እኔ ከሞትኩ… ብርሃን ይብቀል

14 May 2015

 

                                         

የብሌን ልገሳን ከሌሎች ዓይነት የሰውነት ክፍሎች ልገሳ (ለምሳሌ ከኩላሊት ልገሳ) ከሚለዩት ነገሮች አንዱ ከሞት በኋላ የሚደረግ መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህም ለጋሹ በዙሪያው ላሉት ሰዎች ማለትም ለቤተሰቦቹና ለቅርብ ወዳጆቹ ጥብቅ የአደራ ቃል ማስተላለፍ ይጠበቅበታል

ከሁለት ዓመታት በፊት አንድ የስልክ ጥሪ ወደ ኢትዮጵያ የዓይን ባንክ ይደርሳል፡፡ ደዋዩ የዓይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል የገቡ መሆኑን ይገልጹልና ጤንነታቸው እየተዳከመ እንደመጣ ይናገራሉ፡፡ ከሕልፈታቸው በኋላም ብሌናቸው ስለሚወሰድበት ሁኔታ ለመነጋገር እንደሚፈልጉ ይናገራሉ፡፡ ይህ የሆነው ሕይወታቸው ሊያልፍ ሦስት ቀን ሲቀረው ነው፡፡ ይህ አጋጣሚ የስልክ ጥሪውን ለተቀበለችው የእዚያን ጊዜ ሥራ አስኪያጅ አስደንጋጭ ነበር፡፡ ምክንያቱም በተለመደው አሰራር መሠረት አንድ ለጋሽ ሕይወቱ ካለፈ በኋላ ይደወልላቸዋል እንጂ በቅርቡ ልሞት ነው ብሎ የሚደውል ሰው ስላልነበረ ነው፡፡ ሥራ አስኪያጇ ጥቂት ከተረጋጋች በኋላ ደዋዩንም አጽናንታ ይሰነባበታሉ፡፡ በማግሥቱ መልሳ ስትደውል ግን ስልካቸው ዝግ ስለነበር ከባድ ኀዘን ተሰማት፡፡ ሆኖም በሦስተኛው ቀን ከለጋሹ ቤተሰብ ስልክ ተደወለ፡፡ «/ር መብአፅዮን በቅዱስ ያሬድ ሆስፒታል ሕይወታቸው ስላለፈ መጥታችሁ ብሌናቸውን አንሱ»የሚል መልዕክትም ከስልኩ ተሰማ፡፡ የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ ባለሙያዎችም በቦታው በመገኘት የለጋሹን ብሌን ሊወስዱ ቻሉ፡፡

ከተመሠረተበት ከ1996 .ም ጀምሮ ድርጅቱ ከላይ የተጠቀሰውን ጨምሮ በሦስት ዓይነት ዘዴዎች የዓይን ብሌኖችን ይሰበስባል፡፡ ሁለተኛው ዓይነት ዘዴ ቀድመው ቃል ካልገቡ ሰዎች ልገሳ የሚደረግበት መንገድ ነው፡፡ ሟቹ ስለዓይን ብሌን ልገሳ ባያውቅም ቤተሰቦቹ የሚያውቁ ሲሆን፤ በሕልፈት ጊዜ ለዓይን ባንኩ ደውለው ልገሳው ይደረጋል፡፡ ሦስተኛው ዓይነት ዘዴ ደግሞ ለጋሹም ሆነ በአካባቢው ያሉ ሰዎች ስለ ዓይን ብሌን ልገሳ ምንም ዕውቀት ሳይኖራቸው ነው፡፡ ይህ የሚደረገው በጥቁር አንበሳና በጳውሎስ ሆስፒታሎች ባሉት ባለሙያዎች አማካኝነት የሟቹን ቤተሰቦች ስለ ዓይን ባንኩ በማስረዳትና እስኪረጋጉ ጠብቆ ልገሳውን እንዲያደርጉ በማስተማር ነው፡፡

ብሌኖቹ ወዴት ይሄዳሉ?

1998 .ም በተደረገ አንድ አገር አቀፍ ጥናት ከ300 ሺህ በላይ ሰዎች በዓይን ብሌን ጠባሳ መጠቃታቸው ታውቋል፡፡ የዓይን ብሌን ጠባሳ በልዩ ልዩ ምክንያቶች የሚከሰት ሲሆን፤ ለከፊልና ሙሉ ዓይነ ስውርነት ይዳረጋል፡፡ ሆኖም በሕክምና ዕርዳታ መልሰው ብርሃናቸውን ማግኘት ይችላሉ፡፡ በዓይን ብሌን ጠባሳ የተጎዱ ሰዎች መልሰው ማየት የሚችሉትም ብሌናቸው ሲቀየር ብቻ ነው፡፡ ይህ ሕክምና የብሌን ንቅለ ተከላ ይባላል፡፡ የተጠቀሰው ጥናት ከተደረገ ዘጠኝ ዓመታት ተቆጥሯል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ይህ ቁጥር ምን ያክል ሊጨምር እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡

በዚህ ችግር ተጠቂ ከሆኑ ሰዎች ቁጥር ጋር ሲነጻጸር በጣም ጥቂት ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት የዓይን ባንኩ ለ1,067 ሰዎች ያክል እንደገና የማየት ዕድልን ሰጥቷል፡፡ በአገሪቱ ውስጥ በአምስት የተለያዩ ቦታዎች በሚገኙ ዘጠኝ ባለሙያዎቹም በዓመት እስከ 170 ብሌኖችን ለታካሚዎቹ ይተክላል፡፡ ከእነዚህ ዕድለኞች አንዱ ቀሲስ አንዱዓለም ወልደትንሳኤ ናቸው፡፡

ቀሲስ አንዱዓለም በኮተቤ አካባቢ የሚኖሩ የ57 ዓመት አባወራ ናቸው፡፡ የዓይን ሕመም የጀመራቸው ገና በልጅነታቸው ነበር፡፡ በሂደትም የግራ ዓይናቸው ሙሉ ለሙሉ ማየት አቆመ፡፡ ቀኝ ዓይናቸውንም ያስቸግራቸው ጀመር፡፡ ስለዚህም ገና በልጅነት ዕድሜያቸው እየተመሩ ለመሄድ ተገደዱ፡፡ የቆሎ ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ የዓይናቸው ችግር ተባብሷል፡፡ ዓይናቸው ውስጥ ፀጉር የመሰለ ነገር አበቀለ፡፡ በርካታ የግልና የመንግሥት የጤና ተቋማትን ጎበኙ፡፡ ነገር ግን መፍትሔ ሊያገኙ አልቻሉም ነበር፡፡

በሰማኒያዎቹ መጨረሻ ላይ ሐረር በሚገኘው ጦር ኃይሎች ሆስፒታል ውስጥ የሚሠሩ አንድ ዶክተር የቀሲስ አንዱዓለም ብሌን መቀየር እንደሚኖርበት ሆኖም ይህ ቴክኖሎጂ ወደ አገር ውስጥ ስላልገባ ውጭ አገር ካልሆነ በስተቀር ሊታከሙ እንደማይችሉ ይነግሯቸዋል፡፡ ስለዚህም ቀሲስ አንዱዓለም ይህ ዓይነቱ ሕክምና ወደ አገር ውስጥ እስኪገባ የግድ መጠበቅ ነበረባቸው፡፡ በመጨረሻም በ2001 .. የግራ ዓይናቸው ብሌን ሊቀየርላቸው ቻለ፡፡

«አሁን ዓይን ሐኪም ቤት ግድግዳ ላይ ያሉትን መፈተኛ ጽሑፎች እስከ ስድስት ሜትር ርቀት ላይ አያለሁ፡፡ ለማንበብም ምንም አያስቸግረኝም፡፡ ጸሎቴን አደርሳለሁ፡፡ በመሥሪያ ቤትም ሥራዬን በሚገባ አከናውናለሁ» ይላሉ አቧራ ለመከላከል መነጽር የሚያደርጉት ቀሲስ አንዱዓለም፡፡

የዓይን ብሌን ንቅላ ተከላ ምንድን ነው?

ይህቺን ጽሑፍ ከማዘጋጀቴ በፊት የዓይን ብሌን ልገሳ ሲባል የማስበው ነገር ሙሉው የዓይናችን ክፍል ከሰውነታችን ነቅሎ ይወጣል የሚለው የተሳሳተ ግንዛቤ ነበር፡፡ ይህ አስተሳሰብ የበርካታ ሰዎችም እምነት ነው፡፡ ሆኖም የዓይን ብሌን ልገሳ ሲባል ዓይናችን ከነ ሙሉ አካሉ፤ ከነ ድቡልቡልነቱ ይለገሳል ማለት አይደለም፡፡ ዓይን ልዩ ልዩ ክፍሎች ያሉት ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ ለልገሳ የሚውለው በእንግሊዝኛ ኮርኒያ የሚባለው በአማርኛ ደግሞ ብሌን የሚባለው የዓይን ክፍል ብቻ ነው፡፡ በእርግጥ በተለምዶ ብሌን ብለን የምንጠራው ጥቁሩን የዓይናችንን ክፍል ሲሆን፤ ኮርኒያ ግን ይሄን ጥቁሩን የዓይናችን ክፍል የሚሸፍን መስታዎት መሰል ነገር ነው፡፡ «ከለጋሽ ላይ የምትወስደው ብሌን የአውራ ጣታችንን ጥፍር ነው የምታክለው፡፡ ብሌኗ ከዓይናችን ክፍል ጥቁር የምትመስለው ነች፤ ግን ጥቁር አይደለችም እንደ መስታዎት ብርሃን አስተላላፊ ነች» ሲሉ ዶ/ር መነን አያሌው ያብራራሉ፡፡

የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ ሜዲካል ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር መነን ሥራቸውን አስቸጋሪ ከሚያደርጉባቸው ነገሮች ዋነኛው ይህ የግንዛቤ እጥረት እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ «ከፍተኛው ችግር የማህበረሰቡ ግንዛቤ አናሳ የመሆን ችግር ነው፡፡ በጣም ትንሽ ነች፤ ይህቺን የምታክል አካል ከእኔ ዓይን ላይ ተነስቶ ለወገን ቢተካ እና ያ ሰው ማየት ቢችል ትልቅ ነገር ነው»፡፡ በውጭ አገር ያለውን ልምድ እንደ ምሳሌ የሚጠቅሱት ዶ/ር መነን ሌሎች አገሮች የደረሱበት ደረጃ እንድንደርስ ያልማሉ፡፡ «በሌሎች አገሮች አሁን ለልገሳ ሄደው ወትውተው አይደለም ብሌኖች የሚሰበስቡት፡፡ ሕንድ አገር ለምሳሌ ሰዉ በጣም ስለገባው ደውለው ነው የሚጠሩህ፡፡ እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ እንኳን ሁለት ሕንዳዊያን ሰዎች ሲያልፉ ቤተሰባቸው ጠርቶን ሄደን ሰብስበናል፡፡ እኛ ሄደን እባካችሁ የራሳችሁን ወይም የዘመዳችሁን ብሌን ለግሱ ከማለት አልፈን እንደዚያ ደረጃ መድረስ ነው የምንፈልገው»፡፡

የዓይን ብሌኗ ከለጋሹ ላይ ከተወሰደች በኋላ ከለጋሹ ላይ የደም ናሙና ይወሰድና ከተላላፊ በሽታዎች የፀዳ መሆኑ ይረጋገጣል፡፡ ከዚያ በኋላ ብሌኑ በልዩ ኬሚካል ውስጥ ተቀምጦ ወደ ቤተ ሙከራ ገብቶ ጤነኛ መሆኑ ይረጋገጣል፡፡ ይህ የንቅለ ተከላው የመጀመሪያ ክፍል ነው፡፡ ከዚህ በኋላ የሚቀጥለው የተለገሰው ብሌን እንዲተከልለት እነኚህን ወጪዎች ለመጋራት ፈቃደኛ የሚሆን ታካሚ ማግኘት ነው፡፡

የዓይን ዋጋው ስንት ነው?

ከስድስት ዓመታት በፊት በዓይን ባንኩ የብሌን ተከላ አገልግሎት አግኝተው ዕይታቸው የተሻሻለላቸው ቀሲስ አንዱዓለም ከ500 ብር በላይ ነበር የከፈሉት፡፡ በአሁኑ ሰዓት ግን ይህ ክፍያ በስንት እጥፍ አድጎ ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም፡፡ ሆኖም ይህ ክፍያ «የብሌኑ ዋጋ አይደለም» ይላሉ ዶ/ር መነን፡፡ ነገር ግን ብሌኑ ከለጋሹ ተነስቶ ለተቀባዩ እስኪተከል ድረስ የሚደረግለት ምርመራ ብዙ ወጪዎች እንዳሉት ይናገራሉ፡፡«ከለጋሽ ላይ የደም ናሙና ተወስዶ ጤንነቱ ሲመረመር የቤተ ሙከራ ወጪ አለ፡፡ ብሌኑን በጥንቃቄ ለማስቀመጥ የሚያገለግል ኦፕቲዞል የሚባል ኬሚካል አለ፡፡ አንዷ ብልቃጥ ከሃምሳ ዶላር በላይ ነች፡፡ ሌሎች መድኃኒቶችና የቁሳቁስ ወጪ አለ፡፡ ለሠራተኞች ወጪ አለ፡፡ ይሄ ሲደማመር በጣም የተጋነነ ዋጋ ነው፡፡ ሆኖም ሌሎች በርካታ ወጪዎች አልተካተቱም»፡፡

የአንድን ብሌን ጤንነት አረጋግጦ ለተለጋሹ ለማቅረብ በእነኚህ መንገዶች ሲያልፍ የሚያስፈልገው ወጪ በብር ተመን ምን ያህል ነው? የሚለውን ጥያቄ ዶ/ር መነን ሲመልሱ «በጠቅላላ የአንድ ብሌንን ጤንነት ለማረጋገጥ በአሁኑ ሰዓት ከአራት እስከ ሰባት ሺህ ብር ያወጣል» ብለዋል፡፡ ይህም ወጪ በታካሚው እንዲሸፈን ይጠበቃል፡፡

ይህን ወጪ እንደሚሸፍኑ ተስማምተው ሕክምና ካገኙ ሰዎች መካከል የ63 ዓመቱ አቶ መሐመድ ብርሃን ማሕሙድ አንዱ ናቸው፡፡ ከአስራ ሰባት ዓመታት በፊት የዓይን ሕመም ሲጀማምራቸው የሞራ ገፈፋ ቀዶ ጥገና የተደረገላቸው አቶ መሐመድ ብርሃን መርካቶ ውስጥ የምትገኘውን ቁርስ ቤታቸውን በማስተዳደር ለረጅም ዘመናት በጥንካሬ ሲሰሩ የኖሩ ነጋዴ ናቸው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ሥራውን ለልጆቻቸው ያስረከቡት አቶ መሐመድ ብርሃን «ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ ግን አስቸጋሪ ሆነብኝ፡፡ የግራ ዓይኔ በጣም ታስቸግረኝ ጀመር፡፡ መኪና መንዳት ሁሉ አቆምኩኝ» ይላሉ፡፡

በዚህ ጊዜ ወደ ሕክምና ተቋም ያመራሉ፡፡ የዓይን ብሌናቸው መቀየር እንዳለበት ሲነገራቸውም ወደ ዓይን ባንኩ ሄደው ይመዘገባሉ፡፡ ይህ የሆነው በጥቅምት ወር 2007 .. ነው፡፡ አቶ መሐመድ ብርሃን በአሁኑ ጊዜ የዓይን ብሌናቸው ተቀይሮላቸው በምኒልክ ሆስፒታል ውስጥ ክትትል እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ስለተደረገላቸው ሕክምና እንዲሁም ስለከፈሉት ክፍያ ሲጠየቁም «በአረብኛ ቀረኒያ ይባላል፡፡ የዓይን ብሌን ማለት ነው፡፡ እሱ ነው የተቀየረልኝ፡፡ 4,990 ብር ነው የከፈልኩት፡፡ ግን ብር ከፈልኩኝ አልልም፡፡ በብላሽ ነው ያገኘሁት፡፡ ለብርሃን መቶ ሺ እንኳን ያንሰዋል» ብለው ሲናገሩ በስሜት ነው፡፡

ነገር ግን ወደ ዓይን ባንኩ የሚሄዱ ሁሉ የመክፈል አቅም አላቸው ማለት አይደለም፡፡ እንዲውም ብዙዎች ታካሚዎቻቸው የሚጠየቀው ክፍያ ከአቅማቸው በላይ እንደሚሆንባቸው ይታወቃል፡፡ ሆኖም ታካሚው የመክፈል አቅም የሌለው ከሆነ ወጪዎቹን ለመሸፈን የሚቻልባቸው አማራጮችም እንዳሉ «በገንዘብ ችግር ምክንያት ብቻ ብሌን እያስፈለገው ሳይታከም አይቀርም» ሲሉ ዶ/ር መነን ያብራራሉ፡፡ «በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ግለሰቦች ወጪ ይሸፈናል፡፡ በተጨማሪም በከተማው አንዳንድ ቦታዎች ላይ ካስቀመጥናቸው የእርዳታ ማሰባሰቢያ ሳጥኖች ከሚገኘው ገንዘብ የተወሰነውን በመውሰድ ለዚህ ዓይነት አገልግሎት እንዲውል ይደረጋል»፡፡

ብርሃን ለምን ይቀበር!

የዓይን ብሌን ለመለገስ በርካቶች በደስታ ቃል የሚገቡ ቢሆንም ሌሎች በርካቶች ደግሞ አሁንም ፈቃደኞች አይሆኑም፡፡ ከሕልፈታቸውም በኋላ ቢሆን ከሰውነት አካል ውስጥ የአንዱን መጉደል ሲያስቡት የሚያስፈራቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ እንደ ቀሲስ አንዱዓለም በሌሎች ልገሳ ተጠቃሚ የሆኑ ሰዎች ደግሞ «ለሌላ ሰው የሚያገለግል ከሆነ እኔ የራሴንም መልሼ መናዘዝ እፈልጋለሁ» ይላሉ፡፡ ከዚህም በላይ «ጤናማ የሆናችሁም ሰዎች ይሄን ብታደርጉ መልካም ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ አፈር ነው የሚበላው፡፡ ከሞትን ወዲያ ምን ያደርግልናልሲሉ ብርሃን እንዳንቀብር ይጠይቃሉ፡፡

ብሌን መለገስ ለሌላው ሰው ሕይወት እንደመስጠት መሆኑን የሚያስረዱት ቀሲስ አንዱዓለም በሞቱ ሌሎችን ያዳነውን ክርስቶስን እንደ አብነት ያነሳሉ፡፡ «ይሄን ትምህርት የምናገኘው እየሱስ ክርስቶስ ደሙን አፍስሶ እኛን እንዳዳነን ሁሉ እኛም ብሌናችንን ብንለግስ ሌላ ሰው አዳንን ማለት ነው፡፡ እሱ እንዲያውም ዓለምን ነው ያዳነው በደሙ፡፡ እኛ ደግሞ ግፋ ቢል ሁለት ሰው ነው፡፡ ተጎድቶ ማዳን ያለ ነገር ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ጉዳት አይደለም፡፡ ምክንያቱም ሰውየው ከሞተ በኋላ ነው የሚሰጠው»፡፡

የብሌን ልገሳን ከሌሎች ዓይነት የሰውነት ክፍሎች ልገሳ (ለምሳሌ ከኩላሊት ልገሳ) ከሚለዩት ነገሮች አንዱ ከሞት በኋላ የሚደረግ መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህም ለጋሹ በዙሪያው ላሉት ሰዎች ማለትም ለቤተሰቦቹና ለቅርብ ወዳጆቹ ጥብቅ የአደራ ቃል ማስተላለፍ ይጠበቅበታል፡፡ ከሕልፈታቸው ሦስት ቀን አስቀድመው ለዓይን ባንኩ በመደወል ስለ ልገሳው ጉዳይ በድፍረት ሊወያዩ የሞከሩት መ/ር መብአፅዮን ያደረጉትም እንደዚያ ነው፡፡ ቤተሰቦቻቸውን፣ ጎረቤቶቻቸውንና የንስሃ አባታቸውን በተናጠል እያናገሩ የብሌናቸው ልገሳ ጉዳይ በመደናገጥ እንዳይረሳ አደራ የማስቀመጡን ድርሻ ሳይረፍድ ሊወስዱ በመቻላቸው የገቡት የልገሳ ቃል ሊፈፀምላቸው ችሏል፡፡ ይህንን ጉዳይ ዶ/ር መነንም አስረግጠው ያስረዳሉ፡ «ዋናው ጠቃሚ ጉዳይ ለጋሾች ለቤተሰብ ማሳወቃቸው ነው፡፡ ምክንያቱም ለጋሹ ከሞተ በኋላ ኃላፊነቱን ሊወስዱለት የሚችሉት እነሱ ስለሆኑ»፡፡ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0000137267
TodayToday78
YesterdayYesterday126
This_WeekThis_Week1281
This_MonthThis_Month3349
All_DaysAll_Days137267

         በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።