ባቡር ኢትዮጵያን የት ያደርሳታል? "የፈለገችበት ያደርሳታል!» - ዶ/ር ኢንጂነር ጌታቸው በትሩ Featured

02 Sep 2015

ኢትዮጵያ ግዙፍ የባቡር ፕሮጀክቶችን እየገነባች ናት። እነዚህ የባቡር ፕሮጀክቶቻችን የኢትዮጵያን ህዳሴ በማቅረብ ታላቅ ተስፋ ተጥሎባቸዋል። እኛም ባቡር የት ያደርሰናል ስንል ፕሮጀክቶቹን የሚመሩትንና እንግሊዝ ከነበረው ኑሯቸው አገራቸው ገብተው ይህንን ታላቅ አገራዊ ስራ በማከናወን ላይ የሚገኙትን የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ኢንጂነር ጌታቸው በትሩን ጠይቀናል ። እሳቸውም እጅግ በመተማመንና በጠነከረ ተስፋ «የፈለገችበት ያደርሳታል» ሲሉ መልሰውልናል። ጊዜው የኢትዮጵያ ነው።

ትኩረት ለባቡር ትራንስፖርት

በአሁኑ ወቅት አገልግሎት እየሠጠ የሚገኘውና ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የየብስ ትራንስፖርት የተጠቃሚውን ፍላጐት በማርካት ላይ የሚገኝ አይደለም። በዚህ ላይ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ለማደግ የሚፈልገውን አቅም የሚያጠናክር አልሆነም። ስለዚህ መንግስት የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ በማስተዋል ያገኘው ብቸኛ አማራጭ የባቡር ትራንስፖርት በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ችሏል።

በዚህ እቅድ አምስት ሺህ ኪሎ ሜትር መገንባት እንደሚቻል ቢታመንም በአንድ ጊዜ ለማከናወን የተወሰነው ግን ሁለት ሺህ ኪሎ ሜትሩን ብቻ ነው።

የኮርፓሬሽኑ መቋቋም

በአንድ አገር የባቡር መስመር ዝርጋታ ለመጀመር አገሪቱን የሚመራ መንግስት የፓለቲካ ቁርጠኝነት ሲኖረው በተግባር የሚፈፀም ብቻ ነው። ይህ የፓለቲካ ቁርጠኝነት የሚመጣው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከፍ እንዲል ሲታሰብና ለማደግ ሁለንተናዊ ዕቅድ ሲኖር ነው። በዚህ ምክንያት የአገራችን መንግስት ለልማታችን መፋጠን የባቡር መጓጓዣ ሊኖረን እንደሚገባ አስቀድሞ አስፈላጊነቱንና አዋጪነቱን በማጥናት ተግባራዊ እንዲሆን ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን እንዲቋቋም ወሰነ።

መዳረሻ ሥፍራዎች

በረጅም ጊዜ ለመሥራት ከታቀደው የባቡር መስመር ዝርጋታ ውስጥ ቅድሚያ የተሰጠው ከአዲስ አበባ -ጅቡቲ ወደብ ድረስ የሚዘረጋው ዋናው ነው። ይህ መስመር ለወጪና ገቢ ዕቃዎች አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዝ በመሆኑ የሚጓጓዙ ዕቃዎች በጠቅላላው በተቀላጠፈ ሁኔታ በተፈላጊው ሥፍራ እንዲደርሱ የሚያግዝና ለአገሪቱ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ በመሆኑ ቅድሚያውን ይዟል። በተጓዳኝም ከአዋሽ -ወልድያና ከወልድያ-መቀሌ ያለው መሥመር ሥራው እየተፋጠነ ይገኛል።

በአዲስ አበባ ከተማም ከጦርኃይሎች-አያት የመኖሪያ መንደር ድረስና ከቃሊቲ እስከ ጦርኃይሎች ያሉት መስመሮች ተጠቃሽ ናቸው።

የሌሎች አገሮች ልምድ

በልማት እጅግ ወደፊት የተራመዱትና የአገራቸው ዕድገት ታላቅ ደረጃ መድረሱ የሚጠቀስላቸው አገራት በተለይም አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ኒውዝላንድ፣ ካናዳ፣ አውስትራሊያና ቻይናን የመሣሠሉትን አሁን ላሉበት ደረጃ ያበቃቸው የባቡር መጓጓዣ መሆኑን ታሪካቸው ያስረዳል።

የእነዚህ አገሮች የኢኮኖሚ ዕድገት የተፋጠነው ማንኛውንም ሥራ ለመስራትና የህዝቦቻቸውን ግንኙነት ያጠናከረው እንዲሁም ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱበትና የሥራ ውጤቶቻቸውን የሚያጓጉዙበት ምቹና ፈጣን የባቡር መጓጓዣእንዲኖር በማድረጋቸው ነው።

በኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ ለውጥ ልናይበት የምንችለው ዋናው መስመራችን ከአዲስ አበባ-ጅቡቲ ያለው ሲሆን፤ በአዲስ አበባ ከተማም የተዘጋጀው የባቡር መስመር በቅርቡ ሥራ ሲጀምርና የከተማው ነዋሪ ሲጠቀምበት ሌላ የባቡር መስመር እንዲኖረን የምንመኝበት ሁኔታ ይኖራል።

ምን ሊያመጣ?

የአገራችን የባቡር መስመር ግንባታ መከናወን በአሁኑ ወቅት በትራንስፖርት እጥረት የገጠመንን ችግር በከፍተኛ መጠን ያቃልልልናል።በትራንስፖርት እጥረት ምክንያት በሰዓቱ በሥራ ገበታችን መገኘት የተሳነን ይህንኑ መጓጓዣ በመጠቀም ባቀድነው ሰዓት ተጠቃሚ እንሆናለን። የቦታ ርቀት ለሥራችን እንቅፋት አይሆነንም።

ክልሎችን አቋርጦ የሚጓዘው መስመርም የህዝቦችን ትስስር የባህል ልምድ ልውውጥና መልካም ግንኙነትን ያጠናክራል። ለምሳሌ ህንድ የፌዴራሊዝም አስተዳደር ያላት አገር ናት ሕዝቦቿ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ናቸው። ከአንዱ ስፍራ ወደ ሌላው የሚንቀሳቀሱት በባቡር ነው። የባህልና የልምድ ልውውጣቸውም የበዛ ነው። በእኛም አገር ባቡር ከሌላ ክልል አዲስ አበባ መጥቶ ሥራውን ሠርቶ ወደ መኖሪያው የሚመለስበትን ዕድል ይፈጠራል። ይህ ምቹ ሁኔታ በርካታ ዜጐች ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው ወደ ውጭ ለመላክና የሚያስፈልገውን ሸቀጥ ለማስገባት ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ይኖረዋል። በርግጥም አገራችን በፈጣን ዕድገት ላይ እንደመሆኗ መጠን ይህን የማጓጓዣ መስመር መጠቀም ለልማታችን አጋዥ ስለሚሆን እንደርስበታለን ተብሎ የተገመተውን የዕድገት ደረጃ ቀድመን እንደርስበታለን የሚል ይሆናል።

ባቡርና ኢትዮጵያ

የባቡር መጓጓዣ በኢትዮጵያ ውስጥ በአጼምኒልክ ዘመን የተጀመረና ለአገልግሎት የዋለ መሆኑን ማንም አይዘነጋውም።ያኔ የተጀመረውን የጉዞ መስመር በማጠናከር ለማስቀጠል ግን ብዙ እንቅፋቶች አጋጥመው የመጓጓዣ መስመሩ ከአገልግሎት ውጭ ሆኖ ቆይቷል።

ይሁን እንጂ የባቡር መስመር መኖር ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው የጐላ በመሆኑ እንደ አዲስ መጀመሩ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ሆኗል። በተለይም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ሥራው እንዲጀመር የነበራቸው ፍላጐት ከፍተኛ ነበር። ሥራውን በቅርበት በመከታተልና በመምራት ውጤታማ ሆኖም የማየት ጉጉት ነበራቸው። ምክንያቱ ደግሞ ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት የህዝቦችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥና ከጐረቤት አገሮች ጋር ያለንን የኢኮኖሚ ትስስር የሚያፋጥንና ለአገሪቱ ፈጣን ዕድገት ወሳኝ እንደሆነ ስለሚያምኑ ነው። በርግጥም የጉዞ መስመሩ ኢትዮጵያን ወደፈለገችበት ደረጃና ሥፍራ ያደርሳታል።

በየትኛውም ሥፍራ ልማት ማከናወን ቢያስፈልግ የመጓጓዣ እጥረት ስለማይኖር የምርትና የአቅርቦት ሥራው የተፈጠነ ይሆናል።

የለውጥ አቅጣጫ

ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ትጠቀስበት በነበረው የድህነትና የረሃብተኛነት ምሳሌነት በአሁኑ ወቅት በተያያዝነው የልማት አቅጣጫ በማደግ ላይ ከሚገኙት አገሮች አንዷ ሆኖ ለመጠራትና የወደፊት ተስፋዋ ንሩህ መሆኑ እየተጠቀሰ ይገኛል። ይህንን የፈጣን ዕድገት ግስጋሴ ለማስቀጠል አሁን በመገንባት ላይ ያለው ግዙፍ የመጓጓዣ ፕሮጀክት በርግጠኛነት የዕድገት አቅጣጫችንን በማፋጠን አስገራሚ ለውጥ የምናመጣበት ዕድል እንዳለ ያመላክታል በዚህ ሂደት የለውጥ አቅጣጫችን አመርቂና አስደሳች ይሆናል።

ሠላምና ዕድገት

ለአገሪቱ የዕድገት ርምጃ አጋዥ ይሆናል ብለን የጀመርነው የባቡር መስመር ግንባታ በአገራችን ውስጥ የሕዝቦችን ግንኙነትና ተጠቃሚነት በከፍተኛ ደረጃ ሲያሻሽል ጐረቤት አገራት ከእኛ ጋር ግንኙነታቸውን እንዲያጠናክሩ ያበረታታል። በነዚህ ምክንያት የጋራ ተጠቃሚነታችን እየጐላ ስለሚሄድ ለዕድገታችን ሰላምን ማረጋገጥ እንዳለብን ስለሚታመን የቀጠናችንን ሰላም የማስጠበቁ ሃላፊነት የጋራችን ይሆናል ማለት ነው። ይህ ሃሳብ የመንግስታችን የረጅም ጊዜ የማደግና የመበልፀግ ዓላማ በመሆኑ ቁርጠኝነቱን ስላሳየ የሁሉንም ተጠቃሚነት ያረጋግጣል ማለት ነው።

 

ፀሃፊው አያሌው ንጉሴ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0000137263
TodayToday74
YesterdayYesterday126
This_WeekThis_Week1277
This_MonthThis_Month3345
All_DaysAll_Days137263

         በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።