ሽብርተኛነት የወቅቱ ዓለም አቀፍ ስጋት Featured

14 May 2015

 

                    

የሽብር ተግባሩ አገሪቱ የተያዘችውን የልማት እንቅስቃሴ እንዳይጐዳና እንቅፋት እንዳይሆን የፀረ ሽርተኝነት ሕግ በማርቀቅና በማፅደቅ የዜጐቿን በሰላም ወጥቆ የመግባት ደህንነት የሚረጋገጥበት ተግባር ፈፅማለች

ጦርነት አንድ ገፅታ ነው፡፡ በውል ከሚያውቁት፤ ጠላትነቱን ለይቶ በሚመጣና በተከላካይ ወገን የሚደረግ የመገዳደል ተግባር፡፡ ከዚህ ውጪ የሰው ሕይወት በተፈጥሮ አደጋ ሊያልፍ ይችላል፡፡ ሆነ ተብሎ በታቀደ የጥፋት ተልዕኮ አማካኝነት ባላሳቡትና ባላወቁት ወጥመድ ሕይወታቸው የሚያልፍ ሕፃናት፤ ወጣቶች፣ ጐልማሶችና አረጋውያን እንዲሁም የጥፋቱ ሰለባ የሚሆነው ተቋም ወይም ንብረት ምንኛ አሳዛኝ ነው፡፡

በሠላም እየኖርን ነው ብለው ሲያስቡ በድንገተኛ ወረራ ጥቃት የደረሰባቸው፤ ለጉዳያቸው ወጥተው በዚያው የቀሩ፤ በድናቸው ለቀብር ያልበቃውን ሁሉ ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡ የዚህ ሁሉ ድርጊት ማጠንጠኛ የወቅቱ ሥጋት ወደሆነው «አሸባሪነት» ይወስደናል፡፡

«አሸባሪነት» የሚለውን ቃል የአሜሪካው ስቴት ዲፓርትመንት ሲተነትነው፡- «አስቀድሞ በደንብ የታሰበበት፤በፖለቲካ ምክንያት የተነሳሳ እና በጦር ተጋጣሚነት በማይታዩ ክፍሎች የሚፈፀም አመፅ ሲሆን፤ በንዑስ ብሔራዊ ቡድኖች እና በህቡዕ ክፍሎች የሚፈፀም ተግባር ነው» ይለዋል፡፡

ሽብርተኝነት የንፁሐንን ዜጐች ሕይወት በጅምላ የሚያጠፋ ፤ የአገርን ሀብት፤ የልማት አውታሮችንና ተቋማትን የሚያወድም ኃላፊነት የጎደለው የአረመኔነት ተግባር መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡

ሽብርተኝነት ጉዳት ማድረስ ብቻ ሳይሆን ዓላማው የራስን ፍላጐት በሌሎች ላይ በኃይል ለመጫን የሚደረግ የማስገደድ ተግባርና ተቀባይነት የሌለው የጉልበትኞች ድርጊት ነው፡፡

ሽብርተኝነት መሠረቱ ከኃይማኖት ጋር ተያይዞ የመነሳቱና ይህም አስተሳሰብ በብዙዎች ዘንድ እውነት ተደርጐ የመወሰዱ ነገር ችግሩን ከማቅለል ይልቅ እያባባሰው መምጣቱን እንድንረዳ ያደርገናል፡፡ በዚህ የአስተሳሰብ መስመር ኃይማኖትን በተሳሳተ መንገድ መጠቀሚያ በማድረግ ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ያሉት የኃይማኖት አክራሪዎች ሆነው ይስተዋላሉ፡፡ ኃይማኖቶች የሠላምና የፍቅር መሥሪያ እንዲሆኑ ከመረዳት ይልቅ የእርስ በርስ መተላለቂያ እያስመሰሉ ማቅረብ ለብዙዎች መጥፋት መንስኤ ሆኗል፡፡

አክራሪነት(Fundamentalist) የሚለው ቃል በቀዳሚነት ተፅፎ የሚገኘው እ... 1909 በታተመው «The Fundamentalist: A Testimony to the Truth» በተሰኘው መጽሐፍ ላይ ነው፡፡ የዚህ እሳቤ ዋና ግቡ በእምነት ውስጥ ዘመናዊነትን ይዘው የተነሱ የእምነቱን መሠረታዊ ግዴታዎች ማሟላት እንደሚገባ ለማሳሰብ ነበር፡፡

በወቅቱ የሥነ-መለኮት ቃል ተደርጐ ከመወሰድ ያላለፈው «አክራሪነት» ከዓመታት በኋላ በአሜሪካ ጆን ስኩፕስ የተባለ የሁለተኛ ደረጃ መምህር ክስ ተመስርቶበት ፍርድ ቤት ሲቀርብ አስተሳሰቡ ሌላ መልክ ያዘ፡፡

ስኩፕስ እ..አ በ1925 የግዛቲቱን ሕግ እንደጣሰ ተደርጐ ተከስሶ ነበር፡፡ ይኸውም የሚያስተምረው የሥነ ሕይወት (Biology) ትምህርት የሰውን አፈጣጠር አስመልክቶ «ማንኛውም የሰው ልጅ በመለኮታዊ አፈጣጠር ወደ ምድር የመጣ ሳይሆን ከዝንጀሮነት ቀስ በቀስ እየተለወጠ የመጣ መሆኑን አላስተምርም» በማለቱ ነበር፡፡

ፍርድ ቤቱ በስኩፕስ ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ ቢያስተላልፍበትም በወቅቱ የሞራል ድል አግኝቷል የሚለው አስተሳሰብ በርካቶችን አሳምኗል፡፡ ከዚህ በኋላ እ..አ በ1930 የኃይማኖት አክራሪዎች እያቆጠቆጡ በመውጣት ከሌላው ህብረተሰብ ራሳቸውን ማግለልን ተያያዙት፡፡ ይህንን ተከትሎ በሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ከፍተኛ የሚባል የእምነት ሥርዓት ክለሳ ተደረገና በሁለተኛው የቫቲካን ጉባዔ «አክራሪነት» የሚለው መጠሪያ በወቅቱ የተደረገውን ለውጥ ለሚቃወሙ ወገኖች የተሰጠ ስያሜ ሆነ፡፡

እነዚህ «አክራሪዎች» ተብለው የተፈረጁት የካቶሊክ እምነት እንደጥንቱ ባህላዊ ልምዷንና እምነቷን እንድትቀጥል የሚሹ ነበሩ፡፡

..አ በ1985 «በሮማው ካቶሊክ ጳጳስ ዳግማዊ ጆንፖል ላይ የተቃጣው የመግደል ሙከራና የአክራሪነት መሠረት» (The assassination Attempt Against the Pope, and the Roots of Terrorism) በሚል በኢቫን ፖልቼቭ በተጻፈው በመጽሐፍ ላይ «ተግብሮቱ መንስዔውን ያረጋግጣል» (The End Justifies the means) በሚል ርዕስ «አሸባሪ» በመባል የተፈረጀው መህሜት ዓሊ አጅካ እ..አ በሜይ 13/1981 በሮም ቫቲካን ከተማ በቅዱስ ፒተርስ አደባባይ ዳግማዊ ጆንፖል ላይ ተደጋጋሚ ተኰስ አድርጐ በማቁሰሉ በግድያ ሙከራ እጅ ከፍንጅ ተያዘ፡፡

መህሜት ዓሊ እጅካ በሮማ ከተማ ለ72 ሰዓታት የፍርድ ሂደቱ ከታየ በኋላ እ..አ በጁላይ 1981 የዕድሜ ልክ እሥራት ተፈርዶበት ለ19ዓመታት ወህኒ ተወርውሮ ቆየ፡፡ በአገሪቱ ለወንጀለኞች በሚደረገው ምህረት የወቅቱ ፕሬዚዳንት ካርሎ አዝግሊዮ ምህረት እንዲያገኝ ፈቅደው እ... በጁን 2000 ወደ ቱርክ እንዲሄድ ተደረገ ፡፡

ይህንን የግድያ ሴራ ማን አቀናበረው? ከወንጀለኛው ጀርባ ማን አለ? የሚለውን ለመመለስ የተካሄደው ምርመራ ተዳፍኖ የቀረ ቢሆንም የግሪኩ ጋዜጠኛ ማኖስ ሀሪስ እ..አ በ1984 ባሳተመው «Terrorism, First Born of the CIA» በሚለው መጽሐፍ ወንጀለኛው መህሜት ዓሊ አጅካ የሽብርተኛ ቡድን አባል እንደነበርና በቱርክና በብዙ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች የብዙ ሰዎችን ሕይወት እንዳጠፋ አጋልጧል፡፡

ያኔ የተጀመረው ለጋው ሽብርተኝነት አል ኢትሀድን፤ አልቃይዳን፤ ታሊባንን፤ አልሸባብን፤ ቦኮሀራምንና አይ.ኤስ.አይ.ኤል.ን የመሳሰሉ አደገኛ ቡድኖች ፈጥሮ የብዙሃን ንፁሕ ዜጎች ሕይወት እየቀጠፈና የጥፋት አድማሱን እያስፋፋ ይገኛል፡፡

አሸባሪ ቡድኖች የዓለም አቀፍ የሽብር መረብ አንድ አካል ሲሆኑ፤ ቡድኖቹ እንደልብ ከቦታቦታ ለመንቀሳቀሳቸውና ለመጠናከራቸው ምክንያት የሆናቸው እንደ ሶማሊያና አንደ መካከለኛው ምሥራቅ አገሮች መንግሥት አልባ ከመሆን ጀምሮ የእርስ በርስ ብጥብጥ የነገሠባቸው መሆናቸው ነው፡፡

ይህንን የአገራቱን ብጥብጥ በመጠቀምና የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙበት ሁኔታ በመመቻቸቱ ከቀላል የነፍስ ወከፍ መሣሪያ ጀምሮ ከባድ መሣሪያዎችንና ተሽከርካሪዎችን ለመታጠቅ ችለዋል፡፡

የሽብር ቡድኖቹ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚያሳዩት ጥንካሬና የይዞታ ማስፋፋት እንደ በጐ ጐን በመታየቱ የቡድኖቹ አባል ለመሆን የሚመለመሉና የሚቀላቀሏቸው በርካቶች ናቸው፡፡

ሽብርተኞቹ ሃይማኖትን በመመርኮዝና ሰበካ በማካሄድ አባሎቻቸውን ከአሜሪካ፤ ከአውሮፓ፤ ከመካከለኛው ምሥራቅና ከአፍሪካ እንደሚመለምሉና ለተለያዩ ግዳጆች እንደሚያሰማሩዋቸው የታወቃል፡፡ በተለይም ቀደም ሲል በሶማሊያ፤ አሁን ደግሞ በሶሪያ፤ በየመን፤ በሊቢያና በሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች የተከሰተው አለመረጋጋት ለጥንካሬዎቻቸው መደላድል ሆኗቸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በርካታ አገሮች በእነዚህ የሽብርተኛ ቡድኖች የውጊያ ብቃታቸው መጠናከር፤ ዘመናዊ የጦር መሣሪያ መታጠቃቸው፤ በሽምቅ ውጊያ ታክቲክና የፈንጂ አጠቃቀም በላቀ ደረጃ ላይ መገኘታቸው ከፍተኛ ስጋት ላይ ጥሏቸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀንድ በአል-ኢትሀድ አማካኝነት የመጀመሪያዋ የሽብር ጥቃት ሰለባ እንደነበረች አይነዘጋም፡፡ አደገኛውን አዝማሚያ በመገንዘብ ከፍተኛ የመከላከል ተግባር ፈፅማለች፡፡ ይህንን አዎንታዊ ርምጃ በማጠናከርም በወሰደችው የፀረ ሽብር ተግባር በጊዜው ያልተዋጠላቸውና የተቃውሞ ድምፃቸውን ያሰሙ በርካቶች ነበሩ፡፡

ኢትዮጵያ በአልኢትሀድና በአልሸባብ አማካኝነት በተቃጣባት ጥቃት በርካታ ዜጐቿ የሕይወት መስዋዕትነት ሲከፍሉ በሆቴሎች፣ በተሽከርካሪዎችና ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች በተጠመዱ ፈንጂዎች ንብረቶች ወድመዋል፡፡

የሽብር ተግባሩ አገሪቱ የተያዘችውን የልማት እንቅስቃሴ እንዳይጐዳና እንቅፋት እንዳይሆን የፀረ ሽርተኝነት ሕግ በማርቀቅና በማፅደቅ የዜጐቿን በሰላም ወጥቆ የመግባት ደህንነት የሚረጋገጥበት ተግባራት ፈፅማለች፣፡

ይህ የመከላከል ተግባር በአንዳንዶች ዘንድ የዴሞክራሲ አፈና ያመጣል የሚል ወቀሳ ቢያስከትልም በተግባር እንደታየው ግን ይህንን አስተሳሰብ የሚያራምዱ ወገኖች ሳይቀሩ የፀር ሽብርተኝነት ሕጋቸውን እንደገና የማጠናከር ተግባር መጀመራቸው ሽብርተኝነት አደገኛ አዝማሚያ እየያዘ መምጣቱን መገንዘባቸውን የሳያል፡፡

ኢትዮጵያ ያረቀቀችውና በተግባር ያዋለችው የፀረ ሽብርተኝነት ሕግ በዓለም ካሉ ዴሞክራሲያዊ አገሮች የአሠራር ሂደትና ሕግ የተወሰደ መሆኑ በርግጠኝነት እየተገለጸ ቢሆንም አንዳንዶች ሕጉን ሲያጥላሉት ይታያሉ፡፡

ኢትዮጵያውያን ሽብርተኝነት የሚያስከትለውን ጥፋት ከማንም በላይ የሚገነዘቡት ተጠቂነትን በተግባር ያረጋገጡት በመሆኑ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በተለይም በናይጄሪያ፤ በሶሪያ፤ በሊቢያ፤ በኢራቅ፤ በየመንና በሌሎች የቀጣናው አገሮች በአሸባሪዎች እየተፈፀመባቸው ያለው አደጋ መንስዔው የአገራቱ አለመረጋጋትና የውስጥ ችግሮቻቸው ሲሆኑ፤ አንዳንዶቹ ውስጣቸው ያለው የፖለቲካ አስተዳዳርና የዴሞክራሲ እጦት መሆኑ ይገለጻል፡፡

በኢትዮጵያ የሽብርተኝነት ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ባይሆንም ለሽብርተኛነት ተግባር ምቹ ሁኔታ ይኖር ይሆን በማለት በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሠላምና ልማት ኢኒስቲትዩት ከፍተኛ ተማራማሪ ለሆኑት ለአቶ ይነበብ ጌትነት ጥያቄ አቅርበን ነበር፡-

«በኢትዮጵያ በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠ የሃይማኖት እኩልነት ሰፍኗል፡፡ አንዱ የአንዱን ሃይማኖት አክብሮና እንደ ራሱ ሃይማኖት አድርጐ የሚያይበት ሁኔታ ጥንትም የነበረ ነው፤አሁንም ቀጥሏል፡፡ ማንም የራሱን ሃይማኖት የሚያስፋፋበትና አስተምህሮቱን የሚተገብርበት ሥርዓት የተገደበ አይደለም፡፡

«አገሪቱ በልማት ጉዳና እየተራመደች በመሆኗ ዜጐቿ ቀስ በቀስ የልማቱ ተጠቃሚ እየሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ በከተማ የነበረው የተስፋፋ ሥራ አጥነት በተቀየሰው የልማት ፖሊሲ ወጣቱ እየተደራጀ የሥራ ባለቤት እየሆነ ነው፡፡ በመኖሪያ ቤት እጥረት ይሰቃይ የነበረው ህብረተሰብ በቤት ግንባታ ልማት ተጠቃሚነትን ተጐናጽፏል፤ የመሠረተ ልማት አውታሮች በመስፋፋታቸው በከተማና በገጠር ያለው ልዩነት እየጠበበ ሁለቱም ወገኖች ተመጋጋቢ ጥቅም የማግኘት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡

« አርሶ አደሩ ዘመናዊ የግብርና ዘዴ በመጠቀሙ ሀብት እያፈራ የላቡ ተጠቃሚ ሆኗል፡፡ መልካም የጤናና የትምህርት ፖሊሲ በመቀረፁ በበሽታ ይሰቃዩ የነበሩ ዜጐች የጤና ፖሊሲው ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በትምህርቱ መስክም በርካታ ዩኒቨርሲቲዎች በመከፈታቸው የከፍተኛ ትምህርት ዕድል የሚያገኙ ወጣቶች ሥራ ፈጣሪ የመሆን ብቃትን ተላብሰዋል፡፡

« ዴሞክራሲ በአገራችን እንዲስፋፋ የፖለቲካ ምህዳሩ ሁሉንም ያሳተፈ እንዲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች ተደራጅተው የራሳቸውን አስተሳሰብ ለማራመድ የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ስለዚህ እነዚህን መሠል የዕድገት አቅጣጫን የሚያመለክቱ በርካታ ጠቃሚ ጉዳዮች በሚከናወኑበት አገር ለሽብርተኛነት ማንሰራራት ምቹ ሁኔታ የለም፡፡» ሲሉ አቶ ይነበብ ያብራራሉ፡፡

እንደ ባለሙያው ማብራሪያ በኢትዮጵያ የተረጋጋ ሰላምና የልማት እንቅስቃሴ እንዳይኖር የሚናፍቁ በርካታ የውጭና የውስጥ ኃይሎች ቢኖሩም ለዚህ ተግባራቸው ምቹ ሁኔታ ባለመኖሩ ከምኞት ያለፈ ተግባር ማከናወን አይችሉም፡፡

በአንዳንድ አገሮች እንደሚታየውና አሸባሪ ቡድኖቹ ሲገልጹ እንደሚደመጠው የእስልምና ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ከጀርባው መላውን ዓለም የመቀየርና የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤት መሆን እንደሚያስቡ በግልጽ ያመለክታል፡፡

በተለይም በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ስጋትን ያስከተለው አይ.ኤስ.አይ.ኤል. በሰብዓዊ ዕርዳታ ተግባር የተሰማሩ የውጭ ዜጎችን ሳይቀር አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ አንገታቸውን በስለት ሲቆርጥ ማየት የተለመደ ድርጊት ነው፡፡

በኢትዮጵያ ይህንን ዓይነቱን የጥፋት ተግባር ማየት የሚፈልግ ይኖራል ተብሎ ባይገመትም የፀረ ሽብር ሕጉን እንደ ዴሞክራሲ ማፈኛ አድርጎ በመቁጠር የራሳቸውን የፖለቲካ ኪሳራ የሚካክሱበት ሁኔታ በአንዳንዶች ዘንድ ይጠፋል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ይሁን እንጂ የሽብር ስጋቱ ሁሉንም ዜጎች የሚመለከት በመሆኑ ጥፋቱም ማንንም ከማንም የሚለይ ስለማይሆን በዚህ ጉዳይ ላይ የጋራ ጠንካራ አመለካከት ሊኖር ይገባል፡፡

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

የጎብኝዎች ብዛት

0000137266
TodayToday77
YesterdayYesterday126
This_WeekThis_Week1280
This_MonthThis_Month3348
All_DaysAll_Days137266

         በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።