ባለ ብዙ ፋይዳው ቅጠል Featured

14 May 2015

 

                                

ዘመናዊ ሕክምና ከባሕላዊው ቀድቶ ወይም ባሕላዊውን በመመሥረት መድኃኒቶችን አምርቶ እንደሚያቀርብ ይታወቃል፡፡ በዚህ መልኩ በመድኃኒት ቅመማ ሳይንስ በዋናነት ግብዓት ሆነው የሚያገለግሉት ደግሞ ዕፀዋት ሲሆኑ ከዕፀዋት ክፍልም በአብዛኛው ለእንዲህ ዐይነት ጥቅም ሲውል የሚታየው ቅጠላቸው ነው፡፡ ለዛሬ ከጥንታውያን ግብፆች፣ ግሪኮችና ሮማኖች ጊዜ ጀምሮ የጎላ ቀሜታ ስለሚሰጥ አንድ የቅጠል ዐይነት ላካፍላችሁ ወደድኩ፡፡ ይህ ቅጠል በሦስቱ ጥንታውያን አገሮች ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ1,000 ዓመተ ዓለም ጀምሮ ይጠቀሙበት የነበረ ሲሆን በእኛም አገር በሰፊው ጥቅም ላይ የሚውል ነው፡፡

ግቢያችን ውስጥ እንደ ቀልድ አፈር አስይዘነው በቀላሉ የሚለመልመው ይህ ተክል ሻያችንን ለማጣፈጥና መልካም መዐዛ ለመስጠት ወደር አይገኝለትም፡፡ ሆኖም ለሻይ ማጣፈጫነት ከመጠቀም ባሻገርም በርካታ የጤና ጠቀሜታዎች እንዳሉት ሳይንስ አረጋግጧል፡፡ እንዲህ በሰፊው ለማተት የተነሳሁት ናና ቅጠል ብለን ስለምንጠራው ተክል ነው፡፡

ናና ቅጠል አብዛኞቻችን እንደምንጠቀምበት ቅጠሉን በቀጥታ ከመጠቀምም በላይ ከውስጡ የሚጨመቀው ዘይት ልዩ ልዩ መድኃኒቶችን ለማዘጋጀት፣ ሳሙናዎችና የመዋቢያ ምርቶች መልካም መዐዛ እንዲይዙ ለማድረግ እንዲሁም ምግብና መጠጥን ማጣፈጥ ለመሳሰሉ እጅግ በርካታ ግልጋሎቶች ይውላል፡፡

በናና ቅጠል ውስጥ የሚገኘው ሜንት ለጉንፋን፣ ለሳል፣ ለጉሮሮ፣ ለሳይነስ፣ በአጠቃላይ በመተንፈሻ አካላት ለሚከሰቱ እክሎች ዐይነተኛ መፍትሄ ሲሆን የልብ ትኩሳት፣ ማጥወልወል፣ ትውኪያ፣ የአንጀት ባክቴሪያ ለመሳሰሉ ለምግብ እንሽርሽሪት ሥርዓት ችግሮችም ፍቱን መድኃኒት መሆኑ ተረጋግጧል፡፡

ታዲያ እኛም በፋብሪካ ውስጥ ከዚህ ባለ ብዙ ጥቅም ተክል የሚዘጋጀውን ዘይት ማግኘት ባንችል እንኳ በየቤታችን የናና ቅጠልን በቀጥታ በመጠቀም የሚከተሉትን ጥቅሞች ማግኘት እንችላለን፡፡

የመተንፈሻ አካላት ችግሮችን ለመቅረፍ

ልክ እንደ ቪክስ ሁሉ የናና ቅጠል ዘይት ልዩ ልዩ የመተንፈሻ አካላት ችግሮችን ለማስወገድ ይጠቅማል፡፡ ይህን ዘይት በደረታችን ላይ ቀብቶ በስሱ መታሸት ጉሮሯችን በቂ ፈሳሽ እንዲያመነጭ ሲለሚያስችልና የመታፈን ስሜትን ስለሚያስወግድ ጉንፋን እና ሳልን ለመከላከል ይጠቅማል፡፡ በተጨማሪም በእንፋሎት መልኩ መታጠን ተመሳሳይ ጥቅሞችን ይሰጣል፡፡

የጉንፋን እና የሳል መድኃኒቶች የሜንታ ጣዕምና ጠረን እንዲኖራቸው የሚያደርገው ሜንቶል የተባለ ንጥረ ነገር ናና ውስጥ በብዛት ስለሚገኝ የናና ቅጠልን ወይም ዘይቱን ማሽተት የአፍንጫ መታፈንን ያስወግዳል፡፡

የአስም በሽታ ላለባቸው ሰዎች የተሻለ አማራጭ ከመሆኑም በላይ የሳንባ ነቀርሳ በሽታ ተመልሶ እንዳይከሰትና ወደ ከፋ ደረጃ እንዳይባባስ የማድረግ አቅምም አለው፡፡

ለመልካም የአፍ ጠረን እና የጥርስ ጤንነት ወደር እንደማይገኝለት የሚነገርለት የናና ቅጠል የጥርስ ሳሙናዎችን ለመሥራት ዋና ግብዓት ነው፡፡ በጥንት ጊዜ ደርቆ የተፈጨ የናና ቅጠል ለመልካም የአፍ ጠረንና ጥርስን ለማንጣት አገልግሎት ይውል የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ አንድ ሁለት ጠብታ የናና ቅጠል ዱቄት ጥርስ ሳሙናችን ላይ ጨምረን እንድንጠቀም ይመከራል፡፡

ከአዕምሮ ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለማስወገድ

የናና ቅጠል በሰው ልጅ አዕምሮ ጤናማነት ላይ የራሱ የሆኑ በጎ ተፅዕኖዎችን ማሳረፍ ይችላል፡፡ ከእነኚህም መካከል የቅጠሉ መዐዛ የማስታወስ ችሎታን፣ አትኩሮትን፣ ንቁነትንና የሥራ አፈፃፀም ብቃትን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚጨምር በሙከራ ተረጋግጧል፡፡

ከዚህም በላይ የጭንቀት ስሜትንና ራስ ምታትን ለመከላከል የተወሰኑ የናና ዘይት ጠብታዎችን በግንባርና ጭንቅላት ላይ መቀባት ወይም ደግሞ በጨርቅ ላይ ጠብ አድርጎ መዐዛውን ወደ ውስጥ መሳብ በባለሙያዎች ይመከራል፡፡

ተጨማሪ የናና ጠቀሜታዎች

ሌላው የናና ቅጠል ጠቀሜታ ለሕፃናትና ለእናቶች ነው፡፡ በሕፃናት ላይ የሚከሰትን ከፍተኛ የሆነ ሆድ ሕመም ለመፈወስ ናና ከማንኛውም መድኃኒት ያልተናነሰ ፈውስ ይሰጣል፡፡ አጥቢ እናቶችም የናና ቅጠል ጭማቂ በማዘጋጀትና የጡት ጫፍ ላይ በመቀባት በማጥባት ወቅት የሚያጋጥም መሰነጣጠቅና ሕመምን ያቃልላል፡፡

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0000137306
TodayToday117
YesterdayYesterday126
This_WeekThis_Week17
This_MonthThis_Month3388
All_DaysAll_Days137306

         በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።