«የአፍሪካውያንን ጥቅም የማያስከብር ኀብረት ፋይዳ የለውም»- አዲሱ የአፍሪካ ኀብረት ሊቀመንበርና የጊኒ ፕሬዚዳንት አልፋ ኮንዴ Featured

31 Jan 2017

የአጀንዳ 2063 ስኬት በወጣቶች ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ላይ ይወሰናል

የአፍሪካ ኀብረት የአፍሪካውያንን መብቶችና ጥቅሞች ለማስጠበቅ ከመቼውም በበለጠ ጊዜ በትኩረት መስራት እንዳለበት የጊኒ ፕሬዚዳንትና አዲሱ የአፍሪካ ኀብረት ተመራጭ ሊቀመንበር አልፋ ኮንዴ አስታወቁ፡፡ የበለፀገች አፍሪካን ዕውን ለማድረግ የተቀረጸው አጀንዳ 2063 ስኬታማ የሚሆነው የአህጉሪቱ ወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ሲረጋገጥ መሆኑን ተሰናባቿ የአፍሪካ ኀብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ገለጹ፡፡

በአፍሪካ ኀብረት አዳራሽ ትናንት የተጀመረው የኀብረቱ 28ኛው ጉባኤ የጊኒ ፕሬዚዳንት አልፋ ኮንዴን የወቅቱ የአፍሪካ ኀብረት ሊቀመንበር አርጎ መርጧቸዋል፡፡ ሊቀመንበሩ ለጉባዔው ባደረጉት የመጀመሪያ ንግግር እንደገለጹት፤ የአፍሪካውያንን ጥቅምና መብቶች የማያስከብር ኀብረት ፋይዳ የለውም፡፡ በመሆኑም የአፍሪካ ኀብረት ከመቼውም በላይ ለአፍሪካውያን መብትና ጥቅም መከበር ሊሰራ ይገባዋል፡፡

እንደ ሊቀመንበሩ ገለጻ፤ አፍሪካ በልማትና ዕድገት ጎዳና ላይ ብትሆንም አሁንም አብዛኛው የአፍሪካ ህዝብ በድህነትና በሰላም እጦት እየተፈተነ ይገኛል፡፡ በመሆኑም አፍሪካውያን መሪዎች ለአህጉሪቱ ህዝብ ሰላም መከበርና ልማት መፋጠን በፓን አፍሪካኒዝም ስሜት በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል፡፡

ለአፍሪካ ልዕልና የአፍሪካ መሪዎች አስተሳሰብና የአፍሪካውያን መተባበር መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን የጠቆሙት የኀብረቱ የወቅቱ ሊቀመንበር፤ በአፍሪካ ለሚከናወነው ሁለንተናዊ የልማትና የሰላም ተግባር ከዓለምአቀፍ ድርጅቶችና ተቋማት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት፡፡ የአህጉሪቱ ድምጽ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሳይቀር ችላ እየተባለ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህ ዙሪያ ጠንካራ ሥራ ማከናወን እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል፡፡

‹‹አፍሪካውያን ሲተባበሩ ድምጻቸው ይበልጥ ተሰሚነት ይኖረዋል›› ያሉት አልፋ ኮንዴ፤ አፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ ልዩ ተቋማት ውስጥ ያላት አነስተኛ ውክልናና ተሳትፎ እንዲለወጥ የአህጉሪቱ መንግሥታት የተቀናጀ ጥረት ሊያደርጉ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ በዚህ መልኩ በመረባረብና ዲፕሎማሲዊ ትብብራቸውን በማሳደግ የአህጉሪቱን የላቀ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል፡፡

እንደ ሊቀመንበሩ ገለጻ፤ አፍሪካ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግሯን በኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመተካት ለኃይል ልማት ተቀዳሚ ትኩረት ልትሰጥ ይገባታል ፡፡ የኃይል ፍላጎቷ ለኢንዱስትሪያላይዜሽን ጉዞዋ ብቻ ሳይሆን ለህዝቦቿ የተሻለ ኑሮ ጭምር አጋዥ ሊሆን ይገባል ፡፡ 700 ሚሊዮን ያህል አፍሪካውያን የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ ያልሆኑ በመሆናቸውም የኃይል ፍላጎቷን ከታዳሽ ኃይል ልታሟላ ይገባታል፡፡

ተሰናባቿ የኀብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ዶክተር ንኮሳዛና ዲላሚኒ ዙማ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ አፍሪካ ሰላሟና ፀጥታዋ የተጠበቀ እንዲሁም የበለጸገች አፍሪካን ማየት የሚቻለው እምቅ አቅም ያላቸው የአህጉሪቱ ወጣቶች በልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ ንቁና ቀጥተኛ ተሳትፎ ሲያደርጉ ብቻ ነው፡፡ ይህን አቅም ጥቅም ላይ ለማዋልም የአህጉሪቱ መንግሥታት ለወጣቶች ልዩ ዕድሎችንና ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠርና የመተግበር ኃላፊነት አለባቸው፡፡ አጀንዳ 2063ን ለማሳካት የሚደረገው ርብርብ ይሄንኑ ይጠይቃል ፡፡

ከአህጉሪቱ ህዝብ መካከል 200ሚሊዮን ያህሉ ከ15 እስከ 24 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ እንደሚገኝ የጠቆሙት ዶክተር ዙማ፤ ሁኔታው ለአፍሪካ ልማት ተጨማሪ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ነው ያመለከቱት፡፡ይህን ሀብት ባግባቡ መጠቀም እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ ለአፍሪካ ወጣቶች የትምህርትና የጤና አገልግሎት ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ፣ የሥራ ዕድል ሊፈጠርላቸው እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት፡፡

ጠንካራ የፓን አፍሪካኒዝም ስሜት ለወጣቶች ተሳትፎ ትልቅ ግብዓት እንደሚሆንም ጠቁመው ፣የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የሲቪክ ማኅበራት የማይተካ ሚና እንዳላቸውም ነው ያመለከቱት ፡፡

እንደ ተሰናባቿ ሊቀመንበር ገለጻ፤ በአፍሪካ ካለው የሥራ አጥ ቁጥር 60 በመቶውን የሚሸፍኑት ወጣቶች ናቸው፡፡ በአህጉሪቱ በትምህርት ዝግጅትና በሥራ ፍላጎት መካከል ያለውን ክፍተት የሚሞሉ የልህቀት ማዕከላት ያስፈልጋሉ ፡፡ አገራት ይህን ሲያከናውኑም ወጣቶች በበኩላቸው የመማር፣ የመደራጀትና የመሳተፍ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በበኩላቸው፤ አፍሪካ የቀጣይ ዕድገቷ መሰረት ወጣቱ መሆኑን አመልክተው፣ አፍሪካውያን በትምህርትና ሌሎች ዘርፎች ላይ ኢንቨስት በማድረግ ወጣቱን ማብቃት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል፡፡

አፍሪካ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበች መሆኗን የገለጹት ዋና ፀሐፊው፤ ወጣቶችን ማብቃትና ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ የዘላቂ ልማትና ዕድገት ዋስትና እንደሆነም ነው የተናገሩት ፡፡ በወጣቱ ላይ መስራት በአህጉሪቱ ለሚታየው የሰላም እጦትና ድህነት መፍትሄ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

እንደ ዋና ፀሐፊው ማብራሪያ፤አፍሪካውያን ከዚህ ጎን ለጎንም ሴቶችን በመደገፍና በማብቃት ልማታቸውን ብቻ ሳይሆን ሰላማቸውን ለማስፈንም መትጋት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለአፍሪካውያን የሰላም እጦት ምክንያት የሆኑ የዘር፣ የድንበርና የስልጣን የግጭት ምክንያቶችን በመግታትም ዴሞክራሲን በማጎልበት ሰላማዊ የስልጣን ሽግግርን በማምጣት እና መፈንቅለ መንግሥትን በማስቀረት ለሰላማቸው ሊሰሩ ያስፈልጋል፡፡

የቻድ ፕሬዚዳንትና ተሰናባቹ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ኢድሪስ ዴቢ በበኩላቸው ‹‹አፍሪካ በርካታ ችግሮች እየገጠሟት ቢሆንም፣ በወጣቶቿ ተሳትፎ በአስተማማኝነት ትሻገራቸዋለች›› ሲሉ ተናግረዋል ፡፡ የአህጉሪቱ ወጣቶች ኀብረቱ ይፋ በሚያደርጋቸውና በሚተገብራቸው የልማትና የዴሞክራሲ መርሐ ግብሮች ውስጥ በንቃት በመሳተፍ የአህጉሪቱን ዕድገት አስተማማኝ ደረጃ ላይ ማድረስ እንደሚኖርባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

28ኛው የአፍሪካ ኀብረት የመሪዎች ጉባዔ የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ እየመከረ ይገኛል፡፡

 

አንተነህ ቸሬ እና ወንድወሰን ሽመልስ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0002770771
TodayToday795
YesterdayYesterday2274
This_WeekThis_Week10302
This_MonthThis_Month100001
All_DaysAll_Days2770771

       በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።