«ከሚያለያዩን ይልቅ የሚያገናኙን ዕሴቶች ይገዝፋሉ» - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ Featured

14 Apr 2018
«ከሚያለያዩን ይልቅ የሚያገናኙን ዕሴቶች ይገዝፋሉ» - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ፎቶ ፀሐይ ንጉሴ

በብሔራዊ ቤተመንግሥቱ በር ላይ በርካታ ጋዜጠኞች ይታያሉ፡፡ ሰዓቱ ገና 11፡00 ሰዓት ቢሆንም፣ ከግቢው በር አንስቶ የሚታዩት ግዙፍ ዛፎች በወቅቱ ከነበረው ደመና ጋር ተዳምረው አካባቢውን አጨልመውታል፡፡

ጥበቃዎች የጋዜጠኞች ስም እየጠየቁ በእጃቸው ከያዙት ወረቀት ላይ የተፃፈውን ስም ዝርዝር በማናበብ ማስገባት ቢጀምሩም፣ እንዳለመታደል ሆነና ስማችሁ ባለመኖሩ አትገቡም ከተባሉ ጋዜጠኞች መካከል ሆንን፡፡ ከብዙ የስልክ ግንኙነት በኋላ ለአንድ ሰዓት ደጅ ጠንተን ግብዣውን ለመቋደስ ተፈቀደልን፡፡
በቤተመንግሥቱ ሰፊ አዳራሽ የምግብ ብፌ ተደርድሯል፡፡ ከስር ነጭ ሸሚዝ ለብሰው ከላይ ጥቁር ኮት የደረቡት አስተናጋጆች የአፕል፣ የብርቱካንና የማንጎ እንዲሁም የተለያዩ የፍራፍሬ ጁሶችን ለተጋባዦች እያቀረቡ ናቸው፡፡
የሃይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ ነባር የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ኃላፊዎች፣ የሲቪክ ማህበራት መሪዎች፣ ታዋቂ ደራሲያን እና የተለያዩ አርቲስቶች በአዳራሹ ታድመዋል፡፡ አንዳንዶቹ ቆመው አንዳንዶች ደግሞ ተቀምጠው ጁስ እየተጎነጩ በቡድን በቡድን ሆነው ይወያያሉ፡፡
ዋነኛው የመታደሚያ አዳራሽ ተከፈተናም ሁሉም ወደዚያው አመራ፡፡ የሚጠበቁት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቦታው እስከሚደርሱም አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን ማነጋገር ጀመርን፡፡
ፖለቲከኛው ዶክተር መረራ ጉዲና «ከዚህ ቀደም ብዙ ዕድሎች አምልጠዋል፡፡ ንጉሡ ሲወርዱ፤ ደርግ ሲወርድ፤ የ1997ቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች በሙሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አምልጠዋል፡፡ ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምርጫ አራተኛ ዕድል ነው፡፡» ካሉ በኋላ ይህኛውም ያመልጣል ያሚል ስጋት እንዳደረባቸው ገለጹልን፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዕድሉን ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን በመጥቀስም፣ ስጋታቸው ኢህአዴግ ምን እያሰበ ነው? የሚለው ላይ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ኢህአዴግ ለለውጥ ተዘጋጅቷል? የሰፋ መድረክ፤ ለአንድ መቶ ሚሊዮን ሕዝብ የሚሆን ዴሞክራሲ አለው ወይ የሚለው? በአዕምሯቸው እንደሚመላለስ ያመለክታሉ፡፡
በፖለቲካው ውስጥ ለዓመታት ባደረጉት ተሳትፎ የሚታወቁት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ «የፖለቲካ ፓርቲዎች ተንቀሳቅሰው ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ በሕገመንግሥቱ የተቀመጡ መብቶች መከበር አለባቸው» ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
«የኢህአዴግ ርዕዮተ ዓለም ሕገመንግሥቱን ማስፈፀም የሚያስችል አይደለም ያሉት ፕሮፌሰር በየነ፣ የመድብለ ፓርቲ ሥልጣንን ለፕሮፓጋንዳ ሳይሆን ፍትሃዊ በሆነ ምርጫ ሥልጣን ለማጋራት መዋል ያስፈልጋል ሲሉም ይገልጻሉ፡፡
«የኢህአዴግ ርዕዮተ አለሙ እስካልተለወጠ ድረስ የጠቅላይ ሚኒስትር ለውጥ ብቻውን ተፎካካሪ ፓርቲዎች ዕድሉን እንዲያገኙ አያስችልም፡፡» በማለት ዋነኛውና የሚፈቅደው አካል የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
በእራት ግብዣው ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፤ አገሪቷ በቀጣይ የምታካሂደው አገራዊ ምርጫ ሕገመንግሥቱን በተከተለ መልኩ ከልብ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ነፃ እንዲሆን ፓርቲያቸው አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ አስታወቁ፡፡
ዴሞክራሲን ማስፈን አለመቻል ሃሳብ ከመለዋወጥ ይልቅ ጥይት ለመለዋወጥ መንስኤ ሆኖ ማለፉን የኢትዮጵያ ታሪክ እንደሚመሰክር ጠቅሰው፣ ከዚህ በኋላ ግን በመወያየትና በመደማመጥ ማመን እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት፡፡ «የዕውነት፣ የዕውቀትና የቀናነት ብቸኛው ባለቤት እኔ ነኝ፤ አገር ወዳድና ለአገር አሳቢ እኔ ብቻ የሚል አካሄድ ተቀባይነት አይኖረውም» ብለዋል፡፡
«ኢትዮጵያን ማስተዳደር ውስብስብና ከባድ ኃላፊነት ነው፡፡ የምንታገልላቸው ፓርቲዎች ከልባችን ብንወዳቸውም ሁሉንም ነገር በድርጅት መነፅር ብቻ እንይ ካልን አገራችንን እንጎዳለን» ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሁሉም አገር ማስቀደምን አስመልክቶ ሊያስብ ይገባል ሲሉም ያሳስባሉ፡፡
«የሚያለያዩን ነገሮች ቢኖሩም የጋራ እሴቶቻችን ብዙ ናቸው» ያሉት ዶክተር አብይ፤ የታዋቂውን የነፃነት አርበኛ የኔልሰን ማንዴላን ሃሳብ በመጥቀስም «ሰዎች ጥላቻ የሚሰማቸው መጥላትን ተምረውት ነው፡፡ እናም ሰዎች ማፍቀርንም ከተማሩ አፍቃሪዎች ናቸው» ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡ ይህ ሃሳብ በሁሉም ልብ ውስጥ መታተም እንዳለበትም ነው ያመለከቱት፡፡ «ትናንት ያለፈውን በመማሪያነት በመውሰድ የተሻለች አገር ለመገንባት በጋራ መስራት ይጠበቅብናል» ሲሉ ይገልጻሉ።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሕዝብ ፍላጎት ማንፀባረቂያ ናቸው፡፡ ሕዝብንና መንግሥታዊ ሥልጣንን የሚያገናኙ ድልድዮች በመሆናቸውም በተለይም ፓርላሜንታዊ ሥርዓት ሊሳካ የሚችለው በፓርቲዎች ቀጥተኛና ሙሉ ተሳትፎ በመሆኑ ተሳትፏቸው የግድ ነው፡፡
«የዴሞክራሲ ሥርዓት ምሰሶ የሕግ የበላይነት፣ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብቶች ናቸው» ያሉት ዶክተር አብይ፤ ዴሞክራሲ አለ ከተባለ ዜጎች በአገራቸው ጉዳይ ላይ ውሳኔ ሲሰጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በተወካዮቻቸው አማካኝነት ድምፅ ሊኖራቸው ይገባል» ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ለዚህም የተፎካካሪ ፓርቲዎች ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑንም በመጥቀስ፣ መንግሥት በዚህ በኩል ፅኑ ፍላጎት እንዳለውም አረጋግጠዋል፡፡


ዜና ሐተታ
ምህረት ሞገስ

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0002770767
TodayToday791
YesterdayYesterday2274
This_WeekThis_Week10298
This_MonthThis_Month100001
All_DaysAll_Days2770767

       በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።