About Us

 

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

 

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ከተቋቋመበት ከ1962 .ም ጀምሮ እስከ አሁን የተለያዩ አደረጃጀቶችና አወቃቀሮችን አሳልፏል። በ1969 የማስታወቂያና የማከፋፈያ ተግባራት ለሌላ መምሪያ ተሰጥተው «የኢትዮጵያ ፕሬስ መምሪያ» በሚል መጠሪያ በመምሪያ ደረጃ ለማስታወቂያ ሚኒስቴር ተጠሪ ሆኖ ተደራጀ። በድርጅት ደረጃ እስከ ተዋቀረበት 1987 .ም ድረስ የህትመት ውጤቶችን በማዘጋጀት ማለትም በኤዲቶሪያል ሥራው ብቻ ተወስኖ ቀርቷል። የማስታወቂያና የሥርጭት ሥራዎች በሌላ መምሪያ እየተከናወነ በጐንዮሽ ግንኙነት የኤዲቶሪያል ሥራው በአንድ በኩል፣ የአድቨርቶሪያልና የስርጭት ሥራ በሌላ በኩል ሲከናወን ቆይቷል።

በዚህ ወቅት የግዥ፣ የሰው ኃይል የበጀት ወዘተ. ሥራዎች የሚከናወኑት በማስታወቂያ ሚኒስቴር ስለነበር አደረጃጀቱ ደረጃውን ዝቅ ከማድረጉም በላይ አንድ የህትመት ሚዲያ ተቋም ሊይዝ ይገባው የነበረውን አደረጃጀት ካለመያዙም ባሻገር ስራውን በተቀላጠፈ አግባብ ከመነሻ እስከ መድረሻ ለማከናወን ሲቸገር ቆይቷል። በመሆኑም የማስታወቂያና የሥርጭት ሥራው ተገንጥሎ አስፈላጊ ግብአቶች በሌላ አካል እየቀረበለት ውስብስብ በሆነ ችግር ውስጥ እስከ 1987 አጋማሽ ዘልቋል።

1987 .ም የፀደቀው የኢፌዲሪ ዴሞክራሲያዊ ሕገመንግሥት በስራ ላይ መዋል ለመረጃ ነፃነት ትግበራው አዲስ መንገድ ከመክፈቱ ባሻገር ድርጅቱ ያሉበትን ችግሮች በመገንዘብ አዲስ አደረጃጀት እንዲፈጠር በር ከፍቷል። በዚሁ መሠረት በመንግሥት ባለቤትነት ስር ያሉ የመገናኛ ብዙሃን በኅብረተሰቡ መካከል ሃሳቦችና አመለካከቶች መንሸራሸራቸውን ለማረጋገጥ እንዲሁም የተቋምና የአሠራር ነፃነት እንዲኖራቸው ለማድረግ አዋጅ ቁጥር 113/1987 ተደነገገ። በኋላ ይህንኑ አዋጅ በማሻሻል በወጣው አዋጅ ቁጥር 75/1989 ላይም የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በአዲስ መልክ ተቋቋመ።ይህ አዋጅ በወቅቱ በርካታ ለውጦች ያመጣ ሲሆን እስከ አሁንም ድረስ ለ 18 ዓመታት በሥራ ላይ ውሏል።

በአወቃቀሩም ሥራ አመራር ቦርድ፣ ዋና ሥራ አስኪያጅና ሌሎች ሠራተኞች ሲኖሩት የቦርዱ ተጠሪነትም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው። ይሁንና ከ18 ዓመታት በኋላ ግን አገራችን እየተገበረችው ካለው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አንፃር እንዲሁም ሁሉን አቀፍ በሆነው የህዳሴ ጉዞ የሚታየው ፈጣን ዕድገት የህትመት ሚዲያው ዘርፍ የሚመጥን ሆኖ ባለመገኘቱ አዋጁም ሆነ የህትመት ሚዲያው አደረጃጀትና አሠራር እንደገና መቃኘት ያለበት መሆኑ ታምኖበታል።

          በተጨማሪም በድርጅቱ ማቋቋሚያ አዋጅ አንቀጽ አምሰት ንዑስ አንቀጽ 6 እና 11 ለሥራው አስፈላጊ የሆኑ የህትመት አገልግሎቶችን ማቋቋም እንደሚችል እና የፕሬስ አገልግሎት ስለሚስፋፋበትና በተስማሚ ቴክኖሎጂ የሚደራጅበትን ሁኔታ በማጥናት ሃሳብ አቅርቦ እንደሚያስፈቅድ በግልጽ የተደነገገ በመሆኑ ይህንኑ መነሻ በማድረግ ኮርፖሬት የህትመት ሚዲያ አዋጭነት ጥናት በማካሄድ ወደ ኮርፖሬት ለመሸጋገር የተለያዩ ጥረቶች በመደረግ ላይ ይገኛሉ።

 

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የአሁኑ ተቋማዊ ገፅታ

 

      የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ብቸኛ የህዝብ የኅትመት ሚዲያ ተቋም ነው። የድርጅቱ ታሪካዊ አመጣጥ በኢትዮጵያ ስነ ጽሑፍ አጀማመርና የሕትመት ቴክኖሎጂ ወደ አገሪቱ መግባት ጋር በእጅጉ ይያያዛል።

ኢትዮጵያ የራሷ ቋንቋና ሆሄያት ያላት ብቸኛ አፍሪካዊት አገር ናት። ለሕትመት ዘርፍ መሠረት የጣሉ የበርካታ እሴቶች ባለቤት ነች። በብራና የተፃፉ መፃሕፍትን ጨምሮ በእጅ እየተፃፈ በየሳምንቱ በአራት ገፅ ይወጣ የነበረው የአዕምሮ ጋዜጣ ለአሁኑ የሕትመት ሚዲያ ዘርፍ አሻራቸውን ጥለዋል።

      ጋዜጣና መጽሔቶችን መጽሐፍትንና ሌሎች ዕትሞችን በእጅ ፅፎ ማሰራጨት እጅግ ከባድ ሥራ በመሆኑ ሥራውን የሚያቀል የሕትመት መሣሪያዎች ወደ አገራችን መግባት ግድ ሆኖ መገኘቱ በተለያየ ጊዜ በተለያየ የአገራችን ክፍል ቀላል የማተሚያ ማሽኖች መግባታቸው በእጅ ይፃፈ የነበረውን በእጅ የሕትመት መሣሪያ እንዲከናወን መደረጉ ለአገራችን የሕትመት ሚዲያ ከፍተኛ አስተዋፅዎ አበርክቷል።

     በአንዳንድ ጥናቶች ተመዝግበው የሚገኙት የታሪክ ድርሳናት እንደሚያስረዱት በ1857 የእጅ ሕትመት መማሪያ መግባቱን በ1859 የመጀመሪያው የፕሪንት ሚዲያ በሀገራችን መጀመሩን በ1874 ኩሪያለ አፈትሪ የተሰኘ መጽሔት ለመጀመሪያ ጊዜ በኢጣሊያ ቋንቋ መታተሙን የዘገቡ ሲሆን በ1893 አባማሪ በርናርድ በተባሉ ሚሲዮናዊ ላ ሲሜዩኒ ዲ ኢትዮጵ የተባለ ሣምንታዊ ጋዜጣ በአማርኛና በፈረንሳይኛ ሐረር ውስጥ ሲያሳትሙ እንደነበር ተጠቅሷል።

«የዜና ማሰራጫ ዘዴ በኢትዮጵያ» በሚል ርዕስ በ1959 በማስታወቂያ ሚኒስቴር ሥነ-ጽሑፍ ማዘጋጃና በውጭ ቋንቋ በሚታተሙ ጋዜጦችና መጽሔቶች ክፍል የተዘጋጀ ጥናታዊ ጽሑፍ እንደሚያስረዳው አባ በርናርድ «ላ ሰሜዮኒ ዲ ኢትዮጲ» የተባለውን ጋዜጣ በሐረር ማሳተም ከጀመሩ ከሁለት ዓመት በኋላ እንድሪአስ ኤ ካቫዲ የተባለ የግሪክ ነጋዴ የመጀመሪያውን የአማርኛ ቋንቋ ጋዜጣ ማሳተም መጀመራቸው ተዘግቧል።

ይህ ጋዜጣ አዕምሮ የሚል መጠሪያ የነበረው ሲሆን በህትመት መሣሪያ በመታተሙ ቅጅው በየሳምንቱ ወደ ሁለት መቶ ከፍ ብሏል። የአገራችን የሕትመት ሚዲያ በዚህ መንገድ እያደገ መጥቶ «ኢትዮጲ ኮሜርሲያል»«ከሰቴ ብርሃን» «አጥበያ ኮኮብ» የተባሉ ሳምንታዊ ጋዜጦች እስከጣሊያን መረራ ሲታተሙ ቆይተዋል።

ከወረራው በኋላ የሕትመት ሚዲያው በመድከሙ ከባንዲራችን ጋዜጣ በስተቀር የቀሪዎቹ ሕትመት ቆሟል። ከድል በኋላ የሕትመት ሚዲያው እንደገና በማንሰራራት በትግርኛና በአረብኛ፣ በጣሊያንኛ፣ በአርብኛና በፈረንሳይኛ፣ በአማርኛ፣ በትግርኛና በአማርኛ፣ በእንግሊዝኛ፣ በአማርኛ የሚታተሙ በርካታ ጋዜጦች ከ1934 በኋላ ታትመዋል።

የሕትመቶቹ ባለቤት ጽሕፈት ሚኒስቴር፣ ማስታወቂያ ሚኒስቴር እና የአገር ፍቅር ማህበር ነበሩ። እነኝህን ህትመቶች አሰባስቦ እንዲያስተዳድር የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በ1962 .ም ተቋቋመ።

በውል ባልታወቀ ጊዜ (አንዳንዶች 1956 ይሉታል) ድርጅቱ በማስታወቂያና መርሐ ብሔር ሥር ሆኖ በመምሪያ ደረጃ ጋዜጦችና መጽሔቶችን ሲያስተዳድር ተጨማሪ ህትመቶችን ሲያዘጋጅና ሲያሳትም ቆይቶ በ1987 .ም በአዋጅ ቁጥር 113/1987 ሕጋዊ ሰውነት ያለው የሕትመት ሚዲያ ተቋም ሆኖ በመቋቋሙ ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ ይገኛል።

የድርጅቱ ዋነኛ ዓላማ መንግሥት የሚያወጣቸውን አዋጆች ፖሊሲዎች እንዲሁም የሚፈጽማቸውን ተግባራት የማብራራት፣ ሕዝቡ የሚያነሳቸውን ቅሬታዎችና ፍትሃዊ ጥያቄዎች የማስተጋባት በሕዝብና መንግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት የማጠናከርና ሕዝብን በማገልገል፣ የፖለቲካ ኃይሎች ፍትሐዊ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ማድረግ ነው።

 

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ህትመት ውጤቶች

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በአሁኑ ወቅት በአራት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ እንግሊዘኛ፣ ኦሮሚኛና አረቢኛ ) አራት ጋዜጦችን-ሁለት ዕለታዊ (Broad sheet) እና ሁለት ሳምንታዊ ጋዜጦች (Tabloid) እንዲሁም በየሁለት ወሩ የሚዘጋጅ አንድ መጽሔትን እያዘጋጀ ያሰራጫል። ወጥነት ባለው መንገድ ባይሆንም በህትመት ጋዜጠኝነትና አጠቃላይ አሰራሩ ላይ የሚያተኩሩ ጥናቶችን እያስጠና በ«ሕትመት ሚዲያ ጆርናል» ለህትመት እንዲበቁ የሚያደርግ ሲሆን መጽሔቶችና ዓመታዊ መጽሐፎችም በተቋም ደረጃ ይወጣሉ።

 

የአዲስ ዘመን ጋዜጣ

የኢጣሊያ ፋሽስት ወረራ ጦር በአፄ ምኒልክ የጦር ሠራዊትና ለነፃነት ቀናኢ በሆኑት የኢትዮጵያ ጀግኖች በ1888 .ም በአድዋ ጦርነት የደረሰበትን ሽንፈት ለመበቀል የሞሶሎኒ ጦር በ1928 .ም ዳግም ኢትዮጵያን ወረረ። ከ1928-1933 የኢትዮጵያ አርበኞች በዱር በገደሉ ተሰድደው ወራሪውን ጦር መፈናፈኛ እንዳያገኝ ካደረጉት በኋላ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት መገባደዱን ተከትሎ በእናትና አባት አርበኞች ተጋድሎ በመጨረሻም በእንግሊዝ የጦር ኃይል ስትራቴጂያዊ ድጋፍ ኢትዮጵያ ሙሉ ነፃነቷን ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ማረጋገጥ ችላለች።

በወረራው ምክንያት ስደትን የመረጡት የወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ነፃነት መመለሱን ተከትሎ ዙፋናቸው እንደተረከቡ ካከናወኗቸው ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ተግባራት አንዱ መገናኛ ብዙኃን በማደራጀትና በማቋቋም ላይ ያተኮረ ነበር። በዚህም መሠረት ግንቦት 30 ቀን 1933 .ም አዲስ ዘመን በሚለው መጠሪያ የሚታወቀውን ብሔራዊ ጋዜጣ በይፋ ሥራ አስጀምረዋል። የጋዜጣው ስያሜ ንጉሡ አዲስ አበባ ሚያዝያ 27 ቀን 1933 .ም በድል አድራጊነት ሲገቡ ይህ የአዲስቷ ኢትዮጵያ የአዲስ ዘመን መጀመሪያ ነው' ማለታቸውን መሠረት ያደርጋል።

ጋዜጣው ቅዳሜ ግንቦት 30 ቀን 1933 ባለሁለት ገጽ የመጀመሪያ ዕትም ለንባብ ማብቃቱን መረጃዎች የሚጠቁሙ ሲሆን የሥርጭቱ መጠን 10ሺ ቅጂ የጋዜጣው መጠንም አርበ ጠባብ /ታብሎይድ/ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል። እስከ ሰኔ 30 ቀን 1937 .ም ድረስ በታብሎይድነቱ የቀጠለ ሲሆን በመካከሉ አርበ ሰፊ (Brood sheet) እስከሆነበት1940ዎቹ ድረስ በበርሊነየር / መካከለኛ መጠን/ በአራትና ስድስት ገፆች ሲታተም ቆይቷል።

ጋዜጣው በመጀመሪያው እትም ርዕስ አንቀጹ ' የአዲስ ዘመን ጋዜጣ መጀመር' በሚል ርዕስ ባስነበበው ጽሑፍ ' ይህ አዲስ ዘመን ተብሎ የተሰየመው ጋዜጣ ከዛሬ ጀምሮ ወደፊት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የነፃነቱን ሥራ ይሠራ ዘንድ ተመሠረተ' በማለት የተቋቋመበትን ዓላማ ያስረዳል። ርዕስ አንቀጹ በመቀጠልም ' ይህ ጋዜጣ የፕሮፓጋንዳ ጋዜጣ ሳይሆን እውነትን አገልግሎትን ረዳትነትን መሠረት አድርጐ ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ በአዲስ ስራ ተመርቶ እንዲረዳ የቆመ ነው' ቢልም ' አገልግሎት ስንል የኢትዮጵያን ነፃነት ሲመለስ ራሳቸውን መስዋዕት አድርገው የነበራቸውን ጥቅም ሁሉ አስወግደው ለሕዝባቸውና ለአገራቸው ሲሉ የሰው አቅም ሊሸከመው የማይችለውን ድካም ተቀብለው ማናቸውም ሰው ሊያደርገው ያልቻለውን በኢትዮጵያ ሕይወት ውስጥ እስከ ዛሬ ያልታየውን ሥራ ከፍጻሜ ላደረሱ ለንጉሠ ነገሥታችንና ላቆሙት መንግሥት የሚያገለግል እንደሆነ ነው ' በማለትም በዋነኝነት የተቋቋመበትን ዓላማ በግልጽ ይተነትናል።

አዲስ ዘመን ከግንቦት 1933 እስከ ታኅሣሥ 1951 .ም ድረስ በሳምንታዊ መልክ / በአርበ ጠባብ በመካከለኛ በአርበ ሰፊ መጠን/ ሲታተም ከቆየ በኋላ በኢትዮጵያ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን መመሥረቱን ምክንያት በማድረግ በሳምንት ወደ ስድስት ቀን ወደሚታተም ዕለታዊ ጋዜጣነት ሊሸጋገር በቅቷል። ከመስከረም 1 ቀን 1993 .ም ጀምሮ ደግሞ ጋዜጣው ከሰኞ እስከ እሁድ በሳምንት ሰባት ቀናት ወደመታተም ተሸጋግሯል። ከታኅሣሥ 3 ቀን 2004 .ም በኋላም የጋዜጣው መጠን ወደ መካከለኛ ጋዜጣነት / በርሊኒየር/ ዝቅ ያለ ሲሆን / የፊትና ጀርባ ገጾችን በሙሉ ቀለም በማሳተምም ጋዜጣው ከ70 ዓመታት በኋላ መሠረታዊ የአቀራረብ ለውጥ ሊያመጣ በቅቷል።

 

የኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣ

በድርጅቱ ከሚታተሙ የኅትመት ውጤቶች አንዱ የሆነው የእንግሊዝኛው «The Ethiopian Herald » ጋዜጣ መታተም የጀመረው በ1940 .ም ገደማ ነው። (ከአዲስ ዘመን 7 ዓመት ዘግይቶ ማለት ነው) በመካከለኛ ቅርጽ አራት ገጾችን ይዞ መውጣት የጀመረው ይህ ጋዜጣ እንደ አዲስ ዘመን ሁሉ የመንግሥት ዋነኛ ልሳን በመሆን አገልግሏል።

ከሦስት ዓመት ጉዞ በኋላ መጠኑ ወደ አርበ ሰፊ (Brood sheet) ከማደጉ ባሻገር ቋሚ አምዶችን በመክፈት ከሰኞ በስተቀር ሳምንቱን ሙሉ መታተም ቀጠለ። ሁለት ገጽ የዜና ገጽ ሁለት ገጽ ዓምድ እየያዘ በመውጣት እስከ 1990ዎቹ መጀመሪያ ድረስ ዘልቋል። ጋዜጣው ከዚያ ወዲህ ተጨማሪ ሁለት ዓምዶችን አከሉ ገጹን ወደ ስድስት ከማድረሱ ባሻገር ማስታወቂያዎችንም በስፋት እየያዘ አሁንም ከሰኞ በስተቀር በመታተም ላይ ይገኛል።

ኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣ ከአዲስ ዘመን ቀጥሎ በየዕለቱ እየወጣ ያለ የድርጅቱ የኅትመት ውጤት ከመሆኑ ባሻገር በውጭ ቋንቋ የሀገሪቱን ፖሊሲ የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫና የሕዝቡን ፍላጎት ለማንፀባረቅ የሚረዳ ኅትመት ነው። ማኅበራዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ አዝናኝና አስተማሪ ጽሑፎችን ይዞ በመውጣትም ይታወቃል።

 

ዘመን መፅሔት

ዘመን መጽሔት የተመሠረተችው በ1993 .ም ሲሆን በወቅቱም ያላት የገጽ ብዛት 36 ነበር። በወቅቱም መጽሔቱ በሦስት የኢዲቶሪያል ቦርድ አባላት የራሱ ሠራተኞች ሳይኖሩት ነበር የተጀመረው። ሥራዎቹም የሚሠሩት በየዝግጅት ክፍሎች ከነበሩ ጋዜጠኞች ነበር። የሽፋን ገጽም ከለር የነበረ ሲሆን ጠንካራ ሽፋን ነበረው። በይዘት ደረጃም የፖለቲካ የማኅበራዊ እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች የሚጋለጡባቸው እንዲሁም የኪነጥበብ ጉዳዮችን ዘግቦ ነበር።

ከዚያም በኋላ በዝግጅት ክፍል ደረጃ ተዋቅሮ በዋናነትም በፖለቲካ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ሚዛናዊ ዘገባ በማቅረብ በአንባቢያን ዘንድ ተፈላጊ መፅሄት ለመሆን ችላለች ። መጽሔቷም በተለያዩ የለውጥ ጉዞዎች ላይ ያለፈች ሲሆን በየወቅቱ የመሻሻል ሁኔታዎችን በማሳየት ተነባቢነትን የተረፈች ሆናለች ።

 

አልዓለም ጋዜጣ

በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በአረቢኛ የሚታተም ብቸኛው መንግሥታዊ ጋዜጣ ሲሆን አዲስ ዘመን መታተም ከጀመረ (1933) ወዲህ ባሉት አራት ዓመታት ውስጥ ሥራ ጀምሯል። ይሄውም ንጉሱ ከእንግሊዝ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ በሱዳን በኩል ስለነበር ተከትለዋቸው የመጡ ሱዳናዊ ባለሙያዎች በጋዜጣ ዝግጅቱ ላይ ተሳትፈዋል። በወቅቱ 4 ገፅ ያላት ሳምንታዊ አርበ ጠባብ መጠን (ታብሎይድ) ጋዜጣ ሲሆን 2 ገፅ በአማርኛ፣ 2 ገፅ በአረብኛና የሚታተም ነበር። ዋና አዘጋጁም ሊባኖሳዊው ኒማር የሚባል ሰው እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።

 

ጋዜጣው በዚህ ሁኔታ ሥራ ቢጀምርም የንጉሱ ስርዓት ሲወገድ መጠንና ለውጥ አሳይቷል። ይሄውም ከ1968 .ም አጋማሽ አንስቶ የገፅ ብዛቷን 8 ያደረሰች ሲሆን በአረብኛ ቋንቋ ብቻ መውጣት ጀምራለች። ከዚህም በላይ አዘጋጆቹ ግብፅ ሀገር ተምረው የመጡ ኢትዮጵያውያን መሆናቸው ይነገራል።

 

የዓልአለም ጋዜጣ ዋነኛ የይዘት ትኩረቷም የመካከለኛው ምስራቅና የኢትዮጵያ ማህበረ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚ ጉዳዮች ናቸው። እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድና ዓረቡ ዓለም የሚታዩ ዘርፈ ብዙ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ላይ በማተኮር የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ አቋም እንዲንፀባረቅባት ጥረት ይደረጋል። ዋነኛ አንባቢዎችም በኢትዮጵያ የሚገኙ የአረብኛ ተናጋሪ ሀገራት ኢምባሲ ቆንስላዎች (ሠራተኞች)ና አረብኛ ተናጋሪ ዜጐች ናቸው።

 

በሪሳ ጋዜጣ

የበሪሳ ጋዜጣ በ1968 .ም በአክሲዎን ተደራጅተው በግል ያትሙት ከነበረው ግለሰቦች ተወርሶ በወቅቱ አጠራር በማስታወቂያ ሚኒስቴር ሥር መታተም ሲጀምር በ8 ገጽ 2,500 ቅጂ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ። ጋዜጣው በዚህ ወቅት በሳባ ፊደል ይፃፍ እንደነበረና በነጭና ጥቁር ቀለም እንደሚታተም ለማወቅ ተችሏል።

በኋላ እንደሌሎቹ የድርጅቱ የህትመት ውጤቶች ሁሉ ስራው በፕሬስ ድርጅት ስር ሆኖ እስከአሁን የዘለቀ ሲሆን ስርጭቱም በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልል ነው።

የጋዜጣው መጠን መጀመሪያ ሲጀመር በርሊነር በሚባለው የጋዜጣ መጠን የሚታተም ሲሆን በኋላ ላይ ከመስከረም 1ቀን 1985 .ም ጀምሮ ታኅሣሥ2 ቀን 1985 ብሮድ ሺት ሆኖ ታትሟል።

ከዚህ ጊዜ ጀምሮ አሁን እስካለንበት ጊዜ ድረስ ሎጐው ባለቀለም ሆኖ በታብሎይድ ቅርጽ በቁቤ (ላቲን አልፋቤት) እየተፃፈ በመታተም ላይ ይገኛል።


ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0000108458
TodayToday7
YesterdayYesterday116
This_WeekThis_Week246
This_MonthThis_Month2171
All_DaysAll_Days108458

         በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።