2770766

       በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።